የግብፆች ዕቅድ፦ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሱዳንን እንደ እሳት⁉️

ታረክ የሚነግረን ኢትዮጵያ እንጂ ግብፅ ከቶውንም የሱዳን ህዝብ ወዳጅ ሆና እንደማታውቅ ነው። ከ100 አመታት በላይ ግብፅ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ሱዳንን በምስለኔ ስትመራ፣ ስትወጋ- ስታዋጋ፣ ሃብቷን ስትበዘብዝ፣ ግዛቷን ስትነጥቅ፣ ከአለም እንድትገለል ስታደርግ ኖራለች።

▪በዘመነ ቅኝ አገዛዝ፥  የአፍሪካ ሃገራት የተጫነባቸውን የቅኝ አስተዳደር ለማስወገድ ሲረዳዱ፤ ግብፅ ከእንግሊዝ ጋር ተጣምራ የጎረቤት ሱዳንን ህዝብ ስትረግጥ ስትበዘብዝ ነው የኖረችው።

ግብፅ እና እንግሊዝ አንግሎ ኢጂኘት (Anglo-egypt sudan) በሚል ሱዳን ላይ በዘረጉት የቀኝ አስተዳደር ስርአት ምድር ላይ ያለን ሁሉንም አይነት ጭቆና እና በደል በሱዳን ህዝብ ላይ አድርሰዋል ። በነዚህ ጊዜያት ሱዳናውያን ሁሉ ነገራቸውን ነው ያጡት። ማንነታቸው ተሰልቧል፤ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ሃብታቸው ተነጥቋል፤ ብሄራዊ ኩራት እና ስነልቦናቸው ተበርዟል፤ በሃገራቸው ግዞተኛ ሆነዋል። ግብፅ የሱዳን ቀኝ ገዢ ነው የነበረችው !!

ከነፃነት ማግስት ጀምሮም ቢሆን ግብፅ ለሱዳን ህዝብ ክብር ኖሯት አያውቅም። የድንበር ወረራ ስትፈፅም ‘ያልጣማት’ የሱዳን አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግስት ስታካሂድ ኖራለች። ሱዳን እዳትረጋጋ አማፂያን በማስታጠቅ እና በማስጠልል ነው ያለፋት ስልሳ አመታትን የተጓዘችው።

ግብፅ የሱዳን ጠላት እንጂ መልካም ተጎራባች ሃገር  ሆና ከቶም አታውቅም።

ሁለቱ ሃገራት ከ1200 ኪሜ የሚረዝም ድንበር ይጋራሉ፤ በድንበራቸው አቅራቢያ ከ2.5 ሚሊየን በላይ ህዝብ ይኖራል። ሆኖም ግብፅ ከ1956 ጀምሮ ሃሊያብ የተሰኘ በማዕድን ሃብት የበለፀገ የሱዳን ግዛትን በሃይል ወራ ይዛለች። ቦታው 700ሺ ቶን የሚገመት የማግኒዚየም ማዕድን ክምችት እንዲሁም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ እምቅ ሃብት ያለበት ነው። ስፍራው በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በግብፅ መንግስት ወታደሮች ቁጥጥር ስር ነው።

ግብፅ መራሹ ወረራ ሃገራቱ በግጭት የታጀበ ውጥረት ውስጥ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። በግብፅ መንግስት ውሳኔ ንግድም ይሁን የሰው እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ድንበራቸው ተዘግቶ ቆይቷል። በሁለቱ ሃገራት የሚኖሩት ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የጋራ ባህል እና ታሪክ ያላቸው የኑቢያ ነገድ ህዝቦችን ክፋኛ ጎድቷል። የኑቢያ ህዝብ የቆዳ ቀለም ጥቁር ፥ቁጥራቸውም አነስተኛ በመሆኑ የግብፅ መንግስት ስርአታዊ አድሎን ያደርግባቸዋል። የእነርሱ ጉዳት ከሌላው የግብፅ ህዝብ ጉዳት እኩል አይታይም።

ሱዳን ፥ግብፅ በሃይል የወሰደችባትን የሃሊያብ መሬት ለማስመለስ ብዙ ወታደራዊ እና ዲኘሎማሲያዊ ሙከራዎችን ከማድረግ አሁንም አልቦዘነችም።

ግብፅ ሁሌም ልማቷን የምታሰላው በሱዳናዊያን ጉዳት ነው!!

▪ግብፃውያን መሪዎች፥ ሱዳን ሳትጎዳ ግብፅ የምትለማ፣ ሱዳን ሳትበጣበጥ ግብፅ ሰላም የምትሆን እንዲሁም ሱዳን ሳትፈረካከስ ግብፅ ታላቅ ሃገር የምትሆን አይመስላቸውም። ይህ የክፋ ጎረቤት ሰይጣናዊ ሃሳብ ነው።

ግብፃውያን በ1960ዎቹ የአስዋን ግድብን ሆን ብለው የሱዳን ድንበር አቅራቢያ ሲገነቡ አንድ ነገር አስልተው ነበር። ይኸውም የግድቡ ውሃ መተኛ ስፍራ (ናስር ሃይቅ) ሱዳን ውስጥ እንዲሆን ፣ በዚህም  በውሃ መተኛ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ከ200 ሺህ በላይ ህዝቦች እንዲፈናቀሉ ማድረግ ነበር። ያሰቡትም ሆኗል!! ከለም አካባቢ ተነስተው በበረሃ ላይ ሰፍረዋል። ሱዳንን እንደ ሉአላዊ ሃገር የማያከበር፤ ህዝቦቿን የሚጎዳ የግብፅ የጠላትነት ተግባራት በዚህ አያበቃም።

ሱዳን ዛሬ ሁለት ሃገር እንድትሆን ‘መሀንዲሶች’ ግብፃውያን ናቸው። “ከጠንካራ እና ሰላማዊ ከሆነች ሱዳን ግብፅ አታተርፍም” የሚለው የግብፅ መንግስታት ስርአታዊ እሳቤ እስከ ዘመነ አብዱልፈታህ አልሲሲ ዘልቋል። የሱዳንን አንድነት ሸርሽሮ ፥ ወደ ብዙ ትንንሽ ሃገርነት ለመቀየር አድብተው እየሰሩ ነው።

በውስጥ፥ በዳርፉር፣ በደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል በተሰኙ የሱዳን ግዛቶች አማፂያን እንዲያይሉ የትጥቅ አቅርቦት፣ የዲኘሎማሲ ከለላ እና ወታደራዊ ስልጠና እያደረጉ ነው። በውጭ ደግሞ፣ ግብፅ ዋንኛ ጠላቴ ከምትላት ኢትዮጵያ ጋር ሱዳን የማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ የማራገቡን ስራ እየሰራች ትገኛለች።

የትሮይ ፈረስ ??

ሰሞንኛው የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ላይ ግጭትን ለማባባስ የካይሮን ደፋ ቀና ማለት ላጤነ የሴራው ፣ ምንነት፣ ባለቤቱ እና ግቡ ምን እንደሆነ   ይገለጥለታል።የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ጥያቄ 100 አመታትን የዘለቀ ነው፤  የሚሊሻዎች እና የገበሬዎች ግጭት ማስተናገዱም የተለመደ ነው። እንደ ልዩ ክስተት ዛሬ መልኩን ቀይሮ ሁለቱን ህዝቦች ወደ መደበኛ ውጊያ የሚያስገባ አንዳች ነገር የለውም። ታዲያ ” ነገርየው ለምን ጦዘ?” ስንል ተከታዩን የወቅቱን እውነት እናገኛለን።

ሱዳን አሁን እየተመራች ያለችው በግብፅ ሹመኞች  ነው።የሱዳንን ሽግግር መንግስት በበላይነት እየመራ ያለው ወታደራዊ ምክር ቤት ስልጣን የጨበጠው የግብፅን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ በውጭም በውስጥም ሊያስጠብቅ ቃል በመግባት ፥ በዋናነት ከግብፅ ባገኘው ድጋፍ ነው( ሳኡዲ እና አረብ ኤምሬቶችም አሉ)። ይህ ሃይል በእያንዳንዱ እርምጃው የሱዳንን ብቻ ሳይሆን የግብፅን ጥቅም ታሳቢ ያደርጋል። በውስጥም ይሁን በውጭ ጉዳዮች ግብፅን የማይጠቅም አንዳች ተግባር አይፈፅምም።በሌላ መልኩ የሱዳን ወታደራዊው ሃይል ለግብፅ የትሮይ ፈረስ ነው፤ ላሻት አላማ ማስፈፀሚያነት ወደ አሻት አቅጣጫ ትጋልበዋለች።

በግብፅ ትዕዛዝ ቀይ ባህርን ተሻግሮ በየመን የሚዋጋ ከ10 ሺህ በላይ ሰራዊት ማሰማራቱን ልብ ይሏል። አድርግ የተባለውን ይፈፅማል።

ከሰሞኑም ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠሩት ግጭትም በጌቶቻቸው የተወጠነ ፤ የእነርሱን ተልዕኮ ያነገበ ነው።  ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጭም የሰላም አየር በማሳጣት ፣በመወጠር እና በማጋጨት ቢቻል ህልውናዋን ማሳጣት፤ ካልሆነ በተራዘመ ቀውስ እንድትዳክር ማድረግ ነው አላማው።ይህ የዘመናት የግብፅ ቅዠት ነው። ወቅታዊው የሱዳን የፓለቲካ ሃይሎች ክፍፍል እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለው ውስጣዊ አለመረጋጋት ለክስተቱ ጊዜያዊ በር የከፈተ ይመስላል። አጋጣሚው ዘላቂ ቁርሾ እንዳይወልድ በስክነት እና በብልሃት መመርመር እና መወሰን ያስፈልጋል።

የግብፅ መንግስት የተዳከመች ሱዳን እና ኢትዮጵያን(ሁለት የላይኛው ተፋሰስ ሃገራት) ለመፍጠር ከመቼውም በላይ እየዳከረ የሚገኝበት ወቅት ነው።

▪እዚህ ጋር አንድ ነገር ላስታውስ። ግብፃዉያን የሚያውቁት ግን ሁሌም ማመን የማይፈልጉት አንድ እውነት አለ ፥ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት “በመልካም ጉርብትና” ላይ የታነፀ መሆኑን!! ይህ ተረት ወይ አፈ-ታሪክ አይደለም!!

የኢትዮጵያ  እና የሱዳን ህዝቦች መልካም የሆነ ጉርብትና ወረቀት ላይ ያለ ሳይሆን በመኖር የተገለፀ ፣ እየተገለፀም ያለ ነው። ብዙ ሺህ አመታትን በሰላም፣ በመከባበር፣ በመጠቃቀም የተጋመደ ነው። በባህል፣ በሃይማኖት፣ በስልጣኔ፣ በጋብቻ አብሮነታቸው የታገመደ ነው። የመንግስታቱ ግንኙነት መሰረትም ይህ የህዝቦቹ ወዳጅነት ነው።

One thought on “የግብፆች ዕቅድ፦ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ሱዳንን እንደ እሳት⁉️

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡