Category Archives: ብሔርተኝነት

​ኢትዮጲያ የእኔ ናት! ብሔር መብት የለውም! /ክፍል-3/

“John Locke” የተባለው ፈላስፋ “An Essay Concerning Human Understanding” በሚለው መፅሃፉ የሰው ልጅ ሁለት ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት እንዳሉት ይገልፃል። እነሱም፣ ማሰብ (Thinking) እና ፍቃድ (Will) ናቸው። በዚህ መሰረት፣ የሰው ልጅ በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል። በራስ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ደግሞ “ነፃነት” (Liberty) ይባላል። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። 
የሰው ልጅ ነፃነት ለሦስት ይከፈላል። እነሱም፣ 1ኛ፡- ሌላውን ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፣ … መብት። 2ኛ፡- በባዕድ መንግስት ወይም ለሌላ አካል ተገዢ ያለመሆን መብት፣ እና 3ኛ፡- ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት መብት ናቸው። በአማርኛ “መብት” (right) የሚለውን ቃል አንድ ሰው በአንድ ነገር ወይም ጉዳይ ላይ የሚፈልገውን ለማድረግ ሆነ ላለማድረግ የሚያስችለው ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት ሁሉን-አቀፍና ምሉዕ የሆነ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሲሆን መብት ደግሞ ነፃነትን የማስከበር “ስልጣን” (authority) ነው። 

ነፃነት ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል ወሳኝነት በነፃ-ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት እንደመሆኑ መጠን ከኃላፊነት ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለዚህ፣ ሕይወትን በነፃ ፍላጎትና ምርጫ ለመምራት የሚያስፈልገው ነፃነት የሚገኘው ለተግባራዊ እንቅስቃሴያችን “ኃላፊነት” (responsibility) መውሰድ ስንችል ነው። ከዚህ አንፃር፣ ጀርመናዊው ፈላስፋ “Nietzsche” “Only individuals have a sense of responsibility” ይላል። በመሆኑም፣ ኃላፊነት መውሰድ የሚችሉት ግለሰቦች (individuals) ብቻ ናቸው።

የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ሀገር” የሚለውን ቃል “በውስጡ ህዝቦች የሚኖሩበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት” እንደሆነ ይገልፃል። በተመሳሳይ፣ “ሉኣላዊ” (Sovereign) ማለት ደግሞ “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” እንደሆነ ይገልፃል። ስለዚህ፣ በተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሉዓላዊ ሀገር፥ መንግስት የሚመሰርቱት በነፃነት ለመኖር ነው። 

ስለ መንግስት አመሰራረት ከተፃፉት መፅሃፍት ውስጥ በ“Thomas Hobbes” የተፃፈው “Leviathan” የተሰኘው መፃሃፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። እንግሊዛዊ ፈላስፋ በተጠቀሰው መፅሃፍ ስለ መንግስት አመሰራረት እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ ትንታኔ ሰጥቶበታል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሉዓላዊ ሀገር የሚመሰርቱት በተፈጥሮ ካገኙት ነፃነት ላይ የተወሰነውን በውክልና ለመንግስት አሳልፈው በመስጠት እንደሆነ ይገልፃል። 

በዚህ መሰረት፣ መንግስት የሚመሰረተው የሁሉም ሰዎች መብትና ነፃነት እንዲከበር ነው። በመሆኑም ሁሉም ሰዎች የሌሎችን መብት ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር ለመስራት፥ ለመናገር፥ ለመፃፍ፣ እንዲሁም በባዕድ መንግስት ወይም ለሌላ ሦስተኛ አካል ቁጥጥር ስር እንዳይወድቁ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን “ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት መብትን” ለመንግስት አሳልፈው ይሰጣሉ። ይህ የውል ስምምነት ደግሞ በሕገ መንግስት አማካኝነት የሚከናወን ይሆናል። 

ሕገ-መንግስት በጥቅሉ በመንግስትና በሕዝብ መካከል የተደረሰ ስምምነት አይደልም። ከዚያ ይልቅ፣ “እያንዳንዱ” ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ የተስማሙበት ሰንድ ነው። በዚህ የውክልና ሰነድ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ በገቡት ውል መሰረት የሁሉም ሰዎች ነፃነት እኩል እንዲከበር እያንዳንዱ ሰው ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣኑን በውክልና ለመንግስት አሳልፎ ይሰጣል። ይህን “Thomas Hobbes” እንደሚከተለው ገልፆታል፡- 

 “This is more than consent, or concord; it is a real unity of them all in one and the same person, made by covenant of every man with every man, in such manner as if every man should say to every man: ‘I authorize and give up my right of governing myself to this assembly of men, on this condition; that you give up, your right to them, and authorize all their actions in like manner.’ This done, the multitude so united in one person is called a COMMONWEALTH… And he that carries this person is called sovereign, and said to have sovereign power;….” Leviathan, Part-II, CH. XVII, Para-13 

ከላይ በተገለፀው መሰረት ለመንግስት በውክልና የተሰጠው ስልጣን ከእያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ የተቀነሰ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት፥ ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ የመንግስት ሉዓላዊ ስልጣን ከእያንዳንዱ ሰው ላይ የተቀነሰ ነፃነት ወይም ራስን-በራስ የማስተዳደር ስልጣን ነው። በመሆኑም፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቱ እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ወይም ግለሰብ ነው። 

በኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት ግን የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን (sovereign power) ባለቤት እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። ከዚያ ይልቅ፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ በሕገ መንግስቱ ተገልጿል። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በራሳቸው ኃላፊነት (responsibility) መውሰድ አይችሉም። በመሆኑም፣ መብትና ነፃነት የላቸውም፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆኑ አይችሉም።     

አንድ ነገር ነፃነት እንዲኖረው በቅድሚያ እንደ ሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ሊኖረውና በራሱ ፍቃድና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የሌለው አካል በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መሰረት፤ መስራት፥ መናገር፥ መፃፍ…መብት፣ ያለገደብ ከቦታ-ቦታ የመንቀሳቀስ መብት፣ እንዲሁም ራሱን በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ይህ መብት እንዲኖረው በቅድሚያ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። 

እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ምክንያታዊ ፍጡር በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ ይችላል። ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤ የቋንቋ፥ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም የታሪክና ኢኮኖሚ ትስስር ውጤት ናቸው። በእርግጥ እያንዳንዱ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ የግለሰቦች ስብስብ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ግለሰብ በራሱ የሚመራበት ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የለውም። ምክንያቱም፣ ብሔር ልክ እንደ ግለሰብ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ የሚመራ ምክንያታዊ ፍጡራን አይደለም። 

በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ የማይችል አካል ደግሞ “ነፃነት” (Liberty) የለውም። በመሆኑም፣ በነፃ-ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት (right) የለውም። በመሰረቱ፣ መብት ወይም ስልጣን እንዲኖርህ በቅድሚያ የሚከበር ነፃነት ሊኖርህ ይገባል። ነፃነት የሌለው አካል ራስን-በራሱ የማስተዳደርና የመምራት ስልጣን ሊኖረው አይችልም።

ራስን-በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት አቅምና ስልጣን የሌለው አካል ለመንግስት በውክልና አሳልፎ የሚሰጠው ስልጣን የለውም። ማንኛውም ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መንቀሳቀስ ስለማይችል ነፃነት የለውም። በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። በመሆኑም፣ ራስን-በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት መብት የሌለው አካል ለመንግስት በውክልና አሳልፎ የሚሰጠው ስልጣን የለውም።  

የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ነው” የሚለው ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። የራሳቸው መብትና ነፃነት እስከሌላቸው ድረስ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ሊሆኑ አይችሉም። “የሕዝብ ሉዓላዊነት”ን የሚደነግገው የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 (1) “ኢትዮጲያዊያን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” ተብሎ መስተካከል አለበት። 

በአጠቃላይ፣ “ኢትዮጲያ የማን ናት?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “የእኔ ናት!” ነው። እኔ ምክንያታዊ ፍጡር ስለሆንኩ ነፃነት፥ መብትና ስልጣን አለኝ። ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በራሱ ነፃነት የለውም! መብት የለውም! ስልጣን የለውም! 

​ኢትዮጲያ የማን ናት? መብቱ የዜጎች፣ ስልጣኑ የብሔሮች ነው! /ክፍል-2/

“ኢትዮጲያ የማን ናት፡ የብሔሮች ወይስ የዜጎች?” በሚል ርዕስ ባወጣነው የመጀመሪያ ክፍል የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ፍፁም አምባገነን እየሆነ መምጣቱን ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ውስጥ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው መርህ ላይ መንጠልጠሉና በዚህም ራሱ የዘረጋውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ቀልብሶታል።  
በመሰረቱ፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው ሕገ-መንግስታዊ መርህ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። ሌላው ቀርቶ ከሕገ-መንግስቱ ጋር ራሱ ይጋጫል። በአጠቃላይ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ “ፀረ-ዴሞክራሲያዊ” ነው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ-ደግፍ” እንዲሉ መንግስታዊ ስርዓቱ ደግሞ በዚህ መርህ ላይ እንደመሆኑ ሕገ-መንግስቱ፥ ብሎም ፖለቲካዊ ስርዓት ካልተቀየረ በስተቀር ዴሞክራሲ “ላም አለኝ በሰማይ…” እንደሚሉት ሆኖ ይቀራል። በዚህ ፅሁፍ፣ “ከሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ አንፃር የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ እንመለከታለን። በቀጣይ ክፍል ደግሞ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት አንፃር የተሳሳተ መሆኑን እንመለከታለን።    

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው”።ነገር ግን፣ ይህ መርህ ከሉዓላዊነት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። በዚህ ረገድ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ በግልፅ ለመረዳት እንዲያስችለን የሕገ-መንግስቱን የቃላት አጠቃቀም እና የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀውን የኣማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት በማድረግ ፅንሰ-ሃሳቡን በዝርዝር እንመለከታለን። 

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(5) መሰረት “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ባህሪይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምን፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር “ማህብረሰብ” ነው። (የቃላት ድግግሞሽን ለማስቀረት ሲባል እንደየሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” የሚለው “ብሔር” ተብሎ ሊፃፍ ይችላል።) በዚህ መሰረት፣ ብሔር በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም በታሪክ፣ ኢኮኖሚና በመልክዓ ምድር የተሳሰረ ማህብረሰብ ነው። በመሆኑም፣ የብሔር መብቶች ከእነዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 39 ላይ “የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት” በሚል የተጠቀሱት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይህን ያመለክታሉ። 

መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተደነገጉበት የሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት መሰረት፣ በንዑስ አንቀፅ 39(1) “ማንኛውም ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(2) “ማንኛውም ብሔር በቋንቋው የመናገር፥ የመፃፍ፥ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ፥ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(3) ደግሞ “ማንኛውም ብሔር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት” እንዳለው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሕገ-መንግስቱ ንዑስ አንቀፅ 40(3) መሰረት “የመሬት ባለቤትነት መብት”፣ እንዲሁም በንዑስ አንቀፅ 43(1) መሰረት ደግሞ “የልማት መብት” እንዳላቸው ይጠቅሳል። 

በዋናነት በሕገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከዚህ በተረፈ፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ ስር የተዘረዘሩት በሙሉ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው። በክፍል ሁለት ከተዘረዘሩት ውስጥ ከአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) በስተቀር ያሉት በሙሉ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ግን እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ከላይ የተጠቀሱት የብሔር መብቶች ይኖሩታል።

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሉኣላዊ” (Sovereign) የሚለውን ቃል “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። “ሉዓላዊነት” (Sovereignity) ማለት ደግሞ “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” እንደሆነ ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” የሆነ አካል በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል።     

በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሙሉ መሰረታዊ የግለሰብ መብትና ነፃነት ሊሆኑ ይችላሉ። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ግን በአንቀፅ 39፣ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት መብቶች ብቻ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ግለሰብ ምሉዕ መብትና ነፃነት አለው። በተቃራኒው አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ግን ምሉዕ መብትና ነፃነት የለውም። 

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንተሞከረው፣ “ሉኣላዊነት” (Sovereignity) ማለት “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሉዓላዊ ስልጣን እንዲኖረው በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍለ አንድና ሁለት ስር ከተዘረዘሩት 31 መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት የሆኑት በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውጪ ያሉት በሙሉ የግለሰብ መብቶች ናቸው። 

እያንዳንዱ ግለሰብ በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት የብሔር መብቶች እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ይኖሩታል። እያንዳንዱ ብሔር ግን በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) ከተጠቀሱት ውጪ ሌላ ዴሞክራሲያዊ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እንደ ግለሰብ በራሱ ሃሳብና አመለካከት የሚንቀሳቀስ ምክንያታዊ ፍጡር ስላልሆነ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሉትም። በተመሳሳይ፣ እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ስላልሆነ “ሰብዓዊ” መብት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ በሕገ-መንግስቱ ራሱ ምሉዕ መብት ያለው ግለሰብ እንጂ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አይደለም። 

በአጠቃላይ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችለው እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ እንጂ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች አይደሉም። ምክንያቱም፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት በምዕራፍ ሦስት ስር ከዘረዘራቸው 31 መሰረታዊ መብቶች ውስጥ ሦስት መብቶች ብቻ ያሏቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች “የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” እንደሆኑ ይገልፃል። ነገር ግን፣ “ሉኣላዊነት” የምሉዕ መብትና ነፃነት ባለቤትነት እንደመሆኑ መጠን ውስን መብት ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ሊኖራቸው አይችልም። በዚህ መሰረት፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ በግልፅ መረዳት ይቻላል። 

በመጨረሻም፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ምሉዕ የሆነ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አለው። በዚህ መሰረት፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችሉት ሁሉም ኢትዮጲያዊያን ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ ተደንግጓል። ስለዚህ፣ ሕገ-መንግስቱ እርስ-በእርስ እንዲጋጭ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው? 

በመሰረቱ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ባለመብት ብቻ ሳይሆን ባለስልጣን ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ሉዓላዊ ስልጣን ያለው አካል በሀገሪቱ መንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። ስለዚህ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተጠሪነቱ ለዚህ አካል ይሆናል። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት፤ የሀገሪቱ ዜጎች መብትና ነፃነት አላቸው፣ ብሔሮች ደግሞ የሉዓላዊ ስልጣን አላቸው። ዜጎች ምሉዕ መብት አላቸው፣ ነገር ግን መብታቸውን የመጠየቅ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን የላቸውም። ብሔሮች ደግሞ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን አላቸው፣ የሚጠይቁት ምሉዕ መብት ግን የላቸውም። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት መብቱ የዜጎች ሲሆን ስልጣኑ ግን የብሔሮች ነው! 

በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ ዜጎች የማይጠይቁት መብት ሲኖራቸው፣ የሀገሪቱ ብሔሮች ደግሞ የማይጠቀሙት ስልጣን አላቸው። የኢህአዴግ መንግስት ዘወትር ስለ ብሔር መብትና እኩልነት ይደሰኩራል። ዜጎች የመብትና እኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ ግን እንደ ጠላት እያደነ ያስራል፥ ይገድላል፥…ወዘተ።  

​ኢትዮጲያ የማን ናት? የብሔሮች ወይስ የዜጎች: ክፍል-1 

ከዴሞክራሲ ቅፅበት ወደ አምባገነናዊ ፅልመት በ10 አመት
ከድጋፍና ተቃውሞ ባሻገር ሁላችንም የኢህአዴግ መንግስት የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥንቃቄ ማጤንና ማወቅ ይኖርብናል። ተወደደም-ተጠላ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው። በመሆኑም፣ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ባህሪ ማወቅ አለባቸው። ምክንያቱም፣ አላዋቂ ደጋፊ መንግስትን ለውድቀት ይዳርጋል። አላዋቂ ተቃዋሚ ደግሞ የለውጥ እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ፣ ሁላችንም “የተወሰነም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ለምን ተመልሶ አምባገነን ሆነ?” ብለን መጠየቅ አለብን። 

በእርግጥ “እንዴ…ለመሆኑ የኢህአዴግ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ሞክሮ ያውቃል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። “ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ጥሩ ነው” ይባላል። የኢህአዴግ መንግስትም ቢያንስ በ1987 ዓ.ም ባፀደቀው ሕገ-መንግስት እና በ1997ቱ ምርጫ (እስከ ምርጫው ዕለት ማታ ድረስ) ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ማድረጉ ሊታወስ ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ከ1997 ዓ.ም በፊት “ሕገ-መንግስቱ ይከበር!” ሲል የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በቀጣይ አስር አመታት ግን ሕገ-መንግስቱን የሚጥሰው እሱ ራሱ ሆነ። 

የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% “አሸነፍኩ” ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው። የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል። 

የኢህአዴግ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል። 

በአጠቃላይ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ የታየው የዴሞክራሲ ቅፅበት ከአስር አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ በአምባገነናዊ ፅልመት ተውጧል። በተለይ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተዘረዘሩት አብዛኞቹ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተጥሰዋል። በተደጋጋሚ ጥሰት ከተፈፀመባቸው ውስጥ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 14፥ 15፥ 16፥ 17፥ 18፥ 19፥ 20፥ 21፥ 25፥ 26፥ 27፥ እና 28 ላይ የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም በአንቀፅ፡- 29፥ 30፥ 31፥ 37፥ 38፥ 40 እና 44 ላይ የተደነገጉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። 

“የሕዝብ ሉዓላዊነት” ወይስ “የብሔር ሉዓላዊነት”?

በመሰረቱ የኢሀአዴግ መንግስት እንደ መንግስት የተቋቋመው እነዚህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር ነበር። ይሁን እንጂ፣ እነዚህን መብቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጥሰው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ነው። ታዲያ፣ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተደጋጋሚ የሚጣሱበት ምክንያት ምንድነው? የኢህአዴግ መንግስት ለምን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር እንደተሳነው ለማወቅ በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት መንግስታዊ ስርዓቱ የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል። 

ማንኛውም ሰው በራሱ አመለካከት ትክክል የመሰለውን ነገር ያደርጋል። ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግን ከግል አመለካከታቸው ባለፈ ሥራና ተግባራቸው የሚመራበት ፖሊሲ፥ መርህና መመሪያ አላቸው። ለእነዚህ ደግሞ ዋና መሰረታቸው ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግስት ነው። ምክንያቱም፣ የመንግስት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። 

በእርግጥ አምባገነናዊም ሆኑ ዴሞክራሲያዊ መንግስታት በሕገ-መንግስታቸው ውስጥ፤ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የሕግ-የበላይነት፣ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ የዜጎች መብትና ነፃነት፣…ወዘተ የሚሉ መሰረታዊ መርሆች አሏቸው። ነገር ግን፣ በተለይ አምባገነን መንግስታት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማረጋገጥ በሚል ሰበብ የዜጎችን መብትና ነፃነት ሲጥሱ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ሀገሪቷንና ሕዝቡን ሲያስተዳድር የነበረው የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚገድቡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ነው። 

ባለፉት አስር አመታት የታየው የኢህአዴግ መንግስት አስተዳደር ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ተፃራሪ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለምሳሌ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 12 መሰረት “የመንግስት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት አለ” እንዳይባል ባለፉት አስር አመታት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ምን ያህል እንደተንሰራፋ መንግስት ራሱ ጠንቅቆ ያውቃል። በአንቀፅ፡-11 መሰረት “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም” እንዳይባል በቅርቡ በእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና በደል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። እንደ ማዕከላዊና ቅሊንጦ ባሉ እስር ቤቶች በፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣…ወዘተ ላይ የሚፈፀመውን የስቃይ ምርመራና እንግልት የሚያውቅ በአንቀፅ፡-10 መሰረት “የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በጭራሽ እንዳልተከበረ ይመሰክራል። በመጨረሻም፣ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፀረ-ሽብር አዋጁ እየተዳኘ ባለበት ሁኔታ በአንቀፅ፡-9 መሰረት “የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ተረጋግጧል” ሊባል አይቻልም። 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከሕገ-መንግስቱ አምስት (5) መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አራቱን ተግባራዊ እያደረገ እንዳልሆነ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡-8 ላይ የተጠቀሰውን “የሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ ግን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። በእርግጥ በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው የሕዝብን የስልጣን የበላይነት አያሳይም። ከዚያ ይልቅ፣ በንዑስ አንቀፅ 8(1) ላይ እንደተገለፀው፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መሰረታዊ መርህ፤ “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው” በሚል ተገልጿል። ቀጥሎ ባለው ንዑስ አንቀፅ 8(2) ደግሞ ሕገ-መንግስቱ (የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች) ሉዓላዊነት መገለጫ” እንደሆነ ይገልፃል። 

በሕገ-መንግስቱ መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተግባር “የብሔር ሉዓላዊነት” ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች” እንጂ የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። በእርግጥ ይህ መርህ ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ጋር ይጋጫል። በመሆኑም፣ ባለፉት አሰር አመታት ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ከመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት፣ ከሕገ-መንግስቱ የበላይነት አንፃር ለተፈጠሩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ዋና መነሻ ምክኒያት ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከላይ የተጠቀሰው መርህ በሕገ-መንግስቱ ከተጠቀሱት መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር ይጣረሳል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት ይህን መርህ ለመከተል ጥረት ባደረገ ቁጥር የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ይጥሳል። በአጠቃላይ፣ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ዴሞክራሲ እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ለቅፅበት ታይቶ እንዲጠፋነና በምትኩ አምባገነናዊ ፅልመት የሰፈነው የኢህአዴግ መንግስት ከሌሎች የዴሞክራሲ መርሆች ይልቅ ይሄን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከሩ ምክንያት ነው። 

ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነሱም፣ አንደኛ፡- “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑ እና ሁለተኛ፡- ፖለቲካዊ ስርዓቱ በዚህ የተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ናቸው። በሚቀጥለው ክፍል “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ብሔር ወይስ ግለሰብ?” በሚል የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 የተመሰረተበትን የተሳሳተ እሳቤ በዝርዝር እንመለከታለን።         

ብሔርተኝነት እና አንድነት

ብሔርተኝነት ራስ-ወዳድነት ነው!!!

አንዳንድ ሰዎች በብሔርተኝነትና ዘረኝነት ወይም በብሔር እና በዘር ልዩነት ላይ በተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ አድርገው ሲያቀርቡ ሳይ በጣም ይገርመኛል። ነገር ግን፣ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት ተለያይተው አያውቁም። “ዘረኛ” የሚለው ቃል “በዘር ምክንያት ለአንዱ የሚያደላ፣ ሌላውን የሚጎዳ፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን፥ አመለካከትን የሚያራምድ” ማለት ነው። “ብሔርተኛ” ደግሞ “ለብሔሩ (ጎሳው) ብቻ የሚስብና የሚያደላ፣ በሌላ ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ነው። “ዘረኝነት” የዘረኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ሲሆን “ብሔርተኛ” ደግሞ የብሔርተኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ነው። በዚህ መሰረት፣ ዘረኛ ሆነ ብሔርተኛ ሁለቱም በአድልዎ ላይ የተመሰረቱ አመለካከቶች ናቸው። በሁለቱም ውስጥ ለራስ ዘር/ብሔር ማድላት፥ መደገፍና ክፍ ክፍ ማድረግ አለ። በተመሳሳይ፣ በሁለቱም ውስጥ የሌላን ዘር/ብሔር ማግለል፥ መለየትና መጥላት አለ። በዘረኝነትና ጠባብነት ውስጥ ራስን መውደድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጥላት፣ ለራስ ማዳላትና መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማግለልና መጉዳት አለ። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ማለት ራስ-ወዳድነት ነው!!! በራስ-ወዳድነት ወይም ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መጨረሻው አድሏዊና ጨቋኝ የሆነ ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው።

አንድነት እኩልነት ነው!!!

ብዙውን ግዜ “አንድነት” የሚለው ቃል የተዛባ ትርጉምና ፍቺ ሲሰጠው ማየት የተለመደ ነው። በአብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ በስፋት የሚንፀባረቀው የአህዳዊ አንድነት ፅንሰ-ሃሳብ ነው። በዚህ መሰረት “አንድነት” ሲባል የአንድ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥…ወዘተ ተመሳሳይነት ተደርጎ ይገለፃል። ይህ ደግሞ በብሔርተኛ ቡዱኖች ዘንድ የአንድ ብሔር፥ ቋንቋና ባህል የበላይነት እንደሆነ ይገልፃሉ። ነገር ግን፣ የሁለቱም ወገኖች አመለካከት የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም፣ የአንድነት ፅንሰ-ሃሳብ በብሔር፥ ቋንቋ ወይም ባህል ተመሳሳይነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ፖለቲካዊ አንድነት በሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሁለም ሰው እኩል መብትና ነፃነት አለው። በመሆኑም፣ “ለእኔ የሚገባኝ መብትና ነፃነት ለሁሉም ሰው ይገባል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ “አንድነት” ሲባል “ሁላችንም እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባል” ማለት ነው። በአጠቃላይ፣ አንድነት ማለት እኩልነት ነው!!! በአንድነት ወይም እኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የብዙሃን መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል። 

እያንዳንዱ ሰው እንደ አፄ ሚኒሊክ ቅዱስና እርኩስ ነው!

የኢህአዴግ መንግስት ስለ ተቃዋሚዎች ይናገራል። ተቃዋሚዎች ስለ ኢህአዴግ ይናገራሉ። ግማሹ ቴዲ አፍሮ ኮንሰርት እንዳያዘጋጅ ፍቃድ ተከለከለ ይላል። ሌላው የጎሳዬ ተስፋዬን ኮንሰርት ¨Boycott” አድርጉ ይላል። አንዱ ድንገት ተነስቶ ስለ ቀድሞ ታሪክ የሆነ ነገር ይናገራል፣ ከዛ ሕዝቤ ሁላ በጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ ያዙኝ-ልቀቁኝ ይላል። ይኸው ነው የእኛ ነገር። ሁሉም ይናገራል። አንዱ በጭፍን የሚደግፈውን፣ ሌላው በጭፍን ይቃወማል። እርስ-በእርስ መጯጯህ እንጂ መደማመጥና መግባባት ተስኖናል። ሁሉም የራሱን እውነት ለመናገር እንጂ የሌሎችን ለማዳመጥና ለመረዳት ዝግጁ አይደለም።

በእርግጥ እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ትክክል ነው። ሁሉም ሰው የሚናገረውና የሚፅፈው ነገር በተግባር የሚረጋገጥ እውነት ሆነ በቃላት የተለወሰ ውሸት ለውጥ የለውም። ሁሉም ሰው በራሱ እይታ ትክክል የመሰለውን ነው የሚያደርገው። ሰው በጭራሽ ስህተት ለመስራት ብሎ አይሳሳትም። ይሄን ለመረዳት በጣም ቀላል ነው። ለምሳሌ፣ እርስዎ፥ አንቺ ወይም አንተ እስኪ ዛሬ የተናገራችሁትን ወይም ያደረጋችሁትን ነገር መለስ ብላችሁ አስቡ። እውነትም ሆነ ውሸት መናገር ያለባችሁን ተናግራችኋል አይደል? አምናችሁበትም ይሁን ሳታምኑበት የሆነ ተግባር ፈፅማችኋል። ከቦታ (space)፣ ግዜ (time) እና ምክንያት (cause) አንፃር ሲታይ የፈፀማችሁት ድርጊት ለራሳችሁ ትክክል ነው። በ“phenomenologist epistemology” ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት፣ እያንዳንዱ ሰው የሚፈፅመው ተግባር ሌሎች ሰዎች በእሱ ቦታ ቢሆኑ የሚፈፅሙትን ተግባር ስለሆነ ድርጊቱ ሁልግዜም ትክክል ነው፡-

“Man chooses and makes himself by acting. Any action implies the judgment that he is right under the circumstances not only for the actor, but also for everybody else in similar circumstances.”

እኛ ለራሳችን የምንሰጠውን ግምት ሁሉም ሰው ለራሱ ይሰጣል። እኛ በምንናገረውና በምንፅፈው ነገር ላይ ትክክል ነን ብለን እንደምናስበው ሁሉም ሰው በራሱ፥ ለራሱ ትክክል ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው በመካከላችን አለመግባባት የተፈጠረው? ለምን እያንዳንዱ ሰው በራሱ ትክክል መሆኑንና የእሱን እውነት ተቀብለን ለመረዳት ጥረት አናደርግም? በአጠቃላይ፣ እርስ-በእርስ ከመጯጯህ ባለፈ መደማመጥና መግባባት የተሳነን ምክንያቱ ምንድነው?

አወዛጋቢ በሆኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች ዙሪያ ተነጋግሮ መግባባት የተሳነን ሌሎች ሰዎች፣ በተለይ የቀድሞ መሪዎች ስህተትን አውቀውና ፈቅደው እንደፈፀሙት ስለምናስብ ነው። እኛ በራሳችን “ባለማወቅ” ስህተት ልንሰራ እንደምንችል እናውቃለን። አወዛጋቢ የሆኑ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶችን ሌሎች ሰዎች በስህተት ሳይሆን አውቀውና ፈቅደው፤ በክፋትና ምቀኝነት ወይም ሌሎችን ያለ አግባብ ለመጉዳትና ራሳቸውንን ለመጥቀም ብለው እንደፈፀሟቸው እናስባለን። ለእኛ ሲሆን “ሳናውቅ በስህተት…” የምንለውን ለሌሎች ሲሆን “አውቀው በድፍረት እንደፈፀሙት” እናስባለን።

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ ሁሉም ሰው በራሱ “ትክክል” ብሎ ያመነበትን ነው የሚፈፅመው። እኛ “ስህተት ነው” ብለን የምንቃወመው ተግባር ከድርጊት ፈፃሚዎቹ ቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ሲታይ ግን ትክክል ነው። በእርግጥ ትክክክኝነቱ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛ ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ እኛም እነሱ በነበሩበት ቦታ (space)፣ ግዜ (time) እና ምክንያት (cause) ላይ ብናስቀምጥ አሁን የምንቃወመውን ተግባር ሳናዛንፍ ደግመን እንፈፅመዋለን።

የሰው ልጅ ሁሉንም ነገር በራሱ አውቆና ፈቅዶ ያደረገው ይመስለናል። ታሪካዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች በሰዎች ነፃ ፍላጎትና ፍቃድ (will) የተደረጉ ይመስሉናል። ይህ ግን ከቦታ፥ ግዜና ምክንያት አንፃር ከድርጊቱ ወይም ክስተቱ ያለንን ርቀት ወይም የግንዛቤ እጥረት ከመጠቆም የዘለለ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም፣ ሌሎች ሰዎች በፍቃዳቸው ያደረጉት የመሰለንን ነገር ቀርበን ወይም በጥልቀት ስናውቀው ምርጫና አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ እንደተፈፀመ እንረዳለን።

የሰው ልጅ አንድ በጣም አስቂኝ ባህሪ አለው። የሌሎች ሰዎችን ተግባር አግባብነት ወይም ትክክለኝነት የሚፈርጀው “እኔ ብሆን ኖሮ እንደዛ አላደርግም ወይም እኔ ብሆን ኖሮ እንደዚህ አደርግ ነበር” በሚል እሳቤ ላይ ተመስርቶ ነው። ይህም በሞራላዊ ወይም ምክንያታዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ሰው ራሱን በድርጊት ፈፃሚው ቦታ (space)፣ ግዜ (time) እና ምክንያት (cause) ቢያስቀምጥ አሁን “እንዴት እንደዚህ አደረገ?” እያለ የሚቃወመውን ተግባር ሳያዛንፍ ይደግመዋል። የሰው ልጅ ይህን እውነት ሺህ ግዜ በተግባር አረጋግጦታል፡፡ ነገር ግን፣ ይህን ሃቅ አምኖ መቀበል ሞቱ እንደሆነ “Leo Tolstoy” እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-    

“…series of experiments and arguments proves to him that the complete freedom of which he is conscious in himself is impossible, and that his every action depends on his organization, his character, and the motives acting upon him; yet man never submits to the deductions of these experiments and arguments. However often experiment and reasoning may show a man that under the same conditions and with the same character he will do the same thing as before, yet when under the same conditions and with the same character he approaches for the thousandth time the action that always ends in the same way, he feels as certainly convinced as before the experiment that he can act as he pleases.” War And Peace: EP2|CH8, Page 1159.

ዛሬ ላይ የምንቃወመውን ተግባር ከተፈፀመበት ቦታና ግዜ፣ እንዲሁም የተፈፀመበትን ምክንያት ጠንቅቀን ስናውቅ ምርጫና አማራጭ በሌለበት አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ አንደተፈጸመ እንገነዘባለን። ምርጫና አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የተፈፀመ ተግባርን “ትክክል” ወይም “ስህተት” ብሎ መፈረጅ አይቻልም። ምክንያቱም፣ አንድን ተግባር ትክክል ወይም ስህተት ብሎ ለመፈረጅ በቅድሚያ አማራጭ መኖር አለበት። አማራጭ በሌለበት ምርጫ ሊኖር አይችልም። አማራጭ በሌለው አስገዳጅ ምርጫ የተፈፀመ ተግባርን ትክክል ወይም ስህተት ብሎ መፈረጅ አይቻልም። ድርጊት ፈፃሚው ያደረገው እኛም በእሱ ቦታ ብንሆን የምናደርገውን፥ ያለ ማዛነፍ የምንፈፅመውን ነው።

በተለያዩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እርስ-በእርስ ከመጯጯህ ባለፈ መደማመጥና መግባባት የተሳነን ለዚህ ነው። የቀድሞ ሆኑ የአሁን መሪዎች የሚፈፅሟቸው ተግባራት አውቀውና ፈቅደው፥ ሌሎችን ለመጉዳት ወይም ራሳቸውን ለመጥቀም አስበው ይመስለናል። ከዚያ በኋላ “እከሌ ጀግና ነው! እከሌ ባንዳ ነው! አፄ ሚኒሊክ ቅዱስ ነው! አፄ ሚኒሊክ እርኩስ ነው!” እያልን እንጯጯሃለን፡፡ እያንዳንዱ ሰው በአፄ ሚኒሊክ ቦታ ላይ ቢሆን እሱ ያደረገውን ሳያዛንፍ ይደግመዋል! ስለዚህ፣ እያንዳንዱ ሰው እንደ አፄ ሚኒሊክ ቅዱስና እርኩስ ነው!     

ዘረኝነትን ሲያቆላምጧት “ብሔርተኝነት” አሏት!

አንዳንድ ሰዎች በአክራሪ ብሔርተኝነትና በዘረኝነት መካከል፣ እንዲሁም በብሔር ልዩነት እና በዘር ልዩነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት የተለያዩ ናቸው ሲሉ ይገርሙኛል። ነገር ግን፣ የብሔርተኝነትና ዘረኝነት ፅንሰ-ሃሳብ ፍፁም ተመሳሳይ ናቸው። የዓለም ታሪክን ስንመለከትም ብሔርተኝነትና ዘረኝነት በጭራሽ ተለያይተው አያውቁም። በዚህ ፅሁፍ የሁለቱን የብሔርተኝትና ዘርኝነት ፅንሰ-ሃሳብን ከታሪክ ጋር አቀናጅተን በዝርዝር እንመለከታለን።  

በቅድሚያ “ዘረኛ” የሚለው ቃል “በዘር ምክንያት ለአንዱ የሚያደላ፣ ሌላውን የሚጎዳ፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን፥ አመለካከትን የሚያራምድ” የሚል ፍቺ አለው። “ብሔርተኛ” ደግሞ “ለብሔሩ (ጎሳው) ብቻ የሚስብና የሚያደላ፣ በሌላ ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። “ዘረኝነት” የዘረኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ሲሆን፣ “ብሔርተኛ” ደግሞ የብሔርተኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ነው። “ብሔር” የሚለው ቃል “አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት ያለው፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፥…የተሳሰረና በተወሰነ ክልል ውስጥ የሚኖር ሕዝብ” የሚል ፍቺ አለው። “ብሔረሰብ” የሚለው ቃል ደግሞ “ከደም አንድነት ይልቅ በክልል፥ በቋንቋና በባህል አንድነት ላይ የተመሰረተ፣ የተለያዩ ነገዶች የተዋሃዱበት ማህብረሰብ” ማለት ነው።

በመሰረቱ፣ ዘረኝነት እና ብሔርተኝነት በአድልዎ ላይ የተመሰረቱ አመለካከቶች ናቸው። ሁለቱም ውስጥ ለራስ ዘር/ብሔር ማድላት፥ መደገፍና ክፍ ክፍ ማድረግ፣ የሌላን ዘር/ብሔር ደግሞ ማግለል፥ መለየትና መጥላት አለ። በዘረኝነትና ብሔርተኝነት ውስጥ ራስን መውደድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጥላት፣ ለራስ ማዳላትና መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማግለልና መጉዳት አለ። ስለዚህ ሁለቱም በተመሳሳይ የተሳሳተ አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካዊ ስርዓቶችን ታሪካዊ አመጣጥ ስንመለከት ደግሞ ዘረኝነትና ብሔርተኝነት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን። ምክንያቱም፣ በዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካዊ ስርዓቶች በሙሉ መነሻቸው አሳፋሪ ሽንፈት፣ አክራሪ ብሔርተኝነት እና የጎሳ ፖለቲካ ናቸው። “የጎሳ ፖለቲካ” ማለት ደግሞ “በዘር፥ በጎሳ፥ በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው።

በዘረኝነት ታሪካዊ አመጣጥ ዙሪያ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው “George M Fredrickson”፣ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ በአውሮፓ “ዘረኝነት” (Racism) የሚባል ነገር ታይቶ እንደማይታወቅ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ የዘረኝነት ምልክት ለመጀመሪያ ግዜ የታየው በ13ኛውና 14ኛው ክ/ዘመን በስፔን ሲሆን እሱም አይሁዶችን ከሰይጣንና ባዕድ አምልኮ ጋር በማያያዝ ነበር የተከሰተው። ነገር ግን፣ በ16ኛው ክ/ዘመን የስፔን መንግስት ይህን የተሳሳተ አመለካከት በይፋ በማገዱ ተወግዷል። ከዚያ በኋላ፣ ዘረኝነት ማቆጥቆጥ የጀመረው በ17ኛው ክ/ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በአሜሪካ ነው። ለዚህ ደግሞ እ.አ.አ. በ1667 በደቡባዊ አሜሪካ ቨርጅኒያ ግዛት የጥቁር አሜሪካዊያንን ጉልበት ለመበዝበዝ የወጣው ሕግ ተጠቃሽ ነው። ይሁን እንጂ፣ ዘረኝነት ተንሰራፍቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በ19ኛው ክ/ዘመን ማብቂያ ላይ ነው።

“George M Fredrickson” የ19ኛው ክ/ዘመን በአሜሪካና አውሮፓ የነፃ-መውጣት፣ የብሔርተኝነት እና የኢምፔሪያሊዝም (Emancipation, Nationalism and Imperialism) ዘመን እንደነበር ይገልፃል። በተለይ ከ1870 – 1880 ያሉት ዓመታት በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ለዘረኝነት መነሻ የሆነው የዘውግ ብሔርተኝነት (Ethnic Nationalism) በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት ነበር። በዚህ ወቅት በጀርመን በርሊን የተፈረመው “The scramble of Africa” የተሰኘው አፍሪካን የመቀራመት ስምምነት የምዕራብ ሀገራት የአክራሪ ብሔርተኝነት ውድድርን አጥናክረው የቀጠሉበት እንደነበር፤ “…an assertion of the competitive ethnic nationalism that was existed among European nations” በማለት ግልፆታል።

በመጨረሻም፣ “Fredrickson” ዘረኝነት ጫፍ ደርሶ ጨቋኝ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመሆን የበቃው በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ ወቅት ከተፈጠሩት “በግልፅ ዘረኛ የሆኑ መንግስታት” (Overtly Racist Regimes) የሚባሉት በአሜሪካ፣ በጀርመንና በደቡብ አፍሪካ የነበሩት ናቸው። እነዚህ ዘረኛ መንግስታዊ ስርዓቶች በዘር ላይ የተመሰረቱ ጨቋኝ ሕጎችና መመሪያዎች ከማውጣታቸው በፊት በግልፅ ብሔርተኛ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ይህን “Fredrickson” እንዲህ ሲል ገልፆታል፦

“racist principles were not fully codified into laws effectively enforced by the state or made a central concern of public policy until the emergence of what I will call ‘overtly racist regimes’ in the last century.”

ከላይ የተጠቀሱት በዘረኝነት የተመሰከረላቸው ፖለቲካዊ ስርዓቶች ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ መሰረት አላቸው። እነሱም፣ አንደኛ፡- አሳፋሪ ሽንፈት (Humiliating defeat)፣ ለሽንፈቱ ሌሎች ብሔሮችን፥ ብሔረሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ (Scapegoating) እና የአንድን ብሔር የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሌሎችን ብሔሮች መብትና ነፃነት የሚገድቡ ሕጎችን ማውጣትና ተግባራዊ ያደረጉ ናቸው።

እንደ “Fredrickson” አገላለፅ፣ በአሜሪካ የዘረኝነት ስርዓት መዘርጋት የተጀመረው በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች ሲሆኑ ዋና መነሻ ምክንያቱ በበደቡባዊ አሜሪካ የሚገኙ ነጮች በአሜሪካ የእርስ-በእርስ ጦርነት ወቅት አሳፋሪ ሽንፈት ስለገጠማቸው እንደሆነ ይጠቅሳል። እነዚህ ነጭ አሜሪካዊያን በጦርነቱ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት በጥቁሮች ላይ አሳብበዋል (Scapegoat)። በመጨረሻም፣ በ20ኛው ክ/ዘመን በአሜሪካ የከተሞች መስፋፋት በእርሻ ማሳዎች ላይ የሚውሉ ጥቁሮችን ለመቆጣጠር አመቺ ባለመሆኑና የጥቁሮችን ጉልበት ብዝበዛ ለማስቀጠል በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ሕግና ደንብ በማውጣት ተግባራዊ አደረጉ። በተመሳሳይ፣ ጀርመኖች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ለጋጠማቸው አሳፋሪ ሽንፈት አይሁዳዊያንን ተጠያቂ አድርገዋል። ከዚያ በመቀጠል፣ አይሁዶችን በዘር በመለየትና በመነጠል የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በመጨረሻም፣ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች በእንግሊዝ ጦር ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ተጠያቂ አድርገዋል። የእንግሊዝ ጦር ከደቡብ አፍሪካ ሲወጣ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት በመዘርጋት በጥቁሮች ላይ ግፍና በደል ፈፅመዋል።

በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት የሚዘረጋው፣ አንድ ብሔር ወይም ሀገር በታሪክ ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈትና ፀፀት ራሱን ለማውጣት ሲል በሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ብሔር፥ ሕዝብ ከዚህ ቀደም ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈትና ቀውስ ራሱን ለማውጣትና በሌሎች ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች ላይ የበላይነቱንና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ጨቋኝ የሆነ ፖለቲካዊ ስርዓት ይዘረጋል። ዘረኝነት እንዲኖር የተለየ ቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት ያለው ማህብረሰብ መኖር አለበት።

ብሔርና ብሔርተኝነት በሌለበት ዘረኝነት ሊኖር አይችልም። የዘር ልዩነት ቢኖርም እንኳን በቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦናዊ አመለካከት ተመሳሳይ በሆኑ ሕዝቦች መካከል ዘረኝነት ሊኖር አይችልም። ስለዚህ፣ ዘረኝነት እንዲኖር በቅድሚያ የቋንቋ፣ የባህልና የስነልቦናዊ አመለካከት ልዩነት መኖር አለበት። በመሆኑም፣ ዘረኝነት እንዲኖር በቅድሚያ ብሔርና አክራሪ ብሔርተኝነት መኖር አለበት። በዚህ መሰረት፣ ብሔርተኝነት እና ዘረኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። 

በመጨረሻም፣ አሁን በሀገራችን የተዘረጋው በብሔር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስርዓት በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንና አለመሆኑን ለማወቅ ከጥንት ጀምሮ በአማራና ትግራይ መካከል የነበረው የዘውግ በሔርተኝነት፣ የአፄ ሚኒሊክ ወደ ስልጣን መምጣት (የትግራይና ሸዋ ዘውዳዊ አገዛዝ)፣ እንዲሁም የሕውሃት የትግል ማኒፌስቶ እና ስለ አማራ ሕዝብ የነበረው አቋምና አመለካከትን በማየት በራሳችሁ መፍረድ ትችላላችሁ። ለዚህ ያግዛችሁ ዘንድ “Fredrickson” የዘረኛ ስርዓት ዋና መለያ ባህሪ ያለውን የመጀመሪያ መስፈርት በመጥቀስ ፅሁፌን እቋጫለሁ፡- 

“First there is an official ideology that is explicitly racist. Those in authority proclaim insistently that the difference between the dominant group and the one that is being subordinated or eliminated are permanent or unbridgeable. Dissent from this ideology is dangerous and is likely to bring legal or extralegal reprisals, for racist egalitarianism is heresy in an overtly racist regime.” 

  

ደርግና ኢህአዴግ፡ ጨቋኝ ስርዓት የሚፈጠረው በልሂቃን መከፋፈል ነው!

ባለፈው ዓመት የቀድሞ የአየር ኃይል ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) “ድርግነት እያቆጠቆጠ – ዴሞክራሲ እየጨላለመ ነው – ሕዝቦች ጠንቀቅ በሉ” በሚል ርዕስ ማሳሰቢያ አዘል ፅሁፍ አውጥተው ነበር። ነገር ግን፣ እንደ ጄ/ል አበበ ያሉ የቀድሞ ጦር አዛዦች ራሳቸው የገረሰሱት የድርግ ስርዓት “ተመልሶ ሊመጣ ነውና ተጠንቀቁ” የሚል ማሳሰቢያ መስጠታቸው ለብዙዎች ግራ ያሰኛል። ምክንያቱም፣ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ዘመን በዜጎች ላይ በደልና ጭቆና የሚፈፅመው በመከላከያና ደህንነት ኃይሎች አማካኝነት መሆኑ ግልፅ ነው። ስለዚህ፣ የደርግ ስርዓት ተመልሶ ቢመጣ እንኳን በእነሱና በቀድሞ ባልደረቦቻቸው አማካኝነት እንደሆነ መገመት ይቻላል። ታዲያ እነዚሁ ሰዎች ተመልሰው “ደርግነት እያቆጠቆጠ ነው” ሲሉ መስማት ለብዙዎች ግር የሚያሰኝ ነገር ነው።

በእርግጥ ላለፉት አስር አመታት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ የታየውን ለውጥ በጥሞና ላስተዋለ ነገሩ ሁሉ “ከድጡ ወደ ማጡ!” የሚሉት ዓይነት እንደሚሆንበት አልጠራጠርም። በመሰረቱ፣ ፍርሃት (fear) የጨቋኝ ስርዓት መርህና መመሪያ ነው። በጨቋኝ ስርዓት ስር የሚኖሩ ዜጎች በእለት-ከእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ፍርሃት እንደ ጥላ ይከተላቸዋል። ፍርሃት፤ የዜጎችን ነፃነት የሚገድብ፣ የእኩልነትን የሚያጠፋ፣ ፍትህን የሚያጓድል፣ በአጠቃላይ ዴሞክራሲን የሚገድል “ጥላ-ወጊ” ነው። ዛሬ በኢትዮጲያ ላይ የፍርሃት ድባብ (climate of fear) ተንሰራፍቷል።

በተለይ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የግል ሚዲያ፣ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች እና የፍትህ ተቋማት ስራና አሰራርን በዝርዝር ስንመለከት ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (constitutional democracy) ከስረ-መሰረቱ እየተናደ በመፍረስ ላይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በተጠቀሰው ግዜ ውስጥ፤ በተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች፥ በጋዜጠኞችና የመብት ተሟጋቾች ላይ የሚደርሰው እስራት፥ ስደትና እንግልት፣ በምርመራ ስም የሚደርስባቸው መከራና ስቃይ፣ እንዲሁም ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ፥ አካል ጉዳት፥ እስራትና እንግልትን ስንመለከት “ደርግነት ከማቆጥቆጥም አልፎ እንደ ዋርካ ዛፍ አድጎና ተንዘርፏል” ለማለት ያስደፍራል።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ ባለፉት አስር አመታት ደርግነት ከማቆጥቆጥ አልፎ ስር ሰድዶ በቅሏል። በዚህም በሁላችንም ሕይወትና እንቅስቃሴ ላይ የፍርሃት ድባብ አጥልቷል። ነገር ግን፣ “የደርግ ስርዓት እንዴትና ለምን ተመልሶ መጣ?” የሚለው ለብዙዎቻችን ግልፅ አይደለም። ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ ደግሞ ስለ ፖለቲካዊ አገዛዝ ባለን ግንዛቤ ላይ ይወሰናል። ለምሳሌ፣ “ኢትዮጲያን እየገዛ ያለው ማን ነው?” ተብለን ብንጠየቅ አብዛኖቻች የተወሰነ የፖለቲካ ቡድንን፥ የመንግስት ባለስልጣናትን ወይም የጦር መሪዎችን ስም ከመዘርዘር አናልፍም። ነገር ግን፣ የፖለቲካ አገዛዝ የሚመራው በፖለቲካ ፓርቲ፥ ባለስልጣናት ወይም የጦር ጄኔራሎች አይደለም።

“በሳንጃ የፈለከውን ማድረግ ትችል ይሆናል ከላዩ ላይ መቀመጥ ግን አትችልም” (You can do everything with bayonets, except sit on them) እንደሚባለው፣ ሀገርና ሕዝብን በጦር ኃይል መግዛት አይቻልም። በእርግጥ ሀገርና ሕዝብን በጦር ኃይል ቁጥጥር ስር ማዋል ይቻል ይሆናል።  ነገር ግን፣ በወታደሮችና በጦር መሳሪያ መግዛትና ማስተዳደደር አይቻልም። ለምሳሌ፣ የፈረንሳዩ ንጉስ ናፖሊዮን “Napoleon” ስፔንን በመውረር ሙሉ-በሙሉ በቁጥጥሩ ስር አውሏት የነበረ ሲሆን ሀገሪቷንና ሕዝቡን ለአንዲት ቀን እንኳን መግዛት እንደተሳነው ምሁራን ይገልፃሉ። በፈረንሳዩ ናፖሊዮን እና በስፔን ሕዝብ መካከል የነበረው ሁኔታ በአምስት አመቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት በሞሶሎኒ እና በኢትዮጲያ ሕዝብ መካከል ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ይመስለኛል።

ሕዝብና ሀገርን በወታደር ብዛትና በጦር መሳሪያ መቆጣጠር ቢቻልም መግዛት ግን አይቻልም። ምክንያቱም፣ ሀገርን ለመግዛት በመሪነት ቦታ ላይ መቀመጥና ህዝብን መምራት ይጠይቃል። የመሪነት ሚናን በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የግድ ያስፈልጋል። በሕዝብ ዘንድ ያለ ተቀባይነት ደግሞ የሚወሰነው በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ነው። ስለዚህ፣ ሀገርን መግዛት የሚችለው በሌላ ሳይሆን በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት (public opinion) አማካኝነት ነው። “THE REVOLT OF THE MASSES” በሚለው መፅሃፉ “Jose Ortega y Gasset” ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ አብራርቶታል፡-   

“By “rule” we are not here to understand primarily the exercise of material power, of physical coercion. This stable, normal relation amongst men which is known as “rule” never rests on force.…It is necessary to distinguish between a process of aggression and a state of rule. Rule is the normal exercise of authority, and is always based on public opinion, to-day as a thousand years ago, amongst the English as amongst the bushmen. Never has anyone ruled on this earth by basing his rule essentially on any other thing than public opinion…. In Newton’s physics gravitation is the force which produces movement. And the law of public opinion is the universal law of gravitation in political history.” THE REVOLT OF THE MASSES፡ CH.XIV፡ Page 71 – 80 

በስልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን ምንም ያህል ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ቢኖረው በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እስከሌለው ድረስ ሀገሪቱን መምራት አይችልም። ሌላው ቀርቶ እንደ ናፖሊዮን ያሉ ጦረኛ መሪዎች እንኳን ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት የብዙሃኑን ሃሳብና አስተያየት ይጠይቃሉ። በአጠቃላይ፣ ጨቋኝ ስርዓት እንዲኖር በቅድሚያ በደልና ጭቆናን አምኖ የተቀበለ ማህብረሰብ መኖር አለበት። ለዚህ ደግሞ የብዙሃኑን ሃሳብና አመለካከት ለጭቆና በደልና ጭቆናን እንዲቀበል ተደርጎ መቅረፅ ያስፈልጋል።

የፖለቲካ ኃይል ወይም የስልጣን ለውጥ (ሽግግር) ማለት በራሱ የብዙሃኑ አስተያየትና አመለካከት ለውጥ ነው። የብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ለውጥ በሌለበት የፖለቲካዊ ስርዓት ለውጥ በራሱ ትርጉም የለውም። ምክንያቱም፣ ሀገርና ሕዝብን ለመምራት የሚያስችል ኃይል (ruling power) የሌለው የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ-ቢስ ነው። ነገር ግን፣ በደልና ጭቆናን አምኖ የሚቀበል ማህብረሰብ እንዴት መፍጠር ይቻላል?   

በመሰረቱ አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጋ የራሱ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የለውም። የብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት (public opinion) የሚቀረፀው በጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን አማካኝነት ነው። እነዚህ ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ላይ የበላይነትና ቁጥጥር አላቸው። በዚህ መሰረት፣ የፖለቲካ ልሂቃን በደለና ጭቆናን አጥብቆ የሚጠየፍና የሚቃወም ወይም በተቃራኒው “በደልና ጭቆናን ባይደግፍ እንኳን አምርሮ የማይቃወም” የፖለቲካ ማህብረሰብ መፍጠር ይችላሉ።

ነገር ግን፣ የአንድ ሀገር የፖለቲካ ልሂቃን ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል አንፃር የተማሩና የተሻለ የፖለቲካ ግንዛቤ ያላቸው እንደመሆኑ መጠን ከጨቋኝ ስርዓት ይልቅ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲኖር ይሻሉ። በየትኛውም ማህብረሰብ ዘንድ ከመብትና ነፃነት ይልቅ በደልና ጭቆናን የሚያቀነቅን የፖለቲካ ልሂቅ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ይሁን እንጂ፣ ልሂቃን ስለ መብትና ነፃነት እየተናገሩ ባለበት ሁኔታ በደልና ጭቆናን አምኖ የተቀበለ ማህብረሰብ ለምን ይፈጠራል?

በመሰረቱ ጨቋኝ ስርዓት ሕዝብና ሀገርን ለመምራት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ የሚፈጠረው በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ አመለካከት ሳይኖር ሲቀር ነው። ይህ ደግሞ የሚፈጠረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን እርስ-በእርስ የሚጋጩ/የማይስማሙ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በሚያራምዱበት ወቅት ነው። የፖለቲካ ልሂቃን እርስ-በእርስ የሚጋጩ አቋሞችና አጀንዳዎችን በሚያራምዱበት ወቅት የዜሮ-ድምር ጨዋታ ይጀመራል።

በዜሮ-ድምር ፖለቲካ አንደኛው ወገን የሚሰጠው ሃሳብና አስተያየት የሌላኛውን ወገን አቋምና አመለካከት ውድቅ በማድረግ ላይ ያነጣጠረ ነው። ይህ ደግሞ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ወጥ የሆነ የጋራ አመለካከትና ግንዛቤ እንዳይፈጠር ያደርገዋል። በብዙሃኑ ዘንድ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት በሌለበት ሀገር ለማስተዳደር የሚያስችለው ኃይል (ruling power) ሊኖር አይችልም። የፖለቲካ ልሂቃን የብዙሃኑን አመለካከትና ግንዛቤ ከመቅረፅ አንፃር ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲሳናቸው ሀገርና ሕዝብ መምራትና ማስተዳደር የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ መሰረት፣ ጨቋኞች የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው በምሁራኑ/ልሂቃኑ ቦታ ራሳቸውን ይተካሉ። ይህን ሂደት “Jose Ortega y Gasset” እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-    

“What happens is that at times public opinion is nonexistent. A society divided into discordant groups, with their forces of opinion cancelling one another out, leaves no room for a ruling power to be constituted. And as “nature abhors a vacuum” the empty space left by the absence of public opinion is filled by brute force. At the most, then, the latter presents itself as a substitute for the former. Consequently, if we wish to express the law of public opinion as the law of historical gravitation, we shall take into consideration those cases where it is absent, and we then arrive at a formula which is the well-known, venerable, forthright commonplace: there can be no rule in opposition to public opinion.” THE REVOLT OF THE MASSES፡ CH.XIV፡ Page 71 – 80 

በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ልሂቃን በዋናነት “በኢህአፓ” እና “መኢሶን” አማካኝነት ለሁለት ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ ሲጠዛጠዙ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ወታደራዊ ደርግ ስልጣን ተቆጣጠረ። በድጋሜ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ልሂቃን “በአህዳዊ አንድነት” እና “በብሔር እኩልነት” ጎራ ለይተው እርስ-በእርስ ሲጠዛጠዙ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ አምባገነናዊ የኢህአዴግ መንግስት ተፈጠረ።

በመጀመሪያ ደርግ በኢህአፓ የተቃጣበትን የነጭ ሽብር ጥቃት ለመመከት መኢሶን ወደ ራሱ አስጠግቶ በቀይ-ሽብር ዘመቻ ኢህአፓ አባላትና አመራሮችን አጠፋ። ኢህአፓዎችን አጥፍቶ ሲጨርስ ከስሩ ያስጠጋቸውን የመኢሶን አባላትና አመራሮች አጠፋ። በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት በ1997ቱ ምርጫ ከቅንጅት የተቃጣበትን የሕልውና አደጋ ለማስወገድ እንደ ሕብረት ያሉ ብሔርተኛ የፖለቲካ ቡድኖችን ወደ ራሱ አስጠግቶ የቅንጅት አባላትና አመራሮችን በእስርና በስደት ደብዛቸው እንዲጠፋ አደረገ። ከዚያ በመቀጠል፣ ቅንጅቶችን አጥፍቶ ሲጨርስ ከስሩ ያስጠጋቸውን ብሔርተኛ ቡድኖችን በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አማካኝነት ደብዛቸውን በማጥፋት ላይ ይገኛል። በደርግ የቀይ-ሽብር ዘመቻ ሆነ የኢህአዴግ ፀረ-ሽብር አዋጅ ዓላማቸው አንድና አንድ ነው – በሕዝብ ላይ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር ነው። ምክንያቱም፣ ሕዝብ በደልና ጭቆናን ተቀብሎ የሚኖረው በፍርሃትና ሽብር ውስጥ ብቻ ነውና።