Category Archives: Amazing Story

ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እና የተቀደዱ ዘገባዎች!

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ የታሰሩበትን ወንጀል አስመልክቶ ሪፖርተር ጋዜጣ ባቀረበው ዘገባ የሚከተለው ይገኝበታል፦

“ተጠርጣሪው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ሲሆኑ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል””

ሊጣላ የመጣን ቢለምኑት አይመለስም!” እንደሚባለው ሆኖ እንጂ፣ አቶ ሳምሶን ወንድሙ በተከሰሱበት ወንጀል የማይከሰስ የመንግስት ሃላፊ ማግኘት በራሱ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም፣ ያልተጠናቀቁ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እንደተጠናቀቁ አስመስሎ ማቅረብ የኢህአዴግ መንግስት መለያ ባህሪ ነዋ፡፡ ለምሳሌ፣ ሪፖርተር ጋዜጣ በዚህ አመት ግንቦት ወር ላይ ባወጣው ሌላ ዘገባ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ1998 ዓ.ም ሲጀመር በ3 አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ከአሥር ዓመታት በኋላም ሥራ እንዳልጀመረ ገልጿል፡፡ በተመሣሣይ፣ የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም ሁለት ዓመት የተጓተተ ከመሆኑ በላይ፣ አሁን ያለበት የሥራ አፈጻጸም 41 በመቶ ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ በአጠቃላይ ከተያዘለት 11 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ 9 ቢሊዮን ብር አስፈልጎታል፡፡ 

በ2003 ዓ.ም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ኘሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ ባቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መሰረት የአቶ ሳምሶን ወንድሙ መ/ቤት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ አመት ብቻ ሳይሆን በየወሩ ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚያቀርብ መሆኑ” እንደ ጥሩ ተሞክሮ መወሰድ እንዳለበት ይገልፃል፡፡ በሌላ በኩል “የተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማት የፕሮጀክት አስተባባሪ የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም” ተብሎ በኦዲት ሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ 

በመጨረሻም፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ከሁለት አመት በፊት “የተንዳሆ ግድብ ለዓመታት ተጓተተ” የሚለው የኢቢሲ ዘገባ… “ለዓመታት የተጓተተ ዘገባ” ነው!” በሚል ርዕስ ያቀረበውን ዘገባ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን እንደተጠናቀቁ አስመስሎ ማቅረብ በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ዘንድ የተለመደ ተግባር መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ በመሆኑም፣ ሙሉ ዘገባውን እንድታነቡት ጋብዘናችኋል፡፡

ምንጭ፦ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ድረገፅ

  1. ወጪው ከ1 ቢ. ብር በታች ነው የተባለው ግንባታ፣ ከ5 ቢ. ብር በላይ ፈጅቶም አላለቀም።  
  2. ቢበዛ በ3 ዓመት ውስጥ ግንባታው ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ፣ 10 ዓመት አልበቃውም።
  3. ግድቡ እየተጓተተ ወጪው እንደናረ፣ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አድማስ ሲዘገብ ቆይቷል።
  4. በ2006 ዓ.ም፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ ግንባታው መዝረክረኩን ገልጿል – (አዲስ አድማስ)።
  5. ነገሩ ሲባባስም፣ አምና፣ የገንዘብ ሚ.ር፣ ለግድብ በጀት አልመድብም ብሏል። (አዲስ አድማስ)።
  6. የመንግስት ሚዲያ (ኢቢሲ) እና የመሳሰሉ፣ እነዚህን ዘገባዎች፣ “ጨለምተኛ” ሲሏቸው ነበር።


ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ይፈጃል ተብሎ በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የተንዳሆ ግድብ ፕሮጀክት፣ በሁለት ወይም በሦስት ዓመት እንዲጠናቀቅ ነበር የታሰበው። ምን ዋጋ አለው? ወጪው ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል። አስር አመትም ሞላው። ግን ግንባታው አላለቀም። የሚያሳዝንና የሚያስቆጭ ትልቅ ኪሳራ ነው። 

በዚህ መሃል…ኢቢሲ፣ ድንገት ተነስቶ፣ ይህንን የኪሳራ መረጃ ዘንድሮ የሚነግረን፣ የት ከርሞ ነው? ላለፉት ስድስት አመታት የት ነበር? “የግድቡ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ እየተከናወነ ነው” የሚል… ከእውነት የራቀ፣ ‘የሌለ’ ዜና ለመስራት ሲተጋ ነበር፡፡ ለዚያውም ለበርካታ አመታት።

እና፣ አሁን ምን አዲስ ነገር ተፈጠረና ነው፣ ‘ግንባታው ተጓተተ፤ ወጪው ሸመጠጠ’ የሚል ዜና የሚያቀርብልን? ምናልባት፣ በአዲስ መንፈስ፣ ‘ከእንግዲህ ትክክለኛ ዜና እሰራለሁ’ የሚል፣ የአዲስ አመት እቅድ አውጥቶ ይሆን? ቢሆንማ፣ ጥሩ ነበር። 

ግን አይደለም። “ትክክለኛ ዜና የመስራት እቅዱ፣ ለተንዳሆ ግድብ ብቻ ነው” ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው። እንዴት ካላችሁ፣… ኢቢሲ፣ ከተንዳሆ ዜና ጎን ለጎን፣ ስለ ህዳሴ ግድብ ያቀረበውን ዜና መመልከት ትችላላችሁ።   

ኢቢሲን ስትከፍቱ፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ በጊዜው እየተከናወነ ነው” የሚል ዜና መስማታችሁ አይቀርም። ለሕዳሴ ግድብ፣ ከፍተኛ ክብር ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያዊያን፣ ዜናውን በትኩረት አዳምጠውት ይሆናል። በእርግጥ፣ በየጊዜው የሚደጋገም ዜና ስለሆነ፣ ‘ሳልሰማው አመለጠኝ’ የምንለው አይነት ዜና አይደለም። ባለፈው ሳምንት ቢያመልጣችሁ፣ ከዚያ በፊት በወዲያኛው ሳምንት፣ ተመሳሳይ ዜና ሰምታችሁ ሊሆን ይችላል። ካልሆነም፣ በያዝነው ሳምንት ትሰሙታላችሁ፤… ወይም በሚቀጥለው ሳምንት።

የሕዳሴ ግድብን የሚመለከት፣ የግንባታ ዜና እየተደጋገመ መምጣቱ አይደለም ችግሩ። የሕዳሴ ግድብ፣ እንደ ትልቅነቱ፣ በየጊዜው ከግንባታው ሂደት ጋር ብዙ አዳዲስ መረጃዎች ይኖራሉ። በዚህም ምክንያት፣ የሕዳሴ ግድብ፣ በተደጋጋሚ የዜና ርዕስ ሲሆን ብንሰማ፣ ችግር የለውም። ችግሩ ሌላ ነው። የተሳሳተ መረጃና የውሸት ዜና፣ (ለዚያውም እየተደጋገመ) መምጣቱ ነው ችግሩ።

ኢቢሲ፣ እንደተለመደው፣ “የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜው እየተከናወነ ነው” ካለ በኋላ፤ የግድቡ ግንባታ፣ 47% ላይ መድረሱን ገልጿል። ከምር ለመናገር፣ በትልቅነቱ የሚጠቀስ ግድብ፣ የዚህን ያህል ተገንብቶ ማየት፣ ቀላል ነገር አይደለም። ብዙ ተሰርቷል። ኢቢሲ፣ ይህችን እውነተኛ ዜና ብቻ መግለፅ እየቻለ፣ “በተያዘለት እቅድ፣ በጊዜ እየተከናወነ ነው” የሚል ውሸት ለምን ይጨምርበታል? ግራ ያጋባል።

ምንጭ፦ ዶች-ቬሌ ራድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ድረገፅ

‘ከተያዘለት እቅድ ዘግይቷል።  ግንባታው ግን 47% ደርሷል’ ብሎ እንዲዘግብ መጠበቅ ያስቸግራል። ቢያደርገውማ፣ “the truth, the whole truth, nothing but the truth” እንደሚባለው፣ እውነተኛ መረጃ… የተሟላ እውነተኛ መረጃ፣… ሌላ ነገር (ውሸት) ያልተቀላቀለበት እውነተኛ መረጃ… ይሆን ነበር። 

ግን፣ እሺ… ይቅር። እውነተኛ መረጃን አሟልቶ ለመናገር ፈቃደኛ አይሁን። ግንባታው መዘግየቱን ሳይገልፅ ይተወው። ጎደሎ መረጃ መናገር ይችል ነበር – ግንባታው፣ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ብቻ መግለፅ! ያው፣ ‘የተሟላ እውነት’ አይደለም። ግን፣ ቢያንስ ቢያንስ… ውሸት አልተቀላቀለበትም። አይደለም?
ለነገሩ ይህንን እንተወው። ኢቢሲ፣ ‘እንዲህ ቢያደርግ’፣ ‘እንዲያ ቢያደርግ’ እያልን ለምን በከንቱ እንደክማለን። ኢቢሲ፣ ለዚህ ሁሉ ደንታ ያለው አይመስልም። ደንታ ቢኖረው ኖሮ፣ በየጊዜው እየደጋገመ በድፍረት፣ የሃሰት መረጃ ይናገር ነበር? አገር ምድሩ የሚያውቀው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ፣ የሃሰት መረጃ መናገር… ሌላ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በጣም ቀላል ጉዳይ ነዋ።       

የግድቡ ግንባታ፣ “በአምስት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል” ተብሎ እንደነበር ማስታወስ ያቅተናል? አሁን፣ አራት አመት ተኩል ሆኖታል። ግንባታው ግን፣ ወደ ማጠናቀቂያው ሳይሆን፣ ወደ ግማሽ ነው እየተጠጋ ያለው። ቢያንስ፣ ተጨማሪ አራት አመታት ያስፈልጉታል ማለት ነው። ኢቢሲ፣ ይህንን ሳይገነዘብ ቀርቶ ይሆን፣ ቀን ከሌት የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጨው? እንዴት ሊሆን ይችላል? 

አሁን አይደለም፣… ከአመት ከሁለት አመት በፊትም፣ የግንባታ ሂደቱንና አዝማሚያውን ለመገንዘብ ከባድ አልነበረም። ከሦስት ዓመት በፊት፣ መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በአዲስ አድማስ የወጣውን ዘገባ ማየት ይቻላል። 

የመንግስት ፕሮጀክቶችን በሚዳስሰው በዚሁ ዘገባ ላይ፣ የሕዳሴ ግድብ ተጠቅሷል። የሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት፣ የታቀደለትን ያህል እየፈጠነ እንዳልሆነ ዘገባው ገልፆ፤ በዚያ አያያዙ፣ ግንባታው ከስምንት እስከ አስር አመት ሊፈጅ እንደሚችል ይጠቁማል። ይሄ ከሦስት ዓመት በፊት የወጣ ዘገባ ነው። በእርግጥም፣ አሁን እንደሚታየው፣ ግድቡ በተያዘለት ጊዜ (ማለትም ዘንድሮ) ሊያልቅ አይችልም። ግማሽ ያህል ይቀራል።

 ይሄ፣ መንግስትን የመተቸት ወይም የማወደስ፣ የመደገፍ ወይም የመቃወም ጉዳይ አይደለም። ጥሬ መረጃ ነው። ችግሩ፣ ኢቢሲ፣ ለእንዲህ አይነት መረጃ፣ “ፊት የሚሰጥ” አልሆነም። ግን፣ አስቡት። ችግሮችን በመደበቅ፣ ማስተካከል አይቻልም። “ችግር አለ” ብለን ካልተናገርን፣ “ችግር ብን ብሎ የሚጠፋ” ይመስል! “በተያዘላቸው እቅድ እየተከናወኑ ነው” ብሎ መናገር ብቻውን፤ “የእቅድ ክንውን” ሆኖ ይመዘገባል ካልተባለ በቀር። 

ለእውነተኛ መረጃ፣ “ፊት የማንሰጥ” ከሆነ፣ የመጓተትና የመዘግየት ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ ተገቢውን ያህል ትኩረት የሚያገኙበትም ሆነ የሚስተካከሉበት እድል እንዴት ይፈጠራል? 

 በተንዳሆ እና በሌሎች የስኳር ፕሮጀክት ላይ ያየነው ኪሳራ፣ ሳይስተካከልና መፍትሄ ሳያገኝ ለአመታት እየተባባሰ የመጣውም በዚሁ ምክንያት ነው። ስለ ተንዳሆ ግድብም ሆነ ስለሌሎቹ ፕሮጀክቶች፣ ኢቢሲ መረጃ ሳያገኝ ወይም ችግሩን ሳይገነዘብ ቀርቶ ነው? 

እሺ፣ አላወቀም፤ አልተገነዘበም እንበል። ግን፣ ለማወቅና ለመገንዘብ ፈቃደኛ እስከሆነ ድረስ፣ ቀላል ዘዴዎችን አያጣም ነበር። በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የወጡ ዘገባዎችን ማንበብ፣ ያን ያህል ከባድ ስራ አይደለም።

ሌሎች የስኳር ፕሮጀክቶች፣ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክትም ጭምር፣ በ1997 ዓ.ም በወጣላቸው እቅድ እየሄዱ እንዳልሆነ፣ በ2001 ዓ.ም በአዲስ አድማስ ሲዘገብ አስታውሳለሁ። 

የተንዳሆ ግድብ፣ በ98 ዓ.ም፣ ከዚያም በ99 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ተመድቦለት በፓርላማ ከፀደቀ በኋላ፣ ምን እንደተከሰተ የሚዘረዝር ሌላ ሰፊ ዘገባም በዚሁ ጋዜጣ ቀርቧል። በሰፊው መቅረቡ አለምክንያት አይደለም። በየአመቱ የሚመደበው ገንዘብ ቀላል አይደለም። ከመቶ ሚሊዮን ብሮች እስከ ቢሊዮን ብር ይደርሳል። ግን፣ ግድቡ ተገንብቶ አላለቀም። እንደገና፣ የ2000 ዓም. በጀት ሲዘጋጅም፣ ገንዘብ ተመደበለት – የግድብ ግንባታውን ዘንድሮ ለማጠናቀቅ በሚል። ግን አልተጠናቀቀም።

በቀጣዮቹ አመታትም… በ2003፣ ከዚያም በ2004… ምንም የተቀየረ ነገር የለም። የበጀት ሰነዶቹ ላይ፣ አረፍተ ነገሮቹ እንኳ አይቀየሩም። “የተንዳሆ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቀ…” የሚለው ፅሁፍ “ኮፒ ፔስት” እየተደረገ በየአመቱ ይደጋገማል – ዓመተ ምህረቱ ብቻ እየተቀየረ።

የመንግስት ቴሌቪዢን ግን፣ እውነታውን ከመዘገብ ይልቅ (እናም መፍትሄ እንዲበጅለት ከማሳሰብ ይልቅ)፣ የአዲስ አድማስ አይነት ዘገባዎችን ለማስተባበል ነበር የሚተጋው – ፕሮጀክቶቹ፣ በተያዘላቸው እቅድ በጊዜ እየተገነቡ ነው’ እያለ። 
ለዚህ ምላሽ እንዲሆንም ይመስላል፣ “እንደ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመሳሰሉ ትልልቆቹ እቅዶች’ኮ ለአመታት እየተጓተቱ እስከ ዛሬ መዝለቃቸውን ራሱ መንግስት አይክደውም” የሚል ፅሁፍ በአዲስ አድማስ የታተመው (ሰኔ 2 ቀን 2004 ዓ.ም)። “መቼ ነው መንግስት፣ የማይሳኩትን እቅዶች በግልፅ የሚነግረን” በሚል ርዕስ የቀረበ ትንታኔ ላይ ከተጠቀሱት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ፣ የተንዳሆው ፕሮጀክት ነው። አዲስ አድማስ እንዲህ፣ እውነተኛ መረጃዎችን በመስከረም 2005 ዓ.ም ሲዘግብ፣ የመንግስት ሚዲያ በዚያ ሰሞን ምን ዘገበ?

መስከረም 3 ቀን 2005 ዓ.ም የኢዜአ ርዕስ እንዲህ ይላል – “የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በቀጣዩ ጥር ወር በከፊል ወደ ሥራ ይገባል”።

ለነገሩ፣ የመንግስት ሚዲያ፣ በቀላሉ ለእውነተኛ መረጃ “ፊት ይሰጣሉ” ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ለመረዳት ከፈለጋችሁ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተርን ሪፖርት መመልከት ትችላላችሁ። የተንዳሆ ፕሮጀክት፣ እጅጉን እንደተጓተተና በከፍተኛ የሃብት ብክነት እንደተዝረከረከ፣ ዋናው ኦዲተር ሰፊ ዝርዝር ሪፖርት ያቀረበው በ2006 ዓ.ም ነው። አዲስ አድማስ ይህንን ዘግቧል። በመንግስት ሚዲያ ግን አልተዘገበም።
ሰሞኑን ድንገት ተነስቶ ግን ፕሮጀክቱ ለዓመታት መጓተቱን የሚገልጽ ዘገባ አሰራጨ፡፡ ለዓመታት ለተጓተተ ፕሮጀክት ለዓመታት የተጓተተ ዘገባ !!

እስኪ ይህን የኦዲት ሪፖርት ተመልከትና አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለምን እንደታሰሩ ንገረኝ?

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተጠርጥረው የታሰሩት “የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተውና ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ያልተጠናቀቁና ችግር ያለባቸውን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደተጠናቀቁና ያላንዳች ችግር ግንባታቸው እንዳለቀ አስመስለው በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል” በሚል እንደሆነ የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል፡፡ ነገር ግን፣ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ያለውን ሁኔታ ለማጤን መረጃዎችን ሳፈላል በ2003 ዓ.ም የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ኘሮጀክቶች አፈፃፀምን አስመልክቶ ያቀረበው የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት (pdf) አገኘሁ፡፡ ይህ ሪፖርት በውስጡ ከያዛቸው አስገራሚ መረጃዎች ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር (ገ/ኢ/ል/ሚ)  በየወሩ የአፈፃፀም ሪፖርት የሚያቀርበው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን “ብቻ” መሆኑንና ሌሎች መስሪያ ቤቶች ግን በጭራሽ ሪፖርት እንደማያደርጉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ የገ/ኢ/ልማት ሚኒስቴር ስለተገኘው የክትትልና የግምገማ ውጤት ሚኒስቴር በየሩብ ዓመቱና በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ እንዳቁሞ እንደነበር መርዶ ይነግረናል፡፡  

እያንዳንዱ የልማት ፕሮጀክት ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ካልገጠሙ በቀር፣ በተዘጋጀለት የጥናት ሰነድ ላይ በተመለከተው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሊጀመርና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እና የገንዘብ መጠን መሰረት መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ ፕሮጀክት ለማወቅ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በ2003 ዓ.ም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ገፅ 28 ላይ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና የገንዘብ መጠን የማይጠናቀቁ መሆኑን እንዲህ ይገልፃል፦

በኦዲቱ በናሙና ተመርጠው ከታዩት 8 የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች መካከል አምስቱ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዳልተጠናቀቁና ተጨማሪ ጊዜ እንደወሰዱ ታውቋል፡፡ እንደዚሁም በውኃ ሀብትና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሥር ከሚካሄዱት ኘሮጀክቶች ውስጥ በኦዲቱ ለናሙና የታዩት ሁለት ኘሮጀክቶች የአፈጻጸሙ ሁኔታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ የከሰም ተንዳሆ የግድብና መስኖ ልማት ግንባታ ፕሮጀክት እ.አ.አ በ2004 የተጀመረ ሲሆን በወቅቱ 1.669 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ እስከ 2002 ዓ.ም. ብቻ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ለገ/ኢ/ልማት ሚኒስቴር መ/ቤት ከቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁንም ሥራው ያልተጠናቀቀና የከሰም ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት 69%፣ የተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት 55% ያህል ብቻ እስከ 2002 በጀት ዓመት የፊዚካል አፈጻጸም መከናወኑን ከውሃ ሃብትና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክት አስተባባሪ በቃል የተገለጸልን ሲሆን ይህን የሚገልጽ የአፈጻጸም ሪፖርት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተጠይቀው “ፈቃደኛ” ሊሆኑ አልቻሉም፡፡” 

በገፅ 34 ደግሞ ኘሮጀክቱ አዋጪ መሆን/አለመሆኑ ጥናቱ ተጀምሮ ከፍተኛ ወጪ ከተደረገበት በኋላ የተቋረጠ ኘሮጀክት ስለመኖሩ የሚከተለውን በማሳያነት ይጠቅሳል፦  

“ይሁን እንጂ በኦዲቱ ወቅት፣ በግብርና ሴክተር ስር ያለው የእንስሳት ሃብት ልማት ማስተር ፕሮጀክት (በእርዳታ) ጥናት፣ የፕሮጀክት ዝግጅቱ ሁለተኛ ደረጃ (phase) ላይ ሲደርስ ተቋርጧል፡፡ ለምን ጥናቱ እንደተቋረጠ የሚኒስቴር መ/ቤቱ የፕላንና ፕሮግራም ዳይሬክተር ተጠይቀው በሰጡት መልስ፣ የፕሮጀክቱ ረቂቅ ጥናት ቀርቦ አማካሪው በተሰጠው ቢጋር /TOR/ መሰረት ስራውን ባለማከናወኑ ምክንያት በመንግስት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ስራው የተቋረጠ መሆኑንና ስራውን እንደገና መልሶ ለማስጀመር ጥረት ተደርጎም እንዳልተሳካ ተገልጿል፡፡ ከፕሮጀክቱ ጠቀሜታ አንጻር የዝግጅት ሂደቱ ሁለተኛ ደረጃ (phase) ደርሶ ለጥናት ዝግጅት የሚያስፈልገው ሃብት በ2000 በጀት ዓመት ብር 4‚922‚220፣ በ2001 በጀት ዓመት ብር 23‚480 እና በ2002 በጀት ዓመት ብር 11‚630.00 በድምሩ ብር 4‚957‚330 ወጪ ተደርጎ እንዲቋረጥ መደረጉ ታውቋል፡፡ ስለሆነም በወቅቱ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ባለመደረጉ፣ የወጣው ከፍተኛ ገንዘብ እንዲባክን ከመደረጉም በላይ ሀገሪቱ ለ20 ዓመታት የምትመራበት ማስተር ፕላን አለመዘጋጀቱ ከኘላኑ ተግባራዊነት የሚገኘውን ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያሳጣ በመሆኑ ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡” 

ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርበው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የሚቀርብ ስላለመሆኑ፦

“በፕሮጀክት አስፈጻሚ አካላት ስለ ፕሮጀክቶች የስራ አፈጻጸም በየሶስት ወሩ የክትትልና ግምገማ ውጤት ሪፖርት እየተዘጋጀ ለሚ/ር መ/ቤቱ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ስለተገኘው የክትትልና የግምገማ ውጤት ሚኒስቴር መ/ቤቱ በየሩብ ዓመቱና በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ማድረግ አለበት፡፡ ይሁን እንጂ በአስፈጻሚ መ/ቤቶች እየተዘጋጀ ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚቀርበውን የፕሮጀክቶች የሩብ ዓመት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የግምገማ እና የተጠቃለለ ሪፖርትና የግምገማ ውጤት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማይቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስለ ሁኔታው የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ፣ የፕሮጀክት አስፈጻሚዎች የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የተጠቃለለ ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት በአሁኑ ወቅት የማይቀርብ መሆኑን፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት ላለው የፕሮጀክቶች ክትትልና ግምገማ ዴስክ የአፈጻጸም ሪፖርት ይቀርብና ከመ/ቤቶች ጋር ውይይት ይደረግበት እንደነበርና ሆኖም በአሁኑ ወቅት የተቋረጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ የሪፖርቱ መቋረጥ የበላይ አካል በገንዘብና ኢኮኖሚ ል/ሚ/ር የተዘጋጀ እና የተገመገመ የፕሮጀክቶችን አጠቃላይ የሥራ ሂደት ሁኔታ የሚያውቅበት እና የሚከታተልበት መንገድ እንደሌለ የሚያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪም ከፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለበላይ አካል ቀርቦ እልባት እንዳያገኙ ያደርጋል፡፡ ስለሆነም የገ/ኢ/ል/ሚ/ር ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርብለትን የፕሮጀክቶች የሩብ ዓመት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም የግምገማ እና የተጠቃለለ ሪፖርት ለሚኒስትሮች ም/ቤት የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት ሆኖ ሳለና ተጠቃሚው ክፍል እንዳይላክ ሳይጠይቅ እንዲቋረጥ መደረጉ አግባብነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡” 

በመጨረሻም በሪፖርቱ ገፅ 36 ላይ ከአስፈጻሚ መ/ቤቶች የሚቀርበው የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት ይዘት ወጥነት የሌለውና በፕሮጀክት ክትትል መመሪያው መሰረት ስላለመሆኑ የሚከተለውን ብሏል፦

“የፕሮጀክት ስፈጻሚዎች በጸደቀው የፕሮጀክት ሰነድ መሰረት፣ በፕሮጀክት የድርጊት መርሃ ግብር፣ በክትትልና ግምገማ መመሪያ እንዲሁም በሥምምነቶች መሠረት በትክክል የፕሮጀክቱን የስራ ሂደት፣ ግብዓት፣ ውጤት፣ ስኬት እንዲሁም የፕሮጀክቱን ፋይዳ (impact) በመከታተል በየ3 ወሩ ለ/ገ/ኢ/ል/ሚ/ር ሪፖርት ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በኦዲቱ ወቅት እንደታየው፣ በዚህ የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት አቀራረብ በኩል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በጥሩ ተሞክሮ የሚገለጽ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የበጀት ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ የበጀት ባለሙያ ጋር በተደረገው ቃለ ምልልስ እና ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ከቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርቶች እንደተገነዘብነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መ/ቤት የፋይናንስ እና የፊዚካል አፈጻጸም ሪፖርት በየሩብ አመት ብቻ ሳይሆን በየወሩ ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሌሎች ሴክተሮች የሪፖርት አቀራረብ ሲታይ፣ ከጤና ሴክተር፣ ከትምህርት ሴክተር እና ከግብርና ሴክተር አስፈጻሚዎች ለገ/ኢ/ል/ሚ/ር የሚቀርበው የፕሮጀክት የፊዚካል እና የፋይናንስ አፈጻጸም ሪፖርት በሚ/ር መ/ቤቱ በተዘጋጀው የሪፖርት ማቅረቢያ ቅጽ (ፎርማት) መሰረት አለመሆኑ ታውቋል፡፡ የሚቀርበው ሪፖርትም በየሩብ አመቱ መሆን ሲገባው፣ በየ6 ወር ወይም በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ሆኖ ተገኝቷል፡፡” 

“ዓለምገና ሰርቆ-ማሣያ ሕንፃ’ጋ ጠብቂኝ!”

ብዙውን ግዜ “ሙስና” ሲባል ፖለቲካዊ ችግር እንደሆነና በመንግስት ባለስልጣናት ብቻ እንደሚፈፀም እናስባለን። በእርግጥ የመንግስት አሰራርና አመራር ለሙስና መስፋፋት አስተዋፅዖ አለው፡፡ ይህን በተመለከተ “ኢህአዴግ እና ሙስና ስጋና ነፍስ ናቸው” የሚለውን ፅሁፍ መመልከት ይቻላል። ነገር ግን፣ ሙስና ፖለቲካዊ ብቻ አይደለም። ከዚያ በተጨማሪ ሙስና የከፋ ማህበራዊ ችግር መገለጫ ነው። በመሰረቱ የሙስና ወንጀል የሚስፋፋው እንደ ሕዝብና ሀገር ያሉንን ማህበራዊ ሃብቶች (social capital) ስናጣ ወይም ማህበራዊ ኪሳራ (social deficit) እንዳለ በግልፅ ይጠቁማል። በዚህ ፅሁፍ በዓለም-ገና የሚገኘውንና በተለምዶ “ሰርቆ-ማሳያ” የሚባለውን ሕንፃ እንደ ማሳያ በመውስድ ሃሳቡን በዝርዝር እንመለከታለን።
image

ከሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የሙስና ችግር ከሚስተዋልባቸው አከባቢዎች አንዱ በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነው። በተለይ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ የሆነ መሬት ወረራና ሙስና እንደነበር ይታወቃል። ከፍተኛ የሆነ የሙስና ችግር ከታየባቸው ከተሞች ውስጥ የዓለምገና ከተማ አንዷ ናት። ለዚህ ፅሁፍ በማሳያነት የወሰድነው የሰርቆ-ማሣያ ሕንፃም የሚገኘው በዚህች ከተማ ነው። በእርግጥ “ሰርቆ-ማሣያ” የሚለው የሕንፃው ትክክለኛ መጠሪያ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የዓለምገና ነዋሪዎች ሕንፃው “የሙስና ቅርስ” መሆኑን ለመጠቆም በተለምዶ የሰጡት ስያሜ ነው።

እኔ የሕንፃውን ባለቤት በግል አላውቃቸውም። ስለ ሕንፃው ያወቅኩት ራሱ ከአዲስ አበባ ወደ ወሊሶ እየሄድኩ ሳለ ከጎኔ የነበረ አንድ ተሳፋሪ “ይህ ህንፃ ሰርቆ-ማሣያ ይባላል” ብሎ ካሳየኝ በኋላ ነው። ስለዚህ ግለሰቡን በሙስና ወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ ተጨባጭ መረጃ የለኝም። ነገር ግን፣ የዓለምገና ነዋሪዎች ስለ ግለሰቡና ስለተጠቀሰው ሕንፃ ምን ይላሉ? ይህን ለማወቅ ዛሬ ጠዋት በፌስቡክ ገፄ ላይ ስለ ሕንፃውና ግለሰቡ መረጃ ያላቸው ሰዎች እንዲጠባበሩኝ ጠያቄ ነበር።

በዚህ መሰረት ብዙ ሰዎች የተለያዩ መረጃዎችን በፌስቡክና በስልክ አድርሰውኛል። ከደረሱኝ መረጃዎች ውስጥ “የሕንፃው ባለቤት አቶ መርጋ ይባላሉ፣ በመጀመሪያ በቱሉ-ቦሎ ማዘጋጃ መዝገብ ቤት ውስጥ ይሰሩ ነበር፣ ቀጥሎ ደግሞ በዓለምገና ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመሬት አስተዳደር ክፍል ሰርተዋል፣ በአንድ ወቅት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው ነበረ፣ እንዲሁም በዓለምገና ከሚገኘው የሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ በተጨማሪ ፉሪ (Furii) በሚባል አከባቢ ሌላ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ አላቸው” የሚሉት ይጠቀሳሉ።

አሁንም ቢሆን ግለሰቡ የሙስና ወንጀል ሰርተዋል እያልኩ አይደለም። በእርግጥ ግለሰቡን በአካል አግኝቼ ብጠይቃቸው “በስርቆት ሳይሆን በራሴ ጥረት ያፈራሁት ሃብት ነው” እንደሚሉኝ አልጠራጠርም። ነገር ግን፣ በሙስና የተገኘ ሃብት ባይሆን ኖሮ የዓለምገና ነዋሪ ለሕንፃው “ሰርቆ-ማሳያ” ሣይሆን “ሰርቶ-ማሳያ” የሚል ስያሜ ያወጣለት ነበር። ግለሰቡ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል፥ አልፈፀሙም የሚለውን ለሚመለከተው አካል መተው ይሻላል። ነገር ግን፣ ግለሰቡ ሰርቶ ሆነ ሰርቆ በሕንፃው ስያሜ ላይ ብቻ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ከዚህ ቀጥሎ “ሰርቆ.ማሳያ” የሚለው ሕንፃ በዓለምገና መሃል ከተማ መገኘቱ ምን ያሳያል? እና  በማህብረሰቡ ስነ-ልቦና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንመለከታለን።

በመጀመሪያ ደረጃ የሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ ባለቤት በራሳቸው ጥረት የተገነባ ቢሆንም እንኳን አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ በሙስና የተገኘ ሃብት እንደሆነ አምኖ ተቀብሏል። በመሆኑም፣ “የሰርቆ-ማሳያ ህንፃ በከተማዋ መሃል መኖሩ ምን ያሳያል?” ለሚለው፦ አንደኛ፡- ለማህብረሰቡ የሞራል ሕግ መገዛት፣ የፀረ-ሙስና ግዴታን መወጣት፣ ሥነ-ምግባር ከጎደለው ተግባር መታቀብ፣ …ወዘተ የሚሉት ማህበራዊ እሴቶች ሙሉ በሙሉ መጣሳቸውን ያሳያል። ሁለተኛ፡- ሙስና በመንግስትና የንግድ ተቋማት ዘንድ የተለመደ ሥራና አሰራር እንደሆነ ያሳያል። ሦስተኛ፡- በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ ቅጣትና እገዳ የሚጥሉ ማህበራዊ ደንቦች ትርጉም አልባ መሆናቸውን ያሳያል። በዚህ ምክንያት፣ ለሙስና ምቹ የሆኑ ማህበራዊ እሴት፣ ልማድና ደንብ መፈጠሩን፣ ይህም ትልቅ ማህበራዊ ኪሳራ (social deficit) እንዳስከተለ በግልፅ ይጠቁማል። በአጠቃላይ፣ ሙስና የማህበራዊ ሕይወታችን አካል ሆኗል ማለት ይቻላል።

በመጨረሻም፣ ሙስና በገሃድ የሚስተዋል ችግር መሆኑ ምን ዓይነት ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል? ይህን ለመረዳት የአንድ ከተማ ማዘጋጃ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ወይም የመሬት አስተዳደር ኃላፊ ከልጁ ጋር በሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ በኩል ሲያልፍ የሚያደርጉትን ምናባዊ ቃለ-ምልልስ እንመልከት፡-

ልጅ፡- “አባዬ…ይሄ ሕንፃ ለምን “ሰርቆ ማሳያ” ተባለ?”
አባት፡- “ባለቤቱ በሙስና የሰራው ሕንፃ ስለሆነ ነው”
ልጅ፡- “የት መስሪያ ቤት ነበር የሚሰራው?”
አባት፡- “እኔ የምሰራበት ቢሮ ነበር የሚሰራው?”
ልጅ፡- “ታዲያ ስንት አመት ተፈረደበት?”
አባት፡- “ሦስት አመት ብቻ ታስሮ ተፈታ”

ከዛ ልጅ በአግራሞት በውስጡ እንዲህ ይላል “ምነው አንተም ሦስት አመት ታስረህ ሚሊዬነር ብትሆን?” አሃ… ሃቀኝነት ለአንተና ለቤተሰብህ ምን አተረፈ? ሃቀኛ ሰራተኛ ድህነት ሲሸምት፣ ሙሰኛ ሃብትና ንብረት እያፈራ፤ አንተ በቤት ኪራይ ስትኖር ሙሰኛ ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ያከራያል፤ አንደ እኔ መምህር ከሆንክ ደግሞ፣ አንተ የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጥህ ስትለምን እንደ አቶ መርጋ ያለው ደግሞ በሪል-ስቴት ቪላ ቤቶች እየሰራ በውድ ዋጋ ይሸጣል። የዓለምገና ልጆች ወደፊት መሆን የሚፈልጉት እንደ እኔ ዓይነት ደሃ የዩንቨርሲቲ መምህር ሳይሆን እንደ አቶ መርጋ ያለ የመዝገብ ቤት ሰራተኛ ነው።

በመንግስት ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ ቅጣትና ተጠያቂነት ከሌለ አብዛኛው ሰው ከመስራት ይልቅ መስረቅ ይመርጣል። እንደ ዓለምገና ባሉ ከተሞች ሙስና በአረዓያነት የሚያስጠቅስ ተግባር ሆኗል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ፣ የመሃምድ ሰልማን “ፒያሳ፡ መሃሙድ’ጋ ጠብቂኝ” በሚለውን መፅሃፍ፣ በተለይ የፒያሳን ማራኪ ገፅታና ትዝታዎች ያስታውሳል። በዚህም፣ የአዲስ አበባ ከተማን ማራኪ ገፅታና ትዝታዎች በአንባቢዎቹ አዕምሮ ውስጥ እንዲቀረፅ ያደርጋል። ነገር ግን፣ “ዓለምገና፡ ሰርቆ-ማሳያ ሕንፃ’ጋ ጠብቂኝ” ሲባል ግን፤ መስረቅ የሃጢያት ሳይሆን የሃብት ምንጭ እንደሆነ፤ ሙስና በሕግ ሆነ በሥነ-ምግባር እንደማያስጠይቅ፤…ሙስኛ ቢታሰር ምን ይሆናል – እስር ቤት ሆኖ የዘረፈውን ሃብቱን ያስተዳድራል፣ ከእስር ሲፈታ ኢንቨስተር ይሆናል። በአጠቃላይ፣ በተለምዶ “ሰርቆ-ማሳያ” የሚለው ስያሜ “መስራት ምን ሊረባኝ – መስረቅ ይሻለኛል” የሚል ዓይነት አመለካከት በማህብረሰቡ ዘንድ እንደሰረፀ ያሳያል፡፡ ሙሰኝነት፥ ስርቆት እንደ መልካም ገፅታና ተግባር ስያሜ ሆኖ ሲያገለግል ከማየት የበለጠ ማሀ ኪሣራ ያለ አይመስለኝም፡፡

“እኛ ወደብ መች ቸገረን” ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ ከዘመን መጽሔት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርገዋል። እስካሁን ድረስ ቃለመጠይቁን በሶስት ተከታታይ ክፍሎች አቅርቧል። በሶስተኛው ክፍል ከቀረበው ውስጥ ዶ/ር አርከበ ከዘመን ለቀረበላቸው “ግንቦት 20 ኤርትራንም ወደብም አሳጥቶናል የሚሉ ወገኖች አሉና ለእነዚህ ወገኖች ምላሽዎ ምንድን ነው?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ አስገራሚና አነጋጋሪ ሆኖ አግኝተንዋል፡፡ በመሆኑም፣ ጥያቄውንና የተሰጠውን ምላሽ ከመፅሄቱ ድረገፅ ላይ እንደሚከተለው ወስደናል፡፡ ******

ዘመን፡- ግንቦት 20 ኤርትራንም ወደብም አሳጥቶናል የሚሉ ወገኖች አሉና ለእነዚህ ወገኖች ምላሽዎ ምንድን ነው?

ዶክተር አርከበ፡- ስለ ወደብ የሚያነሳ ነገር ግን ስለ ሕዝብ የማያነሳና የማያስብ ግለሰብ ወይም ቡድን ብቻ ነው ስለ መሬት የሚያነሳው። አገር ማለት ሕዝብ ነው። ስለሆነም ስለ ሕዝቦች በምናስብበት ጊዜ የኤርትራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ነው መወሰድ ያለበት።

የኤርትራ ሕዝብ ምን ይፈልጋል? ለብዙ ዓመት በጦርነት ውስጥ የቆየ ሕዝብ ነው፤ ከ30 ዓመታት በላይ። ከኢትዮጵያ መገንጠል እንፈልጋለን አሉ። ይሔንን በማየት ኢህአዴግ ጦርነቱ መራዘም የለበትም ብሎ ከድል በኋላ ዓመትም ሳይሞላው ሪፈረንደም እንዲካሔድ አደረገ። በዚያን ወቅት እንደ ኤርትራ ሕዝብ ተመሳሳይ ጥያቄ የነበራቸው ሕዝቦች ነበሩ፤ እንደ ዩጐዝላቪያ ያሉ። እናም የዚያን ጊዜ የተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፈረንደሙን እንዲመራ ነበር። በዚህም 99 በመቶ የሚሆነው የኤርትራ ሕዝብ ነፃ ኤርትራን እንፈልጋለን አለ። ሕዝቡ ፍላጐቱን በድምፅ አረጋገጠ ማለት ነው። የሕዝቡ ፍላጐት ደግሞ መሟላት አለበት።

ዴሞክራሲ ማለት ለሕዝብ መቆም ማለት ነው። ማነው የመጀመሪያ አገር ኤርትራን እንደ አገር የተቀበለው? የኢትዮጵያ መንግሥት ነበር። ያ ሆኖ ሰላም ማረጋገጥ ተችሏል። ስለዚህ ያንን ያደረግነው ከሰላም፣ ከዴሞክራሲ፣ ከሕዝቦች መብት ማረጋገጥ አንፃር ነውና ይሔ መሆኑ ተገቢ ነው።

ግን ዋናው ነጥብ ምንድንነው “ወደብ ልማት ያመጣል” ብለው የሚያስቡ ሰዎች ስለ ኢኮኖሚ ልማት ምንም የማይገባቸው ሰዎች ናቸው። በአካባቢያችን ሠፋፊ ወደብና የባህር ዳርቻ ያላቸው አገሮች እነማን ናቸው? አንዷ ሶማሊያ ናት። ሁለተኛዋ ማናት? ኤርትራ ናት። ሁለቱንም እንያቸው በጥፋት ሂደት ያሉ አገሮች ናቸው። ሶማሊያ ግን አሁን በተሻለ እንቅስቃሴና መረጋጋት ውስጥ ናት። ኢኮኖሚ ልማት በእነዚህ አገራት የለም።

“እኛ ወደብ መች ቸገረን”

ስለዚህ ልማትና ዕድገትን የሚያመጣው ወደብና የባህር ዳርቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ያለ ማየት አስተሳሰብ ምንጭ ነው። እኛ ወደብ መች ቸገረን፡፡ በጂቡቲና በበርበራ መጠቀም እንችላለን። የኤርትራም ሁኔታ መቀየሩ አይቀርም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ለዘለዓለም ይኖራል ብለን አንገምትም።

በእኔ ግምት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ ለውጥ ይመጣል ባይ ነኝ። የኤርትራን ወደብ እንጠቀማለን። የኬንያን ወደብ መጠቀም እንችላለን። ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ መስመር ለመገንባት ታቅዷል። የሱዳንንም እንጠቀማለን። ቢቻል ወደብ ቢኖረን ጥሩ ነበር ግን የሁሉም መቋጫና መፍትሔ እርሱ ነው ማለት አይደለም። የሚያመጣው መሠረታዊ ለውጥም የለም በእኔ እምነት።

በውጭ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ክርክር በሚዲያ ሳይ ነበር። ከተቃዋሚዎች አንዱ “እንዴት ብለን ነው የኢትዮጵያን ውሃ ለጅቡቲ የምንሰጠው?” የሚል ሃሳብ ነው ያነሳው። እነዚህ ሰዎች በእኔ ግምት ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳላቸው አይገባኝም።

ውሃ ልከን ገቢ ብናገኝ ምንድን ነው ችግሩ? የኤሌክትሪክ ኃይል ልከን ገቢ እንደምናገኘው ሁሉ ውሃም ልከን ገቢ ብናመጣ ጉዳት የለውም ጥቅም እንጂ፡፡ ውሃ መላክ ነዳጅ ከመላክስ ምን ልዩነት አለው? ምንም ልዩነት የለውም። እና የዚህ ሰው አስተሳሰብ ልማታዊ አስተሳሰብ ነው? ጅቡቲ ያለው ሕዝብ ውሃ እየፈለገ ውሃ የጠማውን ሰው ውሃ መከልከል ተገቢ ነው? በባህላችንስ ይሔ አለ? ስለዚህ የሚነሱ ነጥቦች በጣም አሳፋሪ ናቸው።

እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ዙሪያ የእይታቸው አድማስ መለወጥ አለበት። ጊዜው ግን አልፏቸው ሔዷል። አጀንዳው ተቀይሯል። እያወሩ ያሉት ግን ከአስር ዓመት በፊት የነበረ አጀንዳ ነው። እና ችግሩ የአቋምና የአስተሳሰብ ችግር ነው።

ሰው ራሱን ለመሆን የተለየ ቦታና ግዜ መምረጥ የለበትም!

ከታች የሚታየውን አስገራሚ ፎቶ በፌስቡክ ገፄ ላይ ከለጠፍኩ በኋላ የሚሰጡት አስተያየቶች ይበልጥ አስገራሚ ሆኑብኝ። በተለይ አንዳንዶች የተወካዩን ጤንነት ሲጠራጠሩ ሳይ የግለሰቡን የግል ታሪክ ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ። ምክንያቱም፣ በተባበሩት መንግስት የሀገሩ ቋሚ ተወካይ ለመሆን የበቃን ሰው የአዕምሮ ጤንነትና ብስለት ከመጠራጠር ይልቅ ጉዳይ በዝርዝር ማወቅ ተገቢ ነው።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፓፓዋ ኒው ጊኒ (Papua New Guinea) ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር “Rai” በሀገራቸው ባህላዊ አለባበስ የተ.መ.ድን ስብሰባ ሲካፈሉ የሚያሳይ


በዚህ አመት ግንቦት ወር ላይ በተባበሩት መንግስታት የፓፓዋ ኒው ጊኒ “Papua New Guinea” ቋሚ ተወካይ በመሆን የተሾሙት ግለሰብ ስማቸው “Max Hufanen Rai” ይባላል። እ.አ.አ. በ1954 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ዛሬ ላይ የ63 ዓመት ጎልማሳና የስድስት ልጆች አባት ናቸው። በካንቤራ (Canberra) ከሚገኘው የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ “Australian National University” በዓለም አቀፍ ሕግ (International Law) የተመረቁ ሲሆን ከፓፓዋ ጊኒ ዩኒቨርሲቲ (University of Papua Guinea) ደግሞ በመጀመሪያ ድግሪ (Bachler of Arts) ተመርቀዋል።   

“Mr. Rai” እ.አ.አ. ከ1997 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በ“Federated States of Micronesia” እና “Marshal Islands”፣ እንዲሁም ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም ደግሞ በቻይና የሀገሪቱ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል። በ2013 የፓፓዋ ጊኒ የማዕድን ሚኒስትር ዋና ፀኃፊና አማካሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም ደግሞ የሀገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዋና ዳይሬክተር (Director General) በመሆን አገልግለዋል። በመጨረሻም፣ እ.አ.አ. በ2017 ግንቦት ወር ላይ በተባበሩት መንግስታት የሀገሪቱ ቋሚ መልክተኛ ሆነው ተሾመዋል።

በፎቶው ላይ እንደሚታየው “Mr. Rai” በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የተገኙት ከሞላ ጎደል እርቃናቸውን ነው። በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚገኙ የዓለም ሀገራት ተወካዮች በ”Mr. Rai” አለባበስ ከመጠን ያለፈ አግራሞት ውስጥ ገብተው እንደነበር ዘገባዎች ያስረዳሉ።

በእርግጥ ለብዙዎች የአምባሳደሩ አለባበስ ግርምትን ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን፣ አንድ ሰው ከብዙ ሰዎች ጋር አብሮ የተነሳውን ፎቶ ብትሰጡት በመጀመሪያ በዓይኑ የሚፈልገው የራሱን ፊት ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ የሚያውቀውን ሰው ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ማለት የዓለም ህዝቦች በጋራ የተነሱት ፎቶ እንደማለት ነው። የአብዛኞቻችን ተወካዮች በቋንቋም ሆነ በአለባበስ ራሳቸውን ወይም ሕዝባቸውን አይመስሉም። ከሞላ-ጎደል ሁሉም ማለት ይቻላል ከራሳቸው ይልቅ አውሮፓዊያን መስለው ነው በቦታው የሚገኙት። የፓፓዋ ጊኒ ተወካይ ግን ራሳቸው በእውን የሆኑትንና የወከሉት ማህብረሰብ መስለው ነው በስብሰባው አዳራሽ የተገኙት። ለዚህ ነው የዙሉ ጎሳ (Zulu) ተወካዮች በተባበሩት መንግስታት የደቡብ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር እንደ ፓፓዋ ጊኒ ተወካይ ራሳቸውን ሆነው፥ እኛን መስለው ይገቡ ዘንድ ጥያቄ ያቀረቡት። 

በፓፓዋ ኒው ጊኒ (Papua New Guinea) የሚገኝ ማህብረሰብ ባህላዊ አለባበስ


አንዳንድ ሰዎች በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዲህ ያለ አለባበስ ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላል። ነገር ግን፣ እንዲህ ያለ አስተያየት “አምባሳደሩ ለምን እኛን አልመሰለም?” ከሚል የራስ-ወዳድነት ስሜት የመነጨ እንኳን አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እኛ የራሳችንን ባህልና እሴት ረስተንና ትተን፣ የምዕራባዊያን ባህልና እሴትን ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ነው። ስለዚህ፣ የግለሰቡን አለባበስ የሚነቅፉ አስተያየቶች ከራስ-ወዳድነት ይልቅ “አምባሳደሩ ለምን አውሮፓዊያንን አልመሰለም?” ከሚል የአስተሳሰብ ባርነት (conceptual colonization) የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

በአጠቃላይ፣ የአምባሳደሩ አለባበስ የራሱንና የሚወክለውን ሕዝብ ባህልና እሴት የሚያንፀባርቅ ነው። በአጠቃላይ “Mr. Rai” በአለባበሱ የገለፀው ራሱን ነው። ስለዚህ፣ በተባበሩት መንግስታት የሀገሪቱ ቋሚ ተወካይ ሆኖ ወደ ኒውዮርክ ሲሄድ ሌሎችን መስሎ ሳይሆን ራሱን ሆኖ ነው። አንድ ሰው ራሱን ለመሆን የተለየ ቦታና ግዜ መምረጥ የለበትም። እያንዳንዱ ሰው ሁልግዜ ራሱን መሆን መቻል አለበት። መቼም፥ የትም ቢሆን ሰው የሆነውን ሲሆን፥ የሆነው ሲመስል ደስ ይላል። በተቃራኒው፣ በግድ እኛን ምሰል ማለት፥ ሌሎችን መስሎ መገኘት፣ በዓለም ላይ ለተፈጠሩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ዋና ምክንያት ነው።

ወይኔ…ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ!

እናንተ! ዛሬ በጣም ስድብ አምሮኛል። መሰደብ ለምጄዋለሁ። እኔያማረኝ መሳደብ ነው። ይሄው ከነጋ ጀምሮ፤ ስድብ…ስድብ፣ ስደብ…ስደብ ይለኛል፣ ያለ ወትሮዬ መሳደብ፥ መስደብ አምሮኛል። ችግሩ ማንን ልስደብ? “ራስህን ሰደብ” እንዳትሉኝ። ራሴን ሁሌ እንደሰደብኩት ነው። በሰራሁት ስራ አንድም ቀን ረክቼ አላውቅም። ስለዚህ፣ ሁልቀን ራሴን እንደወቀስኩ፥ እንደሰደብኩ ነው። ዛሬ ግን ያማረኝ ሌላን ሰው መስደብ ነው። እ…እ… የቀድሞ ጠ/ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ትዝ… አሉኝ።

ጠ/ሚ መለስ በአንድ ወቅት “’መለስ መላጣ’ ማለት ይቻላል፣ መላጣዬን መንካት ግን አይቻልም” ያሉትን ታስታወሳላችሁ? አቦ… ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልኝማ! አንድ የምሰድበው ሰው አገኘሁኝ! እንሆ ስድብና ተሰዳቢ በነፃ ተገኝቷል። ኑ እንሳደብ! “መለስ መላጣ፣ መለስ መላጣ፣ መለስ መላጣ፣….መሌ መላጣ፣ መልዬ መላጣ፣….መላጣ…ጣ…ጣ…ጣ” ኤጭ… ስድቡ መላ-አጣ!

አንድ ዓይነት ስድብ መሳደብ ይሰለቻል። አንድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ስድቡ በተሰዳቢው የተፈቀደ ሲሆን ያስጠላል። የተፈቀደ ስድብ ልክ እንደ አደረ ገንፎ ቀዝቃዛ ነው። አያረካም፣ ሺህ ግዜ ቢሳደቡት ጥም አይቆርጥም። ከዚያ ይልቅ፣ ስድብ ልክ እንደ ትኩስ ገንፎ መፋጀት አለበት። ከተሳደቡ አይቀር በድንገት ሳይጠበቅ፥ ሳይታሰብ ከፍ-ዝቅ አድርጎ ሲሆን ያረካል። ስለዚህ፣ አንዲት ቃል አስፈቅዶ “መለስ መላጣ” ማለት ስድብ አይደለም። ከሰደቡ አይቀር እንደ አበበ ገላው በእልህና ቁጭት ውስጥ ሆኖ የጭቃ ዶፍ ማውረድ ነው። ወራጅ አለ!

እዚህ ሀገር ከተፈቀደው ስድብ ውጪ መሳደብ ክልክል ነው። እንደ አበበ ገላው ዲያስፖራ ካልሆንክ በስተቀር እንደመጣልህ እሳደባለሁ ብትል መከራ ይከተልሃል። እንኳን መሳደብ ስለ አበበ ገላው የአሰዳደብ ስልት ማውራት በራሱ አመት ከስድስት ወር ያሳስራል። ለዚህ ደግሞ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ቋሚ ምስክር ነው። (ጌቾ እንኳን ለቤትህ አበቃህ!) ስለዚህ፣ ሀገር ጥለህ ካልወጣህ በስተቀር ከተሰዳቢዎች ፍቃድ ውጪ መሳደብ ያስቀጣል!

አይ አሜሪካ!… ከአሜሪካኖቹ ይልቅ ለኢትዮጲያኖች ስድብ ስትመች አኮ አይጣል! ዲያስፖራዊች፤ መለስን በስብሰባ አዳራሽ፣ ሬድዋንን በገበያ አዳራሽ፣ አቦይ ስብሃትን በሬስቶራንት፣ ግርማ ብሩን በመኖሪያ ቤት፣ …. ወዘተ እየሄዱ የፈለጉትን ባለስልጣን እንደ ይሳደባሉ። ኢትዮጲያ ውስጥ ግን እንኳን መሳደብ የአሜሪካውን ስድብ በሹክሹክታ ማውራት አትችልም።

እኔ ታዲያ የት ሄጄ ልፈንዳ፣ ማንን ምን ብዬ ልስደብ?! ለምሳሌ፣ “መለስ መላጣ” ማለት ይቻላል። ይህን የስድብ ፍቃድ ተጠቅመህ “መለስ ብሔርተኛ!” ማለት ትችል ይሆናል። ነገር ግን፣ አውቀህ ወይም አዳልጦህ “መለስ ዘረኛ” ብለህ ከተሳደብክ፣ ወይም ከጠ/ሚኒስትሩ በፊት ፓርቲያቸውን አስቀድመህ “ኢህአዴግ ሌባ፣ መለስ ዘረኛ” ብለህ ከተሳደብክ ሲዖልን በአካል ሄደህ ታየዋለህ። አቶ ኤርሚያስ ለገሰ “የመለስ ቱርፋቶች” በሚለው መፅሃፉ ገፅ 40 ላይ በካዛንቺሱ መንግስት መኖሪያ ቤት በአይኑ የተመለከተውን እውነታ እንዲህ ገልፆታል፡-

የመለስ ቱርፋቶች፡ ባለቤት አልባ ከተማ፣ ከፍል አራት፥ ገፅ 40 ላይ የተወሰደ

ታዲያ እኔ ማንን ልስደብ? ፓርቲውንና መሪውን መስደብ፥ መሳደብ ፈጽሞ አይታሰብም። ነገር ግን፣ መንግስትን ለብቻው ነጥዬ ብሰድበውስ? ሆሆይ… “ወንዴ አያሌውን ያየ መንግስትን አይሳደብም” አትሉኝም እንዴ? የወንዴ አያሌውን አድራሻ ማወቅ ለምትሹ፣ አዲስ አበባ ቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 08 የቤት ቁጥር “ጎዳና” ነው። “ወንዴ መንግስትን በመሳደቡ ምን አጋጠመው?” ለምትሉ ደግሞ ከታች በምስሉ ላይ የሚታየውን የክስ ቻርጅ እስከ መግለጫው ድረስ በጥሞና አንብቡ፡-

ከማህበራዊ ሚዲያዎች የተገኘ የክስ ቻርጅ

እሺ ታዲያ አሁን ምን ይሻለኛል? ዛሬ ስድብ—ስድብ ብሎኛል። የኢህአዴግ ፓርቲን፣ የኢህአዴግ መሪን፣ የኢህአዴግ መንግስትን መስደብ፥ መሳደብ መከራና ስቃይ ከባድ ነው። እኔ ደግሞ መሳደብ አምሮኛል። ኧ… እነአንቶኔ “ለምን ኢህአዴግን ብቻ ትሳደባለህ?” ሲሉ ይሰማኛል። ለመሆኑ ኢህአዴግን ብሰድበው ምኑ ይጎዳል? ደግሞስ ከኢህአዴግ የበለጠ መሰደብ ያለበት ከቶ ከወደየት ይገኛል? ግልፅ አይደለም? ቆይ ትንሽ ዘርዘር ላድርግላችሁ…

ኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት ነው። የኢህአዴግ መንግስት ደግሞ አስተዳደራዊ መዋቅር ነው። ድርጅትና መዋቅር ልክ እንደ ሰው-ልጅ የሞራል ስብዕና የላቸውም። በእኔ ስድብ የኢህአዴግ ፓርቲና መንግስት የሞራል ስብዕናው አይነካም። እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ክብርና ሰብዕናው አይጎዳም። ኢህአዴግን ስሰድብ ሞራላቸው የሚነካው ድርጅቱና መንግስቱ ሳይሆን በመዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው። የኢህአዴግ ፓርቲን ወይም መንግስትን ስሳደብ አንዳንድ አባላቱና አመራሮቹ በእኔ ስድብ ራሳቸውን ይሰድባሉ።

ይቅርታ! እኔ እነሱን አልሰደብኩም። እኔ የሰደብኩት ድርጅቱንና መንግስትን ነው። እነሱ ግን ስድቡን ለራሳቸው ወስደው ራሳቸውን በራሳቸው ይሰድባሉ። የሰደብኩት ድርጅትና መንግስት በራሱ የሚነካ ሞራል እና የሚናገር አንደበት የለውም። አንዳንድ የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው ሰዎች ግን በእኔ ስድብ ራሳቸውን እየሰደቡ “መንግስትን ሰድበሃል” እያሉ ይከሱኛል። የበታችነት ስሜት የተጠናወተው ሰው በስሙ ሲጠሩት እንኳን በንቀት የሰደቡት ይመስለዋል። ኢህአዴግን እኔ ብሰድበው ምንም አይጎዳም። በተሰደብን ባዮች ላይ የደረሰው ጉዳት ግን በራሳቸው የአመለካከት ችግር እንጂ በእኔ ስድብ ምክንያት የተፈጠረ አይደለም። ስለዚህ፣ ወሳኙ ነገር የእነዚህን ሰዎች የአመለካከትና ግንዛቤ መለወጥ ነው። ይሁን እንጂ፣ ኢህአዴግና መንግስት ተሰደበ እያሉ ምስኪኖችን መወንጀል፥ ማሰር፥ መቀጥቀጥ፥ … ራስን በራስ መስደብ ነው።

ሌላው ከኢህአዴግ የበለጠ መሰደብ ያለበት ከቶ ከወደየት ይገኛል? እኔ የምለው፣ ማጅራቴን አንቆ አላላውስ ካለኝ የጭቆና ቀንበር ሌላ ማንን ልስደብ ኖሯል? ስኳር፥ ዘይት፥ ዱቄት፣…የግብር ጭማሪ፥ የበጀት ጭማሪ፥ የደመዋዝ ጭማሪ፣… መብራት፥ ውሃ፥ ኔትዎርክ፣…ኢኮኖሚ፥ ፖለቲካ፥ ትምህርት፣… በፀረ-ሽብር ሌላ ሽብር፣ በሰላምና ልማት በደልና ግፍ፣¸መብትና ነፃነትን በጉልበትና ፍርሃት፣ … ስንቱ ተዘርዝሮ ይቻላል! እንደው በጥቅሉ፣ መቼ መኖር፥ መታሰር፥ መገረፍና መሞት እንዳለብኝ በመወሰን ፈጣሪ የሰጠኝን የሕይወት ፀጋ ከቀማኝ ኢህአዴግ የበለጠ ስድብና መሰደብ የሚገባው ያለ ሌላ አካል አለ እንዴ?ይኄው ዛሬ ከነጋ ጀምሮ ኢህአዴግን ስደብ…ስደብ ይለኛል።

እንዴ…በቃ አማረኝ! ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ! ታፈንኩ፥ አፈነኝ! ብሶት፥ ቁጭት፥ ምሬት ወስጤን አቃጠለኝ። በነፃነት ማሰብ፥ መናገርና መፃፍ ወንጀል መሠለኝ። የኢህአዴግ ስራው ቀርቶ ስሙ ራሱ አስጠላኝ። የእሱ የሆነ ነገር ሁሉ ገማኝ፥ ጠነባኝ! ነፃነት ናፈቀኝ፣ በፍርሃት መኖር ሰለቸኝ። ኢህአዴግ እጅግ በጣም አስጠላኝ! ስድብ አማረኝ! ኢህአዴግን መስደብ አማረኝ! ምን ያደርጋል ታዲያ መሳደብ ሳልጀምር ስድብ አለቀብኝ ወይስ ፍርሃት አነቀኝ?

የኢህአዴግ “የደርግ ናፋቂዎች” እና የእናቴ “ጭራቅ” አንድ ናቸው!

ውድ ተማሪዎች “በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ አከባቢ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ለተከሰተው የፀጥታ ችግር እንደ ዋንኛ መንስዔ ሊሆን የሚችለው የቱ ነው?” ለሚለው የጥያቄ “የደርግ ሥርዓት ናፋቂዎች የፈጠሩት ችግር” ተብሏል። “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” ማለት ምን ማለት ነው? የደርግን ስርዓት የሚናፍቁትስ እነማን ናቸው።

image

በእርግጥ እናንተ የደርግ ስርዓትን በተግባር አታውቁትም። የደርግ ስርዓት ሲወድቅ እኔም ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። በእርግጥ ቤተሰቦቻችሁ የደርግ ስርዓትን ሊያውቁት ይችላሉ። በተለይ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የደርግ ስርዓትን በተግባር ኖረው አይተውታል። እኔና እናንተ ግን የደርግ ስርዓትን ባንኖርበትም መፅሃፍ በማንበብ፣ በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን በመጠየቅ ማወቅ እንችላለን።

በተለይ ደግሞ በቀይ-ሽብር ዘመን የደረሰውን በደልና ጭፍጨፋ በሰው-ልጅ ታሪክ እጅግ አሰቃቂ የሚባሉ ድርጊቶች በኢትዮጲያኖች ላይ እንደተፈፀመ እንገነዘባለን። ለምሳሌ፣ እኔ ሰሞኑን ሳነብ ያገኘሁትን አንድ መረጃ ላካፍላችሁ። የቀይ-ሽበር ዘመቻ በተጀመረ የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ብቻ እንደ እናንተ ያሉ 5000 ተማሪዎች እንደ አውሬ ታድነው ተገድለዋል፣ 30000 ደግሞ ታስረዋል። በጠቅላላ በቀይ-ሽብር ዘመን የተገደሉት ኢትዮጲያኖች ብዛት 500000 (ግማሽ ሚሊዮን) ይደርሳል።

ከቀይ-ሽብር በኋላ ደግሞ ለምሳሌ በትግራይ ሃውዜን ባፈፀመው የአየር ድብደባ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 1800 ንፁሃን ዜጎችን ገድሏል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የደርግን አስከፊነት በግልፅ ለመረዳት እንዲያግዛችሁ፣ በሸገር ሬድዮ ጣቢያ “የጨዋታ እንግዳ” ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩና ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብይ መኮንን ጋር ያደረገችውን ጭውውት ከጣቢያው ድህረ-ገፁ ላይ አውርዳችሁ ብታዳምጡት ብዙ ጠቃሚ መረጃዎች ታገኙበታላችሁ።

አያችሁ ተማሪዎች፣…”የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” ማለት ይሄን ሁሉ መከራና ስቃይ የሚናፍቁ ሰዎች ማለት ነው። በእርግጥ በሰው ልጅ ታሪክ እንዲህ ያለ የመከራና ስቃይ ዘመን የሚናፍቁ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው። በእርግጥ እንዲህ ያሉ ሰዎች እርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ያንን አሰቃቂ ዘመን እያስታወሱ እኔና አናንተን በነፃነት እንዳንናገር፥ እንዳናስብ በፍርሃት ቆፈን መለጎም የሚሹ ሰዎች ናቸው።

ውድ ተማሪዎች፣ የእናንተ ወላጆች ያደርጉ እንደሆነ እኔ አላውቅም። እኔ ልጅ ሳለሁ ግን “ዋ…ጭራቅ ይበላሃል” እያለች ታስፈራራኝ ነበር። ለምሳሌ፣ “ወንዝ ውስጥ ብቻህን ከተቀመጥክ “ጭራቅ” ይበላሃል” ትለኛለች። ማታ ማታ እያለቀስኩ ሳስቸግር “ጆሮ የሚቆርጠው ሰውዬን ልጥራው” ትለኛለች። እኔም ካደኩ በኋላ፣ ታናሾቼን “ጆሮ ቆራጩ መጣ!” እያልኩ አስፈራርቼያለሁ። …ሌላ እናንተ የተባላችሁት ነገር ካለ ጨምሩበት። ነገር ግን፣ ጭራቁም ሆነ ጆሮ-ቆራጩ ማስፈራሪያ እንጂ በእውን የሉም። በአጠቃላይ፣ ልጆች ሲያስቸግሩ ታላላቆቻችን ለማስፈራሪያነት የፈጠሯቸው አስፈሪ ምናባዊ ምስሎች ናቸው።
    
በተመሳሳይ፣ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” የሚለው እንደ እናንተ ያሉ ወጣቶችን ለማስፈራራት የፈጠረው አሰቃቂ ምናባዊ ምስል ነው። ከኢህአዴግ መንግስት በስተቀር የደርግን ስርዓት የሚናፍቅ አንድም ኢትዮጲያዊ የለም። ውድ ተማሪዎች፣ አሁንም ደግሜ የምላችሁ፣ ሀገርን መሃን ያደረገ፣ አንድ ትውልድን ያጨናገፈን የደርግ ስርዓት የሚናፍቅ ኢትዮጲያዊ በጭራሽ የለም።

ልክ በሕፃንነት እድሜዬ እናቴን ሳስቸግር “ጭራቅ ይበላሃል፣ ጮሮ ቆራጩን ልጥራው፣…” እያለች እንደምታስፈራራኝ ሁሉ የኢህአዴግ መንግስትም እኔና እናንተን ለማስፈራራት የፈጠረው ምናባዊ ድርሰት ነው። ከ2008 ዓ.ም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለታየው የፀጥታ ችግር ዋና መንስዔው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ በአደባባይ እንዳመነው “የመልካም አስተዳደር ችግር” ነው። የተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚያነሱት የመብትና ነፃነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በወታደርና በጥይት ለማፈን ጥረት በማድረጉ የተከሰተ ችግር ነው።

በአጠቃላይ፣ አሁን በፈተናችሁ ላይ የተጠቀሰው “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች የፈጠሩት ችግር” የሚለው ልክ እንደ እናቴ “ጭራቅና ጆሮ-ቆራጩ ሰውዬ” የፈጠራ ድርሰት ነው። ልዩነቱ እናቴ ስላስቸገርኳት ትቆጣኛለች፣ ታስፈራራኛለች፣ ትገርፈኛለች። የኢህአዴግ መንግስት ግን መብትና ነጻነቴን ስለጠየቅኩት ያስረኛል፣ ይደበድበኛል፣ ይገድለኛል! እናቴ እኔን በስነ-ምግባር አንፃ ልታሳድገኝ ነው፣ ኢህአዴግ ግን የዜግነት መብቴን ነፍጎ የራሱን እድሜ ለማራዘም ነው።