የተጨቆኑ የመስኖ ግድቦች እና ሰፋፊ እርሻዎቻችን (ክፍል 1)

በዚህ ፅሁፍ የግለሰቦች ስም እንደ አስፈላጊነቱ ቢጠቀስም፤ መናገሩ መቼም ቢሆን ካደረሱት በጎነት ወይም ግፍ አይበልጥምና፤ የመፍትሄው አካል አድርጎ መውሰድ ይበጃል። የፀሃፊው አቋም መሆኑንም ልብ ይሏል

ኢ/ር ዩሱፍ ከድር 
የCETA አባልና የመስኖ መሀንዲስ
ኢ/ር ዩሱፍ ከድር 
የCETA አባልና የመስኖ መሀንዲስ

የመስኖ ግድቦቻችን ከውሃ ማቆሪያነት እና ከፖለቲካ ተፋሰስነት ድነው እውነተኛ ያርሶአደሩ መከታ ከሆኑ ለሀገሪቱ የወደፊት እድገት እጅግ ወሳኝ እና ትልቅ ተስፋ ናቸው የተባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፋብሪካ፤ መንገድ፤ ባቡር፤ ስልክ፤ ንግድ ወዘተ የቱንም ያህል ቢስፋፋ፤ በዘላቂና በቂ የግብርና ምርቶች እስካልታገዘ ድረስ፤ ተገኘ የሚባለው ሀገራዊ ዕድገት የእንቧይ ካብ ከመሆን አይድንም፤ ዘላቂነቱ መሰረት አይኖረውም፡፡ ልምዳች የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡

ዘላቂ ዕድገትን ለማረጋገጥ ደግሞ፤ በስርዓት ተጠንተውና ተገንብተው አገልግሎት ላይ መዋል በቻሉ የመስኖ እርሻዎች እንጂ፤ ለጊዜያዊ አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ታቅደው በሚገነቡ፤ በቅንጅት በማይሰሩም በማይመሩም፤ በካድሬ ጣልቃ ገብነት በሚዘወሩ፤ ለምዝበራ በተጋለጡ፤ ተጀመሩ ሲባል በሚቋረጡ ወዘተ መስኖ እርሻዎች ከሆነ በተቃራኒው የማህበረሰብን ሰላም እና ኑሮ በማናጋት የሀገር ህልውናን ቀውስ ውስጥ የመክተት አቅም እንዳላቸው አሁን ሀገራችን የምትገኝበት ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ትልቅ ወንዝ ገድቦ ጥቅም ላይ አለማዋል፤ ሀገር የሚያፈርስ ሀይለኛ ቦምብ እንደ ማጥመድ ይቆጠራል፡፡ ቶሎ ካልደረስን አይቀርልንም፡፡ በደለል ክምችት ዕድሜያቸው እያጠረ ያለው፤ አልዌሮ እና ተንዳሆ ግድብ አገልግሎት ሳይሰጡ ቢፈርሱ እና አደጋ ቢያደርሱ ምን ሊባል ነው? በነገራችን ላይ በመነሻ ጥናታቸው መሰረት አልዌሮ እና ጎዴ የቀራቸው የአገልግሎት ዕድሜ ከ 30 ዓመት በታች ነው፤ ግማሽ ዕድሜያቸው አብቅቷል፡፡ ሌሎቹም አብረው እያዘገሙ ናቸው፡፡

እነዚህ ትላልቅ ግድቦች እና ሌሎች የመስኖ እርሻዎቻችን መንገድ እንዲቀሩ፤ ነባሮቹም እንዲሽመደመዱ የተደረገው እንዴት ባለ መንገድ ነው? ወያኔ ከተከተላቸው የአጭር እና የረዥም ጊዜ ስልቶች መካከል የተወሰኑትን እነሆ፡፡ተቀበል እንግዲህ!!!…

ወያኔ ከሰራው ስራ አንዱ በሰበብ ባለፈው መንግስት የተጀመሩትን ማስቆም፤በስራ ላይ የነበሩትን ደግሞ ማውደም ነበር::

ጣና በለስ፤ አልዌሮ እና ጎዴ በአግባቡ ተጠንተውና ከፊል አካሎቻቸው በአግባቡ ከተገነባ በኋላ ቀጣይ ስራዎቻቸው ሙሉ በሙሉ አቋርጦ እንደ አሮጌ እቃ የተጣሉ የመስኖ ልማቶቻችን ሁነኛ ምሳሌ ናቸው፡፡ በደርግ የተጀመረ ልማት ለሀገር አይጠቅምም ብሎ ነገር አለ እንዴ? ሀገር የማውደም ድብቅ አጀንዳ ካልሆነ በስተቀር፤ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት ደፍሮ የሚያቀርብላቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ ከሰም እና ተንዳሆ ግድብ እና መስኖ ልማቶችም እንዲሁ፤ በስኳር ልማት በዓለም ተወዳዳሪ ለመሆን በሚል ስውር ሽፋን ሊገነቡ ከታሰቡ አስር ፋብሪካዎች መካከል ናቸው፡፡ ግድቦቹ እና የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የተመረጠው መሬት ደግሞ፤ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥራቱን የጠበቀ የጥጥ ምርት ይገኝበት የነበረ እና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጉልህ ሚና የነበረው የመካከለኛው አዋሽ መስኖ እርሻን በማጥፋት ነበር፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ፤ ወንጂ የመሰለ ነባር እርሻን ለማስፋፋት በሚል፤ እንደ ወለንጪቲ ቦፋ ያሉ በርካታ አዳዲስ እርሻዎችን በመጨመር፤ ውጤታማ የነበረውን ፋብሪካ ይዘውት ሊጠፉ እያንገዳገዱት ይገኛል፡፡

ባለሙያዎች ብቁ ጠያቂ እና ተረጋግተው የሚሰሩ እንዳይሆኑ ማድረግ::

ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ያሰበ መንግስት፤ ዕቅዱን ለማሳካት በዋናነት ከሚያስፈልጉት የማስፈፀሚያ መሳሪያዎች መካከል በዘረፉ የሰለጠኑ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ለዚያውም የሀገር ውስጥ ባለሙያ፡፡ ከያሉበት በማሰባሰብ፤ አቅማቸውን በማሳደግ፤ ከለላ በመስጠት ወዘተ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ድጋፍ ያደርጋል፤ ይንከባከባል ወዘተ ተብሎ የሚጠበቀው የወያኔ መንግስት ግን፤ በተቃራኒው ይሰራ ነበር፡፡ 

ብዙ ምጣድ ጥዶ ጋጋሪን በሙሉ ማባረር? በእንጀራ ጋገራ ሽፋን የራስን ስውር ዓላማ ለመፈፀም የሚደረግ አሻጥር ካልሆነ ታድያ ምን ሊባል ነው?
ባለሙያዎች ዞር ሲደረጉ ከነበረባቸው ግልፅ እና ስውር ተግባራቶች መካከል ጥቂቶቹን እንይ፡፡ ሙያዊ አቅም አለው ወይም ለፖለቲካ ወጥ ረገጣችን ታዛዥ ላይሆን ይችላል ብለው የገመቱትን ትልቅ ፕሮጀክት እየመራ የሚገኝ የመስኖ ባለሙያን ዞር በማድረግ እና በማጥፋት ተወዳዳሪ የሌላቸው አቶ ሽፈራው ጃርሶ ናቸው፡፡ ብቁውን ዞር አድርገው፤ ታዛዥ ካድሬ ባለሙያ ሰይመው ያሻቸውን ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ በስራ አስኪያጅነት እና በቦርድ አመራርነት በቆዩባቸውም ሆነ ተጽዕኖ ማሳደር ከሚችሉባቸው ተቋማት ለምሳሌ ኦሮሚያ መስኖ ጥናት እና ግንባታ ቢሮዎች፤ ፌዴራል ጥናትና ዲዛይን ኢንተርፕራይዝ፤ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ቢሮ እና ፋብሪካ እርሻ፤ ወዘተ ከሀላፊነት ያስነሱትና ያነሱት፤ ወደ ሌላ አካባቢ በምደባ የወረወሩት፤ ከስራ ያሳገዱት፤ ከደረጃ ዝቅ ያደረጉት ያስደረጉት የመስኖ ባለሙያ ተቆጥሮ አይዘለቅም፡፡

አንድ ምሳሌ ብናነሳ፤ አለማያ ዩኒቨርስቲ በግብርና ምህድስና ዘርፍ (Agricultural Engineering) አብረው ተምረው አንድ ላይ ተመርቀው፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ተቋማት ተቀጥረው በመስኖ ሙያ ላይ ይሰሩ የነበሩ አራት ብቁ ባለሙያዎች (አንደኛው የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ነው)፤ የአቶ ሽፈራው ጃርሶ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ከኦሮሚያ ቢሮዎች በአንድ ጊዜ ወደ ስምንት የሚደርሱ የመስኖ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ቢሮ ተቀጣሪ የተወሰኑ ባለሙያዎችን ከካባቢው ዞር እንዲሉ ካለ በቂ ምክንያት ወደ ተለያዩ የፋብሪካ እርሻዎች ለመመደብ ያደረጉት ሙከራ በክስ ከሽፎባቸዋል፡፡ ሰውየው በየሄዱበት መስሪያ ቤት ባለሙያውን የልማት ጠር የሚል ታርጋ ለጥፈውለት ማባረርና ማሸማቀቅ ተቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑ፤ የመስኖ ልማቶቹን ለማሰናከል ሆነ ተብሎ የሚደረግ ስለ መሆኑ አሁን እርሻዎቻችን የሚገኙበት ሁኔታ ምስክር ነው፡፡ ባለሙያዎቹ የተባረሩባቸው ድርጅቶች ደግሞ፤ የመስኖ ግድቦችን እና እርሻዎችን በማጥናት፤ በመንደፍ፤ በመገንባት፤ በማስተዳደር ስራ ላይ ቀንደኛ ተዋናይ ሲሆኑ ቀደም ሲል ከተጠቀሱ መስኖ ተቋማት መካከል በእሳቸው ሀላፊነት እና ጣልቃ ገብነት ምክንያት የተሰናከሉት ከሰም፤ ተንዳሆ፤ ፈንታሌ ቦሰት ጥቂቶቹ ሲሆኑ፤ አደጋ ያንዣበበባቸው ደግሞ ኩራዝ፤ ወልቃይትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ውሀ እና መስኖ ሙያ ውስጥ ሲሰራ ለቆየ፤ በመንግስት ተቋማት ለበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ተስፋ ቆርጠውና ተገፍተው ወደ ሌላ ሀገር እንዲሰደዱ ተደርገዋል:: የዚህ ሰለባ የሆኑና ወደፊትም የሚሆኑ ባለሙያዎችን ቤቱ ይቁጠረውና ሁላችንም የምናወቃቸውን ለማሳያነት ላንሳ፡፡ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድርድር ፊት መሪ እና የውሀ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትር፤ ዶ/ር ኢንጂኔር ስለሺ በቀለ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ በሌሎችም ተቋማት በመምህርነትና በተመራማሪነት ለረጅም ዓመታት ሲሰሩ ቆይተው የተባበሩት መንግስታት ቢሮን ተቀላቅለው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሀገራቸውን ለማገልገል ባላቸው ጠንካራ ፍላጎት ምክንያት ባይመለሱ ኖሮ፤ የግድቡ ግንባታ ድርድርን በአሸናፊነት ለመወጣት እና አሁን ያለውን ቁመና ይኖረው ነበር ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እሳቸው ከዚህ መጥፎ ሲስተም አምልጠው ለትልቅ ስኬት ቢያበቁንም፤ ከዚህ ቀደም ያጣናቸው ባለሙያዎች ስንት ይሆኑ? 

ደካማ፤ ያልተረጋጉ፤ ያልተቀናጁ ተቋማትን መፍጠር፤ 

ጠንካራዎችን ማድከም፡ በአንድ ወቅት ስመጥር የነበሩና ስራዎቻቸው አሁን ድረስ በየገጠር ቀበሌው ውስጥ የሚታይላቸው የአማራ፤ የኦሮሚያ፤ የትግራይ፤ የደቡብ ክልሎች መስኖ ጥናትና ግንባታ ተቋማት ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ድንገት ከመድረክ ጠፍተው፤ አቅመ ቢስ በሆኑ ተመሳሳይ የክልል ተቋማት እንዲተኩ ተደርገዋል፡፡ የትላልቅ መስኖዎች ባለቤት የሆኑት የፌዴራል እና ክልል ውሀ መስኖ እና ኢነርጂ ቢሮዎች ፍፁም የማይተዋወቁ እና የስራ ግንኙነታቸው የላላ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ 
በተጨማሪም የመስኖ ልማቱን ለሁለት ከፍሎ በግብርና ሚኒስቴር እና በውሀ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር በማዋቀር የስራ ወሰንና ሀላፊነት መምታታት እና መዘበራረቅ እንዲፈጠር ተደርጓል፤ የትላልቅ መስኖዎች ጥናትን፤ ግንባታን እና አስተዳደርን እንዲሁ ለበርካታ ተቋማት በማከፋፈል ከግብ እንዳይደርሱ ተቀይደዋል፡፡ እነዚህ ተቋማት በየጊዜው ራሳቸውን እንደ አዲስ እያዋቀሩ ውጤታማ እንዳይሆኑ ተደርገዋል፡፡ ለማሳያ ያህል እንኳን፤ አንድ እኔ የተሳተፍኩበት የዳሰሳ ጥናት ሰላሳ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ዘጠና ቀበሌዎችን ለመዞር እድል ሰጥቶኝ ነበር፡፡ ከዳሰሳው የተገኘው ውጤት እንደሚያሳየው የሁሉም ቀበሌዎች ቀዳሚ የልማት ችግር ሆኖ የተገኘው የመጠጥ ውሀ፤ ሁለተኛው መብራት ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የመስኖ ልማት ነው፡፡ ኢንተርኔት እና ተንቀሳቃሽ ስልክ እንዲሁም የገጠር መንገድ ለሁሉም ቀበሌዎች መዳረሱ ቢያስደንቀኝም ቅሉ፤ ሲበዛ የከነከነኝ ግን ሶስቱም ህዝቡ የጠየቃቸው የመሰረተ ልማት ዘርፎች ከአለፉት ሀያ ምናምን ዓመታት ጀምሮ አሁንም ድረስ፤ በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር ተወሽቀው መዝለቃቸው ነው፡፡ አቅም ሲገኝ፤ ራሳቸውን ችለው ለየብቻ ይዋቀራሉ፤ ነበር ያሉት ዶ/ር ካሱ ኢላላበጊዜው፡፡

የመስኖ ግድቦቻችን ወቅታዊ ጉዳይም ቢሆን ያው ነው፡፡ ሰበብ መነሻ እንዲሁም ጥሩ ምሳሌ በመሆናቸው እናብራራው፡፡

እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ፤ የትላልቅ መስኖ ግድቦችን ጥናትና ግንባታ የሚከታተለው እና ግንባታቸው ከተጠናቀቀ በኋላም በባለቤትነት የሚያስተዳደረው ውሀ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቢሆንም ቅሉ፤ በአቅም ውስንነት ምክንያት እዚህ ግባ የሚባል ስራ መስራት አልቻለም ነበር፡፡ የመስኖ ግድቦች ሁኔታ ያሳሰበው መንግስት (አለመልማታቸው ይሆን ወይም ሌላ እንጃ)፤ ከአራት እና አምስት ዓመታት በፊት፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የተገነቡና በመገንባት ላይ ያሉ አስራ አንድ የሚደርሱ የመስኖ ግድቦችን ተረክቦ እንዲያስተዳድር፤ ሌሎች የመስኖ ግድብ ግንባታዎችን እንዲያካሂድ በሚል እና የመስኖ ውሀ ሽጦ የሚመልሰው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር ከንግድ ባንክ በብድር ተሰጥቶት በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ ምንም እንኳን ግድቦቹን በባለቤትነት የወሰደው ኮንስትራክን ኮርፖሬሽን ራሱ የብዙዎቹ ግድቦች ተቋራጭ መሆኑ እና ግንባታ ስራ ላይ የተሰማራ በመሆን አወቃቀሩን በተመለከተ ጥያቄ ቢያስነሳ እና በቀጣይም ችግር መፍጠሩ ቢረጋገጥም (አላቻ ጋብቻ እንዲሉ)፤ በወቅቱ የተረሱ የመስኖ ግድቦቻችን ባለቤት አገኙ፤ ቀን ወጣላቸው ተብሎለታል፡፡ 
የሚገርመው ግድቦቹ እርሻ አልባ በመሆናቸው ውሀ የሚገዛ ደንበኛ በሌለበት ብድር መመለሱን አጠያያቂ ቢያደርገውም፤ እንደ ጅምር ይበል የሚያሰኝ ተግባር ተብሎ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑም ግድብ አስተዳደር ዘርፍን አቋቁሞ በበርካታ መዋቅራዊ ችግሮች የተተበተበና ለሀገራችን ፍጹም አዲስ የሆነ ዘርፍን በማንቀሳቀስ መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን ማከናወን ችሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉን ከጥንስሱ ያቋቋመው እና በእግሩ ለማቆም ሲንቀሳቀስ የነበረውን ጠንካራና ልምድ ያለው ብቁ ባለሙያ እና የዘርፍ ሀላፊን ኬንያ የሚገኝ ዓለም ዓቀፍ ተቋም በከፍተኛ ደሞዝ ወሰደው (ገለል አደረገው እንበል)፡፡ 

የመንግስት ለውጥን ተከትሎ ደግሞ በውሀ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር፤ ከግድብ አስተዳደር ዘርፍ ጋር ተወራራሽ ሀላፊነት የተሰጠው የመስኖ ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ የባንክ ብድር ያሳሰበው ግድብ አስተዳደር ዘርፍ፤ ግድቦቹን ወደ ልማት አስገብቶ ውሀ ተጠቃሚ በማድረግ፤ አንድም ከውሀ ሽያጭ ገቢ ሰብስቦ ብድር ለመመለስ፤ በሌላም በኩል ሀገሪቱን በሰብል ምርት ለማገዝ በሚል ዓላማ፤ ስራ ፈትተው የተቀመጡ ግድቦቻችን ላይ በሰብል ልማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመሳተፍ የሚረዳ የአዋጭነት ጥናት አዘጋጅቶ ለመንግስት አካላት ቢያቀርብም የስራ ወሰናችሁ አይደለም በሚል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በዚህ ሳያበቃ፤ እግሩ ያልጠናው የግድብ አስተዳደር ዘርፍ የተረከባቸው እና ችግሮች የተጫኑት የመስኖ ግድቦቻችን ሸክም እና የመስኖ ውሃ ተጠቃሚ ደንበኛ አለመኖር ሳያንሱ፤ የሀላፊነት መደራረብ፤ የአወቃቀር ችግር፤ ውስጣዊ ድጋፍ እጦት፤ አመራር ብቃት ማነስና የውስጥ መጠላለፍ ወዘተ ተደርበውበት እየተንደፋደፈ መሆኑ እየታወቀ፤ ውጤት አላስመዘገበም የሚል ወቀሳ ከውስጥ (የመስኖ ግድቦቹ ግንባታ ላይ እጃቸው በነበረበት ግለሰቦች ፊት መሪነት፤ አዲሱን አመራራ በማሳሳት) ይዘንብበት ጀመር፡፡ በሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ ፍሬያማ አልሆነም በሚል የተዛባና የተቻኮለ ምክንያት፤ በግዙፍነታቸው ዝቅ ከሚሉ ዘርፎች ለምሳሌ ህንፃ ግንባታ አንሶ በማዕከል ደረጃ እንዲዋቀር ተፈረደበት፡፡

ለሀገሪቱ ዕድገት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ዘርፍ መሆኑ በሚያስተዳድረው በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ እና ቀደም ሲል የጠቃቀስናቸው ፋይዳዎች የሚናገሩ ቢሆንም፤ ካለማወቅ ይሁን ወይም በተተበተብንበት ረዥም ስውር ሴራ ምክንያት፤ ብልጭ ብሎ የነበረው ትልቅ ራዕይ ዳግም ለመጨለም ተቃርቧል፡፡ ሴራው አስተሳሰባችንን ጭምር ሳያዛባው አልቀረም እላለሁ፡፡ ለነገሩ ከጥንስሱ፤ ተጠቃሚ በሌለበት ውሀ ሸጠህ መልስ ብሎ በከፍተኛ ወለድ ገንዘብ ማበደር፤ የግድቦቹን ግንባታን በአግባቡ አጠናቆ ካላስረከበ መስሪያ ቤት ጋር ማዋቀር፤ ተመሳሳይ ሀላፊነት ለሁለት መስሪያ ቤቶች በአዋጅ መስጠት፤ ወዘተ በእርግጥ ግድቦቹ ወደ ልማት እንዲገቡ ታስቦ የተሰሩ ናቸውን የሚል ጥያቄ መጫሩ አይቀርም፡፡ መፈተሽ ግድ ይላል፡፡

ፀረ መስኖ ልማት የትምህርት ስርዓት፡
የመስኖ እርሻን በተመለከተ የነበረው የትምህርት ስርዓትን (አሁንም የተሻሻለ አይመስለኝም) ስንፈትሽ ግን፤ በእርግጥ ወያኔ ግብርናን ማዕከል ያደረገ ፖሊሲ ይከተል ነበር ወይ ያስብላል፡፡ ዓለማያ ዩኒቨርስቲ ይሰጥ የነበረው፤ በዘርፉ በርካታ ብቁ ባለሙያዎችን ያፈራው የግብርና ምህድስና (Agricultural Engineering) የትምህር ዘርፍ ካለ በቂ ምክንያት (በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ገነት ዘውዴ ፊታውራሪነት) በማስፈራራት መዝጋት እና ቀስ በቀስ የመስኖ ሙያ ትምህርት ከካሪኩለሞች ውስጥ መወገዳቸውን ትኩረት አይስጠው እንጂ ሁሉም ያስታውሰዋል፡፡በ አርባ ምንጭ፤ ሀዋሳ፤ ወሎ፤ መዳ ወላቡ፤ ሀሮማያ ዩኒቨርስቲዎች፤ በውሀ ሀብትና መስኖ ምህንድስና (Water and Irrigation Engineering) የሙያ ዘርፍ በመጀመሪያ ድግሪ ለማስመረቅ የተቀረፀው የትምህርት ፕሮግራም፤ አለ ለማለት ካልሆነ፤ ከመስኖ ይልቅ ውሀ እና ሲቪል ምህድስና ላይ ያተኮረ ነው፡፡ መስኖ ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች ሽፋን 8 ከመቶ ሲሆን ሲቪል ምህድስናን የሚመለከቱ ትምህርቶች ሽፋን ግን 24 ከመቶ ይደርሳል፡፡ ታዲያ ውሀ እና ሲቪል ምህንድስና ማለት ይቀል ነበር እኮ፡፡ ለመስኖ ቅርብ የሆኑ ሙያዎች ትምህርትቶችም ቢሆኑ እንኳን፤ በውስን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ብቻ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

በዲላ፤ ጎንደር፤ መቀሌ፤ ወለጋ፤ ባህር ዳር፤ ዩኒቨርስቲዎች በውሀ ሀብትና መስኖ አስተዳደር የሙያ ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን ማስመረቅ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን፤ የሙያ ዘርፉ በሲቪል ሰርቪስ ዝርዝር ውስጥ ባለመካተቱ ተመራቂ ተማሪዎች ስራ ማግኘት አልቻሉም በሚል ምክንያት ትምህርቱ የተቋረጠ ከመሆኑም በላይ፤ ተመራቂ ተማሪዎችን ወደ ስራ የሚያስገባ ድርጅት (የመንግስትም ሆነ የግል) ባለመገኘቱ እንደገና ተጠርተው የተመረቁበት ሞያ ስያሜ በሌላ እንዲቀየር መደረጉ የቅርብ ትዝታ ነው፡፡ 

አርሶ አደሩ የመስኖ ተጠቃሚ ለመሆን ተደጋጋሚ ጥያቄ እያነሳና የመስኖ መሰረተ ልማቶች በተገቢው መንገድ እያገለገሉ አለመሆናቸውን እየወተወቱ፤ ብዛት እና ጥራት ያለው የመስኖ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ቢታውቅም፤ ትምህርቱ መቋረጡ የመስኖ ልማትን ለማኮላሸት የተደረገ መሆኑን ይነግረናል፡፡

በዚህ ብቻ ሳያበቃ የመስኖ ሰብል አመራረት፤ የመስኖ ውሀ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሙያዎች ባለመኖራቸው፤ የመስኖ ልማቱ ሀላፊነት በሲቪል መሀንዲስና ውሀ ሀብት መሀንዲ እንዲወድቅ ሆኗል፡፡ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፤ የሚኒስትሮቻችን አማካሪዎች (የህዳሴ ግድብ አማካሪ ኮሚቴን ጨምሮ) የወረዳ እና ዞን ባለሙያዎች ወዘተ ውስጥ የመስኖ ባለሙያዎች ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ሲሳተፉ ም አይታይም፡፡ ከላይ እስከ ታች መዋቅር ውስጥ የሉበትም ማለት ይቻላል፡፡ በየ መስሪያ ቤቱ ያሉ ባለሙያዎች በሌላ ስራ ላይ ተጠምደው ከሙያቸው ርቀዋል፡፡ በየወረዳ በሚገኙ ግብርና ቢሮዎች ውስጥ፤ የመስኖ አካላት ንድፍ በሲቪል ምህድስና ምሩቃን ሲሰሩ ማየትም የተለመደ ነው፡፡ የሚገርመው ሌላው ነገር፤ በየገጠር ቀበሌው የእንስሳ፤ የሰብል፤ የአፈር ጥበቃ ወዘተ ኤክስቴሽን ተመራቂ ባለሙያዎች ተመድበው ሲሰሩ፤መስኖን በተመለከተ ግን የመጀመሪያ ተመራቂ ባለሙያዎች የተገኙት ከአንድ እና ሁለት ዓመት በፊት መሆኑ ነው፡፡ ለዚያውም በስንት ውትወታ፡፡ ላለፉት ሀያ ዓመታት በየትኛውም የቴክኒክ ተቋም አይሰጥም ነበር፡፡

ፅሁፉ በዝርዝር ማሳያዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል

ቸር እንሰንብት
***
#ምንጭ፦ የአማራ ኢኮኖሚ ሽግግር ማዕከል ገፅ

3 thoughts on “የተጨቆኑ የመስኖ ግድቦች እና ሰፋፊ እርሻዎቻችን (ክፍል 1)

 1. #ኢትዬጵያ ለዘላለም ትኑር !!! 💚💛❤️

  በመጠኑም ቢሆን ከማውቀው እና ካነበብኩት የጣና በለስ ፕሮጀክት ውድመት : ከ እቃዋች ዝርፍያ : ሽሽት እና ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ወደ መፈራረስ : ውድቀት እና ጥልቅ የማይፈታ እርሃብ ከወረወረን መንግስት ተብዪ ማፍያ ጀርባ ያለው “ወያኔ” እሚባል እኩይ መሆኑን ከተረዳውበት ቀን አንስቶ በውስጤ ትልቅ ጥላቻ እና ጥያቄ ከተነሳ ዘመናት ተቆጥሯል : ” በርግጥ እነዚህ ሰዎች ግን ኢትዮጵያውያን ናቸው ?????, ከነዚህ ሰዋች ውጭ የገዛ ሃገሩን ለማጥፋት በርትቶ የሚሰራ ማን ነው??????”
  ወገን ይሄ ፖለቲካ አይደለም … ይሄ እምንቃጠልላት ሃገራችንን የመኖሯ / የመጥፌያዋ መስመር ላይ ደርሰናል !!!!! ጠላቶቻችን በተነሱልን ልክ : በቁጭት እና በኢትዮጵያዊነት በአንድነት መነሳት ከቻልን ብቻ እና ብቻ ነው ሃገራችንን ማዳን : ማስቀጠል እምንችለው::

  #ድል ለ ኢትዬጵያውያን !!!

  #ኢትዬጵያ ለዘላለም ትኑር !!! 💚💛❤️

  Like

 2. ሰላም ጤና ይስጥልኝ, TPLF በአ.አ እየሰሩት ያሉት ወንጀል በተመለከት ከባድ ጥቆማ ነበረኝ, ከእነ ማስረጃው አለኝ እና ለማን መናገር እንዳለብኝ አላውቅም, እባክህ contact አድርገኝ።

  Like

 3. ሰላም ጤና ይስጥልኝ, TPLF በአ.አ እየሰሩት ያሉት ወንጀል በተመለከት ከባድ ጥቆማ ነበረኝ, ከእነ ማስረጃው አለኝ እና ለማን መናገር እንዳለብኝ አላውቅም, እባክህ contact አድርገኝ።
  (Email: rockadis2211@gmail.com )

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡