Author Archives: Seyoum Teshome

About Seyoum Teshome

ነፃነት መብት አይደለም፣ ሰው መሆን ነው፣ የሕይወት ትርጉምና ፋይዳ ነው። የሰዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሙሉ አንፃራዊ ነፃነትን ለማሳደግ የሚደረግ ጥረት ነው። ይህ ጦማር ገፅ የነፃነቴ ማሳያ፣ ሰው የመሆኔ ምልክት ነው፡፡

​የትላንት ምርኮኞች /ክፍል-2/

የትላንት ምርኮኞች ክፍል አንድ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት በሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን መካከል መግባባት የለም። ለዚህ ዋናው ምክንያት ልሂቃኑ በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ተከፍለው እርስ-በእርስ መጠላለፋቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ከእለት ወደ እለት አምባገነናዊና ጨቋኝ እየሆነ መጥቷል። በዚህ መሃል የዜጎች ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት ክፉኛ ተገድቧል፡፡ ዛሬ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት ውስጥ የሚደረግ ሆኗል። በመሆኑም፣ ዘላቂ ሰላም፥ ልማትና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በቅድሚያ በሀገራችን ፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለው መጠላለፍ ማስቀረት ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ ልሂቃኑ በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ለይተው የሚጠላለፉበት ምክንያት ምንድነው?
በብሔርተኞች እና የአንድነት አቀንቃኞች መካከል ያለው ልዩነት ፖለቲካዊ ስርዓቱ “በብሔር እኩልነት ወይስ በአህዳዊ አንድነት” ላይ መመስረት አለበት በሚል ነው። ሁለቱም ወገኖች የአመለካከታቸውን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ በአብዛኛው ወደ 19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ በመመለስ ታሪካዊ ማስረጃ ሲያቀርቡ ይስተዋላል። ነገር ግን፣ በተመሳሳይ ግዜና ቦታ ስለነበሩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች እያወሩ ፍፁም ተቃራኒ የሆኑ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ። 

በተለይ ደግሞ በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመን ስለነበረው አገዛዝ ያላቸው አመለካከት ዋና መለያ ነው። ብዙውን ግዜ ብሔርተኞች የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝን አፍሪካዊ የቅኝ-አገዛዝ ስርዓት እንደሆነ ሲገልፁ ይሰማል። የአንድነት አቀንቃኞች ደግሞ የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ የቅኝ-አገዛዝ ኃይሎችን በማሸነፍ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ተምሳሌት እንደሆነ ይገልፃሉ። በጥቅሉ ብሔርተኞች የአፄ ሚኒሊክን ዘመን ከብሔር ጭቆና ጋር ሲያይዙት አንድነቶች ደግሞ ከሀገራዊ አንድነት ጋር ያያይዙታል። 

በዚህ መሰረት፣ ሁለቱም ወገኖች ስለአንድ ጉዳይ እየተናገሩ እርስ-በእርስ አይግባቡም፥ አይስማሙም። ምክንያቱም፣ አንደኛው ወገን የሚናገረውና የሚያደርገው ነገር በሙሉ የሌላውን ወገን ሃሳብና አመለካከት ውድቅ (nullify) በማድረግ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው። በመሆኑም፣ የሀገራችን ልሂቃን በሰከነ መንገድ ከመነጋገርና መግባባት ይልቅ እርስ-በእርስ በመዘላለፍና መጠላለፍ ይቀናቸዋል። 

ችግሩ በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ የተሰለፉት የፖለቲካ ልሂቃን “የትላንት ምርኮኞች” መሆናቸው ነው። ሁለቱም ወገኖች ትላንት ላይ ቆመው የነገውን መንግስት ለመመስረት የሚታትሩ ናቸው። ብሔርተኞች ሆኑ አንድነቶች ወደፊት በኢትዮጲያ ስለሚያስፈልገው ፖለቲካ ስርዓት እንደ መነሻና ማስረጃ የሚያደርጉት ከ100 ዓመት በፊት የነበረው የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ ነው። 

ብሔርተኞች የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት የብሔር መብትና እኩልነትን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት ይገልፃሉ። ለዚህ ደግሞ ከአፄ ሚኒሊክ ዘመን ጀምሮ የተዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦችን መብትና እኩልነት የሚጋፋ መሆኑን ይገልፃሉ። በኢህአዴግ መንግስት የተዘረጋው የብሔር ፖለቲካም በዚህ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በሌላ በኩል የአንድነት አቀንቃኞች የአፄ ሚኒሊክ አገዛዝ የሀገሪቱን አንድነትና ነፃነት ያረጋገጠ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህ አንድነት ግን በብሔር ፖለቲካ አማካኝነት አደጋ ላይ እንደወደቀ ይገልፃሉ። 

በጥቅሉ ሲታይ ግን የሁለቱም ወገኖች የፖለቲካ አመለካከት ትላንትና በሆነው ላይ እንጂ ነገ መሆን ባለበት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ብሔርተኞች የቀድሞውን በደል እንደ ምክንያት ሲያቀርቡ፣ አንድነቶች ደግሞ የቀድሞውን ድል እንደ ማሳያ ይጠቅሳሉ። ነገር ግን፣ እንደ “Jose Ortega y Gassett” አገላለፅ ማንኛውም መንግስት የሚመሰረተው ትላንት በሆነው ሳይሆን ነገ ሊሆን በሚችለው ላይ ነው፡-    

 “The State is always, whatever be its form- primitive, ancient, medieval, modern- an invitation issued by one group of men to other human groups to carry out some enterprise in common. State and plan of existence, programme of human activity or conduct, these are inseparable terms. The different kinds of State arise from the different ways in which the promoting group enters into collaboration with the others.” The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 97.  

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የኢትዮጲያ መንግስታዊ ስርዓት ባለፉት ዘመናት በሆነውና በተደረገው ሳይሆን ነገ ላይ ሊሆንና ሊደረግ በሚችለው ላይ መመስረት ነበረበት። በብሔርተኝነት እና አንድነት ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ የሚጠዛጠዙት የሀገራችን ልሂቃን የወደፊቱን አቅጣጫ በትላንትው እሳቤ ለመወሰን በመሞከር ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ የትላንትናው መንገድ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አይወስድም። ነገር ግን፣ ምንም ያህል ቢፈጥኑ፥ ቢዘገዩ አንዳቸውም ካሰቡበት አይደርሱም፡፡ ምክንያቱም፣ ሀገርና መንግስት የሚመሠረተው በነገ እንጂ በትላንት እሳቤ አይደለም፡፡ 

በመጨረሻም፣ የሁለቱም መንገድ የተሳሳተ መሆኑ እንዳለ ሆኖ “ለምን እርስ-በእርስ ይጠላለፋሉ?” የሚለውን እንመልከት፡፡ የብሔርተኝነት መንገድ ትክክል ካልሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ የአንድነትን መንገድ መከተል ይመስላቸዋል። በተመሳሳይ፣ የአንድነቶች መንገድ ትክክል ካልሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ የብሔርተኞችን መንገድ መከተል ይመስላቸዋል። ይህ “ጥቁር ወይም ነጭ” በሚል የፍፁማዊነት (infallability) ላይ የተመሠረተ አመለካከት ነው፡፡ የሁለቱም ወገኖች አመለካከት በግትር ፍፁማዊነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም፣ የአንዱ ወገን ትክክለኝነት የሚረጋገጠው በራሱ ምክንያት ሳይሆን በሌላው ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ፣ የራስን ሃሳብና አመለካከት ለማረጋገጥ የሌላኛውን መንገድና አካሄድ ውድቅ ማድረግ የግድ ነው። 

በአጠቃላይ፣ በፍፁማዊ የፖለቲካ አመለካከት ለሚመሩ የፖለቲካ ቡድኖች የአንዱ ስኬት ለሌላው ውድቀት ነው፡፡ ስለዚህ፣ የብሔርተኞች ስኬት የሚረጋገጠው በአንድነቶች ውድቀት ነው፡፡ ይህ አንደኛው ወገን ትክክል ሌላኛው ስህተት ስለሆነ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የሁለቱም ወገኖች መንገድና አካሄድ ስህተት ስለሆነ ነው። ምክንያቱም፣ ብሔርተኝነት እና አንድነት የሚያቀነቅኑ ወገኖች በሙሉ የትላንት ምርኮኞች ናቸው። በድጋሜ እንደ ”Jose Ortega y Gassett” አገላለፅ፣ የትላንት ምርኮኞቾ ለህዝብ የሚበጅ መንግስት መመስረት አይችሉም፦

“Not  what we were yesterday, but what we are going to be to-morrow, joins us together in the State.”  The Revolt of the Masses, Ch. XIV: Who Rules the World?, Page 97.  

​የትላንት ምርኮኞች /ክፍል-1/

የሀገራችን ልሂቃን በጥቅሉ “የብሔርተኝነት እና የአንድነት አቀንቃኞች” በሚል ለሁለት መክፈል ይቻላል። አብዛኛውን ግዜ በሁለቱ ወገኖች መካከል መጯጯህ እንጂ መደማመጥ የለም። በመካከላቸው በመግባባት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ውይይት ማድረግ አይቻልም። በእርግጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ምሁራን የገላጋይነት ሚና ይጫወታሉ። ሆኖም ግን፣ ምሁራንም የእብድ ገላጋይ ከመሆን አላለፉም። 

የፖለቲካ ልሂቃኑ በጋራ ጉዳዮች ላይ መወያየት ከተሳናቸው ብሔራዊ መግባባት (national consensus) ሊኖር አይችልም። ብሔራዊ መግባባት በሌለበት በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ግራ-መጋባት እና አለመተማመን ይሰፍናል። የብዙሃኑ አመለካከት (public opinion) በግራ-መጋባትና አለመተማመን ውስጥ ሲወድቅ ለጨቆና ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። 

በመሠረቱ የመንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚወሰነው በብዙሃኑ አመለካከት ነው። ምክንያቱም፣ አምባገነን ሆነ ጨቋኝ መንግስት በብዙሃኑ አመለካከት ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር አይፈፅምም። አንድን ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ባይደግፍ እንኳን በጋራ የማይቃወም መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። እንዲህ ያለ ማህብረሰብ የሚፈጠረው ደግሞ የፖለቲካ ልሂቃኑ እርስ-በእርስ መግባባት ሲሳናቸው ነው። የልሂቃኑ አለመግባባት በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ግራ-መጋባትና አለመተማመን እንዲሰፍን ያደርገዋል። ግራ-የተጋባና እርስ-በእርሱ የማይተማመን ሕብረተሰብ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት የለውም። በመሆኑም፣ የመንግስትን ተግባር ባይደግፍ እንኳን በጋራ አይቃወምም። 

ከላይ በተጠቀሰው መሠረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከእለት ወደ እለት ፍፁም አምባገነናዊና ጨቋኝ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል። ለምሳሌ፣ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል በተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ የመብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ንፁሃን ዜጎች ላይ የሚወስደውን የኃይል እርምጃ ባይደግፍም በጋራ አይቃወምም። ስለዚህ፣ ከጨቋኝ ስርዓት በፊት እርስ-በእርስ መወያየትና መግባባት የተሳናቸው ልሂቃን፣ በዚህ ደግሞ ግራ-የተጋባና የማይተማመን ሕብረተሰብ መፈጠር አለበት። 

የኢህአዴግ መንግስት የተፈጠረው በዚህ አግባብ ነው። በእርግጥ አሁን ያለው የብሔር የፖለቲካ በራሱ በ1960ዎቹ የነበረው የብሔርተኝነት እና አንድነት ፖለቲካ ውጤት ነው። በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ግን የብሔርተኝነት ሆነ የአንድነት አራማጅ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ፍፁም አምባገነናዊ ነው። መነሻው ብሔርተኛ ይሁን እንጂ ከብሔርተኞች ጋር ስምምነት የለውም። ከእሱ የተለየ ሃሳብ ያነሱ ብሔርተኞችን በጠባብነት፣ የአንድነት አቀንቃኞችን ደግሞ በትምክህተኝነት ይፈርጃል። በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት እያገኙ ሲሄዱና ሕዝባዊ ንቅናቄ ሲፈጥሩ ደግሞ በሽብርተኝነት ወንጀል ይከሳቸዋል። 

በአጠቃላይ የኢህአዴግ መንግስት ከእለት ወደ እለት ጨቋኝና አምባገነን እንዲሆን ያስቻሉት የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው። ልሂቃኑ እርስ-በእርስ መወያየትና መግባባት ስለተሳናቸው ብዙሃኑን የሕብረተሰብ ክፍል ግራ-ተጋብቷል፣ መንግስት ደግሞ ይበልጥ አምባገነን ሆኗል። ስለዚህ፣ የኢትዮጲያ ፖለቲካ መሰረታዊ ጥያቄ “የፖለቲካ ልሂቃኑ ለምን እርስ-በእርስ መወያየትና መግባባት ተሳናቸው?” የሚለው ነው። የዚህ ደግሞ መልሱ አጭርና ግልፅ ነው፡፡ አዎ…እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙሃኑ የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን “የትላንት ምርኮኞች” ናቸው። “ለምንና እንዴት” የሚለው በቀጣይ ክፍል በዝርዝር እንመለከታለን። ለአሁኑ የትላንት ምርከኞችን አመለካከት በአጭሩ በመዳሰስ ፅሁፌን ላብቃ፡፡

የትላንት ምርከኞች ጨዋታ ስለወደፊቱ ሳይሆን ስላለፈው ነው። ነገር ግን፣ ትላንት የሄደ፥ ያለፈ ነገር ስለሆነ አይቀየርም። የከርሞ ሰዎች ደግሞ ስለ ነገ ይወያያሉ። ነገ ተስፋ ነው። የነገ ተስፋ ይቀየራል፤ ብሩህ ወይም ጭለማ ይሆናል። የትላንት ምርኮኞች ስለ ትላንቱ በደል እና ድል ያወራሉ። ስለ ትላንቱ በደል ብቻ ማውራት ቂምና በቀል ይወልዳል። ስለ ትላንቱ ድል ብቻ ማውራት ባዶ ጉራ፥ የማቃት ስቅታ ይሆናል። የከርሞ ሰው ከትላንቱ በደልና ድል ይልቅ ስለ ነገ ተስፋና እድል በጋራ ይወያያል። የትላንት ምርኮኞች ስላለፈው የተናጠል በደልና ድል ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ ይጯጯሉ፥ ይጠላለፋሉ። 

ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እና የተቀደዱ ዘገባዎች!

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የታሰሩበትን ወንጀል አስመልክቶ ሪፖርተር ጋዜጣ ባቀረበው ዘገባ የሚከተለው ይገኝበታል፦

“ተጠርጣሪው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ሲሆኑ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል””

ሊጣላ የመጣን ቢለምኑት አይመለስም!” እንደሚባለው ሆኖ እንጂ፣ አቶ ሳምሶን ወንድሙ በተከሰሱበት ወንጀል የማይከሰስ የመንግስት ሃላፊ ማግኘት በራሱ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፣ ያልተጠናቀቁ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እንደተጠናቀቁ አስመስሎ ማቅረብ የኢህአዴግ መንግስት መለያ ባህሪ ነዋ፡፡ ለምሳሌ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በዚህ አመት ግንቦት ወር ላይ ባወጣው ሌላ ዘገባ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ1998 ዓ.ም ሲጀመር በ3 አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ከአሥር ዓመታት በኋላም ሥራ እንዳልጀመረ ገልጿል፡፡ በተመሣሣይ፣ የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም ሁለት ዓመት የተጓተተ ከመሆኑ በላይ፣ አሁን ያለበት የሥራ አፈጻጸም 41 በመቶ ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ በአጠቃላይ ከተያዘለት 11 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ 9 ቢሊዮን ብር አስፈልጎታል፡፡ 

በ2003 ዓ.ም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ኘሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ ባቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መሰረት የአቶ ሳምሶን ወንድሙ መ/ቤት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ አመት ብቻ ሳይሆን በየወሩ ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚያቀርብ መሆኑ” እንደ ጥሩ ተሞክሮ መወሰድ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል “የተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማት የፕሮጀክት አስተባባሪ የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም” ተብሎ በኦዲት ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ 

በመጨረሻም፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሁለት አመት በፊት “የተንዳሆ ግድብ ለዓመታት ተጓተተ” የሚለው የኢቢሲ ዘገባ… “ለዓመታት የተጓተተ ዘገባ” ነው!” በሚል ርዕስ ያቀረበውን ዘገባ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን እንደተጠናቀቁ አስመስሎ ማቅረብ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዘንድ የተለመደ ተግባር መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ በመሆኑም፣ ሙሉ ዘገባውን እንድታነቡት ጋብዘናችኋል፡፡

ምንጭ፦ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ድረገፅ

  1. ወጪው ከ1 ቢ. ብር በታች ነው የተባለው ግንባታ፣ ከ5 ቢ. ብር በላይ ፈጅቶም አላለቀም።  
  2. ቢበዛ በ3 ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ፣ 10 ዓመት አልበቃውም።
  3. ግድቡ እየተጓተተ ወጪው እንደናረ፣ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አድማስ ሲዘገብ ቆይቷል።
  4. በ2006 ዓ.ም፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ ግንባታው መዝረክረኩን ገልጿል – (አዲስ አድማስ)።
  5. ነገሩ ሲባባስም፣ አምና፣ የገንዘብ ሚ.ር፣ ለግድብ በጀት አልመድብም ብሏል። (አዲስ አድማስ)።
  6. የመንግስት ሚዲያ (ኢቢሲ) እና የመሳሰሉ፣ እነዚህን ዘገባዎች፣ “ጨለምተኛ” ሲሏቸው ነበር።


ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ይፈጃል ተብሎ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የተንዳሆ ግድብ ፕሮጀክት፣ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት እንዲጠናቀቅ ነበር የታሰበው። ምን ዋጋ አለው? ወጪው ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል። አስር አመትም ሞላው። ግን ግንባታው አላለቀም። የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ትልቅ ኪሳራ ነው። 

በዚህ መሃል…ኢቢሲ፣ ድንገት ተነስቶ፣ ይህንን የኪሳራ መረጃ ዘንድሮ የሚነግረን፣ የት ከርሞ ነው? ላለፉት ስድስት አመታት የት ነበር? “የግድቡ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ እየተከናወነ ነው” የሚል… ከእውነት የራቀ፣ ‘የሌለ’ ዜና ለመስራት ሲተጋ ነበር፡፡ ለዚያውም ለበርካታ አመታት።

እና፣ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው፣ ‘ግንባታው ተጓተተ፤ ወጪው ሸመጠጠ’ የሚል ዜና የሚያቀርብልን? ምናልባት፣ በአዲስ መንፈስ፣ ‘ከእንግዲህ ትክክለኛ ዜና እሰራለሁ’ የሚል፣ የአዲስ አመት እቅድ አውጥቶ ይሆን? ቢሆንማ፣ ጥሩ ነበር። 

ግን አይደለም። “ትክክለኛ ዜና የመስራት እቅዱ፣ ለተንዳሆ ግድብ ብቻ ነው” ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። እንዴት ካላችሁ፣… ኢቢሲ፣ ከተንዳሆ ዜና ጎን ለጎን፣ ስለ ህዳሴ ግድብ ያቀረበውን ዜና መመልከት ትችላላችሁ።   

ኢቢሲን ስትከፍቱ፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ በጊዜው እየተከናወነ ነው” የሚል ዜና መስማታችሁ አይቀርም። ለሕዳሴ ግድብ፣ ከፍተኛ ክብር ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያን፣ ዜናውን በትኩረት አዳምጠውት ይሆናል። በእርግጥ፣ በየጊዜው የሚደጋገም ዜና ስለሆነ፣ ‘ሳልሰማው አመለጠኝ’ የምንለው አይነት ዜና አይደለም። ባለፈው ሳምንት ቢያመልጣችሁ፣ ከዚያ በፊት በወዲያኛው ሳምንት፣ ተመሳሳይ ዜና ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል። ካልሆነም፣ በያዝነው ሳምንት ትሰሙታላችሁ፤… ወይም በሚቀጥለው ሳምንት።

የሕዳሴ ግድብን የሚመለከት፣ የግንባታ ዜና እየተደጋገመ መምጣቱ አይደለም ችግሩ። የሕዳሴ ግድብ፣ እንደ ትልቅነቱ፣ በየጊዜው ከግንባታው ሂደት ጋር ብዙ አዳዲስ መረጃዎች ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት፣ የሕዳሴ ግድብ፣ በተደጋጋሚ የዜና ርዕስ ሲሆን ብንሰማ፣ ችግር የለውም። ችግሩ ሌላ ነው። የተሳሳተ መረጃና የውሸት ዜና፣ (ለዚያውም እየተደጋገመ) መምጣቱ ነው ችግሩ።

ኢቢሲ፣ እንደተለመደው፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜው እየተከናወነ ነው” ካለ በኋላ፤ የግድቡ ግንባታ፣ 47% ላይ መድረሱን ገልጿል። ከምር ለመናገር፣ በትልቅነቱ የሚጠቀስ ግድብ፣ የዚህን ያህል ተገንብቶ ማየት፣ ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ተሰርቷል። ኢቢሲ፣ ይህችን እውነተኛ ዜና ብቻ መግለፅ እየቻለ፣ “በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜ እየተከናወነ ነው” የሚል ውሸት ለምን ይጨምርበታል? ግራ ያጋባል።

ምንጭ፦ ዶች-ቬሌ ራድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ድረገፅ

‘ከተያዘለት እቅድ ዘግይቷል።  ግንባታው ግን 47% ደርሷል’ ብሎ እንዲዘግብ መጠበቅ ያስቸግራል። ቢያደርገውማ፣ “the truth, the whole truth, nothing but the truth” እንደሚባለው፣ እውነተኛ መረጃ… የተሟላ እውነተኛ መረጃ፣… ሌላ ነገር (ውሸት) ያልተቀላቀለበት እውነተኛ መረጃ… ይሆን ነበር። 

ግን፣ እሺ… ይቅር። እውነተኛ መረጃን አሟልቶ ለመናገር ፈቃደኛ አይሁን። ግንባታው መዘግየቱን ሳይገልፅ ይተወው። ጎደሎ መረጃ መናገር ይችል ነበር – ግንባታው፣ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብቻ መግለፅ! ያው፣ ‘የተሟላ እውነት’ አይደለም። ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ… ውሸት አልተቀላቀለበትም። አይደለም?
ለነገሩ ይህንን እንተወው። ኢቢሲ፣ ‘እንዲህ ቢያደርግ’፣ ‘እንዲያ ቢያደርግ’ እያልን ለምን በከንቱ እንደክማለን። ኢቢሲ፣ ለዚህ ሁሉ ደንታ ያለው አይመስልም። ደንታ ቢኖረው ኖሮ፣ በየጊዜው እየደጋገመ በድፍረት፣ የሃሰት መረጃ ይናገር ነበር? አገር ምድሩ የሚያውቀው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ፣ የሃሰት መረጃ መናገር… ሌላ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በጣም ቀላል ጉዳይ ነዋ።       

የግድቡ ግንባታ፣ “በአምስት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል” ተብሎ እንደነበር ማስታወስ ያቅተናል? አሁን፣ አራት አመት ተኩል ሆኖታል። ግንባታው ግን፣ ወደ ማጠናቀቂያው ሳይሆን፣ ወደ ግማሽ ነው እየተጠጋ ያለው። ቢያንስ፣ ተጨማሪ አራት አመታት ያስፈልጉታል ማለት ነው። ኢቢሲ፣ ይህንን ሳይገነዘብ ቀርቶ ይሆን፣ ቀን ከሌት የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጨው? እንዴት ሊሆን ይችላል? 

አሁን አይደለም፣… ከአመት ከሁለት አመት በፊትም፣ የግንባታ ሂደቱንና አዝማሚያውን ለመገንዘብ ከባድ አልነበረም። ከሦስት ዓመት በፊት፣ መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በአዲስ አድማስ የወጣውን ዘገባ ማየት ይቻላል። 

የመንግስት ፕሮጀክቶችን በሚዳስሰው በዚሁ ዘገባ ላይ፣ የሕዳሴ ግድብ ተጠቅሷል። የሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት፣ የታቀደለትን ያህል እየፈጠነ እንዳልሆነ ዘገባው ገልፆ፤ በዚያ አያያዙ፣ ግንባታው ከስምንት እስከ አስር አመት ሊፈጅ እንደሚችል ይጠቁማል። ይሄ ከሦስት ዓመት በፊት የወጣ ዘገባ ነው። በእርግጥም፣ አሁን እንደሚታየው፣ ግድቡ በተያዘለት ጊዜ (ማለትም ዘንድሮ) ሊያልቅ አይችልም። ግማሽ ያህል ይቀራል።

 ይሄ፣ መንግስትን የመተቸት ወይም የማወደስ፣ የመደገፍ ወይም የመቃወም ጉዳይ አይደለም። ጥሬ መረጃ ነው። ችግሩ፣ ኢቢሲ፣ ለእንዲህ አይነት መረጃ፣ “ፊት የሚሰጥ” አልሆነም። ግን፣ አስቡት። ችግሮችን በመደበቅ፣ ማስተካከል አይቻልም። “ችግር አለ” ብለን ካልተናገርን፣ “ችግር ብን ብሎ የሚጠፋ” ይመስል! “በተያዘላቸው እቅድ እየተከናወኑ ነው” ብሎ መናገር ብቻውን፤ “የእቅድ ክንውን” ሆኖ ይመዘገባል ካልተባለ በቀር። 

ለእውነተኛ መረጃ፣ “ፊት የማንሰጥ” ከሆነ፣ የመጓተትና የመዘግየት ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ተገቢውን ያህል ትኩረት የሚያገኙበትም ሆነ የሚስተካከሉበት እድል እንዴት ይፈጠራል? 

 በተንዳሆ እና በሌሎች የስኳር ፕሮጀክት ላይ ያየነው ኪሳራ፣ ሳይስተካከልና መፍትሄ ሳያገኝ ለአመታት እየተባባሰ የመጣውም በዚሁ ምክንያት ነው። ስለ ተንዳሆ ግድብም ሆነ ስለሌሎቹ ፕሮጀክቶች፣ ኢቢሲ መረጃ ሳያገኝ ወይም ችግሩን ሳይገነዘብ ቀርቶ ነው? 

እሺ፣ አላወቀም፤ አልተገነዘበም እንበል። ግን፣ ለማወቅና ለመገንዘብ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ፣ ቀላል ዘዴዎችን አያጣም ነበር። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጡ ዘገባዎችን ማንበብ፣ ያን ያህል ከባድ ስራ አይደለም።

ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትም ጭምር፣ በ1997 ዓ.ም በወጣላቸው እቅድ እየሄዱ እንዳልሆነ፣ በ2001 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ሲዘገብ አስታውሳለሁ። 

የተንዳሆ ግድብ፣ በ98 ዓ.ም፣ ከዚያም በ99 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ተመድቦለት በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ፣ ምን እንደተከሰተ የሚዘረዝር ሌላ ሰፊ ዘገባም በዚሁ ጋዜጣ ቀርቧል። በሰፊው መቅረቡ አለምክንያት አይደለም። በየአመቱ የሚመደበው ገንዘብ ቀላል አይደለም። ከመቶ ሚሊዮን ብሮች እስከ ቢሊዮን ብር ይደርሳል። ግን፣ ግድቡ ተገንብቶ አላለቀም። እንደገና፣ የ2000 ዓም. በጀት ሲዘጋጅም፣ ገንዘብ ተመደበለት – የግድብ ግንባታውን ዘንድሮ ለማጠናቀቅ በሚል። ግን አልተጠናቀቀም።

በቀጣዮቹ አመታትም… በ2003፣ ከዚያም በ2004… ምንም የተቀየረ ነገር የለም። የበጀት ሰነዶቹ ላይ፣ አረፍተ ነገሮቹ እንኳ አይቀየሩም። “የተንዳሆ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቀ…” የሚለው ፅሁፍ “ኮፒ ፔስት” እየተደረገ በየአመቱ ይደጋገማል – ዓመተ ምህረቱ ብቻ እየተቀየረ።

የመንግስት ቴሌቪዢን ግን፣ እውነታውን ከመዘገብ ይልቅ (እናም መፍትሄ እንዲበጅለት ከማሳሰብ ይልቅ)፣ የአዲስ አድማስ አይነት ዘገባዎችን ለማስተባበል ነበር የሚተጋው – ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው እቅድ በጊዜ እየተገነቡ ነው’ እያለ። 
ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም ይመስላል፣ “እንደ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ትልልቆቹ እቅዶች’ኮ ለአመታት እየተጓተቱ እስከ ዛሬ መዝለቃቸውን ራሱ መንግስት አይክደውም” የሚል ፅሁፍ በአዲስ አድማስ የታተመው (ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም)። “መቼ ነው መንግስት፣ የማይሳኩትን እቅዶች በግልፅ የሚነግረን” በሚል ርዕስ የቀረበ ትንታኔ ላይ ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ፣ የተንዳሆው ፕሮጀክት ነው። አዲስ አድማስ እንዲህ፣ እውነተኛ መረጃዎችን በመስከረም 2005 ዓ.ም ሲዘግብ፣ የመንግስት ሚዲያ በዚያ ሰሞን ምን ዘገበ?

መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም የኢዜአ ርዕስ እንዲህ ይላል – “የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በቀጣዩ ጥር ወር በከፊል ወደ ሥራ ይገባል”።

ለነገሩ፣ የመንግስት ሚዲያ፣ በቀላሉ ለእውነተኛ መረጃ “ፊት ይሰጣሉ” ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት ከፈለጋችሁ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ሪፖርት መመልከት ትችላላችሁ። የተንዳሆ ፕሮጀክት፣ እጅጉን እንደተጓተተና በከፍተኛ የሃብት ብክነት እንደተዝረከረከ፣ ዋናው ኦዲተር ሰፊ ዝርዝር ሪፖርት ያቀረበው በ2006 ዓ.ም ነው። አዲስ አድማስ ይህንን ዘግቧል። በመንግስት ሚዲያ ግን አልተዘገበም።
ሰሞኑን ድንገት ተነስቶ ግን ፕሮጀክቱ ለዓመታት መጓተቱን የሚገልጽ ዘገባ አሰራጨ፡፡ ለዓመታት ለተጓተተ ፕሮጀክት ለዓመታት የተጓተተ ዘገባ !!

እስኪ ይህን የኦዲት ሪፖርት ተመልከትና አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለምን እንደታሰሩ ንገረኝ?

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተጠርጥረው የታሰሩት “የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል” በሚል እንደሆነ የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል፡፡ ነገር ግን፣ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ያለውን ሁኔታ ለማጤን መረጃዎችን ሳፈላል በ2003 ዓ.ም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ኘሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ ያቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት (pdf) አገኘሁ፡፡ ይህ ሪፖርት በውስጡ ከያዛቸው አስገራሚ መረጃዎች ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር (ገ/ኢ/ል/ሚ)  በየወሩ የአፈፃፀም ሪፖርት የሚያቀርበው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን “ብቻ” መሆኑንና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ግን በጭራሽ ሪፖርት እንደማያደርጉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የገ/ኢ/ልማት ሚኒስቴር ስለተገኘው የክትትልና የግምገማ ውጤት ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱና በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ እንዳቁሞ እንደነበር መርዶ ይነግረናል፡፡  

እያንዳንዱ የልማት ፕሮጀክት ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ካልገጠሙ በቀር፣ በተዘጋጀለት የጥናት ሰነድ ላይ በተመለከተው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሊጀመርና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እና የገንዘብ መጠን መሰረት መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ ፕሮጀክት ለማወቅ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በ2003 ዓ.ም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ገፅ 28 ላይ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና የገንዘብ መጠን የማይጠናቀቁ መሆኑን እንዲህ ይገልፃል፦

በኦዲቱ በናሙና ተመርጠው ከታዩት 8 የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች መካከል አምስቱ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳልተጠናቀቁና ተጨማሪ ጊዜ እንደወሰዱ ታውቋል፡፡ እንደዚሁም በውኃ ሀብትና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሥር ከሚካሄዱት ኘሮጀክቶች ውስጥ በኦዲቱ ለናሙና የታዩት ሁለት ኘሮጀክቶች የአፈጻጸሙ ሁኔታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ የከሰም ተንዳሆ የግድብና መስኖ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት እ.አ.አ በ2004 የተጀመረ ሲሆን በወቅቱ 1.669 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ እስከ 2002 ዓ.ም. ብቻ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ለገ/ኢ/ልማት ሚኒስቴር መ/ቤት ከቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁንም ሥራው ያልተጠናቀቀና የከሰም ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት 69%፣ የተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት 55% ያህል ብቻ እስከ 2002 በጀት ዓመት የፊዚካል አፈጻጸም መከናወኑን ከውሃ ሃብትና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ በቃል የተገለጸልን ሲሆን ይህን የሚገልጽ የአፈጻጸም ሪፖርት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተጠይቀው “ፈቃደኛ” ሊሆኑ አልቻሉም፡፡” 

በገፅ 34 ደግሞ ኘሮጀክቱ አዋጪ መሆን/አለመሆኑ ጥናቱ ተጀምሮ ከፍተኛ ወጪ ከተደረገበት በኋላ የተቋረጠ ኘሮጀክት ስለመኖሩ የሚከተለውን በማሳያነት ይጠቅሳል፦  

“ይሁን እንጂ በኦዲቱ ወቅት፣ በግብርና ሴክተር ስር ያለው የእንስሳት ሃብት ልማት ማስተር ፕሮጀክት (በእርዳታ) ጥናት፣ የፕሮጀክት ዝግጅቱ ሁለተኛ ደረጃ (phase) ላይ ሲደርስ ተቋርጧል፡፡ ለምን ጥናቱ እንደተቋረጠ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር ተጠይቀው በሰጡት መልስ፣ የፕሮጀክቱ ረቂቅ ጥናት ቀርቦ አማካሪው በተሰጠው ቢጋር /TOR/ መሰረት ስራውን ባለማከናወኑ ምክንያት በመንግስት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ስራው የተቋረጠ መሆኑንና ስራውን እንደገና መልሶ ለማስጀመር ጥረት ተደርጎም እንዳልተሳካ ተገልጿል፡፡ ከፕሮጀክቱ ጠቀሜታ አንጻር የዝግጅት ሂደቱ ሁለተኛ ደረጃ (phase) ደርሶ ለጥናት ዝግጅት የሚያስፈልገው ሃብት በ2000 በጀት ዓመት ብር 4‚922‚220፣ በ2001 በጀት ዓመት ብር 23‚480 እና በ2002 በጀት ዓመት ብር 11‚630.00 በድምሩ ብር 4‚957‚330 ወጪ ተደርጎ እንዲቋረጥ መደረጉ ታውቋል፡፡ ስለሆነም በወቅቱ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ፣ የወጣው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲባክን ከመደረጉም በላይ ሀገሪቱ ለ20 ዓመታት የምትመራበት ማስተር ፕላን አለመዘጋጀቱ ከኘላኑ ተግባራዊነት የሚገኘውን ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያሳጣ በመሆኑ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡” 

ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርበው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የሚቀርብ ስላለመሆኑ፦

“በፕሮጀክት አስፈጻሚ አካላት ስለ ፕሮጀክቶች የስራ አፈጻጸም በየሶስት ወሩ የክትትልና ግምገማ ውጤት ሪፖርት እየተዘጋጀ ለሚ/ር መ/ቤቱ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ስለተገኘው የክትትልና የግምገማ ውጤት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በየሩብ ዓመቱና በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በአስፈጻሚ መ/ቤቶች እየተዘጋጀ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚቀርበውን የፕሮጀክቶች የሩብ ዓመት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የግምገማ እና የተጠቃለለ ሪፖርትና የግምገማ ውጤት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማይቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስለ ሁኔታው የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ የፕሮጀክት አስፈጻሚዎች የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የተጠቃለለ ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት በአሁኑ ወቅት የማይቀርብ መሆኑን፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት ላለው የፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ዴስክ የአፈጻጸም ሪፖርት ይቀርብና ከመ/ቤቶች ጋር ውይይት ይደረግበት እንደነበርና ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተቋረጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ የሪፖርቱ መቋረጥ የበላይ አካል በገንዘብና ኢኮኖሚ ል/ሚ/ር የተዘጋጀ እና የተገመገመ የፕሮጀክቶችን አጠቃላይ የሥራ ሂደት ሁኔታ የሚያውቅበት እና የሚከታተልበት መንገድ እንደሌለ የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪም ከፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለበላይ አካል ቀርቦ እልባት እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የገ/ኢ/ል/ሚ/ር ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርብለትን የፕሮጀክቶች የሩብ ዓመት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የግምገማ እና የተጠቃለለ ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ሆኖ ሳለና ተጠቃሚው ክፍል እንዳይላክ ሳይጠይቅ እንዲቋረጥ መደረጉ አግባብነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡” 

በመጨረሻም በሪፖርቱ ገፅ 36 ላይ ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርበው የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት ይዘት ወጥነት የሌለውና በፕሮጀክት ክትትል መመሪያው መሰረት ስላለመሆኑ የሚከተለውን ብሏል፦

“የፕሮጀክት ስፈጻሚዎች በጸደቀው የፕሮጀክት ሰነድ መሰረት፣ በፕሮጀክት የድርጊት መርሃ ግብር፣ በክትትልና ግምገማ መመሪያ እንዲሁም በሥምምነቶች መሠረት በትክክል የፕሮጀክቱን የስራ ሂደት፣ ግብዓት፣ ውጤት፣ ስኬት እንዲሁም የፕሮጀክቱን ፋይዳ (impact) በመከታተል በየ3 ወሩ ለ/ገ/ኢ/ል/ሚ/ር ሪፖርት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በኦዲቱ ወቅት እንደታየው፣ በዚህ የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት አቀራረብ በኩል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በጥሩ ተሞክሮ የሚገለጽ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የበጀት ባለሙያ ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ እና ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርቶች እንደተገነዘብነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መ/ቤት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ አመት ብቻ ሳይሆን በየወሩ ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሌሎች ሴክተሮች የሪፖርት አቀራረብ ሲታይ፣ ከጤና ሴክተር፣ ከትምህርት ሴክተር እና ከግብርና ሴክተር አስፈጻሚዎች ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚቀርበው የፕሮጀክት የፊዚካል እና የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት በሚ/ር መ/ቤቱ በተዘጋጀው የሪፖርት ማቅረቢያ ቅጽ (ፎርማት) መሰረት አለመሆኑ ታውቋል፡፡ የሚቀርበው ሪፖርትም በየሩብ አመቱ መሆን ሲገባው፣ በየ6 ወር ወይም በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡” 

​ኢትዮጲያ የእኔ ናት! ብሔር መብት የለውም! /ክፍል-3/

“John Locke” የተባለው ፈላስፋ “An Essay Concerning Human Understanding” በሚለው መፅሃፉ የሰው ልጅ ሁለት ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት እንዳሉት ይገልፃል። እነሱም፣ ማሰብ (Thinking) እና ፍቃድ (Will) ናቸው። በዚህ መሰረት፣ የሰው ልጅ በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል። በራስ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ደግሞ “ነፃነት” (Liberty) ይባላል። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። 
የሰው ልጅ ነፃነት ለሦስት ይከፈላል። እነሱም፣ 1ኛ፡- ሌላውን ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፣ … መብት። 2ኛ፡- በባዕድ መንግስት ወይም ለሌላ አካል ተገዢ ያለመሆን መብት፣ እና 3ኛ፡- ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት መብት ናቸው። በአማርኛ “መብት” (right) የሚለውን ቃል አንድ ሰው በአንድ ነገር ወይም ጉዳይ ላይ የሚፈልገውን ለማድረግ ሆነ ላለማድረግ የሚያስችለው ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት ሁሉን-አቀፍና ምሉዕ የሆነ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሲሆን መብት ደግሞ ነፃነትን የማስከበር “ስልጣን” (authority) ነው። 

ነፃነት ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል ወሳኝነት በነፃ-ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት እንደመሆኑ መጠን ከኃላፊነት ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለዚህ፣ ሕይወትን በነፃ ፍላጎትና ምርጫ ለመምራት የሚያስፈልገው ነፃነት የሚገኘው ለተግባራዊ እንቅስቃሴያችን “ኃላፊነት” (responsibility) መውሰድ ስንችል ነው። ከዚህ አንፃር፣ ጀርመናዊው ፈላስፋ “Nietzsche” “Only individuals have a sense of responsibility” ይላል። በመሆኑም፣ ኃላፊነት መውሰድ የሚችሉት ግለሰቦች (individuals) ብቻ ናቸው።

የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ሀገር” የሚለውን ቃል “በውስጡ ህዝቦች የሚኖሩበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት” እንደሆነ ይገልፃል። በተመሳሳይ፣ “ሉኣላዊ” (Sovereign) ማለት ደግሞ “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” እንደሆነ ይገልፃል። ስለዚህ፣ በተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሉዓላዊ ሀገር፥ መንግስት የሚመሰርቱት በነፃነት ለመኖር ነው። 

ስለ መንግስት አመሰራረት ከተፃፉት መፅሃፍት ውስጥ በ“Thomas Hobbes” የተፃፈው “Leviathan” የተሰኘው መፃሃፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። እንግሊዛዊ ፈላስፋ በተጠቀሰው መፅሃፍ ስለ መንግስት አመሰራረት እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ ትንታኔ ሰጥቶበታል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሉዓላዊ ሀገር የሚመሰርቱት በተፈጥሮ ካገኙት ነፃነት ላይ የተወሰነውን በውክልና ለመንግስት አሳልፈው በመስጠት እንደሆነ ይገልፃል። 

በዚህ መሰረት፣ መንግስት የሚመሰረተው የሁሉም ሰዎች መብትና ነፃነት እንዲከበር ነው። በመሆኑም ሁሉም ሰዎች የሌሎችን መብት ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር ለመስራት፥ ለመናገር፥ ለመፃፍ፣ እንዲሁም በባዕድ መንግስት ወይም ለሌላ ሦስተኛ አካል ቁጥጥር ስር እንዳይወድቁ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን “ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት መብትን” ለመንግስት አሳልፈው ይሰጣሉ። ይህ የውል ስምምነት ደግሞ በሕገ መንግስት አማካኝነት የሚከናወን ይሆናል። 

ሕገ-መንግስት በጥቅሉ በመንግስትና በሕዝብ መካከል የተደረሰ ስምምነት አይደልም። ከዚያ ይልቅ፣ “እያንዳንዱ” ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ የተስማሙበት ሰንድ ነው። በዚህ የውክልና ሰነድ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ በገቡት ውል መሰረት የሁሉም ሰዎች ነፃነት እኩል እንዲከበር እያንዳንዱ ሰው ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣኑን በውክልና ለመንግስት አሳልፎ ይሰጣል። ይህን “Thomas Hobbes” እንደሚከተለው ገልፆታል፡- 

 “This is more than consent, or concord; it is a real unity of them all in one and the same person, made by covenant of every man with every man, in such manner as if every man should say to every man: ‘I authorize and give up my right of governing myself to this assembly of men, on this condition; that you give up, your right to them, and authorize all their actions in like manner.’ This done, the multitude so united in one person is called a COMMONWEALTH… And he that carries this person is called sovereign, and said to have sovereign power;….” Leviathan, Part-II, CH. XVII, Para-13 

ከላይ በተገለፀው መሰረት ለመንግስት በውክልና የተሰጠው ስልጣን ከእያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ የተቀነሰ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት፥ ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ የመንግስት ሉዓላዊ ስልጣን ከእያንዳንዱ ሰው ላይ የተቀነሰ ነፃነት ወይም ራስን-በራስ የማስተዳደር ስልጣን ነው። በመሆኑም፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቱ እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ወይም ግለሰብ ነው። 

በኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት ግን የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን (sovereign power) ባለቤት እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። ከዚያ ይልቅ፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ በሕገ መንግስቱ ተገልጿል። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በራሳቸው ኃላፊነት (responsibility) መውሰድ አይችሉም። በመሆኑም፣ መብትና ነፃነት የላቸውም፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆኑ አይችሉም።     

አንድ ነገር ነፃነት እንዲኖረው በቅድሚያ እንደ ሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ሊኖረውና በራሱ ፍቃድና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የሌለው አካል በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መሰረት፤ መስራት፥ መናገር፥ መፃፍ…መብት፣ ያለገደብ ከቦታ-ቦታ የመንቀሳቀስ መብት፣ እንዲሁም ራሱን በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ይህ መብት እንዲኖረው በቅድሚያ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። 

እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ምክንያታዊ ፍጡር በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ ይችላል። ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤ የቋንቋ፥ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም የታሪክና ኢኮኖሚ ትስስር ውጤት ናቸው። በእርግጥ እያንዳንዱ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ የግለሰቦች ስብስብ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ግለሰብ በራሱ የሚመራበት ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የለውም። ምክንያቱም፣ ብሔር ልክ እንደ ግለሰብ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ የሚመራ ምክንያታዊ ፍጡራን አይደለም። 

በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ የማይችል አካል ደግሞ “ነፃነት” (Liberty) የለውም። በመሆኑም፣ በነፃ-ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት (right) የለውም። በመሰረቱ፣ መብት ወይም ስልጣን እንዲኖርህ በቅድሚያ የሚከበር ነፃነት ሊኖርህ ይገባል። ነፃነት የሌለው አካል ራስን-በራሱ የማስተዳደርና የመምራት ስልጣን ሊኖረው አይችልም።

ራስን-በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት አቅምና ስልጣን የሌለው አካል ለመንግስት በውክልና አሳልፎ የሚሰጠው ስልጣን የለውም። ማንኛውም ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መንቀሳቀስ ስለማይችል ነፃነት የለውም። በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። በመሆኑም፣ ራስን-በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት መብት የሌለው አካል ለመንግስት በውክልና አሳልፎ የሚሰጠው ስልጣን የለውም።  

የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ነው” የሚለው ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። የራሳቸው መብትና ነፃነት እስከሌላቸው ድረስ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ሊሆኑ አይችሉም። “የሕዝብ ሉዓላዊነት”ን የሚደነግገው የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 (1) “ኢትዮጲያዊያን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” ተብሎ መስተካከል አለበት። 

በአጠቃላይ፣ “ኢትዮጲያ የማን ናት?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “የእኔ ናት!” ነው። እኔ ምክንያታዊ ፍጡር ስለሆንኩ ነፃነት፥ መብትና ስልጣን አለኝ። ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በራሱ ነፃነት የለውም! መብት የለውም! ስልጣን የለውም! 

የኬኒያን ምርጫ እየተከታተሉ ኢትዮጵያን መታዘብ (የትነበርክ ታደለ – ጋዜጠኛና መምህር)

“ሀገራችንም ብሄራችንም ኬኒያ ናት። የምንፎካከረው ይህቺኑ ሀገር ለመለወጥ ነው እንጂ ለሌላ አይደለም። ስለዚህ ተቃዋሚም ሆንን ደጋፊ በጋራ መስራት ይኖርብናል። በውድድር አንዱ ማሸነፍ ሌላው መሸነፍ ያለ ቢሆንም ስላሸነፍናችሁ የምናጎድልባችሁ አንዳች ነገር አይኖርም። እኔ እጆቼን ወደ ተቀናቃኜም ሆነ ወደ ደጋፊዎቻቸው እዘረጋለሁ። ኑ ለሀገራችን በጋራ እንስራ!” – ለሁለተኛ ጊዜ የተመረጡት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ

….ከማክሰኞው የምርጫ እለት በኋላ ናይሮቢ አይኗን ጠራርጋ የነቃችው የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ማለዳ ወፍ ክንፉን ሳይታጠብ ብድግ ብለው “የምርጫውን ውጤት አንቀበልም፣ የተጭበረበረ ነው” ብለዋል በሚለው አስደንጋጭ ዜና ነበር።……. በዚህ ምክኒያት ላለፉት አራት ቀናት ከተማዋ ጸጥ ረጭ እንዳለች ቆየች።

አይኖች ሁሉ ወደ ቴሌቪዥን ቻናሎች አቅንተዋል። እውነታው ጎዳናው ላይ ሳይሆን የቴሌቪዥን ስክሪኖች ላይ ነው ያለው። ጎዳናውማ ሰው እንደናፈቀ አራት ቀኑ። ቴሌቪዢኖቹ ግን በየደቂቃው ዜና ያመነጫሉ።

ይህ የተጠበቀ ነበር።…….ከወራት በፊት ነው ናይሮቢያውያን ሱፐርማርኬቶችን ሲያጨናንቁ የከረሙት። “ምርጫው ደርሷል በጊዜ አስቤዛችሁን ሸማምቱ!” የሚለው መልእክት የሁሉም ነበር።……. ምርጫው ምን ይዞ እንደሚመጣ አይታወቅማ!

…….ዛሬ ዛሬ ለአፍሪካውያን ምርጫ የሚሉት የስልጣን ማሸጋገሪያ ስርአት የጦርነት ያህል አስፈሪና የብዙዎችን ህይወት ለሞት፤ ገሚሱን ለእስር እንዲሁም ለስደት የሚዳርግ እየሆነ ነው፡፡

አንድ አፍሪካዊት ሀገር ምርጫ ልታካሂድ ነው ሲባል ስጋት፣ ፍርሀት፣ ሽሽት፣ ጭንቀት ይነግሳል። ህዝብ ያልፈለገው ተቃዋሚ “እንዴት ሆኖ!” ሲል በአደባባይ ይፈክራል። ወንበር የያዘውም “ማን ባቀናው?” በሚል ንፉግነት የምርጫ ውጤቱን ወደ ጎን ገፍቶ የራሱን ሌላ መንገድ ይከተላል። በዚህም ሰበብ በሚነሳ ግጭት ተራው ህዝብ ለሞት ይዳረጋል።

አሁን መላ ኬኒያውያን ተሸብረዋል።……ዜናው ይቀጥላል። የተቃዋሚው ሁነኛ መሰረት የሆኑት በናይሮቢ የሚታወቀው “ኪቢራ” የተባለው መንደርና የ”ኪሱሙ” ክፍለ ግዛት ረብሽ ተነስቷል።…….. በተለይ ደግሞ የተቃዋሚው ደጋፊዎች “ራይላ ከሌለ ሰላም የለም!” የሚለው መፈክር ከተሰማ በኋላ ነገሩ እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ እንዳልሆነ ተገምቷል።

ሚዲያ ለሰላምና መረጋጋት

……ይህ በሚሆንበት ወቅት ሁሉ የኬኒያ ሚዲያዎች በምርጫ ኮሚሽኑ አዳራሽ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሁነት በቀጥታ ስርጭት እንዲሁም ተቃዋሚዎች የሚሰጡትን መግለጫዎች በሰበር ዜና እግር ከእግር እየተከታተሉ ለህዝብ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል። ….ጣቢያዎቹ የሙሉ ሰአት የዜና እወጃቸውን ሙሉ በሙሉ ሰርዘዋል። ህዝብ ለመረጃ ጆሮውን አቁሞ ሳለ ለዜና እንዴት ሰአት ይጠበቃል?

…… የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን….ወዘተ የሚሰጡት መግለጫና ማብራሪያ ሁሉ በየደቂቃው ለህዝብ ጆር ይደርሳል።……..የምርጫ ኮሚሽኑ ከአስር በላይ ጊዜ ለህዝብ መረጃዎችን ሲያቀርብ ጋዜጠኞች ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከህዝብ የሰበሰቧቸውን ጥያቄዎችና ስጋቶች ለምርጫ ኮሚሽኑ እያቀረቡ ምላሽ እንዲሰጥባቸው አድርገዋል።……

….. በአንዳንድ ቦታ ለታዩት የተቃውሞ ድምጾችም የጸጥታ ሀላፊው “በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞዋችሁን ማሰማት በህገ መንግስቱ የተፈቀደላችሁ መብት ነው።……” በማለት ዜጎች ከግጭት ይልቅ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማንኛውንም የተቃውሞ ስሜታቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።…በዚህም ምክኒያት የኬኒያ ሰላም በፍጥነት ወደ ቦታው ተመልሷል።

ኬኒያውያን ከዘር አስተሳሰብ ይልቅ ወደ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ከፍ ማለትን ያመላከተው የኡሁሩና የኦዲንጋ ውጤት በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ፖለቲካ የሚባለው (ሀገር የማስተዳደር ጥበብ) የሚዘወረው በፖለቲከኞቹ ዘር (ብሄር)( የት-መጤነት) መሰረት ያደረገ ነው። ፖለቲከኞቹም በሚያቀርቡት የፖለቲካ መርህ፣ የጠራ ፖሊሲ ወይም የፖለቲካ ብስለት ይልቅ በህዝቦች መካለከል ያለውን (Group thinking, Group identity) መጠቀሚያ ያደርጉታል።……. ህዝቡንም “ምን ይዞልን መጣ?” ሳይሆን “ማን መጣ?” በሚል ጥያቄ ወደ ምርጫ ጣቢያ ይልኩታል።

….በዚህ ደግሞ ሁሌም እንደ ምሳሌ ስትነሳ የኖረችው ሀገረ ኬኒያ ናት። የኬኒያ ፖለቲካ በዘር አስተሳሰብ (Race thinking) እንደሆነ ይነገራል።…በዚህ የ2017 ሀገራዊ ምርጫ ግን (በኔ እይታ) ኬኒያውያን ጥያቄያቸው “ማን ነው?” ሳይሆን “ምንድነው?” የሚል እንደሆነ በምርጫ ድምጻቸው አሳይተዋል። ለተፎካካሪዎቹ የተሰጡት ድምጾች እንደሚያመለክቱት ሁለቱም የኔ ከሚሉት ጎሳ የተወሰኑ ድምጾችን እንዳጡና እንዲሁም ባልጠበቁባቸው ስፍራዎች የተሻለ ድምጾችን መሰብሰባቸው ነው።

..ዛሬ እለተ እሁድ ከቀኑ ስድስት ሰአት ሙዋንጊ ቲካ ሮድ በሚባለው (high way) እያሳበረ ወደ (Down-town) አሳፍሮኝ እየነዳ ነው።…… ሙዋንጊ ናይሮቢ ከገባሁ ጀምሮ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጠኝ ሾፌር ሲሆን ሰው ካልጠየቀው በስተቀር የማያወራ ዝምተኛ ሰው ነው።…… ላወራው ፈልግያለሁ።…..

“What is your opinion? ስለምርጫው ምን ታስባለህ?” አልኩት።…… “You know, election comes and go but Kenya, ምርጫ ይመጣል ይሄዳል። ከኒያ ግን ሁሌም ትኖራለች።” አለኝና ዝም አለ…….

“About the result?” ትንሽ ገፋ አድርጌው የልቡን እንዲያወራኝ ፈለኩ። “ውጤቱን እንዴት አገኘሀው?” …….. “You know, there is always another day, another chance…” ሙዋንጊ የመረጠውን እንዳላገኘ አውቅያለሁ። ነገር ግን ደግሞ ያልመረጠውን እንደተቀበለና ለነገው ደግሞ ተስፋ እንዳለው አነጋገሩ ይናገራል።…….

የኬኒያ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበር?

ይህ ጥያቄ ሊመለስ የሚገባው “ከማን ጋር ሲነጻጸር?” የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ ነው። ከየትኛው ሀገር ምርጫ ጋር ሲነጸጸር ነው ኬኒያውያንን እና የኬኒያን የመንግስት መዋቅር ማመስገን የሚገባው?

እንደ አንድ የሌላ አፍሪካ ሀገር ታዛቢ ስመለከተው …..ይህ ሁሉ የምርጫ ታዛቢ፣ ይህ ሁሉ ገለልተኛ የሚዲያ ተቋም፣ ይህ ሁሉ የአደባባይ ላይ መረጃ፣ እንዲህ ያለ ትእግስተኛና መፍትሄ አፈላላጊ ፖሊስና መከላከያ፣ ይህ ሁሉ ……. የትኛው የአፍሪካ ሀገር ነው ያለው? ከዚህ የተሻለ ያለው ሀገር ያለ እንደሆን ያኔ ስለ ኬኒያ ምርጫ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት እናወራ ይሆናል! እስከዚያ ግን ብልህ ከጎረቤቱ ይማራልና ከዚህ ሁሉ አንዱም የሌለን እኛ ልክ እንደ ጀማሪ፣ ዛሬ እንደተሰራ ሀገር፣ ሶስት ሺህ አመታት መንግስት እንዳላየን ከባለ ሀምሳ አመት እድሜዋ ኬኒያ እንማራለን!! እናም የኬኒያ 2017 ህዝባዊ ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ ነበር!!!
Asanteni Sana!! ካሪቡ ኬኒያ!!
ተፈጸመ!-

​ኢትዮጲያ የማን ናት? መብቱ የዜጎች፣ ስልጣኑ የብሔሮች ነው! /ክፍል-2/

“ኢትዮጲያ የማን ናት፡ የብሔሮች ወይስ የዜጎች?” በሚል ርዕስ ባወጣነው የመጀመሪያ ክፍል የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ፍፁም አምባገነን እየሆነ መምጣቱን ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ውስጥ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው መርህ ላይ መንጠልጠሉና በዚህም ራሱ የዘረጋውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ቀልብሶታል።  
በመሰረቱ፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው ሕገ-መንግስታዊ መርህ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። ሌላው ቀርቶ ከሕገ-መንግስቱ ጋር ራሱ ይጋጫል። በአጠቃላይ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ “ፀረ-ዴሞክራሲያዊ” ነው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ-ደግፍ” እንዲሉ መንግስታዊ ስርዓቱ ደግሞ በዚህ መርህ ላይ እንደመሆኑ ሕገ-መንግስቱ፥ ብሎም ፖለቲካዊ ስርዓት ካልተቀየረ በስተቀር ዴሞክራሲ “ላም አለኝ በሰማይ…” እንደሚሉት ሆኖ ይቀራል። በዚህ ፅሁፍ፣ “ከሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ አንፃር የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ እንመለከታለን። በቀጣይ ክፍል ደግሞ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት አንፃር የተሳሳተ መሆኑን እንመለከታለን።    

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው”።ነገር ግን፣ ይህ መርህ ከሉዓላዊነት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። በዚህ ረገድ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ በግልፅ ለመረዳት እንዲያስችለን የሕገ-መንግስቱን የቃላት አጠቃቀም እና የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀውን የኣማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት በማድረግ ፅንሰ-ሃሳቡን በዝርዝር እንመለከታለን። 

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(5) መሰረት “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ባህሪይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምን፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር “ማህብረሰብ” ነው። (የቃላት ድግግሞሽን ለማስቀረት ሲባል እንደየሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” የሚለው “ብሔር” ተብሎ ሊፃፍ ይችላል።) በዚህ መሰረት፣ ብሔር በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም በታሪክ፣ ኢኮኖሚና በመልክዓ ምድር የተሳሰረ ማህብረሰብ ነው። በመሆኑም፣ የብሔር መብቶች ከእነዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 39 ላይ “የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት” በሚል የተጠቀሱት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይህን ያመለክታሉ። 

መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተደነገጉበት የሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት መሰረት፣ በንዑስ አንቀፅ 39(1) “ማንኛውም ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(2) “ማንኛውም ብሔር በቋንቋው የመናገር፥ የመፃፍ፥ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ፥ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(3) ደግሞ “ማንኛውም ብሔር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት” እንዳለው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሕገ-መንግስቱ ንዑስ አንቀፅ 40(3) መሰረት “የመሬት ባለቤትነት መብት”፣ እንዲሁም በንዑስ አንቀፅ 43(1) መሰረት ደግሞ “የልማት መብት” እንዳላቸው ይጠቅሳል። 

በዋናነት በሕገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከዚህ በተረፈ፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ ስር የተዘረዘሩት በሙሉ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው። በክፍል ሁለት ከተዘረዘሩት ውስጥ ከአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) በስተቀር ያሉት በሙሉ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ግን እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ከላይ የተጠቀሱት የብሔር መብቶች ይኖሩታል።

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሉኣላዊ” (Sovereign) የሚለውን ቃል “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። “ሉዓላዊነት” (Sovereignity) ማለት ደግሞ “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” እንደሆነ ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” የሆነ አካል በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል።     

በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሙሉ መሰረታዊ የግለሰብ መብትና ነፃነት ሊሆኑ ይችላሉ። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ግን በአንቀፅ 39፣ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት መብቶች ብቻ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ግለሰብ ምሉዕ መብትና ነፃነት አለው። በተቃራኒው አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ግን ምሉዕ መብትና ነፃነት የለውም። 

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንተሞከረው፣ “ሉኣላዊነት” (Sovereignity) ማለት “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሉዓላዊ ስልጣን እንዲኖረው በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍለ አንድና ሁለት ስር ከተዘረዘሩት 31 መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት የሆኑት በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውጪ ያሉት በሙሉ የግለሰብ መብቶች ናቸው። 

እያንዳንዱ ግለሰብ በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት የብሔር መብቶች እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ይኖሩታል። እያንዳንዱ ብሔር ግን በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) ከተጠቀሱት ውጪ ሌላ ዴሞክራሲያዊ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እንደ ግለሰብ በራሱ ሃሳብና አመለካከት የሚንቀሳቀስ ምክንያታዊ ፍጡር ስላልሆነ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሉትም። በተመሳሳይ፣ እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ስላልሆነ “ሰብዓዊ” መብት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ በሕገ-መንግስቱ ራሱ ምሉዕ መብት ያለው ግለሰብ እንጂ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አይደለም። 

በአጠቃላይ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችለው እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ እንጂ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች አይደሉም። ምክንያቱም፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት በምዕራፍ ሦስት ስር ከዘረዘራቸው 31 መሰረታዊ መብቶች ውስጥ ሦስት መብቶች ብቻ ያሏቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች “የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” እንደሆኑ ይገልፃል። ነገር ግን፣ “ሉኣላዊነት” የምሉዕ መብትና ነፃነት ባለቤትነት እንደመሆኑ መጠን ውስን መብት ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ሊኖራቸው አይችልም። በዚህ መሰረት፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ በግልፅ መረዳት ይቻላል። 

በመጨረሻም፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ምሉዕ የሆነ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አለው። በዚህ መሰረት፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችሉት ሁሉም ኢትዮጲያዊያን ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ ተደንግጓል። ስለዚህ፣ ሕገ-መንግስቱ እርስ-በእርስ እንዲጋጭ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው? 

በመሰረቱ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ባለመብት ብቻ ሳይሆን ባለስልጣን ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ሉዓላዊ ስልጣን ያለው አካል በሀገሪቱ መንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። ስለዚህ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተጠሪነቱ ለዚህ አካል ይሆናል። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት፤ የሀገሪቱ ዜጎች መብትና ነፃነት አላቸው፣ ብሔሮች ደግሞ የሉዓላዊ ስልጣን አላቸው። ዜጎች ምሉዕ መብት አላቸው፣ ነገር ግን መብታቸውን የመጠየቅ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን የላቸውም። ብሔሮች ደግሞ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን አላቸው፣ የሚጠይቁት ምሉዕ መብት ግን የላቸውም። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት መብቱ የዜጎች ሲሆን ስልጣኑ ግን የብሔሮች ነው! 

በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ ዜጎች የማይጠይቁት መብት ሲኖራቸው፣ የሀገሪቱ ብሔሮች ደግሞ የማይጠቀሙት ስልጣን አላቸው። የኢህአዴግ መንግስት ዘወትር ስለ ብሔር መብትና እኩልነት ይደሰኩራል። ዜጎች የመብትና እኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ ግን እንደ ጠላት እያደነ ያስራል፥ ይገድላል፥…ወዘተ።