ለጅግና ሰው ህይወት እና ሞት አንድ ናቸው‼️

እንዲህ ያለው ጀግና መሪ “አንድ ለእናቱ ሺህ ለጠላቱ” ይባላል። አብይ እንደ ማንኛችንም አንድ ሰው ነው። ጠላቶቹ ሺህዎች ናቸው። ነገር ግን አንድ ብቻውን ሆኖ ሺህዎችን ያርበደብዳል። በዓለም ላይ ያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ ከያሉበት ተጠራርተው አብረውበታል። እኛም እውነትን እንዳንናገር፣ ኢትዮጵያዊነትን እንዳንዘምር ታፍነናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ይልቅስ ወዳጄ አንድ ሚስጥር ልንገርህ፣ ኢትዮጵያዊነት እና ጀግንነት አንድ ላይ የተቆራኙ ናቸው። ለሀገር መሞት ጌጥ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ይሄ አፈታሪክ አይደለም። በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መኖሯ በራሱ ምስክር ነው። ሌላ ልጨምርልህ፣ እስኪ ከላይ ያለውን ቪዲዮ ለአፍታ ተመልከተው። “እኛ ወደ ግንባር የዘመትነው ኢትዮጵያን ለመታደግ አሊያም ኢትዮጵያ ለመሆን ነው”

ስማኝ’ማ የሀገሬ ልጅ አቢቹ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ላይ “እኛ ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን” ብሎ ሲናገር አጉል ጉራ መስሎህ ነበር እንዴ? አይደለም! ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ዘመናትን ተሻግራ መኖሯ በራሱ እማኝ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ማንኛውም ሀገር አይደለችም። እንደ ቡርኪናፋሶ፣ ኬኒያ አሊያም ናይጄሪያ በቅኝ ገዢዎች ተጠፍጥፋ የተሰራች ሀገር አይደለችም።

ኢትዮጵያ ሁለት ናት፦ መስዕዋትነት እና ነፃነት! እነዚህ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት በተለየ ሉዓላዊነቷን ሳታስደፍር የኖረችው ጀግኖች ልጆቿ በከፈሉት መስዕዋትነት ነው። አባቶቻችን በመስዕዋትነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ጠብቀው ያስረከቡን እኛ ልጆቿ በነፃነት እና እኩልነት እንድንኖር ነው።

የወያኔ ክፋቱ/ጥፋቱ ምንድነው? አባቶቻችን በመስዕዋት ባቆሟት ሀገር ላይ በነፃነት ፋንታ ፍርሃት፣ ከእኩልነት ይልቅ የራሱን የበላይነት አሰፈነ፣ ከአንድነት እና አብሮነት ይልቅ ልዩነት እና ጥላቻን እየሰበከ እርስ በእርስ አባላን። በሀገራችን ላይ ባዕድ አደረገን። በወራሪ ጠላት የተያዝን ቢመስለን “እምቢኝ!” አልን። የወያኔን የጭቆና ቀንበር ለመጣል በምናደርገው ትግል ውስጥ ዶ/ር አብይ የተወለደው።

ኢትዮጵያዊ ሆነን ስንወለድ አባቶቻችን በነፃነት እና እኩልነት የምንኖርባት ኢትዮጵያ የምትባል ገፀ-በረከት አውርሰውናል። ይህን ገፀ-በረከት ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ የኢትዮጵያውያን ነፃነት በአንድ ወገን የበላይነት ወይም በወራሪ ጠላት እንዳይገፈፍ የመጠበቅ ግዴታ አለብን። ጨቋኞች እና ጠላቶችን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል መስዕዋትነት እንከፍላለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

መስዕዋትነት እና ነፃነት የኢትዮጵያዊነት ሁለት ገፅታዎች ናቸው። የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት በማስከበር በነፃነት እንኖራለን አሊያም ደግሞ ከጠላት ጋር ተዋድቀን መስዕዋት እንሆናለን። በነፃነት ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ መስዕዋትነት ስንከፍል ደግሞ ኢትዮጵያ ነን። የምንኖረው በነፃነት ነው፣ የምንሞተው ለነፃነት ነው። ሁለቱም ኢትዮጵያ እና ስለ ኢትዮጵያ ናቸው። ዶ/ር አብይ ሲኖር ኢትዮጵያዊ፣ ሲሞት ኢትዮጵያ ነው!

ስማኝ’ማ፣ ለጅግና ሰው ህይወት እና ሞት አንድ ናቸው! በህይወት እስካለ ድረስ ለሀገሩ ይኖራል/ይሰራል። ከሞተም በኋላ ሉዓላዊነቷን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ባወረሳት ሀገር ውስጥ ለዘላለም ይኖራል። አድዋ ምንድነው ነው። አድዋ ዝም ብሎ ቦታ አይደለም። አሊያም ደግሞ የድል በዓል እንዳይመስልህ። አድዋ ማለት ለእኔ እና እናንተ የተከፈለ መስዕዋትነት ነው።

አድዋ የሚለው ቃል ኢትዮጵያ እስካለች ድረስ ይኖራል። ኢትዮጵያ የፈረሰች ዕለት ግን ቃሉም ይረሳል። ምክንቱም ኢትዮጵያ ማለት አድዋ ላይ መስዕዋት የሆኑት ጀግኖች አባቶቻችን ናቸው። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ክና አንድነት፣ የዜጎች እኩልነት እና ነፃነት የተገፈፈ ዕለት አድዋ የሚለው ቃል የመፈረካከስ ይጀምራል። ምክንያቱም አድዋ ላይ የተከፈለው መስዕዋት ከንቱ ሆነ ማለት ነው። ወያኔ “አድዋን ትቶ ስለ አኖሌ ሲለፍፍ የኖረው ለምን ይመስልሃል። ልክ እንደ ፋሽስት ኢጣሊያ የኢትዮጵያ ጠላት ስለሆነ ነው።

ወያኔን ለማስወገድ መስዕዋት የምንከፍለው የአባቶቻችንን መስዕዋትነት ለማክበር፣ ለቀጣይ ትውልድ የምናስረክበው ሀገር እንዲኖረን ነው። ዶ/ር አብይ የዘመተው ለዚህ ነው! የተረከባትን ኢትዮጵያ አንድነቷን እና ነፃነቷን ጠብቆ ያስረክባል። ለዚህ ደግሞ በጀግንነት ተዋግቶ ያሸንፋል ወይም መስዕዋት ይሆናል። አፄ ሚኒሊክ በጀግንነት ተዋግቶ አሸንፏል። አፄ ቴድሮስ በጀግንነት ተዋግቶ ራሱን ሰውቷል። አፄ ሚኒሊክ ያሸነፈው በእልፍ ጀግኖች መስዕዋትነት ነው። አፄ ቴድሮስ ራሱን መስዕዋት ያደረገው ጀግና ስለሆነ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር የምንለው ለምንድነው? አንደኛ፦ የአባቶቻችን መስዕዋትነት በከንቱ እንዳይቀር፣ ሁለተኛ፦ እኛም በነፃነት የምንኖርባት ወይም መስዕዋት የምንሆንላት እንዳናጣ ነው። የሚኖርበት እና የሚኖርለት ሀገር የሌለው ሰው ባሪያ ነው። በባርነት ስር ያለ ሰው እንኳን ዜግነት በህግ የተሰጠ መብት የለውም። ስለዚህ ኢትዮጵያ በልጆቿ ደምና አጥንት ለዘላለም ታፍራ እና ተከብራ ትኖራለች‼️ አሜን🇪🇹