የ1.9 ቢሊዮን ብር የጦስ ዶሮ! ሜቴክ በበላ እሱባለው ተመታ!

ይድረስ ለፊደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፥ አዲስ አበባ

አመልካች፡- እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ

ጉዳዩ፡- የኦዲት ሪፖርት ማስተካከያ ለጠቅላይ አቃቢ ህግ እንዲፃፍልን  በድጋሚ ስለመጠየቅ፤

አመልካች እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበትን ቦታ ደን የመመንጠር እና የማጽዳት ስራ ለመስራት በ2006 ዓ.ም ከሜቴክ ጋር በንዑስ ስራ ተቋራጭነት ውል ገብተን እና በውሉ መሰረት የሰራነውን ስራ በሜትር አስለክተን 1136.80 ሄክታር አስረክበናል፡፡ 160 ማህበራት ለመነጠሩት 56,682 ሄክታር ሜቴክ ከመብራት ኃይል 2.5 ቢሊየን ብር ከተቀበለ በኋላ 1.9 ቢሊዮን ብር የት እንደገባ ያልታወቀ እና የባከነ በመሆኑ ምክንያት የፊደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሜቴክን ኦዲት አድርጎ አረጋገጥኩት ባለው ሪፖርት ውስጥ እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ያለ ጨረታ ውል ገብቶ ስራ የሰራ እና ከተሰራው ስራ መጠን በላይ 593,244.56 ብር ትርፍ የመንግስት ገንዘብ ተከፍሎት ተገኝቷል በማለት ለጠቅላይ አቃቢ ህግ ባቀረበው የተሳሳተ የኦዲት ሪፖርት መሰረት ጠቅላይ አቃቢ ህግ በእሱባለው ተካልኝ ላይ ያልተገባ የሙስና ወንጀል ክስ ሊመሰረት ችሏል፡፡

ፀሁፍና ምስል በእሱባለው ተካልኝ፣ ድምፅ ፍሬው ሃይሉ፣ ቅንብር EthioWikiLeaks

የፊደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የህዝብ እና የመንግስት ሀብት በግለሰቦች እንዳይዘረፍ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦች ሀብትም ያለአግባብ በመንግስት ባለስልጣናት እንይነጠቁ ህግን፣ ውልን እና ስምምነትን መሰረት አድርጎ ፍትህ እንዳይዛባ በድጋሚ ህጋዊ ሰነዶችን ብቻ መርምሮ እና አረጋግጦ የተስተካከለ ሪፖርት ለጠቅላይ አቃቢ ህግ ያቀርብልናል የሚል ጽኑ እምነት ስላለን በደብዳቤ ቁጥር ET128/12 በቀን 28/11/2012 ዓ.ም የማስተካከያ ጥያቄ ከ56 ገጽ የማስረጃ ኮፒዎች ጋር ብናቀርብም በጽሁፍ ምላሽ ስላልተሰጠን ይህን ማመልከቻ በድጋሚ ልንጽፍ ተገደናል፡፡  

ምስል 1፦ እሱባለው ተካልኝ

ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱን ማስተካከያ የምንጠይቅባቸው ዋና ዋና መነሻ ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.  እሱባለው ተካልኝ ህንጻ ስራ ተቋራጭ ያለ ጨረታ ውል ገብቶ ስራ ሰራ ለተባለው በጥቃቅን እና አነስተኛ የገበያ ትስስር ድጋፍ እና የመንግስት ያለ ጨረታ ግዥ መመሪያ መሰረት የተፈጸመ ውል ስለሆነ በወንጀል የሚያስጠይቅ አይደለም፡፡ ያለ ጨረታ ውል ገብተን ስራውን የሰራነው ከ160 ማህበራት ጋር እንደነበር ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያ ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ከመጀሩ በፊት እኛ ቀድሞ የመነጠርነው ደን ድጋሚ አድጎ የቤንሻንጉል ክልል ወጣቶች ያለ ጨረታ ስራው ተሰቷቸው ድጋሚ የተሰራ መሆኑ እየታወቀ እኛ ተለይተን ያለ ጨረታ ውል ገብተው ስራ ሰሩ በሚል ሰበብ በወንጀል ልንጠየቅ አግባብ አይደለም

2.  ሜቴክ ኦዲት ተደርጓል ተብሎ ከቀረበው ሪፖርት ውስጥ እሱ ባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ 2,259,711.83 ብር ብድር የወሰድን መሆኑን ያመለክታል፡፡ በእርግጥም ይህ ክፍያ የተፈጸመው ለተሰራ ስራ እና ከልኬት ጋር የተያያዘ ስላልሆነ የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ አልቆረጥንበትም፡፡ የቆረጥነው የብድር መቀበያ ደረሰኝ ነው፡፡ ለዚህ ብድር መያዣም የነበረው ሜቴክ ለሰራነው ስራ ክፍያ በለቀቀ ጊዜ ተቀንሶ የሚከፈል የነበረ እና ክፍያውን የተከለከልን በመሆኑ ብድሩ ሳይቀናነስ በኦዲተሩ ሪፖርት ላይ ይታያል፡፡ ከለኪው እና ከተረካቢው ጋር በመተባበር ያልተሰራ ስራ እንደተሰራ በማስመሰል 593,244.56 ብር ትርፍ የመንግስት ገንዘብ ወስዳችኋል የተባለው ሀሰት መሆኑን ከማስረዳታች በፊት 593,244.56 ብር  መታሰብ ያለበት ካልተመለሰው ብድር ላይ እንጂ ቀድሞ ከተከፈለው ክፍያ ላይ ሊሆን የማይገባው በመሆኑ እና የብድር ይመለስልኝ ጥያቄ ደግሞ በፍትሃብሔር ህግ እንጂ በወንጀል ህግ የሚያስጠይቅ አለመሆኑ እየታወቀ ለአቃቢ ህግ ክስ እንዲመች ተደርጎ “ ከተሰራው ስራ መጠን በላይ 593,244.56 ብር  ተከፍሎ የተገኘ” ተብሎ የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ሊታረም ይገባዋል፡፡

ምስል 2፦ እሱባለው ተካልኝ

3.  በንዑስ ስራ ተቋራጭነት የስራ ውል ገብተው በውሉ እና በስምምነቱ መሰረት ሰርተው 3 ጊዜ በሜትር የተለካላቸው እና በሚመለከተው አካል ጸድቆ በተዘጋጀው የክፍያ ሰርተፍኬት የሁሉም ማህበራት የስራ መጠን ድምር 56,488.50 ሄክታር የደን ብምጣሮ ውስጥ 1,136.80 ሄክታር ወይም 2% የደን ምጣሮ ስራ የተሰራው በእሱባለው ተካለኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ሲሆን የሜቴክ የቀድሞ ባለስልጣናት አስገዳጅ ተጽእኖ ተጠቅመው በሜትር ሲለካ ተጭበርብሯል በሚል ባሉባልታ ሰበብ ተዳፋትና ወጣ ገባ የሆነ ቦታ የቆዳ ስፋትን በትክክል በማይለካ 2DGPS በተባለ መሳሪያ፣ በቋሚ ድበር (ኮርድኔት) ሳይኖረው ድጋሚ መለካት በማይችልበት ሁኔታ በሌለንበት ቦታውን ለክተናል በማለት የሁሉም ማህበራት የስራ መጠን በድምሩ 29,249 ሄክታር ብቻ ነው ከተባለው ውስጥ የእሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ 577.89 ሄክታር ብቻ ነው በማለት  ቀሪ ክፍያ 6,493,862.95 ብር በግፍ ከልክለውናል፡፡

4.  ውል እና ስምምነት በተዋዋይ ወገኖች መካከል ህግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚሰራው ስራ የመለኪያ መሳሪያ ስምምነታችን በሜትር በመሆኑ በሜትር እየተለካ 3 ጊዜ ክፍያ ተፈጽሞልናል፡፡ በሜትር የተለካልን 1,136.80 ሄክታር በባለ ስልጣናቱ ያለ አግባብ ውድቅ ተደርጎ ባልተስማማንበት የ2DGPS መለኪያ 577.89 ሄክታር ነው የተባለው ተቀባይነት የሚያገኝበት የህግ አግባብ የለም፡፡

5.  የተመነጠረው ቦታ ተዳፋት እና ወጣ ገባ የበዛበት በመሆኑ መለካት ያለበት በ2DGPS ሳይሆን በሜትር መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ (የአሁኑ ጂኦስፓንሻል) ደብዳቤ በፃፈው መሰረት 577.89 ሄክታር ብቻ ነው የተባለው የ2DGPS መጠን ተቀባይነት የለውም፡፡ 2DGPS ትክክለኝነት የሚጎለው ስለመሆኑ ከሜቴክ ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዱ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አደራዳሪዎች ያመኑ ስለመሆኑ የጽሁፍ ማስረጃ ተያይዟል፡፡ በተጨማሪም በ2DGPS የቆዳ ስፋት አለካክ እና Error Factor of 2DGPS Google በማድረግ እውነታውን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

6.  የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ ከቦታው ድረስ ሄዶ በእያንዳንዳችን የተመነጠረውን ቦታ ድጋሚ በሜትር ለመለካት ሞክሮ ቀድሞ ስራውን ካስረከብን በኋላ በወሰን መለያነት እንጠቀምባቸው የነበሩ ጊዚያዊ የዛፍ ድንበሮችን ቁረጡና ውጡ ተብለን በመካከላችን የነበሩት ወሰኖች ስለጠፋ በሜትርም ሆነ በሌላ የመለኪያ መሳሪያ በድጋሚ መለካት እንደማይቻል ያረጋገጠበትን የጽሁፍ ማስረጃ የሰጡን በመሆኑ ድጋሚ በገለልተኛ ወገን ተለክቶ 577.89 ሄክታር ብቻ ነው የተባለው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ምስል 3፦ እሱባለው ተካልኝ

7.  የሜቴክ የ2DGPS 29,249 ሄክታር ሁሉም ማህበራት የስራ መጠን እንደሆነ እና 577.89 ሄክታር በእኛ ተሰርቷል የተባለው መጠን ውድቅ  ተደርጎ በሌለንበት፣ በምን እና እንዴት እንደተለካ ሳናውቅ ከስምምነታችን ውጭ የተዘጋጀው የልኬት መጠን ተቀባይነት ባይኖረውም የኢትጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ የሁሉም ማህበራት የተሰራውን በአንድ ላይ 32,244.89 ሄክታር መሆኑ አረጋግጫለው ካለው ውስጥ 2% ድርሻችን 577.89 ሄክታር ብቻ ሳይሆን 644.90 ሄክታር ነው፡፡ ይህ ጭማሪ ለሌሎች ማህበራት እንደየ ድርሻው የተከፋፈሉ መሆኑን እና እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ሊከፈን የሚገባ ድርሻ 624,585 ብር እንዳይከፈለን ተቀንሶ ይባስ ብሎ የ593,244.56 ብር ባለእዳ ተደርገናል፡፡

8.  ከውል ያልመነጨ እና መረጃው ከየት እንደሆነ ያልታወቀው እንዲሁም የሜቴክን 577.89 ሄክታር መጠን ውድቅ የሚያደርገው ሌላው ማስረጃ በጠቅላላ መመንጠር ከነበረበት 123,189 ሄክታር ውስጥ 31.73% ወይም 39,087.28 ሄክታር ብቻ የተመነጠረ መሆኑን በዋና ኦዲተሩ ተረጋግጧል ተብሎ ለጠቅላይ አቃቢ ህግ ቀርቧል፡፡ ከ39,087.28 ሄክታር ውስጥ የእሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ 2% ድርሻችን 577.89 ሄክታር ብቻ ሳይሆን 781.74 ሄክታር ነው፡፡ በዚህ ስሌት እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ከሜቴክ 2,403,606 ብር ያልተከፈለን ቀሪ ክፍያ እንዳለን እንጂ የ593,244.56 ብር ባለእዳ መሆናችንን አያስረዳም፡፡ በጠቅላላ የምንጣሮ ስራ 31.73% ወይም 39,087.28 ሄክታር በ160 ማህበራት ብቻ የተሰራ አይደለም እንዳይባል እኛ ከወጣን በኋላ ሌሎች ማህበራት ገብተው የሰሩት ድጋሚ ያደገውን ብቻ ለመመንጠር መሆኑን ልብ ይለዋል፡፡

9.  የደን ምንጣሮ ስራ 3 ዓይነት ደረጃ እና ዋጋ የነበረው ሲሆን ይህ ደረጃ እና ዋጋ በመጀመሪያው የደን ይዘት እና የድንበር ዞፎቹ ከመቆረጣቸው በፊት ካልሆነ በቀር በድጋሚ ልኬት ጊዜ ለይቶ ማወቅ አይቻልም፡፡ ደረጃውን እና ዋጋውን የያዘው ሰነድ ቀድሞ በጋራ በተፈራረምንበት እና በተሰጠን ቴክ ኦፍ ሽት እና የክፍያ ሰርተፍኬት ብቻ በመሆኑ ይሄን ህጋዊ ሰነድ ወደ ጎን በመተው በዳግም ልኬት ጊዜ ደረጃው ሳይታወቅ ስለ ዋጋ እና የክፍያ ሂሳብ መስራት የማይቻል በመሆኑ የዳግም ልኬቱን መሰረት ያደረገው የኦዲት ሪፖርት ትክክል ነው ለማለት አይቻል፡፡

10. ኦዲተሩ በውል እና  በስምምነት መሰረት ቀድሞ የተዘጋጀውን የክፍያ ሰርተፍኬት አልተቀበልኩትም ያለበት ምክንያት ሌሎች ማህበራት የሁላችንም በአንድ ላይ ተለክቶ የሚመጣውን የዳግም የልኬት ውጤት ምንም ይሁን ምን እንደሚቀበሉ ማሻሻያ ውል ፈርመዋል በማለት ነው፡፡ ቀድመው ከተከፈላቸው ያነሰ የልኬት ውጤት ከመጣ የእዳ ድርሻቸውን ለሜቴክ ሊመልሱ፤ ቀድሞ ከተከፈላቸው በላይ ጨምሮ ከመጣላቸው ደግሞ በድርሻቸው ሊከፈላቸው እንዲሁም በፍርድ ቤት ሜቴክን ላይከሱ የጋራ የስምምነት ማሻሻያ  በተፈራረሙት መሰረት የዳግም የልኬት ውጤት በማህበራቱ እንደየ ድርሻቸው እንዲከፋፈል ተደርጓል፡፡ የእሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ድርሻችን እንደሌሎቹ ታሳቢ ያልተደረገው በዳግም የልኬት ውጤት ላይ ስምምነት ስላላሻሻላችሁ እና በሜቴክ ላይ የመሰረታችሁትን ክስ ለማቋረጥ ባለመቻላችሁ እንዲሁም ፍ/ቤቱ በገለልተኛ ባለሙያ ድጋሚ አስለክቶ ባገኘው የልኬት ውጤት መሰረት በሜቴክ ተሸንፋችኋል በማለት የፍ/ቤቱን ውሳኔ ላለመንካት ቀድሞ በሜቴክ በ2DGPS የተለካውን 577.89 ሄክታር ትክክል እንደሆነ ወስደው እንዳረጋገጡ ኦዲተሮቹ በቃል ነግረውናል፡፡ ነገር ግን የላባችን ውጤት የሆነ ቀሪ ክፍያ እንዳለን በኦዲተሩ የታወቀ እና የተረጋገጠ ቢሆንም ከሜቴክ ጋር የቀድሞ ባለስልጣንናት ባለመስማማታችን የተነሳ በሀሰተኛ ማስረጃ በወንጀል ያለ አግባብ ተከሰናል፡፡

ምስል 4፦ እሱባለው ተካልኝ

10.1.   ሌሎች ማህበራት በድጋሚ ልኬት ውጤት ላይ የሜቴክ ባለስልጣናት አስገዳጅ ተጽእኖ መኖሩን እያወቁ በህግ የመከሰስ እና የመክሰስ መብታቸውን የሚያሳጣ ስምምነት መፈረማቸው ህጋዊ ውል ይሆናል በማይባልበት ሁኔታ እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ የባለስጣናቱን ዛቻና ማስፈራሪያ ተቋሙመን ህገ ወጥ ስምምነት ባለመፈረማችን እና በህግ የበላይነት አምነን በ2007 ዓ.ም (ከለውጡ በፊት) ሜቴክ በህግ እንዲጠየቅ በፊደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ፍታብሔር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 162183 ክስ መስርተን በፍትህ አደባባይ ትግል መጀመራችን የሚደነቅ ተግባር ሆኖ ሳለ እውነታውን ወደ ጎን በመተው ከቀድሞ የሜቴክ ባለስልጣናት ጋር ለምን አልተስማማችሁም ነበር ? ለምንስ ሜቴክን ከሰሳችሁ በሚሉ አግባብ ያልሆኑ ምክንያቶች የድካማችንን ዋጋ ልንቀማ እና በፈጠራ ክስ የመኖር መብታችን ተጥሶ የምንታሰርበትን አሰራር የሚከተሉ አካላት ለፍትህ የቆሙ ናቸው ለማለት አይቻልም፡፡

10.2.   እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ስለ ዳግም ልኬት የስምምነት ማሻሻያ ከሜቴክ ባለስልጣናት ጋር አልተፈራረምንም ማለት ቀድሞ በተዋዋልነው እና በተስማማነው መሰረት የተዘጋጀው ቴክ ኦፍ ሺት እና የክፍያ ሰርተፍኬት ያልተሻረ በመሆኑ 1,136.80 ሄክታር በኦዲተሩ ተቀባይነት የሚያጣበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡

10.3.   የመንግስት ተቋማትን ሳይቀር ለቅሚያ ማስገደጃነት የሚጠቀሙት የቀድሞ የሜቴክ ባለስልጣናት በተጽኖ አስገድደው ባዘጋጁት የድጋሚ የ2DGPS የልኬት ውጤት ስምምነት ባለመፈረማችን የሁሉም ማህበራት ስራ በአንድ ላይ ተለክቷል ከተባለው የ32,244.89 ሄክታር 2% ድርሻችን የ644.90 ሄክታር ታስቦ ቀሪ ክፍያ ሊከፈለን ሲገባ ከ29,2249 ሄክታር የ2DGPS የልኬት መጠን ውስጥ እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ 577.89 ሄክታር ኦዲተሩ እንዲቀበለው ተደርጎ የ67 ሄክታር ክፍያ ያለአግባብ ተቀንሶ ባለእዳ እንድንሆን ተደርጓል፡፡

10.4.   ከለውጡ በፊት የፍርድ ቤቶች አሰራር በባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ችግር ውስጥ እንደነበረ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ ለመረጃ አሰባሰብ በሚመረጡ ባለሙያዎች እና ተቋማት ላይም ተጽኖው ከባድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የምህንድስና ትምህርት ክፍል ከሜትር እና ከ2DGPS ይህንን ቦታ ለመለካት የተሻለው የቱ ነው ? ሌላም የመለኪያ ዘዴ ካለ ተብሎ በፍ/ቤት ተጠይቆ 2DGPS በፍጹም ለዚህ ቦታ መለኪያነት ሊውል እንደማይች፤ በሜትር መለካት ምንም ችግር የሌለው ሲሆን ከቦታው ስፋት አኳያ ጊዜና ወጪ ስለሚጠይቅ ቀድሞ የታወቀና የተመዘገበ የደንበር መለያ ወይም ኮርድኔት እና ካርታ ካለ ከዚሁ ከቢሮ ሳንወጣ DEM በተባለ ዘዴ የእያንዳንዱን ማህበር ቦታ የቆዳ ስፋት ለይቶ ማወቅ እንደሚቻል እና ከቢሮአቸው ሆነው የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍብትን ቦታ ናሙና ወስደው በ2DGPS በመለካት እና ናሙናውን ቦታ ድጋሚ DEM ዘዴ የቆዳ ስፋቱን በመለካት የDEM የልኬት መጠን ከ2DGPS የልኬት መጠን ከ30% በላይ እንደሚጨምር አረጋግጧል፡፡  ለፍርድ ቤቱ እንዲጽፍ የተደረገው ቦታው መለካት ያለበት በሜትር እንደሆነ እና ድንበሩ (ኮርድኔቱ) ስለማይታወቅ ቦታውን ድጋሚ መለካት አይቻልም የሚል ማስረጃ ከኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ ፍርድ ቤቱ ከተቀበለ እና ብይን ከሰጠበት በኋላ ነው፡፡

10.5.   በሜቴክ የቀድሞ ባለስልጣና ጠቋሚነት ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ሱፐር ቪዥን ስራዎች በሜትር መለካት የሚችለውን በሜትር በመለካት ከቦታው ተፈጥሮዓዊ አቀማመጥ አኳያ በሜትር ለመለካት የማይቻለውን በDEM ዘዴ ግራቀኙ የሚያሳዮትን ቦታ ለክቶ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ነገር ብን በሜትር የማይለካ ቦታ ላይ ሥራ ያልሰራነወ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

ምስል 5፦ እሱባለው ተካልኝ

10.6.   ዛፍ በመጥረቢያ ቆርጠን ያፀዳነውን ቦታ በሜትር ለመለካት የማይቻለውን በDEM ዘዴ ይለከ፤ ደንበሩ ባይታወቅም ግራ ቀኙ የእየራሳቸውን በሚያሳዩት ድንበር ተለክቶ ይቅረብ የሚለውን ትእዛዝ በሜቴክ ባለስልጣናት በተመረጡት ባለሙያዎች ትእዛዙን ከተቀበሉ በኋላ እኛ እምናሳያቸውን ቦታ አንለካም በማለት በሌለንበት ሜቴክ የሚያሳየውን ቦታ ብቻ በሜትር የሚለካ ቦታ ስለሌለ DEM በተባለ ዘዴ ለክተናል ብለው በእሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ የተመነጠረ 533.97 ሄክታር ብቻ እደሆነ እንኳን በ2DGPS ተለክቷል የተባለበው 577.89 ሄክታር በ30% ሊጨምር ይቅር እና ከ2DGPS የልኬት መጠን በ8% ያህል ቀንሰው 533.97 ሄክተር ለፍርድ ቤቱ አቅርበው ለማስፈረድ ሞክረው ሜቴክ የተከሳሽ በሳሽነት ቀድሞ በጠየቀው የ577.89 ሄክታር ዳኝነት መሰረት 1,323,260.11 ብር እንድንመልስለት ተሰውኖለታል፡፡ 533.92 ሄክታር ነው የተባለው    የDEM የልኬት መጠን የተሰላው ዮንቨርስቲው በሰጠው ሙያዊ ማብራሪያ እና የአለካክ ዘዴ እንዳልሆነ የዮንርስቲው ባለሙያ ገልጸውልናል፡፡ ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል ተባለ እንጂ ቦታውን በሜትር መለካት አይቻልም የሚል አስተያየትም የዩንቨርስቲው  ባለሙያ አልሰጡም፡፡

10.7.   ሜቴክ በተከሳሽ ከሳሽነት በጠየቀው ዳኝነት መሰረት እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ ከሜቴክ ቀድሞ የወሰደው ክፍያ 8,523,437.11 ብር እንሆነ እና ለሜቴክ ተመላሽ የሚያደርገው እዳ 1,323,260.11 ብር እንደሆነ ተደርጎ የተሰጠው የፍርድ ውሳኔ ስህተት እንደሆነ ኦዲተሩ አረጋግጦ ውሳኔውን ያልተቀበለው ቢሆንም በሌላ በኩል ስህተቱን ለማስተካክል በውልና በስምምነት መሰረት የተዘጋጀውን 1,136.80 ሄክታር መቀበል ሲገባው ሀቁን ወደ ጎን በመተው ፍ/ቤቱ በገለልተኛ ባለሙያ ድጋሚ አስለክቶ 577.89 ሄክታር መሆኑን ስላረጋገጠ እና ስለወሰነ ውሳኔውን መቀየር እንደማይቻል አድርገው በ2DGPS ተለክቷል የተባለውን 577.89 ሄክታር በማጽናት እና የ593,244.56 ብር ባለ እዳ እንድንሆን ተደርጎ በድጋሚ  ፍትህን የሚያዛባ የኦዲት ሪፖርት አቅርቧል፡፡    

10.8.   የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ሱፐር ቪዥን ባለሙያዎች ፍርድ ቤቱ ግራቀኙ የሚያሳዮትን ቦታ የሚቻለውን በሜትር በሜትር የማይቻለውን በDEM ዘዴ እንዲለካ ታዞ የነበረ ቢሆንም ሜቴክ የሚያሳየውን ቦታ ብቻ እንጂ እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ የሚያሳየውን ቦታ አንለካም ከማለታቸው በተጨማሪ 1ሜትር በ1 ሜትር የሆነ ቦታ በሜትር የሚለካ አካባቢው ላይ የለም በማለት በDEM በተባለ ዘዴ ብቻ በሌለንበት ለክተናል ብለው የDEM የአለካክ ዘዴ ከ2DGPS ያነሰ የልኬት ውጤት ሊሆን በማይችልበት ሁኔታ ሆን ብለው እኛን ለመጉዳት በማሰብ ሀሰተኛ ማስረጃ ፈጥረው በፍርድ ቤት አቅርበው ያስወሰኑብን ስለሆነ ጉዳዩ በፖሊስ ይመርመርልን ብለን ለልደታ ፖሊስ መምሪያ ባመለከትነው መሰረት በምርመራ ቁጥር 47/11 ወንጀል የተፈጸመ መሆኑ ተጣርቶ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት በመ.ቁ 229397 አቃቢ ህግ መደበኛ ክስ ከመሰረተባቸው በኋላ በዳይሬክቶሬት ትእዛዝ ክሱ እንዲቋረጥ ታዘናል ብሎ የተጠርጣሪዎቹ ክስ ያለአግባብ ተቋርጦ ኦዲተሩ ባቀረበው የተሳሳተ ሪፖርት መሰረት ክሱ ተቀነባብሮ ወደ እኛ ሊገለበጥ ችሏል፡፡

10.9.   የፍትሃብሄር ክርክር ያደረግንበት ፍርድ ቤት በሜቴክ የቀድሞ ባለስልጣናት አስገዳጅ ተጽእኖ ምክንያት የተዛባ ፍትህ የሰጠ ለመሆኑ የማያጠራጥር እና መስተካከል ያለበት ሆኖ ሳለ ኦዲተሩ እውነታውን እያወቀ የተሳሳተ የፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክለኛ መረጃ እንደሆነ አድርጎ ለሌላ ዳኛ እንዲቀርብ በማድረግ ለ2ኛ ጊዜ ፍትህ የሚያዛባ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ በሞራልም ሆነ በህግ ተቀባይነት ያለው ተግባር አይደለም፡፡ በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የ2DGPS ልኬት መጠን 577.89 ሄክታር ስህተት እንደሆነ ኦዲተሩ ለአቃቢ ህጉ ለመግለጽ ያልፈለገበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ የፍርድ ቤት ውሳኔ መሻር ስልጣን ባይኖረው እንኳን ከንጹ ህሊና አኳያ በተበደሉ ዜጎች ላይ ለተጨማሪ በደል የወንጀል ክስ እንዲመሰረት ሀሰተኛ ማስረጃ ለአቃቢ ህግ ከመስጠት ተቆጥቦ ቢቻል ስህተቱ እንዲታረም ስልጣን ላለው አካል ጉዳዩን ማሳወቅ ነበረበት፡፡

10.10. ከአባይ ወንዝ ማዶ ለማዶ የሆኑ 2 ቦታዎች ቀኝ ሳይት (የስራ ቦታ) አደንቅሽ ሰፈር 794 ሄክታር እና ግራ ሳይት አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ 342.80 ሄክታር በድሩ 1,136.80 ሄክታር ሰርተን በሜትር አስለክተን ያስረከብን ሲሆን ቀኝ ሳይት አደንቅሽ ሰፈር ከተሰራው 794 ሄክታር ውስጥ አቶ ተራመድ መንግስቴ የተባሉ ግለሰብ ከእኛ ላይ ኮንትራት ወስደው 310 ሄክታር የሰሩ ለመሆኑ በሜትር ተለክቶላቸው የነበረ ሲሆን ሜቴክ ይሄንን ቦታ አቶ ተራመድ የሰሩትን ጨምሮ  ድጋሚ በ2DGPS ለክቼ 226.80 ሄክታር ብቻ መሆኑን አረጋግጫለው ብሏል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመ.ቁ 172128 ቀድሞ በሜትር በተለካው 310 ሄክታር ክፍያ ለአቶ ተራመድ መንግስቴ እንድንከፍላቸው ወስኖላቸው ሳለ ለዚህ ቦታ ሜቴክ በ2DGPS 226.80 ሄክታር ነው ብሎ በለካው ለእኛ  መከፈል አለበት የሚል ማንኛውም ውሳኔ  ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ ነው፡፡

በአጠቃይ እሱባለው ተካልኝ ህንፃ ስራ ተቋራጭ 1,136.80 ሄክታር ስለመስራታችን ከ3ቱ ህጋዊ የክፍያ ሰርተፍኬቶቻችን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ማስረጃዎቹን ውድቅ የሚያደርግ ማስተባበያ ወይም የውል ማሻሻያ ያልተገኘ ስለሆነ ኦዲተር መስሪያ ቤቱ እንዲቀበላቸው እና እንዲያጸናቸው፤ ካልሆነም ፍትህ አግኝተን ሁሉንም ክፍያችንን እስክናገኝ የሁሉም ማህበራት አንድ ላይ ተለክቷል ከተባለው እና ከታመነው 39,087.281 ሄክታር እና ሌላ 32,244.89 ሄክታር 2% ድርሻችን ታስቦ እንዲከፈለን እንዲሁም ያለአግባብ ለጠፋው 1.9 ቢሊየን ብር እኛን የጦስ እስረኛ አድርጎ የመኖር መብታችን እንዲጣስ ታስቦ በሀሰት ማስረጃ ከተቀነባበረው የፈጠራ የወንጀል ክስ ነፃ እንድንሆን እንድትረዱን እየተማጸንን ምላሹን በጽሁፍ እንድትሰጡን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡                                              

                                                    ከሰላምታ ጋር

                                                    እሱባለው ተካልኝ

ግልባጭ

ለ፡-