“የሰንደቅ ዓላማና አርማ ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አልቀረበም” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (አዲስ አድማስ) 

ህገ መንግስቱን ከማርቀቅ አንስቶ እስከ ማፅደቅ በነበረው ሂደት ወሳኝ ሚና የነበራቸው የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ የሰነድ ማስረጃዎችን በመንተራስ ስለ ህገ መንግስቱና የጸደቀበትን ሂደት መቼም ቢሆን ከማስረዳት ሰልችተውና ቦዝነው አያውቁም፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ አሁን ለነገሰው አለመግባባት መንስኤው ምን እንደሆነና መፍትሄውን እንዲሁም ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ከዶ/ር ነጋሶ ገዳዳ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ እንዲህ አጠናቅረነዋል፡-

የቀድሞ የኢትዮጲያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ምንጭ፦ አዲስ አድማስ)

****አሁን በሥራ ላይ ያለው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ እንዴት ነበር በህገ መንግስቱ የተካተተው ?

በመጀመሪያ በህገ መንግስቱ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች ብለን፣ ረቂቅ ሃሳቦችንና ጉዳዮችን ሰብስበን በዝርዝር አሰፈርን፡፡ በጥያቄ መልክ 73  ጉዳዮችን ነው በዝርዝር ያስቀመጥነው፡፡ እነዚህን 73 ጥያቄዎች ደግሞ ቅርፅ ያስያዙልን ኤክስፐርቶች (ባለሙያዎች) ነበሩ፡፡ ጥያቄዎቹ ተዘርዝረው የነበረው በመጠይቅ መልክ ሲሆን “ድጋፍ”፣ “ተቃውሞ” በሚል ተለይተው ነው፣ የህዝብ አስተያየት የተሰበሰበባቸው፡፡ የተቃውሞና ድጋፍ ውጤቱ የተሰላውም  በመቶኛ ነበር፡፡ 

እስቲ ለምሳሌ ያህል ይጥቀሱልን— ?

ለምሳሌ አጨቃጫቂው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ማለትም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠልን የሚፈቅደው በመጠይቅ ዝርዝሩ ተካትቶ ነበር፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተመረጡ 23 ሺህ ቀበሌዎች ላይ ነው የህዝብ ውይይት የተደረገው፡፡ እኔ ለምሳሌ ደምቢዶሎ ላይ አወያይቻለሁ፡፡ ደምቢዶሎ ትልቅ ከተማ ነው። ህዝቡ ከ50 ሺህ አያንስም ግን እኔ ያወያየኋቸው ከ200 አይበልጡም፡፡ በዚህ አይነት ነው ውይይቶች የተካሄዱት፡፡ 

በዚህ መሰረት ለምሳሌ አንቀፅ 39 (የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠል) ላይ በክልል አንድ (ትግራይ) መቶ በመቶ ድጋፍ አግኝቷል። በክልል ሁለት (አፋር) ደግሞ ይህ አንቀፅ 98 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በክልል 3 (አማራ ክልል) 89 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ክልል 4 (ኦሮሚያ ላይ) 97 በመቶ ድጋፍ አኝቷል፡፡ ክልል 5 (ሶማሌ) 72 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ክልል 6 (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) 88 በመቶ ነበር ድጋፍ ያገኘው፡፡  ክልል 12 (ጋምቤላ) ደግሞ 59 በመቶ ድጋፍ አግኝቷል፡፡  

በዚህ መንገድ ነው በጉዳዮቹ ላይ ከህዝብ ሃሳብ የተሰበሰበውና ህገ መንግስቱ ውስጥ የሚካተቱ አንቀፆችን በባለሙያዎች እንዲቀረፁ ያስደረግነው። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ፣ ይሄ ሁሉ የረቂቅ ሂደት ሲከናወን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ አልተነሳም ነበር፡፡ ትልቁ ጥያቄ የነበረው ሀገሪቱ ፌደራሊዝም ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም የሚለው ነበር እንጂ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ እንደ ሌሎቹ አንቀፆች የድጋፍና የተቃውሞ ድምፅ ከህዝብ አልተሰበሰበበትም፤ ለህዝብ ውይይትም አልቀረበም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ የሰንደቅ አላማን ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አላቀረበም።  

ለምንድን ነው የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ለህዝብ ውይይት ያልቀረበው?

በወቅቱ ዋናው ትኩረት፣ የሀገሪቱ ስርአት ፌደራል ይሁን አይሁን የሚለውና የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጉዳይ ነበር፡፡ ለዚህ ይመስለኛል የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ያን ያህል ትኩረት ያላገኘው። አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ትኩረቱ የፌደራሊዝም ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ ፌደራል ይሁን አይሁን በሚለው ላይ ከክልሎች (ከህዝብ) የተሰበሰቡ አስተያየቶች የመቶኛ ስሌትን ስንመለከት ደግሞ፤ ክልል አንድ (ትግራይ) 99 በመቶ ፌደራሊዝም ይሁን የሚለውን ሲደግፍ፣ ክልል 2 (አፋር) 97 በመቶ፣ ክልል 3 (አማራ) 92 በመቶ፣ ክልል 4 (ኦሮሚያ) 95 በመቶ፣ ክልል 5 (ሶማሌ) 65 በመቶ፣ ክልል 6 (ቤኒሻንጉል ጉሙዝ) 60 በመቶ ደግፎታል፡፡ ክልል 12 (ጋምቤላ) 84 በመቶ፣ ክልል 13 (በወቅቱ ሃረሪ ይመስለኛል) 97 በመቶ፣ ክልል 14 (አዲስ አበባ) 93 በመቶ ፌደራሊዝሙን ሲመርጡ፣ ድሬደዋ ላይ 11 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነበር የመረጠው፡፡ ትንሹ ቁጥር የድሬደዋ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ እኔ ዘንድ ያሉ ሰነዶች፣ በወቅቱ አንዳንድ ያልተወያዩ ክልሎች እንዳሉም ያመላክታል፡፡  

የሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ እንዴት በህገ መንግስቱ ላይ ተደነገገ ታዲያ?

አርቃቂ ኮሚሽኑ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ መግባት አለበት ብሎ በራሱ አስገብቶት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በእንዲህ መልኩ የሰንደቅ አላማውን ጉዳይ በአንቀፅ 3 አስቀምጦ፣ ከየክልሉ ለተውጣጡትና የህገ መንግስት ጉባኤ አባላት አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህ አንቀፅ ስር ሶስት ንኡስ አንቀፆች አሉ፡፡ የአርማ ጉዳይን፣ የክልሎች ሰንደቅ አላማን የተመለከቱ ናቸው፡፡ በጉባኤው በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙም ክርክር አልተካሄደም ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ ውይይት የተደረገው፣ ለሁለት ቀናት ማለትም፣ ጥቅምት 29 እና 30፣ 1987 ዓ.ም የነበረ ሲሆን በሰንደቅ ዓላማው ጉዳይ ሃሳባቸውን የሰጡ ሰዎች 37 ብቻ ነበሩ፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ ድንጋጌ፣ 513 የጉባኤው አባላት ድጋፍ ሲሰጡበት፣ በ4 ተቃውሞና በ5 ድምፀ ተአቅቦ ነው ፀድቆ፣ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 በመሆን የተደነገገው፡፡ 

በወቅቱ የአርማው መቀመጥ ጉዳይ ላይ የቀረበ ጠንካራ ተቃውሞ አልነበረም?

ብዙም አልነበረም፡፡ አቶ ግርማ ብሩ (አሁን አምባሳደር) ብቻ ነበር “የአርማና የባንዲራ ልዩነት ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያቀረበው እንጂ ብዙም ጠንካራ ክርክርና ጥያቄ አልተነሳም፡፡ ሻለቃ አድማሴም እንዲሁ ተቃውሞ አቅርበው ነበር፡፡ ከክልል 5 (ሶማሌ) የተወከሉት አቶ አሊ አብዱ፤ ሶስቱ ቀለማትና አርማው እንዳለ ሆኖ፣ “ነጭ” ቀለም ይጨመርበት የሚል ሃሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ከአፋርም እንዲሁ ነጭ ቀለም ይጨመርበት የሚል ሀሳብ ተሰንዝሮ ነበር፡፡ በዚህ የአርማ መጨመር ጉዳይ ላይ በተሰጠው የጉባኤው አባላት ድምፅ መሰረት፤ 517 ሰዎች አርማ መጨመር አለበት ሲሉ፣ 4 ተቃውሞ እንዲሁም 4 ድምፀ ተአቅቦ አድርገው ነበር፡፡ 

የክልሎች ሰንደቅ አላማን በተመለከተስ — የተነሱ ሃሳቦችና ክርክሮች ነበሩ?

አሁን በህገ መንግስቱ አንቀፅ 3 ንኡስ አንቀፅ 3 ስር ተደንግጎ የሚገኘውና “የፌደራሉ አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ አላማና አርማ ሊኖራቸው ይችላል” የሚለውን በተመለከተ፣ ብዙም የተቃወመ አልነበረም፡፡ ነገር ግን “ብቻውን የሚውለበለብ ሳይሆን ከፌደራሉ ጋር ጎን ለጎን ነው የሚውለው” በሚለው ላይ የተወሰኑ ሃሳቦች ተሰንዝረው ነበር፡፡ በዚህ ጎን ለጎን መውለብለብ አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ በተሰጠ ድምፅ፡- ድጋፍ 5፣ ተቃውሞ (ጎን ለጎን መሰቀል አያስፈልግም ያሉ) ደግሞ 517 ነበሩ፡፡ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉ 8 ነበሩ፡፡ 

አሁን ግን ከፌደራሉ ጎን ለጎን መሆን አለበት የሚል መመሪያ ወጥቷል …. ይሄ እንግዲህ በህገ መንግስቱ ያልተወሰነ፣ ነገር ግን በመመሪያ የወጣ ይመስለኛል፡፡ 

በፌደራሉ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የቀረቡ ሌሎች ሃሳቦችስ ነበሩ?

እንግዲህ ይሄ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት በዓለም ላይ የታወቅንበት፣ የነፃነት አርማም ስለሆነ መቀየር አያስፈልግም፤ ነገር ግን በመሃሉ  የሃይማኖት፣ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትን የሚወክል አርማ የግድ መኖር አለበት—የሚል ሃሳብ ነው በስፋት የተሰነዘረው፡፡ 

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ ከፍተኛ አለመግባባትና ልዩነት እየተፈጠረ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ይገምታሉ?

ቀደም ብሎ እኔ እንደማውቀው፣ የኢህአዴግ ስብሰባዎች ካልሆኑ በስተቀር ብዙ ጊዜ ህዝቡ ይዞ የሚወጣው ሌጣውን ነበር፡፡ በተለይ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል አካባቢ በተለይ ኮከቡ ያለበትን ሠንደቅ ዓላማ ተቃውሞ እንደሚቀርብበት በሚገባ የተመለከትኩት፣ በእነዚህ ሁለት ዓመታት (2008 እና 2009) ጊዜ ውስጥ በተፈጠሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ላይ ነው፡፡ በተቃውሞዎቹ በግልፅ በባለኮከቡ ሠንደቅ ዓላማ ያለው ተቃውሞ በአብዛኛው ታይቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሄን ሰንደቅ ዓላማ ይቃወማሉ፡፡ በኦሮሚያ በኩል የሚታየው ተቃውሞ ደግሞ ከማንነትና ከማንነት መለያ ጋርም የተያያዘ ነው የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ በኢሬቻ በዓል ላይ ሁለት አይነት ነው የሚታይ የነበረው፡፡ የኦነግ ደጋፊዎች የኦነግን መለያ ባንዲራ ሲያውለበልቡ ነበር፣ በሌላ በኩል የአባገዳዎች ባንዲራም ታይቷል፡፡ የክልሉ ባንዲራም ራሱን ችሎ ነበር፡፡  
ስለዚህ አሁን በኦሮሚያ ያለው ሶስት አይነት ባንዲራ ነው ማለት ነው … 

እኔ የአባገዳዎች ባንዲራ ማለትም ጥቁር፣ ቀይ እና ነጭ ቀለማት በተከታታይ ያሉበት ባንዲራ እንዴት መጣ ብዬ ሽማግሌዎችን ለመጠየቅ ሞክሬ ያገኘሁት መረዳት አለ፡፡ ይህ ባንዲራ በሁለት ጎሳዎች (አካላት) ጦርነት መካከል በሠላም ለማለፍ የሚያሣዩት ምልክት ነበር፡፡ ከላይ ጥቁር ቀለም የሆነው በገዳ ስርአት ሽማግሌዎችን ይወክላል፤ ከአባገዳ ጀምሮ ያሉትን ይወክላል፡፡ ቀዩ ደግሞ እድሜያቸው ከ18-40 የሆኑ ወጣቶችን ይወክላል። ወጣትነት ትኩስ ሃይል መሆኑን ለማሳየት ነው፤ የወጣትነት እድሜ ስራ የሚሰራበት፣ ጦርነት የሚሳተፉበት እድሜ ነው፡፡ ነጩ ቀለም ደግሞ ህፃናትን ይወክላል፡፡ ህፃናት ገና ከፈጣሪ ስለመጡ ንጹሐን ናቸው የሚል ትርጉም አለው፡፡ በኦሮሞ ባህል ህፃናት እስከ 8 ዓመት እድሜያቸው በፆታ አይለዩም፡፡ ወንዱም ሴቱም ተመሣሣይ ፀጉር፣ ተመሣሣይ አለባበስ ነው የሚኖራቸው፡፡ 

የብዙ ሰዎችን ፍላጎት ስናይ፣ በክልሉ ካሉ ሶስት አይነት ባንዲራዎች የሚቀበሉት፣ የአባ ገዳዎቹን ይመስላል፤ ግን የህዝቡን ስሜት ህዝበ ውሣኔ ባልተካሄደበት ሁኔታ ማወቅ አይቻልም። የፌደራሉን ባንዲራ ያለመቀበል ስሜት የሚታየውም  ከዚህ  አንፃር ይመስለኛል፡፡ የፌዴራል ስርአት የኛን ጥያቄ ስላልመለሰ፣ የፌደራል ሠንደቅ አላማ አይወክለንም የሚል ስሜት ያለ ይመስላል፡፡

ታዲያ እንዴት ነው በአንድ አገራዊ ሠንደቅ ዓላማ  መስማማትና መግባባት የሚቻለው?

አስቀድሜ እንዳልኩት፣ ይህ አሁን መመሪያ ወጥቶለት በግድ ሊተገበር በታሠበው ሠንደቅ ዓላማና አርማ ላይ ህዝቡ ውይይት አላደረገበትም። በሌላ በኩል ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በእኩል በሂደቱ አልተሣተፉም፡፡ ኢህአፓ፣ መኢሶን፣ ኦነግ፣ ኢሠፓ ሌሎችም በዚህ ሂደት አልተሣተፉም። እነዚህ ኢትዮጵያውን ናቸው፣ ደጋፊዎች አሏቸው፤ ነገር ግን በሠንደቅ ዓላማው ጉዳይ ውይይት አላደረጉም፡፡ በህገ መንግስቱ ላይም እንዲሁ። በሌላ በኩል፤ በረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይም ሆነ በፀደቀው ህገ መንግስት ላይ ህዝቡ የራሱ ፍላጎት ስለመካተቱ የሚያንፀባርቅበት ህዝበ ውሣኔ አልተካሄደም፡፡ እንዳለ ወደ ህዝቡ ነው ፀድቆ የወረደው፡፡ የሠንደቅ ዓላማው ሆነ ሌሎች ችግሮች የሚመነጩት፣ አንደኛው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይ ህዝበ ውሣኔ ካልተካሄደበት ስርአቱ ወይም ህገ መንግስቱ በህዝቡ ተቀባይነት እንዳለው ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻለውም ማለት ነው፡፡ 

አሁንም የሚሻለው በህገ መንግስቱም ሆነ በሠንደቅ አላማው ጉዳይ ላይ የማሻሻያ ሃሣቦች ካሉ፣ ማሻሻያ ይደረግ የሚሉ አካላት ፊርማ አሠባስበው ቢያቀርቡና፣ ጉባኤ ተደርጎ፣ ለህዝብ ውሳኔ ቢቀርብ ነው፡፡ ሁነኛ መፍትሄ የሚሆነው ህዝበ ውሣኔ ማካሄድ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዋሳኝ ድንበሮች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች መንስኤያቸው ምንድን ነው?

ችግር የተፈጠረው የፌደራል ስርአት መርህን ካለማክበር ነው፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በህገ መንግስቱ ተሰጥቷል፡፡ ይሄ ባለበት ሁኔታ ደግሞ በጋራ በሚዋሰኑበት ድንበራቸው ሊከተሉት የሚገባ መርህ አለ፡፡ የጋራ አስተዳደርና የግል አስተዳደር የሚባል መርህም በህገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ ይሄን መርህ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻል ነው አንዱ ችግር፡፡

የዲሞክራሲ ጥያቄም አለ፡፡ ህገ መንግስቱን የሚቀበሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እስካሉ ድረስ የእነዚህ ድርጅቶች በማናቸውም መልኩ በምርጫ ተፎካክረው አስተዳደር መሆን የሚችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር የፌዴራል ስርአቱ ችግር ላይ ይወድቃል። አጋር ድርጅቶች የሚያስተዳድሩት ክልልም ሆነ ኢህአዴግ በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች፣ በነፃ ምርጫ ተወዳድሮ፣ የክልል አስተዳዳሪነት ስልጣን የሚያዝበት ሁኔታ እስካልተፈጠረና የገዥው ፓርቲ፤ ”የእኔ ፕሮግራም ብቻ ነው ተግባራዊ መደረግ ያለበት” የሚል አመለካከት ካልቀረ በስተቀር ችግሩ ሊፈታ አይችልም፡፡

በስፋት የሚታየው ድንበርን አስታኮ የሚፈጠር ችግር በህዝበ ውሳኔ እንዲፈታ ነው በመርህ ደረጃ የተቀመጠው፡፡ በዚህ መሠረት በሁሉም ቦታዎች እልባት የተሰጠ አይመስለኝም፡፡ ህዝበ ውሣኔ ቢደረግም ተግባራዊ ማካለል አለማድረግ ሌላው የግጭት መንስኤ ነው፡፡

አሁን መፍትሄው ምንድነው?

መፍትሄው ዲሞክራሲን ማስፋት፣ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ መርሆችን  መተግበር ነው። ህዝበ ውሣኔ የተደረገባቸውን ጉዳዮችም በጊዜ መደምደም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ በጊዜ ካልተመለሱ የፌደራል ስርአቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ 

ምናልባት ከእርስዎ  በኋላ በይፋ ለህዝብ አሳውቆ ሥልጣንን በመልቀቅ ረገድ አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ ሁለተኛው የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ የእሳቸው በዚህ ወቅት ከሥልጣን መልቀቅ አንደምታው ምን ሊሆን ይችላል ?

በዝርዝር ለመናገር ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም እሳቸው ማብራሪያ አልሰጡበትም፡፡ በውስጥ ያሉ ሁኔታዎችንም ማወቅ ባልተቻለበት ሁኔታ  ብዙ መናገር አይቻልም፡፡

የእሳቸው ከስልጣን መልቀቅ ለኢህአዴግ ወይም ለመንግሥት ብዙ የሚያጎድሉበት ይመስልዎታል?

ኦህዴድን ከመሠረቱት መካከል ዋናው ሰው ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ 1993 ላይ በተንገዳገደ ጊዜ ከታደጉት ሰዎች አንዱ ናቸው። ጦርነቱንም ከመሩት አንዱ ቁልፍ ሰው ናቸው፡፡ የኦሮሚያን አስተዳደር ከኦነግ ጋር ሆነው ከወሰኑ የኦህዴድ ሰዎች ዋነኛው ናቸው፡፡ በኋላ ላይም ኦነግ ከኦሮሚያ እንዲወጣ በማድረግ በኩልም ቁልፍ ሰው ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ በ1993 መከፋፈል በመጣ ጊዜ የእነ አቶ መለስን ቡድን ከታደጉት አንዱ ቀልፍ ሰው ናቸው፡፡ እስከ 1993 ድረስ ወታደር ነበሩ፡፡ ሜጄር ጀነራል ነበሩ፡፡ ወደ ሲቪል የመጡበት አካሄድም ትክክልና ህጋዊ አልነበረም፡፡ ለኔ እስካሁን ጀነራል ናቸው እንጂ ሲቪል አይደሉም፡፡ ምክንያቱም የጀነራልነት ማዕረጉን የሠጠሁት እኔ ነኝ፤ ማዕረጉንም ሊያነሳ የሚችለው ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ ያ ማለት እኔ ነበርኩ ማንሳት የነበረብኝ፡፡ 

በወቅቱ ጉዳዩ ለእርስዎ  አልቀረበም ነበር?

ፈፅሞ አልቀረበም፡፡ በዚያን ጊዜ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈፃሚም በጉዳዩ ላይ አልተወያየም፡፡ ይሄ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በተወሰኑ ሰዎች ሊሆን ይችላል እንጂ በድርጅቱ ደረጃ በኢህአዴግም ሆነ በኦህዴድ ውስጥ ውይይት አልተደረገበትም፡፡ ነገር ግን ሰውየው የእነ አቶ መለስን ቡድን በመታደግ ጥሩ ሚና ነበራቸው። ከዚህ ባሻገር በፊንፌኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞንን በማቋቋም፣ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከልን በማቋቋምም ወሳኝ ሚና ነበራቸው፡፡ የኦሮሚያ ዋና ከተማን ወደ አዲስ አበባ በማምጣትም ይታወቃሉ።

ከስልጣን ለመልቀቃቸው ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል?

እኔ እንደሚመስለኝ የሶማሊያና ኦሮሚያ ግጭት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ እንደሰማሁት ከሆነ በአጠቃላይ በአካሄዶች አለመደሰታቸውና የህዝቡ ቅሬታ በአግባቡና በታሰበው መንገድ እየተፈታ አይደለም የሚል ቅሬታም እንዳላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የግጭቱ ጉዳይ ብቻ አይመስለኝም፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ችግር እንዳለ በሚገባ የሚያመላክት ነው፡፡

*****

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ 

Advertisements

ሆድ ያባውን ቻርተር ያወጣዋል

በሃገራችን መንግስዊ ስልጣን ላይ መሰየሙ ለኢህአዴግ ከሰጠው ጥቅም አንዱ የፈለገውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለእርሱ የፖለቲካ ትርፍ የሚጠቅመው በመሰለው ወቅት እና ሁኔታ አንስቶ ወደ ጠረጴዛ ማምጣቱ ነው፡፡ አለቅነቱ ያመጣለትን በጎ ሁኔታ በመጠቀም ኢህአዴግ እሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ወደ መረሳት በተጠጋ መልኩ ሲያድበሰብሰው የኖረውን ለኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የተሰጠ ህገ-መንግስታዊ መብት ጉዳይ ዛሬ ትኩስ አድርጎ እነሳው  ይገኛል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖረው ይገባል ተብሎ በህገ-መንግስት የተሰጠውን መብት አፈፃፀም አስመልክቶ መንግስት ያወጣውን ረቂቅ አዋጅ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ዶክመንቱ በመንግስት ይፋ ከመደረጉ በፊት ጉዳዩን አስመልክቶ ማን እንዳወጣው ያልታወቀ ዝርዝር አንቀፆችን የያዘ ሰነድ በተለያዩ ድህረገፆች ተለቆ፣ በሰፊው ተነቦ፣ እጅግ ሲያነጋገር ሰንብቶ ነበር፡፡ ዶክመንቱ በተለይ በውጭ ሃገር የከተሙ የኦሮሞ ምሁራንን ቀልብ የሳበ የመነጋገሪ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል፡፡

“ኢህአዴግ መራሹ የሃገራችን መንግስት ለእሩብ ምዕተ አመት ዝም ብሎት የቆየውን አጀንዳ ዛሬ ለምን ማንሳት ፈለገ?” የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እርግጠኛውን መልስ የሚያውቀው መንግስት ራሱ ቢሆንም መላምቶችን መሰንዘር ግን ይቻላል፡፡ መንግስት የአዲስ አበባ መስተዳድርን ከኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች ጋር አቀናጅቶ ለማልማት የሚያስችል እቅድ አውጥቼ ተግባራዊ አደርጋለሁ በማለቱ ባለፈው አመት ከኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው “በቃ ትቼዋለሁ” ማለቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከሚታወቅበት ማድረግ የፈለገውን ሳይደርግ እንቅልፍ ያለመተኛት ባህሪው አንፀር ነገሩን በአፉ እንዳወራው እርግፍ አድርጎ ይተወዋል ማለት ያስቸግራል፡፡ እናም ከአንድ አመት በኋላ ይህን ዶክመንት ይፋ ማድረጉ፣ በዶክመንቱ ውስጥ የተዘረዘሩ ሃሳቦች የኦሮሚያ አጎራባች ዞኖችን ከአዲስ አበባ ጋር በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ለማቆራኘት የታለሙ አንቀፆች ከመኖራቸው፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ወሰን አሁንም በቁርጥ ያልተቀመጠ ከመሆኑ፣ የአዲስ አበባ አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሬቱ ለልማት ከተፈለገ ካሳ ይከፈላቸዋል እንጅ መነሳታቸው አይቀርም ከሚለው የአዋጁ ክፍል ጋር ሲጣመር የአፈፃፀም አዋጁ ለረዥም ወራት ተቆጥቶ የነበረው የክልሉ ህዝብ ከአንድ አመት ገዘፍ ያለ እስር፣ እጎራና እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካመጠው ድንጋጤ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያለውን ስሜት ለመለካት ያለመ ትልቅ የግመታ ተልዕኮ ያነገበ ይመስላል፡፡

ሌላው መላምት አቶ ጌታቸው ረዳ ‘እሳት እና ጭድ የሆኑ ቡድኖች አንድነት ያሳዩት እኛ ስራችንን ስላልሰራን ነው’ ካሉት ንግግር ጋር ይቆራኛል፡፡ ከአመት በፊት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ባልተለመደ ሁኔታ የትብብር ዝንባሌ ማሳየታቸውን ኢህአዴግ በበጎ ጎኑ እንዳልተመለከተው፣ ይልቅስ የመንግስቱ ድክመት ያመጣው ክፉ ውጤት አድርጎ እንዳሰበው የአቶ ጌታቸው ንግግር ምስክር ነው፡፡ በዚህ ግንዛቤ ውስጥ የከረመው  የኢህአዴግ መንግስት ታዲያ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” የምትል  ከዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ጋር ክፉ ፀብ ያላት ሃረግ ያዘለ አዋጅ አስነግሯል፡፡

“ልዩ ጥቅም”  የሚለው ቃል “Privilege” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ይወክላል፡፡ ይህ ቃል ደግሞ የዲሞክራሲ ዋና ከሆነው የዜጎች እኩልነት መርህ ጋር በእጅጉ ይጣላል፡፡ዲሞክራሲ በሰፈነበትም ሆነ ወደ ዲሞክራሲ እያመራ ባለ  ሃገር የአንድ ወገን ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር ማንሳት ወደ ሰሜን ለመሄድ ተነስቶ ወደ ደቡብ እንደ መንጎድ ያለ አልተገናኝቶ ነገር ነው፡፡ ለኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የሚያስገኘው  አዋጅ መነሾ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ነው ሲባል “የህገ-መንግስቱ ምንጭስ ማን ነው?” ወደ ሚለው ወሳኝ ጥያቄ ይመራል፡፡

ለህገ-መንግስቱ እርሾ የሆነው የሽግግር ዘመኑ ቻርተር በሻዕብያ፣ በህወሃት እና በኦነግ ለተፈጠሩበት አላማ እንዲያገለግል ሆነኖ ተቦክቶ ተሰልቆ ካለቀ በኋላ፤ ሰፍቶ ተስፋፍቶ ህገመንግስት ይሆን ዘንድ በህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽኑ በኩል ለህዝብ ውይይት ይቅረብ የተባለው እንደው ለቡራኬ ያህል ብቻ እንደሆነ በወቅቱ የነበሩ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ያሉ ፖለቲከኞች ይመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡ ህወሃት ኦነግ እና ሻዕብያ የሽግግር ዘመኑ አድራጊ ፈጣሪዎች እንደመሆናቸው ህገ-መንግስቱን ባዋለደው በዚህ ወሳኝ ወቅት እነዚህ “ሶስቱ ኃያላን” ያልወደዱት አካል ለምሳሌ የአማራው ብሄር እና የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት አቀንቃኝ ዜጎች ሃሳብ፣ እምነት እና ፍላጎት በቅጡ አልተወከለም፡፡ ስለዚህ የህገ-መንግስቱ አረቃቅም ሆነ ኢትዮጵያ ከሽግግር መንግስት ወደ ተመራጭ መንግስት ተዘዋወረች የተባለበት ሂደት የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ የወከለ አካሄድ አልነበረም፡፡ ይህን የሂደቱ  ዋና ተዋናይ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶም ደግመው ደገግመው የሚመሰክሩት ብቻ ሳይሆን የሂደቱ አካል “በመሆኔም እፀፀታለሁ” ያሉበት ነው፡፡

ህገ-መንግስቱ የረቀቀበት መንገድ እንዲህ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ቢሆንም ኢህዴግ ስህተት እንደሌለው መለኮታዊ መዝገብ ቆጥሮት የህገ-መንግስቱን ስም ስንቅ አድርጎ ወሳኝ የፖለቲካ ቁማሮችን በአሸናፊነት ይወጣበታል፡፡ ራሱን ህጋዊ ባላንጦቹን ህገ-ወጥ አድርጎ ህግን በመናድ ከሶ ዘብጥያ ያወርድበታል፡፡ ያሰበውን ለማድረግ እንደ እጁ መዳፍ በሚያውቀው ህገ-መንግስት የተፃፈውን መጥቀስ ቀርቶ ከዛም በላይ የሚሄደው ኢህአዴግ በዚህ አዋጅም ያየነው የተለመደውን ማንነቱን ነውና እግዚኦ የሚያስብል ነገር የለውም፡፡ የሚገርመው ነገር ያለው ሌላ ቦታ ነው- በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች መንደር፡፡

ከስራው አንድ አፍታ የማይዘናጋው፣ የሚያተርፍበት የመሰለውን የፖለቲካ ቁማር አጥብቆ በመያዝ የሚታወቀው ኢህአዴግ ለኦሮሚያ ክልል ከሃያ አምስት አመት በፊት የማለላትን በአዲስ አበባ ላይ  የልዩ መብት ባለቤት የመሆን ቃል ለመፈፀም አዋጅ አውጥቻለሁ ሲል በገራገርነት ቃሉን ለማክበር አስቦ ብቻ አይመስልም፡፡እንደሚታወቀው መንግስት ይህን ረቂቅ አዋጅ ያወጣው ፓርላማው ለእረፍት በሚዘጋበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በአዋጁ ዙሪያ ከህዝቡ የሚነሱ አስተያቶችን፣ የፖለቲከኞችን አሰላለፍ በማጤን ራሱን የፖለቲካ ትርፍ በሚያጋብስበት መስመር ለማሰለፍ ነገሮችን የማጤኛ ጊዜ ለማግኘት ይመስለኛል፡፡ይህን ይበልጥ የሚያስረዳው አቶ ለማ መገርሳ ደግመው ደጋግመው አዋጁ ለውይይት ክፍት ነው እንጅ ያለቀለት አይደለም ሲሉ መሰንበታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም መንግስት በቴሌቭዥኑ የአፈፃፀም አዋጁን ከማወጁ በፊት ቀደም ብሎ ባለቤቱ ያልታወቀ ዶክመንት በማህበረዊ ድህረገጾች እንዲከላወስ ሲደረግ፣ብዙ ሲያነጋግር መንግስት አለሁበትም የለሁበትምም ሳይል ድምጹን አጥፍቶ የነገሮችን አካሄድ ሲከታተል ሰነበተ፡፡ከርሞ ከርሞ በቴሌቭዥኑ ያስነገረው አዋጅ የወጣበት ጊዜም እንዲሁ በድንገት የተደረገ አይመስለኝም፡፡  በዚሁ ጊዜ ትቂት የማይባሉ የኦሮሞ ብሄር ፖለቲከኞች ሰተት ብለው ወደ ወጥመዱ ውስጥ ሲገቡ በሰነዱ ውስጥ እጅግ የተገለለው፣እንደሌላ ሊቆጠር ምንም ያልቀረው የኢትዮጵያ ብሄርተኝት አቀንቃኙ አካል ዝምታን መርጦ ከኢህአዴግ ጋር ካብ ለካብ መተያየቱን መረጠ፡፡አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አራማጆች ብቻ ሳይሆን ምሁራን ጭምር ባለቤቱ እንኳን በውል ባልታወቀ ሰነድ ዙሪያ አስደንጋጭ የክርክር ነጥቦች ያዘሉ ረዣዥ ክርክሮች አምጥተው ራሳቸውን ለግምት አደባባይ አሰጡ፡፡ምሁራን ተብየዎቹ በመገናኛ ብዙሃን(በኦ.ኤም.ኤን እና በቪኦኤ) ቀርበው ሲወያዩ በጆሮየ የሰማኋቸውን እና የገረሙኝን ብቻ ላንሳ፡፡

“የባለቤትነት” እና “የልዪ ጥቅም” እሳቤዎች ንትርክ

ባለቤቱ ያልታወቀው ሰነድ የአዲስ አበባ አደባባዮችን ለመጠቀም ሳይቀር የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በአዲስ አበባ ለሚጠይቁትን ነገር ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል በሚሉ አንቀጾች ተሞላውን ሰነድ እየጠቀሱ ይህ እጅግ ትንሽ ነገር እንደሆነ እና በአዲስ አበባ ላይ ባለቤት የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ እንደ እንግዳ ቆጥሮ በገዛ ቤቱ ሊያስተናግድ እንደሞከረ ደፋር እንግዳ ቆጥረው አብጠልጥለውታል፡፡መሆን ያለበትን ሲያወሱም ከዶክመንቱ ስያሜ ጀምሮ መሆን ያለበት የባለቤትነት አዋጅ እንጅ የልዩ ጥቅም አዋጅ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ተከራካሪዎቹ ሲያክሉም በአዲስ አበባ የሚኖር ማንኛውም ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የሆነ ተቋምም ሆነ ሌላ አካል የሚኖረው በኦሮሚያ ምድር መሆኑን እንዲያስታውስ፣ትንሽም ብትሆን አመታዊ ግብር ለኦሮሚያ ክልል መክፈል አለበት፣ ቀረጥ እና ግብር በሚከፈልባቸው የጉምሩክ ጣቢዎች ላይም በርከት ያሉ ኦሮሞ ተወላጆች ሊታዩ ያስፈልጋል፣ አዲስ አበባ ራሷም መተዳደር ያለባት በኦሮሚያ ክልል ስር እንጅ በፌደራል መንግስቱ ስር መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ሌላው አስገራሚም አስቂኝም የሆነው የክርክር ነጥብ ጭብጥ ደግሞ ይህን ይላል፤ ‘አሁን አዲስ አበባ የሚኖረው አብዛኛው ሰው የከተሜነት ዲሲፕሊን የሚያንሰው፣በሌሎች ዓለማት ያሉ የከተማ ነዋሪዎች የተላበሱት ትህትና የሚጎድለው፤ ለኦሮሞ ባህል እና ማንነት ክብር ለማሳየት የሚለግም ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ መስተካከል አለበት፡፡በአዲስ አበባ መኖር የሚቻለው ባለቤቱን የኦሮሞ ህዝብ እስካበሩ ብቻ ነው፡፡ ይህን እስካደረገ ድረስ መኖር ይችላል ካልሆነ ግን አዲስ አበባን ለባለቤቶቿ ለቆ ሌላ ሰፊ ቦታ ፈልጎ አዲስ ዋና ከተማ መመስረት ነው፤አዲስ ሚመሰረተውን ዋና ከተማ ኦሮሚያ ላይ ማድረግም ይቻላል፡፡’ ይሄ ኦነግን አደቁኖ ካቀሰሰው ‘የውጡልኝ ከሃገሬ’ ፖለቲካዊ ፈሊጥ የተቀዳ ነው፡፡ ወንድም ህዝብን ማግለልን እንደ ፖለቲካ ስኬት ዳርቻ የሚቆጥረው የኦነግ መናኛ ፖለቲካዊ አካሄድ ፓርቲውን እድሜ ብቻ አድርጎት እንደቀረ ተረድቶ ራመድ ማለት ፖለቲካዊ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ኦነግ እንኳን ብሎት ብሎት አልሆን ሲለው የተወውን ውራጅ ፖለቲካ ትርክት አንግቦ መንገታገት ራስን የፖለቲካ ማስፈራሪያ ከማድረግ፤ ቆምኩለት የሚሉትን ህዝብም በጥርጣሬ ከማሳየት ያለፈ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡

የዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ‘አዲስ አበባ የኦሮሞ ህዝብ የብቻ ታሪካዊ እርስት ነች’ የሚለውን አስገራሚ እሳቤ ብንቀበል እንኳን ቀደምት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው የተባሉት ኦሮሞዎች መኖሪያ የነበረችው አዲስ አበባ እና የአሁኗ አዲስ አበባ የተለየች መሆኗን ማገናዘብ ይህን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ከባዱ ነገር ከላይ ባሉት ተከራካሪዎች መጤ ይሁን ሰፋሪ እየተባሉ ያሉት ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ላባቸውንም እድሜያቸውንም ጨርሰው ያቀኗትን አዲስ አበባን ጥለው ወደ መድረሻቸው ይድረሱ፤ ወይም ሌላ ረባዳ መሬት ፈልገው የሃገራቸውን ዋና ከተማ ይመስርቱ የሚለው ሃሳብ  ይሰምርልኛል ብሎ ወደ አደባባይ ይዞ መቅረቡ ነው፡፡ከሰሞኑ በቪኦኤ ቀርበው የሚከራከሩ ዶ/ር ኃ/መስቀል የተባሉ ሌላ የኦሮሞ ምሁር ደግሞ ሌላ ክርክር ያመጣሉ፡፡ ሰውየው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሃረርም፣ በድሬዳዋም፣በሞያሌም ላይ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሊከበርላት ይገባል ሲሉ በህገ-መንግስቱም ያልተጠቀሰ ሰፋ ያለ ፍላጎት ያለው ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የሰውየው ክርክር መነሾው እነዚህ ከተሞች ኦሮሚያ ክልል መሃል ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡ ሐምሌ 8/2009 ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቃል-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ነጋሶ ሃረርም በኦሮሚያ መሃከል ስለምትገኝ በሚል ኦነግ በሽግግሩ ወቅት የኦሮሚያ ክልል በከተማዋ ላይ ልዩ መብት  እንዲኖረው ጥያቄ አቅርቦ ምክንያቱን በማላውቀው ነገር ህገመንግስቱ ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል ይላሉ፡፡፣

ከላይ የተነሱት የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች እና ምሁራን  የክርክር ነጥቦች ሲጠቃለሉ አሁን ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላትን መብት የባለቤትነት እንጅ የልዩ ጥቅም ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡የኦሮሚያን ህገመንግስታዊ ልዩ መብት ለመተግበር ወጣ የተባለው ረቂቅ አዋጅም መቃኘት ያለበት ከዚሁ አንፃር ነው የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተቃራው የቆመው፤ የአዲስ አበባ ነዋሪም  ሆነ ከተማዋን እንደ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አንድያ መገለጫ ምድር አድርጎ የሚያስበው ዜጋ ይህን የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞችን እና ምሁራን ክርክር ትዝብትም፣ጥርጣሬም፣ድንጋጤም ባጠላበት ዝምታ ነው ያስተዋለው፡፡እንደውም ከነዚህ አይነት የኦሮሞ ብሄርተኞች ይልቅ ቢያስ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአዲስ አበባ እንዲኖር የፈቀደው ኢህአዴግ እጅግ የተሻለ እንደሆነ ቢታሰብ የሚገርም ነገር የለውም፡፡ የኢህአዴግ እቅድም ይኽው ነው – ለመገመት የተዘጋጀን ማስገመት፤ በዚህ ውስጥ ራሱን የተሻለ መድህን አድርጎ ማሳየት! ሲቀጥልም ለአንድ ሰሞን ሲሰማ የነበረውን የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦችን የትብብር ድምፅ በነዚህ የኦሮሞ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ድምፅ በመተካት ሃያ አምስት አመት ሲሰበክ የኖረውን የጥርጣሬ እና የመፈራራት መንፈስ መልሶ በቦታው እንዲተካ ማድረግ ነው፡፡አቶ ጌታቸው ረዳ ኢህአዴግ ቸል አለው ያሉት የቤት ስራም ይሄው ሳይሆን አይቀርም፡፡

አንድም አፍታ ከስራው መዘናጋትን የማያውቀው ኢህአዴግ ይህን ቻርተር ይዞ ብቅ ሲል የኦሮሞ ምሁራንም ቻርተሩ ይስመር አይስመር እንኳን በውል ሳያጤኑ ሆዳቸው ያባውን ሁሉ ትዝብትን ሳይፈሩ አውጥውታል፡፡ ጭራሽ የኦሮሞ ህዝብ አንድ አመት ሙሉ ሲሞትለት የኖረው ጥያቄ አዲስ አበባን በባለቤትነት የማስተዳደር ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ለማድረግም ይቃጣዋል ክርክራቸው፡፡ባለፈው አመት የኦሮሞ ህዝብ አምርሮ ሲያነሳው የኖረው አንገብጋቢ ጥያቄ ከኖረበት ቀየው በድንገት ባዶ እጁን ወይም እፍኝ በማትሞላ ካሳ መፈናቀሉን በመቃወም እንጅ  አዲስ አበባን ለኦሮሞ ቤት ለሌላው የሰው ቤት ለማድረግ አልነበረም፡፡የልሂቃኑ ክርክር እና የአገሬው ኦሮሞ ችግር እና ፍላጎት ይህን ያህል አልተገናኝቶ መሆኑ ግር ያሰኛል፡፡ከሃገር ርቀው እንደመኖራቸው  ሃገርቤት ያለውን ኦሮሞ መሰረታዊ ጥያቄ ለማወቅ ይቸገራሉ ቢባል እንኳን ቆምኩለት ከሚሉት” ህዝብ  የልብ ርትታ እንዲህ እጅግ መራራቁ ጤናማ አይመስልም፡፡

አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ፖለቲከኞች ደጋግመው የሚያነሱት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ይገባል የሚሉት የባለቤትነት መብት ጥያቄ ማስረጃ አድርገው የሚያነሷቸው ነጥቦች ወደ ሶስት ማጠቃለል ይቻላል፡፡ አንደኛው እና ለተቀሩት መከራከሪያ ነጥቦች መሰረት የሚሆነው ኦሮሞዎች የአዲስ አበባ ቀደምት ህዝቦች ናቸው የሚለው ትርክት ነው፡፡ለዚህ ትርክት ከማለት ባለፈ በበቂ ታሪካዊ መዛግብት የተደገፈ ማስረጃ ከተከራካሪዎች ሲቀርብ  አላጋጠመኝም፡፡ ይልቅስ ከዚህ እሳቤ በተቃራኒው የቆሙ ተከራካሪዎች የተሻለ የታሪክ ማስረጃ አቅርበው ይከራከራሉ፡፡ሁለተኛው የሃገራችን ህገ-መንግስት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ መብት እንዲኖራት ስለሚያዝ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ሶስተኛው የክርክሩ ማስረጃ አዲስ አበባ(ሐረር፣ድሬዳው፣ሞያሌ ጭምር የሚሉ ተከራካሪዎችም አሉ)በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ በመሆኗ ከኦሮሚያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን ስለምትጠቀም፣ከተማዋ ለውጋጆቿ መዳረሻም አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖችን ስለምትጠቀም ኦሮሚያ በከተማዋ ላይ ልዩ ጥቅም ያስፈልጋታል የሚል ነው፡፡ እነዚህ የክርክር ማስረጃዎች ተደርገው የቀረቡ እሳቤዎች ራሳቸው ሊጠየቁ የሚገቡ በመሆናቸው በሚቀጥለው እትም እመለስባቸዋለሁ፡፡

​ኢትዮጲያ የማን ናት? የብሔሮች ወይስ የዜጎች: ክፍል-1 

ከዴሞክራሲ ቅፅበት ወደ አምባገነናዊ ፅልመት በ10 አመት
ከድጋፍና ተቃውሞ ባሻገር ሁላችንም የኢህአዴግ መንግስት የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥንቃቄ ማጤንና ማወቅ ይኖርብናል። ተወደደም-ተጠላ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው። በመሆኑም፣ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ባህሪ ማወቅ አለባቸው። ምክንያቱም፣ አላዋቂ ደጋፊ መንግስትን ለውድቀት ይዳርጋል። አላዋቂ ተቃዋሚ ደግሞ የለውጥ እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ፣ ሁላችንም “የተወሰነም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ለምን ተመልሶ አምባገነን ሆነ?” ብለን መጠየቅ አለብን። 

በእርግጥ “እንዴ…ለመሆኑ የኢህአዴግ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ሞክሮ ያውቃል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። “ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ጥሩ ነው” ይባላል። የኢህአዴግ መንግስትም ቢያንስ በ1987 ዓ.ም ባፀደቀው ሕገ-መንግስት እና በ1997ቱ ምርጫ (እስከ ምርጫው ዕለት ማታ ድረስ) ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ማድረጉ ሊታወስ ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ከ1997 ዓ.ም በፊት “ሕገ-መንግስቱ ይከበር!” ሲል የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በቀጣይ አስር አመታት ግን ሕገ-መንግስቱን የሚጥሰው እሱ ራሱ ሆነ። 

የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% “አሸነፍኩ” ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው። የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል። 

የኢህአዴግ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል። 

በአጠቃላይ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ የታየው የዴሞክራሲ ቅፅበት ከአስር አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ በአምባገነናዊ ፅልመት ተውጧል። በተለይ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተዘረዘሩት አብዛኞቹ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተጥሰዋል። በተደጋጋሚ ጥሰት ከተፈፀመባቸው ውስጥ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 14፥ 15፥ 16፥ 17፥ 18፥ 19፥ 20፥ 21፥ 25፥ 26፥ 27፥ እና 28 ላይ የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም በአንቀፅ፡- 29፥ 30፥ 31፥ 37፥ 38፥ 40 እና 44 ላይ የተደነገጉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። 

“የሕዝብ ሉዓላዊነት” ወይስ “የብሔር ሉዓላዊነት”?

በመሰረቱ የኢሀአዴግ መንግስት እንደ መንግስት የተቋቋመው እነዚህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር ነበር። ይሁን እንጂ፣ እነዚህን መብቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጥሰው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ነው። ታዲያ፣ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተደጋጋሚ የሚጣሱበት ምክንያት ምንድነው? የኢህአዴግ መንግስት ለምን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር እንደተሳነው ለማወቅ በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት መንግስታዊ ስርዓቱ የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል። 

ማንኛውም ሰው በራሱ አመለካከት ትክክል የመሰለውን ነገር ያደርጋል። ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግን ከግል አመለካከታቸው ባለፈ ሥራና ተግባራቸው የሚመራበት ፖሊሲ፥ መርህና መመሪያ አላቸው። ለእነዚህ ደግሞ ዋና መሰረታቸው ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግስት ነው። ምክንያቱም፣ የመንግስት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። 

በእርግጥ አምባገነናዊም ሆኑ ዴሞክራሲያዊ መንግስታት በሕገ-መንግስታቸው ውስጥ፤ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የሕግ-የበላይነት፣ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ የዜጎች መብትና ነፃነት፣…ወዘተ የሚሉ መሰረታዊ መርሆች አሏቸው። ነገር ግን፣ በተለይ አምባገነን መንግስታት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማረጋገጥ በሚል ሰበብ የዜጎችን መብትና ነፃነት ሲጥሱ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ሀገሪቷንና ሕዝቡን ሲያስተዳድር የነበረው የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚገድቡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ነው። 

ባለፉት አስር አመታት የታየው የኢህአዴግ መንግስት አስተዳደር ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ተፃራሪ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለምሳሌ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 12 መሰረት “የመንግስት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት አለ” እንዳይባል ባለፉት አስር አመታት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ምን ያህል እንደተንሰራፋ መንግስት ራሱ ጠንቅቆ ያውቃል። በአንቀፅ፡-11 መሰረት “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም” እንዳይባል በቅርቡ በእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና በደል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። እንደ ማዕከላዊና ቅሊንጦ ባሉ እስር ቤቶች በፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣…ወዘተ ላይ የሚፈፀመውን የስቃይ ምርመራና እንግልት የሚያውቅ በአንቀፅ፡-10 መሰረት “የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በጭራሽ እንዳልተከበረ ይመሰክራል። በመጨረሻም፣ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፀረ-ሽብር አዋጁ እየተዳኘ ባለበት ሁኔታ በአንቀፅ፡-9 መሰረት “የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ተረጋግጧል” ሊባል አይቻልም። 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከሕገ-መንግስቱ አምስት (5) መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አራቱን ተግባራዊ እያደረገ እንዳልሆነ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡-8 ላይ የተጠቀሰውን “የሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ ግን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። በእርግጥ በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው የሕዝብን የስልጣን የበላይነት አያሳይም። ከዚያ ይልቅ፣ በንዑስ አንቀፅ 8(1) ላይ እንደተገለፀው፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መሰረታዊ መርህ፤ “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው” በሚል ተገልጿል። ቀጥሎ ባለው ንዑስ አንቀፅ 8(2) ደግሞ ሕገ-መንግስቱ (የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች) ሉዓላዊነት መገለጫ” እንደሆነ ይገልፃል። 

በሕገ-መንግስቱ መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተግባር “የብሔር ሉዓላዊነት” ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች” እንጂ የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። በእርግጥ ይህ መርህ ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ጋር ይጋጫል። በመሆኑም፣ ባለፉት አሰር አመታት ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ከመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት፣ ከሕገ-መንግስቱ የበላይነት አንፃር ለተፈጠሩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ዋና መነሻ ምክኒያት ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከላይ የተጠቀሰው መርህ በሕገ-መንግስቱ ከተጠቀሱት መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር ይጣረሳል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት ይህን መርህ ለመከተል ጥረት ባደረገ ቁጥር የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ይጥሳል። በአጠቃላይ፣ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ዴሞክራሲ እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ለቅፅበት ታይቶ እንዲጠፋነና በምትኩ አምባገነናዊ ፅልመት የሰፈነው የኢህአዴግ መንግስት ከሌሎች የዴሞክራሲ መርሆች ይልቅ ይሄን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከሩ ምክንያት ነው። 

ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነሱም፣ አንደኛ፡- “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑ እና ሁለተኛ፡- ፖለቲካዊ ስርዓቱ በዚህ የተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ናቸው። በሚቀጥለው ክፍል “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ብሔር ወይስ ግለሰብ?” በሚል የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 የተመሰረተበትን የተሳሳተ እሳቤ በዝርዝር እንመለከታለን።         

ምክር ቤቱ ሶስት ዳኞችን በስነ ምግባር ችግር አሰናበተ

አዲስ አበባ ጥር 28/2008 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስነ-ምግባር ችግር የታየባቸውን ሶስት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች አሰናበተ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ እንዲሰናበቱ ያደረጋቸው ዳኞች የህግ ጥሰት በመፈጸምና ለህገመንግስቱ ታማኝ ባለመሆን በፈፀሙት የስነ- ምግባር ጉድለት ነው።

ምክር ቤቱ እንዲሰናበቱ ያደረገው በዛሬው እለት ከዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበለትን ማስረጃ መሰረት በማድረግ ነው።

ከዳኝነት ስራቸው እንዲሰናበቱ ምክር ቤቱ ቅጣት ያስተላለፈባቸው ዳኞች አቶ ግዛቸው ምትኩ፣አቶ ሀብታሙ ሚልኪ እና አቶ አብረሐ ተጠምቀ ናቸው።

ምክር ቤቱ አቶ ግዛቸውን ከዳኝነት ሥራቸው እንዲሰናበቱ ያደረገው “ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል በተደጋጋሚ የሚጠቅሱ በመሆኑ፣ለህገ-መንግስቱ ታማኝ ባለመሆናቸው፣ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባል ያልሆነችው መንግስት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰት ስለሚፈጽም ተጠያቂ ላለመሆን ነው፣በኢትዮጵያ የብሔር እኩልነት አልተረጋገጠም” በማለታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

እንዲሁም በጀት ከሚመለስ ለምን እቃ አይገዛም ወይም ለምን ዳኞች እንዲከፋፈሉት አይደረግም የሚል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት የሚያራምዱ ለመሆናቸው ለምክር ቤቱ ቀርቧል።

ህገመንግስቱን በታማኝነት ሙሉ ለሙሉ ባለመቀበላቸውና የዳኝነት ነጻነትና ገለልተኝነት የጎደለባቸው በመሆኑ ምክር ቤቱ ከስራቸው እንዲሰናበቱ አድርጓል።

አቶ ሀብታሙ ሚልኪ ደግሞ “በተከራካሪዎች ላይ የስነ-ምግባር ግድፈት በመፈፀም፣በግልጽ አሰራር፣በዳኝነት ነጻነት ችግርና በፍርድ ቤቶች ተዓማኒነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖን የሚያሳርፍ ከባድ ጥፋት ፈፅመዋል” የሚል ማስረጃ በመቅረቡ ነው።

ዳኛው በሰሩት የስነ ምግባር ግድፈት በአስተዳደሩ ከተመደቡበት ስራ ውጭ የሌላ ችሎት መዝገብ ስበው በማየትና ትእዛዝ በመስጠታቸው፣ የተለያዩ ተደራራቢ ድንጋጌዎችን መተላለፋቸው፣በተመሳሳይ ደረጃ ባለ ዳኛ ከተሰጠ ትእዛዝ በተቃራኒ ትዕዛዝ በመስጠታቸው እንደሆነ ተገልጿል።

በምክር ቤቱ እንዲሰናበቱ የተደረጉት ሦስተኛው ዳኛ አቶ አብርሐ ተጠምቀም በዓቃቤ ህግ በኩል እንዳያዩት አቤቱታ የቀረበበትን መዝገብ ማየት መቀጠላቸው ከቀረቡባቸው አምስት የስነ ምግባር ግድፈቶች አንዱ ነው።

ዳኛው ከተከሳሽ ወገን ዝምድና ያላቸው በመሆኑ ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ እንዲዘዋወር በሌላ ደኛ ቀጠሮ የተላለፈበት ችሎት በአዲስ አበባ እንዲታይ ትእዛዝ ለውጠው ሰጥተዋልም ተብሏል።

በሌላ ዳኛ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፎበት ውሳኔ ተሰጥቶበት ለቅጣት ያደረ መዝገብ ወስደው ቅጣቱን በመወሰናቸውና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ሲታይ የነበረ የወንጀል ጉዳይ እንዲቋረጥ ጉዳዩን በሚያዩ ዳኞች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠራቸው መሆኑን ተገልጿል።

ማስተባበያ እንዲቀርብለት የተያዘ የቅሬታ ነጥብ በተዘዋዋሪ ችሎት በደቡብ ክልል ሲታይ በነበረው የወንጀል ክርክር በዓቃቤ ህግ የቀረቡ ምስክሮችን ያለ አግባብ በማዋካብና ገለልተኛ ባለመሆናቸው ምክር ቤቱ አሰናብቷቸዋል።
****
Featured, 07 Feb 2016|ፖለቲካ
www.ena.gov.et

ethiothinkthank.com