Tag Archives: ethnic-nationalism

​ኢትዮጲያ የእኔ ናት! ብሔር መብት የለውም! /ክፍል-3/

“John Locke” የተባለው ፈላስፋ “An Essay Concerning Human Understanding” በሚለው መፅሃፉ የሰው ልጅ ሁለት ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪያት እንዳሉት ይገልፃል። እነሱም፣ ማሰብ (Thinking) እና ፍቃድ (Will) ናቸው። በዚህ መሰረት፣ የሰው ልጅ በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያደርጋል። በራስ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ደግሞ “ነፃነት” (Liberty) ይባላል። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት የሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። 
የሰው ልጅ ነፃነት ለሦስት ይከፈላል። እነሱም፣ 1ኛ፡- ሌላውን ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፣ … መብት። 2ኛ፡- በባዕድ መንግስት ወይም ለሌላ አካል ተገዢ ያለመሆን መብት፣ እና 3ኛ፡- ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት መብት ናቸው። በአማርኛ “መብት” (right) የሚለውን ቃል አንድ ሰው በአንድ ነገር ወይም ጉዳይ ላይ የሚፈልገውን ለማድረግ ሆነ ላለማድረግ የሚያስችለው ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ ነፃነት ሁሉን-አቀፍና ምሉዕ የሆነ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሲሆን መብት ደግሞ ነፃነትን የማስከበር “ስልጣን” (authority) ነው። 

ነፃነት ያለ ምንም ውጫዊ ኃይል ወሳኝነት በነፃ-ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት እንደመሆኑ መጠን ከኃላፊነት ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ስለዚህ፣ ሕይወትን በነፃ ፍላጎትና ምርጫ ለመምራት የሚያስፈልገው ነፃነት የሚገኘው ለተግባራዊ እንቅስቃሴያችን “ኃላፊነት” (responsibility) መውሰድ ስንችል ነው። ከዚህ አንፃር፣ ጀርመናዊው ፈላስፋ “Nietzsche” “Only individuals have a sense of responsibility” ይላል። በመሆኑም፣ ኃላፊነት መውሰድ የሚችሉት ግለሰቦች (individuals) ብቻ ናቸው።

የኣማርኛ መዝገበ ቃላት “ሀገር” የሚለውን ቃል “በውስጡ ህዝቦች የሚኖሩበት፣ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት” እንደሆነ ይገልፃል። በተመሳሳይ፣ “ሉኣላዊ” (Sovereign) ማለት ደግሞ “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” እንደሆነ ይገልፃል። ስለዚህ፣ በተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሉዓላዊ ሀገር፥ መንግስት የሚመሰርቱት በነፃነት ለመኖር ነው። 

ስለ መንግስት አመሰራረት ከተፃፉት መፅሃፍት ውስጥ በ“Thomas Hobbes” የተፃፈው “Leviathan” የተሰኘው መፃሃፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። እንግሊዛዊ ፈላስፋ በተጠቀሰው መፅሃፍ ስለ መንግስት አመሰራረት እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ ትንታኔ ሰጥቶበታል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሉዓላዊ ሀገር የሚመሰርቱት በተፈጥሮ ካገኙት ነፃነት ላይ የተወሰነውን በውክልና ለመንግስት አሳልፈው በመስጠት እንደሆነ ይገልፃል። 

በዚህ መሰረት፣ መንግስት የሚመሰረተው የሁሉም ሰዎች መብትና ነፃነት እንዲከበር ነው። በመሆኑም ሁሉም ሰዎች የሌሎችን መብት ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር ለመስራት፥ ለመናገር፥ ለመፃፍ፣ እንዲሁም በባዕድ መንግስት ወይም ለሌላ ሦስተኛ አካል ቁጥጥር ስር እንዳይወድቁ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን “ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት መብትን” ለመንግስት አሳልፈው ይሰጣሉ። ይህ የውል ስምምነት ደግሞ በሕገ መንግስት አማካኝነት የሚከናወን ይሆናል። 

ሕገ-መንግስት በጥቅሉ በመንግስትና በሕዝብ መካከል የተደረሰ ስምምነት አይደልም። ከዚያ ይልቅ፣ “እያንዳንዱ” ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ የተስማሙበት ሰንድ ነው። በዚህ የውክልና ሰነድ ላይ እያንዳንዱ ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በጋራ በገቡት ውል መሰረት የሁሉም ሰዎች ነፃነት እኩል እንዲከበር እያንዳንዱ ሰው ራሱን-በራሱ የማስተዳደር ስልጣኑን በውክልና ለመንግስት አሳልፎ ይሰጣል። ይህን “Thomas Hobbes” እንደሚከተለው ገልፆታል፡- 

 “This is more than consent, or concord; it is a real unity of them all in one and the same person, made by covenant of every man with every man, in such manner as if every man should say to every man: ‘I authorize and give up my right of governing myself to this assembly of men, on this condition; that you give up, your right to them, and authorize all their actions in like manner.’ This done, the multitude so united in one person is called a COMMONWEALTH… And he that carries this person is called sovereign, and said to have sovereign power;….” Leviathan, Part-II, CH. XVII, Para-13 

ከላይ በተገለፀው መሰረት ለመንግስት በውክልና የተሰጠው ስልጣን ከእያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ የተቀነሰ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብት፥ ስልጣን ነው። ስለዚህ፣ የመንግስት ሉዓላዊ ስልጣን ከእያንዳንዱ ሰው ላይ የተቀነሰ ነፃነት ወይም ራስን-በራስ የማስተዳደር ስልጣን ነው። በመሆኑም፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቱ እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ወይም ግለሰብ ነው። 

በኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት ግን የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን (sovereign power) ባለቤት እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። ከዚያ ይልቅ፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ በሕገ መንግስቱ ተገልጿል። ነገር ግን፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በራሳቸው ኃላፊነት (responsibility) መውሰድ አይችሉም። በመሆኑም፣ መብትና ነፃነት የላቸውም፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆኑ አይችሉም።     

አንድ ነገር ነፃነት እንዲኖረው በቅድሚያ እንደ ሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ሊኖረውና በራሱ ፍቃድና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የሌለው አካል በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መሰረት፤ መስራት፥ መናገር፥ መፃፍ…መብት፣ ያለገደብ ከቦታ-ቦታ የመንቀሳቀስ መብት፣ እንዲሁም ራሱን በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ይህ መብት እንዲኖረው በቅድሚያ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ መቻል አለበት። 

እያንዳንዱ ግለሰብ እንደ ምክንያታዊ ፍጡር በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ ይችላል። ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤ የቋንቋ፥ ባህልና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም የታሪክና ኢኮኖሚ ትስስር ውጤት ናቸው። በእርግጥ እያንዳንዱ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ የግለሰቦች ስብስብ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ግለሰብ በራሱ የሚመራበት ምክንያታዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የለውም። ምክንያቱም፣ ብሔር ልክ እንደ ግለሰብ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ የሚመራ ምክንያታዊ ፍጡራን አይደለም። 

በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ የማይችል አካል ደግሞ “ነፃነት” (Liberty) የለውም። በመሆኑም፣ በነፃ-ፍላጎት (free will) የመንቀሳቀስ፣ አማራጭ መንገድን የመወሰና፣ በራስ ምርጫ የማሰብ፣ ማድረግና የመኖር መብት (right) የለውም። በመሰረቱ፣ መብት ወይም ስልጣን እንዲኖርህ በቅድሚያ የሚከበር ነፃነት ሊኖርህ ይገባል። ነፃነት የሌለው አካል ራስን-በራሱ የማስተዳደርና የመምራት ስልጣን ሊኖረው አይችልም።

ራስን-በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት አቅምና ስልጣን የሌለው አካል ለመንግስት በውክልና አሳልፎ የሚሰጠው ስልጣን የለውም። ማንኛውም ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በራሱ ፍላጎት (ሃሳብ) እና ፍቃድ (ምርጫ) መንቀሳቀስ ስለማይችል ነፃነት የለውም። በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። በመሆኑም፣ ራስን-በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት መብት የሌለው አካል ለመንግስት በውክልና አሳልፎ የሚሰጠው ስልጣን የለውም።  

የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ነው” የሚለው ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የራሳቸው መብትና ነፃነት የላቸውም። የራሳቸው መብትና ነፃነት እስከሌላቸው ድረስ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ሊሆኑ አይችሉም። “የሕዝብ ሉዓላዊነት”ን የሚደነግገው የኢፊዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 (1) “ኢትዮጲያዊያን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” ተብሎ መስተካከል አለበት። 

በአጠቃላይ፣ “ኢትዮጲያ የማን ናት?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “የእኔ ናት!” ነው። እኔ ምክንያታዊ ፍጡር ስለሆንኩ ነፃነት፥ መብትና ስልጣን አለኝ። ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ በራሱ ነፃነት የለውም! መብት የለውም! ስልጣን የለውም! 

​ኢትዮጲያ የማን ናት? መብቱ የዜጎች፣ ስልጣኑ የብሔሮች ነው! /ክፍል-2/

“ኢትዮጲያ የማን ናት፡ የብሔሮች ወይስ የዜጎች?” በሚል ርዕስ ባወጣነው የመጀመሪያ ክፍል የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ፍፁም አምባገነን እየሆነ መምጣቱን ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋና ምክንያቱ ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ውስጥ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው መርህ ላይ መንጠልጠሉና በዚህም ራሱ የዘረጋውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ቀልብሶታል።  
በመሰረቱ፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው ሕገ-መንግስታዊ መርህ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። ሌላው ቀርቶ ከሕገ-መንግስቱ ጋር ራሱ ይጋጫል። በአጠቃላይ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ “ፀረ-ዴሞክራሲያዊ” ነው። “በእንቅርት ላይ ጆሮ-ደግፍ” እንዲሉ መንግስታዊ ስርዓቱ ደግሞ በዚህ መርህ ላይ እንደመሆኑ ሕገ-መንግስቱ፥ ብሎም ፖለቲካዊ ስርዓት ካልተቀየረ በስተቀር ዴሞክራሲ “ላም አለኝ በሰማይ…” እንደሚሉት ሆኖ ይቀራል። በዚህ ፅሁፍ፣ “ከሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ አንፃር የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ እንመለከታለን። በቀጣይ ክፍል ደግሞ ከሀገርና መንግስት አመሰራረት አንፃር የተሳሳተ መሆኑን እንመለከታለን።    

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው”።ነገር ግን፣ ይህ መርህ ከሉዓላዊነት ፅንሰ-ሃሳብ ጋር ይጋጫል። በዚህ ረገድ ያለውን የተሳሳተ እሳቤ በግልፅ ለመረዳት እንዲያስችለን የሕገ-መንግስቱን የቃላት አጠቃቀም እና የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ያዘጋጀውን የኣማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት በማድረግ ፅንሰ-ሃሳቡን በዝርዝር እንመለከታለን። 

በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 39(5) መሰረት “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” ማለት ሰፋ ያለ የጋራ ባህሪይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብለው የሚያምን፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር “ማህብረሰብ” ነው። (የቃላት ድግግሞሽን ለማስቀረት ሲባል እንደየሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ” የሚለው “ብሔር” ተብሎ ሊፃፍ ይችላል።) በዚህ መሰረት፣ ብሔር በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነልቦናዊ አመካከት፣ እንዲሁም በታሪክ፣ ኢኮኖሚና በመልክዓ ምድር የተሳሰረ ማህብረሰብ ነው። በመሆኑም፣ የብሔር መብቶች ከእነዚህ ተፈጥሯዊ ባህሪያት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 39 ላይ “የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት” በሚል የተጠቀሱት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይህን ያመለክታሉ። 

መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በተደነገጉበት የሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል ሁለት መሰረት፣ በንዑስ አንቀፅ 39(1) “ማንኛውም ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(2) “ማንኛውም ብሔር በቋንቋው የመናገር፥ የመፃፍ፥ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ፥ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት”፣ በንዑስ አንቀፅ 39(3) ደግሞ “ማንኛውም ብሔር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ መብት” እንዳለው ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በሕገ-መንግስቱ ንዑስ አንቀፅ 40(3) መሰረት “የመሬት ባለቤትነት መብት”፣ እንዲሁም በንዑስ አንቀፅ 43(1) መሰረት ደግሞ “የልማት መብት” እንዳላቸው ይጠቅሳል። 

በዋናነት በሕገ-መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከዚህ በተረፈ፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ ስር የተዘረዘሩት በሙሉ የግለሰብ ሰብዓዊ መብቶች ናቸው። በክፍል ሁለት ከተዘረዘሩት ውስጥ ከአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) በስተቀር ያሉት በሙሉ የግለሰብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ግን እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ከላይ የተጠቀሱት የብሔር መብቶች ይኖሩታል።

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ሉኣላዊ” (Sovereign) የሚለውን ቃል “ነፃ የሆነ መሬት፣ ነፃ የሆነ፥ ምሉዕ ስልጣን ያለው ሀገር፥ መንግስት” የሚል ፍቺ ይሰጠዋል። “ሉዓላዊነት” (Sovereignity) ማለት ደግሞ “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” እንደሆነ ይገልፃል። በዚህ መሰረት፣ “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” የሆነ አካል በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል።     

በአጠቃላይ፣ በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሙሉ መሰረታዊ የግለሰብ መብትና ነፃነት ሊሆኑ ይችላሉ። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብቶች ግን በአንቀፅ 39፣ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት መብቶች ብቻ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ግለሰብ ምሉዕ መብትና ነፃነት አለው። በተቃራኒው አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ግን ምሉዕ መብትና ነፃነት የለውም። 

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንተሞከረው፣ “ሉኣላዊነት” (Sovereignity) ማለት “ምሉዕ የሆነ መብት፥ የነፃነትና ሥልጣን የበላይነት” ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሉዓላዊ ስልጣን እንዲኖረው በቅድሚያ ምሉዕ መብትና ነፃነት ሊኖረው ይገባል። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ክፍለ አንድና ሁለት ስር ከተዘረዘሩት 31 መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ውስጥ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች መብት የሆኑት በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ውጪ ያሉት በሙሉ የግለሰብ መብቶች ናቸው። 

እያንዳንዱ ግለሰብ በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) የተጠቀሱት የብሔር መብቶች እንደ አንድ ብሔር ተወላጅ ይኖሩታል። እያንዳንዱ ብሔር ግን በአንቀፅ 39፣ ንዑስ አንቀፅ 40(3) እና 43(3) ከተጠቀሱት ውጪ ሌላ ዴሞክራሲያዊ መብት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም፣ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እንደ ግለሰብ በራሱ ሃሳብና አመለካከት የሚንቀሳቀስ ምክንያታዊ ፍጡር ስላልሆነ ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሉትም። በተመሳሳይ፣ እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ስላልሆነ “ሰብዓዊ” መብት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ በሕገ-መንግስቱ ራሱ ምሉዕ መብት ያለው ግለሰብ እንጂ ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ አይደለም። 

በአጠቃላይ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችለው እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ እንጂ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች አይደሉም። ምክንያቱም፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት በምዕራፍ ሦስት ስር ከዘረዘራቸው 31 መሰረታዊ መብቶች ውስጥ ሦስት መብቶች ብቻ ያሏቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች “የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” እንደሆኑ ይገልፃል። ነገር ግን፣ “ሉኣላዊነት” የምሉዕ መብትና ነፃነት ባለቤትነት እንደመሆኑ መጠን ውስን መብት ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ሊኖራቸው አይችልም። በዚህ መሰረት፣ የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት እርስ-በእርሱ እንደሚጋጭ በግልፅ መረዳት ይቻላል። 

በመጨረሻም፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ምሉዕ የሆነ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አለው። በዚህ መሰረት፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆን የሚችሉት ሁሉም ኢትዮጲያዊያን ወይም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 መሰረት “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች እንደሆኑ ተደንግጓል። ስለዚህ፣ ሕገ-መንግስቱ እርስ-በእርስ እንዲጋጭ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው? 

በመሰረቱ፣ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆነ አካል ባለመብት ብቻ ሳይሆን ባለስልጣን ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ሉዓላዊ ስልጣን ያለው አካል በሀገሪቱ መንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ይኖረዋል። ስለዚህ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተጠሪነቱ ለዚህ አካል ይሆናል። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት፤ የሀገሪቱ ዜጎች መብትና ነፃነት አላቸው፣ ብሔሮች ደግሞ የሉዓላዊ ስልጣን አላቸው። ዜጎች ምሉዕ መብት አላቸው፣ ነገር ግን መብታቸውን የመጠየቅ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን የላቸውም። ብሔሮች ደግሞ ምሉዕ (ሉዓላዊ) ስልጣን አላቸው፣ የሚጠይቁት ምሉዕ መብት ግን የላቸውም። በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት መብቱ የዜጎች ሲሆን ስልጣኑ ግን የብሔሮች ነው! 

በአጠቃላይ፣ የሀገሪቱ ዜጎች የማይጠይቁት መብት ሲኖራቸው፣ የሀገሪቱ ብሔሮች ደግሞ የማይጠቀሙት ስልጣን አላቸው። የኢህአዴግ መንግስት ዘወትር ስለ ብሔር መብትና እኩልነት ይደሰኩራል። ዜጎች የመብትና እኩልነት ጥያቄ ሲያነሱ ግን እንደ ጠላት እያደነ ያስራል፥ ይገድላል፥…ወዘተ።  

​ኢትዮጲያ የማን ናት? የብሔሮች ወይስ የዜጎች: ክፍል-1 

ከዴሞክራሲ ቅፅበት ወደ አምባገነናዊ ፅልመት በ10 አመት
ከድጋፍና ተቃውሞ ባሻገር ሁላችንም የኢህአዴግ መንግስት የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥንቃቄ ማጤንና ማወቅ ይኖርብናል። ተወደደም-ተጠላ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለው ኢህአዴግ ነው። በመሆኑም፣ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ባህሪ ማወቅ አለባቸው። ምክንያቱም፣ አላዋቂ ደጋፊ መንግስትን ለውድቀት ይዳርጋል። አላዋቂ ተቃዋሚ ደግሞ የለውጥ እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ፣ ሁላችንም “የተወሰነም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ሲያደርግ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ለምን ተመልሶ አምባገነን ሆነ?” ብለን መጠየቅ አለብን። 

በእርግጥ “እንዴ…ለመሆኑ የኢህአዴግ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ሞክሮ ያውቃል እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። “ለሰይጣንም ቢሆን የድርሻውን መስጠት ጥሩ ነው” ይባላል። የኢህአዴግ መንግስትም ቢያንስ በ1987 ዓ.ም ባፀደቀው ሕገ-መንግስት እና በ1997ቱ ምርጫ (እስከ ምርጫው ዕለት ማታ ድረስ) ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ጥረት ማድረጉ ሊታወስ ይገባል። ይሁን እንጂ፣ ከ1997 ዓ.ም በፊት “ሕገ-መንግስቱ ይከበር!” ሲል የነበረው የኢህአዴግ መንግስት በቀጣይ አስር አመታት ግን ሕገ-መንግስቱን የሚጥሰው እሱ ራሱ ሆነ። 

የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% “አሸነፍኩ” ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው። የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል። 

የኢህአዴግ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል። 

በአጠቃላይ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ የታየው የዴሞክራሲ ቅፅበት ከአስር አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ በአምባገነናዊ ፅልመት ተውጧል። በተለይ የፀረ-ሽብር ሕጉ ከወጣበት ግዜ ጀምሮ በሕገ-መንግስቱ ምዕራፍ ሦስት ስር የተዘረዘሩት አብዛኞቹ መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ተጥሰዋል። በተደጋጋሚ ጥሰት ከተፈፀመባቸው ውስጥ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 14፥ 15፥ 16፥ 17፥ 18፥ 19፥ 20፥ 21፥ 25፥ 26፥ 27፥ እና 28 ላይ የተደነገጉት ሰብዓዊ መብቶች፣ እንዲሁም በአንቀፅ፡- 29፥ 30፥ 31፥ 37፥ 38፥ 40 እና 44 ላይ የተደነገጉት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። 

“የሕዝብ ሉዓላዊነት” ወይስ “የብሔር ሉዓላዊነት”?

በመሰረቱ የኢሀአዴግ መንግስት እንደ መንግስት የተቋቋመው እነዚህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር ነበር። ይሁን እንጂ፣ እነዚህን መብቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጥሰው የኢህአዴግ መንግስት ራሱ ነው። ታዲያ፣ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተደጋጋሚ የሚጣሱበት ምክንያት ምንድነው? የኢህአዴግ መንግስት ለምን የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር እንደተሳነው ለማወቅ በፅሁፌ መግቢያ ላይ እንደገለፅኩት መንግስታዊ ስርዓቱ የሚመራበትን መርህና መመሪያ በጥሞና ማጤን ያስፈልጋል። 

ማንኛውም ሰው በራሱ አመለካከት ትክክል የመሰለውን ነገር ያደርጋል። ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ግን ከግል አመለካከታቸው ባለፈ ሥራና ተግባራቸው የሚመራበት ፖሊሲ፥ መርህና መመሪያ አላቸው። ለእነዚህ ደግሞ ዋና መሰረታቸው ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ-መንግስት ነው። ምክንያቱም፣ የመንግስት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። 

በእርግጥ አምባገነናዊም ሆኑ ዴሞክራሲያዊ መንግስታት በሕገ-መንግስታቸው ውስጥ፤ የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ የሕግ-የበላይነት፣ የመንግስት ግልፅነትና ተጠያቂነት፣ የዜጎች መብትና ነፃነት፣…ወዘተ የሚሉ መሰረታዊ መርሆች አሏቸው። ነገር ግን፣ በተለይ አምባገነን መንግስታት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማረጋገጥ በሚል ሰበብ የዜጎችን መብትና ነፃነት ሲጥሱ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት አስር አመታት ሀገሪቷንና ሕዝቡን ሲያስተዳድር የነበረው የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚገድቡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ነው። 

ባለፉት አስር አመታት የታየው የኢህአዴግ መንግስት አስተዳደር ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ተፃራሪ እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለምሳሌ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡- 12 መሰረት “የመንግስት አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት አለ” እንዳይባል ባለፉት አስር አመታት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ምን ያህል እንደተንሰራፋ መንግስት ራሱ ጠንቅቆ ያውቃል። በአንቀፅ፡-11 መሰረት “መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገባም” እንዳይባል በቅርቡ በእስልምና ሃይማኖት መሪዎች ላይ የተፈፀመውን ግፍና በደል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። እንደ ማዕከላዊና ቅሊንጦ ባሉ እስር ቤቶች በፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾች፣…ወዘተ ላይ የሚፈፀመውን የስቃይ ምርመራና እንግልት የሚያውቅ በአንቀፅ፡-10 መሰረት “የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በጭራሽ እንዳልተከበረ ይመሰክራል። በመጨረሻም፣ ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፀረ-ሽብር አዋጁ እየተዳኘ ባለበት ሁኔታ በአንቀፅ፡-9 መሰረት “የሕገ-መንግስቱ የበላይነት ተረጋግጧል” ሊባል አይቻልም። 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ከሕገ-መንግስቱ አምስት (5) መሰረታዊ መርሆች ውስጥ አራቱን ተግባራዊ እያደረገ እንዳልሆነ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ፡-8 ላይ የተጠቀሰውን “የሕዝብ ሉዓላዊነት” መርህ ግን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል። በእርግጥ በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው የሕዝብን የስልጣን የበላይነት አያሳይም። ከዚያ ይልቅ፣ በንዑስ አንቀፅ 8(1) ላይ እንደተገለፀው፣ “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መሰረታዊ መርህ፤ “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ናቸው” በሚል ተገልጿል። ቀጥሎ ባለው ንዑስ አንቀፅ 8(2) ደግሞ ሕገ-መንግስቱ (የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች) ሉዓላዊነት መገለጫ” እንደሆነ ይገልፃል። 

በሕገ-መንግስቱ መሰረት “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተግባር “የብሔር ሉዓላዊነት” ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች” እንጂ የሀገሪቱ ዜጎች አይደሉም። በእርግጥ ይህ መርህ ከተቀሩት የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ጋር ይጋጫል። በመሆኑም፣ ባለፉት አሰር አመታት ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ከመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት፣ ከሕገ-መንግስቱ የበላይነት አንፃር ለተፈጠሩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ዋና መነሻ ምክኒያት ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከላይ የተጠቀሰው መርህ በሕገ-መንግስቱ ከተጠቀሱት መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር ይጣረሳል። በዚህ ምክንያት፣ መንግስት ይህን መርህ ለመከተል ጥረት ባደረገ ቁጥር የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ይጥሳል። በአጠቃላይ፣ በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ ዴሞክራሲ እንደ ተወርዋሪ ኮኮብ ለቅፅበት ታይቶ እንዲጠፋነና በምትኩ አምባገነናዊ ፅልመት የሰፈነው የኢህአዴግ መንግስት ከሌሎች የዴሞክራሲ መርሆች ይልቅ ይሄን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከሩ ምክንያት ነው። 

ለዚህ ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እነሱም፣ አንደኛ፡- “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑ እና ሁለተኛ፡- ፖለቲካዊ ስርዓቱ በዚህ የተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ናቸው። በሚቀጥለው ክፍል “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት ብሔር ወይስ ግለሰብ?” በሚል የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 8 የተመሰረተበትን የተሳሳተ እሳቤ በዝርዝር እንመለከታለን።         

ብሔርተኝነት እና አንድነት

ብሔርተኝነት ራስ-ወዳድነት ነው!!!

አንዳንድ ሰዎች በብሔርተኝነትና ዘረኝነት ወይም በብሔር እና በዘር ልዩነት ላይ በተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ አድርገው ሲያቀርቡ ሳይ በጣም ይገርመኛል። ነገር ግን፣ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት ተለያይተው አያውቁም። “ዘረኛ” የሚለው ቃል “በዘር ምክንያት ለአንዱ የሚያደላ፣ ሌላውን የሚጎዳ፣ የዘረኝነት አስተሳሰብን፥ አመለካከትን የሚያራምድ” ማለት ነው። “ብሔርተኛ” ደግሞ “ለብሔሩ (ጎሳው) ብቻ የሚስብና የሚያደላ፣ በሌላ ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ነው። “ዘረኝነት” የዘረኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ሲሆን “ብሔርተኛ” ደግሞ የብሔርተኛ አቋምን የያዘ አመለካከት ነው። በዚህ መሰረት፣ ዘረኛ ሆነ ብሔርተኛ ሁለቱም በአድልዎ ላይ የተመሰረቱ አመለካከቶች ናቸው። በሁለቱም ውስጥ ለራስ ዘር/ብሔር ማድላት፥ መደገፍና ክፍ ክፍ ማድረግ አለ። በተመሳሳይ፣ በሁለቱም ውስጥ የሌላን ዘር/ብሔር ማግለል፥ መለየትና መጥላት አለ። በዘረኝነትና ጠባብነት ውስጥ ራስን መውደድ ብቻ ሳይሆን ሌሎችን መጥላት፣ ለራስ ማዳላትና መጥቀም ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማግለልና መጉዳት አለ። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ማለት ራስ-ወዳድነት ነው!!! በራስ-ወዳድነት ወይም ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መጨረሻው አድሏዊና ጨቋኝ የሆነ ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው።

አንድነት እኩልነት ነው!!!

ብዙውን ግዜ “አንድነት” የሚለው ቃል የተዛባ ትርጉምና ፍቺ ሲሰጠው ማየት የተለመደ ነው። በአብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ በስፋት የሚንፀባረቀው የአህዳዊ አንድነት ፅንሰ-ሃሳብ ነው። በዚህ መሰረት “አንድነት” ሲባል የአንድ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥…ወዘተ ተመሳሳይነት ተደርጎ ይገለፃል። ይህ ደግሞ በብሔርተኛ ቡዱኖች ዘንድ የአንድ ብሔር፥ ቋንቋና ባህል የበላይነት እንደሆነ ይገልፃሉ። ነገር ግን፣ የሁለቱም ወገኖች አመለካከት የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም፣ የአንድነት ፅንሰ-ሃሳብ በብሔር፥ ቋንቋ ወይም ባህል ተመሳሳይነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ፖለቲካዊ አንድነት በሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሁለም ሰው እኩል መብትና ነፃነት አለው። በመሆኑም፣ “ለእኔ የሚገባኝ መብትና ነፃነት ለሁሉም ሰው ይገባል” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ “አንድነት” ሲባል “ሁላችንም እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ይገባል” ማለት ነው። በአጠቃላይ፣ አንድነት ማለት እኩልነት ነው!!! በአንድነት ወይም እኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የብዙሃን መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት ያስችላል። 

ብሔርተኝነት ጨቋኝ ሰርዓትን ለማስወገድ እንጂ ዴሞክራሲን ለመገንባት አይጠቅምም! (ክፍል-3)

ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ትግል ከየትና እንዴት መጀመር አለበት? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እንዲቻል የትግሉን መነሻ እና መድረሻ በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል መነሻ ምክንያቱ የዜጎች ነፃነትና እኩልነት አለመከበሩ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ ዓላማ ከሕዝቡ ለሚነሳው የነፃነትና እኩልነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። በመሆኑም፣ የትግሉ የመጨረሻ ውጤት የዜጎች ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። በአጠቃላይ፣ ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል መነሻና መድረሻ የሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ናቸው።

በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን ጨቋኝ ስርዓት እስካለ ድረስ ዜጎች ብሶትና ቅሬታ ይኖራቸዋል። ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን ብሶትና ቅሬታ የሚገልፁበት ምርጫና አማራጭ ሲያጡ ለአመፅና ተቃውሞ ወደ አደባባይ ይወጣሉ። ነገር ግን፣ ጨቋኝ ስርዓት አመፅና ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ከቀድሞ የበለጠ አስፈሪ የሆነ የኃይል እርምጃ በተቃዋሚዎች ላይ ይወስዳሉ። በእንዱህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን ሕዝባዊ ንቅናቄውን በትጥቅ ትግል ወይም በሰላማዊ ትግል ለመምራት ምቹ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በዚህ መሰረት፣ ምንም እንኳን አንድ ዓይነት መነሻና መድረሻ ቢኖረውም ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ሁለት አማራጭ መንገዶች እንዳሉት መገንዘብ ይቻላል፤ አንደኛ፡- በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል፣ ሁለተኛ፡- በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሁሉን-አቀፍ ሰላማዊ ትግል ናቸው። ከዚህ በመቀጠል የመጀመሪያውን የትግል ስልት መሰረታዊ ባህሪና ውጤታማነት እንመለከታለን።

የሕዝቡን አመፅና ተቃውሞ በትጥቅ ትግል የማስቀጠል ዝንባሌ ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን በዋናነት ብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብትን ማቀንቀን ይጀምራለ። ብሔርተኘነት የሕዝቡን ንቅናቄ ለማቀጣጠል የሚያገለግል ሲሆን በራስ-የመወሰን መብት ደግሞ የትግሉ ግብ (ተስፋ) ሆኖ ያገለግላል። በአብዛኞቹ የዓለም ሀገራት የሚካሄዱ የትጥቅ ትግሎች በእነዚህ ሁለት እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ነገር ግን፣ በዚህ መልኩ የሚካሄድ የትጥቅ ትግል ከትግሉ መነሻ ምክንያትና የመጨረሻ ውጤት አንፃረ የተዛነፈ ነው።

በመጀምሪያ ደረጃ የትግሉ መነሻና መድረሻ የሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ነው። ነገር ግን፣ የትጥቅ ትግሉን ለማቀጣጠል ሲባል በማህብረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ የተደረገው የብሔርተኝነት ስሜት ከነፃነትና እኩልነት ይልቅ በራስ-ወዳድነት (egoisim) እና ወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ብሔርተኝነት ፅንሰ-ሃሳብና በሰው ልጅ ላይ ስለሚያስከትለው የሞራል ኪሳራ በክፍል ሁለት በዝርዝር ለመግለፅ ተሞክሯል። ስለዚህ፣ በዚህ ክፍል ዋና ትኩረታችን የትጥቅ ትግል በማህበራዊ ስነ-ልቦና ላይ በሚያስከትለው ተፅዕኖ ላይ ይሆናል። 

Skocpol (1994) and Goodwin (1994) የተባሉ የዘርፉ ምሁራን፣ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ አማፂያን ስኬትና ውድቀታቸው የሚወሰነው በሕዝባዊ አመፅ፥ በብሔርተኝነት፥ በውጪ ኃይሎች ድጋፍ፥ የሽምቅ ውጊያ ስልት፥ ወይም ሌላ ሳይሆን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት ባህሪ እንደሆነ ይገልፃሉ። ጨቋኝ ስርዓት ለማስወገድ የሚደረግ የትጥቅ ትግል በአብዛኛው የሚጀምረው በሽምቅ ውጊያ ስልት ነው። ይህ ደግሞ አማፂያኑ ራሳቸውን በማህብረሰቡ ውስጥ በመደበቅ በመንግስት ላይ ጥቃት የሚፈፅሙበት ስልት ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ደግሞ ከአማፂያኑ ጥቃት በተፈፀመባቸው ቁጥር ከከዚህ በፊቱ የበለጠ የኃይል እርምጃ መውሰድ የተዋጊዎቹን ጥቃትና ድጋፍ ይቀንሳል የሚል እሳቤ አላቸው። ሽምቅ ተዋጊዎቹ በማህብረሰቡ ውስጥ ተደብቀው የሚንቀሳቀሱ እንደመሆኑ መጠን ጨቋ መንግስት በሚወስደው የአፀፋ እርምጃ በማህብረሰቡ አባላት በደልና ጭፍጨፋ ይደርሳል።በማህብረሰቡ ላይ በደልና ጭቆና በተፈፀመ ቁጥር ደግሞ የአማፂያኑ ድጋፍ ይጨምራል፣ የመንግስት ተቀባይነት ይቀንሳል። በዚህ መሰረት፣ የአማፂያኑን ጥቃትና ድጋፍ ለመቀነስ በሚል የሚወሰድ የአጸፋ እርምጃ የሽምቅ ተዋጊዎቹን አቅምና ድጋፍ እየጨመረ፣ የጨቋኙን ስርዓት አቅምና ተቀባይነት እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርገዋል።

በአጠቃላይ፣ በትጥቅ ትግል የአማፂያኑ ስኬትና የጨቋኝ ስርዓት ውድቀት የሚወሰነው በዚህ ስሌት መሰረት ነው። በመሆኑም፣ በትጥቅ ትግል ጨቋኝ ስርዓት የሚወድቀው ንፁሃንን በመጨፍጨፉ ምክንያት ሲሆን፣ አማፂያኑ ደግሞ የሚያሸንፉት ንፁሃንን ዜችን በማስጨፍጨፋቸው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ አንፃር፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል በንፁሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ምክንያት በመሆኑ ተመራጭ አይደልም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ ውጤት በመግቢያው ላይ ከተጠቀሰው የትግሉ መነሻና መድረሻ ጋር ፍፁም ተቃራኒ ነው። የትግሉ መነሻ የሕዝብ ነፃነት እና እኩልነት ቢሆኑም በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሰረፀው በራስ-ወዳድነት ላይ የተመሰረተው የብሔርተኝነት ስሜት በሂደት ወደ ወገንተኝነት እና የተበዳይነት ስሜት ይቀየራል። ከላይ በጦርነት ወቅት አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት ማህብረሰብ ላይ የሚደርሰው በደልና ጭፍጨፋ በሕብረተሰቡ ዘንድ የጠላትነትና ፍርሃት ስሜት እንዲሰርፅ ያደርገዋል። ስለዚህ፣ የትግሉ መነሻ ምክንያት ነፃነትና እኩልነት ናቸው። የትግሉ የመጨረሻ ውጤት ግን የወገንተኝነት/ተበዳይነት እና የጠላትነት/ፍርሃት ናቸው።

ከትጥቅ ትግል በኋላ የሚመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓትም በእነዚህ ስሜቶች ተፅዕኖ ስር ይወድቃል። የወገንተኝነት/ተበዳይነት እና የጠላትነት/ፍርሃት ስሜት በስፋት በሚንፀባረቅበት ማህብረሰብ ዘንድ እንደ አዲስ የሚዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በእንዲህ ያለ የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ የብዙሃኑን ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠበቅ የዋህነት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎ የሚነሱ የመብትና ነፃነት ጥያቄዎችን በፍርሃትና ጥርጣሬ የሚመለከት ይሆናል። እንደ ቀድሞ ስርዓት የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚታትር ሌላ ጨቋኝ ስርዓት ይፈጠራል።             

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል በማድረግ የብዙሃን ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በፍፁም መገንባት አይቻልም። በብሔርተኝነት ላይ በተመሰረተ የትጥቅ ትግል ከስልጣን ያስወገዱት ጨቋኝ ስርዓት “አልሸሹም ዞር አሉ” የሚሉት ዓይነት ነው። ምክንያቱም፣ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ-አውጪ ሳይውል-ሳያድር ጨቋኝነቱ ፍትው ብሎ ይታያል። ለዚህ ደግሞ ጨቋኙን የደርግ ስርዓት በመገርሰስ ወደ ስልጣን ከመጡት የኢህአዴግና የሻዕቢያ መንግስት የበለጠ ጥሩ ማሳያ ያለ አይመስለኝም። (በቀጣዩ ክፍል ደግሞ በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ትግል እንዴት ማካሄድ እንደሚቻል በዝርዝር እንመለከታለን።)          

ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ወደ አውሬነት ይቀይራል (ክፍል-2)

ታላቁ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዜያብሄር አሁን ርዕሱን በረሳሁት ድርሰት ውስጥ በውሻና ሰው መካከል የተደረገ ቃለ-ምልልስ አለ። ሰውዬው ከሚጠጣው አረቄ ትንሽ የቀመሰው ውሻ ሲሰክር በሰውኛ ዘይቤ መሳደብ ይጀምራል፤ “እኛ ውሾች እንደ ሰው “እኛ” እና “እናንተ” ብሎ አናውቅም” ይላል። ባለቤቱ “እንዴት ባክህ?” ሲለው “በቃ…ሁላችንም “እኛ” ነን” ይለዋል። ደራሲው ጋሽ ስብሃት በዚህ ቃለ-ምልልስ ያስተላለፈው መልዕክት በደንብ የገባኝ ከአራት አመታት በኋላ ነው፡፡

የጋሽ ስብሃት ሃሳብ የገባኝ “Edmond Leach” የተባለውን ምሁር ትንታኔ ካነበብኩ በኋላ ነው። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ከሰው ልጅ በስተቀር በሁሉም እንስሳት ዘንድ አንድ ዝርያ እስከሆኑ ድረስ ሁሉም “እኛ” ናቸው። ለምሳሌ፣ ውሻ ጥቁር ሆነ ነጭ፣ የፈረንጅ ሆነ የሀበሻ፣ የጀርመን ሆነ የአሜሪካ፣…ወዘዘተተ ሁሉም ደመ-ነፍሳዊ በሆነ የምልክት ቋንቋ ይግባባሉ። ስለዚህ፣ ውሾች ሲጣሉ ሆነ ሲፋቀሩ የሚግባቡበት፥ ስሜታቸውን የሚገልፁበት የጋራ መግባቢያ አላቸው።

የሰው ልጅን ጨምሮ ሁሉም እንስሳት አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ባህሪ አላቸው። እሱም “ፀብና ጥቃት” (aggression) ውጫዊ እና ውስጣዊ አይደለም። ማለትም፣ የውሻ ፀብና ጥቃት ለምሳሌ በጅብ፥ ቀበሮ፥…ላይ እንጂ የራሱ ዝርያ በሆነ ሌላ ውሻ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። በእርግጥ በውሾች መካከል የእርስ-በእርስ ፀብና ጥቃት ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን፣ በጣም በተለየ አጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር አንድ ውሻ በሌላ ውሻ ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት አይፈፅምም። ብዙ ግዜ ታዝባችሁ እንደሆነ፣ አንድ ጉልበተኛ ውሻ ለፀብ ወይም ለመናከስ እየሮጠ ሲሄድ ሌላኛው ውሻ ጭራውን እያወዛወዘ ከተለማመጠው ወይም መሬት ላይ ከተኛ አይነክሰውም። እዚህ ጋር ሊሰመርባቸው የሚገቡ ሁለት ነጥቦች አሉ። አንደኛ፡- ጉልበተኛው ውሻ የሚፈልገው የሌላውን ውሻ ተገዢነት ወይም ተሸናፊነት ነው፣ ሁለተኛ፡- ውሾች በፀብና ግጭት ውስጥ የሆነው እንኳን እርስ-በእርስ በምልክት ይነጋገራሉ፥ ይግባባሉ።   

ከሁሉም እንስሳቶች በተለየ የራሱን ዝርያ የሚገድል ፍጡር የሰው-ልጅ ብቻ ነው። “Edmond Leach” ይሄን ኢ-ተፈጥሯዊ የሆነ የሰው ልጅ ባህሪ በዋናነት ከሰው ልጅ የቋንቋ አጠቃቀምና አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይገልፃል። በእርግጥ የሰው ልጅ ሁሉም ነገር ከራሱ አንፃር የማየት ባህሪ አለው። ቋንቋችንም ከዚሁ አንፃር የተቃኘ ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው ለራሱ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች፤ እናት፥ አባት፥ ልጆች፥ እህት፥ ወንድም፥ ልጆች፥…ወዘተ ያሉትን “እኛ” ሲል ከዚህ ቀረቤታ ውጪ ያሉትን ደግሞ “እነሱ” ይላል።

“የእኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። “እኛ” የስዩም ቤተሰቦች ከሆንን የጋሽ ስብሃት ቤተሰቦች “እነሱ” ናቸው፣ “እኛ” አሰላዎች ከሆንን “እነሱ” አደዋዎች፥ አሳይታዎች፥…ናቸው። “እኛ” ኦሮሞች ከሆንን እነሱ አማራዎች፥ ትግሬዎች፥ ወላይታዎች፣ “እኛ” ኢትዮጲያዊያን ከሆንን “እነሱ” ግብፃዊያን፥ ኤርትራዊያን፥ ጀርመናዊያን፣ “እኛ” በምድር ላይ የምንኖር ሰዎች ከሆንን “እነሱ” በሌላኛው ዓለም የሚኖሩ “መናፍስት”…ወዘተ ናቸው።

በጣም ቅርብ የሆኑትን “እኛ” ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት ይቻላል። በጣም ሩቅ የሆኑትን “እነሱ” ደግሞ ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት አይቻልም። ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑትን ስራና ተግባር በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም በንግግር መግባባት ስለሚቻል የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። ለእኛ በጣም ሩቅ የሆኑት ደግሞ በእለት-ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ስለሌላቸው ምንም ስጋትና ፍርሃት ሊፈጥሩ አይችሉም።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሩቅ ባሉት “እነሱዎች” እና ቅርብ ባሉት “እኛዎች” መካከል ሌላ ሦስተኛ “እነሱዎች” አሉ። እነዚህ ሦስተኞቹ “እነሱዎች” ከቦታና ግዜ አንፃር ለእኛ ቅርብ ቢሆኑም ሥራና ተግባራቸውን ግን በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም ተነጋግሮ መግባባት አይቻልም። “በእኛዎች” እና በሦስተኛ “እነሱዎች” መካከል ላለው ልዩነት መነሻ ምክንያቱ ተነጋግሮ መግባባት አለመቻል ነው። “እኛ” እና “እነሱ” በሚለው እሳቤ መሰረት፣ ሰዎች የተለየ ቋንቋ ሲናገሩ፣ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ሲሳናቸው፣ በዚህም አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅና መገመት ሲሳነው፣ “እኛ” ሰዎች፥ ሌሎቹን ደግሞ ከሌላ የእንስሳት ዝርያ የመጡ ለምሳሌ “ውሾች” አድርገው ይስላሉ።

የሰው ልጅ በቅርቡ ካለ ሰው ጋር መነጋገርና መግባባት ከተሳነው፣ በዚህም የሰውዬውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅ ሆነ መገመት ከተሳነው፣ አንዱ በሌላው ላይ ስጋትና ፍርሃት ይጭራል። በቅርብ የሚኖሩ ሰዎች የማይነጋገሩ፥ የማይግባቡ፥ የማይተዋወቁና የማይተማመኑ እርስ-በእርስ እንደ ሌላ ፍጡር መተያየት ይጀምራሉ። አንዱ ራሱን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያየ ሌላውን ግን እንደ አውሬ ማየት ይጀምራል። እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ይህን ግዜ የሰው ልጅ ከሰብዓዊነት ወደ አውሬነት ይቀየራል፡-

“…our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. In the non-human world whole species function as a unity. …If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” A Runaway World: Lec. 3: Ourselves and Others, 1967   

ከሰው ልጅ በስተቀር ሌሎች እንስሳት ምንም ያህል ቢራራቁ ወይም ቢቀራረቡ፣ አንድ ዓይነት ዝርያ እስከሆኑ ድረስ በምልክት ቋንቋ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ስለዚህ፣ በመካከላቸው ምንም ያህል ልዩነት ቢፈጠር አንዱ ሌላውን እንደ ሌላ ዝርያ ፍጡር አይመለከተውም። እዚህ ጋር ጋሽ ስብሃት በሰውኛ ዘይቤ “በውሾች ዘንድ “እኛ” እና “እነሱ” የሚባል ነገር የለም” ያለው ማስታወስ ተገቢ ነው። በእርግጥ ውሾች አንድ ዓይነት መግባቢያ ቋንቋ አላቸው። ስለዚህ፣ ከጎንደር ሆነ አሳይታ፣ ከአክሱም ሆነ ወላይታ፣ …ከየትኛውም አከባቢ የመጡ ውሾች እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ነገር ግን፣ ከተጠቀሱት አከባቢዎች የመጡ ሰዎች በአንድ ቦታ ቢገናኙ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት አይችሉም።

እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች በጋራ ጉዳይ ላይ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ከተሳናቸው አንዱ ራሱን እንደ ሰው ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) ማየት ይጀምራል። ይሄ ነገር ግን በውሾች መካከል አይከሰትም። በመሆኑም፣ ሰዎች በብሔርና በዘር ቡድን መስርተው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እርስ-በእርስ ሲጨፋጨፉ ውሾች ግን ሁሉም “እኛ” ስለሆኑ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም። በአጠቃላይ፣ በ”እኛ” እና “እነሱ” እሳቤ ከሚመራው የሰው ልጅ በስተቀር የአንድ ዝርያ እንስሳት እንዲህ በጭካኔ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እርስ-በእርስ መገዳደል እንደ ማንኛውም እንስሳ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ አይደለም። የሰው ልጅ ግን በዘር/ብሔር/ሀገር ተቧድኖ እርስ-በእርስ ይገዳደላል። ለዚህ ዋናው ምክንያት አንዱ ወገን ራሱን እንደ ሰው፣ ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) መመልከቱ ነው። የሰው ልጅ ራሱን “እኛ” እና “እነሱ” ብሎ ለመመደብ የሚጠቀምበት ዋና መለያ መስፈርት “ቋንቋ” ነው። በተመሣሣይ፣ አንድን ብሔር ከሌላው ለመለየት አንዱና ዋንኛው መስፈርት ቋንቋ ነው። በሀገራችን በስፋት የሚስተዋለው የብሔርተኝነት ስሜት በዋናነት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው።

ስለዚህ፣ “ብሔርተኝነት” ሁለት ጎን-ለጎን የሚኖሩ የተለያየ ብሔር ተወላጆችን እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) እንዲተያዩና እንዲጨካከኑ፣ በዚህም እርስ-በእርስ እንዲገዳደሉ በሚያደርግ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን የአውሬነት ባህሪ እንዲላበስ በማድረግ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። እንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም፥ የትም ቢሆን ሕዝብን ወደ ጦርነትና እልቂት የሚወስድ ነው።         

ከዚህ በተጨማሪ፣ ብሔርተኝነት በራሱ የጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት ውጤት ነው። በአማርኛ መዝገበ ቃላት “ጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት” የሚለውን፤ “ጥልቀት የሌለው፣ በስፋት የማይገነዘብ፥ አርቆ ማየት የጎደለው” የሚል ፍቺ አለው። በተመሳሳይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው ደግሞ “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። ስለዚህ፣ ከብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ከእኛ ያነሰ ክብርና ዋጋ መስጠት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ ብሔርተኝነት የአንድን ብሔር መብትና ነፃነት ከማረጋገጥ ባለፈ ራስን ከሌሎች የተሻለ አድርጎ በማሰብ ወይም ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ዝቅተኛ ግምትና ክብር በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ራሱ ጎሳ ብቻ የሚያስብና በሌላው ላይ ጥላቻ ያለው የፖለቲካ ቡድን ከራስ-ክብር (Self-respect) ይልቅ በራስ-ወዳድነት (Egoism) የሚመራ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ለራስ ክብር (Self-respect) የሚደረግ የነፃነትና እኩልነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም የሰብዓዊነት (humanity) እና የጋራ እሰቶችን (common values) በማስረፅ የሚካሄድ ነው።

በራስ-ወዳድነት (Egoism) የተመሰረተ የብሔርተኝነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት ሳይሆን የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም በዋናነት የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም ብሔር ተወላጆችን ልክ እንደ አውሬ በመመልከትና በኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ጭካኔ የተሞላ ነው። ታዋቂው ፈላስፋ “Jean Jacques Rousseau” እንዲህ ያሉ በበታችነትና በራስ-ወዳድነት ስሜት የናወዘ የፖለቲካ አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ጉዳት ወደ ፍፁም አውሬነት ሊቀየሩ እንደሚችሉ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…men who neither valued nor compared themselves could do one another much violence, when it suited them, without feeling any sense of injury. In a word, each man, regarding his fellows almost as he regarded animals of different species, might seize the prey of a weaker or yield up his own to a stronger, and yet consider these acts of violence as mere natural occurrences, without the slightest emotion of insolence or despite, or any other feeling than the joy or grief of success or failure.” WHAT IS THE ORIGIN OF INEQUALITY AMONG MEN, AND IS IT AUTHORISED BY NATURAL LAW?, 1754, Trans. by G. D. H. Cole.

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፍፁም ስህተት ከመሆኑ በተጨማሪ የአውሬነት መገለጫ ነው። በማንኛውም ግዜ ቦታ ቢሆን በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሀገርን ወደ የእርስ-በእርስ ጦርነት የሚያስገባና ጨቋኝ ስርዓት በመዘርጋት የሚቋጭ የድኩማኖች መንገድ ነው። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅ አውሬነት መገለጫ ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት የሚደርግ ሕዝባዊ ንቅናቄና ትግል እንዴት መጀመርና ምን መሰረት ማድረግ እንዳለበት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

ብሔርተኝነት ያደርሳል ከጦርነት፣ ያመጣል ጨቋኝ ስርዓት (ክፍል-1)

ከዚህ ቀደም “የአማራ-ብሔርተኝነት ከየት ወደየት?” የሚል ፅኁፍ ፅፌ ከጨረስኩ በኋላ በስህተት ከኮምፒውተሬ ውስጥ ስላጠፋሁት ሳይታተም ቀረ። ፅኁፉ በዋናነት “ቤተ-አማራ” የሚባለው ቡድን በሚያቀነቅነው የአማራ-ብሔርተኝነት ላይ ያጠነጠነ ነበር። በእርግጥ እንደ ኢህአዴግ ያለ ጨቋኝ ስርዓት ዜጎች የሚያነሱትን የእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን በኃይል ማፈን ባህሪው ነው። የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ሲታፈን ደግሞ የማህብረሰቡ የፖለቲካ ልሂቃን የብሔርተኝነት ስሜት ማቀንቀን ይጀምራሉ።

“የአማራ ብሔርተኝነት” መነሻ ምክንያት የአማራ ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል መታፈኑ ነው። በመሰረቱ “ብሔርተኝነት” የሕዝብ ንቅናቄ ለመቀስቀስ (mobilization) እና ለማዳፈን (demobilization) ዋና መሳሪያ ነው። የመከፋፈል መርሆችን (Principles of division) በማስቀመጥ የሚታወቀው ፈረንሳዊው ተመራማሪ “Bourdieu” የአንድ ሀገር ሕዝብን የመከፋፈል መሰረታዊ ዓላማና ግብን እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“Principles of division function within and for the purposes of the struggle between social groups…What is at stake in the struggle is power over the classificatory schemes and systems which are the basis of the representations of the groups and therefore of their mobilization and demobilization: the evocative power of an utterance which puts things in a different light” Distinction. A social critique of the judgement of taste, 1984.

ከዚህ አንፃር፣ ለምሳሌ የቀድሞ የሕውሃት መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ሕዝብ የመብትና ነፃነት ጥያቄ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ አና በደርግ መንግስት በኃይል ሲዳፈን የትግራይ ልሂቃን የብሔርተኝነት ስሜትን ማቀንቀን እንደጀመሩ ይገልፃል። በመጨረሻም፣ በብሔርተኝነት ስሜት በመቀስቀስ (mobilization) እና በራስ-የመወሰን መብትን (rights of self-determination) ተስፋ በመስጠት የሕወሃት የትጥቅ ትግል ተጀመረ። በሕወሃት መሪነት የተመሰረተው ኢህአዴግ የደርግ ስርዓት ከስልጣን ካስወገደ በኋላ በብሔር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ የአፓርታይድ ስርዓት ዘረጋ።

የብሔር-አፓርታይድ ስርዓት ዓላማና ግብ ደግሞ በሀገሪቱ አብላጫ ድምፅ (majority) ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ሕዝብ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዳፈን (demobilization) ነው። ለዚህ ደግሞ ባለፉት አስር አመታት የኢህአዴግ መንግስት የግምገማ ሪፖርቶች ውስጥ “ትምህክተኝነት” እና “ጠባብነት” የመንግስታዊ ስርዓቱ አደጋዎች በሚል ያልተገለፁበት ግዜ የለም። ብሔርተኝነትን እያቀነቀነ ወደ ስልጣን የመጣው ሕወሃት መራሹ የፖለቲካ ቡድን የአማራና ኦሮሞ ሕዝብን የመብትና ነፃነት ጥያቄ “ትምክህተኛ” እና “ጠባብ-ብሔርተኛ” እያለ ያሸማቅቃል። “ትምክህተኛ” እና “ጠባብ-ብሔርተኛ” የሚሉት “Bourdieu” – “the evocative power of an utterance which puts things in a different light” የሚለው ዓይነት ፋይዳ ያላቸው ቃላት ናቸው።

በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ የሚወስደው ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት ሲሆን መጨረሻው ደግሞ ጨቋኝ ስርዓት መፍጠር ነው። በምንም ዓይነት ተዓምር ቢሆን የብሔርተኝነት ንቅናቄ ወደ ዴሞክራሲ አያደርስም። በመሆኑም፣ ብሔርተኝነት ለሚታገሉለት ሕዝብ መብትና ነፃነት ሆነ ለጎረቤት ሀገር ሰላምና ደህንነት አይበጅም። ለምሳሌ፣ ብሔርተኝነትና በራስ-የመወሰን መብትን ዓላማ አድርገው የተነሱት ሕወሃትና ሻዕቢያን እንመልከት።

በራስ-የመወሰን መብት በክልል ደረጃ ራስን-በራስ ከማስተዳደር እስከ መገንጠል ሊደርስ ይችላል። ሕወሃት ብሔርተኝነት እያቀነቀነ በጀመረው የትጥቅ ትግል አሸንፎ የትግራይ ሕዝብን ራስን-በራሱ እንዲያተዳድር አደረገ። ነገር ግን፣ መብትና ነፃነትን ከማረጋገጥ አንፃር ግን የኢህአዴግ የብሔር ፖለቲካ ለትግራይ ሕዝብ ሆነ ለተቀረው የኢትዮጲያ ህዝብ ከአምባገነንነት ሌላ ያመጣው ትርፍ የለም። በተመሳሳይ፣ የኤርትራ ብሔርተኝነት እያቀነቀነ የትጥቅ የጀመሩት የኤርትራ አማፂያን ከኢትዮጲያ በመገንጠል የራሳቸው ሉዓላዊ ሀገር መሰረቱ። ነገር ግን፣ አሁንም ድረስ የታሪክ ቁስል ከማከክ በዘለለ የኤርትራዊያንን መብትና ነፃነት አልተከበረም። የትጥቅ ትግል ከጀመሩበት የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መንግስት ቀርቶ ከወታደራዊ ደርግ የባሰ ጨቋኝና ጦረኛ የሆነውን የሻዕቢያ መንግስት ከመፍጠር ባለፈ በኤርትራዊያን መብትና ነፃነት ሆነ በጎረቤት ሀገሮች ሰላምና ደህንነት ላይ ያመጡት ለውጥ የለም።

በአጠቃላየ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም ቢሆን የብዙሃንን መብት፣ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አያስችልም። የብሔርተኝነት መጨረሻ ጦርነትና ጨቋኝ ስርዓት ነው። ምክንያቱም፣ የብሔርተኝነት ፅንሰ-ሃሳብ በራሱ ከነፃነት ይልቅ በጠላትነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ሰብዓዊነት ገፍፎ ከተራ እንስሳት በታች ያደርገዋል። በእርግጥ አገላለፁ ኃይለ-ቃል የተቀላቀለበት ወይም ግነት የበዛበት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ እውነታው ይሄ ነው። ብሔርተኝነት ሰውን ከተራ እንስሳት ለምሳሌ፣ ከቀበሮ፥ ጅብ፥ ውሻ፥… በታች ያደርገዋል። በኢ-ሰብዓዊነት እሳቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ንቅናቄ መጨረሻው የሰዎችን ሰብዓዊ መብትና ፖለቲካዊ ነፃነት የሚገፍፍ ጨቋኝና ጦረኛ መንግስታዊ ስርዓት መመስረት ይሆናል። በቀጣዩ ክፍል “ለምንና እንዴት?” የሚለውን በዝርዝር እንመለከታለን።