ውቡ የጣና ሐይቅ በሞት ጥላ ሥር!

በሃገራችን በስፋቱ የቀዳሚነትን ቦታ የሚይዘው ታላቁ ብሄራዊ ሃብታችን የጣና ሐይቅ ህልውና በከፍተኛ አደጋ ውስጥ መሆኑ እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በ3672 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ የተንጣለለው የጣና ሐይቅ ከሰሜን ወደ ደቡብ 84 ኪሎሜትር ርዝመት፤ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ደግሞ 66 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ነው፡፡  ጥልቀቱ ሲለካ በተደጋጋሚ የሚመዘገበው መጠን 9 ሜትር (30 ጫማ) ሲሆን፣ ከፍተኛው ጥልቀት ደግሞ 14 ሜትር (46ጫማ) እንደሚደርስ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዜያት የሚያወጣቸው የጥናት ውጤቶች ጠቁማሉ። ሐይቁ በራሱ ቱሪስቶችን የማማለል ድንቅ ውበት ቢኖረውም በውስጡ በያዛቸው ጥንታዊ አድባራት፣ ገዳማት እና ደሴቶች ምክንያት ከሁለት አመት በፊት በተባበሩት መንግስታት የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ተመዝግቧል፡፡

ሃይቁ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጋር ያለው ቁርኝት ጥብቅ ነው፡፡ በቤተክርስቲያኗ መምህር የሆኑት  መ/ር ዘመድኩን በቀለ “ጣና ማነው? በውስጡ ያሉ ሀብቶችስ ምንድን ናቸው?” በሚል ርዕስ በከተቡት ፅሁፍ የሐይቁ ስያሜ መንፈሳዊ ምክንያት እንዳለው የቤተክርስቲያኗን መዛግብት ጠቅሰው እንዲህ ያትታሉ:

“ሐይቁ ‘ጣና’ የሚለውን ስያሜ ያገኘው እመቤታችን በስደት ዘመኗ በጣና ቂርቆስ ገዳም ውስጥ በነበረች ጊዜ የ3 ወር ከ 10 ቀን ቆይታዋን አጠናቅቃ ወደ ገሊላ ናዝሬት ይመለሱ ዘንድ ይመራቸው የነበረው መልዓከ- እግዚአብሔር ለአረጋዊው ዮሴፍ በህልም ተገልጦ “ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ወደ ሃገራችሁ ሂዱ” ብሎ ስለነገረው ቅዱስ ዮሴፍም ወደ ህፃኑ በመቅረብ “ፀአና በደመና” (“በደመና ጫናት”) ባለው ጊዜ. ፤ የገዳሙ ስም “ጣና” ከሐይቁ ጭምር “ጣና” ተባለ ተብሎ ይተረካል፡፡”

በጣና ሐይቅ በመሃል እና ዳርቻ ወደ 30 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያኖች በብዙ ቢልዮን ከሚገመቱ ውድና ክቡር ቅርሶቻቸው ጋር የሚገኙበትም አስደናቂ ሃይማኖታዊ ሥፍራ ነው ። የመምህር ዘመድኩን ፅሁፍ እንደሚያስረዳው በኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖትን የሰበከውና ያቀጣጠለው  የመጀመሪያውም ለኢትዮጵያ ጳጳስ የሆነው አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ወይም ፍሬምናጦስ መቃብሩም የሚገኘው በጣና ሐይቅ ላይ ነው ። የአፄ ዳዊት፣ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የአፄ ሱስንዮስ፣ የአፄ ፋሲል አስከሬናቸው ሳይፈርስ በክብር ተቀምጠው የሚገኙትም በዚሁ በጣና ሐይቅ ላይ ከሚገኙ ገዳማት በአንደኛው “ዳጋ እስጢፋኖስ” በተባለው ገዳም ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድም ሁለት ዓመት ከስድስት  ወር ያህል በዚሁ በጣና ሐይቅ በቅዱስ ቂርቆስ ገዳም በመቀመጥ ከተለያዩ የዕጸዋት ቀለም በመጭመቅና በመቀመም በራሱ እጅ በብራና ላይ የጻፈው ምልክት አልባው የድጓ መጽሐፉ ፣ የእጅ መስቀሉ፣ ከሐር የተሠራ ካባው የሚገኙት በዚሁ በጣና ሐይቅ ላይ በሚገኘው የቅዱስ ቂርቆስ ገዳም ውስጥ ነው ።

በሐይቁ ላይ  ጣና ነሽ፣ አይሻ ፣ ድል በትግል፣ የካቲት ፣ዳህላክ ፣ አንድነት ፣ ታጠቅ ፣ ኅብረት ፣ሊማሊሞ፣ደቅ እና ጣና ቂርቆስ የሚባሉ ጀልባዎች  የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡበታል፡፡አንድነት፣ታጠቅ እና ሊማሊሞ የተሰኙት ጀልባዎች ፋሽስት ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ሲባረር በአንጋራ ደሴት አስጥሟቸው በጥቆማ ተፈልገው የወጡ ጀልባዎች ናቸው፡፡ አሁን ባለው ይዞታ የጣና ሃይቅ 1,454 ቶን አሳ በዓመት ይመረታል ተብሎ ይገመታል ። ነገር ግን ይሄ ምርት ሐይቁ ያለምንም ችግር ሊያስተናግድው ከሚችለው 15 በመቶ ያህል ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ ።

ብዙ ሳንንከባከበው ይህን ሁሉ በረከት እነሆ ሲለን የኖረው የጣና ሃይቅ ዛሬ ክፉኛ ታሟል፤ደህንነቱ አደጋ ላይ ነው እንደ ፀጉራም በግ አለ ሲሉት ሊሞት እየተንደረደረ ያለው ጣና የድሮ ግርማ ሞገሱ አብሮት የለም፡፡ ድሮ ከጎንደር ፋሲለደስ ቤተ-መንግሥት ማማ ላይ ቆመው ማየት ይቻል የነበረው ውኃ አሁን እየሸሸ እየሸሸ ከዐይን መራቅ ከጀመረ ቆየ፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወደ 672 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚያክል የሃይቁ ክፍል ወደ የብስነት ተቀይሯል ይህ ማለት 3672 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የነበረው የጣና ሃይቅ ስፋት ወደ 3000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ወርዷል፡፡በሌላ አነጋገር የሐዋሳ እና የዝዋይ ሃይቅ ተደምሮ የሚያክለው የሃይቁ ክፍል ወደ የብስነት ተቀይሯል ማለት ነው፡፡
የጣና ሐይቅን አደጋ ላይ ከጣሉት ምክንያቶች አንዱ የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ነው፡፡የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የሐይቁ ጥልቀት ከ50 ሣ.ሜ በላይ እንደቀነሰ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት የሃይቁ በደለል መሞላት ነው፡፡ ይህ ችግር የብዙ አመታት የአፈር መከላት ጥርቅም ውጤት  እንጅ በአንዴ የመጣ ነገር አይደለም፡፡ የጣና ሃይቅ በስፋት እየተከሰተ ካለው የአፈር መከላት እና በደለል መሞላት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ወደ ጣና ሃይቅ የሚገባውን የደለል መጠን ለማጥናት የተደረጉ ጥረቶች ጥቂት ከመሆናቸው በላይ የመረጃ እጥረት እና አስተማማኝነት ይጎድላቸዋል፡፡ በጎርፍ እጥበት ሃይል ተነድቶ በቀጥታ ወደ ሃይቁ የሚገባው የደለል መጠን ምን ያክል እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የታችኛው የጣና ተፋሰስ አማካይ የአፈር መከላት መጠን በዓመት 70 ቶን በሄክታር እንደሚሆን ይገመታል (ክንድዬ፣ 2013፤ NBCBC 2005፤ ጥላሁን እና ሌሎች 2014)፡፡ 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎችን መልሶ ለማልማት የተደረገውን ጥናት መሰረት በማድረግ ከወንዞች እና ከሌሎች ውሃማ ክፍሎች በቀጥታ ወደ ሃይቁ የሚገባው የደለል መጠን በተለይ በአማካይ በዓመት በሄክታር 7 ቶን እንደሆነ ታውቋል (FAO፣ 1986)፡፡ የጣና ሃይቅ የተጣራ ዓመታዊ ደለል የማረጋጋት እና የመያዝ አቅም በዓመት 1,043,888 ቶን ሲሆን ስሌቱም ደለል የማስቀረት አቅሙን 49% ያደርገዋል፡፡ በዚህ መሰረት በዓመት 869,907 ሜትር ኩብ የሆነ አጠቃላይ የደለል ክምችት በሃይቁ ውስጥ እንደሚኖር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ ደለል ወደ ሃይቁ እንዳይገባ የሚታገደግ  በዓባይ ወንዝ እና በጣና በለስ የዋሻ በር ስራ ሊሰራ ይገባል (ሃኒባል ለማ እና ሌሎች፣ 2015)

ሶስተኛው ምክንያት አደገኛ ኬሚካሎች እና የፕላስቲክ ውጤቶች ቀጥታ ወደ ሐይቁ የሚገቡ መሆናቸው ነው፡፡በባህርዳር ከተማ በሀይቁ ዳርቻ የሚገኙ ትልልቅ ሆቴሎች የፍሳሽ መስመር ከሐይቁ ጋር የተገናኝ በመሆኑ ትንንሽ የፕላስቲክ ውጤቶችን ጨምሮ የሆቴሎቹ ውጋጆች ወደ ሀይቁ ይገባሉ፡፡በዚህ መንገድ እንደ ፎስፌትና ናይትሬት ያሉ በውሃው ላይ አረንጓዴ አረም ሊፈጥሩ የሚችሉ ንጥረ ነገሮችን ወደ ጣና ሀይቅን እንዲገቡ ያግዛል፡፡ ይህ ደግሞ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ እንደ አሳ ያሉትን ህይወት ያላቸው ነገሮችን በአጠቃላይ እና የጣና ሀይቅን ስነ-ምህዳር ለዘለቄታው ያዛባዋል (ደጄን እና ሌሎች 2004 )

የእንቦጭ አረም
አራተኛውና ሃይቁን በፍጥነት ወደ አለመኖር ስጋት ይወስደዋል ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ እያሰጋ ያለው የእንቦጭ አረም ነው፡፡ እንቦጭ ውሃማ አካልን ባጭር ጊዜ ውስጥ ይቆጣጠራል፤ የውሃ መሄጃ መንገዶችን ይዘጋል፣ በውሀ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ያውካል  (Mitchell 1976)፤ የውሃውን ንፅህና ያዛባል፣ በውሀ ውስጥ ያለውን የአየር መጠን ይቀንሳል፣ በውሃ ውስጥ ያሉ ህይወት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ያጠፋል  (Penfound & Earle 1948) ; እንቦጭ የውሃ ውስጥን ህይወታዊ እንቅስቃሴ  ሙሉበሙሉ ያውካል  (Gowanloch 1944):: 

በአጠቃላይ እንቦጭ በውሃ አካል ላይ በቀላሉ በመንሳፋፍ የሚራባ ሲሆን፡ መጠኑና ጥልቀቱ አነስተኛ በሆነ የውሃ አካል ደሞ ስሩን ከውሃው በታች ባለ ጭቃ ውስጥ በመስድድ ይራባል፣ እንዲሁም በርጥበታማና ረግረጋማ ቦታወችም ይራባል፡፡ ከ50-100ሴ.ሜ ድረስ የሚረዝም አካል ያለው ሲሆን በማንኛውም ሞቃታማ (ከ12-35 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ) ቦታዎች ባሉ የውሃ አካላት ላይ በፍጥነት የሚራባ መርዛማና አደገኛ አረም ነው፡፡ ከክረምት ይልቅ በጋ ለመራባት ይመቸዋል፡፡ ነገር ግን የሙቀት መጠኑ በጣም አንሰተኛ (ከ 1ሴንቲ ግሬድ በታች ) ከሆነ ሊራባ አይችልም፡፡

በጣም አሲዳማም እና በጣም አልካላይን በሆነ ውሃ በፍጥነት አይራባም ነገርግን የአሲድ መጣኑ ከ 6-7. የሆነ ከሆነ ግን በፍጥነት ይራባል፡፡ በመሆኑም የሚከተሉት ሁኔታዎች ከተሟሉለት (ሙቀቱ፣የአሲድ መጠኑ፡የውሃው ጥልቀት እና ለሰብል ተብለው የሚጨመር ማዳበርያ ታጥቦ ወደሀይቁ ከተጨመረለት) ከ6-15 ባሉት ቀናት ውስጥ በእጥፍ ይራባል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በአፈር መከላት ምክንያት ማዳበሪያ በሰፊው ከሚጠቀመው የሃገራችን አርሶ አደር ማሳ ተከልቶ ወደ ጣና ሃይቅ የሚገባው ማዳበሪያ ያዘለ አፈር ለእምቦጭ አረም መራባት ምቹ ሁኔታን በመፍጠሩ ነው ችግሩ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው፡፡ እንቦጭ በራሱ መርዛማ ከመሆኑ ባሻገር በማንኛውም የዕፅዋት ቅጠል የሚገኙት “ስቶማታ” ተብለው የሚታወቁት ትንንሽ ቀዳዳዎች በዚህ አረም ላይ በበዛት ከመገኘታቸውም በላይ በመጠን ሰፋፊ በመሆናቸው የውሃው የትነት መጠን እጅግ በጣም ከፍተኛ እንዲሆን በማድረግ የውሃ መጠንን ለመቀነስና ለማድረቅ አቻ የሌለው መርዘኛ አረም ነው፡፡

የተፈጥሮ መገኛው ደቡብ አሜሪካ ብራዚል የሆነው እንቦጭ አረም በጣና ላይ የተከሠተው በፈረንጆች አቆጣጠር በ2011 ሲሆን ይሄው አረም ቆቃን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ሐይቆች ውስጥ እንደነበረ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡ በ2014 እና 15 በጣና ሐይቅ ላይ በእንቦጭ ተሸፍኖ የነበረው የጣና ክፍል 20 ሺህ ሔክታር ቢሆንም በ2017 ወደ 24ሺህ ሔክታር ከፍ ብሏል፡፡
እምቦጭ 50 በመቶ የሚሆነውን የሐይቁን ጠርዝ ወሮታል፡፡ እምቦጭ ወደ ጣና የገባው በመገጭ ወንዝ ጫፍ አካባቢ እንደሆነ ሲገመት በፎገራ በኩል ከሩዝ ምርት ጋር ሌሎች ሁለት መጥፎ አረሞች እንደገቡ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱ ሌሎች መጤ አረሞች “Azolla” እና “water lettuce” በመባል ይታወቃሉ(ደሴ እና ሌሎች፣ 2014)

በውሃማ አካላት ላይ ሲታይ በአጥፊነቱ  የሚታወቀው እምቦጭ አረም በርካታ ጥቅምም እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ አውስትራሊያ፤ ኔፓልና ሌሎች ሃገራት ቅጠሉን እንደ ጎመን በመቀቅል ለምግብነት እየተጠቀሙበት የሚገኙ ቢሆንም  በእኛ ሃገር  በቀጥታ ለምግብ ፍጆታነት  ከመጠቀማችን በፊት በኛ ደረጃ የሀገራችን የምግብ ሳይንስ ባለሙያዎች ጥናት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ እምቦጭ የመዳህኒትነት ግልጋሎት እንዳለው፤ የቅጠሉን ቀንበጥ በትንበሹ በመብላት ከተቅማጥ እና ከትኩሳት ህመም ራስን መከላከል እንደሚቻለ በሌላ በርካታ ሃገራት የተሰሩ ጥናቶች ቢጠቁሙም በኛ ሃገርም ለጠቀሜታ ከመዋሉ በፊት ባለሙያዎች አስፈላጊዎን ጥናት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የከብት ፍግ ፣ አመድ ከእንቦጭ ጋር ተደባልቆ አጅግ በጣም የተዋጣለት የአፈር ማዳበርያ ኮምፖሰት በማምረት ቻይናዎች እየጠቀሙበት ይገኛል፡፡ በተጨማሪም አረንጉዋዴውን ቅጠል አፈር ላይ በመነስነስና በማልበስ የአፈርን ለምነትና እርጥበት መጠበቅ ይቻላል፡፡ እንዲሁም የአረሙን ሙሉ አካል በማድረቅና በመቆራረጥ ከአፈር ጋር በመደባለቅ ለማዳበርያነት መገልግል ይቻላል፡፡  የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ፡ ለማገዶነትና የተበከለ ውሃን ለማጣራት  እምቦጭ ፍቱን መዳህኒት እንደሆነ በሌሎች ሃገራት  ተረጋግጧል፡፡ የአረሙ ስር በካይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን (ሊድ፣ ሜርኩሪ፣አርሲኒክ…) ኦርጋኒኪ ዉህዶቸን  ያጣራል :: በኢነዶኒዠያ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ በጥንቃቄ የደረቀውን የአረሙ አካል ለጌጣጌጥ፤ ለሴቶቸ የእጅ ቦርሳ፤  ለነጠላ ጫማ ና ለኮፍያ መስርያ ይጠቀሙበታለ፡፡ ሥለሆነም እንቦጭ ከሚያሰከትለው ጥፋት ባሻገር ከላይ የተገለጹት ጥቅሞች ሥላሉት  ይህንንም ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ውቡን ሐይቃችንን ታድገን ከአረሙ ቱርፋቶችም ለመጠቀሙ ዘላቂ መፍት መዘጋጀት የኖርብናል፡፡

 

 

Advertisements

ሆድ ያባውን ቻርተር ያወጣዋል

በሃገራችን መንግስዊ ስልጣን ላይ መሰየሙ ለኢህአዴግ ከሰጠው ጥቅም አንዱ የፈለገውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለእርሱ የፖለቲካ ትርፍ የሚጠቅመው በመሰለው ወቅት እና ሁኔታ አንስቶ ወደ ጠረጴዛ ማምጣቱ ነው፡፡ አለቅነቱ ያመጣለትን በጎ ሁኔታ በመጠቀም ኢህአዴግ እሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ወደ መረሳት በተጠጋ መልኩ ሲያድበሰብሰው የኖረውን ለኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የተሰጠ ህገ-መንግስታዊ መብት ጉዳይ ዛሬ ትኩስ አድርጎ እነሳው  ይገኛል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖረው ይገባል ተብሎ በህገ-መንግስት የተሰጠውን መብት አፈፃፀም አስመልክቶ መንግስት ያወጣውን ረቂቅ አዋጅ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ዶክመንቱ በመንግስት ይፋ ከመደረጉ በፊት ጉዳዩን አስመልክቶ ማን እንዳወጣው ያልታወቀ ዝርዝር አንቀፆችን የያዘ ሰነድ በተለያዩ ድህረገፆች ተለቆ፣ በሰፊው ተነቦ፣ እጅግ ሲያነጋገር ሰንብቶ ነበር፡፡ ዶክመንቱ በተለይ በውጭ ሃገር የከተሙ የኦሮሞ ምሁራንን ቀልብ የሳበ የመነጋገሪ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል፡፡

“ኢህአዴግ መራሹ የሃገራችን መንግስት ለእሩብ ምዕተ አመት ዝም ብሎት የቆየውን አጀንዳ ዛሬ ለምን ማንሳት ፈለገ?” የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እርግጠኛውን መልስ የሚያውቀው መንግስት ራሱ ቢሆንም መላምቶችን መሰንዘር ግን ይቻላል፡፡ መንግስት የአዲስ አበባ መስተዳድርን ከኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች ጋር አቀናጅቶ ለማልማት የሚያስችል እቅድ አውጥቼ ተግባራዊ አደርጋለሁ በማለቱ ባለፈው አመት ከኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው “በቃ ትቼዋለሁ” ማለቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከሚታወቅበት ማድረግ የፈለገውን ሳይደርግ እንቅልፍ ያለመተኛት ባህሪው አንፀር ነገሩን በአፉ እንዳወራው እርግፍ አድርጎ ይተወዋል ማለት ያስቸግራል፡፡ እናም ከአንድ አመት በኋላ ይህን ዶክመንት ይፋ ማድረጉ፣ በዶክመንቱ ውስጥ የተዘረዘሩ ሃሳቦች የኦሮሚያ አጎራባች ዞኖችን ከአዲስ አበባ ጋር በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ለማቆራኘት የታለሙ አንቀፆች ከመኖራቸው፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ወሰን አሁንም በቁርጥ ያልተቀመጠ ከመሆኑ፣ የአዲስ አበባ አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሬቱ ለልማት ከተፈለገ ካሳ ይከፈላቸዋል እንጅ መነሳታቸው አይቀርም ከሚለው የአዋጁ ክፍል ጋር ሲጣመር የአፈፃፀም አዋጁ ለረዥም ወራት ተቆጥቶ የነበረው የክልሉ ህዝብ ከአንድ አመት ገዘፍ ያለ እስር፣ እጎራና እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካመጠው ድንጋጤ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያለውን ስሜት ለመለካት ያለመ ትልቅ የግመታ ተልዕኮ ያነገበ ይመስላል፡፡

ሌላው መላምት አቶ ጌታቸው ረዳ ‘እሳት እና ጭድ የሆኑ ቡድኖች አንድነት ያሳዩት እኛ ስራችንን ስላልሰራን ነው’ ካሉት ንግግር ጋር ይቆራኛል፡፡ ከአመት በፊት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ባልተለመደ ሁኔታ የትብብር ዝንባሌ ማሳየታቸውን ኢህአዴግ በበጎ ጎኑ እንዳልተመለከተው፣ ይልቅስ የመንግስቱ ድክመት ያመጣው ክፉ ውጤት አድርጎ እንዳሰበው የአቶ ጌታቸው ንግግር ምስክር ነው፡፡ በዚህ ግንዛቤ ውስጥ የከረመው  የኢህአዴግ መንግስት ታዲያ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” የምትል  ከዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ጋር ክፉ ፀብ ያላት ሃረግ ያዘለ አዋጅ አስነግሯል፡፡

“ልዩ ጥቅም”  የሚለው ቃል “Privilege” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ይወክላል፡፡ ይህ ቃል ደግሞ የዲሞክራሲ ዋና ከሆነው የዜጎች እኩልነት መርህ ጋር በእጅጉ ይጣላል፡፡ዲሞክራሲ በሰፈነበትም ሆነ ወደ ዲሞክራሲ እያመራ ባለ  ሃገር የአንድ ወገን ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር ማንሳት ወደ ሰሜን ለመሄድ ተነስቶ ወደ ደቡብ እንደ መንጎድ ያለ አልተገናኝቶ ነገር ነው፡፡ ለኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የሚያስገኘው  አዋጅ መነሾ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ነው ሲባል “የህገ-መንግስቱ ምንጭስ ማን ነው?” ወደ ሚለው ወሳኝ ጥያቄ ይመራል፡፡

ለህገ-መንግስቱ እርሾ የሆነው የሽግግር ዘመኑ ቻርተር በሻዕብያ፣ በህወሃት እና በኦነግ ለተፈጠሩበት አላማ እንዲያገለግል ሆነኖ ተቦክቶ ተሰልቆ ካለቀ በኋላ፤ ሰፍቶ ተስፋፍቶ ህገመንግስት ይሆን ዘንድ በህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽኑ በኩል ለህዝብ ውይይት ይቅረብ የተባለው እንደው ለቡራኬ ያህል ብቻ እንደሆነ በወቅቱ የነበሩ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ያሉ ፖለቲከኞች ይመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡ ህወሃት ኦነግ እና ሻዕብያ የሽግግር ዘመኑ አድራጊ ፈጣሪዎች እንደመሆናቸው ህገ-መንግስቱን ባዋለደው በዚህ ወሳኝ ወቅት እነዚህ “ሶስቱ ኃያላን” ያልወደዱት አካል ለምሳሌ የአማራው ብሄር እና የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት አቀንቃኝ ዜጎች ሃሳብ፣ እምነት እና ፍላጎት በቅጡ አልተወከለም፡፡ ስለዚህ የህገ-መንግስቱ አረቃቅም ሆነ ኢትዮጵያ ከሽግግር መንግስት ወደ ተመራጭ መንግስት ተዘዋወረች የተባለበት ሂደት የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ የወከለ አካሄድ አልነበረም፡፡ ይህን የሂደቱ  ዋና ተዋናይ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶም ደግመው ደገግመው የሚመሰክሩት ብቻ ሳይሆን የሂደቱ አካል “በመሆኔም እፀፀታለሁ” ያሉበት ነው፡፡

ህገ-መንግስቱ የረቀቀበት መንገድ እንዲህ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ቢሆንም ኢህዴግ ስህተት እንደሌለው መለኮታዊ መዝገብ ቆጥሮት የህገ-መንግስቱን ስም ስንቅ አድርጎ ወሳኝ የፖለቲካ ቁማሮችን በአሸናፊነት ይወጣበታል፡፡ ራሱን ህጋዊ ባላንጦቹን ህገ-ወጥ አድርጎ ህግን በመናድ ከሶ ዘብጥያ ያወርድበታል፡፡ ያሰበውን ለማድረግ እንደ እጁ መዳፍ በሚያውቀው ህገ-መንግስት የተፃፈውን መጥቀስ ቀርቶ ከዛም በላይ የሚሄደው ኢህአዴግ በዚህ አዋጅም ያየነው የተለመደውን ማንነቱን ነውና እግዚኦ የሚያስብል ነገር የለውም፡፡ የሚገርመው ነገር ያለው ሌላ ቦታ ነው- በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች መንደር፡፡

ከስራው አንድ አፍታ የማይዘናጋው፣ የሚያተርፍበት የመሰለውን የፖለቲካ ቁማር አጥብቆ በመያዝ የሚታወቀው ኢህአዴግ ለኦሮሚያ ክልል ከሃያ አምስት አመት በፊት የማለላትን በአዲስ አበባ ላይ  የልዩ መብት ባለቤት የመሆን ቃል ለመፈፀም አዋጅ አውጥቻለሁ ሲል በገራገርነት ቃሉን ለማክበር አስቦ ብቻ አይመስልም፡፡እንደሚታወቀው መንግስት ይህን ረቂቅ አዋጅ ያወጣው ፓርላማው ለእረፍት በሚዘጋበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በአዋጁ ዙሪያ ከህዝቡ የሚነሱ አስተያቶችን፣ የፖለቲከኞችን አሰላለፍ በማጤን ራሱን የፖለቲካ ትርፍ በሚያጋብስበት መስመር ለማሰለፍ ነገሮችን የማጤኛ ጊዜ ለማግኘት ይመስለኛል፡፡ይህን ይበልጥ የሚያስረዳው አቶ ለማ መገርሳ ደግመው ደጋግመው አዋጁ ለውይይት ክፍት ነው እንጅ ያለቀለት አይደለም ሲሉ መሰንበታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም መንግስት በቴሌቭዥኑ የአፈፃፀም አዋጁን ከማወጁ በፊት ቀደም ብሎ ባለቤቱ ያልታወቀ ዶክመንት በማህበረዊ ድህረገጾች እንዲከላወስ ሲደረግ፣ብዙ ሲያነጋግር መንግስት አለሁበትም የለሁበትምም ሳይል ድምጹን አጥፍቶ የነገሮችን አካሄድ ሲከታተል ሰነበተ፡፡ከርሞ ከርሞ በቴሌቭዥኑ ያስነገረው አዋጅ የወጣበት ጊዜም እንዲሁ በድንገት የተደረገ አይመስለኝም፡፡  በዚሁ ጊዜ ትቂት የማይባሉ የኦሮሞ ብሄር ፖለቲከኞች ሰተት ብለው ወደ ወጥመዱ ውስጥ ሲገቡ በሰነዱ ውስጥ እጅግ የተገለለው፣እንደሌላ ሊቆጠር ምንም ያልቀረው የኢትዮጵያ ብሄርተኝት አቀንቃኙ አካል ዝምታን መርጦ ከኢህአዴግ ጋር ካብ ለካብ መተያየቱን መረጠ፡፡አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አራማጆች ብቻ ሳይሆን ምሁራን ጭምር ባለቤቱ እንኳን በውል ባልታወቀ ሰነድ ዙሪያ አስደንጋጭ የክርክር ነጥቦች ያዘሉ ረዣዥ ክርክሮች አምጥተው ራሳቸውን ለግምት አደባባይ አሰጡ፡፡ምሁራን ተብየዎቹ በመገናኛ ብዙሃን(በኦ.ኤም.ኤን እና በቪኦኤ) ቀርበው ሲወያዩ በጆሮየ የሰማኋቸውን እና የገረሙኝን ብቻ ላንሳ፡፡

“የባለቤትነት” እና “የልዪ ጥቅም” እሳቤዎች ንትርክ

ባለቤቱ ያልታወቀው ሰነድ የአዲስ አበባ አደባባዮችን ለመጠቀም ሳይቀር የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በአዲስ አበባ ለሚጠይቁትን ነገር ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል በሚሉ አንቀጾች ተሞላውን ሰነድ እየጠቀሱ ይህ እጅግ ትንሽ ነገር እንደሆነ እና በአዲስ አበባ ላይ ባለቤት የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ እንደ እንግዳ ቆጥሮ በገዛ ቤቱ ሊያስተናግድ እንደሞከረ ደፋር እንግዳ ቆጥረው አብጠልጥለውታል፡፡መሆን ያለበትን ሲያወሱም ከዶክመንቱ ስያሜ ጀምሮ መሆን ያለበት የባለቤትነት አዋጅ እንጅ የልዩ ጥቅም አዋጅ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ተከራካሪዎቹ ሲያክሉም በአዲስ አበባ የሚኖር ማንኛውም ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የሆነ ተቋምም ሆነ ሌላ አካል የሚኖረው በኦሮሚያ ምድር መሆኑን እንዲያስታውስ፣ትንሽም ብትሆን አመታዊ ግብር ለኦሮሚያ ክልል መክፈል አለበት፣ ቀረጥ እና ግብር በሚከፈልባቸው የጉምሩክ ጣቢዎች ላይም በርከት ያሉ ኦሮሞ ተወላጆች ሊታዩ ያስፈልጋል፣ አዲስ አበባ ራሷም መተዳደር ያለባት በኦሮሚያ ክልል ስር እንጅ በፌደራል መንግስቱ ስር መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ሌላው አስገራሚም አስቂኝም የሆነው የክርክር ነጥብ ጭብጥ ደግሞ ይህን ይላል፤ ‘አሁን አዲስ አበባ የሚኖረው አብዛኛው ሰው የከተሜነት ዲሲፕሊን የሚያንሰው፣በሌሎች ዓለማት ያሉ የከተማ ነዋሪዎች የተላበሱት ትህትና የሚጎድለው፤ ለኦሮሞ ባህል እና ማንነት ክብር ለማሳየት የሚለግም ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ መስተካከል አለበት፡፡በአዲስ አበባ መኖር የሚቻለው ባለቤቱን የኦሮሞ ህዝብ እስካበሩ ብቻ ነው፡፡ ይህን እስካደረገ ድረስ መኖር ይችላል ካልሆነ ግን አዲስ አበባን ለባለቤቶቿ ለቆ ሌላ ሰፊ ቦታ ፈልጎ አዲስ ዋና ከተማ መመስረት ነው፤አዲስ ሚመሰረተውን ዋና ከተማ ኦሮሚያ ላይ ማድረግም ይቻላል፡፡’ ይሄ ኦነግን አደቁኖ ካቀሰሰው ‘የውጡልኝ ከሃገሬ’ ፖለቲካዊ ፈሊጥ የተቀዳ ነው፡፡ ወንድም ህዝብን ማግለልን እንደ ፖለቲካ ስኬት ዳርቻ የሚቆጥረው የኦነግ መናኛ ፖለቲካዊ አካሄድ ፓርቲውን እድሜ ብቻ አድርጎት እንደቀረ ተረድቶ ራመድ ማለት ፖለቲካዊ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ኦነግ እንኳን ብሎት ብሎት አልሆን ሲለው የተወውን ውራጅ ፖለቲካ ትርክት አንግቦ መንገታገት ራስን የፖለቲካ ማስፈራሪያ ከማድረግ፤ ቆምኩለት የሚሉትን ህዝብም በጥርጣሬ ከማሳየት ያለፈ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡

የዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ‘አዲስ አበባ የኦሮሞ ህዝብ የብቻ ታሪካዊ እርስት ነች’ የሚለውን አስገራሚ እሳቤ ብንቀበል እንኳን ቀደምት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው የተባሉት ኦሮሞዎች መኖሪያ የነበረችው አዲስ አበባ እና የአሁኗ አዲስ አበባ የተለየች መሆኗን ማገናዘብ ይህን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ከባዱ ነገር ከላይ ባሉት ተከራካሪዎች መጤ ይሁን ሰፋሪ እየተባሉ ያሉት ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ላባቸውንም እድሜያቸውንም ጨርሰው ያቀኗትን አዲስ አበባን ጥለው ወደ መድረሻቸው ይድረሱ፤ ወይም ሌላ ረባዳ መሬት ፈልገው የሃገራቸውን ዋና ከተማ ይመስርቱ የሚለው ሃሳብ  ይሰምርልኛል ብሎ ወደ አደባባይ ይዞ መቅረቡ ነው፡፡ከሰሞኑ በቪኦኤ ቀርበው የሚከራከሩ ዶ/ር ኃ/መስቀል የተባሉ ሌላ የኦሮሞ ምሁር ደግሞ ሌላ ክርክር ያመጣሉ፡፡ ሰውየው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሃረርም፣ በድሬዳዋም፣በሞያሌም ላይ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሊከበርላት ይገባል ሲሉ በህገ-መንግስቱም ያልተጠቀሰ ሰፋ ያለ ፍላጎት ያለው ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የሰውየው ክርክር መነሾው እነዚህ ከተሞች ኦሮሚያ ክልል መሃል ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡ ሐምሌ 8/2009 ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቃል-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ነጋሶ ሃረርም በኦሮሚያ መሃከል ስለምትገኝ በሚል ኦነግ በሽግግሩ ወቅት የኦሮሚያ ክልል በከተማዋ ላይ ልዩ መብት  እንዲኖረው ጥያቄ አቅርቦ ምክንያቱን በማላውቀው ነገር ህገመንግስቱ ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል ይላሉ፡፡፣

ከላይ የተነሱት የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች እና ምሁራን  የክርክር ነጥቦች ሲጠቃለሉ አሁን ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላትን መብት የባለቤትነት እንጅ የልዩ ጥቅም ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡የኦሮሚያን ህገመንግስታዊ ልዩ መብት ለመተግበር ወጣ የተባለው ረቂቅ አዋጅም መቃኘት ያለበት ከዚሁ አንፃር ነው የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተቃራው የቆመው፤ የአዲስ አበባ ነዋሪም  ሆነ ከተማዋን እንደ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አንድያ መገለጫ ምድር አድርጎ የሚያስበው ዜጋ ይህን የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞችን እና ምሁራን ክርክር ትዝብትም፣ጥርጣሬም፣ድንጋጤም ባጠላበት ዝምታ ነው ያስተዋለው፡፡እንደውም ከነዚህ አይነት የኦሮሞ ብሄርተኞች ይልቅ ቢያስ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአዲስ አበባ እንዲኖር የፈቀደው ኢህአዴግ እጅግ የተሻለ እንደሆነ ቢታሰብ የሚገርም ነገር የለውም፡፡ የኢህአዴግ እቅድም ይኽው ነው – ለመገመት የተዘጋጀን ማስገመት፤ በዚህ ውስጥ ራሱን የተሻለ መድህን አድርጎ ማሳየት! ሲቀጥልም ለአንድ ሰሞን ሲሰማ የነበረውን የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦችን የትብብር ድምፅ በነዚህ የኦሮሞ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ድምፅ በመተካት ሃያ አምስት አመት ሲሰበክ የኖረውን የጥርጣሬ እና የመፈራራት መንፈስ መልሶ በቦታው እንዲተካ ማድረግ ነው፡፡አቶ ጌታቸው ረዳ ኢህአዴግ ቸል አለው ያሉት የቤት ስራም ይሄው ሳይሆን አይቀርም፡፡

አንድም አፍታ ከስራው መዘናጋትን የማያውቀው ኢህአዴግ ይህን ቻርተር ይዞ ብቅ ሲል የኦሮሞ ምሁራንም ቻርተሩ ይስመር አይስመር እንኳን በውል ሳያጤኑ ሆዳቸው ያባውን ሁሉ ትዝብትን ሳይፈሩ አውጥውታል፡፡ ጭራሽ የኦሮሞ ህዝብ አንድ አመት ሙሉ ሲሞትለት የኖረው ጥያቄ አዲስ አበባን በባለቤትነት የማስተዳደር ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ለማድረግም ይቃጣዋል ክርክራቸው፡፡ባለፈው አመት የኦሮሞ ህዝብ አምርሮ ሲያነሳው የኖረው አንገብጋቢ ጥያቄ ከኖረበት ቀየው በድንገት ባዶ እጁን ወይም እፍኝ በማትሞላ ካሳ መፈናቀሉን በመቃወም እንጅ  አዲስ አበባን ለኦሮሞ ቤት ለሌላው የሰው ቤት ለማድረግ አልነበረም፡፡የልሂቃኑ ክርክር እና የአገሬው ኦሮሞ ችግር እና ፍላጎት ይህን ያህል አልተገናኝቶ መሆኑ ግር ያሰኛል፡፡ከሃገር ርቀው እንደመኖራቸው  ሃገርቤት ያለውን ኦሮሞ መሰረታዊ ጥያቄ ለማወቅ ይቸገራሉ ቢባል እንኳን ቆምኩለት ከሚሉት” ህዝብ  የልብ ርትታ እንዲህ እጅግ መራራቁ ጤናማ አይመስልም፡፡

አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ፖለቲከኞች ደጋግመው የሚያነሱት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ይገባል የሚሉት የባለቤትነት መብት ጥያቄ ማስረጃ አድርገው የሚያነሷቸው ነጥቦች ወደ ሶስት ማጠቃለል ይቻላል፡፡ አንደኛው እና ለተቀሩት መከራከሪያ ነጥቦች መሰረት የሚሆነው ኦሮሞዎች የአዲስ አበባ ቀደምት ህዝቦች ናቸው የሚለው ትርክት ነው፡፡ለዚህ ትርክት ከማለት ባለፈ በበቂ ታሪካዊ መዛግብት የተደገፈ ማስረጃ ከተከራካሪዎች ሲቀርብ  አላጋጠመኝም፡፡ ይልቅስ ከዚህ እሳቤ በተቃራኒው የቆሙ ተከራካሪዎች የተሻለ የታሪክ ማስረጃ አቅርበው ይከራከራሉ፡፡ሁለተኛው የሃገራችን ህገ-መንግስት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ መብት እንዲኖራት ስለሚያዝ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ሶስተኛው የክርክሩ ማስረጃ አዲስ አበባ(ሐረር፣ድሬዳው፣ሞያሌ ጭምር የሚሉ ተከራካሪዎችም አሉ)በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ በመሆኗ ከኦሮሚያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን ስለምትጠቀም፣ከተማዋ ለውጋጆቿ መዳረሻም አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖችን ስለምትጠቀም ኦሮሚያ በከተማዋ ላይ ልዩ ጥቅም ያስፈልጋታል የሚል ነው፡፡ እነዚህ የክርክር ማስረጃዎች ተደርገው የቀረቡ እሳቤዎች ራሳቸው ሊጠየቁ የሚገቡ በመሆናቸው በሚቀጥለው እትም እመለስባቸዋለሁ፡፡

የጄነራል ፃድቃን መልሶ ልብ ማውለቅ….

ከዕለት ተዕለት ግላዊ የኑሮ ግብ ግብ አለፍ ብሎ ለህዝብ ነፃነት፣ የህይወት ለውጥ፣ መከራ ቅለት ሊታገሉ መነሳት ራመድ ያለ ማንነትን ይጠይቃል፡፡ ታግሎ ማሸነፍ ደግሞ የበለጠ ብርታት ይጠይቃል፡፡ ጀነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ የልጅነት ዘመናቸውን በጫካ የገፉ በመሆናቸው እንዲህ ካሉት ወገን ለመመደብ የሚችሉ ናቸው፡፡ ለህዝብ ነፃነት የልጅነት ጊዜን ሰውቶ በረሃ መገኘት ከበድ ያለ ስብዕና አካል ቢሆንም በረሃ መውረዱ፣ ጠመንጃ ዘቅዝቆ አቀበት ቁልቁለቱን መሮጡ በራሱ ውጤት ስላልሆነ በቂ ነገር አይደለምና ውጤቱ በምክንያት መመርመር አለበት፡፡

በረሃ የወረደ ሁሉ፤ ነፍጥ አንስቶ ባሩድ ያቦነነ ባጠቃላይ፤ “ታግየ ነፃ አወጣኋችሁ” ባይ ውለታ አስቆጣሪ በነሲብ፤ “ዘር አዝርቴ ሞቶ አቆማችሁ” ባይ ሃረግ መዛዥ በሞላ  “ከተዋጋ ዘንዳ እንደፈለገ ይሁን፣ ያሻውን ያጥፋ፤ ጥፋትም በጥፋት ላይ ይደራርብ” የሚባልበት ዘመን ከነበረም አልፏል፡፡ ያለንበት ጊዜ የምክንያታዊነት እንጂ የግዝት ዘመን አይደለም፡፡ ስለዚህ፣ ድርጊቱ ተመርምሮ መጠየቅ ያለበት ሁሉ በህግም፣ በህሊናም ይጠየቃል፡፡ በአንድ ወቅት ደደቢት በረሃ ወይ ደንቆሮ ዋሻ መገኘት የተጠያቂነት ድነሽነት (Immunity) አይደለምና ጀ/ል ፃድቃን እና ጓዶቻቸው ላጠፉትም ሆነ በጥፋታቸው ላይ እየደራረቡት ላለው ከቀደመው የባሰ ጥፋታቸው መጠየቅ አለባቸው፡፡

ደርግን መጣል የህግ ሁሉ ፍፃሜ፣ የትክክለኝነት ሁሉ ዳርቻ የሚመስላቸው ህወሃቶች በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያላቸው ግምት ራሳቸው ለራሳቸው ካላቸው ሚዛን ጋር በእጅጉ ይራራቃል፡፡ እነሱ ራሳቸውን የኢትዮጵያ መድህን፣ ምትክ አልቦ ክስተት፣ መታደስ እንጅ መቀየር የሌለባቸው ምጡቃን አድርገው ሲያስቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ለእነሱ ብቻ የሚታያቸውን ፍፅምናቸውን መሬት ላይ ፈልጎ ከማጣቱ የተነሳ ነገራቸው ሁሉ ታክቶታል፡፡ እነሱ የትም እንደ ማይሄዱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተናግረዋል፤ አለፍ ሲልም ጠመንጃቸው በትከሻቸው ነው፡፡ ህዝቡም መሄጃ ስለሌለው እንዳለ አለ፡፡ ህዝቡ በህወሃት/ኢህአዴግ ለሃገር የመቆም ልዕልና ላይ ተስፋ ከቆረጠባቸው ምክንያቶች አንዱ ትልቋን ሃገር ወደብ አልቦ ለማድረግ የሮጠበት የእብድ እሩጫ ነው፡፡ ወደብን ያክል ወሳኝ ነገር እንደ መርገም ‘ነገ ዛሬ ሳትሉ ከእጄ ላይ ውሰዱልኝ’ የሚል “አዋቂ” ከህወሃት ውጭ፣ ከአቶ መለስ ሌላ ከየት ምድር ተፈልጎ ይገኛል? ጄሌ ካድሬዎቹ ተናግረው የማይጠግቡለት የአቶ መለስ “እውቀት ጢቅነት” ኢትዮጵያን ለባህር እጅግ ቀርባ ወደብ አልቦ የሆነች የመጀመሪያዋ የጉድ ሃገር አድርጓታል፡፡

የዓለማችን ወደብ አልባ ሃገራት (ለምሳሌ ቻድ፣ ዩጋንዳ፣ ፓራጓይ፣ ሞንጎሊያ) ወደብ ወደማጣቱ ችግር የከተታቸው የሃገራቸው ጅኦ-ግራፊያዊ አቀማመጥ ከባህር እጅግ ርቀው ከመገኘታቸው የተነሳ ይህን እድል የሚነፍጋቸው በመሆኑ እንጅ “ነፃ አውጭዎቻቸው” ከወደዱት ጋር ፍቅር ለማፅናት በገፀ-በረከትነት ስላስረከቡባቸው አይደለም፡፡ እንደውም የእውነት የህዝብ መንግስት ያላቸው ሃገራት ድንበራቸው ለባህር ቅርብ ሳይሆን እንኳን እንደምንም ብለው ለባህር በር ባለቤትነት የሚያበቃ ኮሪደር ባለቤቶች ይሆናሉ (ለምሳሌ ኮንጎ)፡፡ የጉድ ሃገራችንን ብናይ ግን ለግመል ውሃ መጎንጫነት በታጨው አሰብ ወደብ በኩል ከባህር ያላት ርቀት አዲስ አበባ ከቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) የሚርቀውን ያህል ነው፡፡ ስለ ወደብ ጉዳይ ጮኽው የማይደክማቸው ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያም እንደውም ርቀቱን ‘የእግር መንገድ ያህል የቀረበ’  ይሉታል፡፡

የአሰብን ወደብ ለሃገራችን አስቀርቶም የጠናባቸውን የኤርትራ ፍቅርም አለማጣት ይቻል እንደነበር ለማሰብ ፅኑ ፍቅሩ የፈቀደላቸው ያልመሰለኝ አቶ መለስ እና ጓዶቻቸው ወደብ አስረክበው ያመጡብን ፈተና ከዚህ በመለስ የሚሉት እንዳልሆነ ከነባራዊው ህይወታችን በተጨማሪ የዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያምን “አሰብ የማናት?” የሚል መፅሃፍ ማንበብ ነው፡፡ የትልቁን ጉዳት ጥቂት ገፅታ ለማንሳት ያህል ወደብ የሌለው ሃገር ለዓለም አቀፉ ንግድ ያለው ቅርበት በሰው እጅ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ መርፌ ምላጭ ሳይቀር ከውጭ ለሚያስመጣ ድሃ ሃገር ሁለመናውን የሚያስገባው የሚያስወጣው በሰው ደጅ ነውና ጥብቅ ሚስጥራዊነት የሚሻው የፀጥታም እና የደህንነት ጉዳዮቹ ሁሉ አደባባይ የተሰጡ ናቸው፡፡ ልመና አኮፋዳ ይዘን፣ የሰው ደጅ ላይ ቆመን የምናገኘው የእርዳታ እህል ርሃብ ለሚቆላቸው ወገኖቻችን በጊዜ እንዲደርስ የራስ የሆነ ወደብ ይመረጣል፡፡ እንደ መድኃኒት ነፍስ አድን፣ እንደ ነዳጅ አጣዳፊ የሆኑ ፍጆታዎች እንደልብ ይመላለሱ ዘንድ ማን እንደራስ ወደብ! መንግስት ባለወደቡን ሃገር ካስቀየመ የአስመጭ ነጋዴዎች ንብረት ወደብ ላይ ቀልጦ ሊቀር የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የብዙ ነጋዴ ወገኖቻችን ንብረት ቀልጦ እንደቀረ ይነገራል)፡፡

ከሁሉ በላይ ለወደብ ኪራይ የሚወጣ ገንዘብ እኛን ጎስቋሎችን ቀርቶ የባለፀጋ ሃገሮችን ወገብም የሚቆርጥ ነው፡፡ አወቅኩ ባዮቹ መለስ ዜናዊ እና ጓደኞቹ እንደሚያስቡት ወደብ ገንዘብ ስላለ ብቻ እንደ በቆሎ እና ገብስ በደረሱበት የሚያፍሱት ወይ ደግሞ ከሆነ ዘመን በኋላ ትዝ ሲል ሄደው ‘አሁን የወደብ ባለቤት መሆን አለብኝ’ ብለው አፈፍ የሚያደርጉት ጥይት እንደመግዛት ያለ ርካሽ ነገር አይደለም፡፡ ረብጣ ገንዘብ ተከፍሎም እንኳን በዲፕሎማሲው መስክ ባለወደብ ሃገራትን ማባበልን፣ መለማመጥን ይጠይቃል፡፡ ያለአባት በሆነ ሁኔታ ደረጃችንን አውርዶ ጅቡቲን የሚያለማምጠን ይሄው ነው፡፡ ወደብ ማግኘት ቀላል እንደሆነ ሲናገር የነበረውን መለስ ዜናዊን ላሙ ኮሪደርን ለመገንባት ዙሪያ ጥምጥም ያባዝነው የነበረው ወደብ  እሱ ከጫካ እንደመጣ እንዳሰበው በዋዛ የሚገኝ ነገር ባለመሆኑ ነው፡፡ የሰራውን የሚያውቀው ህወሃት/ኢህአዴግ ለወደብ ኪራይ ስንት እንደሚከፍል በግልፅ ተናግሮ ባያውቅም አመታዊ ወጭው እጅን በአፍ የሚያስጭን እንደሆነ (ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል) ማንም አይጠፋውም፡፡ ይህን ለወደብ የምናወጣውን ወጭ በየትኛው የወጭ ንግድ ምርታችን በምናገኘው ዶላር እንደምናካክሰው   ወደባችንን መርቆ ያስረከበውን አካል የሚያስጨንቅም አይመስለኝ፡፡

ህወሃት ከጫካው ድል መልስ ኤርትራን ካላስገነጠለ እንቅልፍ በአይኑ እንደማይዞር ‘ኤርትራን እንደመንግስት እወቁልኝ’ ከሚለው ጭቅጨቃው የተረዱት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጂሚ ካርተርም ሆኑ  የአፍሪካ ጉዳይ አማካሪያቸው ኽርማን ኮህን ‘እባካችሁ ሃገሪቱን ወደብ አልባ የማድረጉን ነገር ደጋግማችሁ አስቡት’ ብለዋቸው እንደ ነበር ወቅቱን አስመልክቶ የተፃፉ መዛግብትም ያልሞቱት ኽርማን ኮህንም ምስክር ናቸው፡፡ የራሳቸው የኢኮኖሚክስ ህግ ያላቸው አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበራቸው መልስ ‘ወደብ ያለመኖር በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የለውም’ የሚል እብሪት አይኑን የጨፈነው ነበር፡፡ እሺ የኢኮኖሚው ይቅርና በሃገር ደህንነት ላይ ያለው ተፅዕኖስ ምንድን ነው ተብሎ ታስቦ ይሆን?

በወቅቱ ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ዛሬ መልሰው ልብ የሚያደርቅ ክርክር እያመጡ ካሉት ከጄነራል ፃድቃን እና ከሜ/ጄነራል አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) የሚቀድም ሰው መኖር አልነበረበትም፡፡ እውነታው ግን እነዚህ ዛሬ ሆድ ሲያውቅ በሆነ ሁኔታ ደርሰው ለወደብ ደረት ደቂ የሆኑ ሰዎችም ከአቶ መለስ የተለየ ነገር እንደሌላቸው ነው፡፡ ነበረን ቢሉ እንኳን ዛሬ ላይ ይሄን ቢያወሩ ማሞ ቂሎን ካልሆነ ማንንም ሊያሳምኑ አይችሉም፡፡ አቶ መለስ በዚህም አያበቁም የአሰብን ጉዳይ የሚያነሳ ሰው ‘የሃገር ሉአላዊነት የማይገባው ተስፋፊ ነውና ብቻውን እንደሚያወራ ይቆጠራል’ ይሉ ነበር፡፡

እውነት ለመናገር አቶ መለስም ሆኑ ጓዶቻቸው ወደቡን መርቀው ያስረከቡት  ጆቤ በቅርቡ (ለእኔ ቀልድ በመሰለኝ ሁኔታ) እንዳሉት የወደብ ጥቅም እጅግም ስለማይገባቸው ሳይሆን እንዲገባቸው ስላልፈለጉ ነው፡፡ ከህዎሃቶች ብዙ አደናጋሪ ባህሪያት በጣም የሚገርመኝ መልሰው መላልሰው ራሳቸውን ብቻ ማዳመጥ የሚወዱበት ይሉኝታ የራቀው ልማድ ነው፡፡ እነሱ የፈለጉት፣ እንዲሆን የወደዱት ነገር ሁሉ ለሌላው ሰውም ትርጉም የሚሰጥ/መስጠት የሚገባው እውነት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ያሰቡትን አስተሳሰብ ስሁትት እየተነገራቸውም ጆሮው ላይ ሄድፎን ሰክቶ እንደሚዘል ዲጄ በዛው ሙዚቃ ይደንሳሉ እንጂ የሰውም ሃሳብ ለመስማት ጆሯቸውን ሳያዘነብሉ ጎልማሶቹ አረጁ፤ ያረጁት ባሰባቸው፡፡ ይሄ አንድም ለእውቀት ርቆ መቆም ሁለትም ሰው ንቀት ሶስትም “መተኮስ ደጉ” ያመጣው ማናለብኝነት ነው፡፡

ሰሞኑን ጄ/ፃድቃን ፍፁም ብርሃነ ከተባለ ጋዜጠኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃገራችን በቀይ ባህር አካባቢ የነበራትን ህልውና መልሳ ማምጣት አለባት ብለዋል፡፡ ቀጥተኛ፣ ቅን እና የሰውን ግንዛቤ ዝቅ ባላደረገ መንገድ መልስ እንደሚሰጡኝ ተስፋ በማድረግ በዚህ ንግግራቸው ዙሪያ  እና  አጋጣሚውን በመጠቀም ስለ በእርሳቸው እና የ1993 ስንጥቃት ጓዶቻቸው ዙሪያ ያሉኝን አንዳንድ ጥያቄዎች ላንሳ፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄየ እናት ድርጅትዎ ህወሃት ኤርትራን ነፃ ማውጣትን ከትግል ግቦቹ እንደ አንዱ አድርጎ አንግቦ አስራ ሰባት አመት ተዋግቶ፣ ኤርትራ ቀይ ባህርንም ጠቅልላ ነፃ ሃገር ከሆነች ሃያ ስድስት ክረምት እና በጋ ካለፈ በኋላ ዛሬ ብድግ አድርጎ በቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ጠንካራ ህልውና ያስመኘዎት ምን ጥብቅ ጉዳይ ቢገጥምዎ ነው?

ሁለተኛ ቀይ ባህር የሚገኘው ኤርትራን አልፎ እንደሆነ መቼም አያጡትም፡፡ እናት ፓርቲዎ ህወሃት የኤርትራን ሉዓላዊነት መንካት ቀድሞ የሚያጣላው ከእኔው ጋር ነው እያለ  ሲያስፈራራ እንደኖረም ለእርስዎ አይነገርም፡፡ ከሌላ ጥቃት የሚጠብቀውን የኤርትራን ሉአላዊነት ራሱ አይነካውምና ኤርትራን ሳይነኩ በቀይ ባህርን ዙሪያ የኢትዮያን ጠንካራ ህልውና መመስረቱ እንዴት ይሆናል ብለው አሰቡ?

ሶስተኛ የኤርትራ ግዛት እንዳልሆነ በደንብ የሚታወቀውን፣ በደርግ ዘመንም በኤርትራ ውስጥ ሳይሆን በራሱ ራስ ገዝ በሆነ አስተዳደር ሲተዳደር የነበረውን አሰብ ወደብ ያለበትን ክልል የኤርትራ ነው ብሎ የመስጠቱ፣ ቀይ ባህርም ሆነ ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት ሆነው አይውቁም የሚለው ህወሃት  አካል የነበሩ እንደመሆንዎ መጠን ዛሬ በጣም ከረፈደ በኋላ ቀይ ባህርን ለኢትዮጵያ ለመመኘት ሌላው ቢቀር ከሞራል አንፃር ተገቢው ሰው ነኝ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ንግግሬን ይቀበልና ያምነኛ ከዚህ ሃሳብ ጎን ቆሞም ለስምረቱ ይሰራል ብለው ያስባሉ?

አራተኛኤርትራ ከተገነጠለች ብዙ አመታትን ማስቆጠሯ ከፊትዎ የተሰዎረ ነገር አይደለም፡፡ ሃገሪቱ የምትገኝበት ጅኦፖለቲካዊ አቀማመጥ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የአረብ ሃገራትተን ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም በላይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ኢራን፣ ሳውዲ፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ እና ኳታር የበላይ ተቆጣጣሪነታቸውን ለማስረገጥ  የሚሻኮቱበት ቀጠና እንደሆነም አይጠፋዎትም፡፡ ኤርትራ ከአመት በፊት አሰብን ለተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ እና ለሳኡዲ በኪራይ እንደሰጠች ባለማወቅም አልጠረጥርዎትም፡፡ ከነዚህ ሃገራት አንፃራዊ ባለጠግነት፣ ሃያልነት እና የረዥም ዘመን ቀይ ባህርን ከኢትዮጵያ ነጥቆ የአረብ ሃይቅ የማድረግ ምኞት አኳያ እርስዎ የሚናገሩለት የኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ተመልሶ የመጠናከር ህልም እንዴት ስኬታማ ይሆናል ብለው ነው ይህን ሃሳብ ያመጡት?

አምስተኛ የሚያወሩለት የሃገራችን ተመልሶ በቀይባህር አካባቢ የመጠናከር ጉዳይ የሚከናወነው ለኤርትራ ጥብቅና በመቆም ይታወቅ በነበረው፣ ከሻዕብያ ጋር ለነፍስ እየተፈላለግኩ ነው እያለ ሳይቀር የኤርትራን የነፃነት ቀን ደግሶ በሚያከብረው፣ የወደብ አልቦነት ችግሩን ሁሉ በፈጠረው፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ዳርቻ እንድታፈገፍግና የአለም አቀፍ ፖለቲካዊ ተፈላጊነቷ እንዲሞት ያደረገው የእርስዎ ፓርቲ ህወሃት/ኢህአዴግ መሪነት ነው ወይስ በሌላ መንገድ? በህወሃት አጋፋሪነት ከሆነ የባድመውን መጨረሻ ያየው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ተመልሶ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ የሚማገድ ነው ብለው ያስባሉ?

በመጨረሻም ከላይ ካሉት ጥያቄዎቼ ለየት ያለ ነገር ላንሳ፡፡ እንደሚታወቀው ህወሃት/ ኢህአዴግ የምር የተጣላቸውን የቀድሞ ጓዶቹን ምን እንደሚያደርግ ከታምራት ላይኔ እስከ መላኩ ፋንታ፤ ከአቶ አንዳርጋቼው ፅጌ እስከ አቶ ኦኬሎ አኳይ ድረስ የደረሰባቸውን የምናውቀው ነው፡፡ እርስዎ እና የህወሃት ስንጥቃት ጓዶችዎ ግን ከህወሃት ጋር ከፉ የሚመስል ጠብ ተጣልታችሁም በሃገራችሁ እንደፈለጋችሁ እንድትወጡ እንድትገቡ እርስዎማ ጭራሽ ነግደው እንዲያተርፉ ሆነዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ለምን ይመስልዎታል? ለእርስዎ እና ለሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በተለይ የተደረገው የህወሃት ተፃራሪን የመታገስ ያልተለመደ ባህሪ ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ (ያለበት እንኳን በውል ለማይታወቀው) እና ሌሎች የኢህአዴግ የቀድሞ ጓዶች የአሁን ፀበኞች  ሲደገም ያልታየው እንዴት ነው? ይህን የምጠይቀው ለናንተ የዘነበው የህወሃት/ኢህአዴግ የምህረት ዝናብ ለሌሎች ወገኖችም እንዲያካፋ ከመመኘት በተነሳ ነው፡፡

በመጨረሻም በሰሞኑ ንግግርዎትን በተመለከተ በእርስዎ በኩል ያትን ነገሮች ጥያቄዎቼን ተንተርሰው ያስነብቡናል ብየ ተስፋ በማድረግ በራሴ በኩል የሚታዩኝን ነገሮች አንስቼ ላብቃ፡፡  እርስዎና ጓዶችዎ  ሌላውን ለጊዜው እንተወውና ቢያንስ ኢትዮጵያን በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ የባህር በር አልባ ሃገር በማድረጉ ጉልህ ስህተት የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ስራ መስራታችሁ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ ስህተት ማንም ይሳሳታል፡፡ እንዲህ እንደ ነጭ ፈረስ የጎላ ስህተት ግን እንደ እናንተ ፓርቲ በብልህነቱ ብዛት ደርግን መጣሉን መሽቶ እስኪነጋ ከሚተርክ፣ሁሉን አወቅ ነኝ ከሚል አካል የሚጠበቅ አይደለምና ለይቅርታ ይቸግራል፡፡ ይቅርታ መጣም አልመጣ ስህተትን ማመንም አንድ ነገር ቢሆንም ስህተትን ለማመን እና ለማረም እሩብ ምዕተ አመት መጠበቅም እንዲሁ የቅንነት አይደለምና ተቀባይነቱ የማይታሰብ ነው፡፡ በተለይ አሁን በሚያነሱት ጉዳይና ባነሱበት የጊዜ ሁኔታ የሃሳቡን ቅንነት ለመቀበል ይቸግራል፡፡ ያጠፋሰው (ያውም እንዲህ ከይቅርታ በላይ የሆነ ጥፋት) ያጠፋው ጥፋት ከይቅርታም፣ ከእርምትም ድንበር አልፎ እንደማይሆን ከሆነ በኋላ እንዲህ እንደ እርስዎ ተዝናንቶ መናገር ሰው ንቀት ይመስላል፤ ለሽንገላ እና ለበጣም ይቀርባል እንጅ ምንም ትርፍ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የወደቡ ነገር ከሆዱ ያልወጣ፣ መቼም ቀብሮት የማይገባው ጉዳይ ቢሆንም በእርስዎ እና በጓዶችዎ አንደበት እና አሳሳቢነት ያውም ከዚህ ረዥም ዘመን በኋላ ስለወደብ መስማት ግን ጅል ተደርጎ እንደተቆጠረ ከማሰብ የዘለለ ስሜት አይሰጠውም፡፡ ለእርምትም ፣ለይቅርታም፣ለመደመጥም ፣ ለመታመንም እንደ እርስዎ ፓርቲና ጓዶች ረዥም ዘመን እና ሰፊ እድል የተሰጠው የለም፡፡ ግን ያንን አልተጠቀማችሁበትም፡፡ አሁን በተለይ ይሄን ጉዳይ በተመለከተ የሚያምርባችሁ ዝምታ ነው!

 

 

ወደ ትግራይ ሰዎች…

‘በደሜ በላቤ ደማቅ ታሪክ ፀፍኩ’ ባዩ ህ.ወ.ሃ.ት ለመንገዴ መቅናት ምክንያቱ የትግራይ ህዝብ አጋርነት ነው ይላል፡፡ ይህ ግማሽ እውነት ነው፡፡በህወሃት ጥላስር ይታገሉ የነበሩት ትግሬዎች ብቻ አልነበሩም፡፡የቀድሞው የህወሃት ታጋይ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እንደሚናገሩት ስሙ አይነሳም እንጅ ከህወሃት መስራቾች አንዱ ጎንደሬ አማራ ነው፤ሰውየው በአሁኑ ወቅት በሽተኛ እና ችግረኛ ሆኖ አንዳንዴ ቤታቸው እየጠሩ እንደሚያስታምሙትና እንደሚያሳክሙት በአንድ ወቅት መስክረው ነበር፡፡በቅርቡ እንደሰማሁት ይህ ሰው በቂ ህክምና እንኳ ሳያገኝ ህይወቱ እንዳለፈ አንብቤያለሁ፡፡

ከደርግ ግፈኛነት የተነሳ  ህ.ወ.ሃ.ት የሚለውን ስም እንደከልካይ ሳይቆጥር ትግሬ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም የህወሃት አባል ሆኖ ደርግን ተፋልሞ ነበር፡፡ህ.ወ.ሃ.ቶች ግን ይህን ማንሳት አይፈልጉም፡፡ከዚህ ይልቅ መላው ኢትዮጵያዊ ከደርግ ተፋልሞ ነፃነቱን ላቀዳጀው የትግራይ ህዝብ ባለ እዳ እንደሆነ፣የትግራይን ህዝብ ቤዛነት እና ጀግንነት በአንደበታቸውም በድርጊታቸውምያስተጋባሉ፡፡ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት “ኢንዶውመንት” በሚል የዳቦስም ትግራይን የፋብሪካ መክተቻ ማድረጉን ተያያዙት፡፡ ‘ምነው ይህ በረከት ለሌላው የኢትዮጵያ ምድር ቢደርስ?’ የሚል ከተገኘ መልሱ ‘የትግራይ ህዝብ በጦርነት የተጎዳ ጀግና ህዝብ ስለሆነ ይህ አይበዛበትም፤ተራ ቅናታችሁን ትታችሁ የትግራይን ልማት ሬት ሬት እያላችሁም ትቀበሉታላችሁ’ የሚል ነበር፡፡ይህን የሚሉት ስለ “እውቀት ጢቅነታቸው” በጀሌ ካድሬዎቻቸው ማህሌት የሚቆምላቸው አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ ጉድ የተባለ “ጥልቅ እውቀት” ጀግንነት በዘር የሚተላለፍ ቡራኬ አድርጎ ለማቅረብ የማያፍር ነው፡፡ እርሳቸው የወጡበትን ዘውግ ልዩ የሆነ የጀግንነት ቅመም እንዳለው ከአንድም ሁለት ሶስቴ በአፋቸው የተናገሩት አቶ መለስ በተግባራቸው ያደረጉት በአፋቸው ካወሩት እጅግ ዘለግ ያለ ነው፡፡

የኢፈርት እና ደጀና “ኢንዶውመንቶች” ነገር..!

አቶ መለስ የሚመሩትን መንግስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የሲቪል ስልጣን ለወንዛቸው ልጆች ካደሉ በኋላ ለወጡበት ዘውግ ይገባል ያሉትን ሁሉ ከማድረግ እጃቸውን አልሰበሰቡም፡፡ኢፈርት የተባለውን አደናጋሪ እና ሚስጥራዊ የንግድ ኩባንያዎች ባህር አቋቁመው ሚስታቸውን (ያለ አቅሟም ቢሆን)ይህን የፋብሪካ ባህር እንድታስተዳድር ሰየሟት፡፡ወ/ሮ አዜብ ወደ ኢፈርት ቁንጮነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት አዛውንቱ ስብሃት ነጋና ሌሎች ትግራዊያን ኢፈርትን ዘውረዋል፡፡የኢፈርት ፋብሪካዎች ወደ ሰማኒያ የሚደርሱ ሲሆኑ አንዱም “በስህተት” እንኳን ከትግራይ ውጭ አልተገነባም፤ከትግራይ ባልሆነ ኢትዮጵያዊም ተዳድሮ አያውቅም፡፡በአንፃሩ ፋብሪካዎቹ የሚያመርቱት ሸቀጥ በመላ ሃገሪቱ ይራገፋል፣ወደባህር ማዶም ይሻገራል፡፡የፋብሪካዎቹ በአንድ ቦታ መከማቸት ከትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ፋብሪካዎቹ ‘በስኩየር ኪሎሜትር ስንት?’ ተብለው ሊቆጠሩ ምንም ያልቀራቸው ያስመስላል፡፡ የኢፈርት በትግራይ ብቻ መከተም፣በትግራዊ አስተዳዳሪዎች ብቻ መተዳደር ጉዳይ በጣም እያነጋገረ ባለበት ሁኔታ ደግሞ ሌላ ወንድም “ኢንዶውመንት” በእዛው ክልል በቅርቡ ተመስርቷል፡፡የዚህ ምክንያቱ የኢፈርት ኩባንያዎች መበራከት አለቅጥ ሰፍቶ  ለአስተዳደር  አመች ወደ አለመሆን ግዝፈት በመድረሱ ሌላ ኢንዶውመንት እንዳስፈለገ ወ/ሮአዜብ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡የኢፈርት ግዝፈት ሊያመጣ የሚችለውን አስተዳደራዊ ውስብስቦሽ ለመታደግ “ደጀና” የተባለ ትግራይ ከታሚ ኢንዶውመንት በዚህ ከሶስት አመት አካባቢ በፊት ተቋቁሞ እነ አበርገሌን አይነት ኩባንያዎች አቅፎ ልማቱን እያሳለጠ እንደሆነ ሰርክ ይወራል፡፡ አዲሱ ደጀና ኢንዶውመንት ከአስር በላይ ኩባንያዎች በስሩ አቅፎ ታላቁን ኢፈርትን ለመፎካከር ድክ ድክ እያለ ነው፡፡

እነዚህ ኢንዶውመንቶች ከትርጉማቸው ጀምሮ ባለቤትነታቸው፣ኦዲት ያለመደረጋቸው ጉዳይ፣ በአንድ ክልል(በትግራይ) ብቻ እንዲከትሙ ያደረጋቸው ምስጢር ወዘተ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የሚያስቆጣ ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል፡፡የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት እነዚህ ፋብሪካዎች ኦዲት የማይደረጉበት፣የኦዲት ሪፖርታቸውም የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ለሆነው ፓርላማ የማይቀርብበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ተገቢ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ለዚህ የአቶ መለስ መልስ ‘እነሱ እኮ ኢንዶውመንቶች ናቸው ግልፅ ሪፖርት ማቅረብም አይጠበቅብንም’ የሚል የተለመደ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡ አቶ ተመስንም የዋዛ አይደሉምና “ኢንዶውመንት” የሚለውን ቃል ትርጉም በአማርኛ ሆነ በኦሮምኛ በአፋርኛ ሆነ በትግርኛ በፈለጉት ቋንቋ ተርጉመው እንደዚህ አይነኬ የመሆኑን ሚስጥር  ያስረዱን” ሲሉ ቢወተውቱም አቶ መለስ በማስቀየስ እንጅ መልስ በመመለስ ስማይታሙ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡የሆነው ሆኖ “ኢንዶውመንት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአብዛኛው የኮርፖሬት ፈንዶችን ለመግለፅ የሚያገለግል ፅንሰሃሳብ ነው፡፡ከሌሎች የንግድ ማህበሮች በተለየ ከኢንዶውመንት ኮርፖሬት ፈንዶች የሚገኝ ትርፍ ተመልሶ ለልማት የሚዉል  እንጅ  ለባለቤቶች የሚከፋፈል አይደለም፡፡ የአቶ መለስ “ኢፈርት እኮ ኢንዶውመንት ነው” የሚለው መልስም ትርፉ መልሶ ለሌላ ልማት የሚውል ነው ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ በግልፅ ኦዲት ካለመደረግ ጋር የሚያገናኘው ነገር በበኩሌ አይገባኝም፡፡

የኢንዶውመንቶቹን ባለቤትነት በተመለከተ የኢፈርት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአንድ ወቅት  ‘ኢፈርት በተዘዋዋሪ የትግራይ ህዝብ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ:: ‘በቀጥታስ ባለቤቱ የማን ነው?’ የሚለው እስከዛሬ ሚስጥር እንደሆነ አለ፡፡ ለጊዜው በግልፅ ወደ ተነገረን ተዘዋዋሪው ባለቤት የትግራይ ህዝብ እና የኢፈርት መስተጋብር ስንሄድ ኢፈርትን የሚያክል የፋብሪካ ባህር በትግራይ ብቻ እንዲንጣለል ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ማለፍ አይቻልም፡፡ ህወሃት እንደሚለው ኢፈርት እና ደጀና በትግራይ የከተሙት  የትግራይ ህዝብ ወኪል የሆነው ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያፈራውን ገንዘብ ለቆመለት ህዝብ ልማት ማዋል ስላለበት ነው፡፡እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ አንደኛው ለህዝብ ነፃነት የታገለው ህወሃት ምን ሰርቶ ይህን ያህል ገንዘብ አፈሰ? ጠመንጃ ተሸክሞ መባተልን የሚፈልገው የትጥቅ ትግል ሲራራ ንግድ አይደለምና ጥሪት አስቋጥሮ የኩባንያ ባህር ማቋቋም ያስቻለውስ እንዴት ነው? ገንዘቡ በትጥቅ ትግል ወቅት የተገኘነው ከተባለስ የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው በትግራይ ብቻ አልነበረምና ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ኢፈርት ያሉ ባለግዙፍ ኢንዶውመንቶች ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

የትግሬነት እና ህወሃትነት ልዩነት ትርክት ሳንካዎች

በሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንደ የትግራይ ህዝብ እና የህወሃት መስተጋብር ያለ ግራ አጋቢ፣ ብዙ እንደማነጋገሩ ፈር የያዘ መልስ ያልተገኘለት፣ለትንታኔ አስቸጋሪ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ህወሃት የኢህአዴግ ልብ ሆኖ ሃገሪቱን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሲዘውር ከፊት የሚያሰልፋቸው ዋና ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች  ከትግራይ የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ነገር ህወሃት ለሁለት ጥቅም ያውለዋል፡፡ አንደኛው የወንዙን ልጆች በወሳኝ ቦታዎች ኮልኩሎ ከውልደቱ ጀምሮ የተጣባውን የዘረኝነት ዝንባሌ ያፀናበታል፡፡ በሁለተኛ እና በዋነኝነት የትግራይን ህዝብ ደጀን ለማድረግ ልቡን ማግኛ መንገድ አድርጎ ያየዋል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለተመለከተ ለህወሃት ሁለቱም የተሳኩለት ይመስላል፡፡ለዚህ ማሳያው የህወሃት የሃረግ መዘዛ ፖለቲካ ከእርሱ አልፎ በመላ ሃገሪቱ ማርበቡ ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ የመተባበርም ሆነ ያለመተባበር፣ የመተማመንም ሆነ የመጠራጠር ምንጩ ሃረግ መማዘዝ ሆኗል፡፡ይህ በአንድ እናት ሃገር ልጆች መሃከል ከፍተኛ ያለመተማመን አምጥቷል፡፡ ሌላው ህዝብ እርስ በርሱ በጎሪጥ የሚተያይ ተጠራጣሪ ሲሆን የትግራይን ህዝብ ደግሞ የአፋኙ የህወሃት ጠበቃ አድርጎ የመፍራት አዝማሚያ ይታያል፡፡ይሄኔ ከላይ የተጠቀሰው የህወሃት እራሱን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እና ያው አድሮጎ የማቅረቡ አላማ ይሰምራል፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ጋር አንድ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ምንጩ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡በላይኛው የውትድርና ማዕረግ  ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከትግራይ የወጡ ሰዎች መያዙ፤ በሲቪሉ ክንፍም ቢሆን ለረዥም ጊዜ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትነት፣የሃገር ደህንነት ኤጀንሲ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣በስመ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመካሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን ማሾሩ፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር ከዝቅተኛ  እስከ ከፍተኛ የሃፊነት ቦታ የትግራይ ተወላጆች መበራከት፣ይህ ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሲወገዝ አለመታየት ለተመልካች ትግሬን እና ህ.ወ.ሃ.ትን አንድና ያው አድርጎ ያይ ዘንድ ይገፋዋል፡፡አሁን ሃገራችን በምትመራበት የዘውግ ፌደራሊዝም ሁኔታ ህ.ወ.ሃ.ት ድርና ማግ ሆኖ መምራት የሚችለው  የትግራይ ክልልን ብቻ መሆን ሲገባው የህ.ወ.ሃ.ት ሃያል ህልውና በአዲስ አበባም መስተዳድር ቢሮዎችም ሆነ አዲስ አበባ በከተመው የፌደራል መንግስትም ሚታይ የመሆኑ አደገኛ አካሄድ ለህወሃት መራሹ ኢህዴግ የታየው አይመስልም፡፡ባለሃብትነቱም ቢሆን ለሁሉም ባይሆንም ለትግራዊያኑ ብዙ ጊዜ የማይወስድ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡

ከትግራይ የሆኑ ዜጎች በስልጣን እና በሃብት ማማ ላይ በርከት ብሎ መታየት በተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚታይበትን መንገድ በሰፊው ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡መጠኑ ቢለያይም ትግሬ ሁሉ ህወሃትን ይደግፋል፤ትግሬ ሆኖ ከልቡ የህወሃትን ሁለንተናዊ የበላይነት ማብቃት የሚፈልግ ማግኘት አይቻልም የሚለው ሙግት ነው፡፡በዚህኛው ወገን ያሉ አሳቢዎች ክርክራቸውን የሚያጠናክሩት እስከዛሬ በትግራይ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶ አለማወቁን ነው፡፡ ተከራካሪዎቹ በተጨማሪ የሚያነሱት ነጥብ ከትግራይ የሚነሱ የህወሃት ተቃዋሚዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች እንደ ኢፈርት እና የወልቃይት ጥያቄን የተመለከተ ከህወሃት የተለያ አቋም ለማንፀባረቅ ይቸገራሉ የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የቆሙ ተከራካሪዎች ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ ተለያይተው መታየት እንዳለባቸው አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡እነዚህኞቹ ለክርክራቸው ማጥበቂያ የሚያነሱት ሃሳብ የትግራይ ህዝብም የህወሃት ብልሹ አሰራር ሰለባ መሆን፣ሌላ አማራጭ ሃሳብ መነፈግ እና በአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ መጠለፍ፣የአብዛኛውን የትግራይ ህዝብ የድህነት ኑሮ ወዘተ ነው፡፡

የትግራይን ህዝብ እና የህወሃትን አንድነት ልዩነት በተመለከተ የሚነሱት እነዚህ ጎራዎች በየፊናቸው ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎችን አስከትለው ሲያሟግቱ የኖሩ ቢሆኑም ሁለተኛው ማለትም የትግራይን ህዝብ እና ህወሃትን ለይተን እንይ የሚለው ክርክር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡በበኩሌ የዚህ ክርክር ደጋፊዎች መመናመን አብሮነታችንን የሚፈትን፣ የትግራይን ህዝብ ስጋት ላይ የሚጥል አሳሳቢ ነገር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ጥፋት የትግራይ ህዝብም አድርጎ የማየቱ ነገር  በተቻለ ፍጥነት መቀየር ያለበት ነገር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛውን ድርሻ መውሰድ ያለበት ደግሞ ራሱ የትግራይ ህዝብ ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ ምን ይጠበቃል?

ህወሃት እርሱ በስልጣን ሰገነት ላይ ከታጣ ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ እሳት ሆኖ እንደሚበላው ያስፈራራል፡፡  ቀላል የማይባለው ትግራዊም ይህን ተቀብሎ የህወሃት ወንበር የተነቃነቀ በመሰለ ቁጥር ስጋት ይወርሰዋል፡፡ይህን የአብዛኛው ትግራዊ ስጋት የሚረዳው ሌላው የሃገራችን ህዝብ ትግራዊያንን የግፈኛው ህወሃት ወንበር ጠበቃ አድርጎ ያስብና የህወሃት የግፉ ማህበርተኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ይህ ህ.ወ.ሃ.ት ታጥቆ የሰራበት እና ስኬታማ የሆነ የሚመስልበት ፈለግ ነው፡፡ ይህ ነገር ግን መቆም አለበት፡፡ ነገሩን ለመቀየር ደግሞ የትግራይ ህዝብ ማሰብ ያለበት የዚህን ሁሉ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ መነሻው የህወሃት ‘ከሌለሁ የላችሁም’ ስብከት ነው፡፡ ይህንን መመርመሩም ደግ ነው፡፡ የምርምሩ መነሻ ‘ህወሃት ሳይኖር ትግሬ አልነበረም ወይ?’ ብሎ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ሲሆን መልሱ ትግሬ ከህወሃት በፊት ነበረ ነው፡፡ ትግሬ ከህወሃት በፊት ከነበረ ዛሬ እኔ ከሌለሁ የላችሁም የሚለው የህወሃት ዜማ እንዴት መጣ የሚለውን ማስከተልም ተገቢ ነው፡፡የዚህ ዜማ መነሻው ብልጣብልጡ ህወሃት በመላው የትግራይ ህዝብ ስም ግን ለጥቂት ትግሬዎች የሰራው/የሚሰራው አድሎ እና ዘረኝነት ነው፡፡እንደ አሸን ፈልተው ትግራይ የከተሙ የኢፈርት እና ደጀና ኢንዲውመንት ፋብሪካዎች፣በሁሉ ቦታ ብቅ የሚሉ የትግሬ ሹማምንት፣የትግሬ ብቻ የጦር ጀኔራሎች፣ቱጃር ለመሆን የሳምንት እድሜ የሚበዛባቸው ትግራዊ ባለሃብቶች መበራከት ወደ ትግራዊያን  ያጋደለው የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል ማሳያዎች ናቸው፡፡ባልበላው እዳ ላለመጠየቅ የሚወድ ትግሬ ሁሉ ይህን አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን ማውገዝም አለበት፡፡

ወደዚህ ልቦና ለመምጣት ሰፊው የትግራይ ህዝብ ራሱን በሌላው ኢትዮጵያዊ ጫማ ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ ‘እኔ ትግሬ ባልሆን ኖሮ ይህን ጉዳይ እንዴት አየው ነበር’ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር መለስ እና ደቀመዛሙርቶቻቸው ትግሬነታቸው ቀርቶ አፋር ቢሆኑና ኢፈርትን እና ደጀናን የመሰሉ የልማት ተቋማት አፋር  ብቻ እንዲከቱ አድርገው፤ በአፋር አለቆች እንዲዘወሩ ቢያደርጉ፤ ይህ ሳያንስ ደግሞ የአፋር ህዝብ ለእንዲህ ያለው አስተዳደር እድሜ ሲለምን ባየው የሚሰማኝ ምንድን ነው ማለት ያስፈልጋል፡፡ከስልጣን የማይወርዱ የአፋር የመንደር ልጆች የራሳቸው ስልጣን ላይ ሙጥኝ ማለት ሳያንስ የአፋር ባለሃብቶችን የመፍጠር ፕሮጀክት ቀርፀው ሌላውን ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ ባይትዋር ቢያደርጉ ምን ይሰማኝ ነበር? የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ተብለው በፌደራል ወንበር የተቀመጡት ሰውየ የትግራይን ክልል የኢንዱስትሪ ዞን ለማድረግ እቅድ አውጥተው ነበር ተብሎ ከገዛ ባለቤታቸው ሲነገር መስማት ትግራዊ ላልሆነው ሰፊ ህዝብ ደስ የሚያሰኝ ትርጉም አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ አሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ስሜት ለመረዳት ይበጃል፡፡

በግሌ ከትግራዊ ወዳጆቼ እና ጓደኞቼ ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ በአብዛኛው የሚገጥመኝ ክርክር ‘ኢፈርት ትግራይ መከተሙ ለሰፊው ህዝብ ምንም የፈጠረው ነገር የለም፡፡ የፋብሪካዎቹ ባለቤት የህወሃት ባለስልጣኖች እና ዘመድ አዝማዶች ናቸው’ የሚል ነው፡፡ ይህም ግማሽ እውነት ነው፡፡ የእነዚህ ኢንዶውመንቶች ተጠራርቶ ትግራይ ላይ መከተም ለአካባቢው ሰዎች ቢያንስ የስራ እድል መፍጠሩ በሰፊው ትግራዊ መካድ የለበትም፡፡በቀጥታ የስራዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ለከተሞች ማደግ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የፋብሪካዎቹ መኖር የመግዛት ሃይል ያለው ተከፋይ ሰራተኛ በከተሞቹ እንዲኖር በማድረግ በቀጥታ በፋብሪካዎቹ ለመቀጠር ላልቻለው ህዝብ የንግድ እድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ሁሉ እድል ፋብሪካ በገፍ ላልተተከለለት ሌላው ኢትዮጵያዊ ያልተገኘ ነውና የእድገት ሁኔታ መዛባት ማምጣቱ ሃቅ ነው፡፡ ይህን ክዶ መነሳት የመግባቢያን ሰዓት ከማራቅ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

ሌላው ከትግራይ ወገኖቻችን የሚገጥመኝ ክርክር ‘የህወሃት ብልሹ አሰራር የትግራይን ህዝብም መድረሻ ያሳጣ ነገር ነው’ የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡የትግራይ ለፍቶ አዳሪ ድሃ ህዝብ በመዋጮ ብዛት ፍዳውን እንደሚያይ ከቦታው ከመጡ ሁሉ የሚነገር ነው፡፡ የሙስናው ነገር፣ሌላ ድምፅ እንዳይሰማ የማድረጉ አፈና ሁሉ በትግራይም ያለ ነው፡፡ ግር የሚያሰኘው ነገር ግን  የትግራይ ህዝብ አለበት የሚባለውን ግፍ በግልፅ ሲቃወም አይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ለዚህ አፈናው አያሰናዝርም የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ በበኩሌ ይህ አያሳምነኝም:: ምክንያቱም ሌላው ኢትዮጵያዊም የደረሰበትን ብልሹ አሰራር የሚያወግዘው መንግስት ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረለት ሳይሆን የደረሰበት ግፍ ብዛት አፈናውን ችላ ብሎ ድምፁን እንዲያሰማ ስለገፋው ነው፡፡ ስለዚህ የተበደለ ሁሉ በዳዮች ቀንበራቸውን እንዲያለዝቡ መጠየቁ ተፈፅሯዊ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ድምፁን አጥፍቶ አስተዳደራዊ በደሉን እንዲጋት ያደረገው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን መረጃ ከውስጥ አወቆች ለመስማት ጉጉት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ከትግራይ የሆኑ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ በደንብ ቢያስረዱን የትግራይ ህዝብ ያለበትን ችግር ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡

እንደ ህወሃት አገላለፅ በትግራይ የከተሙት  ኢንዶውመንት ተብየዎቹ አላማ ባመጡት ትርፍ ሌላ የልማት ተቋም በትግራይ መመስረት ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ  ልማት ልማትን እየወለደ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ለዚህ ምስክሩ በትግራይ የሚዋለዱት የፋብሪካዎች ብዛት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እንኳን በ850 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የጠርሙስ እና የብርጭቆ ፋብሪካ በእዛው ትግራይ ሊከትም እንደሆነ ትግራዊያን መኳንንት በቴሌቭዥን መስኮት እያወሩ ነበር፡፡ ከሳምት በፊት ደግሞ የመስፍን ኢንጅነሪንግ አልበቃ ብሎ  የምስራቅ አፍሪካን ገበያ ታሳቢ ያደረገ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዛው በትግራይ ስራ ሊጀምር እንደሆን ሰማን፡፡ይህን እያየን “ላለው ይጨመርለታል” ብለን እንድናልፍ ከታሰበ የማይሆን ነው፡፡

በአንፃሩ በሌላው የሃገራችን ክልል  የከባድ ፋብሪካዎች ተከላ ወሬ እንደ ሃምሌ ፀሃይ ተናፍቆም አይገኝ፡፡ ይህን እኔ ትግራዊ ሳልሆን ብሰማው ኖሮ ስሜቴ ዛሬ ትግሬ ሆኘ እንደሚሰማኝ ይሆን ነበር ወይ? ይህን የሚሰራው ህወሃት እድሜ ማጠርስ ያሳስበኝ ነበር ወይ?ይህን ጉልህ የተዛባ አሰራር እያዩ ዝም ማለትስ ይቻላል ወይ? የአንድ ሃገር ሰዎች ሆነን ሳለ ይህ ሲሳይ እኛጋ ያልደረሰው ለምንድን ነው ብሎ መሞገት ወንድም የሆነውን የትግራይ ህዝብ መጥላት ነው ወይ?  ብሎ መጠየቅ ደግ ነው፡፡ ህወሃቶችስ ይህን የፋብሪካ መንደር በትግራይ ብቻ እንዲከትም ያደረጉት ሊጠቅሙን ነው ሊጠቀሙብን? በዚህ ሁኔታ የምናገኘው ጥቅም ምን ያህል ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል፤ ብሎ መመርመር ከሃዲነት ሳይሆን ብልህነት ነው፡፡

የህወሃት ወንበር ሲነቀነቅ የትግራይን ህዝብ የሚያሳስበውን ያህል የብ.አ.ዴ.ን ህልውና የአማራን ህዝብ፣የኦ.ህ.ዴ.ድ በስልጣን ላይ መሰንበት የኦሮሞን ህዝብ፣የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በስልጣን ላይ መታየት የደቡብ ህዝብን፣የሶ.ህ.ዴ.ፓ እድሜ የሶማሌን ህዝብ ወዘተ ያሳስባል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡መልሱ ተቃራኒ ነው፡፡አብዛኛውን ትግራዊ የህወሃት ህልውና ክፉኛ ሲያሳስበው ሌላው ኢትዮጵያዊ እነዚህን ቆምንልህ የሚሉትን የገዥው ፓርቲ  አባል/አጋር  ፓርቲዎች እንደ የባርነት ወኪል አድርጎ ያያል፡፡ የእድሜያቸው ማጠር ከሚያስከፋው የሚያስደስተው በብዙ እጥፍ ይበዛል፡፡ለዚህ ከሰሞኑ በሃገራች ከተሞች ወከለናችኋል የሚሉዋቸውን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባል ፓርቲዎች ለማውገዝ ጎዳና የወጣው ህዝብ ብዛት ማሳያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብም እንደሌሎች ወንድሞቹ ቆምኩልህ እያለ ሌት ተቀን የሚሰብክ የሚያስፈራራውን ህወሃት ህፀፆች ለማውገዝ ማመንታት የለበትም፡፡ ‘ከሌሉ የለሁም’ የሚለውን አጓጉል አስተሳሰብ ትቶ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኖ ህወሃትን ታገስ ተመለስ ፣ካልሆነ ለሚችል ልቀቅ መለት አለበት፡፡ ይህንንም በአደባባይ ማሳየት አለበት፡፡ በተጨባጭ የሚታየውግን ሌላ ነው፡፡

ከላይ በትቂቱ ለማሳየት የተሞከረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል አንስቶ በምክንያት የሚሞግት ሰው ከአብዛኛው ትግራዊያን ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ‘እንዲህ የሚያስበው ትግሬን ስሚጠላ ነው’ የሚል ሲሆን ያጋጥማል፡፡ ይሄ ደመነፍሳዊነቱ የበዛ፣ ለመሞገት የሚያስችል የእውነት ስንቅ የማጣት የሚያመጣው የሽሽት መልስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሬ ወገኖቹን ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ጀማሪ፣እጅግ ሰው አክባሪ፣እንግዳ ተቀባይ ነውና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ህዝብ የሚወድበት እንጅ ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምክንያት የለውም፡፡ልክ ያልመሰለውን ነገር ሲጠይቅ ደግሞ ‘ይህን ያልከው እኛ ትግሬ ስለሆን’ ነው ማለት የጥላቻን መንገድ መጥረግ እንጅ ሌላ ጥቅም የለውም፡፡አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርቡ ‘የምታዩትን አድሎ እንዳላያችሁ እለፉ፤ያኔ እንደምትወዱን እናውቃለን’ ማለት አብሮነትን የሚፈትን አስቸጋሪ አቋም ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ አንፃር ይህ ሁሉ ሲጠበቅ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለትግራዊ ወንድሞቹ የሚያቀርበውን ጥያቄ የሚሰነዝረው ረጋ ብሎ፣ ጥላቻን አርቆ መሆን አለበት፡፡እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት የሆነውን መዛባት ሁሉ ያመጣው ህወሃት ከትግራይ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ተመካክሮ አይደለም፡፡ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ወደትግራይ የሚተመው ፋብሪካ ሁሉ ሲተከል ሰፊው የትግራይ ህዝብም እንደ እኛው በቴሌቭዥን ይሰማል እንጅ የሚያውቀው የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ‘ሌላውን ረስታችሁ ለእኔ ይህን አድርጉልኝ’ ብሎ አዞ ያስደረገው ነገርም አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከትግራዊ ወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር ይህን ሁሉ አስበን መሆን አለበት፡፡ ‘ህወሃት የትግራይን ህዝብ አይወክልም’ ከሚለው ሾላ በድፍን የሆነ ዘይቤ ወጥተን ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ነባራዊ ሃቆች ላይ ተመስርተን አፍረጥርጠን መነጋገር ያለብን ቢሆንም ንግግራችን ‘እኛ እና እነሱ’ የሚል ግድግዳ የተገነባበት መሆን የለበትም፡፡ ከዛ ይልቅ የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን እያሰብን፤ እንደቤተሰብ ውይይት ፍቅር እና መተሳሰብ ባልተለየው መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሁን እያነጋገረን ያለው ጉዳይ ረዥም ዘመን ከተጋራነው ወንድማማችነት የሚገዝፍ አይደለም፡፡ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ከስሜታዊነት የራቀ መሆን አለበት፡፡ ከስሜታችን ምክንያታችን መብለጥ አለበት፡፡ ይህ ካሆነ ዛሬ እንደቀልድ ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር  ነገ የምንፀፀትመበትን ጥፋት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ስለዚህ ጉዟችን ሁሉ ማስተዋል የተሞላበት መሆን አለበት፡፡ በፍቅር ከመነጋገር  እንጅ ከጥላቻ እና ከመጠፋፋት ትርፍ ያገኘ ህዝብ የለምና ንግግራችን ሁሉ ፍቅርን፣እርጋታን እና ምክንያታዊነትን የተሞላ መሆን አለበት፡፡ይህ ካልሆነ ህወሃትን እያገዝነው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡


For your comments and suggestion you can reach her via (e-mail meskiduye99@gmail.com )