​የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል!

በሕገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓት በምትመራ ሀገር፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፤ ህወሓት፥ ብአዴን፥ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ጥምረት የሚመራ ሆኖ ሳለ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ህወሓትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አድሏዊነት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ ይሄ እውነታ እንጆ አድሏዊነት አይደለም። ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ የፌደራል ስርዓቱና ተቋማት፣ እንዲሁም የክልል መንግስታትና ተቋማት የሚተዳደሩበት ሕግ፥ ስርዓትና መዋቅር በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። 
የፖለቲካ ጨዋታውን ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይጫወታሉ። የጨዋታውን ሕግ በማፅደቁ ሂደት ሁሉም ተሳታፊዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ ሕጉ የተረቀቀበት ፅንሰ-ሃሳብ የህወሓት ነው። ይህ የጨዋታ ሕግ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ሲሆን የሕገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ደግሞ በህወሓት የብሔር ፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በመሆኑም የፌደራሉ መንግስትና ተቋማት ይህን የፖለቲካ መርህና አመለካከት ተግባራዊ ለማድርግ የተቋቋሙ ናቸው። 

የሕጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ፣ በሁሉም ደረጃ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች ለሕገ መንግስቱ ተገዢ መሆን አለባቸው። ነገር ግን፣ የሕገ መንግስቱ ትርጉምና ፋይዳ በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ፣ ለሕገ መንግስቱና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ተገዢ መሆን ለህወሓት ተገዢ ከመሆን ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው።

በአጠቃላይ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ከተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ህወሓት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ምክንያቶች፤ አንደኛ፡- መንግስታዊ ስርዓቱ በህወሓት የፖለቲካ መርህና መመሪያ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ሁለተኛ፡- ይህ የፖለቲካ መርህና አመለካከት ፍፁም ስህተት ስለሆነ፣ ሦስተኛ፡- የሥልጣን የበላይነቱን ለማስቀጠል እጅግ አደገኛ የሆነ ሸርና አሻጥር እየፈፀመ ስለሆነ። እነዚህን ችግሮች አንድ ላይ አያይዤ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።  

የዳግማዊ ወያነ ወይም የሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የትግራይ ህዝብን የለውጥ ፍላጎት የብሔርተኝነት ስሜት በመቆስቆስ እና በራስ የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የቀድሞ የህወሓት (TPLF) መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመርና የንቅናቄ ስልት “…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one” በማለት ገልፀውታል። 

ነገር ግን፣ ከህወሃት ብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ያነሰ ክብርና ዋጋ በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። የትጥቅ ትግሉን ለማስጀመር በትግራይ ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃን ስነ-ልቦና ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የአክራሪ ብሔርተኝነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ የተበዳይነትና ወገንተኝነት ስሜት ፈጥሯል። ከደርግ ጋር በተካሄደው ጦርነት የተፈጠረው ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ ፍርሃትና ጥርጣሬ ተቀይሯል። 

የዘውግ ብሔርተኝነት እና በራስ የመወሰን መብት ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር (mobilization) ተጠቅሞ ወደ ስልጣን የፖለቲካ ቡድን የተበዳይነትና ጠላትነት አመለካከት ያለው፣ ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት የሚመለከት ይሆናል። በሕወሃት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ያረፉበት ነው። 

በመጀመሪያ ደረጃ ሕወሃት ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክልና በጦርነት ወቅት በተፈጠረ ከፍተኛ የተበዳይነት፥ ጠላትነትና ፍርሃት አመለካከት የሚመራ ድርጅት እንደመሆኑ በድርጅቱ መሪነትና የፖለቲካ መርህ ላይ ተመስርቶ የተዘረጋው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የሕወሃትን የስልጣን የበላይነት የማስቀጠል ዓላማ ያለው ነው። 

ሁለተኛ እንደ ሕወሃት ያለ የፖለቲካ ቡድን ሌሎች አብላጫ ድምፅ ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይጀምሩ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም አብላጫ ድምፅ ያላቸው ማህብረሰቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ ማድረግ ከቻሉ የአነስተኛ ብሔር የስልጣን የበላይነትንና ተጠቃሚነትን በቀላሉ ያስወግዱታል። ስለዚህ አብላጭ ድምፅ ያላቸውን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጎሳ፥ ብሔርና ቋንቋ በመከፋፈል የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ እና የተቀናጀ ንቅናቄ እንዳይኖራቸው ማድረግ አለበት።

እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን የቆመለትን የአንድ ወገን የስልጣን የበላይነትን ሊያሳጣው የሚችል ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ለውጥና መሻሻል፣ ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ ለማስተነገድ ዝግጁ አይደለም። በተለይ ደግሞ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሃሳብና ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም። በዚህ ምክንያት፣ ላለፉት 25 ዓመታት ሕወሃት/ኢህአዴግ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሳውን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት ለማፈን ጥረት አድርጓል። 

በመሰረቱ ሕወሃት የስልጣን የበላይነቱ በሕገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በዚያ ረገድ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል ለማድረግ ዝግጁ አይደለም። በመሆኑም እያንዳንዱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ጥርጣሬ ይመለከታል። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት በማዳፈን ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እና የፖለቲካ ልሂቃን መንግስትን እንዲፈሩ፣ በዚህም የስርዓቱን ሕልውና ለማስቀጠል ጥረት ያደርጋል። 

በእርግጥ ፍርሃት (fear) የሕወሃት መርህና መመሪያ ነው። ሆኖም ግን፣ በየትኛውም ግዜ፥ ቦታና ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፖለቲካዊ ጥያቄ እኩልነት (equality) ነው። የሁሉም መብትና ነፃነት እስካልተከበረ ድርስ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄን ከማንሳት ወደኋላ አይሉም። እንደ ሕወሃት ያሉ ጨቋኞችም የመብትና ነፃነት ጥየቄ ባነሳው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ጥያቄው ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ፣ ሕወሃት ከሚፈጥረው ሽብርና ፍርሃት ይልቅ እድሜ ልክ በተገዢነትና ጭቆና መኖር ይበልጥ ያስፈራል። 

ዛሬ የሕወሃትን የሰልጣን የበላይነት የሚቃወም፣ በጭቆና ተገዢነት መኖር የሚጠየፍ ትውልድ ተፈጥሯል። ስለዚህ፣ ወይ የሕወሃት የበላይነት በለውጥና ተሃድሶ ያበቃል፣ አሊያም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሕዝባዊ አመፅና አምቢተኝነት ይፈርሳል። በመሆኑም የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል። ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚታየውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በሸርና አሻጥር ወደ ሁከትና ብጥብጥ በመውሰድ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማዳፈን የሚደረገው ጥረት ሁለተኛውን የለውጥ ጉዞ ከማፋጠን የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ የለውም። 

Advertisements

“ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”፡ ​የኦሮሚያ-ሶማሌ ግጭት ለምን፥ እንዴት፥ በማን ተፈጠረ?

“ኢትዮጲያ፡ በግራ መጋባት ወደ እርስ በእርስ ግጭት” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅኁፍ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራሮችን ጨምሮ አብዛኞቹ ልሂቅ በወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ግራ መጋባት ውስጥ እንዳሉ ለመጠቆም ሞክሬ ነበር። በተለይ በኦሮሚያና ሶማሌ አጎራባች አከባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ብዙ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። ግጭቱ ለምን፥ እንዴትና በማን እንደተጀመረና ሀገሪቷ ወደየት እያመራች እንደሆነ ለመረዳት መንግስታዊ ስርዓቱ የሚመራበትን መርህ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። 

የኢህአዴግ መንግስት ሕልውና በሕገ መንግስቱ ላይ የተመሰረተ ነው። ለዚህ ነው የኢህአዴግ መንግስት “ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን” በሚል መርህ የሚመራው። በዚህ መርህ የሚመራበት መሰረታዊ ዓላማ የሕገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆችና መብቶች ለማሰከበር ሳይሆን የራሱን ሕልውና ለማረጋገጥ ሲል ነው። 

የሶማሌ ክልል ፕረዘዳንት አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)

ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ “Aristotle” ስለ ፖለቲካዊ ስርዓት ጥልቅ ትንታኔ በሰጠበት “Politics” የተሰኘ መፅሃፉ እንደ ኢህአዴግ ያሉ መንግስታት “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር” በሚል በስልጣን ላይ የሚቆዩባቸው ሁለት ዓይነት ስልቶች እንዳሉ ይገልፃል። እነዚህም ስልቶች የመጀመሪያው የሕገ መንግስቱን አጥፊዎች ማጥፋት ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ የሕገ-መንግስቱን አጥፊዎች በመፍጠር ነው። ከዚህ በመቀጠል የተጠቀሰውን መፅሃፍ ዋቢ በማድረግ እነዚህን ስልቶች ከሀገራችን ነባራዊ እውነታ ጋር አያይዘን እንመለከታለን።  

1ኛ) አጥፊዎችን በማጥፋት “ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”

በ1997ቱ ምርጫ ኢህአዴግ ሕገ መንግስቱን በከፊል ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሮ መሬት ወድቆ አፈር ልሶ ነው የተነሳው። ከዚያ በኋላ እንደ ቆሰለ አውሬ አደረገው። በወቅቱ ተቃዋሚዎች በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ቀጥተኛ የሆነ የሕልውና አደጋ እንደጋረጡበት ይታወቃል። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት ተቃዋሚዎችን ልክ እንደ “የሙት መንፈስ” ይፈራቸው ጀመረ። ስለዚህ “በሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የመቀልበስ ሙከራ አድርገዋል” በሚል ሰበብ ዋና ዋና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን ለእስርና ስደት ዳረጋቸው። እንዲህ ያለውን የፖለቲካ እርምጃ “የሕገ መንግስቱን አጥፊዎች ማጥፋት” እንደሆነ “Aristotle” እንደሚከተለው ገልፆታል፡-   

 “…it is evident that if we know the causes which destroy constitutions, we also know the causes which preserve them; for opposites produce opposites, and destruction is the opposite of preservation.” Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 108

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ባሉት አመታት የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሉን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ድምጥማጡን በማጥፋት በቀጣዩ የ2002ቱ ምርጫ 99.6% ማሸነፉ ይታወሳል። በዚህ ረገድ በአብነት የሚጠቀሰው የፀረ-ሽብር አዋጁ ነው። ይህ አዋጅ ከሃሳብ እስከ አተገባበሩ ድረስ የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆችና ድንጋጌዎች ይጥሳል። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥…ወዘተ የተከሰሱት በፀረ-ሽብር አዋጁ ነው። ከሞላ ጎደል ሁሉም የተከሰሱት “እንደ ኦነግ፥ ግንቦት7፥ ኦብነግ፥ የኤርትራ መንግስት፥ አልሸባብ ወይም ሌሎች የውጪ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ አሲረዋል” በሚል ነው። 

ከአስር አመት በኋላ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃ ሚዲያና ገለልተኛ የሲቭል ማህበራት በሌሉበት በተካሄደው የ2007ቱ ምርጫ ኢህአዴግ “100% አሸነፍኩ” ብሎ መላው ዓለምን አስገረመ። ይህ ከ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ ለኢህአዴግ መንግስት ህልውና ቀጥተኛ አደጋ የነበረውን የተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድን ሙሉ በሙሉ ከሀገሪቱ ማጥፋቱን ያረጋገጠ ነበር። ተቃዋሚዎችን ከማጥፋት ጎን ለጎን የኢህአዴግ መንግስት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ለማረጋገጥ በውሸትና ግነት የተሞሉ ፕሮፓጋንዳ ይነዛል።  

በዚህ ረገድ ተቃዋሚ ኃይሎችን በግልፅ “ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማት፣ የኒዮ-ሊብራል አጀንዳ አራማኞች፣  የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች፣ ጠባብ ብሔርተኞች፣ የትምክህት ኃይሎች፣ የደርግ ናፋቂዎች…” በማለት በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ጥረት ያደርጋል። በሌላ በኩል ራሱን የአዲሲቷ ኢትዮጲያ ፍትህ፥ እኩልነት፥ ሰላምና ልማት ዋስትና እንደሆነ አድርጎ ያቀርባል። ለምሳሌ “አስማተኛው የ11% ፈጣንና ተከታታይ እድገት፣ ብዙሃንነትና የብሔሮች እኩልነት፣ የፌደራሊዝም ስርዓት፣ በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ደሴት፣….” ነገር ግን፣ ለአስር አመት በ11% የኢኮኖሚ እድገት እና በ100% ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሲያደነቁረው የነበረው ሕዝብ በ11ኛ አመቱ ገንፍሎ አደባባይ ወጣ። 

የኢህአዴግ መንግስት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በ2007 ዓ.ም የተነሳውን ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ያደረገው ጥረት አልተሳካም። ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡትን ዜጎች በመግደል፣ በመደብደብና በማሰር ለማስቆም ያደረገው ጥረት ጭራሽ ችግሩን ይበልጥ አባባሰው። እንደ “Aristotle” አገላለፅ፣ እዚህ ጋር የኢህአዴግ መንግስት አደጋውን ለመከላከል የስልት ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ይገልፃል፡- 

“In the first place, then, men should guard against the beginning of change, and in the second place they should not rely upon the political devices of which I have already spoken invented only to deceive the people, for they are proved by experience to be useless.” Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 108

ይሁን እንጂ፣ በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ወደ አማራ ክልል ተስፋፋ። በ2008 ዓ.ም የመጀመሪያ አጋማሽ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ የወጡትን ዜጎች “ፀረ-ሰላምና ፀረ-ልማት፣ የኒዮ-ሊብራል አጀንዳ አራማኞች እና የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች፣ የደርግ ናፋቂዎች… ወዘተ” በሚል በተለመደው መልኩ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት አደረገ። የኢህአዴግ መንግስት የሕዝቡ ጥያቄ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ መሆኑን ተቀብሎ፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኢትዮጲያ ሕዝብ ይቅርታ ከጠየቁ በኋላም የተቀየረ ነገር የለም። በመጨረሻ በሐምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሳው ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ እርስ-በእርስ የመቀናጀትና የመደጋገፍ አዝማሚያ እያሳየ ሲመጣ አንድ አዲስ ፖለቲካዊ ክስተት ተፈጠረ። 

2ኛ) አጥፊዎችን በመፍጠር “ሕገ-መንግስቱን እንጠብቃለን”

የሶማሌ ክልል ፕረዜዳንት የሆኑት አቶ አብዲ ኢሌ የፌደራሉ መንግስት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተስፋፋውን ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት የክልሉን “ልዩ ፖሊስ” ሊጠቀም እንደሚችል በይፋ ተናገሩ። በመቀጠል ለትግራይ ክልላዊ መስተዳደርና ገዢው ፓርቲ ህወሓት ድጋፍና አጋርነታቸውን አሳዩ። በተቃራኒ የአማራና ኦሮሚያ ክልል መስተዳደሮችን ለፌደራል ስርዓቱ አደጋ የሆነ እንቅስቃሴን መቆጣጠር ተስኗቸዋል በሚል መተቸት ጀመሩ። በመጨረሻም የኦህዴድ/ኢህአዴግ እና የክልሉ ፕረዜዳንትን በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግንኙነት እንዳለው በድፍረት ተናገሩ። 

የኦሮሞና አማራ ሕዝብ ያነሳውን የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በይፋ ለመቃወምና ሕዝባዊ ንቅናቄውን በኃይል ለማዳፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ፍቃደኝነታቸውን የገለፁት ግለሰብ፥ ፕ/ት አብዲ መሃመድ ኦማር (አብዲ ኢሌ) ማን ናቸው? በኦሮሚያና አማራ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ከፌደራል መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ጎን ይሰለፋል ያሉት ልዩ ፖሊስ የተቋቋመበት ዓላማና ተግባር ምንድነው? ይህ ኃይል አሁን በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አጎራባች አከባቢዎች ለተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት የነበረው ሚና ምንድነው? እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ ስለ ልዩ ኃይሉ እና ዋና አዛዡ አመጣጥ ወደኋላ ተመልሰን እንመልከት። 

በመጀመሪያ ደረጃ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የተመሰረተው እ.አ.አ. በ2007 (1999 ዓ.ም) ነው። ልዩ ኃይሉ የተቋቋመበት መሰረታዊ ዓላማ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን (ONLF) በክልሉ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መግታት ነበር። የአሁኑ የሶማሌ ክልል ፕረዜዳንት አብዲ ኢሌ ደግሞ በወቅቱ የልዩ ኃይሉ ዋና አዛዥ ነበሩ። በቀጠይ ጥቂት አመታት ውስጥ በአብዲ ኢሌ የሚመራው የክልሉ ልዩ ኃይል የአማፂያኑን እንቅስቃሴ መግታቱ ይነገርለታል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ልዩ ኃይሉ የተከተለው የውጊያ ስልት ነው። 

አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ባለው ማህብረሰብ ውስጥ ለአማፂያኑ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው የተጠረጠሩ ነዋሪዎችን መጨፍጨፍ ነው። የተባበሩት መንግስታት እና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት አብዲ ኢሌ የሚመራው ልዩ ኃይል ጦርነት የገጠመው ከአማፂያኑ ሳይሆን ከሕዝቡ ጋር ነው። በራሱ ሕዝብ ላይ ጦርነትና ሽብር በመክፈት አማፂያኑን ከውስጡ እንዲያስወጣ ማስገደድ። በዚህም በስልጣን ላይ ያለውን የክልሉን መንግስት ሳይወድ በግድ እንዲደግፍና እንዲቀበል አድርጎታል። ይህ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የተካነበት የራስን ሕዝብ በማሸብር ተቀባይነት የማግኘት ስልትን “Aristotle” አጥፊዎችን በመፍጠር ስርዓቱን መጠበቅ መሆኑን ይገልፃል፡- 

“Constitutions are preserved when their destroyers are at a distance, and sometimes also because they are near, for the fear of them makes the government keep in hand the constitution. Wherefore the ruler who has a care of the constitution should invent terrors, and bring distant dangers near, in order that the citizens may be on their guard,… No ordinary man can discern the beginning of evil, but only the true statesman.” Source: Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 109

እ.አ.አ. በ2010 (2002) ዓ.ም አቶ አብዲ ኢሌ በአማፂያኑ ላይ ያስመዘገቡትን “ስኬት” ተከትሎ የክልሉ ፕረዜዳንት ለመሆን በቁ። ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም በክልሉ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ ሽብርና ጥቃት ሲፈፅሙ እንደነበር “human rights watch” የተባለው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል። እ.አ.አ. ከ2015 (2007/08) ዓ.ም ጀምሮ ግን ከላይ የተጠቀሰውን የውጊያ ስልት በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በሚገኙ አከባቢዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። በዚህ መልኩ የተጀመረው ጥቃት ዛሬ ላይ ከ140ሺህ በላይ ዜጎችን አፈናቅሏል። ከ200 ንፁሃን ዜጎች ደግሞ  ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የሶማሌ ልዩ ኃይል በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ነዋሪዎች ላይ ሽብርና ጥቃት የጀመረው ልክ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው አመፅና ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት የ2008 አመት መገባደጃ ላይ ነው። የክልሉ ልዩ ኃይል እና ዋና አዛዡ የሶማሌ ክልል ሕዝብን በመጨፍጨፍና በማሸበር የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርንን ከክልሉ ለማስወጣት የተፈጠሩ እንደሆነ ተገልጿል። በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ እየፈፀሙት ያለው ጥቃትና ሽብር መጀመሪያ ከተፈጠሩበት ዓላማ ጋር ፍፁም አንድና ተመሳሳይ ነው። ይኸውም የኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጥቃትና ሽብር በመፈፀም የክልሉ ሕዝብ ያነሳውን የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማኮላሸት ነው።  

ከዚህ በተጨማሪ፣ የክልሉ ፕረዜዳንት ትላንት ከሀገር ሽማግሌዎችና የክልሉ መንግስት አመራሮች ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ለተፈጠረው ግጭት በምክንያትነት ያነሷቸው ነገሮች የክልሉ ልዩ ኃይል እና ዋና አዛዡ ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ በግልፅ ይጠቁማል። እነዚህ ምክንያቶች የኢህአዴግ መንግስት ከ1997ቱ ምርጫ ግን የፖለቲካ መሪዎችን፥ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾችን፥ የሃይማኖት መሪዎችን፥…ወዘተ በፀረ-ሽብር አዋጁ ሲከስ የሚጠቀምባቸው “ኦነግ፥ ኦብነግ፥ አልኢተሓድ፥ የኤርትራ መንግስት፥ ሌሎች የውጪ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር፣ …የፌደራል ስርዓቱን በኃል ለማተራመስና አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ለማስመለስ…ወዘተ ከሚለው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። 

በአጠቃላይ፣ ላለፉት አስር አመታት በፌደራል መንግስት ስም አዲስ አበባ ተቀምጦ “ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ” የሚል ሰበብ እየፈጠረ የፖለቲካ መሪዎችን፥ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾችን፥ የሃይማኖት መሪዎችን፥…ወዘተ በእስርና ስደት ከሀገር እንዲጠፉ ሲያደርግ የነበረው የፖለቲካ ቡድን ዛሬ ላይ የስልት ለውጥ አድርጏል። በዚህ መሰረት፣ አጥፊዎቹን ከማጥፋት ይልቅ አጥፊዎችን በመፍጠርና የኦሮሞ ሕዝብን በሽብርና ጦርነት በማሸማቀቅ የመብትና ነፃነት ጥያቄ እንዳያነሳ በማድረግ ላይ ይገኛል። 

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባርን (ONLF) ከሶማሌ ክልል እንዲያስወጣ በሚል በመከላከያ ሠራዊትና የፀረ-ሽብር ግብር ኃይል የተደራጀ መሆኑ ይታወቃል። በሶማሌ ክልል ሕዝብ ላይ ሲፈፅም ለነበረው ጥቃት የተከተለው የዉጊያ ስልት፥ ትጥቅና ዓላማን ከእነዚህ አካላት ማግኘቱ ግልፅ ነው። ዛሬ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ተመሳሳይ የውጊያ ስልት፥ በተመሣሣይ ትጥቅና ድጋፍ፣ ለተመሣሣይ ዓላማ ተግባራዊ እየተደረገ ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለኝም።    

 

ኢትዮጲያ: በግራ መጋባት ወደ እርስ-በእርስ ግጭት!     

አሁን ባለው የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ግራ-መጋባት ይታየኛል። ግራ መጋባቱ በዋናነት “ሀገሪቱ ወደየት እያመራች ነው?” በሚለው ጥያቄ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ ግራ መጋባት ታዲያ በአንዱ ወይም በሌላኛው ወገን ላይ ሳይሆን በሁሉም ወገኖች ላይ የሚስተዋል ነው። የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች እና ደጋፊዎች፣ በብሔርተኝነት እና በአንድነት ጎራ በተሰለፉት ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎችና ደጋፊዎች ላይ በግልፅ ይስተዋላል። በዚህ ፅሁፍ ከሦስቱም ጎራዎች አንዳንድ ምሳሌዎች በመጥቀስ ግራ መጋባቱን ለማሳየት እንሞክራለን። ከዚያ በቀጠል ደግሞ “ሀገራችን ወደየት እያመራች ነው?” የሚለውን ጥያቄ ከሌሎች ሀገራት ታሪክና ፖለቲካዊ ክስተት ጋር በማያያዝ ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን። 

የመጀመሪያው ግራ መጋባት የህወሓት/ኢህአዴግ መስራች እና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አባይ ፀሐዬ በኢትዮጲያ ፌደራሊዝም ስርዓትን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ነው። እንደ እሳቸው አገላለፅ፣ በዩጎዝላቪያ (Yugoslavia) የነበረው የፌደራሊዝም ስርዓት የወደቀው በአንድ ብሔር (the Serbs) የበላይነት ላይ የተመሰረተና ሌሎችን ብሔሮች ያገለለ በመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የሶቭዬት ፌዴሬሽን (Soviet federation) የተበታተነው ደግሞ በስርዓቱ ጨቋኝነት እና በዴሞክራሲ እጦት እንደሆነ ገልፀዋል። 

“አዎ…የህወሓት/ትግራይ የበላይነት አለ’ በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ በዝርዝር ለማብራራት እንደሞከርኩት አሁን ባለው ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ የህወሓት/ትግራይ የበላይነት በግልፅ የሚታይ ሃቅ ነው። በሌላ በኩል፣ የኢህአዴግ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ከሕዝብ ለሚነሱ የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት እያደረገ ነው። በዚህ ምክንያት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከቀን ወደ ቀን ይበልጥ ጨቋኝና አምባገነን እየሆነ መጥቷል። ነገር ግን፣ የመንግስታዊ ስርዓቱ መስራችና ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አባይ ፀሐዬ “ዩጎዝላቪያና ሶቬት ሕብረት የፈረሱት አሁን የኢህአዴግ መንግስት እየፈፀመ ያለውን ስህተት በመፈፀማቸው ነው” ማለታቸው በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ግራ መጋባት ያሳያል። 

ከላይ በተጠቀሰው የአቶ አባይ ፀሐዬ አስተያየት ግራ የተጋባው አንድ የኦሮሞ ብሔርተኛ ወዳጄ “ይሄ ነገር ‘ኣላዋቂነት’ ወይስ ‘ንቀት’ ነው?” በማለት ጠየቀኝ። በእርግጥ እንደ አባይ ፀሐዬ ያሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች “አላዋቂ ናቸው” እንዳይባል ሀገሪቱ የምትመራበትን ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት የቻሉ ናቸው። አይ…ነገረ ስራቸው ሁሉ “ንቀት ነው” እንዳይባል ደግሞ በንቀት ራሳቸውን ለውድቀት አይዳርጉም። ምክንያቱም፣ የዩጎዝላቪያና ሶቬት ህብረት የወደቁበትን መሰረታዊ ምክንያት እያወሱ ተመሳሳይ ስህተት ይፈፅማሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል። 

ሦስተኛውን ግራ መጋባት የታዘብኩት ደግሞ የአንድነት አቀንቃኝ በሆነው ወዳጄ ላይ ነው። ከዚህ ጓደኛዬ ጋር ከረጅም አመታት በኋላ ታክሲ ውስጥ ተገናኘንና እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፡- “የኢህአዴግ መንግስት አሁን ካለንበት የፖለቲካ ቀውስ ላይ ያደረሰን አውቆና አቅዶ ነው ወይስ ሳያውቅ በስህተት ነው?” በእርግጥ አውቆና አቅዶ ሀገሪቱን አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ ማድረስ በጣም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ዕዉቀት ይጠይቃል። ነገር ግን፣ ሀገርና ሕዝብን ለፖለቲካ ቀውስና ውድቀት የሚዳርግ አሻጥር ክፋት እንጂ ዕውቀት ሊባል አይችልም። በሌላ በኩል ደግሞ “ሳያውቁ በስህተት የፈፀሙት ነው” እንዳይባል ደግሞ ስህተታቸውን የነገሯቸውን የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣ …ወዘተ ለእስርና ስደት ዳርገዋቸዋል። 

በግራ መጋባት ወደ እርስ-በእርስ ዕልቂት!

በአጠቃላይ፣ የኢህአዴግ መሪዎች “አያውቁም” እንዳይባል ሀገርና ሕዝብ ይመራሉ፣ “ያውቃሉ” እንዳይባል ደግሞ ራሳቸውን ለውድቀት የሚዳርግ ስህተት ይሰራሉ። በዚህ ምክንያት፣ የእርስ-በእርስ ግጭትና የመበታተን አደጋ ሀገሪቱና ሕዝቡ ላይ ተጋርጧል። ይሄንን ግራ-መጋባት ለመፍታት የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ሃሳብ፣ ተግባራትና ስራዎችን እንደ ማሳያ እያነሱ መከራከር ይቻላል። ይህ ግን ከአንድ መቋጫ ላይ አንደርስም። ስለዚህ፣ ከሃሳብ ይልቅ አመለካከትን፣ ከተግባር ይልቅ መዋቅርን፣ ከሥራ ይልቅ አሰራርን፣… በአጠቃላይ ከፖለቲካዊ ስርዓቱ ይዘት (content) ይልቅ ቅርፁን (form) መመልከት ያስፈልጋል። 

የኢህአዴግ መንግስት መስራቾችና ከፍተኛ አመራሮች፣ እንዲሁም ቀንደኛ ደጋፊዎች ሁሉንም ነገር የሚመለከቱት በብሔር ምንፅር ነው። ድጋፍና ተቃውሞ በብሔር ነው። ሥራቸውን የሚሰሩት በብሔር ነው። ሁሉም ሰው የሚሰራው በብሔር ይመስላቸዋል። ለምሳሌ፣ በኢትዮጲያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፕረዜዳንቶች በሙሉ የአከባቢው ብሔር ተወላጆች ናቸው። ለዚህ ምክንያቱ “የአከባቢው ተወላጅ የሆነ ሰው ለአካባቢው ማህብረሰብ ተገቢ የሆነ የማህብረሰብ አገልግሎት ይሰጣል” የሚል ነው። ስለዚህ የአንድ ዩኒቨርሲቲ ፕረዜዳንት በትምህርት የቀሰመው በዓለም-አቀፋዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ ዕውቀትና ክህሎት ከተወለደበት ማህብረሰብ ውጪ ፋይዳ-ቢስ ነው። አሁን በሀገራችን ያለው መንግስታዊ ስርዓት ዕውቀትና ክህሎትን ሳይቀር የሚመለከተው ከብሔር አንፃር ነው። 

የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ደጋፊዎች ሃሳብና አመለካከታቸው ሙሉ በሙሉ በብሔር ላይ የተመሰረተ ነው። እ.አ.አ. ከ1945 – 1980 ዓ.ም ዩጎዝላቪያን የመሩት “Tito” (Josip Broz) ለረጅም አመታት የሀገሪቱን የመሩት በሀገራዊ አንድነትና የወደፊት አብሮነት መርህ ነበር። የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ አብዛኞቹ የህወሓት/ኢህአዴግ አመራሮች ሀገሪቷን እየመሩ ያሉት በብሔርተኝነትና የታሪክ ቁርሾን በመቆስቆስ ነው። ለምሳሌ፣ “Tito” በዩጎዝላቪያ ”Serbs” እና “Croats” ሕዝቦች መካከል በቀድሞ ዘመን በተካሄደው የእርስ-በእርስ ጦርነት አማካኝነት የተፈጠረውን ቂምና ጥላቻ በማስወገድ የእርቅ መንፈስ ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። 

በተቃራኒው፣ የኢህአዴግ መንግስት ላለፈው ሩብ ክ/ዘመን በተለይ በአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ያለውን የታሪክ ልዩነትና ቁርሾ በመቆስቆስ ቂምና ጥላቻ ለማስፋፋት ጥረት አድርጓል። ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የምሁራን ዕውቀትና አገልግሎት በብሔርና ቋንቋ የሚከፋፍል የፖለቲካ ቡድን ለስርዓቱ ስጋት የሆነ የብሔሮች ጥምረት ሲፈጠር የእርስ-በእርስ ግጭት እንደሚፈጥር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እንዲህ ያለ መንግስት አምሳያው ያለው ምስራቅ አውሮፓ ሳይሆን ደቡብ አፍሪካ ነው። 

የሰቆቃ ልጆች እና የብሔር አፓርታይድ በሚሉ ተከታታይ ፅሁፎች በዝርዝር ለመግለፅ እንደሞከርኩት አሁን በሀገራችን ያለው መንግስታዊ ስርዓት እ.አ.አ. ከ1948 – 1994 ዓ.ም ድረስ በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ጋር ከአመሰራረቱ እስከ ውድቀቱ ድረስ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ብዙዎች በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በዘር ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ያስባሉ። ነገር ግን፣ ለአፓርታይድ ስርዓት መመስረት ዋና ምክንያቱ ዘረኝነት አይደለም። የአፓርታይድ መነሻ ምክንያቱ እ.አ.አ. ከ1899 – 1902 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በእንግሊዞች መካከል የተካሄደው ¨The Second Boers War” ነው። ይህ ጦርነት በነጮች መካከል የተካሄደ ጦርነት እንጂ በጥቁሮችና ነጮች መካከል የተካሄደ አልነበረም። 

የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ በዘር ሀረግና በቆዳ ቀለም ነጮች፥ ጥቁሮች፥ ሕንዶችና ቅይጦች (colored) በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። ሆኖም ግን፣ የፀረ-አፓርታይድ ትግሉ ሲካሄድ የነበረው በዋናነት በጥቁሮችና በነጮች መካከል ነው። የአፓርታይድ ስርዓት መሰረታዊ ዓላማ ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነጮችን የፖለቲካ የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ 70% የሚሆኑትን ጥቁሮች በጎሳና ብሔር መከፋፈል አለበት። 

በዚህ መሰረት፣ የአፓርታይድ ስርዓት የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብን በጎሳና ብሔር ለአስር ክልሎች ከፋፍሏቸዋል። እያንዳንዱ ክልል ራሱን በራሱ የማስተዳደር ስልጣን አለው። ነገር ግን፣ የአንዱ ክልል ነዋሪ በሌላኛው ክልል ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ በሕግ የተከለከለ ነበር። ይህ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አጀንዳና የተቀናጀ እንቅስቃሴ እንዳይኖራቸው የታለመ ነው። 

የአፓርታይድ ስርዓት የአነስተኛ ብሔርን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ሕዝቦች በጎሳና ብሔር በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው። አሁን በኢትዮጲያ ያለው ፖለቲካዊ ስርዓት በደቡብ አፍሪካ ከነበረው ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። የህወሓት/ትግራይ የበላይነትን ለማስቀጠል በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች በመለያየት ላይ የተመሰረተ ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ፣ እ.አ.አ. ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ወደጎን በመተው የመብትና ነፃነት ጥያቄያቸውን በጋራ መጠየቅ ሲጀምሩ የአፓርታይድ መንግስት የወሰደው እርምጃ አሁን በሀገራችን ለሚስተዋለው የፖለቲካ ቀውስና አለመረጋጋት መንስዔን፣ እንዲሁም በሁለቱ ስርዓቶች መካከል ያለውን ተመሳሳይነት በግልፅ ይጠቁማል። 

እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ አመፅና ተቃውሞ ተቀሰቀሰ። ልክ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገራችን አከባቢዎች እንደታየው እ.አ.አ. በ1984 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ አመፅና ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። በሁለቱም አጋጣሚዎች የመንግስት እርምጃ አንድና ተመሳሳይ ነበር። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ያለማቋረጥ ጥረት ተደርጓል። በዚህ ምክንያት፣ የሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሁከትና ብጥብጥ እያመራ ሄደ። 

ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መሪ የነበሩት “Pieter Willem Botha” ልክ እንደ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ለሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ በተደጋጋሚ ቃል ገቡ። የጠ/ሚ ኃይለማሪያም ንግግር ለሁላችንም የቅርብ ግዜ ትዝታ ስለሆነ እዚህ መድገም አያስፈልግም። የአፓርታይዱ መሪ ንግግርና የተሃድሶ እንቅስቃሴ ግን “Stephen Ellis” የተባለው የዘርፉ ምሁር ባቀረበው በጥናታዊ ፅሁፍ እንዲህ ገልፆታል፡- 

“…in a series of speeches, Botha seemed to try to direct the country into reformist paths and away from the racial “Apartheid”…. What is certain is that his idea of ‘healthy power sharing’ meant he would cling to ‘group rights’ as a means of maintaining White control, which he claimed was still in the best interests of South Africa….A changing and increasingly volatile South African society led to the civil insurrection of 1984 and its repercussions around the country. Botha’s response was the repression of activists and liberation movements under a state of emergency. The reform policy stagnated.…” The Historical Significance of South Africa’s Third Force, Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299. 

ይሁን እንጂ የሁለቱም ሀገራት መንግስታት ስር ነቀል ተሃድሶ ማምጣት ተሳናቸው። ከዚያ ይልቅ፣ የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ማድረግ ቀጠሉ። ሆኖም ግን፣ የሁለቱም መንግስታት እርምጃ የሕዝቡን ቁጣና ተቃውሞን ይበልጥ እንዲባባስ አደረገው። በዚህ ምክንያት፣ እ.አ.አ. በ1986 በደቡብ አፍሪካ፣ ባለፈው የ2009 ዓ.ም ደግሞ በኢትዮጲያ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታወጀ። 

በሌላ በኩል የአፓርታይድ ስርዓት የመከላከያና ድህንነት ኃላፊዎች በሕቡዕ ሦስተኛው ኃይል (The third Force) የተባለ ፀረ-አብዮታዊ ቡድን አቋቋሙ። ይህ ከክልል ሚሊሺያዎችና ልዩ ፖሊስ ኃይል የተወጣጣው ቡድን እንደ ዝምባብዌና ሞዛምቢክ ባሉ ጎረቤት ሀገራት የነበረውን የአማፂያን እንቅስቃሴ እንዲያውኩ የተቋቋሙ ነበሩ። የአሰቸኳይ ግዜው ከታወጀ በኋላ ግን በደቡብ አፍሪካ ጦር ወታደራዊ ስልጠና እና ትጥቅ ተሰጥቷቸው የፀረ-አፓርታይድ ትግሉን በማጨናገፍ ተግባር እንዲሰማሩ ተደረገ። የአፓርታይድ ስርዓት በተለይ በደቡብ አፍሪካ “KwaZulu Natal” በሚባለው ክልል የታየውና ዛሬ በሶማሊ ክልል እየታየ ያለው ፍፁም ተመሳሳይ ነው።  

“In April 1986, the State Security Council had endorsed guidelines for a strategy for counter-revolutionary war which, among other things, emphasised that the forces of revolution should not be combatted by the security forces alone, but also by ‘anti-revolutionary groups such as Inkatha … as well as the ethnic factor in South African society’. In the following months, specifically ethnic organisations were armed and trained in KwaZulu and Ciskei, while anti-ANC groups in other places were encouraged and armed in the form of kitskonstabels or special policemen and vigilantes….  In effect, military units, which had carried out the destabilisation of neighbouring countries, were now implementing similar strategies at home, on the instructions of the State President, the State Security Council and the head of the [South Africa Defense Force]”  

Journal of Southern African Studies, Vol. 24, No.2. (Jun., 1998), pp. 261-299


በአጠቃላይ፣ በተለያዩ የደቡብ አፍሪካ ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭት ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ዛሬ በአንዳንድ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊና ደቡብ ክልሎች እየታየ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ፣ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮች መካከል የአርስ-በእርስ ግጭት በመፍጠር የነጮች የበላይነትን ለማስቀጠል ካደረገው ጥረትና ካስከተለው ውጤት በመነሳት ሀገራችን ኢትዮጲያ ወደየት እየሄደች እንደሆነ መገመት ይቻላል። 

በደቡብ አፍሪካ በተለይ እ.አ.አ. ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የጥቁር ጎሳዎችና ብሔሮች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍጠር በሕቡዕ የተሰራው ስራ እ.አ.አ. ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ፍሬ አፈራ። በእርግጥ ከመርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬ አይጠበቅም። በእነዚህ አራት አመታት ውስጥ ብቻ በተነሳ ሁከትና ብጥብጥ 14,000 ደቡብ አፍሪካዊያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።  እ.አ.አ. ከ1948 ዓ.ም የአፓርታይድ ስርዓትን ለመጣል በተደረገው ትግል ከተገደሉት ሰዎች ከ1990 – 1994 ዓ.ም ባሉት አራት አመታት ውስጥ ብቻ የተገደሉት ይበልጣል። ሀገራችን ወደየት እያመራች እንደሆነ ለማወቅ ለሚሻ ከዚህ በላይ ጠቋሚ ማስረጃ አይገኝም። አዎ…ኢትዮጲያ ወደ እርስ-በእርስ ግጭትና ዕልቂት እያመራች ነው!    

ብሔርተኝነት እና አንድነት

ብሔርተኝነት ራስ-ወዳድነት ነው!!!

አንዳንድ ሰዎች በብሔርተኝነትና ዘረኝነት ወይም በብሔር እና በዘር ልዩነት ላይ በተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ አድርገው ሲያቀርቡ ሳይ በጣም ይገርመኛል። ነገር ግን፣ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት ተለያይተው አያውቁም። “ዘረኛ” የሚለው ቃል “በዘር ምክንያት ለአንዱ የሚያደላ፣ ሌላውን የሚጎዳ፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን፥ አመለካከትን የሚያራምድ” ማለት ነው። “ብሔርተኛ” ደግሞ “ለብሔሩ (ጎሳው) ብቻ የሚስብና የሚያደላ፣ በሌላ ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ነው። “ዘረኝነት” የዘረኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ሲሆን “ብሔርተኛ” ደግሞ የብሔርተኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ነው። በዚህ መሰረት፣ ዘረኛ ሆነ ብሔርተኛ ሁለቱም በአድልዎ ላይ የተመሰረቱ አመለካከቶች ናቸው። በሁለቱም ውስጥ ለራስ ዘር/ብሔር ማድላት፥ መደገፍና ክፍ ክፍ ማድረግ አለ። በተመሳሳይ፣ በሁለቱም ውስጥ የሌላን ዘር/ብሔር ማግለል፥ መለየትና መጥላት አለ። በዘረኝነትና ጠባብነት ውስጥ ራስን መውደድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጥላት፣ ለራስ ማዳላትና መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማግለልና መጉዳት አለ። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ማለት ራስ-ወዳድነት ነው!!! በራስ-ወዳድነት ወይም ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መጨረሻው አድሏዊና ጨቋኝ የሆነ ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው።

አንድነት እኩልነት ነው!!!

ብዙውን ግዜ “አንድነት” የሚለው ቃል የተዛባ ትርጉምና ፍቺ ሲሰጠው ማየት የተለመደ ነው። በአብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ በስፋት የሚንፀባረቀው የአህዳዊ አንድነት ፅንሰ-ሃሳብ ነው። በዚህ መሰረት “አንድነት” ሲባል የአንድ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥…ወዘተ ተመሳሳይነት ተደርጎ ይገለፃል። ይህ ደግሞ በብሔርተኛ ቡዱኖች ዘንድ የአንድ ብሔር፥ ቋንቋና ባህል የበላይነት እንደሆነ ይገልፃሉ። ነገር ግን፣ የሁለቱም ወገኖች አመለካከት የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም፣ የአንድነት ፅንሰ-ሃሳብ በብሔር፥ ቋንቋ ወይም ባህል ተመሳሳይነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ፖለቲካዊ አንድነት በሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሁለም ሰው እኩል መብትና ነፃነት አለው። በመሆኑም፣ “ለእኔ የሚገባኝ መብትና ነፃነት ለሁሉም ሰው ይገባል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ “አንድነት” ሲባል “ሁላችንም እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባል” ማለት ነው። በአጠቃላይ፣ አንድነት ማለት እኩልነት ነው!!! በአንድነት ወይም እኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የብዙሃን መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል። 

ዘረኝነትን ሲያቆላምጧት “ብሔርተኝነት” አሏት!

አንዳንድ ሰዎች በአክራሪ ብሔርተኝነትና በዘረኝነት መካከል፣ እንዲሁም በብሔር ልዩነት እና በዘር ልዩነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት የተለያዩ ናቸው ሲሉ ይገርሙኛል። ነገር ግን፣ የብሔርተኝነትና ዘረኝነት ፅንሰ-ሃሳብ ፍፁም ተመሳሳይ ናቸው። የዓለም ታሪክን ስንመለከትም ብሔርተኝነትና ዘረኝነት በጭራሽ ተለያይተው አያውቁም። በዚህ ፅሁፍ የሁለቱን የብሔርተኝትና ዘርኝነት ፅንሰ-ሃሳብን ከታሪክ ጋር አቀናጅተን በዝርዝር እንመለከታለን።  

በቅድሚያ “ዘረኛ” የሚለው ቃል “በዘር ምክንያት ለአንዱ የሚያደላ፣ ሌላውን የሚጎዳ፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን፥ አመለካከትን የሚያራምድ” የሚል ፍቺ አለው። “ብሔርተኛ” ደግሞ “ለብሔሩ (ጎሳው) ብቻ የሚስብና የሚያደላ፣ በሌላ ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። “ዘረኝነት” የዘረኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ሲሆን፣ “ብሔርተኛ” ደግሞ የብሔርተኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ነው። “ብሔር” የሚለው ቃል “አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት ያለው፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፥…የተሳሰረና በተወሰነ ክልል ውስጥ የሚኖር ሕዝብ” የሚል ፍቺ አለው። “ብሔረሰብ” የሚለው ቃል ደግሞ “ከደም አንድነት ይልቅ በክልል፥ በቋንቋና በባህል አንድነት ላይ የተመሰረተ፣ የተለያዩ ነገዶች የተዋሃዱበት ማህብረሰብ” ማለት ነው።

በመሰረቱ፣ ዘረኝነት እና ብሔርተኝነት በአድልዎ ላይ የተመሰረቱ አመለካከቶች ናቸው። ሁለቱም ውስጥ ለራስ ዘር/ብሔር ማድላት፥ መደገፍና ክፍ ክፍ ማድረግ፣ የሌላን ዘር/ብሔር ደግሞ ማግለል፥ መለየትና መጥላት አለ። በዘረኝነትና ብሔርተኝነት ውስጥ ራስን መውደድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጥላት፣ ለራስ ማዳላትና መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማግለልና መጉዳት አለ። ስለዚህ ሁለቱም በተመሳሳይ የተሳሳተ አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካዊ ስርዓቶችን ታሪካዊ አመጣጥ ስንመለከት ደግሞ ዘረኝነትና ብሔርተኝነት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን እንገነዘባለን። ምክንያቱም፣ በዘረኝነት ላይ የተመሰረቱ ፖለቲካዊ ስርዓቶች በሙሉ መነሻቸው አሳፋሪ ሽንፈት፣ አክራሪ ብሔርተኝነት እና የጎሳ ፖለቲካ ናቸው። “የጎሳ ፖለቲካ” ማለት ደግሞ “በዘር፥ በጎሳ፥ በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው።

በዘረኝነት ታሪካዊ አመጣጥ ዙሪያ ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው “George M Fredrickson”፣ እስከ መካከለኛው ዘመን ድረስ በአውሮፓ “ዘረኝነት” (Racism) የሚባል ነገር ታይቶ እንደማይታወቅ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ የዘረኝነት ምልክት ለመጀመሪያ ግዜ የታየው በ13ኛውና 14ኛው ክ/ዘመን በስፔን ሲሆን እሱም አይሁዶችን ከሰይጣንና ባዕድ አምልኮ ጋር በማያያዝ ነበር የተከሰተው። ነገር ግን፣ በ16ኛው ክ/ዘመን የስፔን መንግስት ይህን የተሳሳተ አመለካከት በይፋ በማገዱ ተወግዷል። ከዚያ በኋላ፣ ዘረኝነት ማቆጥቆጥ የጀመረው በ17ኛው ክ/ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በአሜሪካ ነው። ለዚህ ደግሞ እ.አ.አ. በ1667 በደቡባዊ አሜሪካ ቨርጅኒያ ግዛት የጥቁር አሜሪካዊያንን ጉልበት ለመበዝበዝ የወጣው ሕግ ተጠቃሽ ነው። ይሁን እንጂ፣ ዘረኝነት ተንሰራፍቶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው በ19ኛው ክ/ዘመን ማብቂያ ላይ ነው።

“George M Fredrickson” የ19ኛው ክ/ዘመን በአሜሪካና አውሮፓ የነፃ-መውጣት፣ የብሔርተኝነት እና የኢምፔሪያሊዝም (Emancipation, Nationalism and Imperialism) ዘመን እንደነበር ይገልፃል። በተለይ ከ1870 – 1880 ያሉት ዓመታት በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ለዘረኝነት መነሻ የሆነው የዘውግ ብሔርተኝነት (Ethnic Nationalism) በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት ነበር። በዚህ ወቅት በጀርመን በርሊን የተፈረመው “The scramble of Africa” የተሰኘው አፍሪካን የመቀራመት ስምምነት የምዕራብ ሀገራት የአክራሪ ብሔርተኝነት ውድድርን አጥናክረው የቀጠሉበት እንደነበር፤ “…an assertion of the competitive ethnic nationalism that was existed among European nations” በማለት ግልፆታል።

በመጨረሻም፣ “Fredrickson” ዘረኝነት ጫፍ ደርሶ ጨቋኝ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመሆን የበቃው በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይጠቅሳል። በዚህ ወቅት ከተፈጠሩት “በግልፅ ዘረኛ የሆኑ መንግስታት” (Overtly Racist Regimes) የሚባሉት በአሜሪካ፣ በጀርመንና በደቡብ አፍሪካ የነበሩት ናቸው። እነዚህ ዘረኛ መንግስታዊ ስርዓቶች በዘር ላይ የተመሰረቱ ጨቋኝ ሕጎችና መመሪያዎች ከማውጣታቸው በፊት በግልፅ ብሔርተኛ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ይህን “Fredrickson” እንዲህ ሲል ገልፆታል፦

“racist principles were not fully codified into laws effectively enforced by the state or made a central concern of public policy until the emergence of what I will call ‘overtly racist regimes’ in the last century.”

ከላይ የተጠቀሱት በዘረኝነት የተመሰከረላቸው ፖለቲካዊ ስርዓቶች ፍጹም ተመሳሳይ የሆነ መሰረት አላቸው። እነሱም፣ አንደኛ፡- አሳፋሪ ሽንፈት (Humiliating defeat)፣ ለሽንፈቱ ሌሎች ብሔሮችን፥ ብሔረሰቦችን ተጠያቂ ማድረግ (Scapegoating) እና የአንድን ብሔር የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሌሎችን ብሔሮች መብትና ነፃነት የሚገድቡ ሕጎችን ማውጣትና ተግባራዊ ያደረጉ ናቸው።

እንደ “Fredrickson” አገላለፅ፣ በአሜሪካ የዘረኝነት ስርዓት መዘርጋት የተጀመረው በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶች ሲሆኑ ዋና መነሻ ምክንያቱ በበደቡባዊ አሜሪካ የሚገኙ ነጮች በአሜሪካ የእርስ-በእርስ ጦርነት ወቅት አሳፋሪ ሽንፈት ስለገጠማቸው እንደሆነ ይጠቅሳል። እነዚህ ነጭ አሜሪካዊያን በጦርነቱ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት በጥቁሮች ላይ አሳብበዋል (Scapegoat)። በመጨረሻም፣ በ20ኛው ክ/ዘመን በአሜሪካ የከተሞች መስፋፋት በእርሻ ማሳዎች ላይ የሚውሉ ጥቁሮችን ለመቆጣጠር አመቺ ባለመሆኑና የጥቁሮችን ጉልበት ብዝበዛ ለማስቀጠል በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ሕግና ደንብ በማውጣት ተግባራዊ አደረጉ። በተመሳሳይ፣ ጀርመኖች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ለጋጠማቸው አሳፋሪ ሽንፈት አይሁዳዊያንን ተጠያቂ አድርገዋል። ከዚያ በመቀጠል፣ አይሁዶችን በዘር በመለየትና በመነጠል የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በመጨረሻም፣ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች በእንግሊዝ ጦር ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ተጠያቂ አድርገዋል። የእንግሊዝ ጦር ከደቡብ አፍሪካ ሲወጣ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት በመዘርጋት በጥቁሮች ላይ ግፍና በደል ፈፅመዋል።

በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት የሚዘረጋው፣ አንድ ብሔር ወይም ሀገር በታሪክ ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈትና ፀፀት ራሱን ለማውጣት ሲል በሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ብሔር፥ ሕዝብ ከዚህ ቀደም ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈትና ቀውስ ራሱን ለማውጣትና በሌሎች ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች ላይ የበላይነቱንና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ጨቋኝ የሆነ ፖለቲካዊ ስርዓት ይዘረጋል። ዘረኝነት እንዲኖር የተለየ ቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት ያለው ማህብረሰብ መኖር አለበት።

ብሔርና ብሔርተኝነት በሌለበት ዘረኝነት ሊኖር አይችልም። የዘር ልዩነት ቢኖርም እንኳን በቋንቋ፣ ባህልና ስነልቦናዊ አመለካከት ተመሳሳይ በሆኑ ሕዝቦች መካከል ዘረኝነት ሊኖር አይችልም። ስለዚህ፣ ዘረኝነት እንዲኖር በቅድሚያ የቋንቋ፣ የባህልና የስነልቦናዊ አመለካከት ልዩነት መኖር አለበት። በመሆኑም፣ ዘረኝነት እንዲኖር በቅድሚያ ብሔርና አክራሪ ብሔርተኝነት መኖር አለበት። በዚህ መሰረት፣ ብሔርተኝነት እና ዘረኝነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። 

በመጨረሻም፣ አሁን በሀገራችን የተዘረጋው በብሔር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስርዓት በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንና አለመሆኑን ለማወቅ ከጥንት ጀምሮ በአማራና ትግራይ መካከል የነበረው የዘውግ በሔርተኝነት፣ የአፄ ሚኒሊክ ወደ ስልጣን መምጣት (የትግራይና ሸዋ ዘውዳዊ አገዛዝ)፣ እንዲሁም የሕውሃት የትግል ማኒፌስቶ እና ስለ አማራ ሕዝብ የነበረው አቋምና አመለካከትን በማየት በራሳችሁ መፍረድ ትችላላችሁ። ለዚህ ያግዛችሁ ዘንድ “Fredrickson” የዘረኛ ስርዓት ዋና መለያ ባህሪ ያለውን የመጀመሪያ መስፈርት በመጥቀስ ፅሁፌን እቋጫለሁ፡- 

“First there is an official ideology that is explicitly racist. Those in authority proclaim insistently that the difference between the dominant group and the one that is being subordinated or eliminated are permanent or unbridgeable. Dissent from this ideology is dangerous and is likely to bring legal or extralegal reprisals, for racist egalitarianism is heresy in an overtly racist regime.” 

  

የዛሬ “አሸባሪነት” ለቀጣይ ትውልድ የሃፍረት ስንቅ ይሆናል!

“ዝሆኖች ሲጣሉ ሆነ ፍቅር ሲሰሩ የሚጎዳው ሳሩ ነው” የሚል የስዋህሊኛ አባብል አለ። አባባሉ እንደ አሜሪካ ያሉ ኃያላን ሀገራት የውጪ ግንኙነት ፖሊሲን በደንብ ይገልፀዋል። ኃያሏ አሜሪካ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ከሶቬት ሕብረት ጋር ስትጣላ ሆነ በአለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት ከኢትዮጲያ ጋር ፍቅር ስትሰራ በሁለቱም አጋጣሚ ተጎጂዎቹ ጭቁን ሕዝቦች ናቸው።

በእርግጥ አሜሪካ የዴሞክራሲና ብልፅግና ተምሳሌት ናት። የሀገሪቷ መሪዎችም በአለም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው። ባለፈው ግማሽ ክ/ዘመን እንኳን ሀገሪቷ ካፈራቻቸው መሪዎች ውስጥ ፕረዜዳንት ጆሴፍ ኬኔዲ እና ባራክ ኦባማ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ሁለት መሪዎች ከስራዎቻቸው ሁሉ የጥቁሮችን እኩልነት (Equality) ከማረጋገጥ አንፃር ያበረከቱት አስተዋፅዖ ጎልቶ የሚጠቀስ ነው። “የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው” እንዲሉ ፕ/ት ኬኔዲና ኦባማን ያፈራች ሀገር ፕ/ት ሮናልድ ሬገን እና ጆርጅ ቡሽ (ትንሹ) አፍርታለች። እነዚህ ሁለት መሪዎች ደግሞ ከስራዎቻቸው ሁሉ የሽብርተኝነት (Terrorism) ፖሊሲያቸው ተጠቃሽ ነው። ፕ/ት ኬኔዲና ኦባማ የጥቁሮችን እኩልነት ከማረጋገጥ አንፃር በፈፀሟቸው ተግባራት እና ባላቸው የግል ስብዕና አማካኝነት የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ገንብተዋል። በተቃራኒው፣ ፕ/ት ሬገንና ቡሽ ደግሞ ሽብርተኝነትን ለመታገል በሚል የፈጸሟቸው ተግባራት የሀገሪቱን መልካም ገፅታ ጥላሸት ቀብተውታል።

በእርግጥ የፕ/ት ሬገንና የፕ/ት ቡሽ አስተዳደር በሽብርተኝነት ስም የፈፀሟቸው ተግባራት አሜሪካ ከዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንፃር የነበራትን የሞራል የበላይነት አሳጥቷታል። ይሁን እንጂ፣ የአሜሪካኖች በፕ/ት ኬኔዲና ኦባማ መልካም አስተዋፅዖ ተጠቃሚ የሆኑትን ያህል በፕ/ት ሬገን እና ቡሽ የፀረ-ሽብርተኝነት ፖሊሲ ተጎጂ አልሆኑም። በጨቋኝ ስርዓት ስር ለሚኖሩ ዜጎች ግን ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ነው።

በመሰረቱ የጨቋኝ ስርዓት መሪዎች ልክ እንደ ዋልጌ (ባለጌ) ልጅ ከሌላ መንግስት መጥፎ-መጥፎውን እንጂ ጥሩ ልምዱን አይቀስሙም። እንደ አሜሪካ ካሉ የበለፀጉ ሀገራት ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ከመቅሰም ይልቅ የጨቆና ስልቶችንና ዓይነቶችን መቅሰም ይቀናቸዋል። ለምሳሌ፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ ከፕ/ት ኬኔዲ የጥቁሮችን እኩልነት ከመቅሰም ይልቅ የፕ/ት ሬገንን የሽብርተኝነት ፖሊሲን ተቀብሎ ተግባራዊ አድርጓል። በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት ፕ/ት ባራክ ኦባማ ስለ ነፃነትና እኩልነት ከተናገረው ይልቅ የፐ/ት ጆርጅ ቡሽ የፀረ-ሽብርተኝነት ትግልን በታላቅ “ሞራል” ተቀብሎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሁሉም ጨቋኝ መንግስታት የፀረ-ሽብርተኝነት ስልትን እንጂ የእኩልነት መርህን ተቀብለው ተግባራዊ አያደርጉም። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- ጨቋኝ ስርዓት በባህሪው ፀረ-እኩልነት ስለሆነ፣ ሁለተኛ፡- ፀረ-ሽብርተኝነት የእኩልነት ጥያቄን ማፈኛ መሳሪያ ስለሆነ።

የፕ/ት ሬገን አስተዳደር በአንድ በኩል በደቡብ አፍርካ የነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ በጥቁሮች ላይ የሚፈፀመውን በደልና ጭቆና አጥብቆ ይቃወማል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በፀረ-ኮሚኒዝም ትግሉ አፓርታይድን ይደግፋል። በተመሣሣይ፣ የፕ/ት ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር በአንድ በኩል የኢህአዴግ መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈፅመውን በደልና ጭቆና አጥብቆ ይቃወማል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በፀረ-ሽብርተኝነት ትግሉ ኢህአዴግን ይደግፋል። ሆኖም ግን፣ ሁለቱም የአሜሪካ መሪዎች በፀረ-ሽብርተኝነት ስም የሀገራቸውን ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በደቡብ አፍሪካ ሆነ በኢትዮጲያ ያለውን የእኩልነት ጥያቄ ለመገንዘብ ፍላጎትና ተነሳሽነት የላቸውም።

የአሜሪካ መንግስት ጨቋኝ ስርዓትን በአንድ በኩል እየደገፈ በሌላ በኩል የሚቃወመው የአሜሪካን ጥቅም ለማስከበር ብቻ ነው። ፕ/ት ሬገን ከኮሚኒዝም፣ ፕ/ት ቡሽ ደግሞ ከአልቃይዳ ውጪ ያለው ነገር አያሳስባቸውም። ለምሳሌ፣ የቀድሞ የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር “Brian Mulroney” የቀድሞ የአሜሪካና የእንግሊዝ መሪዎች ስለ ፀረ-አፓርታይድ ትግሉ የነበራቸውን አቋምና ግንዛቤ እንዲህ ገልፀውታል፡-

“Over the years, he (Reagan) and Margaret continually raised with me their fears that Nelson Mandela and other anti-apartheid leaders were communists. My answer was always the same. ‘How can you or anyone else know that?’ I’d ask again and again. ‘He’s been in prison for 20 years and nobody knows that, for the simple reason no one has talked to him — including you.’” Brain Biography

የአሜሪካ ከፊል ተቃውሞ ለጨቋኝ ስርዓት እንደ ሙሉ ድጋፍ ነው። በእርግጥ በአሜሪካ “እኩልነት” የዜጎች መብት ሲሆን ለመንግስት ደግሞ ግዴታ ነው። በአሜሪካ ላይ የሚቃጣው የሽብር ጥቃትም ቢሆን በዋናነት በውጪ ሀገር ዜጎች እንደመሆኑ ውጫዊ ስጋት ነው። ለምሳሌ፣ አንድ የአሜሪካ ዜጋ በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ቢያዝ የሚዳኘው በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንጂ በፀረ-ሽብር አዋጅ አይደልም። በጨቋኝ ስርዓት ውስጥ ሲሆን ግን የእኩልነትና ሽብርተኝነት ሚና የተገላቢጦሽ ይሆናል። እኩልነት በአሜሪካ መብት ሲሆን በጨቋኞች ዘንድ ደግሞ ጥፋት (ወንጀል) ነው። የዜጎችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረግ የአመፅና ተቃውሞ ንቅናቄን የመሩ ሰዎች ስማቸው በአረዓያነት ይጠቀሳል። በአፓርታይዷ ደቡብ አፍርካ እና በኢህአዴጓ ኢትዮጲያ ግን በሽብርተኝነት ወንጀል ያስከስሳል።

በአፓርታይድ ዘመን የጥቁሮችን እኩልነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ትግል ሲመሩ የነበሩ ሰዎች በአብዛኛው በአሸባሪነት ተፈርጀው ነበር። በተመሣሣይ፣ በኢትዮጲያ የዜጎች መብትና ነፃነት እንዲከበር ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በእስርና ስደት ላይ ይገኛሉ።

በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረውን የፀረ-አፓርታይድ ትግል ሲመሩ ከነበሩት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የቀድሞ የሀገሪቱ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ናቸው። የጥቁሮች የነፃነት ቀንዲል የሆነው ማንዴላ በአፓርታይድ አገዛዝ በአሸባሪነት ተፈርጀው ነበር። የፕ/ት ሬገን አስተዳደር ይህን ውሳኔ በመደገፍ ማንዴላንና ከሌሎች የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪዎች ጋር በአሸባሪነት ፈርጇቸው ነበር።

በዚህ ምክንያት፣ ኔልሰን ማንዴላ እ.አ.አ. በ2008 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ለጉበኝት ሲሄዱ በቀድሞ አስተዳደር በአሸባሪነት ተፈርጀው ስለነበር የፕ/ት ቡሽ አስተዳደር ልዩ የይለፍ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። ታዲያ በወቅቱ የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ኮንዶሊዛ ራይስ ለማንዴላ የይለፍ ፍቃዱን ከሰጠች በኋላ ሁኔታውን “አሳፋሪ” (embarrassing) በማለት ነበር የገለፀችው። የፕ/ት ሬገን አስተዳደር የፈፀመው ስህተት ለፕ/ት ቡሽ አስተዳደር ባለስልጣናት ሃፍረትን አከናንቧቸዋል። በተመሳሳይ፣ ዛሬ በሀገራችን የፖለቲካ መሪዎች፣ የመብት አቀንቃኞች እና ጋዜጠኞች ላይ “በሽብርተኝነት” ስም እየተፈፀም ያለው ግፍና በደል ለቀጣዩ ትውልድ የሃፍረት ስንቅ ይሆናል   !
image

ስለ ትላንትና ዛሬ መነጋገር ከተሳነን ለነገ ቂም-በቀል አሳደርን፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በጀርመንና ኦስትሪያ የቀኝ-አክራሪ ብሔርተኞች ከእነሱ በስተቀር ሌላ ማንም ትክክል ሊሆን አይችልም በሚል ፅንፍ ረገጡ። ራሳቸውን ከሰው ዘር ሁሉ “ምርጥ” መሆናቸውን ለራሳቸው መሰከሩ። በመጀመሪያ ከሁሉም የተሻሉ ምርጦች መሆናቸውን ደጋግመው ለፈፉ። ቀጠሉና እነሱ ከሌሎች ሁሉ የተሻሉ ምርጦች ስለሆኑ ሌሎች ደግሞ ከእነሱ እኩል ምርጦች ሊሆኑ እንደማይችሉ ማሰብ ጀመሩ። እንዲህ እያለ ሄዶ በመጨረሻ ከምርጦች መሃል ተመራጮችን ለይተው አወጡ። በመጨረሻ ሰብዓዊ ክብራቸውን ከፍፈው በዓለም ታሪክ አሰቃቂ የሆነውን የዘር-ማጥፋት ፈፀሙ።

አክራሪ ብሔርተኞች ከመጨረሻው የሞራል ዝቅጠት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያደረጉት ነገር ቢኖር ከእነሱ እስተሳሰብ ጋር አብሮ የማይሄድ፣ ፅንፍ አክራሪነትን የሚቃወም ፅንሰ-ሃሳብ ያላቸው መጽሃፍትን ሰብስቦ ማቃጠል ነው። በወቅቱ ሁኔታውን የታዘበው የስነ-ልቦና ልሂቁ ሲግመንድ ፍሮይድ፤ “በጣም ተሻሽለናል…ኧረ በጣም ተሻሽለናል! ድሮ ድሮ ፀኃፊዎችን ነበር የምናቃጥለው! ዛሬ ግን መፅሃፍቶቻቸውን እያቃጠልን ነው” ብሎ ነበር። በእርግጥ ይሄ መሻሻል ከሆነ እኛም በጣም ተሻሽለናል። ደርግ ፊደል የቆጠረን ሁሉ መንገድ ላይ በጥይት ዘርሮ ይፎክር ነበር። ኢህአዴግ ደግሞ ፊደል የፃፈን እስር ቤት አስገብቶ ሰብዓዊ ክብሩን ይገፈዋል። ከዚህ አንፃር በጣም ተሻሽለናል!

ሲግመንድ ፍሮይድ የስነ-ልብና ተመራማሪ (psychoanalyst) ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዘ ደግሞ የታሪክ ስነ-ልቦና “Psychohistory” የሚባል የጥናት ዘርፍ አለ። የዚህ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተመራማሪ የሆኑት እንደ “Hans Meyerhoff” and “H. Stuart Hughes” ያሉ ምሁራን እንደሚሉት ታሪክ (history) እና የስነ-ልቦና ምርምር (psychoanalysis) በአስገራሚ ሁኔታ ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ ግብ ነው ያላቸው። ለምሳሌ፣ David E. Stannard” የተባለው ፀኃፊ “Shrinking History” በተሰኘ መፅሃፉ ገፅ 45 ላይ የታሪክና የስነ-ልቦና ምርምር ግብን “to liberate man from the burden of the past by helping him to understand that past” በማለት ይገልፀዋል።

ከላይ እንደተጠቀሰው የታሪክ እና የስነ-ልቦና ምርምር ግብ መሆን ያለበት ሰውን ስላለፈው ግዜ እንዲያውቅ በማድረግ በአመለካከቱ ውስጥ የተቀረፀውን ጠባሳ ማስወገድ ነው። በቀድሞ ታሪክ በተፈፀመ በደልና ጭቆና በግልና በማህበራዊ ስነ-ልቦናችን ላይ ያሳረፈውን ጠባሳ መፋቅና ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተሳነን ጤናማ የሆነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም። የታሪክ ጠባሳን ዘወትር እያወሳን፤ መጥፎ-መጥፎውን በሌሎች ላይ እየለጠፍን፥ ስለራሳችን በጎ-በጎውን እያሰብን፣ የሌሎችን ጥፋት እየዘከርን የራሳችንን ጥፋት ከዘነጋን፣ ሌሎችን ለሁሉም ነገር ተጠያቂ፥ እኛ ደግሞ በሁሉም ነገር ተጠቂ አድርገን የምናስብ ከሆነ፣ እውነታን ማየት፥ ማስተዋል ይሳነናል፣ የሌሎችን መከራና ስቃይ መገንዘብ ይከብደናል። በቀድሞ ታሪክ በእኛ ላይ የተፈጸመውን በደልና ጭቆና ዳግም በሌሎች ላይ እየፈፀምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ቀርቶ በትንሹ እንኳን መገመት ይሳነናል።

ያለፈ ታሪክ የወደፊት ተስፋችንን ማጨለም የለበትም። የታሪክ ጠባሳን እያሰብን ዛሬ ሌሎችን ማቁሰል የለብንም። የዛሬ ቁስል ነገ ላይ ሌላ ጠባሳ ይፈጥራል። የትላንት ቁስል እያከክን ዛሬ ላይ ያቆሰልነው ሰው ነገ በተራው ቁስሉን እያከከ ሊያቆሰለን ይመጣል። ያኔ ዛሬ ላይ እኛ ያላደረግነውን ነገ ላይ ሌሎች እንዲያረጉት መጠበቅ የዋህነት ነው። ዛሬ ላይ በጥፋቱ ሳይሆን ያለፈ ታሪክ እየቆጠርክ የዘራህው ቂም ነገ ላይ በቀል ሆኖ ይጠብቅሃል። የትላንቱን ቂም ይዘህ ዛሬ ላይ ስትበቀለው እሱም ነገ እንዲበቀልህ ቂም እየጠነሰስክ ነው።

ይሁን እንጂ፣ አሁን በኢትዮጲያ ያለው ሁኔታ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ ነው። በጥላቻ ክፉኛ የታመመው ማህበራዊ ስነ-ልቦናችን የታሪክ ጠባሳችንን ከማከም ይልቅ ቂም-በቀል እየደገሰልን ይገኛል። የጥላቻ ፖለቲካን ለማስወገድ በቅድሚያ ስለ ቀድሞ ታሪካችን፣ ስለ ወቅታዊ ፖለቲካችን፣ ስለ የወደፊት ተስፋችን በግልፅ መነጋገር አለብን። በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተደብቆ ያለውን ቂምና ጥላቻ ፍቆ ለማስወገድ ሁላችንም ሃሳብና ስሜታችንን ያለገደብ መግለጽ መቻል አለብን።

እንደኛው ወገን ለብቻው የታሪክ ጠባሳን እያከከ የተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ግን እንኳን ስላለፈው ታሪክ፣ ዛሬ በእውን ያየውን፣ ስለ ወደፊቱ ያሰበውን እንዳይናገር የሚታፈን ከሆነ ነገ ላይ ሌላ ትልቅ ጠባሳ ይኖረናል። እንደ ሀገርና ሕዝብ፣ የቀድሞ ታሪካችን የነገ ተስፋችንን እያጨለመ ነው። ስለ ቀድሞ ታሪክ መፃፍና መናገር ዘረኝነትና ጥላቻ ከሆነ፣ ስለ ዛሬው ፖለቲካ መፃፍና መናገር ወንጀል ከሆነ፣ ነገ ላይ ምን አለን? ስለ ትላንትና ዛሬ መነጋገር ከተሳነን ለነገ ቂም-በቀል አሳደርን፡፡