“ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳጣት በግብጽ የሚደገፉ ናቸው” አቶ አዲሱ አረጋ

የተቃውሞ ሰልፉን እያስተባበሩ ያሉ ቡድኖች ሕዝቡን ተጠቅመው የራሳቸውን የስልጣን ፍላጎት ለማሟላት የሚንቀሳቀሱ ናቸው፣

ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳጣት በግብጽ የሚደገፉ ናቸው – አቶ አዲሱ አረጋ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኮሮናቫይረስ መከላከልና ሰሞኑን በክልሉ በተለያዩ አካላት እየተጠሩ ያሉ ሰላማዊ ሰልፎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫውን የሰጡት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ”ሕዝቡ ከአገር ጥቅም በተቃራኒ ከቆሙት አካላት ሊጠነቀቅ ይገባል” ብለዋል።

የተቃውሞ ሰልፉን እያስተባበሩ ያሉ ቡድኖች ሕዝቡን ተጠቅመው የራሳቸውን የስልጣን ፍላጎት ለማሟላት እየተንቀሳቀሱ ያሉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

”ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዱ በግብጽ የሚደገፍ ሲሆን ኢትዮጵያ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳጣት የሚንቀሳቀስ ነው” ብለዋል።

አቶ አዲሱ ሁለተኛውን ቡድን ‘ወያኔ’ በማለት የገለጹት ሲሆን ”ይህ ቡድን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያሰቃይና ሲበዘብዝ የቆየ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ይኸው ቡድን የለመደው ጥቅም ስለቀረበት ‘ስልጣን ይዞ ያለውን መንግስት ለማዳከም በተለያየ መንገድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።

”ሶስተኛው ቡድን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ መራዘሙን መነሻ ምክንያት በማድረግ በአቋራጭ ስልጣን የሚፈልጉ አካላት ናቸው” ብለዋል።

በመሆኑም ሕዝቡ እየተጠራ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ እነዚህ ሶስት ቡድኖች ተሰባስበው የጠሩት መሆኑን አውቆ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።

”የክልሉ ሕዝብ መሰረታዊ ጥያቄ ካለው በትክክለኛው መንገድ ያቅርብ” ያሉት አቶ አዲሱ፤ ከዚህ ውጪ ባሉት ጉዳዮች ላይ መንግስት ሕግን ለማስከበር ‘አቅሙም፤ ችሎታውም’ አለው ብለዋል።

በክልሉ እስካሁን የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የተሰራውን ስራ በተመለከተም በመግለጫቸው አካተዋል።

በዚህ ረገድ እስካሁን በክልሉ ሰፋ ያሉ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራዎች ቢከናወኑም የሚፈለገውን ያህል የባህሪ ለውጥ እንዳልመጣ ጠቁመዋል።

አሁንም የገበያ ቦታዎች፣ ሰርግ መሰረግ፣ ለቅሶ ማከናወንና በትራንስፖርት አጠቃቀም በኩል አሳሳቢ ሁኔታ እየተስተዋለ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሆኖም የክልሉ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈው የተገኙ 3 ሺህ 700 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ተገቢውን ቅጣት ማሰጠቱን ተናግረዋል።

”በተጨማሪም ከ27 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ክልከላዎችን ተላልፈው በመገኘታቸው በጥቅሉ 19 ሚሊዮን ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል” ብለዋል።

ቫይረሱን ከመመርመር አንጻርም ሰባት የምርምራ ጣቢያዎች በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ስምንቱ ደግሞ በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በክልሉ 10 ሺህ ሰዎችን በለይቶ ማቆያነት የሚያገለግሉ ቦታዎች፣ 22 ሆስፒታሎች የተዘጋጁ ሲሆን 5ቱ ስራ መጀመራቸው ተመልክቷል።

በክልሉ እስከ ዛሬ ድረስ 83 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 15 ሰዎች አገግመዋል።

68 ሰዎች ህክምና እየተከታተሉ ሲሆን የአንድ ሰው ህይወት አልፏል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።