የሃሳብ ነፃነት እና የአስተሳሰብ ባርነት 

አንዳንድ ወዳጆቼ በESAT ሲጠብቁኝ በOBN መምጣቴ አልተዋጠላቸውም። የኦሮሞና አማራ ሕዝብን፤ “ማን አስታራቂ አደረገህ?”፣ “ለምን 2/3ኛ አልክ?”፣ “የኦህዴድ/ኢህአዴግ ደጋፊ ሆንክ?”፣ “ጠቃሚ ደደብ ነህ?” እና የመሳሰሉት ሲሉ አያለሁ። “ጉድጓድ ውስጥ ያለች አይጥ የሰማዩ ስፋት ካለችበት ከጉድጓዱ አፍ ስፋት የሚበልጥ አይመስላትም” እንደሚባለው ሁሉ “በጎሳ ፖለቲካ” ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች ሁሉንም ነገር በብሔር ምንፅር ነው የሚመለከቱት። 

Photo credit: Milkeessaa Midhagaa (Dr.)

የፖለቲካ አቋምና አመለካከታቸው በብሔር ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም አንድን ነገር ሲደግፉ ሆነ ሲቃወሙ በብሔር ነው! ሃሳብና አስተያየት ሲሰጡ በብሔር ነው! የሌሎችን አቋምና አመለካከት ሲተቹ በብሔር ነው። እንደ ብሔር ካልሆነ እንደ ሰው በራሳቸው ማሰብ ሆነ መናገር አይችሉም። 
ከብሔርተኝነት ባለፈ ሰብዓዊነት የሚባል ነገር አለ። እንደ ሰው ስታስብ፣ ሁሉም ሰዎች ልክ እንደ አንተ የተሻለ ነፃነትና ተጠቃሚነት እንደሚሹ ትረዳለህ። ይህን ስትረዳ “ሁሉም ሰው በሰውነቱ እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባዋል” የሚል እምነት ይኖርሃል። የፖለቲካ አቋምና አመለካከትህ ከዚህ አንፃር የተቃኘ ይሆናል። ከአባይ ማዶ፥ ከተከዜ በላይ፥ ከአዋሽ በታች፥ ከኦሞ ግርጌ፣ … በየትኛውም አከባቢ ይስፈር፣ ሁሉም ሕዝብ እንደ ሕዝብ የተሻለ ልማት፥ ሰላምና ዴሞክራሲ ይገባዋል። ኦሮሞ፥ አማራ፥ ጉራጌ፥ ትግሬ፥ ሶማሌ፥ ወላይታ፥ ከንባታ፥…. ሁሉም ትላንት ላይ የጋራ የሆነ አኩሪና አሳፋሪ ታሪክ አላቸው፣ ዛሬ ላይ በአንድ ሀገርና ስርዓት ስር ናቸው፣ ነገ ላይ የጋራ ተስፋና ስጋት አላቸው። 

ስለዚህ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤ ስለ ቀድሞ ታሪካቸው፣ ስለ ዛሬው ሁኔታ እና ስለ ነገ ተስፋና ስጋታቸው እርስ በእርስ መነጋገር አለባቸው። ባለመነጋገር የአለመተማመንና ጥርጣሬ ይሰፍናል። በመነጋገር መተማመንና መግባባት ይሰፍናል። በዚህ መሰረት፣ በመግባባትና ትብብር ላይ የተመሰረተ አንድነት ይኖራል። 

በሕወሃት መሪነት የተዘረጋውና ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በተግባር ላይ የቆየው ፖለቲካዊ ስርዓት፤ ከቀድሞ ታሪክ ጥሩውን እያጣጣለ፥ መጥፎውን እያጋነነ፣ በውሸት ፕሮፓጋንዳ ትላንትን ሲዖል፣ ዛሬን ገነት አስመስሎ እውነትን እንደ ምፅዓት ሩቅ አደረጋት። በእውን የኖርነውን በውሸት ሊያሳምነን ይጥራል፡፡ በተግባር የምናቀውን እውነት በቴሌቪዥን ይዋሸናል፡፡ በዚህ መሃል “#OBN እስኪ በተግባር የምታቀውን፣ ሰሞኑን የታዘብከውን ነገረን?” ሲለኝ መልሴ “እሺ” ነው፡፡ 

ባለፈው አመት በዚህ ሰዓት ጦላይ ነበርኩ፡፡ አምና ሃሳቤን በነፃነት ስለገለፅኩ አሰረኝ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ሃሳብህን በነፃነት ለOBN ስጠን ብሎ ጠየቀኝ፡፡ አምና ፀረ-ሰላም ነበርኩ፣ ዘንድሮ ሰላማዊ ሆንኩ፡፡ ይሄ ልዩነት ከየት መጣ? ከእኔ አይደለም! ከኦህዴድ ነው! አምና የፃፍኩት “የዜጎች መብት፥ ነፃነትና እኩልነት ይከበር!” እያልኩ ነበር፡፡  ዘንድሮ “OBN”  ላይ የተናገርኩት ስለ ዜጎች መብት፥ ነፃነትና እኩልነት ነው፡፡ የእኔ አቋም አንድ ነው፦ “ሁሉም ሰው እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባዋል” የሚል ነው፡፡

እኔ የምናገረው ስለ ኢትዮጲያ ህዝብ መብትና ነፃነት እንጂ ስለ አንድ ብሔር ጥቅምና ተጠቃሚነት አይደለም፡፡ የህዝብ ደጋፊ እንጂ የአንድ ፓርቲ ወይም መንግስት አገልጋይ አይደለሁም፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለተቀበለ ሁሉ ደጋፊ ነኝ፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለገፋ ሁሉ ተቃዋሚ ነኝ፡፡ ህዝብን በሃይል ለማፈን የሚታትርን ደግሞ ውድቀቱ እንዲፋጠን ሃሳብ አዋጣለሁ፡፡ እኔ የምደግፈው አንድ ነው፦ እሱም የኢትዮጲያ ህዝብ ነው! ነገር ግን፣ በጎሳ ፖለቲካ እሳቤ ከአንዱ ጎጥ ስር ለተወሸቀ ሰው ይሄ አንዱን ብሔር ደግፎ ሌላውን “መጥላት” ነው፡፡ ጫን ሲል ደግሞ “የአንድ ፓርቲ አገልጋይነት ነው” ይለሃል፡፡ እኔ የማገለግለው ህዝብ እንጂ አንድ የፖለቲካ ቡድን አይደለም! 

እንደ ሰው ለሚያስብ፣ ህዝብ ለሚያከብር ሰው ይህ ፖለቲካ ሳይሆን የሞራል ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ ራሱን ከእንዲህ ያለ የአስተሳሰብ ባርነት ነፃ ሳያወጣ የእኔን የሃሳብ ነፃነት ከብሔርተኝነትና አገልጋይነት ጋር ለማያያዝ መሞከር ከጉድጓድ ውስጥ እንዳለችው አይጥ ራስን ማስገመት ነው! 

Advertisements

አፈትልኮ የወጣ መረጃ፦ “ስዩም ተሾመን ጨምሮ ሁለት ፀሃፊዎችን ለመግደል ታቅዷል!”

ይህ “ከከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች አፈትልኮ ወጣ” የተባለው መረጃ ለመጀመሪያ ግዜ የደረሰኝ ባለፈው ሳምንት ሲሆን የስልክ ቃለ ምልልስ ይህን ማያያዣ (Link) በመጫን ማዳመጥ ይቻላል። በተደጋጋሚ እንዲህ ያለ የማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ስለሚደርሰኝ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም። ባለፈው ሳምንት መረጃውን ያደረሰኝ ግለሰብ ትላንትም በድጋሜ ከአሜሪካ በቀጥታ የስልክ መስመር ደውሎ ስለሁኔታው በዝርዝር ገለፆልኛል። ከግለሰቡ ጋር ያደረኩትን የስልክ ቃለ ምልልስ ቀድቼዋለሁ። ሁለተኛውን የስልክ ቃለ ምልልስ ይህን ማያያዣ (Link) በመጫን ማዳመጥ ይቻላል፡፡ 

ከላይ የቀረቡት የስልክ ቃለ ምልልሶች የድምፅ ጥራታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ የቃለ ምልልሱን ዋና ሃሳብ እንደሚከተለው በአጭሩ እገልፃለሁ። ከላይ የተጠቀሰው ግለሰብ ከከፍተኛ የደህንነት ኃላፊዎች እና የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጋር ቅርበት እንዳለው ይናገራል። ለምሳሌ፣ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ሬድዋን ሁሴን እና ከከፍተኛ የደህንነት ሃላፊዎች ጋር በአካል ተገናኝቶ እንደሚወያይ ገልጿል፡፡ ይህ ውስጥ አዋቂ እንደሚለው፣ በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካ ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ፣ እኔን ጨምሮ በሦስት ፀሃፊዎች ላይ “መወገድ አለባቸው” የሚል ትዕዛዝ መተላለፉን ገልጿል። ከላይ ከተጠቀሰው ግለሰብ በተጨማሪ፣ ለደህንነት ሰዎች ቅርበት ያላቸው ሌሎች ጓደኞቼ “ስዩም ተሾመ መወገድ አለበት” የሚለው ውሳኔ መተላለፉን እንደሰሙ በመጠቆም ስጋታቸውን ገልፀውልኛል።

ይህን ከመስማቴ በፊት፣ ትላንት ጠዋት ብዙ የፌስቡክ ጏደኞቼ ከአሉላ_ሰለሞን ገፅ ላይ የተወሰደ ምስል ልከውልኝ ነበር። ከታች እንደሚታየው አቶ አሉላ ሰለሞን እኔ እንድታሰር በይፋ ጥሪ አቅርቧል። ውስጥ አዋቂው “ከአሉላ ሰለሞን ጋር እንዴት ስዩም ተሾመ ይወገድ ትላለህ” ብሎ ለረጅም ሰዓት እንደተከራከረው በመግለፅ ከፅሁፉ በስተጀርባ ያለውን እውነታ፣ በተለይ የአቶ አሉላ ሰለሞን የፖለቲካ አቋም በግልፅ ያሳያል፡፡ በዚህ መሠረት፣ አቶ አሉላ ሰለሞን እንደ እኔ የተለየ አቋምና አመለካከት የሚያራምዱ ግለሰቦችን ያለምንም ጥፋትና ማስረጃ እንዲታሰሩ በይፋ ጥሪ ከማቅረብ ጀምሮ ያለፍርድ “መገደል አለባቸው” ብሎ እንደሚከራከር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ህግ በሰፈነበት አሜሪካን ሀገር ተቀምጦ በኢትዮጲያኖች ላይ የሽብር ወንጀል እንዲፈፀም ጥሪና ቅስቀሳ እያደረገ እንደመሆኑ በህግ ሊጠየቅ ይገባል፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካ ሁኔታ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቀው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ሚልኬሳ_ሚደጋ አዲስ አበባ ቦሌ ማተሚያ ቤት አከባቢ ዛሬ ጠዋት ጥቃት እንደተፈፀመበት ተገልጿል። 

በዶ/ር ሚልኬሳ ላይ የተቃጣው ጥቃት ከላይ ከተጠቀሰው መረጃ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከውስጥ አዋቂው ጋር ያደረኩትን የስልክ ቃለ ምልልስን በYouTube እንደሚከተለው አቀናብሬ አውጥቼዋለሁ። 

​የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል!

በሕገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓት በምትመራ ሀገር፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፤ ህወሓት፥ ብአዴን፥ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ጥምረት የሚመራ ሆኖ ሳለ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ህወሓትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አድሏዊነት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ ይሄ እውነታ እንጆ አድሏዊነት አይደለም። ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ የፌደራል ስርዓቱና ተቋማት፣ እንዲሁም የክልል መንግስታትና ተቋማት የሚተዳደሩበት ሕግ፥ ስርዓትና መዋቅር በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። 
የፖለቲካ ጨዋታውን ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይጫወታሉ። የጨዋታውን ሕግ በማፅደቁ ሂደት ሁሉም ተሳታፊዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ ሕጉ የተረቀቀበት ፅንሰ-ሃሳብ የህወሓት ነው። ይህ የጨዋታ ሕግ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ሲሆን የሕገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ደግሞ በህወሓት የብሔር ፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በመሆኑም የፌደራሉ መንግስትና ተቋማት ይህን የፖለቲካ መርህና አመለካከት ተግባራዊ ለማድርግ የተቋቋሙ ናቸው። 

የሕጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ፣ በሁሉም ደረጃ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች ለሕገ መንግስቱ ተገዢ መሆን አለባቸው። ነገር ግን፣ የሕገ መንግስቱ ትርጉምና ፋይዳ በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ፣ ለሕገ መንግስቱና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ተገዢ መሆን ለህወሓት ተገዢ ከመሆን ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው።

በአጠቃላይ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ከተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ህወሓት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ምክንያቶች፤ አንደኛ፡- መንግስታዊ ስርዓቱ በህወሓት የፖለቲካ መርህና መመሪያ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ሁለተኛ፡- ይህ የፖለቲካ መርህና አመለካከት ፍፁም ስህተት ስለሆነ፣ ሦስተኛ፡- የሥልጣን የበላይነቱን ለማስቀጠል እጅግ አደገኛ የሆነ ሸርና አሻጥር እየፈፀመ ስለሆነ። እነዚህን ችግሮች አንድ ላይ አያይዤ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።  

የዳግማዊ ወያነ ወይም የሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የትግራይ ህዝብን የለውጥ ፍላጎት የብሔርተኝነት ስሜት በመቆስቆስ እና በራስ የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የቀድሞ የህወሓት (TPLF) መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመርና የንቅናቄ ስልት “…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one” በማለት ገልፀውታል። 

ነገር ግን፣ ከህወሃት ብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ያነሰ ክብርና ዋጋ በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። የትጥቅ ትግሉን ለማስጀመር በትግራይ ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃን ስነ-ልቦና ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የአክራሪ ብሔርተኝነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ የተበዳይነትና ወገንተኝነት ስሜት ፈጥሯል። ከደርግ ጋር በተካሄደው ጦርነት የተፈጠረው ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ ፍርሃትና ጥርጣሬ ተቀይሯል። 

የዘውግ ብሔርተኝነት እና በራስ የመወሰን መብት ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር (mobilization) ተጠቅሞ ወደ ስልጣን የፖለቲካ ቡድን የተበዳይነትና ጠላትነት አመለካከት ያለው፣ ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት የሚመለከት ይሆናል። በሕወሃት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ያረፉበት ነው። 

በመጀመሪያ ደረጃ ሕወሃት ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክልና በጦርነት ወቅት በተፈጠረ ከፍተኛ የተበዳይነት፥ ጠላትነትና ፍርሃት አመለካከት የሚመራ ድርጅት እንደመሆኑ በድርጅቱ መሪነትና የፖለቲካ መርህ ላይ ተመስርቶ የተዘረጋው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የሕወሃትን የስልጣን የበላይነት የማስቀጠል ዓላማ ያለው ነው። 

ሁለተኛ እንደ ሕወሃት ያለ የፖለቲካ ቡድን ሌሎች አብላጫ ድምፅ ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይጀምሩ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም አብላጫ ድምፅ ያላቸው ማህብረሰቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ ማድረግ ከቻሉ የአነስተኛ ብሔር የስልጣን የበላይነትንና ተጠቃሚነትን በቀላሉ ያስወግዱታል። ስለዚህ አብላጭ ድምፅ ያላቸውን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጎሳ፥ ብሔርና ቋንቋ በመከፋፈል የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ እና የተቀናጀ ንቅናቄ እንዳይኖራቸው ማድረግ አለበት።

እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን የቆመለትን የአንድ ወገን የስልጣን የበላይነትን ሊያሳጣው የሚችል ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ለውጥና መሻሻል፣ ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ ለማስተነገድ ዝግጁ አይደለም። በተለይ ደግሞ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሃሳብና ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም። በዚህ ምክንያት፣ ላለፉት 25 ዓመታት ሕወሃት/ኢህአዴግ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሳውን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት ለማፈን ጥረት አድርጓል። 

በመሰረቱ ሕወሃት የስልጣን የበላይነቱ በሕገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በዚያ ረገድ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል ለማድረግ ዝግጁ አይደለም። በመሆኑም እያንዳንዱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ጥርጣሬ ይመለከታል። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት በማዳፈን ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እና የፖለቲካ ልሂቃን መንግስትን እንዲፈሩ፣ በዚህም የስርዓቱን ሕልውና ለማስቀጠል ጥረት ያደርጋል። 

በእርግጥ ፍርሃት (fear) የሕወሃት መርህና መመሪያ ነው። ሆኖም ግን፣ በየትኛውም ግዜ፥ ቦታና ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፖለቲካዊ ጥያቄ እኩልነት (equality) ነው። የሁሉም መብትና ነፃነት እስካልተከበረ ድርስ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄን ከማንሳት ወደኋላ አይሉም። እንደ ሕወሃት ያሉ ጨቋኞችም የመብትና ነፃነት ጥየቄ ባነሳው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ጥያቄው ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ፣ ሕወሃት ከሚፈጥረው ሽብርና ፍርሃት ይልቅ እድሜ ልክ በተገዢነትና ጭቆና መኖር ይበልጥ ያስፈራል። 

ዛሬ የሕወሃትን የሰልጣን የበላይነት የሚቃወም፣ በጭቆና ተገዢነት መኖር የሚጠየፍ ትውልድ ተፈጥሯል። ስለዚህ፣ ወይ የሕወሃት የበላይነት በለውጥና ተሃድሶ ያበቃል፣ አሊያም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሕዝባዊ አመፅና አምቢተኝነት ይፈርሳል። በመሆኑም የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል። ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚታየውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በሸርና አሻጥር ወደ ሁከትና ብጥብጥ በመውሰድ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማዳፈን የሚደረገው ጥረት ሁለተኛውን የለውጥ ጉዞ ከማፋጠን የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ የለውም። 

​የኦሮሞን መብት የበላ “ኦነግ፥ ግብፅ፥ ህቡዕ፥…” ሲል ያድራል! 

“በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄደ ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ ማን ነው የሚያስተባብረው?” የሚለው ጥያቄ ትልቅ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። ዳኒኤል ብርሃኔ “የተቃውሞ ሰልፉ እየተመራ ያለው ከተጠበቀው በላይ ትልቅ በሆነ የህቡዕ ድርጅት” መሆኑን ገልፀጿል። እኔን የሚያሳስበኝ የዚህ ህቡዕ ድርጅት መፈጠሩና የተቃውሞ እንቅስቃሴውን መምራቱ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ መዋቅሩ በግልፅ ያልተለየ “ትልቅ የህቡዕ ድርጅት ተፈጥሯል” በሚል ሰበብ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሊፈፀም የሚችለው ግፍና በደል ነው። 

ቀጥሎ ያለው ምስል የሁለት ፎቶዎች ቅንብር ነው። የመጀመሪያው ፎቶ ህዳር 25/2008 ዓ.ም ዕለተ ሐሙስ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ላይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች በካምፓሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ሲጀምሩ፣ ከዋናው መግቢያ በር ላይ ደግሞ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አድማ በታኞች ፖሊሶች ናቸው። ከታች ያለው ምስል ደግሞ ጥቅምት 03/2010 ዓ.ም ዕለተ ሐሙስ ከጠዋቱ 2፡00 ላይ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ካምፓሱ ቅጥር ግቢ እየወጡ ያሳያል። 

የተቃውሞ ሰልፍ በወሊሶ፦ ህዳር 2008 እና ጥቅምት 2010 ንፅፅር

በዚህ ፎቶ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች ወይም የከተማ ፖሊሶች ከካምፓሱ በር ላይ አይታዩም። ነገር ግን፣ በከተማው ዋና ዋና መንገዶች ላይ በብዛት ይታዩ ነበር። ከታች ባለው ፎቶ ላይ በግልፅ እንደሚታየው ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የከተማውና የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንደነበር ያሳያል። ከሁለት አመት በፊት የፖሊሶቹ ጥረት ተማሪዎቹና የአከባቢው ማህብረሰብ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳያደርጉ በኃይል ለማስቆም ነበር። ባለፈው ሳምንት ሲያደርጉት የነበረው ደግሞ ተቃውሞ ሰልፉ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይነሳ፣ በዚህም የሰዎች ህይወትና ንብረት እንዳይጠፋ መጠበቅ ነው። 

ባለፈው ሳምንተ በወሊሶ ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ

ከሁለት አመት በፊት ፖሊሶች የተቃውሞ ሰልፉን በኃይል ለመበተን ያደረጉት ጥረት ከሳምንት በኋላ ፈፅሞ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከ50ሺህ በላይ የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ ወጡ። በዚህ ምክንያት፣ በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ። ከከተማዋ አልፎ በመላው ኦሮሚያ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ተፈጠረ። በመጨረሻም በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አማካኝነት ህዝቡና ሀገሪቱ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር ወደቁ። 

ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ግን ፍፁም ሰላማዊ ነበር። ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ላይ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ከ15ሺህ በላይ ሰዎችን ተሳትፈውበታል። ነገር ግን፣ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ ግን ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ሰዎች በሰላም ወደ መደበኛ ሥራቸው ተመልሰዋል። በሕይወትና ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። ከሁለት ዓመት በፊት የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ፖሊሶች በኃይል ለመበተን ባይሞክሩ ኖሮ ዛሬ ከደረስንበት ደረጃ አንደርስም ነበር። በወቅቱ “ወሊሶ፡ ከሰላም ወደ ሱናሚ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፁኁፍ ላይ የተቃውሞ ሰልፉን ወደ አመፅና ብጥብጥ እንዲቀየር ያደረገውን ምክንያት እንዲህ ስል ገልጬ ነበር፡-  

“ከዛሬ 50 አመት በፊት እንደነበረው ሁሉ፣ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ በኃይል ለመበተን የሚደረግ ጥረት ሁኔታውን ይበልጥ ከማባባስ የዘለለ ሚና የለውም። ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በተካሄደ ቁጥር ፖሊስ የተለመደ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ነገሩን ከማባባስ ይልቅ ዋና ተግባሩ በሆነው የሰውና የንብረትን ደህንነት በማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሰራ የተሻለ ነው። የመንግስት ኃላፊዎችም በበኩላቸው የተነሳውን ተቃውሞ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በሚጥስ መልኩ የኃይል እርምጃ በመውሰድ አቋራጭ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ የተነሳውን ጥያቄ በአግባቡ ተቀብለው ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ አለባቸው።” 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በወሊሶ ከተማ ከታየው ሰላማዊ ሰልፍ አንፃር፣ የተቃውሞ ሰልፉን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚቀይሩት ሰልፈኞች፥ ፖሊሶች ወይም ማንነታቸው ያልታወቁ ፀረ-ሰላም ኃይሎች አይደሉም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁከትና ብጥብጥ የሚነሳው በፖለቲካ መሪዎች የተሳሳተ ግምትና ውሳኔ ምክንያት ነው። 

ከሁለት አመት በኦሮሚያ አመፅና ተቃውሞ ሲቀሰቀስ የኢትዮጲያ መንግስት ኦነግና ግብፅን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች እየተካሄደ ያለውን የተቃውሞ ሰልፍ እየተመራ ያለው በጣም ትልቅ በሆነ የህቡዕ ድርጅት ከሚል የለየለት ቅዠት ውስጥ ገብቷል። 

ለሁለት አስርት አመታት “ኦነግ ሞቷል” እያለ ሲፎክር የነበረው የፖለቲካ ቡድን ከሁለት አመት በፊት ኦነግን ከቀበረበት መቃብር፣ ግብፅን ከገባችበት ችግር አውጥቶ “በኦሮሚያ አመፅና ተቃውሞ እየቀሰቀሱ ነው” በማለት የብዙሃን መሳቂያና መሳለቂያ የሆነ ምክንያት ሲያቀርብ ነበር። አሁን ደግሞ “ትልቅ የህቡዕ ድርጅት ተቋቁሟል” ከሚል ቅዠት ውስጥ ገብቷል። ይህ የፖለቲካ ቡድን ፈፅሞ መገንዘብ የተሳነው ነገር ቢኖር፣ የኦሮሞ ሕዝብ የተቃውሞ ሰልፍ እየወጣ ያለው በምንም ምክንያት፣ በማንም አሰስተባባሪነት ሳይሆን ያነሳቸው የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ስላላገኙ ነው። 

ይህን እውነታ ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ መስጠት የተሳነው ቡድን አንዴ “ኦነግና ግብፅ” ሌላ ግዜ “ህቡዕ ድርጅት” እያለ ሲቃዥ ይውላል እንጂ የሕዝቡን የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማስቆም አይችልም። “የማሪያምን ብቅል የበላ ሲለፈልፍ ያድራል” እንደሚባለው ሁሉ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ነፃነት የበላ መንግስት ኦነግ፥ ግብፅ፥ ህቡዕ፥…እያለ ሲለፈልፍ ያድራል!  

 

የዲያስፖራ ፖለቲካ: ከመደማመጥ መጯጯህ፣ ከመተባበር መጠላለፍ

ከBBN_ራዲዮ ጋር ያደረኩት ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል በኢትዮጲያ ስላለው ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተነሳ ስላለው የለውጥ ጥያቄ እና የኢህአደግ መንግስት ፀረ-ለውጥ  አቋምን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ሞክሬያለሁ፡፡ የቃለ ምልልሱን የመጀመሪያ ክፍል ቀጥሎ ያለውን ሊንክ በመጫን ማድመጥ ትችላላችሁ! 

BBN_Radio_Interview_part_one.

በቃለ ምልልሱ ሁለተኛና የመጨረሻ ክፍልን ደግሞ ስለ ዲያስፖራ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ አካሄድ በስፋት ተወያይተናል፡፡ በዚህም ፅንፈኛ ብሔርተኞች እና አክራሪ አንድነቶች፣ እንዲሁም ጥራዝ_ነጠቅ ምሁራን (ልሂቃን) የኢህአዴግ መንግስት እድሜውን እንዲያራዝም ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አልፎ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥና መሻሻል እንዳይመጣ ዋና ማነቆ መሆናቸውን በዝርዝር ለመግለፅ ሞክሬያለሁ፡፡ የቃለ ምልልሱን ሁለተኛ ክፍል ቀጥሎ ያለውን ሊንክ በመጫን ማድመጥ ትችላላችሁ!  

BBN_Radio_Interview_part_two

የዲያስፖራ ፖለቲካ፦ ከመደማመጥ መጯጯህ፣ ከመግባባት መጠላለፍ!

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? “የጋራ አብሮነት ውጤት ነው!” በምን ይገለፃል? “በአደዋ!” 

ይህ ፅሁፍ “ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? በምን ይገለፃል?” በሚል ከአዲስ አዳምስ ለቀረበልኝ ጥያቄ የሰጠሁት ምላሽ ነው፡፡

“ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? በምን ይገለፃል?” ለሚለው ጥያቄ የተሰጡ ምላሾች (ከአዲስ አድማስ ድረገፅ የተወሰደ)

ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ነው፡፡ ዜግነት ደግሞ በአንድ የተወሰነ ሀገር ውስጥ የጋራ አብሮነትን የሚያሳይ ነው፡፡ አንድ ጆሴ ኦርቴጋ የሚባል ፖርቹጋላዊ ፀሐፊ አለ፡፡ ይህ ጸሐፊ፤ ሀገር የሚመሰረተው በምን ላይ ነው? ሲል ይጠይቃል፡፡ ሀገር የሚመሰረተው በእሱ አተያይ፣ በጋራ አብሮነት (common future) ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትም የጋራ አብሮነት ውጤት ነው፡፡ የጋራ መሰረት ያለን፣ የጋራ ጉዳይ ያለን፣ ለወደፊትም የጋራ እድል ያለን ሰዎች ነን፤ በኢትዮጵያዊነት ስር ነው የተሰባሰብነው፡፡፡ ይሄ ማለት ዛሬ እና ትናንት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ነገና ለወደፊትም አብሮ ለመኖር የጋራ ስምምነት ያለን ህዝቦች ነን፡፡ 

የአሁኗ ኢትዮጵያ እንዴት ተመሰረተች? የሚል ጥያቄ ከተነሳ ደግሞ የአሁኗ የቆመችው በአፄ ምኒልክ ዘመን ነው፡፡ አሁን ላይ ላለው የአንድነት ክፍፍልና የእርስ በእርስ መጠላለፍ መሰረት የሆነውም ያንን የኢትዮጵያ አመሰራረት የምንረዳበት መንገድ ለየቅል መሆኑ ነው፡፡ ግማሹ በቅኝ ግዛት (ወረራ) አይነት የተፈጠረች ነች ይላል፤ ግማሹ ደግሞ ቀድሞ የነበረችውና ኋላ ላይ በታሪክ አጋጣሚ የተበታተነች ኢትዮጵያን መልሶ አንድነቷን ማስጠበቅ ነው ይላል። በዚህ መሃል ግን የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች፣ ወደ ምስራቅ አፍሪካ መስፋፋት ሲጀምሩ፣ በወቅቱ ሸዋ፣ ወሎ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ትግሬ በተባሉት አምስት ግዛቶች ላይ ብቻ ተወስና የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ሀገራዊ ኃይልና አንድነት ለማጠናከር፣ ወደ ደቡብ፣ ምስራቅና ምዕራብ አቅጣጫ መስፋፋት ጀመረች፡፡ 


አፄ ምኒልክ፤ በሉአላዊነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመመከት፣ ሁሉም በጋራ መቆም አለባቸው ከሚል መነሻ ነው መስፋፋትን ያደረጉት፡፡ በዚህ መሃል ግጭት ተፈጥሮ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ይሄ ክስተት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ሆኖ የሚታየው አብዛኛው ሀገር፣ አሁን ላይ የያዘው ቅርፅ በእንዲህ አይነት ክስተቶች አልፎ የመጣ ነው፡፡ የዚህ አይነት የማሰባሰብ ውጤት የታየው በአድዋ ጦርነት ላይ ነው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በግልፅ ለአንዲት የጋራ ሉአላዊ ሀገር ተዋድቀዋል፡፡ ስለዚህ አድዋ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ነው፡፡ አድዋ ላይ የምናየው ኢትዮጵያዊነትን ነው፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በጋራ የሉአላዊነት አደጋን የቀለበሱበትና አብሮነታቸውን ያጠናከሩበት፣ ወደፊትም በነፃነት ለመኖር የተስማሙበትና መስዋዕትነት የከፈሉበት፣ ሁሉም ለወደፊት አብሮነታቸው አሻራቸውን ያሳረፉበት ነው አድዋ ማለት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ለኔ አድዋ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማለት በአብሮነት፣የወደፊት ነፃነትን አስከብሮ፣ በጋራ ለማደግ የመስማማት ውጤት ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ነው ነፃነታችንን አስከብረን ዛሬ ላይ የደረስነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ቅኝ ግዛት ውስጥ የወደቁበት ሚስጥሩ፣ ይሄን አብሮነት ማጣታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት በወደፊት አብሮነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ነው ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆንነውና ራሳችንን አስከብረን የኖርነው፡፡ 

የኢትዮጵያ አንድነትን ለማምጣት ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፡፡ ብዙ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል፡፡ ይሄ ግን እኛ ብቻ ሳንሆን  ሰልጥነዋል የተባሉ ሀገሮችም የዛሬ አንድነታቸውን ያገኙት፣ በእንዲህ ያለውና ከዚህም በከፋ ሂደት ነው፡፡ አኖሌ ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ፣ የኢትዮጵያ አንድነት በሚመሰረትበት ሂደት ውስጥ የተፈጠረ ነው፡፡ አኖሌ ላይ ወገኖቻቸው የተጨፈጨፉባቸው ሰዎች ናቸው፣ አድዋ ላይ ለጋራ ነፃነት የተዋጉት፡፡ አድዋን ያለ ኦሮሞ ብሔር ተሳትፎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የአፄ ምኒልክ ወታደር ኦሮሞ ነው፡፡ 

አሁን የሚንጸባረቀው  የመበደል ስሜትና የብሔርተኝነት ስሜትም ሂደት የፈጠረው ነው። በየትኛውም ተመሳሳይ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ባለፈ ሀገር ይሄ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳይን ማንሳት እንችላለን፡፡ ይሄ የመበደል (ብሔርተኝት) ስሜትና የአንድነት ስሜትን የማራመድ ጉዳይ አዲስ ክስተት ሳይሆን ሊፈጠር የሚችል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ልሂቃን እንደሚሉት፤የሀገር አብሮነትን ለማስጠበቅ፣ ይሄን አይነቱን የበደለኝነት ስሜት መዘንጋት ያስፈልጋል፡፡ አሰቃቂ ክስተቶችን መዘንጋትና አስተማሪ ወይም በጎ የሆኑትን መሰብሰብ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ሀገር ያለው የብሔርተኝነት ስሜት መሰረቱ የበደለኝነት ስሜት ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን መዘንጋት ያስፈልጋል፡፡ በአንድነት ጎራ ደግሞ የግድ ኢትዮጵያዊ አንድነትን መቀበል አለብን ብሎ መጫን አያስፈልግም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከእንግዲህ ወዲህ፣ ፈቅደን መርጠን የምንወስደው እንጂ በግድ የሚጫንብን መሆን እንደሌለበት ማስተዋል አለብን። 

የብሔርተኝነቱና የአንድነቱ ጎራ ግጭት በዚህ መንገድ መታረቅና የጋራ የወደፊት አብሮነት መታሰብ ይኖርበታል። የበደለኝነት ስሜትን ትቶ አንድነትን ለማሰብ የአኖሌን ጭፍጨፋ ዘወትር ማንሳቱን ትተን፣ አንድ ያደረገንን አድዋን መዘከር አለብን፡፡ በጎ የታሪክ ገፅታችንን ማጉላት ይገባናል። የቀድሞ ታሪካችን ላይ ቆዝመን አንድነታችንን መሸርሸር ትተን፣ በወደፊት አብሮነታችንና የጋራ ራዕይ ላይ የተመሰረተ የጋራ አንድነትን ለመፍጠር መጣር አለብን፡፡ የፖለቲካ ሃይሎችም አቅጣጫቸው፣በወደፊት የጋራ አብሮነት ላይ የሚያጠነጥን መሆን አለበት፡፡ አሁን ልዩነቶችን ማጉላት ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ 

ዛሬ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ትግሬ እያልን እርስ በእርስ የምንከራከረው፣ የጋራ ጉዳይ፣ የጋራ አገር ስላለን ነው፡፡ ክርክሩ ራሱ የተመሰረተው በጋራ ጉዳያችን ላይ ነው፡፡ አሁን ማተኮር ያለብን “ለወደፊት በጋራ እንዴት እንኑር” በሚለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እየከረረ የመጣውን ልዩነታችንን ማስታረቅ እንችላለን፡፡ 

ስዩም ተሾመ (የዩኒቨርሲቲ መምህር)

*****

ከእኔ ጋራ ሌሎች ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፣ ዶ/ር ንጋት አሰፋ፣ ያሬድ ሹመቴ እና ዳንኤል ብርሃኔ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ ሙሉ ዘገባውን ይህን ማስፈንጠሪያ (Link) በመጫን ማንበብ ትችላላችሁ! 

በኢህአዴግ እና አልቃይዳ መካከል ያለው ልዩነት “በአጥፍቶ መጥፋት” እና “በአዋጅ ማሸበር” ነው! 

ባለፈው በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኘው ¨The Brookings Institution” በዴሞክራሲ ዙሪያ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተሳትፌ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ ከተጋበዙት እንግዶች ውስጥ የቀድሞ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር “Madeleine Albright” ይገኙበታል። በንግግራቸው ወቅት ሽብርተኝነት ለዴሞክራሲ አደጋ እንደሆነ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። በውይይት ወቅት ለቀድሞዋ የአሜሪካ የውጪ ሚኒስትር ጉዳይ አንድ ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር። እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት ዜጎች እየተሸበሩ ያሉት በአሸባሪዎች ሳይሆን በፀረ-ሽብር ሕጉ እንደሆነ በመግለፅ በአሸባሪዎች (terrorists) እና በጨቋኞች (Tyrants) መካከል ያለውን ልዩነት እንዲነግሩኝ ጠይቄያቸው ነበር። 

በአሜሪካ መንግስት ፊት አውራሪነት የተጀመረው አለም-አቀፉ የፀረ-ሽብርተኝነት ትግል እንደ አልቃይዳ ባሉ የሽብር ድርጅቶች በምዕራባዊያን ሰላምና ዴሞክራሲ ላይ የጋረጡትን አደጋ ለማስወገድ ዓላማ ያደረገ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ የአሜሪካኖች የፀረ-ሽብር ዘመቻ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኢሲያ ላይ አሰቃቂ ጦርነት እና ዕልቂት አስከትሏል። እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት ደግሞ የፀረ-ሽብር ዘመቻው በቀጥታ ፀረ-ዴሞክራሲ ሆኗል። በፀረ-ሽብር ትግሉ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ነው።  

የኢህአዴግ መንግስት የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁን በማውጣት በፀረ-ሽብር ስም ሕዝቡ በማሸበር ላይ ይገኛል። የፀረ-ሸብርነት አወጁ ከአሸባሪዎች ጋር ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ ዓላማና ግብ አለው። ከአሸባሪዎች የበለጠ ዜጎችን በፍርሃትና ስጋት የሚያርድ ነው። ይህ ሕግ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከመሸራረፍና ከሕገ-መንግስቱ መርሆች ጋር ተፃራሪ ከመሆኑም በተጨማሪ መሰረታዊ ዓላማው ህዝቡን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል ሳይሆን ንቁ የሆነ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ተሳትፎ እንዳይኖር ማድረግ ነው። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ከወጣ በኋላ ባሉት ጥቂት አመታት የፖለቲካ ነፃነት የሚባል ነገር ተሟጥጦ ጠፍቷል። 

በኢትዮጲያ የፀረ-ሽብር ሕግ መሰረት ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ “በአሸባሪነት” ሊያስከስስ ይችላል። ለምሳሌ፤ “‘የፀረ-ሽብር ሕጉ ይሻሻል!’ የሚል መፈክር ይዛችሁ ውጡ” ማለት – “አመፅና ሁከትን በማነሳሳት – ‘inciting violence and protest’” በሚል ያስከስሳል፤ በሰላማዊ ሰልፍ መንገድ ከተዘጋ – “የሕዝብ አገልግሎትን በማቋረጥ – “disruption of public services’” በሚል አንቀፅ፤ ሰልፈኞቹን “አይዟችሁ በርቱ” ብሎ የተናገረ – “ለአሸባሪዎች የሞራል ድጋፍ በመስጠት – ‘providing moral support or …advice’”፤ “አግ7 ወይም ኦነግ በሰላማዊ መንገድ’ ለመታገል ቆርጧል” ማለት – “አሸባሪነትን በማበረታታት – ‘encouragement of terrorism’” በሚለው አንቀፅ ያስከስሳል። 

በዚህ መሰረት የሀገራችን የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን ነፃነት የሚገድብና የፍርሃትና  ስጋት ምንጭ እንደመሆኑ ከሽብርተኝነት ተለይቶ አይታይም። እንደ የቀድሞዋ የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ “Eliza Manningham Buller” አገላለፅ “…What terrorism does is frighten us through its random effect and deter us from behaving normally. But we compound the problem of terrorism if we use it as a reason to erode the freedom of us all.” 

ሽብርን በሌላ የሽብር ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በራሱ አሸባሪነት ነው። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል በሚል የወጣው የኢትዮጲያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት በመገደቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ሳይሆን፣ የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ ሆኗል። በመሆኑም፣ የጨቋኞች ፀረ-ሽብርተኝነት በተግባር አሸባሪነት ነው። 

የኢትዮጲያ የፀረ-ሸብርተኝነት አወጅ፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚሸራርፍና የሕገ-መንግስቱ መርሆች የሚፃረር፤ በዚህም ከአሸባሪዎች ጥቃት የበለጠ ኢትዮጲያኖችን እያሸበረ ነው። በተለይ ለአዲሱ ትውልድ ትልቅ የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሆኗል። አብዛኞቹ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙ መከራና ግፍ እየተፈፀመባቸው ያሉት እስረኞች የዚህ “አሸባሪ ሕግ” ሰለባ ናቸው። 

ለዚህ ደግሞ ethiotrailtracker.org የተሰኘው ድህረገፅ ያዘጋጀውን ዝርዝር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ድረገፁ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ክሳቸውን በእስር ሆነው የሚከታተሉ እና ጉዳያቸው የተዘጋ በድምሩ የ1405 ዜጎችን ስም ዝርዝር እንደሚከተለው አጠናቅሮታል። 

  • በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ክሳቸውን በእስር ሆነው የሚከታተሉ እስረኞች ዝርዝር  (ብዛት 879) ይህን ማያያዥ (Link) በመጫን በፒዲኤፍ ማግኘት ይችላሉ። 
  • በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የተፈረደባቸው [አሁንም በእስር የሚገኙ ወይም ፍርዳቸውን ጨርሰው የተፈቱ] ፣ ክሳቸው የተቋረጠ እና በነፃ የተለቀቁ እስረኞች ዝርዝር (ብዛት 526) ይህን ማያያዥ (Link) በመጫን በፒዲኤፍ ማግኘት ይችላሉ።