የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ባለመግባባት ቢቋጭ ግብፅ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ሴናርዮዎች!!

(ፀሐፊ: Raphael Addisu|17 June, 2020)

) ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ቀጥታ ጦርነት አትገባም!!

ይህ የማይሆንበትና ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ የምድርም ሆነ የአየር ላይ ጦርነት ለመግጠም የማትደፍርባቸው ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች:-

1ኛ.) በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለማወጅ የሚያበቁ መነሻዎች የሏትም:: ይህ ደግሞ ግብፅን የአንድን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መስራች አባል ሀገር የግዛት ሉዓላዊነት የተፃረረች (aggressor) የሚያደርጋት በመሆኑ በፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ ሌሎች እንደ አፍሪካ ህብረት ባሉ አለም አቀፍ ተቋማት ለሚጣልባት ማዕቀቦች ይዳርጋታል::

2ኛ.) ጦርነት ውስጥ ብትገባ የማታሸንፈው ጦርነት ይናል:: የህዳሴ ግድቡ ላይ በቀጥታ ጥቃት መሰንዘር በግድቡ ስራ ላይ የተሰማሩ የጣሊያን: ፈረንሳይና ቻይና የመሳሰሉ ሀያላን ሀገራት ዜጎች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት መሰንዘር ስለሚሆንባት ከእነዚህ ሀገራት ጋር አደገኛ የዲፕሎማሲ ቅርቃር ውስጥ ይከታታል:: ከዚህም በላይ ህዳሴው ግድብ ላይ የአየር ጥቃት ብትሰነዝር የግድቡን ግንባታ ማስቆምና ማዘግየት ብትችልም ኢትዮጵያ በአፀፋው በግብፅ የአስዋን ግድብ ላይ ከምትሰነዝረው የአየር ጥቃት የተነሳ የአስዋን ግድብ ይፈርሳል::

ይህ ማለት ደግሞ የአስዋን ግድብ ውሃ መላውን ካይሮ ጠራርጎ ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ይከታል ማለት ነው:: ከዚህም የተነሳ የግብፅን አየር ሀይል 80%ቱን ከጥቅም ውጭ በማድረግ (rendering Egypt defenseless) ለሌላ የውጭ ጥቃት ያጋልጣታል:: በተጨማሪም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የካይሮና ተጓዳኝ ከተሞቿን ነዋሪዎች ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል:: አልፎ ተርፎም ከዚህ የተነሳ ለተራዘመ ድርቅ ከመዳረጓ ባለፈ በከረረ አፀፋዊ እርምጃ ኢትዮጵያ በቀጣይነት አባይን ከምንጮቹ (ገባር ወንዞቹ) ሙሉ በሙሉ በመገደብ ግብፅ የምትባል ሀገርን ሰው መኖር ወደማይችልበት (wasteland) እንድትቀይር ሊያስገድዳት ይችላል::

) ከቀጥታ ጦርነት ውጭ ያሏት አማራጮች

እንግዲያውስ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ቀጥታ ጦርነት ካልገባች ሌሎች ምን አይነት እርምጃዎች ልትወስድ ትችላለች ብለን ስንጠይቅ ግብፅ የሚኖራት ብቸኛ አማራጭ ኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ ጦርነቶችን ማወጅ ነው:: እንግዲህ ግብፅ በዚህ መሰረት የሚከተሉትን ሴናሪዮዎች (scenarios) ልትጠቀም ትችላለች::

1ኛ) ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰድ

በዚህ አማራጯ በፀጥታው ምክር ቤት የሚመራ አለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ውሃዎች ላይ የሚነሱ ግጭቶች ገላጋይ ኮሚቴ (a UNCS panel on transboundary waters dispute resolution) ይዋቀርና ጉዳዩ በአለም አቀፍ የድምበር ተሻጋሪ ውሃዎች አጠቃቀም ህጎች አንፃር እንዲዳኝ ይወሰናል:: ግብፅ አሁን ባላት አቅም አደጋውን መቋቋም (mitigate ማድረግ) የማትችለውና አሁን ላይ የደረሰባት የሚታይና ተጨባጭ የሆነ (physical or quantifiable) የኢኮኖሚ ጉዳት ማቅረብ ስለማትችል የፀጥታው ምክር ቤት የውሃውን ሙሌትም ሆነ የግድቡን ግንባት ማዘግየትም ሆነ ለማስቆም በቂ መነሻ (ground) ስለማይኖረው ህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌትም ሆነ ግድቡን ሰርቶ የማጠናቀቅ ስራው ይቀጥላል::

ይህም የፀጥታው ምክር ቤት ግጭት ገላጋይ (ዳኝነት) ኮሚቴ ገላጋይነቱን (arbitration) በቀጠለበት ሁኔታ: የግልግልና ዳኝነት ሂደቱ የተወሳሰበና ኢትዮጵያ አንድ ምዕተ አመት ወደ ኋላ ሄዳ ለደረሰባት የኢኮኖሚ ጉዳት ካሳ ልትጠይቅበት ሁሉ የምትችልበት (ይኼም ራሱን የቻለ የኋልዮሽ የኢኮኖሚ ጉዳት ሞዴሊንግ ላይ የተመሰረተ ሌላ ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ) እና: ረጅም ግዜ የሚወስዱ እንደ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ቀጠናዊ የውሃ ክፍፍል ያሉ መልስ ያላገኙ ጉዳዮች የሚነሱበት ስለሚሆን ጉዳዩ በፀጥታው ምክር ቤት ዳኝነትና ገላጋይነት እንደተያዘ እልባት ሳያገኝ ለአመታት ሊዘልቅ ይችላል::

በተጨማሪም በቀጣይነት የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ አጠቃቀም: የተፈጥሮ የአየር ንብረት ተፅዕኖዎችን በጋራ የመከላከል: በተፋሰሱ የተራዘመ ድርቅ (prolonged hydrological drought) በሚከሰትበት ግዜ እያንዳንዱ የተፋሰሱ ሀገር በመከላከል እና አደጋውን በመቋቋም (mitigation) ስራው የሚኖረውን ሀላፊነትና ድርሻ የመወሰን ጉዳዮች በግልግሉ ሂደት የሚነሱ ይሆናል:: እነዚህ ጉዳዮች ታዲያ ራሳቸውን የቻሉ ጠለቅ ያሉና ግዜ የሚወስዱ ጥናቶች የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ በአጠቃላይ ሂደቱ የተራዘመ (lengthy process) ይሆናል ማለት ነው::

በዚህ ሁሉ ግዜ ውስጥ የቀረው 1/4ኛ ብቻ የሚሆነው የግድቡ ስራና የውሃ ሙሌት የማይቆም በመሆኑ ግድቡ አልቆ ‘fait accompli‘ የሚሆን ይሆናል:: ይህ ማለት ደግሞ የሱዳኑ ሮዝሜሪ አሊያም የግብፁ አስዋን ግድብ ላይ እንደመደራደር ነው የሚሆነው ማለት ነው::

2ኛ.) ኢትዮጵያ ላይ የተቀፅላ ጦርነት ማካሄድ

ሀ) የመጀመሪያው የግብፅ  የተቀፅላ ጦርነት (proxy war) ስትራተጂ የሚሆነው የመንና ሊቢያ ላይ እያደረገች እንዳለችው የውስጥ ሀይሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን  ከውስጥ እንድትታመስ ማድረግ ነው:: ይኸውም ለሀገር ውስጥ የታጣቁ ቡድኖች በሚዲያ የፕሮፖጋንዳ ሽፋን በመስጠት: ገንዘብና በርዕዮት: እንዲሁም የጦር መሳሪያ በማስታጠቅና የውትድርና ስልጠና በመስጠት ነው በኢትዮጵያ ምድር የማያቋርጥ የእርስ በርስ ግጭት (internal conflict/civil war) እንዲኖር/እንዲነሳ በማድረግ ኢትዮጵያን ከውስጥ የማዳከም ስራ ነው::

) ሁለተኛው የተቀፅላ ጦርነት (proxy war) ስትራተጂዋ የሚሆነው የጎረቤት ጠላቶቻችንን በስልጠናና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ በየጊዜው በድንበር አካባቢ ግጭቶችን እንዲቀሰቅሱ በማድረግ ኢትዮጵያን ሰላም አልባ አድርጋ ከልማት እንቅስቃሴዎቿ ማስተጓጎል ነው:: በተረፈም በዚህ ስትራተጂዋ ቀጠናውን ወደ ግጭት ቀጠናነት በመመለስ የቀጠናው ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት በማድረግ ቀጠናዊው ጂኦፖለቲካዊ የሀይል ሚዛን (regional geopolitical power balance) ወደራሷ እንዲያጋድል ማድረግ ሌላኛው አላማዋ ነው የሚሆነው:: ከዚህም የተነሳ በአለም አቀፉም ሆነ በአህጉራዊ መድረኮች የተሻለ የዲፕሎማሲ ሀይል በመሰንዘር (soft power project በማድረግ) ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር ነው ትልቁ ግቧ የሚሆነው::

3ኛ.) የማያቋርጥ የዲፕሎማሲ ጦርነት ዘመቻ መክፈት

ይህን እስከአሁንም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እያካሄደችው እንደሆነ ይታወቃል:: ነገር ግን ከዚህ በኋላ ነገሮች እንደፈለገችው ባይቋጭላት እስከአሁን ካደረገችው በበለጠ ልትቀጥለው የምትችል ሲሆን ይህ አካሄዷ ደግሞ ሌላ ያልጠበቀችውን መዘዝ ሊያስከትልባት ይችላል:: ይኸውም ሌሎች (በተለይም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት) የኢትዮጵያን የግብፅን የበላይነት የሚያኮላሽ የተናጠል እርምጃ (act of defiance against Egypt’s hydro-hegemony) በመከተል በዚሁ ተበረታተውና ተነሳስተው በየራሳቸው የናይል ተፋሰስ ላይ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫና የመስኖ ልማት ግድቦችን ወደመገንባት እንዲገቡ ያደርጋቸዋል:: ከዚህም የተነሳ ሁሉም ሊከላከሉት የሚፈልጉት የጋራ ጥቅም (with a shared threat to protect against their common national interests) ይፈጠርና የግብፅንና አረብ አጋሮቿን ተፅዕኖ በጋራ በመቋቋም ላይ የተመሰረተ የላይኛው ተፋሰስ የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካዊ አጋርነት ክንፍ (upper reparian African states political block against Egypt and its Arab allies) ይፈጠራል::

4ኛ.) ቀጥተኛናተዘዋዋሪ የኢኮኖሚ ጦርነት ማወጅ

በዚህ ረገድ ግብፅ እስካሁን እያደረገች እንዳለችው እንደ አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአረብ ሊግ ያሉ አጋሮቿን ተፅዕኖ በመጠቀም የገንዘብ አበዳሪ የሆኑ እንደ አለም ባንክና አለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ (IMF) የመሳሰሉ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ኢትዮጵያ የልማት ድጋፎች እንዳታገኝ የበለጠ ልትሰራ ትችላለች:: በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በግብፅ የሚሰነዘርባት ኢኮኖሚያዊ ጦርነት የሚያደርስባትን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ኪሳራ በማስላት ወደ ግብፅ የሚፈሰውን የአባይ ውሃ መጠን በመቀነስ ተመጣጣኝ ወይም የከፋ የኢኮኖሚ ኪሳራ በግብፅ ላይ ልታድረስ ትችላለች::

በህዳሴው ግድብ ስራ ላይ መዋል ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ከሚፈጠርላት የኢኮኖሚ ጥንካሬና ይኼም ከሚያመጣው እያደገና እየጎለበተ ከሚሄድ ቀጣይና ጠንካራ ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር ይህ ለኢትዮጵያ በቀላሉ የምትጋፈጠው ተግዳሮት እየሆነላት ይሄዳል:: ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ከቻይና በአፍሪካ አህጉር ላይ እያደገ ከሄደው የኢኮኖሚና የንግድ ትስስር ፍላጎት የተነሳ የጀመረችው ‘Silk Road Economic Belt‘ ፕሮጀክት [የBelt And Road Initiative‘ አካል ነው] የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከአንጋፋ የደቡብ ምስራቅ ኤሲያና የአፍሪካ ኢኮኖሚዎች ጋር የሚያስተሳስር በመሆኑ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና በቀጠናው ጠንካራ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ የበለጠ እያደገ እንዲሄድ ያደርጋል::

ኢትዮጵያ እነዚህ እድሎች የሚፈጥሩላት ሀገራዊ የጥንካሬ አቅም ደግሞ እያንዳንዷ ግብፅ ለምትዘነዝርባትን የኢኮኖሚ ጫና ተመጣጣኝ ወይንም የከፋ አፀፋዊ የኢኮኖሚ ጫና ግብፅ ላይ ለማሳደር [ከግድቡ የምትለቀውን የውሃ መጠን በመቆጣጠርም ሆነ በሌላ መንገድ] እድሉን ስለሚፈጥርላት ግብፅ እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ከመውሰዷ በፊት ደግማ ደጋግማ እንድታስብ ያደርጋታል ማለት ነው::

ቸር እንሰንብት! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!

(የፀሀፊውን Raphael Addisu ሌሎች ፅሁፎች ለማግኘት: ከ https://www.facebook.com/raphael.addisu የFacebook ገፅ ሊንኩ በተጨማሪ በTwitter @EutopianDreams ገፁ #follow ማድረግ ይችላሉ)