Category Archives: Opinion

የትግራይ ህዝብ እና የህውሓት ግኑኝነት ነባራዊ ገፅታ (በሰለሞን ነጋሽ)

መግቢያ
የትግራይ ህዝብ እና የህውሓት ግኑኝነት በተመለከተ በተለያዩ ሰዎች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች እስከዛሬ ድረስ አወዛጋቢ ሆነው ቀጥለዋል። እስከዛሬ ድረስ አወዛጋቢ መሆኑ በራሱ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳስብ ነገር ነው። ከዚህ ቀደም በርካታ ሰዎች ለጉዳይ ትኩረት ሰጥተው የጻፉ፡ የሚድያ ሽፋን የሰጡ፡ የግል ምስክርነታቸውንና ግንዛቤያቸውን በተለያየ መንገድ የገለጹ ቢሆንም፡ ወቅቱ የሚጠይቀው ርዕሰ ጉዳይ በመሆኑ እኔም የራሴን እይታ ማስቀመጥ እንዳለብኝ በማመን ይህን ጽሁፍ አዘጋጅቻለሁ። ጽሁፉ ምናልባትም ከዚህ ቀደም ያልነበራችሁን ግንዛቤ እንደሚያስጨብጣችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

ቅድመ እይታ
በአንድ በኩል ህውሓት ደጋግሞ “እኔና የትግራይ ህዝብ የማንነጣጠል አንድ አካል ነን” የሚል ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ ከህዝቡ መካከል በግልጽ “የለም እኛና እናንተ ለየቅል ነን፡ ገዢና ተገዢ ወይም ጨቋኝና ተጨቋኝ ነን” የሚላቸው በጣም ጥቂት ነው። ጥቂት በመሆኑ የተነሳ እና በህውሓት የረዥም ጊዜ የፕሮፓጋንዳ ስራ የተነሳ፣ በአብዛኛው ሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ፕሮፓጋንዳው ተቀባይነትን አግኝቶ ቆይቷል። ህዝቡና ድርጅቱ የማይነጣጠሉ ናቸው ተብሎ ተደምድሟል።

“ህውሓት እኔና የትግራይ ህዝብ አንድ ነን ይላል፡ አይደለንም ብሎ የሚከራከር ሰው አልተገኘም። ስለዚህ እነሱ አንድ ነን ካሉ እኛ እንዴት አንድ አይደላችሁም ልንል እንችላለን” ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ ነበረ። በተጨማሪም “የትግራይ ህዝብ ከሌላው በተለየ በዚህ ስርዓት ተጠቃሚ ነው፣ ከዚህ የተሻለ ሌላ ሊጠቅመው የሚችል ስርዓት አይኖርም፣ ስለዚህ ጥቅሙን ለማስከበር ከስርዓቱ ጎን የግድ ይሰለፋል” ብለው የሚከራከሩም ጥቂት አይደሉም።

በሌላ በኩል ደግሞ “ህዝቡ ህውሓት እኛን አይወክልም ብሎ ለመናገር ያልቻለው ከሌላው በተለየ በትግራይ አፈናው ስለሚያይል ነው።” እንዲህውም “ህዝቡ በተለየ ተጠቃሚ ሊሆን ቀርቶ ከሌላው በባሰ የባርነትና የድህነት ህይወት ውስጥ እየኖረ ነው።” ብለው ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ቁጥራቸው የማይናቅ ነው። የዛሬ ዓመት ትግራይን እንዲጎበኙ የተደረጉ አርቲስቶች አብዛኞቹ ራሳቸውን ከዚህ ጎራ መድበዋል። እነ አትሌት ፈይሳ፣ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ እና ለሌችም የትግራይ ህዝብ የሚኖረው እንደማንኛው ኢትዮጵያዊ ነው በሚል አቋማቸው እናውቃቸዋለን። እኔም ራሴን ከዚህ ጎራ እመድባለሁ። ክልሉ ውስጥ እንዳደገ፣ እንደተማረና እንደሰራ ሰው ነባራዊውን ሁኔታ ኖሬበት የማውቀው ነውና ይህን አቋም ብይዝ የሚገርም አይሆንም። ማስረዳት ግን ይጠበቅብኛል። እንሆ፥

የተለየ አፈና
ቀጥተኛ አፈና
ትግራይ ከሌሎች ክልሎች ለየት የሚያደርገው በህውሓት ቀጥተኛ አፈና ስር መሆኑ ነው። ህውሓት በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን የተቆናጠጠ ብቸኛ “ሉአላዊ” ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፡ ይህን የበላይነቱን ለማስጠበቅ ቁልፍ ቁልፍ የመንግስት ስልጣኖችን በመያዝና ሁሉንም መንግስታዊ መዋቅር በቁጥጥሩ ስር በማድረግ አገሪቱን በእግር ብረት ጠፍሮ እየገዛ እንደሆን ይታወቃል። በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ የሆኑ የጋራ የአፈና ዘዴዎች ተዘርግተዋል። የጸጥታ ሀይሉ፣ መከላከያው፣ የፍትህ ተቋማቱ፣ የደህንነት ክፍሉ ወዘተ በህውሓት ቁጥጥር ስር ውለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነቱን ለማስጠበቅ የሚጠቀምባቸው የፖለቲካ መሳሪያ መሆናቸው እሙን ነው።

ያም ሆኖ ሌሎች ክልሎች በህውሓት ቀጥተኛ አፈና ስር አይደሉም ያሉት። አፈናው በሌላ third party (ወይም ጠፍጥፎ በሰራቸው ተላላኪ ድርጅቶች) አማካኝነት የሚገለጽ ነው። እነዚህ ፓርቲዎች የህውሓትን ያክል ጥንካሬና aspirations ኖሯቸው ህውሓት በሚያፍነው ወይም ማፈን በሚፈልገው ደረጃ ህዝብን የሚያፍኑ አይደሉም። እንዳውም አንዳንዴ የሚገዳደሩበት (resist የሚያደርጉበት) ሁኔታ አለ። በነዚህ ክልሎች ውስጥ ለሚኖር ህዝብ ይህ ክፍተት ተቃውሞውን በተለያየ መንገድ ለመግለጽ በአንጻራዊነት የተሻለ ዕድል ፈጥሯል። ለምሳሌ የግል ፕሬሶችን በመክፈትና ህዝብን በማነቃቃት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በመመስረትና በህጋዊ ተቃዋሚነት በመንቀሳቀስ፣ ብሎም በአደባባይ ተቃውሞን በማነሳሳት ረገድ በሌሎች ክልሎችይህ ክፍተት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ትግራይ በቀጥታ በነሱ ቁጥጥር ስር መሆኑ እና ደግሞ በዚህ ክልል ተቃውሞ ከተነሳባቸው ለህልውናቸው የመጨረሻ አደገኛ በመሆኑ፣ እነዚህ በሌላ ክልል የሚታዩ የህዝብ የresistance መገለጫዎች ለረዥም ጊዜ በትግራይ እንዳይፈጠሩ ማድረግ ችለዋል። የግል ፕሬስ ትግራይ ውስጥ ከነ አካቴው እንዳይፈጠር አድርገዋል። በሌሎች አካባቢዎች አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ የግል ህትመቶችና መጻህፍቶች የትግራይን ምድር እንዳይረግጡ እገዳ ተጥሎባቸዋል። የግል ሚድያ ለመፍጠር የሞከሩ አንድ ወይም ሁለት ወጣቶችን ገና በለጋነታቸው ሳይበራከቱ ልክ አስገብተዋቸዋል። በትግራይ የሚናገረው ህውሓት ብቻ ነው። የሚደመጠው  ህውሓት ብቻ ነው። ሌላ ድምፅ የለም።

በትግራይ ለረዥም ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲ እንዳይመሰረትና በክልሉ እንዳይንቀሳቀስ ግልጽ በሆነ አፈና አግደውታል። ዓረና ትግራይን ዘግይተውም ቢሆን የፈቀዱት አንድም የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በክልሉ እንደተጀመረ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ለመጠቀም፣ ሁለትም መስራቾቹ የቀድሞ የህውሓት ታጋዮች በመሆናቸው ህዝብ ከኛ በተለየ መልኩ ሊቀበላቸው አይችልምና ለስልጣናችን አደጋ አይሆኑም በሚል እሳቤ መሆኑ ይታወቃል። ያም ሆኖ ሰርጎ ገቦችን ከትተው በየጊዜው ሲያፍረከርኳቸው ይስተዋላል። ስርዓቱን አምርረው የሚቃወሙ ወጣቶች አማራጭ ፓርቲ ሊመሰርቱ ቀርቶ ብሶታቸውን የሚጋሩበት፡ተቃውሞና ትችታቸውን የሚናገሩበት መድረክ ፈጽሞ አያገኙም። የህውሓት ቀይ መስመር በትግራይ ደመቅ ይላል። ህውሓት ተቃውሞ በትግራይ ፈጽሞ አይፈቅድም። እስከመቼውም ድረስ ሊፈቅድ አይችልም።

የመረጃ አማራጭ ከሌለ፣ በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ ህውሓት እየሰራቸው ያሉ ወንጀሎች ህዝቡ የሚያውቅበት መንገድ ከሌለው፣ ህዝቡ ለነጻነቱ እንዲቆም በሰላማዊ መንገድ የሚያነሳሱና የሚያስተምሩ ወጣቶችና ፓርቲዎች ከሌሉ፣ በራሱ ጊዜ ህዝብ ተነስቶ ለመቃወም እድሉ ጠባብ ይሆናል። ወይም በጣም ጊዜ የሚጠይቅ ይሆናል። በአንድ በኩል ህዝቡ ከመታፈኑ በተጨማሪ በጥላቻ የተሞሉ ፕሮፓጋንዳዎችን በየቀኑ ሲለፍፉበትና ሲያሴሩበት ስለሚውሉ በፍርሃት እንዲሸበብ  ተደርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ባልተነቃባቸው ተዘዋዋሪ የአፈና መሳሪዎችን በመጠቀም ህዝቡ በተለይ የገጠሩና የከተማ ድሃው ክፍል ሰጥ ለጥ ብሎ ለህውሓት እንዲገዛ ተደርጓል።

ተዘዋዋሪ የአፈና መንገዶች
የትግራይ እግሪ ምትካል /ትእምት/EFFORT/
ይህ ድርጅት የህውሓትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጡንቻ ያፈረጠመ ጠንካራ ድርጅት ነው። ስልጣን ላይ ለመቆየት የመንግስት መዋቅሮችን መቆጣጠር ብቻውን በቂ አይደለም በሚል እምነት የቆመና የራሱን የኢኮኖሚ ኢምፓየር በአገሪቱና በውጪ አገራት የዘረጋ ድርጅት ነው። እንደ ድርጅት financial freedom ከሌለውና እንደ መንግስት በውጭ እርዳታ የቆመ ከሆነ፣ ህውሓት በፈቀደው መንገድ አገሪቱን መግዛት አይችልምና ከጅምሩ የዚህ ዓይነት ምሰሶ መትከል ነበረበት።

ይህ ድርጅት ፓርቲው በማንኛውም ጉዳይ ፈርጣማና ፍሌክሲብል የሆነ ጡንቻውን እንዲጠቀም ከማስቻል በተጨማሪ፣ በስነልቦና ጦርነት ረገድ የማይናቅ ድልን አቀዳጅቶታል። ዛሬም ድረስ በርካታ ወጣቶች EFFORT የህዝብ ንብረት ነው በሚል ተስፋ ይኖራሉ። ይህን የህዝብ ንብረት “ከጠላት” የመጠበቅ አደራና ግዴታ አለብን ብለውም ያምናሉ። ይህ የህዝብ ሀብት ባለበት ሊጠበቅ የሚችለውና ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ህውሓት ሲኖርና ችግሮቹን በግምገማ በተሃድሶና በመሳሰሉት እንዲፈታ ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ብሎ የሚያምነው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ህውሓት ከስልጣኑ ከተነሳ ይህን ሀብት እናጣለን በሚል ስጋት ትግላቸው ለጥገናዊ ለውጥ ብቻ ይሆናል።

በእርግጥ ዛሬ በትግራይ ተቃውሞ አለ ከተባለ ከዚህ የዘለለ ተቃውሞ አይደለም ሊታይ የሚችለው። ይህ ደግሞ ለህውሓት ድልን አጎናጽፎታል። እኔ ከሌለሁ ትጠፋለህ ከሚለው ፕሮፓጋንዳ ጋር ስምም የሆነ አካሄድ በመሆኑ፣ ህዝቡ ህውሓት ላይ እንዳይነሳ ራሱን የቻለ አንድ ምክንያት ሆኗል። ባጭሩ በተዘዋዋሪ መንገድ የማፈኛ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። ይሄ ወደፊትም አደጋ ያለው አካሄድ በመሆኑ በEFFORT ጉዳይ ላይ በግልጽ መነጋገር ለነገ የሚተው ጉዳይ መሆን የለበትም። በዚህ ዙሪያ ግልጽ የሆኑ ውይይቶችን ማድረግ በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ተገቢ ነው፥ በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ምክንያት ጥገናዊ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አያስፈልግም ብሎ ለሚያምነው ክፍል መልስ ለመሰጠት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በድህረ ህውሓት ለምትኖረን ኢትዮጵያ ይህ ኩባንያ ያልተጠበቀ ችግር ሳይፈጥር በፊት ውይይቱን ከወዲሁ መጀመር የነገ አካሄዳችንን ፈር ለማስያዝ ይረዳል።

ማሕበር ረድኤት ትግራይ /ማረት/REST/
ይህ ድርጅት ላይ ላዩን በእርዳታና በልማት ስራ የተሰማራ ሲቪክ ተቋም ይምሰል እንጂ በብዙዎች ዘንድ ያልተባነነበት mighty የፖለቲካ ድርጅት ነው። በክልሉ ከፍተኛ የፖለቲካ ስልጣን ያለውና ህዝቡን በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ የሚጠቀሙበት ቁጥር አንድ የፖለቲካ መሳሪያቸው ነው። የመሳሪያዎቹ ዝርዝር ከቀላል ወደ ከባድ፥

1• ማረት በህዝብ ስም እርዳታ ይጠይቃል። እርዳታ የፖለቲካ መሳሪያ ነው። የህውሓትን ትዕዛዝ የማያከብር ድሃ በእርዳታ ይቀጣል። ከምግብ ለስራ ይሰናበታል። ወዘተ። ድሃን በጉሮሮው ከቀጣኸው ጉልበት ኖሮት ሊቃወምህ አይችልም። ስለዚህ ቀዳሚው የህውሓት ስራ አብዛኛውን የህዝብ ክፍል አደህይቶ የመግዛት ፖሊሲውን ማስቀጠል መቻሉ ነው። በቁጥጥሩ ስር በሆነ የማረት ተቋም እርዳታና የምግብ ለስራ እድሎችን በመስጠትና በመንፈግ በቀላሉ ህዝቡን ለማንበርከክ የተዋጣለት ከፖሊሲው ጋር የተቀናጀ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ አገልግሎታል።

2• ህውሓት ማንኛውም ዓይነት የውጭ ግብረሰናይ ድርጅት (NGO) ትግራይ ውስጥ ራሱን ችሎ እንዳይንቀሳቀስ ገና ጫካ እያለ ጀምሮ በህግ አግዷል። ፕሮጀክታቸውንና ገንዘባቸውን ይዘው መጥተው ለማረት በማስረከብ፣ በማረት አማካኝነት ፕሮጀክቱ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚጠይቅ አሰራር ይከተላል። መያዶቹ ከተስማሙ የፕሮጀክቱን ሂደት አልፎ አልፎ ሱፐርቫይዝ ለማድረግ ብቻ ይፈቀድላቸዋል። ካልተስማሙ ገንዛባቸውንና ፕሮጀክታቸውን ይዘው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ያደረጋል። ህዝቡ መሃል ገብተው በራሳቸው እቅድና የአፈጻጸም መንገድ እንዲሰሩ ህውሓት ፈጽሞ አይፈቅድላቸውም፤ በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች፥ የመጀመሪያው የውጪ ድርጅቶች ህዝቡን ቀርበው በማነጋገር ህዝቡ ያለበትን ትክክለኛ ሁኔታ እንዳያወቅ፣ አውቀውም ወደ ውጪ እንዳይወጡት በመፈለግ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከህውሓት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ገቢ ህዝቡ እንዲኖረው ስለማይፈለግ ነው።

እነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች ህውሓት በክልሉ የሚኖረውን ሃይል ማዳከም የሚችሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል። ዛሬ NGOዎች ስፖንሰር ያደረጉትን ፕሮጀክት ሱፐርቫይዝ ሲያደርጉ የሚያነጋግሩት ህውሓት ያዘጋጀላቸውን ካድሬዎችን ብቻ ነው። ህውሓት ያላዘጋጃቸው በዕጣ የተመረጡ ተራ ሰዎች ስለሚኖሩበት ህይወት በትክክል እንዲናገሩ አይደረግም። ድንገት ተመርጠው ከሆነም ካድሬ በመሃከላቸው እንዲገኝ ተደርጎ ስለሚናገሩት ነገር እየተሰለሉ ነው። በተናገሩት መሰረት ከተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲገለሉ እንደሚደረጉ ስለሚያውቁ ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ለመናገር ይፈራሉ። በዚህ ምክንያት በተለይ ለውጭ ሚድያዎችና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ክልሉ ዝግ እንደሆነ እስከዛሬ ድረስ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ከህውሓት ቁጥጥር ውጪ የሆነ ገቢ የሚያገኝ ሰው፣ በህውሓት መታዘዝን አሻፈረኝ ሊል ይችላልና ለፖለቲካ ህልውናቸው አደጋ ነው። ስለሆነም ህውሓቶች ይህን ሊፈቅዱ ፈጽሞ አይችሉም።

3• ማረት ከእርዳታ ውጪ በ”ልማት” ትርፍ በሚያስገኙ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው። “የልማት” ስራው ባብዛኛው ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በፕሮጀክት ስም ከውጪ ለሚያገኘው ገንዘብ እንደ ሽፋን የሚጠቀምበት የማጨናበሪያ መንገድ ሲሆን፣ ጎን ለጎን ደግሞ የማሳያውን ልማትም ቢሆን የሚሰራው ለድርጅቱ ታዛዥ የሆኑ አካባቢዎችንና ግለሰቦችን ታርጌት ባደረገ መልኩ ነው። ያም ሆኖ አንዱን የልማት ስራ ከሶስት ወይም አራት የተላያዩ ፕሮጀክቶች ሂሳብ እያወራረደ ኪሱን የሚሞላበት አሰራርን ዘርግቷል። በዚህ መንገድ የሚገኘው ትርፍ የህውሓትን ኪስ ከማደለብ ባሻገር ህዝቡን በሚከተለው መንገድ ለማፈን ይጠቀሙበታል።

4•  ማረት የብድር ሰጪ ተቋም (ደደቢት) በውስጥ ስላለው በዚህ ተቋም አማካኝነት በተለይ ድሃው ገበሬ በተለያዩ ምክንያቶች ብድር እንዲወስድ በህውሓት ይገደዳል። የብድሩ ምንጭ የማረት ትርፍ ነው። የማረት ትርፍ የሚመጣው በተጨናበረ መንገድ ነው። ገበሬው ያለፈቃዱና ያለ በቂ ስልጠና ተገድዶ ለማዳበሪያ ለምርጥ ዘርና ለመሳሰሉ የምርት ግብዓቶች እንዲህውም መጤ የግብርና ፓኬጆች ብድር እንዲወስድ ይደረጋል። ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲህውም ሌሎች ግብዓቶችን የሚያቀርበው ጉና ነው። ጉና በEFFORT ስር ነው። ጉና ምርቱን ለገበሬ አስገድዶ በመሸጥ ያተርፋል። ገበሬው በራሱ ጥሬ ገንዘብ መግዛት ስለማይችል፥ ብድር ከማረት በከፍተኛ ወለድ እንዲወስድ ይደረጋል። ማረት ሌላ ትርፍ ያጋብሳል። ገበሬው ብድሩን ለመክፈል ፍዳውን ያያል። ብድሩን ለመክፈል የግድ በእርዳታና በምግብ ለስራ ፕሮጀክቶች ስር መታቀፍ መቻል ይኖርበታል። በነዚህ ስር ታቅፎ ተጠቃሚ ለመሆን ደግሞ፣ ለህውሓት ታዛዥነቱንና አሜን ባይነቱን ማረጋገጥ አለበት። ወዘተ።

በዚህ ሁኔታ ነው ገበሬውን ሸብበው የያዙት። በተለይ ትግራይ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነው ህዝብ (ገበሬው) በኛ ቁጥጥር ስር ነው ሲሉ ደጋግመው የሚፎልሉትም በዚህ ምክንያት ነው። ገበሬው መቼም ቢሆን አንገቱን ቀና ማድረግ እንዳይችል የተወሳሰበ አሰራር ዘርግተው አስረውታል። ዛሬ የጎንደር ምሊሻ ገበሬና የኦሮሚያ ገበሬ ለነጻነቱ እንደቆመው ዓይነት ተቃውሞ ከትግራይ ገበሬው ይነሳባቸዋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ገበሬው ካልተነሳ ደግሞ ሌላው ያን ያክል ስጋት ላይ የሚጥላቸው ባይሆንም ለሱም የሚቀጥለውን መሸበቢያ አሰራር ዘርግተዋል።

ማሕበር ልምዓት ትግራይ /ማልት/TDA/
ይህ ድርጅት ሲቋቋም በተለይ በዳያስፖራ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በጦርነት የተዳከመችዋን ትግራይ ተረባርበው እንዲያለሙ እድል ይስጣል በሚል ዓላማ ነበር። ነገር ግን በዚህ መንገድ ለበርካታ ዓመታት ከዳያስፖራ ተጋሩ፣ በውጪ አገራት የትግራይ ወዳጆች እና በአገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ባለሃብቶች ከፍተኛ ገንዘብ የተሰበሰበ ቢሆንም መድረሻው ሳይታወቅ እንደተነነና ይህም ጥያቄ አስነስቶ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ድርጅቱ አንዴ እንዲፈርስ፣ ሌላ ጊዜ ተመልሶ እንዲቋቋም ሲደረግ ቆይቷል። ከጅምሩ ዓላማው ፖለቲካዊ እንጂ ልማታዊ ባለመሆኑ፣ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ዳግም እየመጣ የህዝቡን የልብ ትርታ የሚያዳምጡበት ሁነኛ የፖለቲካ መሳርያ ሆኗል። እንግዲህ የኔ ጥርጣሬ በዚህ ድርጅት የተሰበሰበው ገንዘብ፣ ብዙዎች እንደሚሉት በግለሰቦች ተመዝብሮ ድራሹ ጠፍቷል ሳይሆን ወደ EFFORT ወይም የህውሓት ካዝና ገብቷል የሚል ነው። ይህም ማለት በልማት ስም የሚሰበሰበው የመዋጮ ገንዘብ በራሱ ህውሓትን በማደለብ ጥቅም ላይ የሚውል ነው። የህውሓት የገንዘብ ምንጭ መሆኑ በራሱ የፖለቲካ መሳሪያ ቢሆንም ይህ ቀላሉ ጉዳይ ነው።

ከባለሀብት የተጀመረው ለማልት መዋጮ የመሰብሰብ አሰራር፣ ብኋላ የመንግስት ሰራተኛንና ተማሪውን የሚያሳትፍ እንዲሆን ተደርጓል። ከተማሪም ይሁን ከመንግስት ሰራተኛ የሚሰበሰበው ገንዘብ ያን ያህል የረባ ገንዘብ ባይሆንም በማልት ስም ህውሓት ለሚያቀርብላቸው ጥያቄ ባለሀብቶቹ፣ ሰራተኞቹና ተማሪዎቹ የሚሰጡት ምላሽ አወንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ የሚለውን የሚለኩበት የፖለቲካ መሳሪያ ነው። አሉታዊ መልስ የሚሰጡት በርከት ያሉ እንደሆን “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎችን ይወስዳሉ። እርምጃዎቹ ግለሰብ ተኮር ቅጣቶች በመሰንዘር ወይም systematic የሆኑ የአሰራር ለውጦችን በመከተል ሊፈጸሙ ይችላሉ። ማልት የህዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጡ ከስር ከስር እርምጃ የሚወስዱበት መሳሪያ በመሆኑ ከEFFORT እና ከማረት ቀጥሎ ሶስተኛው የተዋጣለት የፖለቲካ መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል።

ከነዚህ ሶስቱ ተቋማት በተጨማሪ እንደማንኛውም ክልል በትግራይ ሌሎች የማፈኛ መንገዶች ስራ ላይ ናቸው። 1ለ5 ጥርነፋ፣ የጸጥታ ሀይሉና መከላከያው በቁጥጥራቸው ስር መሆን፣ የፍትህ ተቋማትና ደህንነት በነሱ ስር መሆን፣ አስገድዶ አባል ማድረግ፣ አባል ላልሆነ ዜጋ የስራ ዕድልና ሌሎች ነገሮችን መከልከል፣ በአንጻሩ ደግሞ አባል ለሆነና ለሚደግፋቸው በተለያዩ መንገዶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ወዘተ በሌላው ክልል እንዳለ ሁሉ በዚህ ክልልም አለ። ለየት የሚለው ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱ ተቋማዊ የአፈና መሳሪያዎች ናቸው።

የትግራይ የተለየ ተጠቃሚ
እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩትን የአፈና መሳሪዎች ላነበበ የትግራይ በተለየ ተጠቃሚነት ሊዋጥለት የሚችል አይሆንም። ትግራይ ከሌላው በተለየ ተጠቃሚ አይደለም። እንዳውም በተለየ የታፈነ ህዝብ ነው። ይህ ማለት ግን በተለየ የተጠቀመ ክፍል የለም ማለት አይደለም። በፍጹም። እንዳውም በተገላቢጦሽ በስርዓቱ በተለየ ተጠቃሚ የሆነው ክፍል የወጣው ባብዛኛው ከዚህ ክልል ነው። በቁጥር ጥቂቶች ናቸው ነገር ግን ፍጹም የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ተቆናጠውቷል። ህውሓት ዓይኑን ጨፍኖ ሊያሞኘን እንደሚሞክረው በኢህአዴግ ስር እንዳሉት እንደ ማንኛውም ድርጅቶች እኩል አይደለም። የተለየ ተጠቃሚምና ፍፁም የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነትን የተቆናጠጠ ብቸኛው ሉአላዊ ፓርቲ ነው።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቁልፍ ቁልፍ የመንግስት ቦታዎችን በቁጥጥሩ ስር አድርጓል። ሁሉንም የመንግስት መዋቅሮችና የገቢ ምንጮችን በቁጥጥሩ ስር አውሏል። መከላከያ፣ ደህንነት፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ አየር መንገድ፣ አየር ሀይል፣ ጉምሩክ፣ ናሽኛል ባንክ፣ ሚድያ፣ ት/ት ሚንስቴርና ከፍተኛ የት/ት ተቋማት፣ አስመጪና ላኪ ድርጅቶች፣ ግብር ሰብሳቢ ባለስልጣን፣ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ የውጭ ምንዛሪ (ጥቁር ገበያ)፣ የመሬት ንግድ፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ ገንዘብ አጠባ (money laundary & illicit financing) ወዘተ በህውሓትና በህውሓት ሰዎች ያልተያዘና ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነ አንድም ዘርፍ የለም። ባጭሩ አገሪቱ የግላቸው ንብረት ሆኗለች። ፓርቲውና ከፍተኛ ካድሬዎች የልዩም ልዩ! ተጠቃሚዎች ናቸው። የነዚህ ሰዎች ልዩ ተጠቃሚነትና የበላይነት፣ ከአጠቃላይ የትግራይ (ህዝብ) የበላይነት ጋር ተምታቶ ሲቀርብ ይታያል። ይህ ስህተት ነው። ሊታረም ይገባል።

ማጠቃለያ
ፕ/ር መስፍን እና ሌሎችም ከዚህ በፊት እንዳሉት የመጨረሻው የድህነት ወለል ላይ ያሉት፣ ቤት ንብረታቸውን ጥለው በአዲስአበባና ሌሎች ከተማዎች ጎዳና ላይ ሲለምኑ የሚውሉ የኔ ቢጤዎች በብዛት ከትግራይ የተሰደዱ ናቸው። ይህ ብቻ አይደለም፣ የሚላስ የሚቀመስ የሌለው፣ የህውሓትን ይሁንታና ምጽዋት ሲጠባበቅ የሚኖረው ህዝብ በትግራይ ያለ ማጋነን ከ80 በመቶ በላይ ይሆናል። ምጽዋት የማይጠብቁ የሚባሉት የመንግስት ሰራተኞች ራሱ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ሲኖሩ ይታያሉ። በተዘረጋባቸው የፖለቲካ መሳሪያ አማካኝነት ታፍነው ይኖራሉ። ብሶታቸውን ለመግለጽ ይፈራሉ። እንደምንም ወደ ውጭ ቢወጡ እንኳን፣ ከወጡ ብኋላም ፍርሃቱ አይለቃቸውም። ህውሓትን ይፈራሉ፣ በዘራቸው ምክንያት እንዳያጠቃቸው ሌላውን ይፈራሉ። የአጣብቂኝ ህይወት ውስጥ ይኖራሉ።

በእርግጥ በዛው ልክ ደግሞ ከህውሓት ጋር አሸሸ ገዳሜ የሚሉ፣ በህዝብ ስም የሚነግዱ፣ በህዝብ ስም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚጋጩ፣ በሌላው ሀዘን ላይ የሚጨፍሩ፣ በሌላው ደስታ ላይ ማቅ የሚለብሱ፣ ሆን ብለው ህዝቡ በሌላ እንዲጠላ የሚሰሩ የህውሓት ገረዶች አሉ። ህውሓት የሚፈልገው ስለሆነ ያሰማራቸው ካድሬዎች ናቸው። በተጠና መንገድ ተግባራዊ እየሆነ ያለ፣ ትግራይንና ትግራዋይን ከሌላው የመነጠል ስራ ነው።

የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን በኢትዮጵያ ማስጠበቅ ካልቻሉ፣ ቢያንስ በትግራይ ማስጠበቅ ይኖርብናል ብለው ያስባሉ። ምሽጋቸውን ትግራይ ላይ እየቆፈሩ ነው። ትግራይን ቄጤማ አድርገዋታልና በከፋ ቀን ጉዝጓዛቸው ትሆን ዘንድ በዝግጅት ላይ ነች። የዚህ እንድምታ ለብዙዎቻችን ምናልባት በደንብ አልገባን ይሆን ይሆናል። ምናልባት ሊታወቅ የማይችል ሊሆን ይችላል። ዛሬ ደርሰው የዓፈርንና የሶማሌን ብሄርተኝነት የሚያራግቡት፡ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ በዘር ከፋፍለው በማበጣበጥ እነሱ በትግራይ ለመሸሸግ ይመስላል። ምናልባት ሌላው ሲባላ እነሱ ደልቷቸው የሚኖሩ መስሏቸው ሊሆን ይችላል። ፍላጎታቸው ምንም ይሁን ምን ትግራይንና ኢትዮጵያን ከዚህ ድርጅትና ከነዚህ ሰዎች ማስጣል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀላፊነትና ግዴታ ሊሆን ይገባል።

በሌላው ክልል እንደምናዬው በአጭር ጊዜ ውስጥ በራሱ ተነሳሽነት የትግራይ ህዝብ በተቃውሞ ይነሳል የሚለው እምነቴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መጥቷል። ምክንያቱም ህዝቡ ህውሓትን ይፈራል፣ ሌላውን ወገኑንም ይፈራል። በተቃውሞ ለመነሳት አንዳቸውን መፍራት የግድ ማቆም አለበት። ሌላውን ወገኑን መፍራት እንዲያቆም በሌላው ወገኑ በኩል የአወንታ ምልክቶችና የትግል አጋርነቶችን ማየት አለበት። ህዝቡን ማግለልና ከህውሓት ጋር ደርቦ መፈረጅ ስህተት ስለሆነ ሊታረም ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሌላውን ወገኑን እየፈራ ህውሓትን ሳይፈራ ለመታገል ይከብደዋል። ምክንያቱም ሌላውን እየፈራ ህውሓትን ሳይፈራ ጭቆና በቃኝ ብሎ ለመነሳት፣ ጠንካራ ትግራዋይነትን (ትግራዋይ ድርጅትን) መፍጠር ይጠበቅበታል። ከህውሓት ብኋላ ህልውናውን ለማስጠበቅ በደንብ መደራጀት እንደሚኖርበት የግድ ማመን ካለበት፣ ያንን ለማሳካት ጊዜ ይፈጃልና በቅርቡ ተቃውሞ ሊያስነሳ አይችልም። ከጊዜው አንጻር የተሻለው አማራጭ ትግራይንም ያካተተ፣ ትግራይን ከህውሓት ነጻ ለመውጣት ጭምር ያለመ ኢትዮጵያዊ ትግል ማካሄድ ነው። ይህን ማድረግ ግድ ይላል።ህውሓት እንደ ድርጅት እስካለ ድረስ የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በሰላም ሊኖር አይችልምና ህውሓት ከኢትዮጵያ ምድር እስከወዲያኛው ማስወገድ ብቸኛው የማታገያ መንገድ ሊሆን ይገባል።

በመጨረሻ በተለይ ህዝባችን ያለበት ሁኔታ የሚያሳስበን በውጪ የምንኖር የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ጋር በመተባበር በህውሓት ምክንያት ዜጎች እየደረሰባቸውን ያለ ግፍ በጋር በማውገዘ የትግል አጋርነታችንን በግልፅ ማሳየት አለብን። በትግራይ ያለዉን እውነተኛ ገፅታ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ማስረዳት ይጠበቅብናል። የትግራይ ህዝብም ለነፃነቱ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲቆም ማነሳሳት ይጠበቅብናል። በቃኝ የሚልበትን ጊዜ ለማፋጠን ብዙ መስራት ይጠበቅብናል። በፕ/ር መስፍን የቀረበ የመፍትሔ ሀሳብ በማካፈል ፅሁፌን ላጠናቅቅ።


ምንጭ፦ Solomonnegash.com

ወደ ትግራይ ሰዎች…

‘በደሜ በላቤ ደማቅ ታሪክ ፀፍኩ’ ባዩ ህ.ወ.ሃ.ት ለመንገዴ መቅናት ምክንያቱ የትግራይ ህዝብ አጋርነት ነው ይላል፡፡ ይህ ግማሽ እውነት ነው፡፡በህወሃት ጥላስር ይታገሉ የነበሩት ትግሬዎች ብቻ አልነበሩም፡፡የቀድሞው የህወሃት ታጋይ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እንደሚናገሩት ስሙ አይነሳም እንጅ ከህወሃት መስራቾች አንዱ ጎንደሬ አማራ ነው፤ሰውየው በአሁኑ ወቅት በሽተኛ እና ችግረኛ ሆኖ አንዳንዴ ቤታቸው እየጠሩ እንደሚያስታምሙትና እንደሚያሳክሙት በአንድ ወቅት መስክረው ነበር፡፡በቅርቡ እንደሰማሁት ይህ ሰው በቂ ህክምና እንኳ ሳያገኝ ህይወቱ እንዳለፈ አንብቤያለሁ፡፡

ከደርግ ግፈኛነት የተነሳ  ህ.ወ.ሃ.ት የሚለውን ስም እንደከልካይ ሳይቆጥር ትግሬ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም የህወሃት አባል ሆኖ ደርግን ተፋልሞ ነበር፡፡ህ.ወ.ሃ.ቶች ግን ይህን ማንሳት አይፈልጉም፡፡ከዚህ ይልቅ መላው ኢትዮጵያዊ ከደርግ ተፋልሞ ነፃነቱን ላቀዳጀው የትግራይ ህዝብ ባለ እዳ እንደሆነ፣የትግራይን ህዝብ ቤዛነት እና ጀግንነት በአንደበታቸውም በድርጊታቸውምያስተጋባሉ፡፡ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት “ኢንዶውመንት” በሚል የዳቦስም ትግራይን የፋብሪካ መክተቻ ማድረጉን ተያያዙት፡፡ ‘ምነው ይህ በረከት ለሌላው የኢትዮጵያ ምድር ቢደርስ?’ የሚል ከተገኘ መልሱ ‘የትግራይ ህዝብ በጦርነት የተጎዳ ጀግና ህዝብ ስለሆነ ይህ አይበዛበትም፤ተራ ቅናታችሁን ትታችሁ የትግራይን ልማት ሬት ሬት እያላችሁም ትቀበሉታላችሁ’ የሚል ነበር፡፡ይህን የሚሉት ስለ “እውቀት ጢቅነታቸው” በጀሌ ካድሬዎቻቸው ማህሌት የሚቆምላቸው አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ ጉድ የተባለ “ጥልቅ እውቀት” ጀግንነት በዘር የሚተላለፍ ቡራኬ አድርጎ ለማቅረብ የማያፍር ነው፡፡ እርሳቸው የወጡበትን ዘውግ ልዩ የሆነ የጀግንነት ቅመም እንዳለው ከአንድም ሁለት ሶስቴ በአፋቸው የተናገሩት አቶ መለስ በተግባራቸው ያደረጉት በአፋቸው ካወሩት እጅግ ዘለግ ያለ ነው፡፡

የኢፈርት እና ደጀና “ኢንዶውመንቶች” ነገር..!

አቶ መለስ የሚመሩትን መንግስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የሲቪል ስልጣን ለወንዛቸው ልጆች ካደሉ በኋላ ለወጡበት ዘውግ ይገባል ያሉትን ሁሉ ከማድረግ እጃቸውን አልሰበሰቡም፡፡ኢፈርት የተባለውን አደናጋሪ እና ሚስጥራዊ የንግድ ኩባንያዎች ባህር አቋቁመው ሚስታቸውን (ያለ አቅሟም ቢሆን)ይህን የፋብሪካ ባህር እንድታስተዳድር ሰየሟት፡፡ወ/ሮ አዜብ ወደ ኢፈርት ቁንጮነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት አዛውንቱ ስብሃት ነጋና ሌሎች ትግራዊያን ኢፈርትን ዘውረዋል፡፡የኢፈርት ፋብሪካዎች ወደ ሰማኒያ የሚደርሱ ሲሆኑ አንዱም “በስህተት” እንኳን ከትግራይ ውጭ አልተገነባም፤ከትግራይ ባልሆነ ኢትዮጵያዊም ተዳድሮ አያውቅም፡፡በአንፃሩ ፋብሪካዎቹ የሚያመርቱት ሸቀጥ በመላ ሃገሪቱ ይራገፋል፣ወደባህር ማዶም ይሻገራል፡፡የፋብሪካዎቹ በአንድ ቦታ መከማቸት ከትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ፋብሪካዎቹ ‘በስኩየር ኪሎሜትር ስንት?’ ተብለው ሊቆጠሩ ምንም ያልቀራቸው ያስመስላል፡፡ የኢፈርት በትግራይ ብቻ መከተም፣በትግራዊ አስተዳዳሪዎች ብቻ መተዳደር ጉዳይ በጣም እያነጋገረ ባለበት ሁኔታ ደግሞ ሌላ ወንድም “ኢንዶውመንት” በእዛው ክልል በቅርቡ ተመስርቷል፡፡የዚህ ምክንያቱ የኢፈርት ኩባንያዎች መበራከት አለቅጥ ሰፍቶ  ለአስተዳደር  አመች ወደ አለመሆን ግዝፈት በመድረሱ ሌላ ኢንዶውመንት እንዳስፈለገ ወ/ሮአዜብ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡የኢፈርት ግዝፈት ሊያመጣ የሚችለውን አስተዳደራዊ ውስብስቦሽ ለመታደግ “ደጀና” የተባለ ትግራይ ከታሚ ኢንዶውመንት በዚህ ከሶስት አመት አካባቢ በፊት ተቋቁሞ እነ አበርገሌን አይነት ኩባንያዎች አቅፎ ልማቱን እያሳለጠ እንደሆነ ሰርክ ይወራል፡፡ አዲሱ ደጀና ኢንዶውመንት ከአስር በላይ ኩባንያዎች በስሩ አቅፎ ታላቁን ኢፈርትን ለመፎካከር ድክ ድክ እያለ ነው፡፡

እነዚህ ኢንዶውመንቶች ከትርጉማቸው ጀምሮ ባለቤትነታቸው፣ኦዲት ያለመደረጋቸው ጉዳይ፣ በአንድ ክልል(በትግራይ) ብቻ እንዲከትሙ ያደረጋቸው ምስጢር ወዘተ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የሚያስቆጣ ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል፡፡የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት እነዚህ ፋብሪካዎች ኦዲት የማይደረጉበት፣የኦዲት ሪፖርታቸውም የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ለሆነው ፓርላማ የማይቀርብበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ተገቢ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ለዚህ የአቶ መለስ መልስ ‘እነሱ እኮ ኢንዶውመንቶች ናቸው ግልፅ ሪፖርት ማቅረብም አይጠበቅብንም’ የሚል የተለመደ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡ አቶ ተመስንም የዋዛ አይደሉምና “ኢንዶውመንት” የሚለውን ቃል ትርጉም በአማርኛ ሆነ በኦሮምኛ በአፋርኛ ሆነ በትግርኛ በፈለጉት ቋንቋ ተርጉመው እንደዚህ አይነኬ የመሆኑን ሚስጥር  ያስረዱን” ሲሉ ቢወተውቱም አቶ መለስ በማስቀየስ እንጅ መልስ በመመለስ ስማይታሙ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡የሆነው ሆኖ “ኢንዶውመንት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአብዛኛው የኮርፖሬት ፈንዶችን ለመግለፅ የሚያገለግል ፅንሰሃሳብ ነው፡፡ከሌሎች የንግድ ማህበሮች በተለየ ከኢንዶውመንት ኮርፖሬት ፈንዶች የሚገኝ ትርፍ ተመልሶ ለልማት የሚዉል  እንጅ  ለባለቤቶች የሚከፋፈል አይደለም፡፡ የአቶ መለስ “ኢፈርት እኮ ኢንዶውመንት ነው” የሚለው መልስም ትርፉ መልሶ ለሌላ ልማት የሚውል ነው ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ በግልፅ ኦዲት ካለመደረግ ጋር የሚያገናኘው ነገር በበኩሌ አይገባኝም፡፡

የኢንዶውመንቶቹን ባለቤትነት በተመለከተ የኢፈርት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአንድ ወቅት  ‘ኢፈርት በተዘዋዋሪ የትግራይ ህዝብ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ:: ‘በቀጥታስ ባለቤቱ የማን ነው?’ የሚለው እስከዛሬ ሚስጥር እንደሆነ አለ፡፡ ለጊዜው በግልፅ ወደ ተነገረን ተዘዋዋሪው ባለቤት የትግራይ ህዝብ እና የኢፈርት መስተጋብር ስንሄድ ኢፈርትን የሚያክል የፋብሪካ ባህር በትግራይ ብቻ እንዲንጣለል ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ማለፍ አይቻልም፡፡ ህወሃት እንደሚለው ኢፈርት እና ደጀና በትግራይ የከተሙት  የትግራይ ህዝብ ወኪል የሆነው ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያፈራውን ገንዘብ ለቆመለት ህዝብ ልማት ማዋል ስላለበት ነው፡፡እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ አንደኛው ለህዝብ ነፃነት የታገለው ህወሃት ምን ሰርቶ ይህን ያህል ገንዘብ አፈሰ? ጠመንጃ ተሸክሞ መባተልን የሚፈልገው የትጥቅ ትግል ሲራራ ንግድ አይደለምና ጥሪት አስቋጥሮ የኩባንያ ባህር ማቋቋም ያስቻለውስ እንዴት ነው? ገንዘቡ በትጥቅ ትግል ወቅት የተገኘነው ከተባለስ የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው በትግራይ ብቻ አልነበረምና ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ኢፈርት ያሉ ባለግዙፍ ኢንዶውመንቶች ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

የትግሬነት እና ህወሃትነት ልዩነት ትርክት ሳንካዎች

በሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንደ የትግራይ ህዝብ እና የህወሃት መስተጋብር ያለ ግራ አጋቢ፣ ብዙ እንደማነጋገሩ ፈር የያዘ መልስ ያልተገኘለት፣ለትንታኔ አስቸጋሪ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ህወሃት የኢህአዴግ ልብ ሆኖ ሃገሪቱን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሲዘውር ከፊት የሚያሰልፋቸው ዋና ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች  ከትግራይ የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ነገር ህወሃት ለሁለት ጥቅም ያውለዋል፡፡ አንደኛው የወንዙን ልጆች በወሳኝ ቦታዎች ኮልኩሎ ከውልደቱ ጀምሮ የተጣባውን የዘረኝነት ዝንባሌ ያፀናበታል፡፡ በሁለተኛ እና በዋነኝነት የትግራይን ህዝብ ደጀን ለማድረግ ልቡን ማግኛ መንገድ አድርጎ ያየዋል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለተመለከተ ለህወሃት ሁለቱም የተሳኩለት ይመስላል፡፡ለዚህ ማሳያው የህወሃት የሃረግ መዘዛ ፖለቲካ ከእርሱ አልፎ በመላ ሃገሪቱ ማርበቡ ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ የመተባበርም ሆነ ያለመተባበር፣ የመተማመንም ሆነ የመጠራጠር ምንጩ ሃረግ መማዘዝ ሆኗል፡፡ይህ በአንድ እናት ሃገር ልጆች መሃከል ከፍተኛ ያለመተማመን አምጥቷል፡፡ ሌላው ህዝብ እርስ በርሱ በጎሪጥ የሚተያይ ተጠራጣሪ ሲሆን የትግራይን ህዝብ ደግሞ የአፋኙ የህወሃት ጠበቃ አድርጎ የመፍራት አዝማሚያ ይታያል፡፡ይሄኔ ከላይ የተጠቀሰው የህወሃት እራሱን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እና ያው አድሮጎ የማቅረቡ አላማ ይሰምራል፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ጋር አንድ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ምንጩ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡በላይኛው የውትድርና ማዕረግ  ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከትግራይ የወጡ ሰዎች መያዙ፤ በሲቪሉ ክንፍም ቢሆን ለረዥም ጊዜ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትነት፣የሃገር ደህንነት ኤጀንሲ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣በስመ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመካሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን ማሾሩ፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር ከዝቅተኛ  እስከ ከፍተኛ የሃፊነት ቦታ የትግራይ ተወላጆች መበራከት፣ይህ ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሲወገዝ አለመታየት ለተመልካች ትግሬን እና ህ.ወ.ሃ.ትን አንድና ያው አድርጎ ያይ ዘንድ ይገፋዋል፡፡አሁን ሃገራችን በምትመራበት የዘውግ ፌደራሊዝም ሁኔታ ህ.ወ.ሃ.ት ድርና ማግ ሆኖ መምራት የሚችለው  የትግራይ ክልልን ብቻ መሆን ሲገባው የህ.ወ.ሃ.ት ሃያል ህልውና በአዲስ አበባም መስተዳድር ቢሮዎችም ሆነ አዲስ አበባ በከተመው የፌደራል መንግስትም ሚታይ የመሆኑ አደገኛ አካሄድ ለህወሃት መራሹ ኢህዴግ የታየው አይመስልም፡፡ባለሃብትነቱም ቢሆን ለሁሉም ባይሆንም ለትግራዊያኑ ብዙ ጊዜ የማይወስድ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡

ከትግራይ የሆኑ ዜጎች በስልጣን እና በሃብት ማማ ላይ በርከት ብሎ መታየት በተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚታይበትን መንገድ በሰፊው ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡መጠኑ ቢለያይም ትግሬ ሁሉ ህወሃትን ይደግፋል፤ትግሬ ሆኖ ከልቡ የህወሃትን ሁለንተናዊ የበላይነት ማብቃት የሚፈልግ ማግኘት አይቻልም የሚለው ሙግት ነው፡፡በዚህኛው ወገን ያሉ አሳቢዎች ክርክራቸውን የሚያጠናክሩት እስከዛሬ በትግራይ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶ አለማወቁን ነው፡፡ ተከራካሪዎቹ በተጨማሪ የሚያነሱት ነጥብ ከትግራይ የሚነሱ የህወሃት ተቃዋሚዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች እንደ ኢፈርት እና የወልቃይት ጥያቄን የተመለከተ ከህወሃት የተለያ አቋም ለማንፀባረቅ ይቸገራሉ የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የቆሙ ተከራካሪዎች ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ ተለያይተው መታየት እንዳለባቸው አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡እነዚህኞቹ ለክርክራቸው ማጥበቂያ የሚያነሱት ሃሳብ የትግራይ ህዝብም የህወሃት ብልሹ አሰራር ሰለባ መሆን፣ሌላ አማራጭ ሃሳብ መነፈግ እና በአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ መጠለፍ፣የአብዛኛውን የትግራይ ህዝብ የድህነት ኑሮ ወዘተ ነው፡፡

የትግራይን ህዝብ እና የህወሃትን አንድነት ልዩነት በተመለከተ የሚነሱት እነዚህ ጎራዎች በየፊናቸው ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎችን አስከትለው ሲያሟግቱ የኖሩ ቢሆኑም ሁለተኛው ማለትም የትግራይን ህዝብ እና ህወሃትን ለይተን እንይ የሚለው ክርክር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡በበኩሌ የዚህ ክርክር ደጋፊዎች መመናመን አብሮነታችንን የሚፈትን፣ የትግራይን ህዝብ ስጋት ላይ የሚጥል አሳሳቢ ነገር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ጥፋት የትግራይ ህዝብም አድርጎ የማየቱ ነገር  በተቻለ ፍጥነት መቀየር ያለበት ነገር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛውን ድርሻ መውሰድ ያለበት ደግሞ ራሱ የትግራይ ህዝብ ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ ምን ይጠበቃል?

ህወሃት እርሱ በስልጣን ሰገነት ላይ ከታጣ ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ እሳት ሆኖ እንደሚበላው ያስፈራራል፡፡  ቀላል የማይባለው ትግራዊም ይህን ተቀብሎ የህወሃት ወንበር የተነቃነቀ በመሰለ ቁጥር ስጋት ይወርሰዋል፡፡ይህን የአብዛኛው ትግራዊ ስጋት የሚረዳው ሌላው የሃገራችን ህዝብ ትግራዊያንን የግፈኛው ህወሃት ወንበር ጠበቃ አድርጎ ያስብና የህወሃት የግፉ ማህበርተኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ይህ ህ.ወ.ሃ.ት ታጥቆ የሰራበት እና ስኬታማ የሆነ የሚመስልበት ፈለግ ነው፡፡ ይህ ነገር ግን መቆም አለበት፡፡ ነገሩን ለመቀየር ደግሞ የትግራይ ህዝብ ማሰብ ያለበት የዚህን ሁሉ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ መነሻው የህወሃት ‘ከሌለሁ የላችሁም’ ስብከት ነው፡፡ ይህንን መመርመሩም ደግ ነው፡፡ የምርምሩ መነሻ ‘ህወሃት ሳይኖር ትግሬ አልነበረም ወይ?’ ብሎ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ሲሆን መልሱ ትግሬ ከህወሃት በፊት ነበረ ነው፡፡ ትግሬ ከህወሃት በፊት ከነበረ ዛሬ እኔ ከሌለሁ የላችሁም የሚለው የህወሃት ዜማ እንዴት መጣ የሚለውን ማስከተልም ተገቢ ነው፡፡የዚህ ዜማ መነሻው ብልጣብልጡ ህወሃት በመላው የትግራይ ህዝብ ስም ግን ለጥቂት ትግሬዎች የሰራው/የሚሰራው አድሎ እና ዘረኝነት ነው፡፡እንደ አሸን ፈልተው ትግራይ የከተሙ የኢፈርት እና ደጀና ኢንዲውመንት ፋብሪካዎች፣በሁሉ ቦታ ብቅ የሚሉ የትግሬ ሹማምንት፣የትግሬ ብቻ የጦር ጀኔራሎች፣ቱጃር ለመሆን የሳምንት እድሜ የሚበዛባቸው ትግራዊ ባለሃብቶች መበራከት ወደ ትግራዊያን  ያጋደለው የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል ማሳያዎች ናቸው፡፡ባልበላው እዳ ላለመጠየቅ የሚወድ ትግሬ ሁሉ ይህን አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን ማውገዝም አለበት፡፡

ወደዚህ ልቦና ለመምጣት ሰፊው የትግራይ ህዝብ ራሱን በሌላው ኢትዮጵያዊ ጫማ ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ ‘እኔ ትግሬ ባልሆን ኖሮ ይህን ጉዳይ እንዴት አየው ነበር’ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር መለስ እና ደቀመዛሙርቶቻቸው ትግሬነታቸው ቀርቶ አፋር ቢሆኑና ኢፈርትን እና ደጀናን የመሰሉ የልማት ተቋማት አፋር  ብቻ እንዲከቱ አድርገው፤ በአፋር አለቆች እንዲዘወሩ ቢያደርጉ፤ ይህ ሳያንስ ደግሞ የአፋር ህዝብ ለእንዲህ ያለው አስተዳደር እድሜ ሲለምን ባየው የሚሰማኝ ምንድን ነው ማለት ያስፈልጋል፡፡ከስልጣን የማይወርዱ የአፋር የመንደር ልጆች የራሳቸው ስልጣን ላይ ሙጥኝ ማለት ሳያንስ የአፋር ባለሃብቶችን የመፍጠር ፕሮጀክት ቀርፀው ሌላውን ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ ባይትዋር ቢያደርጉ ምን ይሰማኝ ነበር? የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ተብለው በፌደራል ወንበር የተቀመጡት ሰውየ የትግራይን ክልል የኢንዱስትሪ ዞን ለማድረግ እቅድ አውጥተው ነበር ተብሎ ከገዛ ባለቤታቸው ሲነገር መስማት ትግራዊ ላልሆነው ሰፊ ህዝብ ደስ የሚያሰኝ ትርጉም አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ አሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ስሜት ለመረዳት ይበጃል፡፡

በግሌ ከትግራዊ ወዳጆቼ እና ጓደኞቼ ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ በአብዛኛው የሚገጥመኝ ክርክር ‘ኢፈርት ትግራይ መከተሙ ለሰፊው ህዝብ ምንም የፈጠረው ነገር የለም፡፡ የፋብሪካዎቹ ባለቤት የህወሃት ባለስልጣኖች እና ዘመድ አዝማዶች ናቸው’ የሚል ነው፡፡ ይህም ግማሽ እውነት ነው፡፡ የእነዚህ ኢንዶውመንቶች ተጠራርቶ ትግራይ ላይ መከተም ለአካባቢው ሰዎች ቢያንስ የስራ እድል መፍጠሩ በሰፊው ትግራዊ መካድ የለበትም፡፡በቀጥታ የስራዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ለከተሞች ማደግ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የፋብሪካዎቹ መኖር የመግዛት ሃይል ያለው ተከፋይ ሰራተኛ በከተሞቹ እንዲኖር በማድረግ በቀጥታ በፋብሪካዎቹ ለመቀጠር ላልቻለው ህዝብ የንግድ እድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ሁሉ እድል ፋብሪካ በገፍ ላልተተከለለት ሌላው ኢትዮጵያዊ ያልተገኘ ነውና የእድገት ሁኔታ መዛባት ማምጣቱ ሃቅ ነው፡፡ ይህን ክዶ መነሳት የመግባቢያን ሰዓት ከማራቅ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

ሌላው ከትግራይ ወገኖቻችን የሚገጥመኝ ክርክር ‘የህወሃት ብልሹ አሰራር የትግራይን ህዝብም መድረሻ ያሳጣ ነገር ነው’ የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡የትግራይ ለፍቶ አዳሪ ድሃ ህዝብ በመዋጮ ብዛት ፍዳውን እንደሚያይ ከቦታው ከመጡ ሁሉ የሚነገር ነው፡፡ የሙስናው ነገር፣ሌላ ድምፅ እንዳይሰማ የማድረጉ አፈና ሁሉ በትግራይም ያለ ነው፡፡ ግር የሚያሰኘው ነገር ግን  የትግራይ ህዝብ አለበት የሚባለውን ግፍ በግልፅ ሲቃወም አይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ለዚህ አፈናው አያሰናዝርም የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ በበኩሌ ይህ አያሳምነኝም:: ምክንያቱም ሌላው ኢትዮጵያዊም የደረሰበትን ብልሹ አሰራር የሚያወግዘው መንግስት ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረለት ሳይሆን የደረሰበት ግፍ ብዛት አፈናውን ችላ ብሎ ድምፁን እንዲያሰማ ስለገፋው ነው፡፡ ስለዚህ የተበደለ ሁሉ በዳዮች ቀንበራቸውን እንዲያለዝቡ መጠየቁ ተፈፅሯዊ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ድምፁን አጥፍቶ አስተዳደራዊ በደሉን እንዲጋት ያደረገው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን መረጃ ከውስጥ አወቆች ለመስማት ጉጉት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ከትግራይ የሆኑ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ በደንብ ቢያስረዱን የትግራይ ህዝብ ያለበትን ችግር ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡

እንደ ህወሃት አገላለፅ በትግራይ የከተሙት  ኢንዶውመንት ተብየዎቹ አላማ ባመጡት ትርፍ ሌላ የልማት ተቋም በትግራይ መመስረት ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ  ልማት ልማትን እየወለደ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ለዚህ ምስክሩ በትግራይ የሚዋለዱት የፋብሪካዎች ብዛት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እንኳን በ850 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የጠርሙስ እና የብርጭቆ ፋብሪካ በእዛው ትግራይ ሊከትም እንደሆነ ትግራዊያን መኳንንት በቴሌቭዥን መስኮት እያወሩ ነበር፡፡ ከሳምት በፊት ደግሞ የመስፍን ኢንጅነሪንግ አልበቃ ብሎ  የምስራቅ አፍሪካን ገበያ ታሳቢ ያደረገ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዛው በትግራይ ስራ ሊጀምር እንደሆን ሰማን፡፡ይህን እያየን “ላለው ይጨመርለታል” ብለን እንድናልፍ ከታሰበ የማይሆን ነው፡፡

በአንፃሩ በሌላው የሃገራችን ክልል  የከባድ ፋብሪካዎች ተከላ ወሬ እንደ ሃምሌ ፀሃይ ተናፍቆም አይገኝ፡፡ ይህን እኔ ትግራዊ ሳልሆን ብሰማው ኖሮ ስሜቴ ዛሬ ትግሬ ሆኘ እንደሚሰማኝ ይሆን ነበር ወይ? ይህን የሚሰራው ህወሃት እድሜ ማጠርስ ያሳስበኝ ነበር ወይ?ይህን ጉልህ የተዛባ አሰራር እያዩ ዝም ማለትስ ይቻላል ወይ? የአንድ ሃገር ሰዎች ሆነን ሳለ ይህ ሲሳይ እኛጋ ያልደረሰው ለምንድን ነው ብሎ መሞገት ወንድም የሆነውን የትግራይ ህዝብ መጥላት ነው ወይ?  ብሎ መጠየቅ ደግ ነው፡፡ ህወሃቶችስ ይህን የፋብሪካ መንደር በትግራይ ብቻ እንዲከትም ያደረጉት ሊጠቅሙን ነው ሊጠቀሙብን? በዚህ ሁኔታ የምናገኘው ጥቅም ምን ያህል ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል፤ ብሎ መመርመር ከሃዲነት ሳይሆን ብልህነት ነው፡፡

የህወሃት ወንበር ሲነቀነቅ የትግራይን ህዝብ የሚያሳስበውን ያህል የብ.አ.ዴ.ን ህልውና የአማራን ህዝብ፣የኦ.ህ.ዴ.ድ በስልጣን ላይ መሰንበት የኦሮሞን ህዝብ፣የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በስልጣን ላይ መታየት የደቡብ ህዝብን፣የሶ.ህ.ዴ.ፓ እድሜ የሶማሌን ህዝብ ወዘተ ያሳስባል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡መልሱ ተቃራኒ ነው፡፡አብዛኛውን ትግራዊ የህወሃት ህልውና ክፉኛ ሲያሳስበው ሌላው ኢትዮጵያዊ እነዚህን ቆምንልህ የሚሉትን የገዥው ፓርቲ  አባል/አጋር  ፓርቲዎች እንደ የባርነት ወኪል አድርጎ ያያል፡፡ የእድሜያቸው ማጠር ከሚያስከፋው የሚያስደስተው በብዙ እጥፍ ይበዛል፡፡ለዚህ ከሰሞኑ በሃገራች ከተሞች ወከለናችኋል የሚሉዋቸውን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባል ፓርቲዎች ለማውገዝ ጎዳና የወጣው ህዝብ ብዛት ማሳያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብም እንደሌሎች ወንድሞቹ ቆምኩልህ እያለ ሌት ተቀን የሚሰብክ የሚያስፈራራውን ህወሃት ህፀፆች ለማውገዝ ማመንታት የለበትም፡፡ ‘ከሌሉ የለሁም’ የሚለውን አጓጉል አስተሳሰብ ትቶ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኖ ህወሃትን ታገስ ተመለስ ፣ካልሆነ ለሚችል ልቀቅ መለት አለበት፡፡ ይህንንም በአደባባይ ማሳየት አለበት፡፡ በተጨባጭ የሚታየውግን ሌላ ነው፡፡

ከላይ በትቂቱ ለማሳየት የተሞከረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል አንስቶ በምክንያት የሚሞግት ሰው ከአብዛኛው ትግራዊያን ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ‘እንዲህ የሚያስበው ትግሬን ስሚጠላ ነው’ የሚል ሲሆን ያጋጥማል፡፡ ይሄ ደመነፍሳዊነቱ የበዛ፣ ለመሞገት የሚያስችል የእውነት ስንቅ የማጣት የሚያመጣው የሽሽት መልስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሬ ወገኖቹን ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ጀማሪ፣እጅግ ሰው አክባሪ፣እንግዳ ተቀባይ ነውና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ህዝብ የሚወድበት እንጅ ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምክንያት የለውም፡፡ልክ ያልመሰለውን ነገር ሲጠይቅ ደግሞ ‘ይህን ያልከው እኛ ትግሬ ስለሆን’ ነው ማለት የጥላቻን መንገድ መጥረግ እንጅ ሌላ ጥቅም የለውም፡፡አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርቡ ‘የምታዩትን አድሎ እንዳላያችሁ እለፉ፤ያኔ እንደምትወዱን እናውቃለን’ ማለት አብሮነትን የሚፈትን አስቸጋሪ አቋም ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ አንፃር ይህ ሁሉ ሲጠበቅ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለትግራዊ ወንድሞቹ የሚያቀርበውን ጥያቄ የሚሰነዝረው ረጋ ብሎ፣ ጥላቻን አርቆ መሆን አለበት፡፡እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት የሆነውን መዛባት ሁሉ ያመጣው ህወሃት ከትግራይ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ተመካክሮ አይደለም፡፡ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ወደትግራይ የሚተመው ፋብሪካ ሁሉ ሲተከል ሰፊው የትግራይ ህዝብም እንደ እኛው በቴሌቭዥን ይሰማል እንጅ የሚያውቀው የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ‘ሌላውን ረስታችሁ ለእኔ ይህን አድርጉልኝ’ ብሎ አዞ ያስደረገው ነገርም አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከትግራዊ ወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር ይህን ሁሉ አስበን መሆን አለበት፡፡ ‘ህወሃት የትግራይን ህዝብ አይወክልም’ ከሚለው ሾላ በድፍን የሆነ ዘይቤ ወጥተን ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ነባራዊ ሃቆች ላይ ተመስርተን አፍረጥርጠን መነጋገር ያለብን ቢሆንም ንግግራችን ‘እኛ እና እነሱ’ የሚል ግድግዳ የተገነባበት መሆን የለበትም፡፡ ከዛ ይልቅ የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን እያሰብን፤ እንደቤተሰብ ውይይት ፍቅር እና መተሳሰብ ባልተለየው መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሁን እያነጋገረን ያለው ጉዳይ ረዥም ዘመን ከተጋራነው ወንድማማችነት የሚገዝፍ አይደለም፡፡ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ከስሜታዊነት የራቀ መሆን አለበት፡፡ ከስሜታችን ምክንያታችን መብለጥ አለበት፡፡ ይህ ካሆነ ዛሬ እንደቀልድ ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር  ነገ የምንፀፀትመበትን ጥፋት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ስለዚህ ጉዟችን ሁሉ ማስተዋል የተሞላበት መሆን አለበት፡፡ በፍቅር ከመነጋገር  እንጅ ከጥላቻ እና ከመጠፋፋት ትርፍ ያገኘ ህዝብ የለምና ንግግራችን ሁሉ ፍቅርን፣እርጋታን እና ምክንያታዊነትን የተሞላ መሆን አለበት፡፡ይህ ካልሆነ ህወሃትን እያገዝነው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡


For your comments and suggestion you can reach her via (e-mail meskiduye99@gmail.com )

“አዎ… የትግራይ/ሕወሃት የበላይነት አለ!”

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል። “የትግራይ የበላይነት የለም” በሚል ካቀረቧቸው ማስረጃዎች ውስጥ ሁለት ነጥቦች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። የመጀመሪያው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የአንድ ብሔር (ክልል) የበላይነትን አያስተናግድም የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የሕወሃት አባላት በኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሆነ ካቢኔ ውስጥ የስልጣን የበላይነት የላቸውም የሚል ነው። ነገር ግን፣ የአንድ ብሄር (ቡድን) የበላይነት መኖር-አለመኖር የሚለካው በመንግስታዊ ስርዓቱ ወይም በባለስልጣናት ብዛት አይደለም። በዚህ ፅሁፍ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ያቀረቧቸውን ሁለት መሰረታዊ የመከራከሪያ ሃሳቦችን ውድቅ በማድረግ “የትግራይ የበላይነት መኖሩን” በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

1ኛ) “የትግራይ የበላይነት” የሚረጋገጠው የስርዓቱ መስራች በመሆን ነው! 
በእርግጥ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በፌዴራሊዝም ስርዓቱ መሰረት እያንዳንዱ ክልል ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣን ስላለው የትግራይም ሆነ የሌላ ብሔር የበላይነት ሊኖር እንደማይችል ገልፀዋል፡-

“/የትግራይ የበላይነት/ የሚባለው አንዳንዱ የተዛባ አመለካከት ነው፣ አንዳንዱ ደግሞ ፈጠራ ነው። ከፌዴራል ጀምረህ የስርአቱን አወቃቀር ነው የምታየው፡፡ /አወቃቀሩ ካልፈቀደ/ “የበላይነት“ የሚፈልግም ካለ ስሜት ብቻ ፤ “የበላይነት አለ“ የሚልም የራሱ ግምት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ …/በኢህአዴግ/ አንዱ በደንብ የገምገምነው እሱን ነው፤ “የትግራይ የበላይነት“ የሚባል የለም ነው፡፡ …ሄደን ሄደን ስርእቱን እንየው ነው፡፡ ስርአቱ “የበላይነት“ እንዲኖር ይፈቅዳል ወይ? የምንፈቅድ አለን ወይ? የትግራይ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም፡፡ ይሄ ስርአት ካልፈረሰ በስተቀር ሊኖር አይችልም፡፡ ይሄ ስርአት የትግራይንም የሌላንም የበላይነት አያስተናግድም፡፡ …ሁሉም ድርጅት የራሱን ነው የሚያስተዳድረው፡፡ ህወሓት ኦሮሚያን ወይም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር አይችልም፡፡ ስርአቱ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ በክልል የበላይነት የሚባለው የሌለ አምጥቶ የመለጠፍ ፈጠራ ነው፡፡ ስርእቱ በዚህ መሰረት አልተገነባም አይሰራም፡፡” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል 

በእርግጥ በፌደራሊዝም ስርዓቱ መሰረት “የትግራይ የበላይነት አለ” ማለት አይቻልም። ነገር ግን፣ በኢትዮጲያ “የትግራይ የበላይነት” መኖርና አለመኖር የሚለካው የሕወሃት ፓርቲ በአማራ ወይም በኦሮሚያ ክልል ላይ ባለው የመቆጣጠር ወይም የማስተዳደር ስልጣን አይደለም። ምክንያቱም፣ በፖለቲካ ውስጥ “የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል የራሱ የሆነ መመዘኛ መስፈርት አለው።

የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት ራሱን የቻለ ፅንሰ-ሃሳብ ሲሆን እሱም “The Class Domination Theory of Power” ይባላል። በዚህ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት መኖርና አለመኖር የሚረጋገጠው ሌሎች የሚተዳደሩበትን ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ባለው ችሎታ ነው። “Vergara L.G.” (2013) የተባለው ምሁር የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነትን፤ “Domination by the few does not mean complete control, but rather the ability to set the terms under which other groups and classes must operate” በማለት ይገልፀዋል።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “የትግራይ የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ማረጋገጥ የሚቻለው መንግስታዊ ስርዓቱ “የአንድ ብሔር/ክልል የበላይነትን ይፈቅዳል ወይስ አይፈቅድም” በሚለው እሳቤ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌሎች ብሔሮችና ክልሎች የሚተዳደሩበትን ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ትልቁ ድርሻ የማን ነው በሚለው ነው። የአማራ እና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች የሚተዳደሩበትን በብሔር ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ከንድፈ-ሃሳብ እስከ ትግበራ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ሕወሃት ነው።

በእርግጥ ዶ/ር ደብረፅዮን እንዳሉት፣ መንግስታዊ ስርዓቱ ሕወሃት የአማራና ኦሮሚያ ክልልን እንዲያስተዳድር አይፈቅድም። ነገር ግን፣ የአማራ ሆነ የኦሮሚያ ክልል የሚተዳደሩበትን መንግስታዊ ስርዓት እና ደንብ የቀረፀው ሕውሃት ነው። ስለዚህ፣ የአማራ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል የሚመሩበትን ስርዓትና ደንብ በመወሰኑ ረገድ ካለው ችሎታ አንፃር “የትግራይ የበላይነት” ስለ መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም።

2ኛ) የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው በፖለቲካ ልሂቃን ነው!
ዶ/ር ደብረፅዮን “የትግራይ የበላይነት” አለመኖሩን ለማሳየት ያቀረቡት ሌላኛው የመከራከሪያ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ብዛት ነው። ከዚህ አንፃር፣ በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ ከፍተኛ የመወሰን ስልጣን ባላቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ የሕወሃት አባል የሆኑ ባለስልጣናት ብዛት ትንሽ መሆኑ ነው፡-

“በፖለቲካ ሃላፊነትም እኩልነት ነው የሚታየው፡፡ በኢህአዴግ ምክር ቤትም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል ውክልና ያላቸው፡፡ ለምሳሌ አንጋፋው ህወሓት ነው በሚል የተለየ ተጨማሪ ቁጥር አይሰጠውም፡፡ ብዙ ውሳኔ በሚወሰንበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ከ36ቱ ከሁላችንም እኩል ዘጠኝ ነው የተወከለው፡፡ አብዛኛው ያልተስማማበት ስለማያልፍ ማንም ድርጅት ዘጠኝ ሰው ይዞ የበላይነት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ….ለምሳሌ በካቢኔ አሁን 30 ነን፡፡ ድሮም ዛሬም ህወሓት ሶስት ሚኒስትር ብቻ እኮ ነው ያለው፤ ሶስት ይዘህ ደግሞ እንዴት ነው የተለየ ልታስወስን የምትችለው?” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

ነገር ግን፣ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና በጠ/ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ያሉት የሕወሃት አባል የሆኑ ባለስልጣናት ብዛት አነስተኛ መሆኑ የስልጣን የበላይነት አለመኖሩን አያሳይም። ምክንያቱም፣ የአንድ ቡድን/ብሔር የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው በባለስልጣናት ብዛት ሳይሆን በፖለቲካ ልሂቃን (political elites) አማካኝነት ነው። በዚህ መሰረት፣ የሕወሃት የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ ልሂቃን ከባለስልጣናት በሚያገኙትን አድሏዊ ድጋፍና ትብብር መንግስታዊ ስርዓቱ እና የባለስልጣናቱ ውሳኔ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማስቻል ነው። ፅንሰ-ሃሳቡን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ያግዘን ዘንድ በድጋሜ ከ“Vergara L.G.” (2013) ፅኁፍ ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፡-

“…political elites are defined as persons who, by virtue of their strategic locations in large or otherwise pivotal organizations and movements, are able to affect political outcomes regularly and substantially. The elites have power over the state, the civil organization of political power. Even though they could have conflicts with the mass, which certainly can affect political decisions from “top down” to “bottom up” the possession of multiples forms of capital (social, cultural, economic, politic, or any other social benefits derived from the preferential treatment and cooperation between individuals and groups) allows [them] to ensure their social reproduction as well as the cultural reproduction of the ruling class.” Elites, political elites and social change in modern societies; REVISTA DE SOCIOLOGÍA, Nº 28 (2013) pp. 31-49.

የፖለቲካ ልሂቃን በመንግስታዊ ስርዓቱ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱና በሲቭል ድርጅቶች ሥራና አሰራር ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ፣ በዚህም የአንድ ብሔር/ፓርቲ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችሉት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ ሲኖር ነው። በዚህ መሰረት፣ የስልጣን የበላይነት ባለው የፖለቲካ ቡድን የተለየ አድሏዊ ድጋፍና ትብብር የሚደረግላቸው ልሂቃን የፖለቲካ አጀንዳን በመቅረፅና በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል።

ከዚህ አንፃር፣ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅን መሰረት በማድረግና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር በሚል ሰበብ ለእስርና ስደት ከተዳረጉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ምን ያህሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው? ተቃዋሚ ይቅርና፣ በ2007 ዓ.ም በመቐለ ከተማ በተካሄደው የኢህአዴግ 10ኛ ጉባዔ ላይ በቀረበው ሪፖርት ላይ የጠባብነትና ትምክህተኝነት አመለካከት አንፀባርቀዋል በሚል ከስልጠና በኋላ የመስክ ክትትል ከተደረገባቸው ጀማሪና መካከለኛ የኢህአዴግ አመራሮች ውስጥ ምን ያህሉ የሕወሃት አባላት ናቸው? ከምርጫ 2002 – 2006 ዓ.ም በኋላ ባሉት አራት አመታት ብቻ፤ 19 ጋዜጠኞችን ለእስር፣ 60 ጋዜጠኞች ደግሞ ለስደት ሲዳርጉ ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ የትግራይ ብሔር ተወላጅ ናቸው? ሦስቱም ጥያቄዎች መልሱ ከሞላ-ጎደል “ዜሮ፥ ምንም” የሚል ነው።

ታዲያ የሕወሃት አባላት “በጠባብነት” እና “ትምክህተኝነት” በማይፈረጁበት፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን “ከግንቦት7 ወይም ኦነግ” ጋር በማገናኘት በፀረ-ሽብር ሕጉ በማይከሰሱበት፣ ያለ ፍርሃትና ስጋት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት በሚገልፁበት፣ የፖለቲካ አጀንዳውን በበላይነት በሚወስኑበት፣ …ወዘተ “የትግራይ የበላይነት የለም” ሊባል ነው። በአጠቃላይ፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ያቀረቧቸው ሁለት የመከራከሪያ ሃሳቦች ምክንያታዊና አሳማኝ አይደሉም። “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው መልሱ “አዎ…አለ!” ነው። እውነታው ይሄ ነው፡፡

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ምርጫ ሰም እና ወርቅ (በመስከረም አበራ)

አለም አቀፉ የጤና ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ “WHO” በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩትን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ሊቀመንበሩ ድርጎ  ሰሞኑን ሾሟል፡፡ ሰውየው የኢትዮጵያን ሁለመና እንደ እንዝርት ከሚያሾረው ህወሃት ዋና ሰዎች አንዱ  ናቸው፡፡ ይህ ከዕጩነታቸው እስከ ምረጡኝ ዘመቻቸው ሁሉን ሙሉ ሁሉን ዝግጁ ሳያደርግላቸው አልቀረም፡፡

ሰውየው ለጤናው ዘርፉ ቀጥተኛ ባለሙያ የሚያደርጋቸው የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ከጥቂት አመት በፊት ለኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትርነት በአቶ መለስ አቅራቢነት ታጭተው ለፓርላማ ሲቀርቡ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ዘንድ ለስፍራው ተገቢ የመሆናቸው ነገር ተነስቶ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ የእሳቸው መንገድ ብቻ እውነትም ህይወትም የሚመስላቸው የማይበገሩት አቶ መለስ ታዲያ ቆጣ ብለው “ቴድሮስ የተፈለገው ለጤና ሴክተሩ  አስተዳደራዊ ስራ እንዲሰራ እንጅ መርፌ እንዲወጋ አይደለም” ሲሉ ወዲህ ጓዳቸውን ወዲያ የወንዛቸውን ልጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን የሃገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሆኑ አደረጉ፡፡

የተሻለ ብቃትም ሆነ ለጤናው መስክ ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሁኔታ ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መሆናቸው ሰውየው በወቅቱ የሃገሪቱን ፖለቲካ በመሃል እጃቸው ይዘው በነበሩት መለስ ዜናዊ ፊት ሞገስ እንዳላቸው ከማስመስከር በቀር ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስም ከሞቱ በኋላ ሳይቀር “የምንወደው መለስ” እያሉ ሟች ሿሚ ሸላሚያቸውን በስስት ይጠራሉ፡፡ዶ/ር ቴድሮስ የሚወዷቸው መለስ አግባብነቱ እያጠያየቀም ቢሆን የወንዛቸውን ልጅ በጤና ሚኒስትርነት ሾመው ብቻ ዝም አላሉም፡፡ የሰሩ ያልሰሩት በጎ ነገር ሁሉ እየተነሳ ሲመሽ ሲነጋ እንዲወደሱ በጎ ፈቃዳቸውን ችረዋቸዋል፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩ ሰዓት የሚወደስ የሚሞገሰው የፓርቲው ሰው ሁሉ የእርሳቸውን እና የባለቤታቸውን የወ/ሮ አዜብን ይሁንታ ካላገኘ ውዳሴ ቅዳሴው ውሎ አያድርም፡፡ ለዚህ ምስክሩ ፖስተራቸው የአንድ ቀን እድሜ ሳያገኝ ከፒያሳ እንዲነሳ የተደረጉት ዶ/ር አርከበ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ወንበር መቀመጣቸው እንኳን በዛ ተብሎ ሲያነጋግሩ የኖሩት ዶ/ር ቴድሮስ ዛሬ የዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ለመሆን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ሁለት ተቃራኒ እይታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው  ‘ዶ/ር ቴድሮስ ጉድ የሆነ ብቃት ስላላቸው ብቻ ዓለም ልምድ ችሎታቸውን ክፉኛ ተመኝቶ በሰፊ ድምፅ መረጣቸው’ የሚለው የፓርቲያቸው ወዳጆች እና በአብዛኛው የወንዛቸው ልጆች እሳቤ ሲሆን ሁለተኛው ከዚህ በተቃራኒው የቆመ ነው፡፡ሁለተኛው እሳቤ ሰውየው በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃም ሆነ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ወቅት የፓርቲያቸው ጉዳይ ፈፃሚ ሆነው ብዙ ግፍ የሰሩ፣ ሲሰራ የተባበሩ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ አድሎ በዞረበት የማይዞረውን የጤና ጥበቃ አገልግሎት ለዛውም በአለም አቀፍ ደረጃ ለመምራት ወንበሩ የሚሰፋቸው፤ አድሎ ያልጎበኘው ስብዕናም የሚያንሳቸው ሰው ናቸው የሚል ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ሰውየው ይሰፋቸዋል በተባለው ወንበር ላይ ለመቀመጥ እንደቋመጡ ተሳክቶላቸዋል፡፡ 

እንደ እውነቱ ከሆነ የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ የስምረቱን ዋነኛ ምዕራፍ ያለፈው የአምባገነን መንጋ በሚርመሰመስበት የአፍሪካ ህብረት እጩነታቸው ተቀባይነት ያገኘ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማነትን እንዲቀዳጁ የወንዛቸው ልጆች የሚዘውሩት የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይነገራል፡፡ ከትልቁ አስተዋፅኦ ዋነኛው አፍሪካን ወክለው ሊወዳደሩ ያሰቡ ሌሎች ሶስት አፍሪካዊ  እጩዎች መንገዳቸው አልጋ ባልጋ እንዳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ተፅዕኖ ስለፈጠረ እንደሆነ ተንታኞች ይከራከራሉ፡፡ይሄ ደረጃ ለዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ በጣም ወሳኝ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት እድሉን አግኝቶ የማያውቀው የአፍሪካ አህጉር እጩ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በተጨማሪ በስመ አፍሪካዊ እጩ የፓርቲያቸው ደመኛ ኤርትራ ሳትቀር የሃምሳ አራቱን የአፍሪካ ሃገራት ድምፅ አፈፍ ለማድረግ ስለሚረዳቸው ነው፡፡በዚህ ላይ ሃገራችንን የሚዘውረው ፓርቲያቸው ሳይሰስት የሚያቀርብላቸው ለምረጡኝ ቅስቀሳ የሚሆን ምቹ ሁኔታ ሲደመር የቢልጌትስ ረብጣ ዶላር ለሌሎቹ ተፎካካሪዎቻቸው እንደሰማይ የራቀ፤ ለእርሳቸው ሙዝ እንደመላጥ የቀለለ ነገር ነው፡፡

ህወሃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ደጋፊ የፓርቲያቸው አባላት፣የወንዛቸው ልጆች   የዶ/ር ቴድሮስን መመረጥ በጥፍራቸው ቆመው የሚኙት ብቻ ሳይሆን በአንድ እግራቸው ቆመው የሚፀልዩበት ጉዳይ እንደሆነ ሲናገሩ ከቃላቸው፣ ሳይናገሩ ከአአድራጎታቸው መረዳት ቀላል ነው፡፡ ለዶ/ር ቴድሮስ የምርጫ ስኬት በሃገራችን መንግስት የተደረገው ከፍተኛ የማሻሻጥ ስራ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ ልማት ባንክ ዳይሬክተርነት ለተወዳደሩት በችሎታቸውም እንደ አብዛኖቹ ኢህኤደግ ባለስልጣናት እንደነገሩ ላልሆኑት አቶ ሶፊያን አህመድ ሲደረግ አላየንም፡፡ ይህ ለምን ሆነ፤የቴድሮስ መመረጥ ለእናት ፓርቲያቸው ህወሃት ምኑ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

ለጠንካራ ሰው ጠኔ ፈውስ

ዶ/ር ቴድሮስ ዋና የሆኑበት በስመ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የሚያሾረው ህወሃት ሁሉን በትከሻቸው ጥሎባቸው የነበረው ደንዳናው አምባገነን መለስ ዜናዊ ድንገት ወደማይቀረው ከሾለኩ በኋላ ፓርቲው ውቃቢ ርቆታል፡፡ ከ1993ቱ የፓርቲው ስንጥቃት ወዲህ ለረዥም ጊዜ በአቶ መለስ ጠንካራ መዳፍ ከመጨምደዱ የተነሳ በአንድ ሰው አድራጊ ፈጣሪነት መመራትን፤ የሰውን ልጅ እንደመለኮት የማየት ነገር በህወሃትም ሆነ በኢህአዴግ ውስጥ እንደ ትክክለኛ ነገር ይወሰዳል፡፡ በመሰረቱ ለዲሞክራሲ ተራራውን ቧጠጥኩ፣ በእሾህ አሜከላ፤ በጠጠር በጭንጫ አስራ ሰባት አመት ተራመድኩ የሚል ፓርቲ የፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ባንዲራ የሆነውን አምባገነን የማንገስ ኋላ ቀርነት እንደ ደህና ሙያ ማውራት አልነበረበትም፡፡ ያለ አምባገነን ሃገርን ጥሩ አድርጎ መምራት እንደሚቻል መረዳት ለዲሞክራሲ ሞቼ ተነስቼ ለሚል አካል ቀርቶ ለማንም ሰው ከባድ አይደለም፡፡

ወደው ይሁን ከአቶ መለስ ጋር የመጋፋቱን አቀበት አስቸጋሪነት ተረድተው  የህወሃትም ሆነ የኢህአዴግ መኳንንት አቶ መለስን “እንዳልክ” ማለቱን መርጠው ኖረዋል፡፡ በዚህ መሃል ሳይታሰብ የመጣው ማንንም የማይፈራው ሞት ከአምላክ የሚያስተካክሉትን ሰው ይዞት እብስ ሲል (ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ትዝ እንዳይላቸው አድርገው ረስተዋልና) ሃሳባቸውን የሚጥሉበት፣እንደ ልዕለ-ሰብ የሚመኩበት በሟቹ እግር የሚተካ ተመላኪ ይሻሉ፡፡ ከሰው ፍጥረት የሚስተካከለው እንደሌለ ተናግረው ከማይጠግቡለት የአምባገነኑ መለስ “የአዋቂነት” ሙላት የሚተካከል መፅናኛ ከህወሃት ወገን እንዲወጣ ያማትራሉ፡፡ አምባገነንነት ከባለራዕይነት፣ እብሪት ከአዋቂነት፣ ሴረኝነት ክህደት ሳይቀር ከልቅና የተፃፈለትን መለስን ለመተካት ከህወሃት መንደር ፈልጎ ማግኘቱ ቢቸግርም የበለጠው ችግር ሌላ ነው፡፡

ዘላለም ህወሃትን በዋናው ወንበር ማስቀመጡን መታገስ እየከበደው በመጣው የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ህወሃቱ አቶ መለስ በተነሱበት የእውነት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ላይ ሌላ የህወሃት ሰው ማስቀመጡ ነው እንደ ጉተና ከባዱ ነገር፡፡ይሄን ነገር ማድረጉ ወከልነው የሚሉት ህዝብ ዘንድ ሞገስ የሌላቸውን ብአዴን እና ኦህዴዶች ፊትም ሳያጠቁር አይቀርም፡፡ ይህን እንቅፋት ለመቀነስ ከብአዴን፣ኦህዴድ እና አጋር ተብየዎች ይልቅ የህወሃት ሰዎችን በዓለም መድረክ ሳይቀር ክፉኛ የመፈለግ ልቅና “በተግባር” ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በእጅም በእግርም የሞት የሽረት ሩጫ አድርጎ ዶ/ር ቴድሮስን ለአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ማስመረጡ ጥቅሙ ለሰውየው ብቻ ሳይሆን ለእናት ፓርቲያቸውም የሚተቅመው ለዚህ ነው፡፡

ህወሃቶች  በኢህአዴግ ከታቀፉ ፓርቲዎች ሁሉ ራሳቸውን በፖለቲካ የበሰሉ፤ ይገዙ ይነዱ ዘንድ የተገባ አድርገው እንደሚያስቡ በአቶ ገብሩ አስራት መፅሃፍ ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተቀምጧል፡፡ ተዘዋዋሪው ብዙ ቢሆንም በቀጥታ የተቀመጠው ግን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ህወሃቶች እየተሰበሰቡ ስለጉዳዩ ሲፈጩ ሲሰልቁ ሌሎች የኢህአዴግ አባል/አጋር ፓርቲዎች ያልተገኙት በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ህወሃቶች ስለሆኑ በመጀመሪያ እነሱው ነገሩን እንዲያብላሉት፤በውሳኔው ላይም ከፍተኛ ሚና መጫዎት ያለባቸው እነዚህ “ምጡቅ ተገንዛቢዎች” እንዲሆኑ ታስቦ እንደነበረ በመፅሃፉ ገፅ፡206 ላይ ተገልጧል፡፡ ሌላው አጋጣሚ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ህወሃት ብቻ የናኘበትን ምክንያት ሲጠየቁ ነገሩ የችሎታ ጉዳይ እንደሆነ የገለፁበት አስገራሚ ንግግር ነው፡፡ ሶስተኛ ለመጨመር ያህል እስከ ቅርብ ጊዜ የህወሃት መኳንንት የጦር ጀነራልነቱን ቦታ የተቆጣጠሩበትን ሚስጥር ሲያስረዱ ህወሃቶች ያላቸውን “ምጡቅ የውትድርና እውቀት እና ልምድ” በመጥቀስ፤ ይህንኑ “እውቀት ጢቅነታቸውን” ለሌሎች እስኪያካፍሉ ድረስ ብቻ በጀነራልነቱ ላይ እንደበረከቱ ፈርጠም ብለው ሲያስረዱ ትናንት ስልጣኑ ላይ የወጡ እንጅ ሃያ ምናምን አመት የኖሩ አይመስሉም፡፡

እስካሁን በስልጣ ላይ ተወዝተው ለመኖራቸው፤ ወደፊትም ለሰባት ጉልበታቸው የሚመኙትን ስልጣን በእጃቸው ለማቆየት ህወሃቶች እንደ ማሳመኛ የሚያነሱት በፖለቲካ ውትድርናው “አለን” የሚሉትን ልቅናቸውን ነው፡፡ የሰሞኑ የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ ታዲያ በመለስ እግር ይተኩት ዘንድ ሲዋትቱለት የኖሩትን የጠንካራ ሰው ሃራራቸውን ተንፈስ ለማድረግ፤ የፓርቲያቸውን አባላት ሃገር ቀርቶ ዓለምን ለመምራት የመመረጥ ምጡቅነት ለተገዳዳሪዎቻቸው ለማሳየት እንደጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል፡፡በጓዶቻቸው ዘንድ ምጡቅነታቸው ብቻ እንዳስመረጣቸው ሆድ ሲየውቅ የሆነ ከበሮ የሚደለቅላቸው ዶ/ር ቴድሮስ “WHO”ን መርተው እስኪመለሱ (ህወሃት ሌላ ክፉ እጣ ካልገጠመው) በስመ ኢህአዴግ ሃገሪቱ በአቶ ኃይለማርያም እንደነገሩ እያዘገመች እንድትቆይ አድርጎ ለዶ/ር ቴድሮስ የእውነተኛ ጠቅላይነቱን ገፀ-በረከት እነሆ ለማለት የሚጠይቀው ቀላል ነገር “WHO”ን የሚያክል ታላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅትን የመሩበትን ምጥቀታቸው በኢቢሲ ሰሚን እስኪያቅረው መተረክ ብቻ ነው፡፡

ለቤት ጣጣ መላ

የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ ህወሃትን አገኘው ለሚባለው “ለባዕድ” ጮክ ብሎ የማይነገር ውስጠ-ፓርቲ መጎሻመጥ እንደ አንዳች ማስታገሻ እድል ተደርጎ መወሰዱም አይቀርም- በመለስ ራዕይ አስፈፃሚ ነን ባዮች፡፡ልብ ብሎ ላደመጠ በ1993ቱ ስንጥቃት ተባራሪ የህወሃት መኳንንቶች ፅሁፍ ንግግር ሳይቀር (በማወቅ ሳይሆን ባለማወቅ፣ በቀጥታ ሳይሆን በዘወርዋራ) እንደሚገለፀው የህወሃት ከኳንንት “መለስ ራዕይ አይቷል አላየም”፣ “የህዝባዊ አመፁምክንያት ውስጥ ነው ከውጭ” በሚልም ሆነ በሌላ ምክንያት ለሁለት ጎራ ተከፍለው እንደሚቆራቆሱ ማወቅ አይከብድም፡፡ “የምንወደው መለስ” ሲሉ ሟቹን አለቃቸውን የሚያሞካሹት ዶ/ር ቴድሮስ ምድባቸው ‘መለስ ራዕይ አይቷል እኛ ደግሞ እሱን ውልፊት ሳይል እናስፈፅማለን’ ከሚሉት ወገን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ሰውየው ከሰሞኑ በለስ ቀንቷቸው ወደ አለም ዓቀፍ ተቋም ዋናነት ወንበር መውጣት በምዕራባዊያን ዘነድ የቅቡልነት ምልክት እንደሆነ ታስቦ ለተቀናቃኝ የዘመድ ፀበኞቻቸው በመጠኑም ቢሆን የመለስ ራዕይ ሰባኪዎች የበላይነታቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ አድርገው መውሰዳቸው አይቀርም፡፡     
  
ከምዕራባዊያን ጋር ፍቅር እንደገና

በስተመጨረሻው “ጥሩ” አምባገነን የወጣቸው አቶ መለስ የዛሬ 27 አመት በተወለዱ በ33 አመታቸው ወደ ስልጣን ሲወጡ በምዕራባዊያን መሪዎች ዘንድ “ወጣት ዲሞክራት መሪ” የሚል ችኩል ሊሻን ተለጥፎላቸው ነበር፡፡ ማድበስበስ፣ ማስመሰል፣ ፍርድ መገምደል መለያቸው የሆነው ምዕራባዊያን መሪዎች እንደ ድሮው ማሞካሸታቸውን ቢቀንሱም አሁንም ኢህአዴግ የሚፈልገውን በውሸት ሳቃቸው አጅበው መናገራቸውን አልተውም፡፡ እንደ ትጥቅ ትግል የሚሞክረውን በጥይት ድምፅ የታጀበ፣በእስር ስደት ያረገን  ምርጫ “ውጤቱ እንጂ ሂደቱ ደግ ነበር” ከማለት አፋቸውን ሞልተው “ዲሞክራሲያዊ ነው” እስከማለት ፍርድ ሲገመድሉ ያጋጥማል፡፡

ምዕራባዊያኑ መንግስታት እንዲህ የተውሸለሸለ አቋም ቢኖራቸውም በእነሱው የሚደጎሙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከኢህአዴግ ጋር ቢያንስ በአመት አንዴ (አመታዊ ሪፖርታቸውን ሲያወጡ) መነታረካቸው አይቀርም፡፡  እነዚህ ተቋማት “እንከን አልቦ ነኝ” ለማለት የሚሞክረውን የኢህአዴግን መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዝ ኋላቀርነት አብጠርጥረው ገበያ የሚያወጡ በመሆናቸው በአለም መድረክ የነበረውን የፖለቲካ ኪሎ በትንሹም ቢሆን ሳይቀንሱበት፤ ከየአቅጣጫው ማፈስ የለመደውን ዶላር ሳያመናምኑበት አልቀሩም፡፡

ሁሌ ጥግ የሚፈልገው ኢህአዴግ ታዲያ የምዕራባዊያንን እጅ ማጠር፣ውዳሴ መቀነስ ተከትሎ የተሰማውን ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ቻይናን እንደ ምትክ ካፖርት መልበሱ ብቻ ስላላስታገሰለት የአፍሪካ ሃገራትን ደርቦ “ሰው በሰው ይተካልን” ማዜም ይፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ በጣም ይመካበት የነበረው በአፍሪካ ቀንድ በተለይ በሶማሌ አለኝ የሚለው የሠላም አለቅነት ሚና ከሶማሌ አዲሱ ፕሬዚደንት ፋርማጆ መመረጥ ወዲህም ሆነ ቀድም ብሎ እያጣ እንደመጣ ነው ሁኔታዎች የሚያሳዩት፡፡የኢትዮጵያ መንግስት ከፋርማጆ መመረጥ ትቂት ቀደም ብሎ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ጦሩን ከሱማሌ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ወደ ሳዑዲ በተጓዙ ሰዓት ፋርማጆን ሪያድ ላይ አስጠርተው እንዳናገሩ፤ ፋርማጆም በአሜሪካ የሚደገፍ ሃገርኛ ጠንካራ ጦር ለሃገራቸው እንደሚሹ እንደተናገሩ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ ነገሩ ወትሮም  በሃገራቸው ፖለቲካ የኢትዮጵያን አድራጊ ፈጣሪነት የማይወዱት አዲሱ የሶማሌ ፕሬዚደንት ኢትዮጵያን ገሸሽ በማድረጉ ላይ እንዳመረሩ ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ከምዕራባዊያን ጋር አቆራኝቶኛል ሲል የሚመካበትን የፀረ-ሽብር ዘመቻ ፊት አውራሪነት፣ የምስራቅ አፍሪካ የሰላም አለቅነት ክር እያሰለለው መጥቷል፡፡ ነገሩ ሲብስ ኢህአዴግ መራሹ የሃገራችን መንግስት በሁለቱ ሱዳኖች ላይ እንዲኖረው የሚፈልገውን የሽምግልና ሞገስ እያጣ በምትኩ በሳልቫኬር በኩል በተለይ በጥርጣሬ እየታየ መምጣት እና ሳልቫኬር ከኢትዮጵያ ይልቅ ለጋንዳ ያላቸው እምነት እየበለጠ መምጣቱ ተደማምሮ መታየት የሚወደውን ኢህአዴግን መታያ ስፍራ አሳጥቶታል፡፡

ከዚህ ሁሉ የተነሳ በምዕራባዊያን ዘንድ ተፈላጊነቱ መቀዛቀዙ የሚገባው ህወሃት/ኢህአዴግ ዛሬ ዋና ሰው ዶ/ር ቴድሮስ በምዕራባዊያን ለሚዘወር አለማቀፍ ተቋም ዋና መሆናቸው ትልቅ ባይሆንም ትንሹን አተልቆ ማየት የሚፈልገው ኢህአዴግ እንደመፅናኛ ሊወስደው፤እየሰለለ የመጣው ከምእራባዊያን ጋር ያስተሳሰረው ገመድ ማፋፊያ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል፡፡

“ነብይ በሃገሩ አይከበርም” እንደማለት?

የዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መመረጥ ጉዳይ የበሰለው ሰውየው አፍሪካን ወክለው የሚወዳደሩ ብቸኛ እጩ የመሆኑናቸውን ነገር የሃገራቸው መንግስት አይገቡ ገብቶ እንዲሰምርላቸው ሲያደርግ ነው፡፡ ህወሃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ሲያደርግ መታየት ያለበት (ዞሮ ዞሮ ወደ ህወሃት የስነ-ልቦና ጉዳይ የሚወስደን)  ነገር “ለምን ዶ/ር ቴድሮስን?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም አቀፉ ተቋም መሪነት በሚወዳደሩበት ወቅት የሃገራችን የጤና ሚኒስትር አልነበሩም፡፡ ሰውየው ውድድራቸውን በሚያጧጡፉበት ወቅት የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይመራ የነበረው በዶ/ር ከሰተብርሃን ከዛም ፕ/ሮ ይፍሩ  ብርሃኑ ነው፡፡ በተለይ ፕ/ሮ ይፍሩ ከበድያለ የትምህርት ዝግጅት እና ሰፋ ያለ በጤናው ዘርፍ ምርምር የመስራት፣የጥናት ወረቀቶችን በማሳተም፣የጤና ፖሊስ አቅጣጫዎችን የማሳየቱ ጠብሰቅ ያለ ልምድ ያላቸው፣በቁጥር ትቂት የሆነውን የህክምና የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ፣በሰው ፊት ቢቀርቡም የማያሳፍሩ ምሁር ናቸው፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መማሪያ ሆስፒታል በሚያስተምሩበት ወቅት በብዙ ታካሚዎች ዘንድ የሚወደዱ፣ የግል የህክምና ክሊኒክ መክፈት እንኳን የማይፈልጉ በምትኩ ከማስተማር የተረፈውን ጊዜያቸውን ሁሉ በዚሁ ሆስፒታል ሆነው ደሃውን ህዝብ የማገልገልን መልካም እድል መርጠው የነበሩ ሰው ናቸው፡፡  ሰውየው ከህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ጋር የመስራት ፍላጎቱ ካላቸው አይቀር ቀደም ብለው ወደ ሴክተሩ መምጣት የሚገባቸው ሰው ነበሩ፡፡

ፕ/ር ይፍሩ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱ አስተዳደራዊ ስራ እንግዳ ስለሆኑ ለ WHO መሪነት አልታጩም ቢባል እንኳን ከእርሳቸው ቀደም ብለው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መስሪያቤቱን የመሩት ዶ/ር ከሰተብርሃን ለውድድሩ ለመታጨት ምን አነሳቸው? ዶ/ር ከሰተብርሃን ከዶ/ር ቴድሮስ በተሻለ በጤናው መስክ ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰው መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ኢትዮጵያን የመወከል ነገር ከሆነ እሳቸውም ቢያንስ በሃገር ውስጥ ከቴድሮስ ጋር መወዳደር ነበረባቸው፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የመጨረሻው እጩ የሆኑት በሃገር ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች መካከል የተሻለውን ለመምረጥ ውድድር ተደርጎ መሆን ነበረበት፡፡ ሆኖም ዶ/ር ቴድሮስ ብድግ ተደርገው ኢትዮጵያን ወካይ ብቸኛ ምጡቅ ሰው የተደረጉበት ስየማ መለኪያው ምን እንደሆነ፣እነማን መራጭ ሆነው፣ በምን መለኪያ ከማን ጋር ተወዳድረው የተደረገ እንደሆነ ስለማይታወቅ ያው ህወሃትነታቸው ከብዙ እውቀት ተቆጥሮላቸው ነው ለማለት ያስገድዳል፡፡

በህወሃቶች ዘንድ ምጡቅ እንደሆኑ የእውቀት ጢቅነታቸው ነገር በሰፊው የሚነገርላቸው ዶ/ር ቴድሮስ በተግባር ሲመዘኑ እንዴት እንደሆኑ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነታቸው ወቅት ስላደረጉት ክፉ በጎ ስራ በጥናት ተደግፈው የወጡ መረጃዎች ስላሉ እዚህ መተረክ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስርትርነታቸውም ወቅት እነ አክሊሉ ሃብተወልድን የመሰሉ ሰዎች ተቀምጠውበት የነበረው ወንበር በጣም ሰፍቷቸው እንደነበረ ማሳያው ብዙ ነው፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ ብቅ ብለው በነበረበት ወቅት ኦባማን ፎቶ ለማንሳት ሞባይላቸውን ወድረው ከጓዶቻቸው ለመቅደም ሲሳመጡ የሚያሳየው ፎቶ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ብዙ ይናገራል፡፡ በአረብ ሃገር ወገኖቻችን የት ወደቃችሁ የሚላቸው ጠፍቶ በነበረበት ሰዓት አንድ የረባ የሚመዘገብ ስራ ሰርተው እንዳላሳዩ ግልፅ ነው፡፡ በግብፅ ወንድሞቻችን ቢለዋ ሲያፏጭባቸው ዶ/ር ቴድሮስ ‘ቆይ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ላጣራ’ ሲሉ እቃ ወድቆ የተሰበረባቸውም ሳይመስሉ ነበር፡፡

የውጭጉዳይ ሚኒስትርነቱ ወንበር ከብዶ እንዳንገዳገዳቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና  ላለፈው ምርጫ ክርክር ቢጤ ሊያደርጉ በተገኙበት ወቅት በደንብ ተናግረውታል፡፡ ይህ የዶ/ር መረራ ንግግር በቦታው ሊከራከሩ የተገኙትን ዶ/ር ቴድሮስን ክፉኛ አስደንግጦ በራስ መተማመናቸውን የተፈታተነ፣ የወንዛቸውን ልጆች የህወሃት አባላትንም ክፉኛ እንዳስቆጣ ያስታውቅ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ብዙ በማይጨክንባቸውን ዶ/ር መረራ ላይ ጥርሱን የነከሰውም ያኔ ይመስለኛል፡፡ ህወሃቶች የዶ/ር ቴድሮስን ለወንበር ብቁ አይደሉም መባል የሚወስዱት  እንደ ህወሃትን የማዋረድ ሴራ እንጅ ያለ የነበረ የምርጫ ክርክር ወግ አይደለም፡፡ ስለሆነም ዶ/ር ቴድሮስን ለዚህ ቀርቶ ለሌላ (ለአለም አቀፍ መድረክ) መሆን እንደሚችሉ አሳይቶ ፣ የህወሃትን ስም ከፍ ከፍ ማድረግን ስለሚሹ በሃገሪቱ ሌላ ሰው የሌለ ይመስል ምንም አይነት ውድድር ሳይደረግ፣ ቴድሮስን አንጠልጥለው ለአምባገነኖች ማህበር (ለአፍሪካ ህብረት) አቅርበው በአንድ አፍ የአፍሪካ ወኪል አድርገው የፈለጉትን አገኙ፡፡ ይህ ሲሆን የዶ/ር መረራ ክርክርም ሆነ ሌሎች ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ሳንካ መረጃን ተንተርሰው የሚናገሩ አካላት “የሃገራቸውን ነብይ እንደማያከብሩ” አላዋቂዎች፣ባንዳዎች ተደርገው እንደሚቆጠሩለት ያስባል- በደስታ ሊሞት የደረሰው ህወሃት!               

ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!

ሁለት ቴዲዎች ባለፉት ሳምንታት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዋና መነጋገሪያ አጀንዳ ሆነው ሰንብተዋል። በእርግጥ ሁለቱም በየፊናቸው ስኬታማ ለመሆን በቅተዋል። ከዚያ በስተጀርባ ግን በሁለቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል የነበረው ውዝግብ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ብዙ ነገር ይጠቁማል።

በመጀመሪያ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሁለቱም ቴዲዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሁለቱም ወገኖች ለድጋፍና ተቃውሟቸው የራሳቸውን ምክንያቶች ዘርዝረዋል። ነገር ግን፣ ከሁለቱ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ሲነሱ የነበሩት ሃሳቦች በዋናነት “ኢትዮጲያ” በሚለው ጭብጥ ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ።

እንደ ማንኛውም እውቅ ሙዚቀኛ በተለይ “ኢትዮጲያ” በሚለው ነጠላ ዜማ እንደወጣ ሌላው ቴድሮስ (ፀጋዬ) የሰነዘረው ሂስና ትችት ከዘፈኑና ዘፋኙ አልፎ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን አሳዝኗል፥ አስቆጥቷል። ከዚያ በተረፈ፣ ዘፋኙ የለቀቀው አልበም ተደማጭነት እንዳያገኝ ወይም ለአድማጭ ተደራሽ እንዳይሆን “በገበያ ላይ መቅረብ የለበትም” የሚል ተቃውሞ አልገጠመውም። ከዚያ ይልቅ፣ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ትኩረታቸው “አርቲስቱ ከብዙሃንነት ይልቅ የአህዳዊ አንድነት አቀንቃኝ ነው” የሚል ነበር። በዚህ ምክንያት ከአርቲስቱ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ በኢትዮጲያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት – ኢብኮ (EBC) እንዳይቀርብ ታገደ። ስለ “ኢትዮጲያ” በመዝፈኑ አርቲስቱን “የአንድነት አቀንቃኝ ነው” በሚል ቃለ-ምልልሱ የሕዝብ ንብረት በሆነው ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይቀርብ ሲከለከል የፖለቲካችን ሕመም አገረሸ። በውሳኔው የቴዲ አፍሮ ደጋፊዎች ክፉኛ ሲቆጡ፣ ተቃዋሚዎቹ ደግሞ በጣም ተደሰቱ። 

የቴዲ አፍሮ ቃለ-ምልልስ በኢብኮ እንዳይተላለፍ በታገደበት ሳምንት ሌላኛው ቴድሮስ (ዶ/ር) “ኢትዮጲያን” ወክሎ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ሆኖ ለመመረጥ የመጨረሻውን ጥረት እያደረገ ነበር። በአንድ በኩል የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ዶ/ር ቴድሮስን በመደገፍ የዓለም-አቀፉ ድርጅት መሪ ሆኖ እንዲመረጥ ድጋፍና ቅስቀሳቸውን አጠናከረው ቀጠሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ውስጥ አብዛኞቹ በዶ/ር ቴድሮስ ላይ ተቃዉሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ከሁለቱም ወገኖች ምርጫው በሚካሄድበት ቦታ በአካል ተገኝተው ያሳዩት ድጋፍና ተቃውሞን እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ደጋፊዎች ለራሳቸው የብዙሃንነት አቀንቃኝ ሆነው የቴዲ አፍሮ አድናቂዎችን “የአንድነት አቀንቃኞች” እያሉ ሲያብጠለጥሏቸው ነበር። ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተርነት የሚደረገው ውድድር ሊጠናቀቅ ሲቃረብና በዶ/ር ቴድሮስ ላይ የሚካሄደው የተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲሄድ በአብዛኛው “የብዙሃንነት አቀንቃኝ” የነበሩት ደጋፊዎቹ ስለ አንድነት ማቀንቀን ጀመሩ። በዚህም “ዶ/ር ቴድሮስ እየተወዳደረ ያለው እንደ ግለሰብ ወይም መንግስት ሳይሆን ኢትዮጲያ እና አፍሪካን ወክሎ እንደመሆኑ ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ኢትዮጲያዊ ድጋፉን ሊቸራቸው ይገባል” የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀረቡ። ቀድሞ የአንድነት አቀንቃኝ የነበሩት አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ደግሞ “ስለ አንድነት ሲባል ዶ/ር ቴድሮስ ከፍተኛ አመራር ከሆኑበት የኢህአዴግ መንግስት ጋር ያለንን ቅራኔና ልዩነት መተው አይቻለንም” በሚል ተቃውሟቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በዚህም የኢትዮጲያ ፖለቲካ ሕመሙ በጣም እንደፀናበት መገንዘብ ይቻላል።

አብዛኞቹ የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጲያ አንድነት ይልቅ ብዙሃንነትን በማስቀደም የሁላችንም በሆነ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቃለ-ምልልሱ እንዳይተላለፍ አደረጉ። በተመሣሣይ፣ አብዛኞቹ የዶ/ር ቴድሮስ ተቃዋሚዎች ከአንድነት ይልቅ የፖለቲካ ልዩነትን በማስቀደም የዓለም-አቀፍ ድርጅት መሪ እንዳይሆን ተቃወሙ። ይሁን እንጂ፣ ሁለቱም ቴዲዎች በየፊናቸው ስኬታማ ሆነዋል። በሁለቱም አጋጣሚዎች ተነስታ የወደቀችው ኢትዮጲያ ናት። ኢትዮጲያ ውስጥ እየኖረ ስለ ሀገር አንድነት ሲዜም የሚቀፋቸው በአንድ ወገን፣ ስለ ኢትዮጲያ አንድነት እያዜሙ የኢትዮጲያን ተወካይ የሆነ ተወዳዳሪ የሚቃወሙ በሌላ ወገን ሆነው አንዱ ሌላውን ሲጠላና ሲያጥላላ በመሃል ግራ ተጋብታ መሄጃ የጠፋት ኢትዮጲያ ናት።

“ኢትዮጲያ” በሚለው አልበም ዙሪያ ከትችትና ተቃውሞ ባለፈ ቃለ-ምልልሱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ ቢታገድም ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በሥራው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። ስለዚህ፣ ቴድሮስ አሸንፏል! ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ዳይሬክተር ጄኔራል ለመሆን ያደረገው ውድድር ምንም ያህል ተቃውሞ ቢገጥመው በምርጫው ስኬታማ ከመሆን አላገደውም። አሁንም ቴድሮስ አሸንፏል። በሁለቱም አጋጣሚዎች የታየው በቂምና ጥላቻ የታጨቀ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ “አንድነት” የሚለውን ቃል ትርጉምና ፋይዳ አሳጥቶታል። በአጠቃላይ፣ ቴዲ አፍሮ እና ዶ/ር ቴድሮስ ሲያሸንፉ ኢትዮጲያ ተሸንፋለች!!!

ዶ/ር ቴድሮስ ያሸነፈባቸው 4 ምክንያቶች እና ማህበራዊ ሚዲያዎች

ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም የጤና ድርጅት ዳሬክተር ሆኖ የተመረጠበት ምክንያት በዋናነት የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ከግለሰብ ይልቅ በሀገራት ዲፕሎማሳዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ፋይዳ አንፃር ስለሆነ ነው። በዚህ መሰረት፣ ዶ/ር ቴድሮስ አሸናፊ የሆነው በሚከተሉት ከአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው፡-

1ኛ – አፍሪካ፡- ዶ/ር ቴድሮስ በኢትዮጲያ መንግስት ሙሉ ድጋፍ የተሰጠው እንደመሆኑ ከሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሳዊ ግንኙነትና በአፍሪካ ሕብረት ውስጥ ያላትን ቁልፍ ሚና በመጠቀም ዶ/ሩ ሙሉ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። 

2ኛ – አውሮፓ፡- ሁለተኛው ተወዳዳሪ “Dr. Nabaro” እንግሊዛዊ መሆናቸውና ሀገራቸው እንግሊዝ ደግሞ ከአውሮፓ ሕብረት መውጣቷ ይታወሳል። በዚህ ምክንያት፣ የእንግሊዙ ተወዳዳሪ ልክ እንደ ዶ/ር ቴድሮስ ከአውሮፓ ሕብረት ሀገራት ሙሉ ድጋፍ የማግኘት እድል አልነበራቸውም።

3ኛ – ኢሲያ፡-  ሦስተኛዋ ተወዳዳሪ ፓኪስታናዊቷ “Nishtar” ከኢሲያ ክፍለ ሀጉር የመጡ ናቸው። ነገር ግን፣ ላለፉት አስር አመታት የዓለም የጤና ድርጅትን የመሩት ዳይሬክተር የዚሁ ክፍለ ሀጉር ተወካይ እንደመሆናቸው እኚህ ተወዳዳሪ ከኢሲያ ሀገራት ሳይቀር ሙሉ ድጋፍ የማግኘት እድል አልነበራቸውም።

4ኛ፡- ላቲን አሜሪካ – “Dr. Nabaro” ከእንግሊዝ ይልቅ ስፔናዊ ወይም ፖርቹጋላዊ ቢሆኑ ኖሮ የላቲን አሜሩካ ሀገራትን ድጋፍ የማግኘት እድሉ ከፍተኛ ይሆን ነበር። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሦስተኛ ተራ ቁጥር ላይ በተጠቀሰው ምክንያት፣ የላቲን አሜሪካ ሀገራት ሌላ የኢሲያ ተወካይ በድጋሜ እንዲመረጥ ድምፃቸውን ለፓኪስታናዊቷ “Nishtar” አይሰጡም። ስለዚህ፣ በላቲን አሜሪካ ሀገራት ዘንድም ቢሆን ዶ/ር ቴድሮስ የመመረጥ እድላቸው ከሁለቱም ተወዳዳሪዎች የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ዶ/ር ቴድሮስ ከሦስቱም ተወዳዳሪዎች የላቀ የማሸነፍ እድል እንደነበራቸው እሙን ነው። ስለዚህ፣ ለዶ/ሩ ፈታኝ የነበረው የሌሎች ሀገራትን ድጋፍ ማግኘቱ አልነበረም። ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የውድድር ስልት በላይ ለዶ/ር ቴድሮስ ትልቅ ፈተና የነበረው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የጋጠማቸው ተቃውሞ ነው።

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የድምፅ አሰጣጡ ከግለሰብ ይልቅ በሀገራት ዲፐሎማሳዊ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ፋይዳ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ዶ/ር ቴድሮስ በማህበራዊ ሚዲያዊች አማካኝነት የገጠማቸው ተቃውሞ በድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ውስን ነው። ነገር ግን፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሀገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ምን ያህል ጉልህ እየሆነ እንደመጣ በግልፅ ያሳያል። በአጠቃላይ፣ የምርጫ ሂደቱ ማህበራዊ ሚዲያዎች ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማህብረሰቡን በንቃት በማሳተፍና ንቅናቄ መፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በግልፅ አሳይቶናል።

ያልተዘጋ እሰር ቤት ውስጥ ነፃነት ያስፈራል!

ከእስር ቤት የወጣሁ ሰሞን ወደ አንድ ባለሱቅ ደበኛዬ ጋር ስሄድ “እንኳን ለቤትህ አበቃህ….” እያለ አገላብጦ ከሳመኝ በኋላ “እኛ እኮ ‘እንትን’ ትመስለን ነበር” አለኝ። “‘እንትን’ ማለት ምን?” አልኩት። ፈራ-ተባ እያለ “እኛ እኮ የመንግስት ጆሮ-ጠቢ፥ ሰላይ ትመስለን ነበር” ሲለኝ ክት ብዬ ሳቅኩ። እንዲህ ማሰቡ በራሱ በጣም ገረመኝና “ያምሃል እንዴ? እስኪ አሁን እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” አልኩትና መልሱን ሳልጠብቅ ሄድኩ።

ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ከእኔ ጋር የአብሮነት ቆይታ ካላቸው ጓደኞቼ ጋር እየተጨዋወትን ሳለ ከመሃላቸው አንዱ “አይ ስዬ…እኔ እኮ ከእነሱ ጋር ትመስለኝ ነበር?” አለኝ። የረጅም ግዜ ጓደኛህ እንዲህ በጥርጣሬ ዓይን እያየህ መቆየቱን ስታውቅ የሆነ በቃ ያበሳጫል። “እንዴ… አንተ እንዴት ነው እንዲህ የምታስበው?” አልኩትና ወደ ሌሎቹ ዞሬ “ቆይ አንዴ ሁላችሁም…” ስል የሁሉም ትኩረት እኔ ላይ ሆነ። ከዚያ “ቆይ ከእናንተ ውስጥ ‘ስዬ ሰላይ ነው’ ብሎ የሚያስብ ነበረ?” እላቸዋለሁ ሁሉም በአንድ ድምፅ “አዎ!” አሉኝ።

ምላሻቸው ከማስገረም አልፎ አስደነገጠኝ። በለሆሳስ “ቆይ እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” ብዬ በውስጤ ማሰላሰል ስጀምር ከጎኔ የነበረው ጓደኛዬ “ቆይ ስዬ…አንተ ራስህ፣ ይህን ያህል ዓመት በነፃነት የፈለከውን እየተናገርክና እየፃፍክ ስትኖር ‘አለመፍራትህ በራሱ ሌላን ሰው አያስፈራም?’ እንደዛ በነፃነት ስትናገርና ስትፅፍ ሁላችንም ‘በቃ… ከኋላው የሆነ ነገር ቢኖር ነው’ ብለን አሰብን። ይሄ’ኮ አንተ የተለየ ነገር ስላደረክ ወይም ከሌሎቻችን በተለየ አንተን አለማመን አይደለም። እንደዛ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ከሁላችንም በተለየ አንተ ብቻ “ነፃ” ስትሆን አያስጠረጥርም ልትለኝ ነው?”

ይህ ከሆነ አምስት ወራት አለፉ። ነገር ግን፣ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስለኝ ነበር” የምትለዋ ጥያቄ ቀጥላለች። ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ቤት እየሄድኩ ሳለ አንድ መስፍን የሚባል ጓደኛዬ አገኘኝና “ስዬ…ድሮ እኮ እንፈራህ ነበር” አለኝ። “ለምን?” እለዋለሁ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስ…” አላስጨረስኩትም! ወደ ቤት እንደገባሁ ይህን ፅሁፍ መፃፍ ጀመርኩ።

በመጀመሪያ ደረጃ ያለኝ ፖለቲካ አቋምና አመለካከት ትክክለኝነቱ የሚረጋገጠው በየእለቱ በማንፀባርቀው ሃሳብና በምሰራው ሥራ ሳይሆን በመታሰሬ መሆኑ በራሱ ያበሳጫል። ነገር ግን፣ ለራሱ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ “ባልተዘጋ እስር ቤት” ውስጥ እየኖረ እንደ እኔ “ታስሮ ለተፈታ” ሰው ከንፈሩን ሲመጥ ማየት በጣም ይገርማል። ኧረ እንደውም ከማስገረም አልፎ አንዳንዴ እንደ እብድ ለብቻ ያስቃል።

“‘እንትን’ ትመስለን ነበር” ሲሉ “ሰላይ ወይም የመንግስት ጆሮ-ጠቢ” ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። ጥያቄው በጓደኞቼ ውስጥ የነበረውን ስጋትና ፍርሃት ያስከተለው ጥርጣሬን ያሳያል። እኔን የጠረጠሩበት ምክንያት ከሌሎች በተለየ መልኩ ሃሳብና አመለካከቴን በነፃነት በመግለፄ ነው። በእርግጥ ሁላችንም የራሳችንን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ እንሻለን። እንዲህ ያለ ነፃነት ለእስርና እንግልት እንደሚዳርግ ደግሞ እናውቃለን። ስለዚህ፣ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት የሚገልጽ ሰው እንደሚታሰር ይጠብቃሉ። ካልታሰረ ደግሞ “‘እንትን’ ቢሆን ነው” ብለው ይጠረጥራሉ።

ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈሩት ሆነ የሌሎችን ነፃነት የሚጠራጠሩት መንግስትን ስለሚፈሩ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Montesquieu” አገላለፅ፣ መንግስት የተፈጠረበት መሰረታዊ ዓላማ ዜጎች እርስ-በእርስ አንዳይፈራሩ ነው፡-

“The political liberty of the subject is a tranquility of mind arising from the opinion each person has of his safety. In order to have this liberty, it is requisite the government be so constituted as one man need not be afraid of another.” Baron de Montesquieu, The Spirit of Laws, trans. Thomas Nugent, 2 vols. (New York: The Colonial Press, 1899), 1:151–162.

የመንግስት ሥራና ተግባር ዜጎች እርስ-በእርስ ሳይፈራሩ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት አንዲገልፁ ማስቻል ነው። ሆኖም ግን፣ በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ዜጎች የራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ ይቅርና የጥቂቶች ነፃነት ብዙሃኑን ለስጋትና ጥርጣሬ እየዳረገው ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የተፈጠረበትን መሰረታዊ ዓላማ ስለሳተ ነው። መንግስታዊ ሥርዓቱ የዜጎችን መብትና ነፃነት ከማስከበር ይልቅ መንግስትን ሕዝቡን የሚፈራና ሕዝቡም እርስ-በእርስ እንዲፈራራ የሚያደርግ ስለሆነ ነው። በመሰረቱ ፍርሃት ለፍፁም አምባገነናዊ መንግስት የተግባር መመሪያና መርህ ነው፡-

“In a tyranny, the moving and guiding principle of action is fear. Fear in a tyranny is not only the subjects’ fear of the tyrant, but the tyrant’s fear of his subjects as well. [It] is not merely a psychological motive, but the very criteria according to which all public life is led and judged.”  On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding

በዚህ መሰረት፣ መንግስትን በመፍራት ሆነ በመጠራጠር፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ከመግለፅ የሚቆጠቡ ሰዎች በሙሉ በፍርሃት መርህና መመሪያ መሰረት ለሚመራው ሥርዓት ተገዢዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስርዓቱን በስልጣን ላይ ለማቆየት የመሚያስፈልገውን ፍርሃት እየለገሱ ስለሆነ እንደ ቀንደኛ ደጋፊ መታየት አለባቸው።

ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ሌሎች በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት የሚዳረጉት በራሳቸው ያጠፉት ጥፋት ወይም የፈፀሙት ወንጀል ስላለ አይደለም። የአምባገነናዊ መንግስት ዓላማም እነሱን በማሰቃየትና በማስፈራራት ወደፊት ለሥርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደ እነሱ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ እንዳይሞክር ለማስፈራራት ነው።

ብዙ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እስር ቤት ውስጥ የተዘጋባቸው ከእስር ቤት ሲወጡ ነፃነታቸውን ስለሚቀዳጁ ነው። በዚህም፣ ከእስር ቤት ውጪ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ስለሚገልፁና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደነሱ ነፃነቱን እንዲቀዳጁ ፈር-ስለሚቀዱ ለእስር ይዳረጋሉ። ምክንያቱም፣ እነዚህ ሰዎች ነፃነታቸውን የሚያጡት እስር ቤት ሲገቡ ብቻ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ከእስር ቤት ውጪ ሀኖ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለን ሰው ማሰርና ማሰቃየት አስፈላጊ አይደለም። በመኖሪያ ቤቱ እና በስራ ቦታ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ የሚፈራ ሰው ባልተዘጋ እስር ቤት ውስጥ ራሱን ያሰረ ስለሆነ ድጋሜ ማሰር አያስፈልግም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ፍርሃትን ማስፈን ለሚሻ ስርዓት ፈሪዎች ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በተደጋጋሚ የሚታሰሩት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ሃሳብና አመለካከቱን ለመግለፅ፣ መብትና ነፃነቱን በይፋ ለመጠየቅ ስለሚፈራ ነው። ስለዚህ፣ እነሱ የሚታሰሩት ሌሎችን ካልተዘጋው እስር ቤት ነፃ ለማውጣት ሲሞክሩ ነው።