ለአማራ ሕዝብ እናስባለን ለምትሉ ወገኖች: አብንን አታባክኑት!

1) ድርጅት ሂደት አለው። በመሃል ውጣ ውረድ ይገጥመዋል። ይሄ በድርጅቶች ዘንድ እንደ ተፈጥሯዊ ሂደት የሚቆጠር ነው። አንድ ሰሞን በደንብ ሰርቶ፣ ሌላ ጊዜ የሚዳከምበት፣ በመጀመርያው ወቅት በደንብ ታግሎ ቀጥሎ የሚቀዘቅዝበት፣ በጥቂት አመራሮቹ ተናባቢ ሆኖ፣ ቀጥሎ የአባላትን ብዛት፣ የአመራሩን ድክመት መቆጣጠር የሚሳንበት ጊዜዎች አሉ። ይህን የድርጅት ተፈጥሯዊ አካሄድ፣ ፈተናና ድከመቶች ተረድቶ መፍትሄ ማምጣት ነው የሚያዋጣው። በአገራችን በርካታ ድርጅቶች ፈርሰዋል። ብዙዎቹ አቅማቸውን አጥተው በተወሰነ ኃይል አሉም የሉም የሚያስብል አጠራጣሪ ሁኔታ ላይ ናቸው። የፈረሱትት በተቀናቃኝ ኃይል ብቻ አይደለም። አባላቱና አመራሩ አቅል ማጣት፣ የአመራሩ ችግር፣ የድርጅት እድገትና ክፍተቶችን ባለመረዳት ነው። የኢህአፓ አባላትና አመራሮች የድርጅታቸው መፍረስ አሁንም ድረስ ይቆጫቸዋል። ያኔ ግን አንዱ አንዱን ጎንትሏል። ዛሬ ያተረፉት ውድቀትና ፀፀት ነው። እንትና ነው ያፈረሰው፣ አይ እንትና ነው የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ለሕዝብ አይፈይድም። የአንድነት፣ የሰማያዊ ወዘተ አባላትና አመራሮች ድክመትና ደረጃውን ሳይረዱ አባክነው አፍርሰዋቸዋል። መኢአድ ብዙ ጊዜ ተጎትቶ ያን ግዙፍ አቅሙን አጥቷል። የእነ ፕሮፌሰር አስራትን መአህድ  ጠላት ከውጭ፣ ብዙ የጠበቀበት ደጋፊና አባል ከውስጥ ብዙ ተፈታትነውታል።

ፀሃፊ ጌታቸው ሽፈራው

አንድ መኪና ነዳጅ ጨርሶ፣ ሞተር ወይንም ሌላ ክፍሉ ተበላሽቶበት፣ አሊያም ሾፌሩ ከፊት የሆነ አደጋ አይቶ፣ ወይ ደክሞት፣ አሊያም ለግሞ ሊቆም ይችላል። ተሳፋሪዎቹ “ዝም ብለህ ካልሄድክ” ካሉት ገደል ነው የሚገባው።  ተሳፋሪዎቹም ጭምር ወርደው አሊያም ጠይቀው መኪናው የቆመበትን ምክንያት ማጣራት አለባቸው።  ካጣደፉት መኪናውም እነሱም አይተርፉም። አብን ምን ገጠመው ብሎ በውስጥ መነጋገር አዋጭ ነው። የሄደበትን ደረጃ ማወቅ ጥሩ ነው። አብን የባለው ምርጫ እንዲራዘም ደፋር ውሳኔ ወስኗል። ቀጥሎ በጦርነቱ ውሳኔ ወስኗል። በቀጠለው ምርጫ ገብቶ ተወዳድሯል። የስልጣን ጉዳይ ላይ ደፋር ውሳኔ ወስኗል። በዚህ ሂደት ከተቀናቃኝ የነበረን እንቅፋት፣ ከገዥዎቹ የነበረን ደባ፣ ከአባላቱና ከሕዝብ የነበረን ፍላጎት አጣጥሞ ለማለፍ የቻላትን አድርጓል። ይህ ሁሉ ብዙ ውጣ ውረድ ነው። ።ለአዲስ ድርጅትና ለወጣቶቹ አሰልች፣ አድካሚ፣ ተስፋ አስቆራጭ ወዘተ ሁነቶች አልፈዋል። በዚህ መሃል ምን አጋጥሞት ነው ተብሎ መጤን አለበት። ኦፌኮ ወላልቋል። ኦነግ ተበታትኗል። አረና ዝም ብሏል። የአብንን ያህል ጩኸት ግን አይሰማባቸውም።

አብን ሕመም ካለበት እንዲታከም ማገዝ ነው። የታመመ ሰው እንዲታከም ይታገዛል እንጅ እንደሞተ ሰው “እሪ” ተብሎ ላዩ ላይ አይለቀበትም። ህመሙን ካላወቀው በአግባቡ መንገር ነው። አብን ታምሞ ከሆነ እንዲያገግም እድል ይሰጠው። የባለሙያ ምክር ይሰጠው። ደጋፊና አባሉ ያግዘው።

የአብን አመራሮች ፌስቡክ ላይ ካለነው ተሽነው፣ ደፍረው ነው የገቡበት። እነሱን መጠየቅ፣ እገዛ ካስፈለግም ማገዝ እንጅ ጮኸቱ መልካም ነገር ይዞ አይመጣም። ስልጣን ላይ የወጡ በእልህ አምባገነን እንደሚሆነው ሁሉ ተቃዋሚዎችም ወዳልሆነ አቅጣጫ  ይገፋሉ። የሰዎች ስብስብ ስለሆኑ እልህና ብሽሽቅ ውስጥ ይገባሉ። የፓርቲ አባልነትና አመራርነት ስያሜ ተሰጣቸው እንጅ እንደኛው ሰዎች ናቸው። ስሜት አላቸው። ቤተሰብ አላቸው። የራሳችን የሚሉት ክብር አላቸው። አማራጭ አላቸው።

2) ቀጣዩ ጊዜ ወሳኝ ነው።  የምክክር ኮምሽን ተቋቁሟል። አንዳንድ ኃይሎች እንደ ወሳኝ የፖለቲካ መታጠፊያ አይተው እየተዘጋጁበት ነው። ይህን ወቅት አማራ በደንብ መጠቀም አለበት። የተቀሙ ማንነቶችና ርስቶች ጉዳይ አለ።  የተዛባ ትርክት አለ። ላዩ ላይ የቆሙበት አሰራሮች አሉ። ይህን ወቅት እንደገና ኃይልን አሰባስቦ የሚገባበት እንጅ ወደመሰላቸት የሚያስገባ አቅል የሚነሳ ንትርክና ጭቅጭቅ የሚደረግበት አይደለም። ጥያቄ ያነሳልናል ብለን የምንጠብቀው አብን ቀርቶ የምንወቅሰው አማራ ብልፅግና በጉባኤ ተበታትኖ ገብቶ የገጠመውን አይተናል። አብን  ለቀጣይ እንዲዘጋጅ የበኩላችን እናድርግ። አመራሩን ነጥሎ ማሞገስም ሆነ ነጥሎ ማበሻቀጥ ለጠላት እንጅ ለወገን አይጠቅምም። ድርጅትን የምንገድለው ነጥለን በማሞገስና ነጥለን በመውቀስ ነው። የቤት ግማሹን ምሰሶ ቆርጠን፣ በቀሪው አንኖርም። ድርጅት ድርጅት ነው።

3) ለጠላት ምቹ እየሆንን ነው። በዚህ ሁለት ሶስት ቀን አንደኛውን እየወቀሱ ሌላውን የሚያሞግሱት ከአሁን ቀደም ፀረ አብን የነበሩ ሰዎች የተመቸናቸው እኛው ነን። ስሜታዊ ከሆነው ፌስቡከኛ ነጥለው ሁለቱንም ለማዳከም እድል ስለሰጣቸው ነው። የማይፅፉ ግን አቅደው የሚያባብሱት ብዙ ናቸው። በሴራ ጉዳዩን ለማጦዝ የሚሞክሩት ብዙ ናቸው። ስለሆነም ለጠላት አለመመቸት ለሁላችንም ይጠቅማል። ዩቱዩበኛው፣ ፌስቡከኛውም ለአጀንዳ እንጅ ለአላማ ላይፈልገው ይችላል። አብንን ለሕልውና ጉዳይ፣ ለአላማ የምንፈልገው መስከን አለብን። ሕመም ካለበት ሕመሙን አብረን ታምመን ማዳን አለብን።

4) አፍለኝነት ድርጅት አይሰራም። ለፖለቲካ አያዋጣም። አንድ ሰሞን አንገቴን እሰጠዋለሁ ስንለው የነበረውን ድርጅት አንገቱ ቢቆረጥም ችግር የለብኝም እስከማለት የሚደርሱ አሉ። አማራ ለረዥም ጊዜ ድርጅት አልነበረውም። ወገኖች ሲጎዱ፣ በመሃል ወጣቶች ሲገደሉ፣ የሆነ ጉዳይ ሲኖር አብን መግለጫ አላወጣም ብሎ እርር ድብን የሚል አለ። መግለጫ ማውጣት ይኖርበት ይሆናል። ግን በእነዚህ ሁነቶች ድምፅ አልሆነንምና የራሱ ጉዳይ ማለት የወደፊቱን አለማሰብ ነው። ድምፅ እንዲሆን ማትጋት እንጅ ማሸማቀቁም አይጠቅምም። ፌስቡክ ላይ መፃፍ ስለምንችል ብቻ የድርጅቱን መብት አንቀማው። በግልና በራሳችን ፈቃድ፣ በማንችለው ኦዲተር ሆነን፣ አቃቤ ሕግ ሆነን፣ ዳኛ ሆነን፣ ጠበቃ ሆነን፣ የበላይ ጠባቂ ሆነን አብንን እንደ ድርጅትም በግለሰቦች ደረጃም ስንገምትና ስንፈርድ እየዋልን ነው። ስህተት ነው። ከድርጅቱ መጠበቅ፣ ድርጅቱ ይህን እንዲያደርግ አግባብ ባለው መልኩ መጠየቅ አለብን።

5) አንዳንዶች ስለሌላ አማራጭ ድርጅት ያወራሉ።  አብን የተሻሉ የተባሉ ወጣቶችን ይዞ የተነሳ ድርጅት ነው። የምናደንቃቸው፣ “እኔ ነፍሴን ልስጥለት” የምንላቸው ሰዎች፣ ፎቷቸውን በፌስቡክ ተሸክመን ጀግና ስንላቸው የከረሙ ሰዎችን የያዘ ነው። “መዳኛችን አብን ነው” ስንል ነበር። ይህን ባልንበት ተስፋ ቆርጠን ሌላ አዲስ ማሰብ  ከወቅታዊ ቅያሜና ስሜት ያለፈ ብስለት የሚታይበት አይሆንም።

አብን የወሰንና ማንነትን ጉዳይ፣ የህዝብ ቆጠራን ወዘተ ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎችን ገዥዎች የግዳቸውን እንዲይዙት አድርጓል። ማንም እየመጣ የፈለገውን አጀንዳ ይጥልበት የነበረውን የአማራ ጉዳይ አይነኬ እንዲሆን፣ ቢያንስ በርካታ ኃይሎች ከመናገራቸው በፊት እንዲያስቡ በማድረግ አብን ትልቅ ሚና ተጫውቷል። አመራር ወዲያ ወዲህ ባለበት ጦርነት አብን ከፊት ተገኝቷል። ይህ ቀላል ጉዳይ አይደለም። ከዚህ የተሻለ አዲስ አማራጭ አመጣላሁ ከማለት አብን በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ማገዝ አዋጭ ነው።

 አብን ደፋር የተባሉት ወጣቶች ስብስብ ነው። አዲስ ድርጅት ቢኖር የሚሉ ውጣ ውረዱን ያልተረዱ ናቸው። አብን ብሔርተኝነቱ በሞቀበት፣ አንድነት በነበረበት ወቅት ብዙዎች የተቀላቀሉት ነው። የአብንን ያህል እድል ያለው ፓርቲ የለም። አይደለም አዲስ ፓርቲ ለአብንም እንቅፋቶች በዝተዋል። የያዙትን ማጥበቅ እንጅ ሌላ አዲስ ድካም፣ ሌላ ስራ ላይ መጠመድ፣ ፖለቲካውን ያዝ ለቀቅ ማድረጉ ብዙም አዋጭ የሚሆን አይመስልም።

6) የስልጣን ጉዳይ መጨቃጨቂያ መሆን የለበትም። አብን የተወዳደረው ስልጣን ሊይዝ ነው። የአብን ደጋፊ የሆነ እንዲያውም ማለት ያለበት “ያንሰዋል” ነው። “ተጨማሪ ስልጣን ያስፈልገዋል” ማለት አለበት። ስልጣን ይዞ እንጅ ፌስቡክ ላይ አጀንዳ እንዲያመጣ ብቻ አይደለም “ድርጅቴ፣ መሪዬ” ያልከው/ ያልሽው። በሌላ አገር የጥምር መንግስት ወዘተ ተብሎ ተቃዋሚዎች ካልተካተትን ብለው ይጮሃሉ። በእኛ አገርም ስልጣን ብቻ ሳይሆን ስብሰባም ሳንጠራ ብለው የሚጮሁ ሞልተዋል። ትክክል ናቸው።

 ሌላ የማይወደው ፖለቲከኛ ሲሾምም ተቃውሞ፣ እደግፈዋለሁ የሚለው የአብን አመራር ሲሾምም ተቃውሞ አይሆንም። የራሴ የሚባል ድርጅት ነገ ስልጣን የመረከብ አቅም ይኖረዋል የሚል አካል ዛሬ በስልጣን ሲለማመዱ መውቀስ የለበትም። የምትጠላው መንግስት አካል የሆነን ስልጣን ያዘ ብለህ የምትቃወም ከሆነ ችግር ነው። ድርጅት የሆነው ቀስ በቀስም ይሁን በአንዴ ያን የምትጠላውን መንግስት ስልጣን ሊረከም ነው። አብን ሙሉውን ስልጣን የመረከብ አቅም የለውም። አንድም ሁለትም ሲይዝ እንደ ፍርፋሪ ከቆጠርከው ከመጀመርያው ነው የተሳሳትከው፣ የተሳሳትነው።

 ዛሬ ስልጣን ምን እንደሆነ፣ ተቋም መምራት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቁ ወንድም እህቶች ናቸው ነገ አገር ሊመሩ የሚችሉት። ከብአዴን አንድ ደፋር ሰው ሲመጣ፣ ወይ ሲገባ ከጎኑ እየቆሙ ተቃዋሚው ስልጣን ያዘ ብሎ መቃወም ለፖለቲካው ግራ መጋባት ይሆናል። ከእነ ድካማቸው የ1960 ዎቹ ተቃዋሚዎች ሰነድ በማዘጋጀት፣ በመተንተን ወዘተ እየጠላናቸውም የሆነውን ጎናቸውን የምናደንቃቸው ልምድ ስላገኙ ነው። በንጉሱም በደርግም ዘመን ስልጣን ላይ ስለነበሩ፣ ስልጣን ላይ የነበሩ ወገኖችን ስላጠቃለሉ ነው። ስልጣንን የምናይበት አይን መስተካከል ይኖርበታል። ስልጣኑ አላማውን እንዳያስረሳው በተገቢው መንገድ እያተጋን መጠቀም የተሻለ ነው። አብንን እያስወቀሰ “የሽግግር መንግስት” ወዘተ የሚለው በሽግግር ስም ስልጣን ፈላጊ ነው። ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ወደጎራው የገቡት ስልጣን ሊይዙ ነው።  

በእርግጥ የማንተቸው አንድ ተቋም፣ የማንጎትተው አንድ የራሳችን ብለን ያስተዋወቅነው ድርጅት፣ ድሮ ጀግናዬ ብለን የማንዘልፈው ማን አለ?

One thought on “ለአማራ ሕዝብ እናስባለን ለምትሉ ወገኖች: አብንን አታባክኑት!

 1. ሀ)
  ይገርማል!
  በዚህ ሰሞን በፋሲል የኔዓለም፣ በናትናኤል መኮንን፣ በታዬ ቦጋለ፣ ኢሳቶች፣ በበለጠ ሞላ (አብን) ላይ (ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ) የማይገባ ጭፍን ዘለፋ እየወረደ ነው፤ የማሸማቀቅ ሙከራም እንዲሁ፤ (በየገጻቸው ኮሜንቶችን ማየት ነው)፡፡ ይህ ዘመቻ የሆነ ግንኙነት ያለው/አንዱ ከሌላው የተያያዘ ይመስላል! (Pattern)፡፡ እኔ ሦስት ነገሮችን አያለሁ – ሁለቱ ውጫዊ አንዱ ውስጣዊ፤
  1) በዲጂታል መድረኩ ላይ የተደራጀ፣ የተቀናጀ የኢትዮጵያ ጠላቶች የጥቃት ሤራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ማሳያ ነው! የእኛም ጸረ ወያኔ ትግል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት!
  2) የጥቃቱ ዋና ዒላማ የተደረጉት በአብዛኛው የብልጽግና ፓርቲ አባልም ደጋፊም ያልሆኑ ናቸው! በሐገርና ዴሞክራሲ ወዳድነታቸው ከወያኔ ንግሥና ዘመን ጀምሮ አምርረው በመታገል ብዙ ዋጋ የከፈሉ መሆናቸውን እንመሰክራለን!
  3) ከጠላት በማይተናነስ ሁኔታ ግን፣ ቁጥሩ ጥቂት የማይባል ሠው፣ የሐገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ – ሥጋቱን፣ ልፋቱንና ተስፋውን – እና የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን የማየትና የመረዳት ትልቅ ችግር ውስጥ የሚገኝም ይመስላል! “መንጋነት” ነው የሚሉት?!
  ለዚህ ብዙ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፤
  ለውጫዊው ጥቃት የተቀናጀ ምላሽ- የመቋቋምና የማሸነፍ ትግል፣ ለውስጣዊው ሥንፍና ደግሞ በትዕግሥት የማስተማርና የተጣራ መረጃ በጊዜ የማቅረብ ጥረትን ይጠይቃል!
  እንኳን ይህንንና ትልቁንም የወያኔ ፈተና እየተወጣነው ነው! አሁንም እንበርታ!
  ለ)
  ትችትና ተቃውሞ መሥመሩን ሲስት የአሉታዊ የአእምሮ ውቅርና የአሉታዊ ጉልበት መገለጫ ብቻ ይሆናል፤ ከጥቅሙም ጉዳቱ ያመዝናል!
  ትችትና ተቃውሞ ጠቃሚ የሚሆነው፣ በማስረጃ፣ በምክንያት፣ በሚዛናዊነት፣ በቅንነት፣ በፍቅር፣ በመፍትሔ ፈላጊነት፣ በገንቢነት መንፈስና ዓውድን በመረዳት ሲታጀብ ነው!
  አሉታዊ የአእምሮ ውቅርና አሉታዊ ጉልበት ያለው ሰው፡
  • ማስረጃ ሣይፈልግ አሉባልታን ያምናል፣ ያሰራጫል
  • ከአለው፣ ከሞላው፣ ከበጎው ነገር ይልቅ የሌለው፣ የጎደለው፣ ክፉው ነገር ቀድሞና ገዝፎ ይታየዋል፣ ያንን ተጣድፎ ያንጸባርቃል
  • ማመስገን የሚባል ከቶ አይመጣለትም፤ መርገም፣ መኮነን ይቀለዋል
  • እንደ ብርሐን የደመቀው የሙሉ ነጭ ልብስ ትልቁ ውበት ሣይታየው፣ በልብሱ ላይ ጠብ ያለ ትንሽ ጉድፍና ይህም የፈጠረው የጨለማ ነጥብ ጎልቶ ይታየዋል፣ ዘሎ አቃቂር ያወጣል፣
  • በጨለማ ላይ የብርሐን ጮራን ማስተዋል አይችልም፣ ተስፋ ብሎ ነገር አይታየውም፣
  • የሰውን ጠንካራ ጎኑን ሳያዩና ሳያበረታቱ፣ እንከኑን ብቻ ነቅሶ ማውጣት፣ መታዘብ፣
  አቃቂር ማውጣት፣ ሰውን መኮነንና መዝለፍ አዋቂነትና ትልቅነት ይመስለውና ከንቱ ይታበያል፣ ይኮፈሳል!
  • አሉታዊ የአእምሮ ውቅርና አሉታዊ ጉልበት ያለው ሰው፣ ሚዛናዊነትና ምክንያታዊነት የጎደለው ጭፍን ትችትና ተቃውሞን ያበዛል፣ መለያውም ያደርገዋል!
  ለራሳችን አዎንታዊ የአእምሮ ውቅርና ጉልበት ለመፍጠር እንትጋ!
  ፈጣሪ ይርዳን!

  Like

ምላሽ ይስጡ

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.