Category Archives: Democracy

“አዎ… የትግራይ/ሕወሃት የበላይነት አለ!”

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል። “የትግራይ የበላይነት የለም” በሚል ካቀረቧቸው ማስረጃዎች ውስጥ ሁለት ነጥቦች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። የመጀመሪያው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የአንድ ብሔር (ክልል) የበላይነትን አያስተናግድም የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የሕወሃት አባላት በኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሆነ ካቢኔ ውስጥ የስልጣን የበላይነት የላቸውም የሚል ነው። ነገር ግን፣ የአንድ ብሄር (ቡድን) የበላይነት መኖር-አለመኖር የሚለካው በመንግስታዊ ስርዓቱ ወይም በባለስልጣናት ብዛት አይደለም። በዚህ ፅሁፍ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ያቀረቧቸውን ሁለት መሰረታዊ የመከራከሪያ ሃሳቦችን ውድቅ በማድረግ “የትግራይ የበላይነት መኖሩን” በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

1ኛ) “የትግራይ የበላይነት” የሚረጋገጠው የስርዓቱ መስራች በመሆን ነው! 
በእርግጥ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በፌዴራሊዝም ስርዓቱ መሰረት እያንዳንዱ ክልል ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣን ስላለው የትግራይም ሆነ የሌላ ብሔር የበላይነት ሊኖር እንደማይችል ገልፀዋል፡-

“/የትግራይ የበላይነት/ የሚባለው አንዳንዱ የተዛባ አመለካከት ነው፣ አንዳንዱ ደግሞ ፈጠራ ነው። ከፌዴራል ጀምረህ የስርአቱን አወቃቀር ነው የምታየው፡፡ /አወቃቀሩ ካልፈቀደ/ “የበላይነት“ የሚፈልግም ካለ ስሜት ብቻ ፤ “የበላይነት አለ“ የሚልም የራሱ ግምት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ …/በኢህአዴግ/ አንዱ በደንብ የገምገምነው እሱን ነው፤ “የትግራይ የበላይነት“ የሚባል የለም ነው፡፡ …ሄደን ሄደን ስርእቱን እንየው ነው፡፡ ስርአቱ “የበላይነት“ እንዲኖር ይፈቅዳል ወይ? የምንፈቅድ አለን ወይ? የትግራይ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም፡፡ ይሄ ስርአት ካልፈረሰ በስተቀር ሊኖር አይችልም፡፡ ይሄ ስርአት የትግራይንም የሌላንም የበላይነት አያስተናግድም፡፡ …ሁሉም ድርጅት የራሱን ነው የሚያስተዳድረው፡፡ ህወሓት ኦሮሚያን ወይም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር አይችልም፡፡ ስርአቱ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ በክልል የበላይነት የሚባለው የሌለ አምጥቶ የመለጠፍ ፈጠራ ነው፡፡ ስርእቱ በዚህ መሰረት አልተገነባም አይሰራም፡፡” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል 

በእርግጥ በፌደራሊዝም ስርዓቱ መሰረት “የትግራይ የበላይነት አለ” ማለት አይቻልም። ነገር ግን፣ በኢትዮጲያ “የትግራይ የበላይነት” መኖርና አለመኖር የሚለካው የሕወሃት ፓርቲ በአማራ ወይም በኦሮሚያ ክልል ላይ ባለው የመቆጣጠር ወይም የማስተዳደር ስልጣን አይደለም። ምክንያቱም፣ በፖለቲካ ውስጥ “የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል የራሱ የሆነ መመዘኛ መስፈርት አለው።

የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት ራሱን የቻለ ፅንሰ-ሃሳብ ሲሆን እሱም “The Class Domination Theory of Power” ይባላል። በዚህ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት መኖርና አለመኖር የሚረጋገጠው ሌሎች የሚተዳደሩበትን ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ባለው ችሎታ ነው። “Vergara L.G.” (2013) የተባለው ምሁር የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነትን፤ “Domination by the few does not mean complete control, but rather the ability to set the terms under which other groups and classes must operate” በማለት ይገልፀዋል።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “የትግራይ የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ማረጋገጥ የሚቻለው መንግስታዊ ስርዓቱ “የአንድ ብሔር/ክልል የበላይነትን ይፈቅዳል ወይስ አይፈቅድም” በሚለው እሳቤ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌሎች ብሔሮችና ክልሎች የሚተዳደሩበትን ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ትልቁ ድርሻ የማን ነው በሚለው ነው። የአማራ እና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች የሚተዳደሩበትን በብሔር ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ከንድፈ-ሃሳብ እስከ ትግበራ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ሕወሃት ነው።

በእርግጥ ዶ/ር ደብረፅዮን እንዳሉት፣ መንግስታዊ ስርዓቱ ሕወሃት የአማራና ኦሮሚያ ክልልን እንዲያስተዳድር አይፈቅድም። ነገር ግን፣ የአማራ ሆነ የኦሮሚያ ክልል የሚተዳደሩበትን መንግስታዊ ስርዓት እና ደንብ የቀረፀው ሕውሃት ነው። ስለዚህ፣ የአማራ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል የሚመሩበትን ስርዓትና ደንብ በመወሰኑ ረገድ ካለው ችሎታ አንፃር “የትግራይ የበላይነት” ስለ መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም።

2ኛ) የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው በፖለቲካ ልሂቃን ነው!
ዶ/ር ደብረፅዮን “የትግራይ የበላይነት” አለመኖሩን ለማሳየት ያቀረቡት ሌላኛው የመከራከሪያ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ብዛት ነው። ከዚህ አንፃር፣ በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ ከፍተኛ የመወሰን ስልጣን ባላቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ የሕወሃት አባል የሆኑ ባለስልጣናት ብዛት ትንሽ መሆኑ ነው፡-

“በፖለቲካ ሃላፊነትም እኩልነት ነው የሚታየው፡፡ በኢህአዴግ ምክር ቤትም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል ውክልና ያላቸው፡፡ ለምሳሌ አንጋፋው ህወሓት ነው በሚል የተለየ ተጨማሪ ቁጥር አይሰጠውም፡፡ ብዙ ውሳኔ በሚወሰንበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ከ36ቱ ከሁላችንም እኩል ዘጠኝ ነው የተወከለው፡፡ አብዛኛው ያልተስማማበት ስለማያልፍ ማንም ድርጅት ዘጠኝ ሰው ይዞ የበላይነት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ….ለምሳሌ በካቢኔ አሁን 30 ነን፡፡ ድሮም ዛሬም ህወሓት ሶስት ሚኒስትር ብቻ እኮ ነው ያለው፤ ሶስት ይዘህ ደግሞ እንዴት ነው የተለየ ልታስወስን የምትችለው?” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

ነገር ግን፣ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና በጠ/ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ያሉት የሕወሃት አባል የሆኑ ባለስልጣናት ብዛት አነስተኛ መሆኑ የስልጣን የበላይነት አለመኖሩን አያሳይም። ምክንያቱም፣ የአንድ ቡድን/ብሔር የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው በባለስልጣናት ብዛት ሳይሆን በፖለቲካ ልሂቃን (political elites) አማካኝነት ነው። በዚህ መሰረት፣ የሕወሃት የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ ልሂቃን ከባለስልጣናት በሚያገኙትን አድሏዊ ድጋፍና ትብብር መንግስታዊ ስርዓቱ እና የባለስልጣናቱ ውሳኔ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማስቻል ነው። ፅንሰ-ሃሳቡን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ያግዘን ዘንድ በድጋሜ ከ“Vergara L.G.” (2013) ፅኁፍ ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፡-

“…political elites are defined as persons who, by virtue of their strategic locations in large or otherwise pivotal organizations and movements, are able to affect political outcomes regularly and substantially. The elites have power over the state, the civil organization of political power. Even though they could have conflicts with the mass, which certainly can affect political decisions from “top down” to “bottom up” the possession of multiples forms of capital (social, cultural, economic, politic, or any other social benefits derived from the preferential treatment and cooperation between individuals and groups) allows [them] to ensure their social reproduction as well as the cultural reproduction of the ruling class.” Elites, political elites and social change in modern societies; REVISTA DE SOCIOLOGÍA, Nº 28 (2013) pp. 31-49.

የፖለቲካ ልሂቃን በመንግስታዊ ስርዓቱ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱና በሲቭል ድርጅቶች ሥራና አሰራር ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ፣ በዚህም የአንድ ብሔር/ፓርቲ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችሉት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ ሲኖር ነው። በዚህ መሰረት፣ የስልጣን የበላይነት ባለው የፖለቲካ ቡድን የተለየ አድሏዊ ድጋፍና ትብብር የሚደረግላቸው ልሂቃን የፖለቲካ አጀንዳን በመቅረፅና በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል።

ከዚህ አንፃር፣ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅን መሰረት በማድረግና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር በሚል ሰበብ ለእስርና ስደት ከተዳረጉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ምን ያህሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው? ተቃዋሚ ይቅርና፣ በ2007 ዓ.ም በመቐለ ከተማ በተካሄደው የኢህአዴግ 10ኛ ጉባዔ ላይ በቀረበው ሪፖርት ላይ የጠባብነትና ትምክህተኝነት አመለካከት አንፀባርቀዋል በሚል ከስልጠና በኋላ የመስክ ክትትል ከተደረገባቸው ጀማሪና መካከለኛ የኢህአዴግ አመራሮች ውስጥ ምን ያህሉ የሕወሃት አባላት ናቸው? ከምርጫ 2002 – 2006 ዓ.ም በኋላ ባሉት አራት አመታት ብቻ፤ 19 ጋዜጠኞችን ለእስር፣ 60 ጋዜጠኞች ደግሞ ለስደት ሲዳርጉ ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ የትግራይ ብሔር ተወላጅ ናቸው? ሦስቱም ጥያቄዎች መልሱ ከሞላ-ጎደል “ዜሮ፥ ምንም” የሚል ነው።

ታዲያ የሕወሃት አባላት “በጠባብነት” እና “ትምክህተኝነት” በማይፈረጁበት፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን “ከግንቦት7 ወይም ኦነግ” ጋር በማገናኘት በፀረ-ሽብር ሕጉ በማይከሰሱበት፣ ያለ ፍርሃትና ስጋት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት በሚገልፁበት፣ የፖለቲካ አጀንዳውን በበላይነት በሚወስኑበት፣ …ወዘተ “የትግራይ የበላይነት የለም” ሊባል ነው። በአጠቃላይ፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ያቀረቧቸው ሁለት የመከራከሪያ ሃሳቦች ምክንያታዊና አሳማኝ አይደሉም። “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው መልሱ “አዎ…አለ!” ነው። እውነታው ይሄ ነው፡፡

የኢህአዴግ “የደርግ ናፋቂዎች” እና የእናቴ “ጭራቅ” አንድ ናቸው!

ውድ ተማሪዎች “በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ አከባቢ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ለተከሰተው የፀጥታ ችግር እንደ ዋንኛ መንስዔ ሊሆን የሚችለው የቱ ነው?” ለሚለው የጥያቄ “የደርግ ሥርዓት ናፋቂዎች የፈጠሩት ችግር” ተብሏል። “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” ማለት ምን ማለት ነው? የደርግን ስርዓት የሚናፍቁትስ እነማን ናቸው።

image

በእርግጥ እናንተ የደርግ ስርዓትን በተግባር አታውቁትም። የደርግ ስርዓት ሲወድቅ እኔም ገና የ3ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። በእርግጥ ቤተሰቦቻችሁ የደርግ ስርዓትን ሊያውቁት ይችላሉ። በተለይ እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የደርግ ስርዓትን በተግባር ኖረው አይተውታል። እኔና እናንተ ግን የደርግ ስርዓትን ባንኖርበትም መፅሃፍ በማንበብ፣ በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን በመጠየቅ ማወቅ እንችላለን።

በተለይ ደግሞ በቀይ-ሽብር ዘመን የደረሰውን በደልና ጭፍጨፋ በሰው-ልጅ ታሪክ እጅግ አሰቃቂ የሚባሉ ድርጊቶች በኢትዮጲያኖች ላይ እንደተፈፀመ እንገነዘባለን። ለምሳሌ፣ እኔ ሰሞኑን ሳነብ ያገኘሁትን አንድ መረጃ ላካፍላችሁ። የቀይ-ሽበር ዘመቻ በተጀመረ የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ብቻ እንደ እናንተ ያሉ 5000 ተማሪዎች እንደ አውሬ ታድነው ተገድለዋል፣ 30000 ደግሞ ታስረዋል። በጠቅላላ በቀይ-ሽብር ዘመን የተገደሉት ኢትዮጲያኖች ብዛት 500000 (ግማሽ ሚሊዮን) ይደርሳል።

ከቀይ-ሽብር በኋላ ደግሞ ለምሳሌ በትግራይ ሃውዜን ባፈፀመው የአየር ድብደባ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ 1800 ንፁሃን ዜጎችን ገድሏል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የደርግን አስከፊነት በግልፅ ለመረዳት እንዲያግዛችሁ፣ በሸገር ሬድዮ ጣቢያ “የጨዋታ እንግዳ” ፕሮግራም ላይ ጋዜጠኛ ማዕዛ ብሩና ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነብይ መኮንን ጋር ያደረገችውን ጭውውት ከጣቢያው ድህረ-ገፁ ላይ አውርዳችሁ ብታዳምጡት ብዙ ጠቃሚ መረጃዎች ታገኙበታላችሁ።

አያችሁ ተማሪዎች፣…”የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” ማለት ይሄን ሁሉ መከራና ስቃይ የሚናፍቁ ሰዎች ማለት ነው። በእርግጥ በሰው ልጅ ታሪክ እንዲህ ያለ የመከራና ስቃይ ዘመን የሚናፍቁ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው። በእርግጥ እንዲህ ያሉ ሰዎች እርኩስ መንፈስ የተጠናወታቸው ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ያንን አሰቃቂ ዘመን እያስታወሱ እኔና አናንተን በነፃነት እንዳንናገር፥ እንዳናስብ በፍርሃት ቆፈን መለጎም የሚሹ ሰዎች ናቸው።

ውድ ተማሪዎች፣ የእናንተ ወላጆች ያደርጉ እንደሆነ እኔ አላውቅም። እኔ ልጅ ሳለሁ ግን “ዋ…ጭራቅ ይበላሃል” እያለች ታስፈራራኝ ነበር። ለምሳሌ፣ “ወንዝ ውስጥ ብቻህን ከተቀመጥክ “ጭራቅ” ይበላሃል” ትለኛለች። ማታ ማታ እያለቀስኩ ሳስቸግር “ጆሮ የሚቆርጠው ሰውዬን ልጥራው” ትለኛለች። እኔም ካደኩ በኋላ፣ ታናሾቼን “ጆሮ ቆራጩ መጣ!” እያልኩ አስፈራርቼያለሁ። …ሌላ እናንተ የተባላችሁት ነገር ካለ ጨምሩበት። ነገር ግን፣ ጭራቁም ሆነ ጆሮ-ቆራጩ ማስፈራሪያ እንጂ በእውን የሉም። በአጠቃላይ፣ ልጆች ሲያስቸግሩ ታላላቆቻችን ለማስፈራሪያነት የፈጠሯቸው አስፈሪ ምናባዊ ምስሎች ናቸው።
    
በተመሳሳይ፣ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች” የሚለው እንደ እናንተ ያሉ ወጣቶችን ለማስፈራራት የፈጠረው አሰቃቂ ምናባዊ ምስል ነው። ከኢህአዴግ መንግስት በስተቀር የደርግን ስርዓት የሚናፍቅ አንድም ኢትዮጲያዊ የለም። ውድ ተማሪዎች፣ አሁንም ደግሜ የምላችሁ፣ ሀገርን መሃን ያደረገ፣ አንድ ትውልድን ያጨናገፈን የደርግ ስርዓት የሚናፍቅ ኢትዮጲያዊ በጭራሽ የለም።

ልክ በሕፃንነት እድሜዬ እናቴን ሳስቸግር “ጭራቅ ይበላሃል፣ ጮሮ ቆራጩን ልጥራው፣…” እያለች እንደምታስፈራራኝ ሁሉ የኢህአዴግ መንግስትም እኔና እናንተን ለማስፈራራት የፈጠረው ምናባዊ ድርሰት ነው። ከ2008 ዓ.ም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለታየው የፀጥታ ችግር ዋና መንስዔው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ በአደባባይ እንዳመነው “የመልካም አስተዳደር ችግር” ነው። የተለያዩ ሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚያነሱት የመብትና ነፃነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በወታደርና በጥይት ለማፈን ጥረት በማድረጉ የተከሰተ ችግር ነው።

በአጠቃላይ፣ አሁን በፈተናችሁ ላይ የተጠቀሰው “የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች የፈጠሩት ችግር” የሚለው ልክ እንደ እናቴ “ጭራቅና ጆሮ-ቆራጩ ሰውዬ” የፈጠራ ድርሰት ነው። ልዩነቱ እናቴ ስላስቸገርኳት ትቆጣኛለች፣ ታስፈራራኛለች፣ ትገርፈኛለች። የኢህአዴግ መንግስት ግን መብትና ነጻነቴን ስለጠየቅኩት ያስረኛል፣ ይደበድበኛል፣ ይገድለኛል! እናቴ እኔን በስነ-ምግባር አንፃ ልታሳድገኝ ነው፣ ኢህአዴግ ግን የዜግነት መብቴን ነፍጎ የራሱን እድሜ ለማራዘም ነው።
 

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 2፡- በትግል ወቅት የተፈፀመው ጭፍጨፋና ያልተመለሰው ጥያቄ

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 1 ፅኁፍ በብሔርተኝነትና በራስ-የመወሰን መብትን መሰረት ያደረገ የትግል እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚጀመር የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችንና የትግራይ አማፂያንን በማሳያነት በመጥቀስ ተመልክተናል። በዚህ ፅኁፍ ደግሞ የደርግና እንግሊዝ ጦር ሰራዊት ከአማፂያኑ የደረሰባቸውን ያልተጠበቀ ሽንፈትና ውርደት ተከትሎ በነፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙትን በደልና ጭቆና እንመለከታለን። ከዚያ በመቀጠል፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአማፂያኑ መሪዎች/ልሂቃን ከጦርነቱ ጎን-ለጎን ለራሳቸው ማንሳት የነበረባቸው “መሰረታዊ ጥያቄ” ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

በክፍል አንድ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የደቡብ አፍሪካ ነባር ነጭ ሰፋሪዎች እና የትግራይ ሕዝብ የትጥቅ ትግል የጀመሩት በራስ-የመወሰን መብታቸውን ለማረጋገጥ ነው። በዚህ መልኩ የተጀመረውን የትጥቅ ትግል ለማክሸፍ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእንግሊዝ እና የደርግ ወታደሮች ተሰማርተው ነበር። የሁለቱም ጦር ሰራዊት በአማፂያኑ ከተደቀነባቸው አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ራሳቸውን ለማዳን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። እስኪ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች የፈፀሙትን ጭፍጨፋ እና ደርግ በትግራይ፥ ሃውዜን ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ የምክንያት-ውጤት ተያያዥነትና ተመሳሳይነት በአጭሩ እንመልከት። 

1. በትግል ወቅት የተፈፀመው ጭፍጨፋ

1.1 በደቡብ አፍሪካ፡ “መሬቱን በእሳት መለብለብ”
እ.አ.አ በ1899 ዓ.ም የእንግሊዝ ጦር አዛዦች በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች ግዛትን “Boers Republic” ለመቆጣጠር ሲዘምቱ ለሽምቅ ተዋጊዎቹ ዝቅተኛ ግምትና ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው። ሽምቅ ተዋጊዎቹን “ኋላ-ቀር፣ ቀሽሞች እና የጫካ ሽፍቶች” በማለት ያጣጥሏቸው ነበር። በእርግጥ የነጭ ሰፋሪዎች ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ከ300 ሺህ አይበልጥም ነበር። ከዚህ ውስጥ ግን 27000 የሚሆኑ የሽምቅ ተዋጊዎች ነበሯቸው። በአንፃሩ በጦርነቱ የተሳተፈው የእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ጠቅላላ ብዛት 500 ሺህ ይደርስ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተዋጊዎች ውጊያው በተጀመረ የመጀመሪያ ሁለት አመታት ውስጥ በእንግሊዝ ጦር ላይ ያልተጠበቀ ድል ተቀዳጁ። እንግሊዝ ከአሰማራቻቸው የወታደሮች አንፃር 5% የሚሆኑት የደቡብ አፍርካ ሽምቅ ተዋጊዎች 22000 የሚሆኑ የእንግሊዝ ወታደሮችን ገደሉ። በዚህም እንግሊዝ ከ1815 – 1915 ዓ.ም ባሉት መቶ አመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማታውቀው አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ተከናነበች። 

አብዛኛው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች በሽምቅ ውጊያው ተሳታፊ ናቸው። ወደ ጦር ሜዳ ሳይሄዱ የቀሩት በአብዛኛው እናቶች፥ ሕፃናት ልጆችና አዛውንቶች ነበሩ። የእንግሊዝ ጦር በሽምቅ ተዋጊዎቹ የሚደርስበት ጥቃት ራሱን ለማዳን “ተዋጊዎቹን ለማጥፋት “መሬቱን በእሳት መለብለብ” (Scorched-earth) የተባለውን የውጊያ ስልት ተግባራዊ አደረገ። ተዋጊዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ-ለሙሉ በእሳት ቃጠሎ እንዲወድሙ ተደረገ።

በዚህ ምክንያት፣ ከመቶ ሺህ በላይ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ወደ ማጎሪያ ካምፕ ከገቡት ውስጥ 28000 የሚሆኑት በርሃብና በበሽታ ሲሞቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ 22000 (81%) የሚሆኑት ከ16 አመት በታች ሕፃናት ናቸው።  ለአንድ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪ ውርደት ማለት ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታጉረው በርሃብና በበሽታ ሲያልቁ እያዩ ምንም ማድረግ አለመቻል ነው። ከዚህ ሰቆቃ የተረፉት ነጭ ሰፋሪዎች እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም እንግዝ ለቅቃ ስትወጣ “ከዳኒኤል ፍራንኮይስ ማለን” (Daniel Francois Malan) መሪነት የአፓርታይድ ስርዓትን መሰረቱ።

1.2 በኢትዮጲያ፡ “ባህሩን በቦምብ ማድረቅ” 

እ.አ.አ በ1979 ዓ.ም ወታደራዊ ደርግ መንግስት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የሚንቀሳቀሱትን አማፂያን በኃይል ለመደምሰስ ቆርጦ ተነሳ። ለዚህ ዓላማ ሁለተኛውን አብዮታዊ ጦር ከፍተኛ ትጥቅ ያለው ከ70ሺህ በላይ ወታደሮች አሰማራ። ከአንድ አመት በኋላ በመጋቢት ወር 1980 ዓ.ም ግን ከ15000 የማይበልጡ የሻዕቢያ ተዋጊዎች ወደ 10000 የደርግ ወታደሮችን በመግደል አሸነፉ። በቀጣዩ ሚያዚያ ወር 1980 ዓ.ም ደርግ ሦስተኛን አብዮታዊ ጦር በማደራጀት በትግራይ የሚንቀሳቀሱ አማፂያንን በኃይል ለመደምሰስ በለገሰ አስፋው መሪነት ተንቀሳቀሰ። 

ሦስተኛን አብዮታዊ ጦር በትግራይ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር የወደቁትን ቦታዎች ለማስለቀቅ እና የኤርትራ-ትግራይ መስመርን ለማስከፈት ያደረገው ጥረት በሕውሓት የውጊያ ስልት በተደጋጋሚ ከሸፈ። የደርግ ሰራዊት በኤርትራ ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈት በኋላ ሻዕቢያን ለማሸነፍ በቅድሚያ ሕወሓትን መደምሰስ እንዳለበት ወስኖ ነበር የመጣው። ነገር ግን፣ የአማፂያኑን ይዞታ መልሶ ለማስለቀቅና የአዲስ አበባ – አስመራ መንገድን ለማስከፈት ባደረጋቸው ውጊያዎች ተደጋጋሚ ሽንፈት ገጠመው።

በመጨረሻም፣ በትግራይ አማፂያን እየደረሰበት ያለው ተደጋጋሚ ሽንፈት ከትግራይ በተጨማሪ ኤርትራንም እያሳጣው እንደሆነ ሲውቅ የወሰደው እርምጃ በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ እልቂት አሰከተለ። በደቡብ አፍሪካ የሸምቅ ተዋጊዎች የተደቀነባቸውን አሳፋሪ ሽነፈት ለማስቀረት ተግባራዊ እንደተደረገው የ¨Scorched-earth” ፖሊሲ፣ የደርግ ሰራዊት “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል ሃውዜን ላይ የአየር ድብደባ ፈፀመ። የሕውሃት መስራችንና የቀድሞ አመራር የነበሩት አረጋዊ በርሄ የሃውዜን ጭፍጨፋንና በትግራይ ሕዝብ ስነ-ልቦና ላይ ያሰከተለውን ጉዳት እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…On on 22 June 1988, that Legesse ordered the aerial bombardment of Hawzien. This attack, conducted by helicopter gunships and MiGs, resulted in 1,800 civilian deaths, the worst single atrocity of the war since the start of the ELF insurrection in 1961…. Many elderly parents who had been reluctant to let their children join the Front were now not only encouraging them but also themselves requesting to be armed and join the militia forces. While the numbers of TPLF brigades grew to more than 20,000 fighters, the Dergue’s forces were dwindling.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam 2008, Page 184 – 317.

ከላይ ከተገለፀው ክስተት በኋላ የደርግ ሰራዊት በሽንፈት ላይ ሽንፈት ማስተናገድ ቀጠለ። በየካቲት ወር 1981 ዓ.ም የሕወሃት ታጋዮች በእንዳ-ስላሴ የተደረገውን ውጊያ ካሸነፉ በኋላ በቀጣዩ አንድ ሳምንት ውስጥ 20000 የደርግ ሰራዊትና የመንግስት ሰራተኞች ትግራይን ለቀው ወጡ። ይህን ተከትሎ መላው ትግራይ በሕወሃት ቁጥጥር ስር ወደቀ። ግንቦት 20/1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ተገረሰሰ።

በአጠቃላይ፣ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የፈፀሙትን በደልና ጭፍጨፋ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ፈፅሞታል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአማፂያኑ መሪዎች/ልሂቃን ከጦርነቱ ጎን-ለጎን ለራሳቸው ማንሳት የነበረባቸው “ጥያቄ” ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

2. በትግል ወቅት ያልተመለሰው ጥያቄ

ለአንድ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪ ወራሪውን የእንግሊዝ ጦር ለማስወጣት በሚደረገው የትጥቅ ትግል መሳተፍ ትክክለኛ ተግባር ነው። በተመሣሣይ፣ ለአንድ የትግራይ ተወላጅ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል መሳተፉ አኩሪ ተግባር ነው። በአጠቃላይ፣ ከኢምፔራሊዝም ወራሪ ሆነ ከአምባገነናዊ ስርዓት ነፃ ለመውጣት የሚደረገው የትጥቅ ትግል አግባብነቱ አጠራጣሪ አይደለም።

ነገር ግን፣ “Edward Said” የተባለው” ምሁር “Frantz Fanon” የተባለ የአልጄሪያ የነፃነት ታጋይን በመጥቀስ፣ የትግል መሪዎች/ልሂቃን የትጥቅ ትግሉን ከመምራት ባለፈ አንድን ጥያቄ መጠየቅና መመለስ እንዳለባቸው ይገልፃል፡-

“This is defensive nationalism of course, yet as Frantz Fanon analysed the situation during the height of the Algerian war of liberation against the French, going along with the approving chorus of Algerian nationalism as embodied in party and leadership is not enough. There is always the question of goal which, even in the thick of battle, entails the analysis of choices. Are we fighting just to rid ourselves of colonialism, a necessary goal, or are we thinking about what we will do when the last white policeman leaves? According to Fanon, the goal of the native intellectual cannot simply be to replace a white policeman with his native counterpart, but rather what he called the invention of new souls.”  REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual, Lec.2: Holding Nations and Traditions at Bay, 1993.

ከላይ እንደተገለፀው፣ ለነፃነት የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት፣ ጦርነቱ ተፋፍሞ የሰማዕታቱ ቁጥር እየጨመረ በሄደበት፤ እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ወይም እንደ ትግራይ ሕዝብ በንፁሃን ላይ በደልና ጭፍጨፋ ሲፈፀም፣ በዚህም ምክንያት የታጋዮች ሕዝባዊ ወገንተኝነትና የጨቋኙ ስርዓት ጠላትነት በናረበት ወቅት፣…የትግሉ መሪዎችና ልሂቃን “የትግላችን የመጨረሻ ግብ ምንድነው?” ብለው መጠየቅና ለዚህም ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

ይህን መሰረታዊ ጥያቄ ለራስ አለመጠየቅ ወይም በሌሎች ታጋዮች ዘንድ እንዲነሳ አለመፍቀድ እና በትግሉ የመጨረሻ ግብ ላይ ግልፅ የሆነ ግንዛቤና አቅጣጫ ማስቀመጥ አለመቻል በሚታገሉለት ሕዝብ እና በትግሉ ሰማዕታት ላይ ክህደት መፈፀም ነው። በትግል ወቅት ይህን ጥያቄ ራስንና ሌሎች ታጋዮችን በመጠየቅ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያየ ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጥ በማድረግ፣ በውይይት የዳበረ ግንዛቤና የጋራ መግባባት ካልተፈጠረ በስተቀር የነፃነት ትግሉ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ ጨቋኙ ስርዓት በተወገደ ማግስት እንደ አልጄሪያ፥ ቦስኒያ፥ ደቡብ ሱዳን፥…ወዘተ የእርስ-በእርስ ጦርነት ይከተላል። ወይም ደግሞ እንደ ኤርትራ የሻዕቢያ መንግስት፥ እንደ ኢትዮጲያ የኢህአዴግ መንግስት፥ እንደ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት፥ …ወዘተ የትግሉ መጨረሻ የቀድሞው ስርዓት ጭቁኖችን አዲስ ጨቋኝ ስርዓት እንዲመሰርቱ ማስቻል ይሆናል።

እንደ አልጄሪያዊው የነፃነት ታጋይና ልሂቅ “Frantz Fanon” አገላለፅ፣ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ ግብ “አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር ነው” (the invention of new souls)። በመሰረቱ፣ የዘር/ብሔር አፓርታይድ የትጥቅ ትግል መሪዎችና ልሂቃን ለራሳቸው አሮጌ ነፍስ ይዘው አዲስ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመመስረት ሲያጣጥሩ የሚፈጥሩት ሌላ ጨቋኝ ስርዓት ነው። ነገር ግን፣ እነዚህን አዳዲስ ነፍሶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ መፍጠር ይቻላል? ከቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት ጋር የትጥቅ ትግል ለመጀመር የተፈጠሩ አሮጌ ነፍሶች ምን ዓይነት ናቸው? በአሮጌ ነፍሶች ውስጥ ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል? ለምንና እንዴት? እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በቀጣይ ክፍሎች በዝርዘር እንመለከታለን።    

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 1፡- ከልዩነት ወደ ጦርነት

“የሰቆቃ ልጆች” በሚል ርዕስ ያቀረብናቸው አምስት ተከታታይ ፅሁፎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጀርመንና ጃፓን ወታደራዊ ፋሽስት፣ እንዲሁም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በእስራኤልና በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት የተመሰረቱበትን ሁኔታ በዝርዝር ለመዳሰስ ሞክረናል።  ከዚህ በመቀጠል “የዘር/ብሔር አፓርታይድ” በሚል ርዕስ በምናቀርባቸው ተከታታይ ፅሁፎች የኢትዮጲያና የደቡብ አፍሪካ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረትን በዝርዝር ለመዳሰስ እንሞክራለን። በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ለዜጎች የመብትና ነፃነት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ እንዴት ወደ ብሔርተኝነት እና ጦርነት እንደሚቀየር እንመለከታለን።

1. የዘር/ብሔር ልዩነት   

እ.አ.አ. በ1950 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ያወጣው የሕዝብ ምዝገባ አዋጅ (Population Registration Act) የሀገሪቱን ዜጎች “ነጭ፥ ጥቁር፥ “ከለርድ” (colored) እና ህንዳዊያን” በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። በተመሣሣይ፣ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀፅ 39(5) የሀገሪቱን ዜጎች በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነ ልቦናን መሰረት በብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ይከፋፍላቸዋል።

በመሰረቱ “አፓርታይድ” (Apartheid) የሚለው ቃል “መለየት” (Separatedness) ወይም “መለያየት” (the state of being apart) ማለት ነው። ዜጎች የሚከፋፈሉት በዘር ሆነ በብሔር በመካከላቸው የሚኖረውን ልዩነት አይቀይረውም ወይም መለያየቱን አያስቀረውም። ስለዚህ፣ “አፓርታይድ” ማለት የአንድ ሀገር ዜጎችን በዘር/ብሔር በመለየትና በመለያየት የሚያስተዳድር ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረትን ከማየታችን በፊት ግን የዘር/ብሔር ልዩነት እንዴት ለፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ እንደሚውል እንመልከት።

በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዘር ሀረግ፥ በቆዳ ቀለም፣ በብሔር፥ በቋንቋ፥ በባህል፥ በልማድ፣ በሥነ-ልቦና፣ በሃማኖት፣…ወዘተ ይለያያሉ። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፥ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብሎ የሚያምን፥ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር ማኅበረሰብ እንደ ሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

ምንግዜም ቢሆን በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እና በሌላ መካከል ልዩነት ይኖራል። ከፖለቲካ አንፃር ሲታይ፣ ልዩነት የሰላም ወይም ጦርነት፣ የዴሞክራሲ ወይም ጭቆና መኖርና አለመኖር መለያ ነው። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሃማኖት፥ ሕልውና (ማንነት)፣…ወዘተ “እኩል” በሚከበርበት፣ ሁሉም ዜጎች የራሳቸውን አመለካከት ያለማንም ጣልቃ-ገብነት የመያዝና ሃሳባቸውን “በነፃነት” መግለፅ በሚችሉበት፣ እንዲሁም ከሀገሪቱ ልማትና እድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚ ከሆኑ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ መኖሩን ያረጋግጣል።

በተቃራኒው፣ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ባልተረጋገጠበት ሀገር ጭቆና መኖሩና ጦርነት ማስከተሉ እርግጥ ነው። በአንድ አከባቢ የሚኖር ማኅብረሰብ ጭቆና ሲደርስበት በቅድሚያ መብቱና ነፃነቱ እንዲከበር በአመፅና ተቃውሞ ብሶትና አቤቱታውን በአደባባይ ይገልፃል። ሆኖም ግን፣ መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የሕዝቡ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ ግጭትና ጦርነት ይቀየራል።

በመሰረቱ በአንድ አከባቢ የሚኖር ማኅብረሰብ የራሱን መንግስት የሚመሰረተው ሕግና ስርዓት እንዲያስከብር፣ በዚሁም የሁሉንም መብትና ነፃነት እንዲያረጋግጥ ነው። የተወሰነ ሕብረተሰብ ክፍል የእኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ሲያነሳ መንግስት በምላሹ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ለእስራት፣ እንግልትና አካል ጉዳት የሚዳረግ ከሆነ እንደ መንግስት መሰረታዊ ዓላማውን ስቷል። መሰረታዊ ዓላማውን የሳተ ነገር ሁሉ ፋይዳ-ቢስ ነው። ስለዚህ፣ ከሕዝቡ የሚነሳን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚሞክር መንግስት ሕጋዊ መሰረት የለውም።

በዚህ ምክንያት በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ውስጥ እንዲህ ያለ ቅሬታ ሲፈጠር የለውጥ አብዮት ማስነሳት ለሚሹ ልሂቃን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ልሂቃን በማህብረሰቡ ውስጥ የለውጥ አብዮት ለመቀስቀስ ከሚጠቀሟቸው ስልቶች ውስጥ ዋናዋናዎቹ የብሔርተኝነት ስሜት እና በራስ-የመወሰን መብት ናቸው። በዚህ መልኩ በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እና በሌላ መካከል ያለ ልዩነት በሂደት ወደ ግጭትና ጦርነት ያድጋል። የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት – TPLF) መስራችና የቀድሞ አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ድርጅቱ የትግል አጀማመር በሰጠው ትንታኔ እንዲህ ይላል፡-   

“Discontent can be caused by a variety of intervening factors but often is articulated in relation to the state that claims to possess the moral and legal authority to manage the affairs of the populace. Once discontent has been created, it can be easily politicized by the elite who seek change and civil disorder may follow. In this circumstance ‘loss of government legitimacy is an important if not critical factor in explaining civil strife events.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Ch.2, Page 24.

2. ብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት

ፖለቲካዊ ስርዓቱ የአንድን ማህብረሰብ እኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማያረጋገጥ ከሆነ የማህብረሰቡ ልሂቃን የተለያየ ዓይነት የለውጥ እርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ። በተለይ መንግስታዊ ስርዓቱ የዜጎቹን መብትና ነፃነት ማረጋገጥ ሲሳነው በቅድሚያ አስፈላጊ የሚሏቸውን የሕግና ፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ ይጎተጉታሉ። የሀገሪቱ መንግስት ስራና አሰራሩን በመቀየር ከሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ከተሳነው አመፅና ተቃውሞ ይቀሰቀሳል። መንግስት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ብሶትና አብቱታውን በአደባባይ እንዳይገልፅ የሚያፍነው ከሆነ የለውጥ ንቅናቄው ወደ ትጥቅ ትግልና ጦርነት ያመራል።

በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የለውጥ ፍላጎት ወደ “አብዮት” (revolution) ለመቀየር እና የትግል ስልቱን ከአደባባይ አመፅና ተቃውሞ ወደ ውጊያና ጦርነት ለማሸጋገር የፖለቲካ ልሂቃኑ ሁለት ነገር መፍጠር አለባቸው። እነሱም፣ አንደኛ፡- በብሔሩ፥ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የወገንተኝነትና የአንድነት ስሜት ለመፍጠር ብሔርተኝነትን ማስረጽ፣ ሁለተኛ፡- የትግሉን ዓላማና ግብ ደግሞ የብሔሩን፥ ብሔረሰቡን ወይም ሕዝቡን በራስ-የመወሰን መብት ማረጋገጥ እንዲሆነ ማሳመን አለባቸው።

ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት በሚደረጉ የሕዝብ ንቅናቄዎች ውስጥ ያለው መሰረታዊ ጥያቄ በራስ የመወሰን መብትን (right of self-determination) ነው። በራስ የመወሰን መበት አንድ ብሔር ወይም ሕዝብ የወደፊት ዕድሉን በራሱ የመወሰን፣ በራሱ ሕግና ደንብ የመተዳደር እና ከእሱ ፍቃድና ምርጫ ውጪ በሆኑ መሪዎች አለመመራት ነው። በዚህ መሰረት፣ ማህብረሰቡ ልዩነቱን በራሱ ማስከበር ይችላል። ከዚህ በፊት ሲያነሳቸው የነበሩት የእኩልነት፥ የነፃነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በራሱ ለራሱ መመለስ ይችላል። ብሔርተኝነት ደግሞ የማህብረሰቡን አባላት በትግሉ ዓላማና ግብ ዙሪያ አንድነትና ቁርጠኝነት እንዲኖረው ያስችላል። በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች እና በኢትዮጲያ ትግራይ የትጥቅ ትግል የተጀመረው በብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት ላይ ተመስርቶ ነው።

2.1 በደቡብ አፍርካ የነጭ ሰፋሪዎች (Boers) የትጥቅ ትግል

በደቡብ አፍሪካ ቀድመው የሰፈሩት ነጮች “Boers” የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ “Boers Republic” በሚል ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ነፃ ግዛቶች ነበሩ። ነገር ግን፣ እ.አ.አ. በ1866 የአልማዝ፣ እንዲሁም በ1886 ደግሞ የወርቅ ማዕድን በአከባቢው መገኘቱን ተከትሎ ብዙ የእንግሊዝና የሌሎች ሀገራት ዜጎች (utilanders) ወደ አከባቢው በብዛት መጉረፍ ጀመሩ። የአዲስ ሰፋሪዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄዶ በ1890ዎቹ የመጀመሪያ ላይ ከነባር ነጮች ”Boers” ጠቅላላ ብዛት በሁለት እጥፍ በለጠ። ይህ በነባር የደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብታቸውና ነፃነታቸው ላይ የሕልውና አደጋ ተጋረጠበት። 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በራስ-የመወሰን መብታቸው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ አዲስ ረቂቅ አዋጅ በማውጣት ተግባራዊ አደረጉ። ይህ አዋጅ የነባር ሰፋሪዎችን በራስ-የመወሰን መብት የሚያረጋግጥ ሲሆን የአዲስ ሰፋሪዎችን ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት የሚገድብ ነበር። አብዛኞቹ አዲስ ሰፋሪዎች ከእንግሊዝ ወይም ከቅኝ-ግዛቶቿ የመጡ እንደመሆናቸው በእንግሊዞች እና በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች (Boers) መካከል አለመግባባት አለመግባባት ተፈጠረ። አለመግባባቱ ወደ ጦርነት ተሸጋገረና በሁለቱ መካከል “Second Boers War” የተባለው፣ በዓለም ታሪክ አሰቃቂ በደልና ጭቆና የተፈፀመበት ጦርነት ተካሄደ። ይህ አሰቃቂ በደልና ጭቆና ደግሞ እ.አ.አ. በ1948 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ለተመሰረተው አፓርታይድ ስርዓት ዋና ምክኒያት ነው።  

2.2 በትግራይ የሕወሃት የትጥቅ ትግል 
በእርግጥ የትግራይ ሕዝብ በራስ የመወሰን ጥያቄን ማንሳት የጀመረው በቀዳማይ ወያኔ አማካኝነት ነው። በቀዳማይ ወያኔ የተካሄደው የአርሶ-አደሮች አመፅ ከባሌና ጎጃም የአርሶ-አደሮች አመፅ ጋር ተመሳሳይ ነው። የአርሶ-አደሮቹ አመፅና ተቃውሞ በዋናነት በእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ማዕከል ያደረገ ነበር። ሆኖም ግን፣ በወቅቱ የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ የወሰደው እርምጃ የአመፅ እንቅስቃሴውን በጦር ኃይል ማዳፈን ነበር። በዚህ መልኩ በወቅቱ የነበረው መንግስት ለሕዝቡ የመብትና ነፃነት ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ቀጣዩን የትግል ስልት በብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል።

በዚህ መሰረት፣ ዳግማዊ ወያነ – ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የማህብረሰቡን የብሔርተኝነት ስሜት በማቀጣጠል እና በራስ-የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የሕወሓት (TPLF) መስራችና የቀድሞ አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመር፣ የንቅናቄ ስልትና ድርጅታዊ አሰራር በተመለከተ እንዲህ ይላል፡- 

“…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one hand and the enforcement of strict internal discipline of its rank and file that able to take on rival forces decisively.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Ch.5, Page 151 – 152.

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሁለቱ ወገኖች፤ በእንግሊዞች እና በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በደርግ መንግስት እና በሕውሃት ታጋዮች መካከል ጦርነት ተካሂዷል። በጦርነቱ ወቅት የእንግሊዝና የደርግ መንግስት እያንዳንዳቸው 22000 ወታደሮች በሦስት አመት ውስጥ ተገድሎባቸዋል። ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ነጮችና በትግራይ ሕዝብ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በሁለቱ ሀገራት የተፈፀመው አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ለዘር/ብሔር አፓርታይድ መመስረት ያለውን አስተዋፅዖ በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።  

የሰቆቃ ልጆች ክፍል-5፡ የጭቆና ፈረሶች ወደ ጦርነት ይወስዳሉ!

ምሁራን መንግስትን በመደገፍ ወይም በመፍራት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስራና አሰራሩን ከመተቸት ይልቅ የመንግስት ቃለ-አቀባይ ከሆኑ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ የአመራርና አስተዳደር ሥራቸውን ከመስራት ይልቅ የምሁራኑን ሃሳብና ዕውቀት ስለ ምን እንደሆነ መወሰን ከጀምሩ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል። ይህ ሲሆን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይጨናገፋል፣ ጨቋኝና አምባገነናዊ ስርዓት ይወለዳል።

ጨቋኝ ስርዓት ወደ ስልጣን የሚመጣው የሀገሪቱ ምሁራን በፍርሃት አንደበታቸው ተለጉሞ የመንግስትን ስራና አሰራር መተቸት ሲቆሙ ወይም በጥቅም ሕሊናቸው ተለጉሞ የመንግስት ቃል-አቀባይ ሲሆኑ ነው። በተለይ ምሁራን ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ባሳዩት የወገንተኝነት ስሜት ልክ ለሌሎች ሀገራትና ሕዝቦች የጠላትነት ስሜት ያዳብራሉ።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ምሁራን የመንግስት ደጋፊ ሲሆኑ የፖለቲከኞቻቸውን ስራና ተግባር እየተከታተሉ ከመተቸት ይቆጠባሉ። ስለዚህ፣ ማህበራዊ ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ የመንግስት ቃል-አቀባይ ሆነው ያገለግላሉ። አምባገነናዊ መንግስት ደግሞ እነዚህን የጭቆና ፈረሶች እየጋለበ ሕዝብና ሀገርን ወደ ጦርነትና እልቂት ይወስዳል። ለዚህ ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ዓመታት በጀርመን እና የጃፓን የተፈጠረውን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

በአንደኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ አብዛኞቹ የምዕራብ አውሮፓ ምሁራን በብሔራዊ ስሜት እየተናጡ ነበር። የፈረንሳይ፥ እንግሊዝ፥ ቤልጂዬምና ዴኒማርክ የመሳሰሉ ሀገራት ምሁራን ለሀገራቸው ሕዝብ ከፍተኛ ወገንተኝነት፣ በዚያው ልክ ለጀርመን ሕዝብና መንግስት ደግሞ የጠላትነት ስሜት በስፋት ሲያንፀባርቁ ነበር። ነገር ግን፣ ምሁራኑ በብሔርተኝነት ስሜት ውስጥ ተዘፍቀው ስለነበረ የፖለቲከኞችን ስራና ተግባር መከታተልና መተቸት አቁመው ነበር። ይህ ደግሞ በጀርመን ለአዶልፍ ሂትለር ወደ ስልጣን መምጣትና ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ፣ “Albert Einstein” በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆታል፡- 

“The passions of nationalism have destroyed this community of the intellect, … The men of learning have become the chief mouthpieces of national tradition and lost their sense of an intellectual commonwealth. Nowadays we are faced with the curious fact that the politicians, the practical men of affairs, have become the exponents of international ideas. It is they who have created the League of Nations.” THE WORLD AS I SEE IT፡ Paradise Lost, Page 19

የአንደኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ሀገራት ምሁራን በብሔራዊ ስሜት ውስጥ ተዘፍቀው በነበረበት ወቅት የፖለቲካ መሪዎች በ“Treat of Versailles” አማካኝነት “League of Nations” የተባለውን ሕብረት መመስረታቸው ይታወቃል። ነገር ግን፣ ስምምነቱ ሲረቀቅ ጀርመን አንደ ባለድርሻ አካል አልተሳተፈችም። ነገር ግን፣ በስምምነቱ መሰረት፤ የተለያዩ የጀርመን ግዛቶችን ለፈረንሳይ፥ ቤልጅዬም፥ ዴኒማርክ፥ እና የመሳሰሉት ሀገራት እንዲሰጡ፣ ቅኝ-ግዛቶቿን ሙሉ-በሙሉ እንድትቀማ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት በራሷና በሌሎች ሀገራት ላይ ለደረሰው ኪሳራ ካሳ እንድትከፍል ይደነግጋል። በመጨረሻም ጀርመን ስምምነቱን በግድ እንድትቀበል ተደረገ።

የጀርመንን ግዛቶችን የተቀራመቱት እንደ ፈረንሳይና ቤልጂዬም ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ ግን የ“Treat of Versailles” የተባለውን የስምምነት ሰነድ ተቀብሎ አላፀደቀውም ነበር። ምክንያቱም፣ ስምምነቱ ከምሁራን እይታና አስተያየት ውጪ እንደመሆኑ በቀጣይ የሚስከትለውን ችግር ከግንዛቤ አላስገባም። ምሁራን በስምምነቱ መነሻ ምክንያትና የመጨረሻ ውጤት ዙሪያ ሃሳብና አስተያየት ሳይሰጡበት በግልብ ስሜታዊነት የተዘጋጀ ነበር። በመጨረሻም የአውሮፓን ሰላም ለማረጋገጥ የተፈረመ ስምምነት የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት አስከተለ።

ምሁራን በብሔራዊ ስሜት እና በመንግስት ቃል-አቀባይነት ተጠምደው በነበረበት ወቅት የተፈረመው ኢ-ፍትሃዊ ስምምነት በአዶልፍ ሂትለር መሪነት የናዚ ፋሽስት ወደ ስልጣን እንዲመጣ ምክንያት ሆነ። ፅንፈኛ አክራሪነትና ዘረኝነት እያቀነቀነ የመጣው ሂትለር በአውሮፓዊያን ላይ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት፣ በአይሁዶች ላይ ደግሞ የዘር-ማጥፋትን አስከተለ። በአጠቃላይ፣ ምሁራን ለራሳቸው ሕዝብ ከመጠን ያለፈ ወገንተኝነት፣ ለሌሎች ደግሞ የጠላትነት ስሜት በሚያንፀባርቁበት ወቅት ለራሱ ሕዝብ ጨቋኝ፣ ለሌሎች ሕዝቦች ደግሞ ጨፍጫፊ የሆነ ፋሽስታዊ ስርዓት ይፈጠራል።

በመሰረቱ፣ የጭቆና ስርዓት በሁለት መርሆች ላይ የተመሰረተ ነው። የመጀመሪያው መርህ “ሕዝብና መንግስት አንድ ናቸው። የቡድን መብት ከግለሰብ ነፃነት ይቀድማል። ስለዚህ፣ የግለሰብ ነፃነት ለቡድን/ሕዝብ/መንግስት ፍላጎት ተገዢ መሆን አለበት” የሚል ነው። ሁለተኛው የጨቋኞች መርህ ደግሞ “የእኛ ቡድን/ሕዝብ/መንግስት በሌሎች ተበድሏል እና/ወይም ከሌሎች የተሻለ መብትና ነፃነት ይገባናል” የሚል ነው።

በመጀመሪያው በሕዝብ ስም የግለሰብን ነፃነትን የሚገድብ – “ፀረ-ነፃነት” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በማንነት ወይም በታሪክ የሌሎችን እኩልነት የሚፃረር – “ፀረ-እኩልነት” ነው። ስለዚህ፣ ምሁራን የጨቋኞችን “ፀረ-ነፃነት” እና “ፀረ-እኩልነት” አመለካከቶች ገና በእንጭጩ ለመቅጨት መረባረብ አለባቸው። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- እንደ ጀርመናዊው ፈላስፋ “Nietzsche” አገላለፅ፣ “የኃላፊነት ስሜት ያለው ግለሰብ ብቻ ነው” (Only individuals have a sense of responsibility)። ስለዚህ፣ ቡድን፣ ብሔር፣ ወይም ሕዝብ በራሱ የኃላፊነት ስሜት አይሰማውም። የኃላፊነት ስሜት የሌለው አካል ደግሞ የራሱ የሆነ መብትና ነፃነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ ከቡድን መብት የግለሰብ ነፃነት መቅደም አለበት።

ሁለተኛ፣ ምሁራን የእነሱ ብሔር ወይም ሕዝብ በሌሎች ብሔሮች/ሕዝቦች/መንግስት ተበድሏል” እያሉ ከመዘርዘር ባለፈ በቀድሞ ስርዓት የተፈፀመውን በደልና ጭቆና ሁሉን-አቀፍ ማድረግ፣ በሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች ላይ ከደረሰው ጋር አያይዘው ማቅረብ አለባቸው። ነገር ግን፣ “ከዚህ ቀደም የእኛ ብሔር ወይም ሕዝብ በሌሎች ብሔሮች/ሕዝቦች/መንግስት ተበድሏል” ብቻ እያሉ ከሆነ፤ “በእኛ ላይ የተፈፀመው በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ መደገም አለበት” እንደ ማለት ይቆጠራል።

ምሁራን የመንግስት ቃል-አቀባይ ከመሆን አልፈው የገዢውን ቡድን የፖለቲካ ዘይቤን (Idelology) በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅ መንቀሳቀስ ከጀመሩ እንደ ወታደራዊ-ፋሽስት ስርዓት ይፈጠራል። የጃፓን ምሁራን አክራሪ ብሄርተኝነትና ዘረኝነት እያቀነቀኑ እ.አ.አ. በ1915 ዓ.ም የፈጠሩት ወታደራዊ ፋሽስት በስተመጨረሻ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የሞራል ኪሳራና አሰቃቂ እልቂት ዳርጓታል።

በጃፓን አክራሪ ብሄርተኝነትና ዘረኝነት መነሻ ምክንያቱ እ.አ.አ. በ1868 ዓ.ም ወደ መሪነት ከመጣው የ“Meiji dynasty” ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ዘውዳዊ አገዛዝ ከረጅም ግዜ በኋላ ጃፓንን ማስተዳደር እንደጀመረ የራሱን የፖለቲካ አይድዮሎጂ በሕዝቡ ውስጥ ማስረፅ ጀምረ። በዚህ ረገድ የጃፓን ምሁራን የነበራቸውን ሚና እና በስተመጨረሻ ያስከተለው የሞራል ቀውስ በተመለከተ “Edward Said” እንዲህ ገልፆታል፡-

 “The tennosei ideorogii (the emperor ideology) was the creation of intellectuals during the Meiji period, and while it was originally nurtured by a sense of national defensiveness, even inferiority, in 1915 it had become a fully fledged nationalism capable simultaneously of extreme militarism and a sort of nativism that subordinated the individual to the state. It also denigrated other races to such an extent as to permit the wilful slaughter of Chinese in the 1930s, for example, in the name of shido minzeku, the idea that the Japanese were the leading race. …After the war, most Japanese intellectuals were convinced that the essence of their new mission was not just the dismantling of tennosei (or corporate) ideology, but the construction of a liberal individualist subjectivity.” REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual፡ Lecture 2: Holding Nations and Traditions at Bay, 30 June 1993.   

ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እንደ ምዕራብ አውሮፓ ምሁራን በብሔራዊ ስሜት በመዋጥ የመንግስት ቃል-አቀባይ ሆነው ሲያገልግሉ እና በሌሎች ሕዝቦችና ሀገራት ላይ የደረሰውን በደልና ጭቆና ከግንዛቤ ሳያስገቡ በራሳቸው ሀገርና ህዝብ ላይ የተፈፀመን በደልና ጭቆና ብቻ መተረክና መዘከር፣ እንዲሁም እንደ ጃፓን ምሁራን የሰዎችን እኩልነትና ነፃነት የሚገደብ የፖለቲካ አይዲዮሎጂ መፍጠርና ማስረፅ በመጨረሻ ሀገርና ሕዝብ ለጦርነትና ለእልቂት ይዳርጋል።

የሰቆቃ ልጆች ክፍል-4፡ የመንግስት ደጋፊ ምሁራን “የጭቆና ፈረሶች” ናቸው! 

4.1 ምሁርና ብሔር

እንደ አይሁዶች ወይም የደቡብ አፍሪካ ነጮች የራሱን ሀገርና መንግስት ለመመስረት፣ እንደ አልጄሪያ ከቅኝ-አገዛዝ ነፃ ለመወጣት፣ ወይም ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ ወታደራዊ መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ውስጥ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት ምን መሆን አለበት? በእርግጥ የምሁራን ስራና ተግባር በብሔር፣ ዘር ወይም ሀገር ሊገደብ አይገባም። ነገር ግን፣ የመጡበት ማህብረሰብ በጨቋኝ ስርዓት ግፍና በደል ሲፈፀምበት ግን በዝምታ ማለፍ አይቻላቸውም።

እያንዳንዱ ምሁር ከተወለደበትና ካደገበት ማህብረሰብ ጋር ያለው ቁርኝት ከየትኛውም ሙያዊ ግዴታና ስነ-ምግባር የበለጠ ጠንካራ ነው። ስለዚህ፣ አንድ ምሁር በተወለደበት ማህብረሰብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን ወደ ጎን ትቶ ማለፍ አይቻልም። በአንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ምሁራን በሙያተኝነት (professionalism) ስም ገለልተኛ መሆንና በደልና ጭቆናን በዝምታ ማለፍ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። ከዚያ ይልቅ፣ ማህብረቡን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ባላቸው አቅምና ባገኙት አጋጣሚ አስተዋፅዖ ማበርከት አለባቸው።

ነገር ግን፣ ጨቋኙ ስርዓት ሲወገድና የሚደግፉት የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት ፍፁም መቀየር አለበት። ጨቋኝ ስርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ኃይል ስለ ቀድሞ ታሪኩ፣ አሁን ላይ ስላለው ሥራና አሰራር፣ ወይም ስለ ወደፊት አቅጣጫና ዕቅዱ ለመግለፅ አስፈላጊ የሆነ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት አሉት። ለዚህ ተግባር የተመደበ የሰው ኃይልና ካፒታል ይኖረዋል። ስለዚህ፣ ምሁራን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሥራና ተግባር እያጎሉ መናገርና መመስከር የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት አይደለም።

4.2 የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት

የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት በማህብረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አጉልቶ በማውጣት የግንዛቤና አመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መስራት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ምሁራን በሙያቸው ችግሮችን ቀድሞ የመለየትና መፍትሄያቸውን የመረዳት ብቃት አላቸው። እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ሙያዊ ትንታኔ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ነው።

እንኳን በጦርነት በሕዝብ ምርጫ ራሱ ወደ ስልጣን የመጡ የመንግስት ኃላፊዎችና የሕዝብ ተወካዮች ለሥራው የሚያስፈልገው በቂ ዕውቀትና ክህሎት የላቸውም። አብዛኛውን ግዜ የፖለቲካ ስልጣን የሚጨብጡ ሰዎች ሕዝብን የማደራጀትና የመቀስቀስ አቅም እንጂ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ስላላቸው አይደለም። “John Stuart Mill” ስለ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አመሰራረትና አሰራር በሚተነትነው መፅሃፉ “Of the Proper Functions of Representative Bodies” በሚለው ክፍል ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ ገልፆታል፡-

“….the very fact which most unfits such bodies for a Council of Legislation qualifies them the more for their other office- namely, that they are not a selection of the greatest political minds in the country, from whose opinions little could with certainty be inferred concerning those of the nation, but are, when properly constituted, a fair sample of every grade of intellect among the people which is at all entitled to a voice in public affairs. Their part is to indicate wants, to be an organ for popular demands, and a place of adverse discussion for all opinions relating to public matters, both great and small; and, along with this, to check by criticism, and eventually by withdrawing their support, those high public officers who really conduct the public business.”  Representative Government, Ch.5: Page  59

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊኖር የሚቻለው በፖለቲከኞች/የፖለቲካ ቡድኖች እና በምሁራን መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል ሲችል ነው። በመሰረቱ፣ የፖለቲከኞች መደበኛ ስራ ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር ነው። የምሁራን ድርሻ ደግሞ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የመንግስት ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል ነው።

ከዚህ አንፃር፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጓቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እና በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና የሚስተካከሉበትን አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ ነው። የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ከምሁራን የተሰጣቸውን ሃሳብና አስተያየት ተቀብለው በሀገሪቱና በሕዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚስተዋሉ ከፍተቶችን ለማስወገድ የፖለቲካ አመራር መስጠትና አስተዳደራዊ ስርዓቱን ማሻሻል ነው።

በዚህ መሰረት፣ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ከተወጡ በመንግስት ሥራዎችና አስራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ወዲያው ይስተካከላሉ። መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል። የመንግስት ስራና አሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነት ይኖረዋል። የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጡ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ይሆናል። ስለዚህ፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ይኖራል።

ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ለዘላቂ ልማት፣ ለአስተማማኝ ሰላም እና ለዳበረ ዴሞክራሲ መሰረት ይሆናል። ያለ ምሁራን ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ምሁራን ሕግ አውጪዎች የሚያፀድቋቸውን አዋጆች፣ የሕግ አስባሪዎች አሰራርና የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኝነትን፣ የሕግ አስፈፃሚዎች የሚያሳልፏቸውን የአፈፃፀም መመሪያዎችና ደንቦች፣ በአጠቃላይ የመንግስት አካላት ሥራና አሰራርን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ከሙያው አንፃር መተንተን፣ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦችን እያነሱ መወያየትና በኃላፊዎችና በሕብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም አለባቸው።

4.3 “የጭቆና ፈረሶች”

በእርግጥ ምሁራን እንደ ማንኛውም ዜጋ የመንግስት ባለስልጣን ሆነው መስራት ይችላሉ። ይህ ሲሆን እንደ ማንኛውም ባለስልጣን የመንግስትን ሥራና ተግባር ደግፈው ሃሳብና አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። የመንግስት ተሿሚ ወይም ባለስልጣን ካልሆኑ ግን የሕዝብን ድምፅ ተቀብለው ማስተጋባት አለባቸው። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ሰራተኛ ሆነ የግል ድርጅት ተቀጣሪ፣ እያንዳንዱ ምሁር ያለውን ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ በተለይ የመንግስትን ስራና አሰራር የመተቸት ማህበራዊ ግዴታ አለበት።

ከዚህ በተቃራኒ፣ መሰረታዊ ችግር ያለባቸው አዋጆች፥ እቅዶችና ውሳኔዎች በተለያዩ የመንግስት አካላት ተግባራዊ ሲደረጉ እያዩ በዝምታ የሚያልፉ ሰዎች እንደ ምሁር ያለባቸውን ማህበራዊ ግዴታ እየተወጡ አይደለም። በተለይ የሕዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን እያጣጣሉ፣ የመንግስትን ስራና ተግባር እያጋነኑ የሚያቀርቡ፣ ከመንግስት ኃላፊዎች በላይ የመንግስት ጠበቃና ደጋፊ ለመሆን የሚቃጣቸው ሰዎች “ምሁር” ለሚለው የክብር ስያሜ አይመጥኑም።  

ምሁራን በዜጎች ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት፣ እንዲሁም የመንግስት ስራና አሰራር ማሻሻል የሚችሉት፣ በአጠቃላይ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም እንዲረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉት ራሳቸውን ከመንግስት ሲነጥሉ ነው። ልክ እንደ የመንግስት ተሿሚ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ፣ ጥሩን እያጋነኑ፥ መጥፎውን እየሸፋፈኑ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰትን በማጣጣል የመንግስትን ጥሩ ምግባር አጉልተው ለማውጣት የሚጥሩ ከሆነ፣ ከሕዝብ ይልቅ በመንግስት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ የከፋ ነው። ምሁራን በደጋፊነት ስም ራሳቸውን ከመንግስት ጋር ማጣበቃቸው በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት “John Stuart Mill” እንዲህ ገልፆታል፡-   

“Nothing but the restriction of the function of representative bodies within these rational limits will enable the benefits of popular control to be enjoyed in conjunction with the no less important requisites of skilled legislation and administration. There are no means of combining these benefits except by separating the functions which guarantee the one from those which essentially require the other; by disjoining the office of control and criticism from the actual conduct of affairs, and devolving the former on the representatives of the Many, while securing for the latter, under strict responsibility to the nation, the acquired knowledge and practised intelligence of a specially trained and experienced Few.” Representative Government, Ch.5: P.59

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ምሁራን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሚያሳልፋቸው የብዙሃኑን እኩልነትና ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ እቅዶችና ውሳኔዎች እንዳይሻሻሉ፣ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዳይደረግባቸው፣ የሕዝብ ጥየቄዎችና ቅሬታዎችን እንዳይሰማ፣ እንዲሁም የመንግስት ኃላፊዎች ያለባቸውን የግንዛቤ እና የብቃት ማነስ ችግር እንዳይቀርፉ እንቅፋት ናቸው።

ምሁራን የመንግስትን እርምጃዎችን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ሙያተኝነት ስም ገለልተኛ መስለው ለማለፍ መሞከራቸው በራሱ በህዝብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን እንደመደገፍ ይቆጠራል። ስለዚህ፣ በገለልተኝነት (neutrality) ስም መንግስትን ከመተቸት የሚቆጠቡ ምሁራን “የመንግስት ደጋፊ ነን” ከሚሉት በምንም የተለዩ አይደሉም።

እንደ ምሁር ከማህብረሰቡ የተጣለባቸውን ግዴታና ኃላፊነት አልተወጡም። በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማንሳት የግንዛቤና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያስከትሉትን ጭቅጭቅና ውዝግብ በመፍራት ማህበራዊ ግዴታቸውን የማይወጡ፣ “ፖለቲካ እሳት ነው!” የሚለውን ያረጀ አባባል እየደጋገሙ ጥግጥጉን የሚሄዱ ሰዎች ትክክለኛ መጠሪያቸው “ምሁራን” ሳይሆን “ፈሪዎች” የሚለው ነው።

በአጠቃላይ፣ “ምሁር” ለመባል በቅድሚያ እንደ ምሁር የተጣለብንን ማህበራዊ ግዴታ መወጣት ያስፈልጋል። ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈራ ወይም መንግስትን ለማሞገስ የሚተጋ ሰው “ምሁር” ለሚለው የከብር መጠሪያ አይመጥንም። ከዚያ ይልቅ፣ የመንግስት ደጋፊዎች ሕሊናቸው በጥቅም ሱስ ተለጉሞ፣ እንዲሁም መንግስትን ለመተቸት የሚፈሩት ደግሞ አንደበታቸው በፍርሃት ቆፈን ተለጉሞ፣ ጭቋኝ ስርዓትን በጀርባቸው ተሸክመው የሚጋልቡ “ፈረሶች” ናቸው። ወታዳራዊ ፋሽስቶች፣ አምባገነኖች፣ የአፓርታይድ ስርዓት አራማጆች፣ …ወዘተ በሕዝብ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ የሚፈፅሙት እነዚህን “የጭቆና ፈረሶች” እያጋለቡ ነው።

የሰቆቃ ልጆች ክፍል-3፡-“ጭቁኖች ለምን ጨቋኝ ይሆናሉ?”

ኤድዋርድ ሰይድ (Edward Said) የተባለው ምሁር፣ የደቡብ አፍሪካ ነጮች ትላንት የሆነውን፣ ዛሬ እየሆነ ያለውንና ነገ የሚሆነውን፣ እያንዳንዱ ታሪካዊ ክስተት የራሱ የሆነ አሳማኝ ምክንያት አለው። ከቦታ፣ ግዜና ምክንያት አንፃር ድርጊቱ ስለተፈፀመበት ሁኔታ ይበልጥ ባወቅን ቁጥር ድርጊቱን ከመፈፀም በቀር ሌላ ምርጫና አማራጭ እንዳልነበረ እንረዳለን። ለምሳሌ፣ እንደ አይሁዶች ከናዚ ጭፍጨፋ የምትሸሽበት ሀገር፥ የሚሸሽግ መንግስት ከሌለህ ከአይሁዶች አፓርታይድ መስራች “ከዴቪድ ቤንጉሪዮ” (David Ben-Gurion) የባሰ አክራሪ አይሁድ ልትሆን ትችላለህ። ወይም ደግሞ እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጮች በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከጠቅላላ ሕዝቡ 10% በበሽታና ርሃብ ሲሞት ከደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ መስራች “ከዳኒኤል ፍራንኮይስ ማለን” (Daniel Francois Malan) የባሰ አክራሪ ነጭ ልትሆን ትችላለህ።

በመሰረቱ ሕልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ (Survival) በሞራል ሆነ በሕግ አግባብ አይዳኝም (Necessity has no law)። ምክንያቱም፣ ከሕግ ወይም ሞራል አንፃር የሚያስከትለው ቅጣት ሕልውናን ከማጣት በላይ አያስፈራም። በዚህ መሰረት፣ በናዚዎችና እንግሊዞች የሕዝባቸው ሕልውና አደጋ ላይ ወድቆ ስለነበር በወቅቱ የተወሰዱ እርምጃዎችን “ትክክል” ወይም ስህተት” ብሎ መፈረጅ አይቻልም። በሁለቱም ሕዝቦች ላይ የተጋረጠው የሕልውና አደጋ ከተወገደ፤ በጀርመን የነበረው የናዚ ፋሽታዊ ስርዓት ከተወገደ እና ደቡብ አፍሪካ ከእንግሊዝ ቀኝ አገዛዝ ስርዓት ነፃ ከወጣች በኋላ ግን ለመሰረታዊ የሕግና ሞራል መርሆች ተገዢ መሆን የግድ ነው።

በዚህ መሰረት፣ በራስ ላይ የተፈፀመን ግፍና በሌሎች ላይ መልሶ መፈፀም ፍፁም “ስህተት” ነው። ምክንያቱም፤ ከሞራል አንፃር – በራስህ ላይ እንዲሆን የማትሻውን ነገር በሌሎች ላይ ማድረግ አግባብ ስላልሆነ፣ ከሕግ አንፃር – ለአንዱ ጥፋት ሌላን ተጠያቂ ማድረግ ስህተት ስለሆነ፣ እንዲሁም ከፖለቲካ አንፃር – የሌሎች ሰቆቃ ለራስ ሰቀቀን ስለሆነ (በሌሎች ላይ የምንፈፅመው ግፍና በደል የእኛን ሕይወትና እንቅስቃሴ በስጋትና ፍርሃት የተሞላ ያደርገዋል)። ስለዚህ፣ በወገንህ፥ ሕዝብህና ሀገርህ ላይ ሲፈፀም በፅናት የታገልከውን ጭቆና መልሶ በሌሎች ላይ መፈፀም ከሞራል፣ ሕግ ወይም ከፖሊቲካ አይታ አንፃር ተቀባይነት የለውም። 

ለምሳሌ፣ እንግሊዞች ግፍና ጭፍጨፋ የፈፀሙት በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ ብቻ አልነበረም። እንግሊዞች በጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ላይ ተመሣሣይ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። ከ1889 – 1902 ዓ.ም (እ.አ.አ.) በተደረገው ጦርነት እንግሊዞች የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ 28000 ነጮች ሲሞቱ በተመሳሳይ ከ15000 በላይ ጥቁሮች ለሞት ተዳርገዋል። ስለዚህ፣ እንግሊዞች በነጮችና ጥቁሮች ላይ እኩል ግፍና በደል ተፈፅሟል። ነገር ግን፣ እንግሊዝ በ1948 ዓ.ም ከደቡብ አፍሪካ ለቃ ስትወጣ ነጮቹ ተመሳሳይ ግፍና በደል በጥቁሮች ላይ መፈፀም ጀመሩ። ታዲያ በአንድ ጨቋኝ ስርዓት ስር አብረው ሲጨቆኑ የነበሩ ሁለት ሕዝቦች ከነፃነት በኋላ አንዱ ሌላውን የሚጨቁንበት ምክንያት ምንድነው?

እንደ ኤድዋርድ ሰይድ በደቡብ አፍሪካ የእንግሊዝን ቅኝ-አገዛዝ፣ በአልጄሪያ የፈረንሳይን፣ በቦስኒያ ወይም የፍልስጤም የነፃነት ትግል ውስጥ፣ በአጠቃላይ ለነፃነትና እኩልነት በሚደረግ ፍልሚያ መሃል “የትግላችን የመጨረሻ ግብ ምንድነው?” ብሎ መጠይቅ ያስፈልጋል። ለሕዝብ እኩልነትና ነፃነት የሚደረግ የሚደረግ ትግል ዋና ግቡ ጨቋኝ ስርዓትን ከስልጣን ማስወገድ ሳይሆን አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር (Invention of new souls) ነው። ከጨቋኝ ስርዓት ጋር ለሚደረገው ትግል አስፈላጊ የነበረው የወገንተኝነትና ጠላትነት ስሜት ከድል በኋላ በአዲስ ነፍስ – በእኩልነትና ነፃነት – መተካት ያስፈልጋል።

በትግል ወቅት ለሚታገሉለት ሀገርና ሕዝብ ልዩ ፍቅርና ወገንተኝነት፣ ለሚወጉት ጠላት ደግሞ ልዩ ጥላቻና ንቀት መፈጠሩ የማይቀር ነው። ምክንያቱም፣ ጨቋኝ ስርዓትን በጦርነት ለማስወገድ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ወይም ሀገር ወገንተኝነት፣ ለጭቆናና ጨቋኞች ደግሞ የጠላትነት ስሜት ማስረፅ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፣ ይህ የወገንተኝነት እና ጠላትነት ስሜት የሚያገለግለው በጦርነት ወቅት ብቻ ነው። ጨቋኙ ስርዓት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ግን ፋይዳ-ቢስ ነው። ምክንያቱም፣ የትግሉ ዋና ዓላማ ጨቋኙን ስርዓት ማስወገድ ሳይሆን እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትህ የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ስርዓት መገንባት ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ መሪዎች ገና በትግል ላይ ሳሉ ጨቋኝ ስርዓትን ካስወገዱ በኋላ ስለሚሰሩት ስራ ማሰብ፣ መናገር፣ መከራከርና ማስተማር አለባቸው። በዚህ መሰረት ጨቋኙ ስርዓት ከተወገደ በኋላ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዴት መገንባት እንደሚቻል ግልፅ ግንዛቤና የተግባር እቅድ ሊኖራቸው ይገባል።

በአጠቃላይ፣ ከጨቋኝ ስርዓት ነፃ ለመውጣት በሚደረገው ትግል አስፈላጊ የሆነው የህዝብ ወገንተኝነትና የጭቆና ጠላትነት በእኩልነትና ነፃነት መቀየር አለባቸው። ከዚህ ቀደም በተለያየ ደረጃ የተጨቀኑ፣ በደልና ጭቆና ያልደረሰባቸው ወይም ደግሞ የጨቋኙ ስርዓት ደጋፊዎች፣ …ወዘተ የሁሉም መብትና ነፃነት የሚከበርበት ስርዓት መዘርጋትና ይህንንም ከግዜ ወደ ግዜ እያሻሻሉ መሄድ ይጠይቃል። በትግል ወቅት የሰረፀው የወገንተኝነትና ጠላትነት መንፈስ ከትግሉ በኋላ በእኩልነትና ነፃነት መቀየር ካልተቻለ ግን ጨቋኙ ስርዓት በተወገደ ማግስት የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት መከሰቱ አይቀርም። ምክንያቱም፣ በትግል ወቅት የሰረፀው የህዝባዊ ወገንተኝነት በሂደት ወደ ፅንፈኛ አክራሪነት ወይም ብሔርተኝነት ይቀየራል።

ቀድሞ ጨቋኙን ስርዓት ለመታገል የሰረፀው የጠላትነት መንፈስ ከትግሉ በኋላ ሌላ ጠላት ይሻል። ይህ የጠላትነት መንፈስ እስካልተቀየረ ድረስ የግድ ጠላት ያስፈልገዋል። ስለዚህ፣ ጨቋኙ ስርዓት ከተወገደ በኋላም በቀድሞ ስርዓት በከፊል የተጨቆኑ፣ ያልተጨቆኑ ወይም ደጋፊ የነበሩትን የሕብረተሰብ ክፍሎች በጠላትነት መፈረጅ ይጀምራል። የጨቋኙ ስርዓት የፈጠረውን ቁስል እያከከ የሚውል የፖለቲካ ቡድን የሚንቀሳቀሰው ትላንት የተፈፀመበትን በደልና ጭቆና እያሰበ፣ የቀድሞ ስርዓት ደጋፊዎችን (ርዝራዦች) እየጠላና ወደፊት ስርዓቱ ተመልሶ ይመጣል በሚል ስጋትና ፍርሃት ነው። ይሄ ደግሞ በሌሎች ላይ እያደረሰ ያለውን በደልና ጭቆና እንዳይገነዘብ ይጋርደዋል።   ለምሳሌ፣ አዶልፍ ሂትለር በ1ኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ጀርመን ከደረሰባት አሳፋረ ሽንፈትና ውርድት ለማንሳት የነደፈው በፅንፈኝነትና ዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ፕሮፓጋንዳ በሂደት ከናዚዎች ቁጥጥር ውጪ ሆነ። ይህ በአይሁዶች ላይ የዘር-ማጥፋት ጭፍጨፋ እና ለ2ኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት ሆኗል። 

አይሁዶች የተፈፀመባቸውን በደልና ጭፍጨፋ ተከትሎ የራሳቸውን ሀገርና መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ ለመመስረት ከተለያዩ የአረብ ሀገሮች ጋር ጦርነት አካሄዱ። እነዚህን ጦርነቶች በድል ለማጠናቀቅ የአይሁዶች ወገንተኝነት እና ለአረቦች የጠላትነት ስሜት ማስረፅ ይጠበቅባቸው ነበር። በጦርነት ወቅት የዳበረ የአይሁዶች የወገንተኝነትና ጠላትነት ስሜት ዛሬ ላይ ለሚታየው የአይሁዶች አክራሪነት እና የጠላትነት መንፈስ በእስራኤል ለተዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት ዋና መሰረት ነው። በናዚዎች ከተፈፀመባቸው ግፍና ጭፍጨፋ የተረፉ የሰቆቃ ልጆች በፍለስጤሞች ላይ ግፍና ጭፍጨፋ የሚፈፅሙበት ይህ የአክራሪነትና ጠላትነት ስሜት ነው። የእስራኤል መንግስት በዌስት ባንክ የሚካሄደውን ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ ለማስቆም ያደረገው ጥረትና ከአክራሪ የአይሁዶች የገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ሊጠቀስ ይችላል። በሀገር ምስረታ ወይም በጦርነት ወቅት የተፈጠረ የወገንተኝነትና የጠላትነት ስሜት በሂደት ወደ ብሔርተኝነት እና ፅነፈኝነት ሊቀየር እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው።

ልላው ከ27000 የማይበልጥ ተዋጊዎች የነበሯቸው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች 500000 ወታደሮች ያሰለፈውን የእንግሊዝ ጦር በውጊያ ለመግጠም በራሱ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ወገንተኝነትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከሚታገሉለት ሕዝብ ውስጥ 10% በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በበሽታና በርሃብ ሲያልቅ የሚፈጥረውን ቁጭትና የጠላትነት ስሜት መገመት ይቻላል። ነገር ግን፣ ይህን በጦርነት ወቅት የተፈጠረን አሮጌ-ስሜት ሳይቀይሩ ሀገርን ማስተዳደር አይቻልም። ምንያቱም ስለ ቀድሞ ስርዓት በደልና ጭቆና ብቻ የሚስብ የፖለቲካ ቡድን ነባራዊ እውነታን በቅጡ መገንዘብ ይሳነዋል። የደቡብ አፍሪካ ነጮች ከእነሱ ጋር እኩል በደልና ጭቆነና ሲደርስባቸወው የነበሩትነን ጥቁሮች በአፓርታይድ ስርዓት መልሰው መጨቆን የጀመሩት በዚህ ምክንያት ነው።

የናዚ ጭፍጨፋ የወለዳቸው የእስራኤል “የሰቆቃ ልጆች” በፍልስጤማዊያን ላይ የፈፅሙት በደልና ጭቆና በተራው ሽብርተኝነትን ወለደ። የአል-ቃይዳ የሽብር ጥቃት ዓለም አቀፉን የፀረ-ሽብር ጦርነት አስከተለ። የኢራቅና አፍጋኒስታን ወረራ እንደ “ISIS” ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን ወለደ። በአጠቃላይ፣ ዛሬ ላይ እንደ አሸን ለፈሉት አሸባሪ ድርጅቶች መነሻ ምክንያታቸው በእስራኤል ያለው የአይሁዶች አፓርታይድ ስርዓት ነው። ታላቁ ምሁር አልበርት አንስታይን (Albert Einstein) ፍልስጤምን መልሶ መገንባት የአይሁድ ሕዝቦችን ሕልውና የማረጋገጥ ጉዳይ እንደሆነ ገልፆ ነበር፡-

“Anything we may do for the common purpose is done not merely for our brothers in Palestine, but for the well-being and honour of the whole Jewish people.”  THE WORLD AS I SEE IT፡ Addresses on Reconstruction in Palestine, Part I, Page 65.

ጨቋኞች በራሳቸው የተፈፀመን አሰቃቂ በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ የሚደግሙት፣ በዚህም ራሳቸውን ከሰቆቃ አዙሪት ማውጣት የሚሳናቸው ነገሮችን ከአንድ ማዕዘን ብቻ ስለሚመለከቱ ነው። የእነዚህ ወገኖች የፖለቲካ አመለካከት በዋናነት ቀድሞ ከተፈፀመባቸው በደልና ጭቆና አንፃር ብቻ የተቃኘ ነው። ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው የሚመራው፣ የወደፊት አቅጣጫቸውን የሚወስኑት “የቀድሞው ጨቋኝ ስርዓት ተመልሶ ይመጣል” በሚል በስጋት ውስጥ ሆነው ነው። እንዲህ ባለ ስጋትና ፍርሃት የሚያደርጉት ነገር የሌሎችን መብትና ነፃነት ይገድባል። በእነሱ ላይ የደረሰው በደልና ጭቆና ተመልሶ እንዳይመጣ ሲታትሩ በሌሎች ላይ ተመሳሳይ በደልና ጭቆና ይፈፅማሉ። ስላለፈው ሲፈሩ የወደፊት ተስፋን ያጨልማሉ። ይህ በተራው ቂምና ጥላቻ እየተጠራቀመ ሄዶ በመጨረሻ ሌላ ጨቋኝ ስርዓትን ይወልዳል።