የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል

ህዝባዊነት እና ዴሞክራሲያዊነት ከማያውቀው የሕወሓት ገዢ መደብ የተጎሰመው የሁከትና ብጥብጥ አቋቁሙኝ ነጋሪት መግለጫ ሰምና ወርቅ።

“መልእክተኛና መልእክቱ ሲገጣጠሙ፣ የመልእክቱ ቅቡልነት ይረጋገጣል” ይባላል። መልእክተኛ በሚያስተላልፈው መልእክት፣ ይዘትና ልክ ወይም በተሻለ መጠን የሚለካ የእውነት፣ የህግ፣ የመርህ እና የሞራል የበላይነትና ስልጣን ሲኖረው ደግሞ፣ መልእክቱ የተላለፈለት ማህበረሰብ ወይም አካል ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ እምብዛም አያንገራግርም፤ አይቸገርምም።

ይህ ተደራራቢ እና አንገብጋቢ የማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአለማቀፍ ደረጃ ያጋጠሙበት ልዩ ህልው የአለማችን ጊዜ ሲሆን ህዝባችንም በአጠቃላይ እንደ አለም ማህበረሰብ አባልነቱ በነዚህ ግዙፍ ችግሮች እየተናጠ ይገኛል። ታድያ እነዚህን ችግሮች ለመመከትና የጎንዮሽ ጉዳቶችን ለመቀነስ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ውስጥ አንዳንዶች ችግሩ ህልውናን የሚፈታተንና በንቃትና በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተገኘ በስተቀር ጥልቅ አዘቅት ውስጥ እንደሚከት በርትዕ፣ በእውነተኝነትና በቅንነት ስለሚገነዘቡ ችግሩን ለመፍታት ሌት ተቀን በሚችሉትም በማይችሉትም መጠን ተሰጥተው መፍትሄ ፍለጋ ይዋደቃሉ።በአንፃሩ አንዳንዶች በነዚህ ችግሮች ውስጥ ማንሰራርያ መደላድል ፈጥረውና ቀውስን አባብሰው የራሳቸውንና የአፍራሽ ሀሳባቸውን ቀጣይነት ማረጋገጥ ስለመቻላቸው እርግጠኛ ባይሆኑም ከነሱ ፍላጎት ባሻገር የመኖርና የመቀጠል ፅኑ ፍላጎት ያለው አሸናፊ ሃይል እንዳለ ባለመቀበል አይኔን ግንባር ያድርገው ብለው የዜሮ ድምር ክፉና አጥፊ ጨዋታቸውን በፊሽካ ለማስጀመር ይታትራሉ።

የህወሓት ጥገኛ ገዢ መደብ የሰሞኑ መግለጫም ሰሙ በህዝባዊነት፣ ህጋዊነት፣ ሰላማዊነት፣ የዲሞክራስያዊነትና የሀገራዊ አንድነት የተለበጠ አዛኝ ቅቤ አንጋችነት ባዶ ጩሀት ሲሆን ፤ ወርቁም በሴረኝነት ፣ በቡድንተኝነት፣ በአገር ጠልነት እና

በኢ ዲሞክራስያዊነት ሁሉን ፍጥረት በሚያስማማ ህዝባዊ ቅቡልነት እጦት የተንሳፈፈን ሃይል በማንኛውም ኢ ሰላማዊ መንገድ በመጠቀም የመተንፈሻ ድጋፍ በመስጠት ለመመለስ ያለመ የስሌት ችግር የሚስተዋልበት ኢ ሞራላዊ የሁከት አታሞ ነው።

የህወሓት የጥገኛ ገዢ መደብና ከተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች የተሰባሰቡ የኩርፍያ አድመኞች በቀድሞ የኢህአደግ አወቃቀር በተለያዩ ግዜያት በተደረጉ ግምገማዎች የስርዓትና የሃገር አደጋዎችን በመለየት ለማስወገድ በተዘጋጁ መድረኮች ሲናዘዙና ለመለወጥ ሲማማሉም ለህዝብና ለሃገር ተቆርቋሪ ሆነው ሳይሆን በለውጥ ፈላጊው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ለመቆየት ካላቸው ጭፍን ስግብግብነት እንጂ ለህዝብና ለሃገር ደህንነት አስበው እንዳልሆነ ባልተበረዙ አሁንም በአላማቸው በፀኑ መስመራዊ የህወሃት አባላትና በመላው የትግራይ ህዝብም ጭምር እንደሚታወቁ ግልፅ ነው።

የመንግስትን ስልጣን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ባሻቸው መንገድ በሴራና በማን አለበኝነት እንዳሻቸው ሲዘውሩ ሰለባዎች ያደረጉዋቸው የተከበሩ ታጋዩች ፣ የፖለቲካ ሃይላት ሙሁራን የደህንነትና ወታደራዊ ከፍተኛ ሙያተኞች ጭምር ከሚኖሩባት ከተማ ለነገ የሚያስተዛዝብ ዳግም የክፋት ሴራ በቀረቻቸው የእስትንፋስ ግዜያቸው ያለ እረፍት ይጎነጉናሉ።እንደ ኮሮና ቫይረስ ባሉ በማያከራክሩ ህልው አለማዊ ፣ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታዎች ውስጥም ሆነን ጭምር ግላዊ ፍላጎቶቻቸው ህዝብ ላይ ለመጫን እየሄዱበት ያለው አቅጣጫና ርቀት አሁንም አነጋጋሪና ዳግም የስህተት ታሪክ ሐውልትና ማፈርያ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።

የለውጥ አይቀሬነትን ማመን መቀበልና ራስን ለለውጥ በሚመጥን ቁመና ማዘጋጀት በለውጥ በክፉ ከመጎዳት የሚታደግና ሲያልፍም ትልቅ የህዝባዊነት የአስተዋይነትና በሃላፊነት የመምራት መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ ባህርያትና መገለጫዎች ከህወሓት የገዢ መደብ እና ከመሰሎቻቸው ከራቁ አመታት የተቆጠሩ በመሆኑ የጥፋት የክተት ነጋሪነታቸውን ማውገዝና እነሱንም የተገለሉ ማድረግ ወቅታዊ የምላሽ እርምጃ ነው።

ይህ ለእኔ ስለኔ እና የኔ ብቻ የሆነ የገዢ መደብ በህዝባዊነት በዲሞክራስያዊነትና በቀናኢ የኢትዮጵያዊ አንድነትም የማያምን መሆኑን አንዳንድ አባላቱ በድፍረት ባለፉት ሁለት አመታት በቀረቡበት ሚዲያዎች ሁሉ ለህዝብና ህዝባዊነት ያላቸውን ቅጥ ያጣ ንቀት በገዛ አፋቸው ያለ ህፍረት መስክረዋል። የሰላም ፈላጊነት፣ ይቅርባይነት፣ የአካታችነት የመንግስትና የህዝብን የማይገባ የትእግስት ችሮታም በመናቅ በተደጋጋሚ ቀይ መስመር ሲጥሱ ተስተውለዋል። ይህ የማይታረምና ለጥፋት ብቻ የተፈጠረ የሚመስል የገዢ መደብም በህዝባዊና መንግስታዊ ትዕግስትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልእኮ ልዩነትን በተግባር የሚማርበት ግዜ ከመቼውም ግዜ በላይ ተቃርቧል።

ባለፉት ሁለት ኣመታት ጊዜ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዚህ ገዢ መደብ ጠንሻሽነትና ፊታውራሪነት የተጠነሰሱና ለብዙዎች ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት መነሻ የነበሩ አሳዛኝ ክስተቶችን ህዝብና የየአካባቢው የፀጥታ ሀይላት ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርኣቱን ብቻ ለማስከበርና ለማስጠበቅ ከቆመው ህዝባዊው የመከላከያ ሰራዊታችን ጋር በቅንጅት በመስራት ያከሸፉት ሲሆን በሴራቸው ሃሳብ የተጠለፉ ሃይላትም ቢሆን በዚህ እኩይ ተሳትፎና ድጋፋቸው ከጊዜ ወደ ግዜ ከህዝብ እየተነጠሉ ይገኛሉ።

አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆንከው መላው የሀገራችን ህዝብ ሆይ፤ በዲሞክራሲ ስም እየማለ እና እየተገዘተ፣ ዴሞክራሲ ማእከላዊነት በሚል ማሞኛ ፈሊጥ ለአመታት እራስን በራስ ለማስተዳደርና ለሀቀኛ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ማበብና መበልፀግ እንቅፋት ሆኖ፣ በምስለኔዎች የሞግዚትነት አሰራር የአገራችን የፖለቲካ እድገት አቀጭጮ፣ በመጠላለፍ ሴራና በመከፋፈል ላይ የመሰረተውን ይህን የገዢ መደብ የጥፋት ሃሳብ በጥብቅ በማውገዝ ሰላምና አንድነትህን በንቃት በመጠበቅ እንድትታገለው ታሪካዊ ጥሪ ይድረስህ፡፡

በተለይም መላው የትግራይ ህዝብ፣ ገበሬዎች፣ የመንግስትና የግል ሰራተኞች፣ ምሁራን፣ ነጋዴዎች ፣ ነባር ታጋዮችና ለፍትህና ለነፃነት አካላችሁን ያጎደላቹ ሀቀኛ የህዝብ ልጆች፣ ወጣቶች፤

•በሀገረ ኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ምስረታ የትግራይ ህዝብ ያለውን ጉልህ ታሪክና ጅግንነት ከካዱና ካሳነሱ፤

•ላለፉት 29 አመታት የትግራይ ህዝብ የታገለለትን አላማ ረስተው ለግልና ቡድናዊ ጥቅማቸው ካደሩ ፤

•ለፍትህ ነፃነትና እኩልነት የህይወት መስዋእትነት መክፈልህን ረስተው ለፍትህ ጥማትና ነፃነት እጦት ዳርገውህ ለስልጣናቸው ሲሉ የፖለቲካ ብልግና ውስጥ ከተዘፈቁ፤

•ህዝባዊ የልማት ተጠቃሚነትን በቡድናዊ ጥቅም ለውጠው በገዛ መሬትህና ሀገርህ ለዘመናዊ ባርነት የሽጡህን፤

•በኢትዮጵያዊ አንድነትህ የማትደራደረውንና፣ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ ጋር በሰላምና በመተሳሰብ ለዘመናት መኖርህ እንቅልፍ ነስቷቸው ሌት ተቀን ከሚያሴሩብህ፤

•ለራሳቸው የግል ስልጣንና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ በመላ የትግራይ ህዝብ እንደተዘመተበት በማድረግ የትግራይ ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማቃረን እንዲሁም በለውጥ ሃይል ከተገነባው መንግስት ጋር ቅራኔ እንዲፈጠር ካደረጉብህ፤

•“በምድር ላይ ያለ የፖለቲካ ሃይል እኔ ነኝ” በሚል ያነሰ አስተሳሰብ፣ በሺዎች አመታት የሚቆጠረውን ጀግንነትህን እና ታሪክህን ወደ አርባዎች አውርደው “ከኛ በላይ ለአሳር” የሚመስለውን ትምክህታዊና ሸውራራ የታሪክ ትርክታቸውን በንቀት ለመጋት ከሚሞክሩ የዘመኑ አዋቂ ነን ባይ አላዋቂዎች፤

•ባስተዋይነቱ፣ በጨዋነቱና በታጋሽነቱ የሚታወቀውን የትግራይ ወጣት በጊዜውና በትውልዱ ታሪክ ሊሰራ አይችልም ብለው ደምድመው ካበቁና በይፋ ከተሳለቁ፤

•ስደትና መከራን ለማጥፋት ለአመታት የህይወት መስዋእትነት በመክፈል የታገልከውን ህዝብ፣ ልጆችህ በየበረሃው እንዲወድቁና ለስደትና እንግልት ከዳረጉ፤

•ለአመታት በስልጣን ዘመናቸው በከተማ ሲንደላቀቁ፣ በመላው የትግራይ ገጠሮችና ከተሞች የንፁህ ውሃ እጦት እሮሮህ ለመስማትና ለመመለስ ጀሮ ዳባ ልበስ ካሉ፤

•ዘመናዊ ትምህርትን በፋና ወጊነት ያስተዋወከውን ጅማሮህን ዘንግተው፣ ልጆችህ በትምህርት ጥራት ከደረጃ በታች እንዲማሩና፣ በዳስ መጠልያዎች ከአመት ወደ አመት እንዲሸጋገሩ ካደረጉ፤

•ከምንም በላይ የጥይት ባሩድ ለሰለቸህ፣ የጦርነት ኪሳራውን በተግባር በማወቅህ አጥብቀህ ሰላም ናፋቂና ፈላጊ መሆንህ የጎረበጣቸው፤

እነዚህ የገዢ መደብ አለቆች ጠንቀኝነታቸውንና ተዘርዝሮ የማያልቀውን ጥፋታቸውን በጊዜው በመገንዘብ፣ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆነህ በድጋሚ እንቢተኝነትህን እንድታሳይና በሰላማዊ መንገድ ታግለህ ታሪክህን በድምቀት እንድታድስ ልዩ ጥሪ እናቀርብልሃለን።

ለህጋዊ፣ ሰላማዊ እና አስተዋይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች፣በፖለቲካዊ አመለካከታቹና አቋማቹ የቱንም ያህል ብትቃረኑ፣ ህዝባዊነት፣ ህጋዊነት እና ሰላማዊነትን ተላብሳችሁ የሚጠበቅባችሁን ታሪካዊ ድርሻ እንድታዋጡ አደራችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን።

እንግዲህ “ከክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅምና” መልእክትና መልእክተኛው የተቃረኑበትን ሰሞነኛ መግለጫው፣ ብሩህና አስተዋይ ለሆነው ህዝባችን ሰምና ወርቁን እንደሚገነዘበው የሚያምነው የብልፅግና ፓርቲ በየትኛውም ደረጃ ህዝባዊ ተሳትፎን በመተማመን ከፊቱ የተጋረጠበትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከልን ቀዳሚ ትኩረቱ በማድረግ፣ ህዝቡ ራሱንና ወገኑን እንዲጠብቅ በአፅንኦት ይገለፃል፡፡

ብልፅግና ፓርቲና የሚመራው መንግስት መላ ትኩረቱ ቫይረሱን መከላከል፣ ሰላም፣ ፀጥታና የህግ የበላይነትን ማስከበር ሆኖ፤ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘሩ፣ ሉአላዊነታችንና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማንኛቸውም ሙከራዎችን ለመቀልበስ የሚያስችል ቁርጠኝነትና አቋም ያለው መሆኑን በልበ ሙሉነት እናረጋግጣለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ

ከትግራይ ብልፅግና ፓርቲ