Tag Archives: Amhara

የፀረ-ሽብር ሕጉ ዓላማ ሕዝቡን መሪ-አልባ ማድረግ ነው!

ባለፈው ጓደኛዬ ከአንድ ታዋቂ ምሁር ጋር አስተዋወቀኝና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየን። እኚህ ምሁር ቀድሞ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር የነበሩ ሲሆን አሁን ጡረታ ወጥተዋል። ቦሌ አከባቢ በሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ለሁለት ሰዓታት ያህል ተወያየን። ውይይታችን በዋናነት ያተኮረው ከኢህአዴግ መንግስት በፊትና በኋላ የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ሚና ምን ይመስላል በሚለው ዙሪያ ያተኮረ ነበር። እኚህ ምሁር ብዙውን ግዜ “The Amhara Hegemony” የምትለዋን አገላለፅ እንደሚያዘወትሩ ስለማውቅ የእኔም ጥያቄ ከዚያ ላይ ነው የጀመረው። “ዶክተር… ይህቺ ‘The Amhara Hegemony’ የሚሏት ነገር ፅንሰ-ሃሳቧ ምንድነው? በቀድሞ ስርዓት ‘የአማራ የበላይነት/አገዛዝ’ አለ ለማለት የቻሉበትን ምክንያት ቢያስረዱኝ?” አልኳቸው።

“በዚያን ግዜ (በደርግና በአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን) አብዛኞቹ የአማራ ምሁራን፣ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ የአማራ ተወላጅ የሆኑ መምህራን ‘የገብርዔል ማህበር፣ የማሪያም ፅዋ፣…ወዘተ እያሉ በየግዜው እየተገናኙ ተሰብስበው ያወራሉ፥ ይጫወታሉ። ማህበርና ፅዋ ይበሉ እንጂ የሚያወሩት እኮ ስለ ሃይማኖት አይደለም። ምሁራን ከመደበኛ ስራቸው ውጪ ሲገናኙ የሚያወሩት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ያው ፖለቲካ ነው። ስለዚህ፣ አብዛኞቹ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ማህበርና ፅዋ እያሉ በየግዜው ይሰበሰቡና ስለ ወቅታዊ ፖለቲካ ያወራሉ። በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብና አስተያየት ይሰጣሉ፣ የጋራ ግንዛቤ ይፈጥራሉ። በዚህም በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ አቋምና አመለካከት ይይዛሉ። ነገር ግን፣ እንደ እኔ ያሉት የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራን ገና ሶስት-አራት ሆነው መሰባሰብ ሲጀምሩ “ኦነግ” ይባላሉ። በተመሳሳይ፣ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጆች ተሰባስበው መምከር ሲጀምሩ “ወያኔ” ይባላሉ።

በቀድሞ ግዜ የአማራ ምሁራን እንደ እኛ “ጠባብ ብሔርተኛ” ወይም “ገንጣይ ወንበዴ” የሚል ስያሜ አይሰጣቸውም ነበር። ስለዚህ፣ የኦሮሞና ትግራይ ምሁራን እንኳን መደራጀት በጋራ ሰብሰብ ብለው ሻይ-ቡና ማለት አይችሉም ነበር። የአማራ ምሁራን ግን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በይፋ መቃወም እስካልጀመሩ ድረስ በፈለጋቸው ቦታና ሰዓት ተገናኝተው ቢመክሩና ቢዘክሩ ግንኙነታቸው ከኦነግ ወይም ከወያኔ ጋር ይያያዝብናል የሚል ስጋት አልነበረባቸውም። በዚህ ሁኔታ ምሁራን ስለ መጡበት ማህብረሰብ መብትና ነፃነት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ በአጠቃላይ ስለሚስፈልገው ለውጥና መሻሻል በጋራ ለመወያየት የሚያስችል ሁኔታ አልነበርም። ምሁራን የሕዝብን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በማንሳትና እርስ-በእርስ በመወያየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥና መጠቆም ካልቻሉ መንግስታዊ ስርዓቱ እንደ አፄ ኃ/ስላሴና ደርግ መጨረሻው አያምርም” አሉኝ።

እኔም ከአፋቸው ቀበል አድርጌ “አሁን ካነሱት ሃሳብ አንፃር ከኢህአዴግ መምጣት በኋላ ምን የተለየ ነገር ተፈጠረ?” የሚል ጥያቄ አስከተልኩ። እሳቸውም “ቅድም ያልኩህ ምሁራን በአብዛኛው የአማራ ምሁራን ሀገር ለቅቀው ወጡ። በተመሳሳይ፣ የኦሮሞ ምሁራን እንዲሁ ሀገር ለቅቀው ወጡ” አሉኝ፡፡ “ለምን?” አልኳቸው።

“እንዴ…ቀድሞ የነበረው የ“Amhara Hegemony” ኢህአዴግ ከጣ በኋላ በ”Tigray Hegemony” ተተካ። የአማራ ልሂቃን እንደ ቀድሞ ግዜ የገብሬልና የማሪያም ማህበር እያሉ መሰባሰብ ከጀመሩ “ከግንቦት7 ጋር ግንኙነት አላችሁ” በሚል ለእስርና እንግልት ይዳረጋሉ። እንደ ቀድሞ ስርዓት አሁንም የኦሮሞ ምሁራን በጋራ ተሰባስበው ሲወያዩ “ኦነግ ናችሁ” እየተባሉ ቁም ስቅለቸውን ያያሉ። የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ግን ሕወሃት/ኢህአዴግን በይፋ እስካልተቃወሙ ድረስ በየግዜው ተገናኝተው ቢወያዩ ነገሩ ከኦነግና ግንቦት7 ጋር ይያያዝብን ይሆናል የሚል ስጋት የለባቸውም። ኢህአዴግን መቃወም ይቅርና በመንግስት ስራና አሰራር ላይ ጠንከር ያለ ትችትና አስተያየት የሰጡ የአማራና ኦሮሞ ምሁራን ግን የግንቦት7ና የኦነግ የሽብር ተልዕኮ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀሱ ተደረሰባቸው ተብለው ወደ እስር ቤት ይወረወራሉ።

የሕወሃት ደጋፊ/አባል የሆኑ ምሁራን የፈላጋቸውን ሃሳብና አስተያየት መስጠት ይችላሉ። የብኣዴንና ኦህዴድ አባልና አመራሮች እንኳን ይህን የማድረግ ነፃነት የላቸውም። የኢህአዴግ መንግስትን ወይም በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ላይ ትችትና ነቀፌታ የሚሰነዝር የብአዴን አባልና አመራር “ትምክህተኛ”፣ የኦህዴድ አባልና አመራር ደግሞ “ጠባብ” የሚል ታፔላ ይለጠፍበታል። ከሕወሃት አባላትና ደጋፊዎች ተፃራሪ የሆነ ሃሳብና አስተያየት ካነሳህና የኢህአዴግ ተቃዋሚ ከሆንክ “ግንቦት7” ወይም “ኦነግ” ትባላለህ፣ የኢህአዴግ አባል ከሆንክ ደግሞ “ትምክህተኛ” ወይም “ጠባብ ብሔርተኛ” ተብለህ በጅምላ ትፈረጃለህ። ስለዚህ፣ ከኢህአዴግ ውስጥ ሆነ ውጪ ያሉ የአማራና ኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ስለ ሕዝባቸው መብትና ነፃነት አንዳች ነገር መተንፈስ አይችሉም። በዚህ ምክንያት የኢህአዴግ መንግስት በተለይ የሕዝቡን ብሶትና ምሬት መረዳት ተስኖታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደፊትም መረዳት የሚችል አይመስለኝም። ስለዚህ፣ ኢህአዴግም እንደ አፄ ኃ/ስላሴ እና ደርግ አገዛዝ መጨረሻ ላይ አወዳደቁ አያምርም።

በመጨረሻም “የተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣ እንዲሁም ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ የወጡ ወጣቶች ሳይቀር ሁሉም የሚከሰሱት በፀረ-ሽብር ሕጉ ነው። ከዚህ አንፃር፣ የፀረ-ሽብር አዋጁን ዓላማና አተገባበር እንዴት ያዩታል?” የሚል ጥያቄ አነሳሁላቸው። እሳቸውም በእርግጠኝነት “የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን መሪ-አልባ ማድረግ ነዋ!” አሉኝ።

“ይሄ ምን ጥያቄ አለው? መንግስት በተግባር የሚያደርገው እኮ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የፈቀደለትን ነው። የብዙሃኑ አስተያየትና አመለካከት የሚቀረፀው ደግሞ ከላይ በጠቀስካቸው ፖለቲከኞች፥ ጋዜጠኞች፥ ፀኃፊያንና በመብት ተሟጋቾች ነው። እነዚህ ሰዎች ስለ ሕዝብ መብትና ነፃነት በተናገሩ ቁጥር መንግስት እንደ “አልቃይዳ” እያደነ በሽብርተኝነት ወንጀል የሚከሳቸው ከሆነ ሕዝቡ መሪ አልባ ይሆናል። በሕገ-መንግስቱ ላይ የተደነገጉ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ የሚገድብ አዋጅ በማውጣት ስለ ሕዝብ መብት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚከራከሩ ሰዎችን ለማሰር፣ ለማሰቃየትና ለማስፈራራት የምትጠቀምበት ከሆነ የአዋጁ ዓላማና ግብ ሕዝቡን መሪ አልባ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መሰረት፣ የፀረ-ሽብር ሕጉ ዓላማና አተገባበር በተለይ የኦሮሞና አማራ ሕዝብን መሪ አልባ የሚያደርግ ነው። መሪ-አልባ ሕዝብን እንዴትም፥ ወዴትም ትመራዋለህ! 

“አዎ… የትግራይ/ሕወሃት የበላይነት አለ!”

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ ዝርዝር ምላሽ ሰጥተዋል። “የትግራይ የበላይነት የለም” በሚል ካቀረቧቸው ማስረጃዎች ውስጥ ሁለት ነጥቦች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። የመጀመሪያው የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የአንድ ብሔር (ክልል) የበላይነትን አያስተናግድም የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የሕወሃት አባላት በኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሆነ ካቢኔ ውስጥ የስልጣን የበላይነት የላቸውም የሚል ነው። ነገር ግን፣ የአንድ ብሄር (ቡድን) የበላይነት መኖር-አለመኖር የሚለካው በመንግስታዊ ስርዓቱ ወይም በባለስልጣናት ብዛት አይደለም። በዚህ ፅሁፍ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ያቀረቧቸውን ሁለት መሰረታዊ የመከራከሪያ ሃሳቦችን ውድቅ በማድረግ “የትግራይ የበላይነት መኖሩን” በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፌ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

1ኛ) “የትግራይ የበላይነት” የሚረጋገጠው የስርዓቱ መስራች በመሆን ነው! 
በእርግጥ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በፌዴራሊዝም ስርዓቱ መሰረት እያንዳንዱ ክልል ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣን ስላለው የትግራይም ሆነ የሌላ ብሔር የበላይነት ሊኖር እንደማይችል ገልፀዋል፡-

“/የትግራይ የበላይነት/ የሚባለው አንዳንዱ የተዛባ አመለካከት ነው፣ አንዳንዱ ደግሞ ፈጠራ ነው። ከፌዴራል ጀምረህ የስርአቱን አወቃቀር ነው የምታየው፡፡ /አወቃቀሩ ካልፈቀደ/ “የበላይነት“ የሚፈልግም ካለ ስሜት ብቻ ፤ “የበላይነት አለ“ የሚልም የራሱ ግምት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ …/በኢህአዴግ/ አንዱ በደንብ የገምገምነው እሱን ነው፤ “የትግራይ የበላይነት“ የሚባል የለም ነው፡፡ …ሄደን ሄደን ስርእቱን እንየው ነው፡፡ ስርአቱ “የበላይነት“ እንዲኖር ይፈቅዳል ወይ? የምንፈቅድ አለን ወይ? የትግራይ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም፡፡ ይሄ ስርአት ካልፈረሰ በስተቀር ሊኖር አይችልም፡፡ ይሄ ስርአት የትግራይንም የሌላንም የበላይነት አያስተናግድም፡፡ …ሁሉም ድርጅት የራሱን ነው የሚያስተዳድረው፡፡ ህወሓት ኦሮሚያን ወይም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር አይችልም፡፡ ስርአቱ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ በክልል የበላይነት የሚባለው የሌለ አምጥቶ የመለጠፍ ፈጠራ ነው፡፡ ስርእቱ በዚህ መሰረት አልተገነባም አይሰራም፡፡” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል 

በእርግጥ በፌደራሊዝም ስርዓቱ መሰረት “የትግራይ የበላይነት አለ” ማለት አይቻልም። ነገር ግን፣ በኢትዮጲያ “የትግራይ የበላይነት” መኖርና አለመኖር የሚለካው የሕወሃት ፓርቲ በአማራ ወይም በኦሮሚያ ክልል ላይ ባለው የመቆጣጠር ወይም የማስተዳደር ስልጣን አይደለም። ምክንያቱም፣ በፖለቲካ ውስጥ “የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል የራሱ የሆነ መመዘኛ መስፈርት አለው።

የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት ራሱን የቻለ ፅንሰ-ሃሳብ ሲሆን እሱም “The Class Domination Theory of Power” ይባላል። በዚህ ፅንሰ-ሃሳብ መሰረት የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነት መኖርና አለመኖር የሚረጋገጠው ሌሎች የሚተዳደሩበትን ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ባለው ችሎታ ነው። “Vergara L.G.” (2013) የተባለው ምሁር የአንድ መደብ/ቡድን/ብሔር የበላይነትን፤ “Domination by the few does not mean complete control, but rather the ability to set the terms under which other groups and classes must operate” በማለት ይገልፀዋል።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “የትግራይ የበላይነት” መኖሩና አለመኖሩን ማረጋገጥ የሚቻለው መንግስታዊ ስርዓቱ “የአንድ ብሔር/ክልል የበላይነትን ይፈቅዳል ወይስ አይፈቅድም” በሚለው እሳቤ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌሎች ብሔሮችና ክልሎች የሚተዳደሩበትን ስርዓትና ደንብ ከመወሰን አንፃር ትልቁ ድርሻ የማን ነው በሚለው ነው። የአማራ እና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች የሚተዳደሩበትን በብሔር ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት ከንድፈ-ሃሳብ እስከ ትግበራ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ሕወሃት ነው።

በእርግጥ ዶ/ር ደብረፅዮን እንዳሉት፣ መንግስታዊ ስርዓቱ ሕወሃት የአማራና ኦሮሚያ ክልልን እንዲያስተዳድር አይፈቅድም። ነገር ግን፣ የአማራ ሆነ የኦሮሚያ ክልል የሚተዳደሩበትን መንግስታዊ ስርዓት እና ደንብ የቀረፀው ሕውሃት ነው። ስለዚህ፣ የአማራ ክልል እና የኦሮሚያ ክልል የሚመሩበትን ስርዓትና ደንብ በመወሰኑ ረገድ ካለው ችሎታ አንፃር “የትግራይ የበላይነት” ስለ መኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም።

2ኛ) የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው በፖለቲካ ልሂቃን ነው!
ዶ/ር ደብረፅዮን “የትግራይ የበላይነት” አለመኖሩን ለማሳየት ያቀረቡት ሌላኛው የመከራከሪያ ሃሳብ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ብዛት ነው። ከዚህ አንፃር፣ በኢህአዴግ መንግስት ውስጥ ከፍተኛ የመወሰን ስልጣን ባላቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ የሕወሃት አባል የሆኑ ባለስልጣናት ብዛት ትንሽ መሆኑ ነው፡-

“በፖለቲካ ሃላፊነትም እኩልነት ነው የሚታየው፡፡ በኢህአዴግ ምክር ቤትም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል ውክልና ያላቸው፡፡ ለምሳሌ አንጋፋው ህወሓት ነው በሚል የተለየ ተጨማሪ ቁጥር አይሰጠውም፡፡ ብዙ ውሳኔ በሚወሰንበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ከ36ቱ ከሁላችንም እኩል ዘጠኝ ነው የተወከለው፡፡ አብዛኛው ያልተስማማበት ስለማያልፍ ማንም ድርጅት ዘጠኝ ሰው ይዞ የበላይነት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ….ለምሳሌ በካቢኔ አሁን 30 ነን፡፡ ድሮም ዛሬም ህወሓት ሶስት ሚኒስትር ብቻ እኮ ነው ያለው፤ ሶስት ይዘህ ደግሞ እንዴት ነው የተለየ ልታስወስን የምትችለው?” ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

ነገር ግን፣ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና በጠ/ሚኒስትሩ ካቢኔ ውስጥ ያሉት የሕወሃት አባል የሆኑ ባለስልጣናት ብዛት አነስተኛ መሆኑ የስልጣን የበላይነት አለመኖሩን አያሳይም። ምክንያቱም፣ የአንድ ቡድን/ብሔር የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው በባለስልጣናት ብዛት ሳይሆን በፖለቲካ ልሂቃን (political elites) አማካኝነት ነው። በዚህ መሰረት፣ የሕወሃት የስልጣን የበላይነት የሚረጋገጠው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ ልሂቃን ከባለስልጣናት በሚያገኙትን አድሏዊ ድጋፍና ትብብር መንግስታዊ ስርዓቱ እና የባለስልጣናቱ ውሳኔ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማስቻል ነው። ፅንሰ-ሃሳቡን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ ያግዘን ዘንድ በድጋሜ ከ“Vergara L.G.” (2013) ፅኁፍ ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፡-

“…political elites are defined as persons who, by virtue of their strategic locations in large or otherwise pivotal organizations and movements, are able to affect political outcomes regularly and substantially. The elites have power over the state, the civil organization of political power. Even though they could have conflicts with the mass, which certainly can affect political decisions from “top down” to “bottom up” the possession of multiples forms of capital (social, cultural, economic, politic, or any other social benefits derived from the preferential treatment and cooperation between individuals and groups) allows [them] to ensure their social reproduction as well as the cultural reproduction of the ruling class.” Elites, political elites and social change in modern societies; REVISTA DE SOCIOLOGÍA, Nº 28 (2013) pp. 31-49.

የፖለቲካ ልሂቃን በመንግስታዊ ስርዓቱ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱና በሲቭል ድርጅቶች ሥራና አሰራር ላይ ተጽዕኖ ማሳረፍ፣ በዚህም የአንድ ብሔር/ፓርቲ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚችሉት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ ሲኖር ነው። በዚህ መሰረት፣ የስልጣን የበላይነት ባለው የፖለቲካ ቡድን የተለየ አድሏዊ ድጋፍና ትብብር የሚደረግላቸው ልሂቃን የፖለቲካ አጀንዳን በመቅረፅና በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳርፉ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል።

ከዚህ አንፃር፣ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅን መሰረት በማድረግና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማስከበር በሚል ሰበብ ለእስርና ስደት ከተዳረጉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና የመብት ተሟጋቾች ምን ያህሉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው? ተቃዋሚ ይቅርና፣ በ2007 ዓ.ም በመቐለ ከተማ በተካሄደው የኢህአዴግ 10ኛ ጉባዔ ላይ በቀረበው ሪፖርት ላይ የጠባብነትና ትምክህተኝነት አመለካከት አንፀባርቀዋል በሚል ከስልጠና በኋላ የመስክ ክትትል ከተደረገባቸው ጀማሪና መካከለኛ የኢህአዴግ አመራሮች ውስጥ ምን ያህሉ የሕወሃት አባላት ናቸው? ከምርጫ 2002 – 2006 ዓ.ም በኋላ ባሉት አራት አመታት ብቻ፤ 19 ጋዜጠኞችን ለእስር፣ 60 ጋዜጠኞች ደግሞ ለስደት ሲዳርጉ ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሉ የትግራይ ብሔር ተወላጅ ናቸው? ሦስቱም ጥያቄዎች መልሱ ከሞላ-ጎደል “ዜሮ፥ ምንም” የሚል ነው።

ታዲያ የሕወሃት አባላት “በጠባብነት” እና “ትምክህተኝነት” በማይፈረጁበት፣ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን “ከግንቦት7 ወይም ኦነግ” ጋር በማገናኘት በፀረ-ሽብር ሕጉ በማይከሰሱበት፣ ያለ ፍርሃትና ስጋት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት በሚገልፁበት፣ የፖለቲካ አጀንዳውን በበላይነት በሚወስኑበት፣ …ወዘተ “የትግራይ የበላይነት የለም” ሊባል ነው። በአጠቃላይ፣ ዶ/ር ደብረፅዮን ያቀረቧቸው ሁለት የመከራከሪያ ሃሳቦች ምክንያታዊና አሳማኝ አይደሉም። “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ?” ለሚለው መልሱ “አዎ…አለ!” ነው። እውነታው ይሄ ነው፡፡