የኢህአዴግ​ ለዛ-ቢስ ቃላቶች ክፍል-1: ጥገኝነት፥ ጠባብነትና አክራሪነት

ባለፉት ሁለት አሰርት አመታት በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ያለ ቅጥ ከመደጋገማቸው የተነሳ ለዛ-ቢስ የሆኑ ቃላት አሉ። ቃላቱ በዜና እወጃ፣ በባለስልጣናት መግለጫ፣ በግለሰቦች አስተያየት፣ በፖለቲካ ክርክር፣ በስልጠና መድረክ፣…ወዘተ ከመደጋገማቸው የተነሳ ለዛ-ቢስ እና ትርጉም-አልባ ወደ መሆን ተቃራበዋል። እነዚህ ቃላት በዋናነት የኢህአዴግ መንግስት “የሩብ ምዕተ ዓመታት ‘ፈተናዎች’ እና ‘ስኬቶች’” በማለት በተደጋጋሚ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚያውላቸው ናቸው። 

ለምሳሌ፣ በ2009 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስልጠና በተዘጋጀ ሰነድ ላይየ፤ “የሩብ ምዕተ ዓመታት የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ እየታዩ ያሉ ፈተናዎችንና መፍትሄዎቻቸው” በሚል ንዑስ-ርዕስ የሚከተሉትን ችግሮች ይዘረዝራል፡- “ባለፉት ሃያ አምስት አመታት የነበሩ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ የትምክህትና ጠባብነት አደጋዎች እንዲሁም ሃይማኖትን ሽፋን የሚያደርገው አክራሪነት ፈተናዎች አሁንም ቅርፃቸውን ቀይረው ወይም በሌላ ተተክተው ስላሉ ፈተናዎቹን ለማለፍ የተከተልናቸውን ስልቶች ይበልጥ አጠናክረን ያገራችንን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማደናቀፍ ወደ የማይቻልበት ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ በመሆኑ…” የከፍተኛ ትምህርት ማህብረሰብ ሥልጠና ለ2009 ትምህርት ዘመን ዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቂያ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፥ መስከረም 2009፥ ገፅ-7 

በተመሣሣይ፣ በ2006 ዓ.ም በመስከረም ወር ላይ ለሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሰጠው ስልጠና ተዘጋጅቶ የነበረው ሰነድ ደግሞ፤ “የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ” በሚል የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፦

“…ትምክህትና ጠባብነት እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት እና የእነዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነው ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ (ኪራይ ሰብሳቢነት) በመፍታት የተያያዝነውን የልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞ አጠናክረን ልንቀጥልበት እንደሚገባ…” የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ፥ ሐምሌ 2006 ዓ.ም፥ ገፅ-34   

ከላይ እንደተጠቀሰው በ2006 ዓ.ም እና በ2009 ዓ.ም የተዘጋጁት ሁለት ሰነዶች በሀገሪቱ እየታዩ ላሉት ችግሮች መንስዔዎች እና መፍትሄዎች አንድና ተመሳሳይ ናቸው። የኢህአዴግ መንግስት አመት በወጣና በገባ ቁጥር ተመሣሣይ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ የሙጥኝ ማለቱ ባለበት እየረገጠ ስለመሆኑ ያሳያል። ነገር ግን፣ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ብቻ በሕዝቡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ሰፊ ነው። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና እያሳየ ያለው የለውጥ ፍላጎት ከእለት-ወደ-እለት እየተቀያየረና እየጨመረ መጥቷል። 

በአጠቃላይ፣ ከሁለት አመት በፊት ሆነ ከሁለት አስርት አመታት በፊት የኢህአዴግ መንግስት ፈተናዎች ተብለው የሚጠቀሱት “ጥገኝነት፣ ትምክህትና ጠባብነት” ናቸው። እነዚህ ቃላት ያለቅጥ ለፖለቲካ ፍጆታ በመዋላቸው ምክንያት ለዛ-ቢስ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የቃላቱን መሰረታዊ ትርጉም አሁን ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር አያይዘን እንመለከታለን። 

ጥገኝነት፥ ጠባብነትና አክራሪነት

የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ባዘጋጀው የኣማርኛ መዝገበ ቃላት መሰረት በማድረግ የቃላቱን ፍቺና ከነባራዊ እውነታ ጋር አያይዘን እንመልከት። በመጀመሪያ “ጥገኛ” (ጥገኝነት) የሚለውን ቃል ስንመለከት፣ “በሌላው አካል ወይም ድርጅት ጥላ ስር የሚንቀሳቀስ” የሚል ፍቺ አለው። በተለይ ከአስር ዓመታት በፊት ራሳቸውን ያልቻሉ፣ በውጪ ኃይሎች እርዳታና ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸው እርግጥ ነው። ዛሬ ላይ በዚህ መልኩ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ ማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም፣ የበጎ-አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ እና ከ1997 ዓ.ም በኋላ ያለው ጠባብ የፖለቲካ ምህዳር ከመንግስት እውቅና ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ድርጅቶችና ማህበራት እንዳይኖሩ አድርጓል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሳው የሻዕቢያ መንግስት፣ ግንቦት7 እና የኦሮሞ ነፃ-አውጪ ግንባር (ኦነግ) ወደ ሀገር ውስጥ “ተላላኪዎችን” ከማስገባት ባለፈ የተደረጀና በእነሱ እርዳታና ድጋፍ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ኃይል የመፍጠር አቅም የላቸውም። አሁን በሀገሪቱ ለተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት የሻዕቢያ መንግስትን፣ ግንቦት7ና ኦነግን ተጠያቂ ማድረግ “የኢህአዴግ መንግስት ከእነዚህ ኃይሎች የባሰ አቅመ-ቢስ ሆኗል” ብሎ በራስ ላይ ከመመስከር ያለፈ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም። በአጠቃላይ፣ “ጥገኛ ኃይሎች…” የሚባለው በመንግስት ድክመት ምክንያት ለተፈጠረ ችግር ሌሎችን ተጠያቂ (externalize) ለማድረግ ነው።    

“ጠባብ ብሔርተኛ” (ጠባብነት) – “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። በእርግጥ ከ20 ዓመታት በፊት ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን የማይቀበሉና በኃይል የመገንጠል ጥያቄ የሚያቀርቡ ኃይሎች ነበሩ። ዛሬ ላይ ግን፣ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ራስን-በራስ የማስተዳደር መብታችን ይከበር የሚሉ እንደ ቅማንት፥ ኮንሶና ወልቃይት ማህብረሰቦችን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ በተረፈ፣ የመገንጠል ጥያቄ በማቅረብ ወይም ፅንፍ የወጣ የብሔርተኝነት አቋም ይዞ ከፍተኛ ግጭትና አለመረጋጋት ሊፈጥር የሚችል የተደራጀ ኃይል የለም ማለት ይቻላል። 

“ትምክህት” (ትምክህተኛ) – “ከመጠን በላይ በራስ መመካት፥ መተማመን፣ ራስን ከፍ አድርጎ የሚያይ” ማለት ነው። ከ10 ዓመት በፊት በብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚቃወሙ ኃይሎች ነበሩ። ከብሔር ማንነት ይልቅ በብሔራዊ አንድነት ላይ ለተመሰረተ አህዳዊ ሥርዓት ቅድሚያ የሚሰጡ ብዙ የአማራ ብሔር ተወላጆች እንደነበሩም እርግጥ ነው። 

በመሰረቱ፣ ጠባብነትና ትምክህተኝነት የጥገኝነት አስተሳሰብ (አመለካከት) ውጤቶች አይደሉም። ጥገኛ የፖለቲካ ኃይል ራሱን ችሎ መንቀሳቀስ አይችልም። “ጠባብ ብሔርተኛ” ከሌሎች ብሔሮች ይልቅ የራሱን ብሔር ወይም ጎሳ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም ነው። “ትምክህተኛ” ደግሞ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሞክር ነው። ሁለቱም ለራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ እንጂ የውጪ ኃይሎች አጀንዳ የሚያስፈፅሙ አካላት አይደሉም። ከዚህ በተጨማሪ፣ አሁን በኢትዮጲያ ካለው ነባራዊ እውነታ አንፃር ለጥገኛ ኃይሎች የሚመች ሁኔታ የለም። ከዚያ ይልቅ፣ በጠባብነት እና ትምክህተኝነት ውስጥ የሚንፀባረቀው የጥገኝነት አስተሳሰብ ሳይሆን አግባብ የሆነ የሁለቱ ሕዝቦች ጥያቄ ነው። 

“ትምክህተኛ” የሚለው እሳቤ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በባህላቸውና በታሪካቸው ላይ ያላቸውን የራስ መተማመን ስሜት የሚሸረሽር ነው። በዚህ መልኩ የሚደረገው ተፅዕኖ በአማራ ልሂቃን ላይ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ይፈጥራል። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው በአማራነቱ ብቻ “ትምክህተኛ” እየተባለ ታሪኩና ማንነቱ እንደ ጥፋት ሲቆጠር በውስጡ የብሔርተኝነት ስሜት ያቆጠቁጣል። 

በተመሣሣይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው እሳቤ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ያለውን ድርሻ የሚያንኳስስ፤ በሀገሪቱ አንድነት ላይ ያለውን የምሶሶነት ሚና ወደ አንድ ግንጣይ ቅርጫፍነት የሚያሳንስ ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የሚገባውን መጠየቁ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ “በጠባብነት” ሲፈረጅ በኃይል ሚዛኑን ውስጥ የሚገባውን ድርሻ ለመያዝ በራሱ መንቀሳቀስ ይጀምራል። 

በአጠቃላይ፣ ኦሮሞን “ጠባብ ብሔርተኛ” በሚል በሀገሪቱ አንድነት ውስጥ የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለነበር፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከብሔርተኝነት ወደ አንድነት እየቀየረ መጥቷል። በተመሣሣይ፣ አማራን “የትምክህተኛ አንድነት” በሚል እንደ ብሔር የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለነበር፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከአንድነት ወደ ብሔርተኝነት እየቀየረ መጥቷል። የሁለቱ ሕዝቦች ጥያቄ በዚህ የሽግግር ሂደት መሰረት ከሁለት ተቃራኒ ጫፎች ወደ መሃል በመምጣት ያልተጠበቀ ጥምረት ተፈጥሯል። ይህ አንደ ቀድሞው በሁለት ተቃራኒ ፅንፈኞች መካከል የተፈጠረ ጥምረት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁለቱም ሕዝቦች በማንነታቸውና በሆኑት ልክ የሚገባቸውን ጥቅምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴው የተፈጠረ የጋራ ጥምረት ነው። በመሆኑም የኦሮሞና አማራ ጥምረት በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ጥምረት ነው።

Advertisements

መግለጫ፡ “ኦሮሚያ የደርግ ሥርዓትን ለማስመለስ ጥረት እያደረገች ነው!” 

የሶማሌ ክልል መስተዳደር ባወጣው መግለጫ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ለተፈጠረው ግጭት መነሻ ያላቸውን አራት ምክንያቶች በዝርዝር ገልጿል፡፡ የተጠቀሱት ምክንያቶች በጣም አስገራሚ ከመሆናቸው በላይ በፌዴራል ስርዓት ላይ የተጋረጠውን አደጋ በግልፅ ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ መግለጫው የክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በግጭቱ ዙሪያ ያላቸውን አቋምና አመለካከት በግልፅ የሚያሳይ ሆኖ ስላገኘነው በመግለጫው የተዘረዘሩትን ምክንያቶች የተወሰኑ የቃላትና አፃፃፍ ግድፈቶችን በማስተካከል እንደሚከተለው አቅርበንዋል፡፡ ሙሉ መግለጫውን ይህን ማስፈንጠሪያ በመጫን ማንበብ ትችላላችሁ፡፡


የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል መንግስትና አገር ሽማግሎች በኦሮሚያ ጥቃት ላይ የጋራ አቋም መግለጫ ይፋ አደረጉ፡፡ጅግጅጋ (Cakaaranews) መክሰኞ መስከረም 23/ 2010 ዓ.ም፡፡…በመድረኩ ላይም የክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራርና የክልሉ አገር ሽማግሎችም ተገኝቷል፡፡ የክልሉ መንግሰት አሮሚያ በኢትዮጵያ ሶማሌ ላይ በቋሚነት የሚታወጃው ተከታታይ ጦርነት መንሰኤዎች እንደሚከተለው ገልፀዋል፡-

  1. ኦሮሚያ የኢትዮጵያ ሶማሌ መሬት በኃይል ለመወሰድና ከጎሮቤት አገራት እንደ ሶማሊላንድና ሶማሊያ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና እንደሁም የጎሮቤት አገራት ወደብ በመጠቀም ኢትዮጵያ የሚያፈራረሱበት ጦር መሳሪያ ለማስገባት ሲሆን በአሮሚያ ሴራ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ከባድ ማቀብ ስለሆነበት ነው፡፡ 
  2. የኦሮሞ ጦርነት በስተጀርባ ያለው ምክንያቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልልን የፈጠረ ሰላምና ማረጋጋት እንደሁም በሻቢያ የጋራ መቀመጭያ የነበሩት ፀረ-ሰላም ኃይሎች እንደ አልኢተሓድ፣ አልኢጃራ፣ ኦቦ (ኦብነግ)፣ ኦነግና የመሳሰሉት ፅንፈኞች ኤርትራ የሚትሰጠው ጦር መሳሪያዎችን በአንድ ጀልባ ሲትላክላቸው ስለነበርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት ስለተደመሰሱና የጦር መሳሪያዎች ማስገባቱ ስለታገደባቸው በኦሮሚያ ክልል ላይ ቁጭት ስላሳድባታል 
  3. የኦሮሞ ጦርነት ምክንያቱ ደግሞ በቅርቡ አሮሞችሁ ሌላ ሸሚዝ በመልበስ የአዲስቷ ኢትዮጵያ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰጥታና ልማትን ያጎፀፈው ኢህዴግን በቀላሉ ለመቀልበስና የፈዴራሊዝም ሥርዓትና የህግ የበላይነትናን ለመተራመስና አንባገነኑ የደርግ ሥርዓት ለማስመለስ ኦሮሚያ እያደረገች የነበረው ቀውስና ብጥብጥን በኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብና መንግስት ስለተወቀሱ ነው፡፡ ከዚህ በተያያዜም የክልሉ መንግስት ኢትዮጵያነታችንም ከማንም ጀርባ ሆነን አንለምንም ብሏል፡፡
  4. ከአሁን በፊት በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎች እና ዞኖች ለመሄድ በሌላ ክልል ተቋርጦ ከረጅም ጉዞ በኋላ ሲደርሱ የነበሩ የክልሉ ወረዳዎችና ዞኖች በክልሉ መንግስት በአጭር ግዜ ውስጥ የተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ልማትን በተላይ መንገድና ድልድዮች በመገንባትና ሁሉም የክልሉ ወረዳዎችና ዞኖች በማስተሳሰሩ፣ ከሌላ ክልል መዞሩ በክልሉ መንግስት ማቅረፉ በኦሮሚያ መንግስት ላይ ቁጭት ስለፈጠርበትና በተላይ በመንገድ መስረተ ልማት እጥረት በኦሮሚያ ክልል ተቋርጦ ሲገኝ የነበሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ወረዳዎች እንደ ለጋሂዳ፣ ሰለሃድ፣ ቁቢ፣ መዩሙሉቆ፣ ቀርሳዱላ እና ፊልቱ ወረዳዎች ከክልሉ ዋና ከተማ በመንገድ መስረተ-ልማትና በትላልቅ ድልድዮች ከማስተሳሰሩ ባሻገር የኢትዮጲያ ሶማሌ ክልል መንግስት በጥቂት አመታት ውስጥ በክልሉ ያከናወናቸው ትላልቅ የውሃ ማቆሪያዎችና ሜጋ የመስኖ ግድቦችሁ ለግብሪና ምርትና ምርታማነትን ስለሚያገለገሉና ከኦሮሚያ ሲቀርብ የነበሩ አትክልትና ፊራፍሬዎችሁ በሶማሌ ክልል ገበያ እንዳይኖቸው የአሮሚያ ክልል መንግስት ለሶማሌ ገበያ የሚየቀረርቡት ምርት ትልቅ ስጋት ስለሆነበት የኦሮሚያ ጦርነት አንዱ ምክንያት ተብሏል፡፡

መሪ-አልባ ሕዝብ እርስ-በእርስ ይጋጫል!

የትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪ ያስፈልገዋል። እንቅስቃሴው አብዮታዊ (revolutionary) ከሆነ የለውጥ መሪ ያስፈልገዋል። ፀረ-አብዮታዊ (reactionary) ከሆነ ደግሞ የስርዓት መሪ ያስፈልገዋል። ለስኬት ብቻ ሳይሆን ለውድቀትም መሪ ያስፈልጋል። ምክንያቱም፣ ከስኬታማ ለውጥ በስተጀርባ ውጤታማ አወዳደቅ አለ። በእርግጥ በውድቀት ውስጥ ሽንፈት ነው ያለው። ነገር ግን፣ ውድቀትን አውቆ ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ አመራር ከሌለ ፖለቲካዊ ቀውስ ይከሰታል። የቀድሞ ስርዓት ወድቆ-አይወድቅም፣ አዲሱ ስርዓት አይመሰረትም። ይህን ተከትሎ የቀድሞ ስርዓት ሳይወድቅ በቁሙ ይፈራርሳል፣ ሕዝባዊ ንቅናቄው ግቡን ይስታል። ይህ ሲሆን የብዙሃንን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረ ንቅናቄ አቅጣጫውን ስቶ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ይወስዳል። ይህ በምናባዊ እሳቤ ላይ ሳይሆን በመሰረታዊ የኃይል ፅንስ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንንም የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት አወዳደቅን እንደ ማሳያ በመውሰድ በዝርዝር እንመለከታለን።

በመሰረቱ፣ “ኃይል” (power) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ነው። የኃይል ፅንሰ-ሃሳብ ለሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል ቀጥተኛ ኃይል (Active power) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተግባሩን ወይም ለውጡን ለመቀበል የሚያስችል ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል (Passive power) ነው። ይህን ጽንሰ-ሃሳብ ለማስረዳት እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ እሳት እና ወርቅን እንደ ማሳያ ይጠቅሳል። እሳት ወርቅን ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ለመቀየር የሚያስችል ኃይል አለው። በሌላ በኩል፣ ወርቅ በሙቀት አማካኝነት ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ለመቀየር የሚያስችል ኃይል አለው። እሳት ወርቅን የማቅለጥ ወይም ቀጥተኛ ኃይል ሲኖረው ወርቅ ደግሞ በእሳት የመቅለጥ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል አለው። ወርቅ እንደ አፈር እሳት ሲነካው የሚፈረካከስ ቢሆን ኖሮ የወርቁ ቅርፅ መለወጥ ወይም መቀየር አይቻልም ነበር። ስለዚህ፣ የወርቅ ጌጥ የሚሰራው የእሳት ሙቀት ከወርቅ የመቅለጥ ባህሪ ጋር በመጣመር ነው። ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው ቀጥተኛ ኃይል ለዉጥን መቀበል ከሚያስችለው ቀጥተኛ ያልሆኑ ኃይል ጋር ካልተጣመረ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ አይቻልም።

በተመሣሣይ፣ አንድን ፖለቲካዊ ስርዓት በተሳካ ሁኔታ መቀየር የሚቻለው በስርዓቱ በደጋፊና ተቃዋሚ ጎራ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የለውጡን አስፈላጊነት እና አይቀሬነት ተገንዝበው በጥምረት መንቀሳቀስ ሲችሉ ብቻ ነው። ይህን ማየት ከመጀመራችን በፊት ግን “ኃይል”ከፖለቲካ አንፃር ያለውን ትርጉምና ፋይዳ በግልፅ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ “ኃይል” (power) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ነው። ከዚህ አንፃር፣ የፖለቲካ ኃይል (political power) ማለት ደግሞ የአንድን ሀገርና ሕዘብ ለማስተዳደር ወይም ፖለቲካዊ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል አቅም፥ ስልጣን ነው። ለፖለቲካዊ አስተዳደር ወይም ለለውጥ የሚያስችለው አቅም ምንጩ የብዙሃኑ አመለካከት (public opinion) ነው።

የአንድ ሕዝብ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያለውን በጥቅሉ የመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚ በማለት ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። “የመንግስት ደጋፊ” በሚለው ጎራ ያለውን ማህብረሰብ በቀጥታ የመንግስት ደጋፊዎች እና መንግስትን በይፋ ባይደግፉ-የማይቃወሙ ናቸው። በተመሳሳይ፣ “የመንግስት ተቃዋሚዎች” የሚባሉት ደግሞ በቀጥታ የመንግስት ተቃዋሚዎች እና መንገስትን በይፋ ባይቃወሙ-የማይደግፉ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ሀገሪቷንና ሕዝቡን መምራት የሚችለው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የመንግስት ደጋፊ ወይም መንግስትን በይፋ ባይደግፍ እንኳን የማይቃወም ከሆነ ነው። ነገር ግን፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መንግስትን የሚቃወም ወይም በይፋ ባይቃወም እንኳን የማይደግፍ ከሆነ ፖለቲካዊ ስርዓቱ መቀየር ወይም መሻሻል አለበት።

አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መንግስትን የሚቃወምበት፣ በይፋ ባይቃወም እንኳን የማይደግፈበት መሰረታዊ ምክንያት የእኩልነት ጥያቄ ነው። የሰው ልጅ ፖለቲካዊ አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚመራው በእኩልነት መርህ ነው። እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር በእኩል አይን መታየት ይሻል። በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ዜጋ ከሌሎች እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ሊኖረው ይገባል። “እኩልነት” (equality) የዴሞራሲያዊ ስርዓት መርህና መመሪያ የሆነበት ምክንያት ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። በመሆኑም፣ ዴሞክራሲ የብዙሃንን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። በተቃራኒው፣ ጨቋኝ ወይም አምባገነን የሆነ መንግስታዊ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። እንዲህ ያለ መንግስታዊ ስርዓት ባለበት ሀገር ዜጎች ያለማቋጥ የእኩልነት ጥያቄ ያነሳሉ።

በእርግጥ ገና ከአመሰራረቱ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት የለም። ይሁን እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በየግዜው ከሕዝብ ለሚነሳው የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፤ ሥራና አሰራሩን ያሻሽላል። ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ግን በተለያየ ግዜ ከዜጎች የሚነሳውን የእኩልነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ያደርጋል። ሆኖም ግን፣ የእኩልነት ጥያቄ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደመሆኑ በሰው-ሰራሽ ኃይልና ጉልበት ማስቆምና ማስቀረት አይቻልም። ስለዚህ. የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ለውጥና መሻሻል ከማምጣት ይልቅ የዜጎችን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በኃይል ለማፈን የሚሞክር መንግስት በራሱ ላይ ውድቀት እየደገሰ ነው። በመጀመሪያ በአመፅና ተቃውሞ የተጀመረ እንቅስቃሴ ቀስ-በቀስ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ያመራል። ከዚያ ቀጥሎ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ይከተላል። በመጨረሻም፣ በጉልበት ላይ የተመሰረተ መንግስት በተመሳሳይ ኃይል ከስልጣን ይወገዳል። በዚህ መልኩ፣ የሕዝቡ ንቅናቄ ከተቃውሞ ወደ አመፅ፣ ከአመፅ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ተሸጋግሮ በመጨረሻ ስርዓት-አልበኝነትና ጦርነት እንዳያስከትል የፖለቲካ መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት አለባቸው።

በብዙሃኑ አመለካከት ላይ ካላቸው ተፅዕኖ ወይም ኃይል አንፃር የፖለቲካ መሪዎችን ሚና ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ የፖለቲካ ኃይል (political power) ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ በሚል ለሁለት ይከፈላል። በዚህ መሰረት፣ የዜጎችን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ መሪዎች መንግስታዊ ስርዓቱን ለመቀየርና መምራት የሚያስችል ቀጥተኛ ኃይል (Active power) ያላቸው ሲሆን የስርዓቱ መሪዎች ግን ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል (Passive power) አላቸው። ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል መንግስታዊ ስርዓቱን በቀጣይነት ለመምራት ወይም ለመቀየር የሚያስችል አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የሚደረገውን እንቅስቃሴ መቀበል ወይም አለመቃወም (Passive) ነው። ስለዚህ፣ የተቃዋሚ መሪዎች ኃይል የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል ሲሆን የጨቋኝ ስርዓት መሪዎች ኃይል ግን የለውጡን እንቅስቃሴ መደገፍ ነው። ይሁን እንጂ፣ የሚፈለገው ለውጥ ለማምጣት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይሎች እኩል አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው።

በተለያየ ግዜና ቦታ ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሳሉ። በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን የመንግስት ድርሻ የሕዝብን ጥያቄ በተገቢ ሁኔታ ተቀብሎ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነው። የሕዝቡን የለውጥና መሻሻል ጥያቄ በተገቢ ሁኔታ ለመመለስ የተቃዋሚ መሪዎች ንቅናቄውን ከፊት ሆነው መምራት ያለባቸው ሲሆን የስርዓቱ መሪዎች ደግሞ የለውጡን አይቀሬነት አውቀውና ተቀብለው ከዚህ ተፃራሪ የሆኑ ተግባራትን ከመፈፀም መታቀብ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን፣ የተቃዋሚ መሪዎች ለሞት፥ እስራትና ስደት በማድረግ ሕዝባዊ ንቅናቄውን መሪ-አልባ ካደረጉት፣ እንዲሁም ለውጡን የማይቀበሉና ለእንቅስቃሴው እንቅፋት የሚሆኑ ከሆነ የሀገሪቱ ፖለቲካ ሚዛኑን ይስታል።

የዜጎችን ጥያቄ በጉልበት ለማፈን መሞከር ውድቀትን ከማፋጠን የዘለለ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ የእኩልነት ጥያቄ በየግዜው የሚለኮስ እሳት ነው። እሳቱ በተለኮሰ ቁጥር እንደ ወርቅ መቅለጥ የተሳነው መንግስት እንደ አፈር ተፈረካክሶ ይወድቃል። ይህ ሲሆን የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚል የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄ አቅጣጫውን በመሳት ወደ ሁከት፥ ብጥብጥ፥ ግጭትና ጦርነት ያመራል። ይህ እንዳይሆን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ኃይሎች እኩል አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው። የለውጡ መሪዎች ሕዝባዊ ንቅናቄው አቅጣጫውን እንዳይስት፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከበዳይ-ተበዳይ ስሜት ይልቅ በእኩልነትና ነፃነት መርህ መመራት አለበት። በሌላ በኩል፣ የስርዓቱ መሪዎች የለውጡን አይቀሬነት፥ የስርዓቱን ውድቀት አምኖ መቀበል፣ እንዲሁም ከለውጡ መሪዎች ጋር ያለ ቅድመ-ሁኔታ ለመወያየት ፍቃደኛና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። በዚህ መልኩ፣ ጨቋኝ ስርዓትን በዘላቂነት ማስወገድና በእኩልነት መርህ የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው አፓርታይድ ስርዓት የወደቀበትና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተዘረጋበትን አግባብ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ብዙውን ግዜ ስለ አፓርታይድ ሲነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የቀድሞ ፕረዜዳንት ኔልሰን ማንዴላ እና የ”ANC” ፓርቲ ናቸው። ነገር ግን፣ በደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ በወቅቱ የአፓርታይድ መንግስት ፕረዜዳንት የነበሩት “ከዲ ክለርክ” (F. W. de Klerk) እና ፓርቲያቸው “National Party” ከኔልሰን ማንዴላ እና “ANC” ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ምክንያቱም፣ ሁለቱም ወገኖች የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድ በጋራ ጥረት ባያደርጉ ኖሮ በደቡብ አፍሪካ የጥቁሮችን እኩልነትና ነፃነት ማረጋገጥ አይቻልም ነበር።

በኔልሰን ማንዴላ መሪነት ሲካሄድ የነበረው የለውጥ ትግል በዋናነት የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድና የጥቁሮችን መብትና ነፃነት ለማረጋገጥ ነው። የጥቁሮችን መብትና ነፃነት እስካልተረጋገጠ ድረስ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ እርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ማምራቱ አይቀርም። በመሆኑም፣ በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት የአፓርታይድ ስርዓትን ማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  መዘርጋት የግድ ነበር። ፕ/ት ዲ ክለርክ ደግሞ ይህን እውነት አምኖ ተቀብሎ ኔልሰን ማንዴላና ሌሎች የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪዎችን ከእስር በመፍታት በደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስለሚዘረጋበት ሁኔታ መወያየት ነበር። ለዚህ ደግሞ ዲ ክለርክ የአፓርታይድ መንግስት ፕረዜዳንት ሆነው ከተመረጡ ከጥቂት ወራት በኋላ እ.አ.አ. በ1990 ዓ.ም (ለነጮች) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፡-

“…only a negotiated understanding among the representative leaders of the entire population is able to ensure lasting peace. The alternative is growing violence, tension and conflict. That is unacceptable and in nobody’s interest. The well-being of all in this country is linked inextricably to the ability of the leaders to come to terms with one another on a new dispensation. No-one can escape this simple truth.” Transition (1990 – 1994) – Documents and Reports – 1990

አሁን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ  በማንሳት ላይ ይገኛሉ። የኢህአዴግ መንግስት የለውጡን አይቀሬነት አውቆና ተቀብሎ ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት እያደረገ ነው። ይህ የኢህአዴግ መንግስት የለውጡን አይቀሬነት አውቆና ተቀብሎ አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል አመራር እንደሌለው በግልፅ ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የመብት ተሟጋቾችን በሽብርተኝነት ወንጀል እየከሰሰ በማሰር ሕዝቡን መሪ-አልባ እያደረገው ይገኛል።

የኢትዮጲያ ፖለቲካ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በተለያዩ አከባቢዎች የሚታየው ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት የማምራት እድሉ ከፍተኛ ነው። በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና “የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” ነበር ያሉት፡፡ መሪ-አልባ ሕዝብ ግን እርስ-በእርስ ያባላል (ይጋጫል)! ስለዚህ፣ ሀገሪቷን ከእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ለመታደግ ሲባል  የኢህአዴግ መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እና የፀረ-ሽብር ሕጉንና ሌሎች አፋኝ ሕጎችን ማስወገድ አለበት፡፡ በመቀጠል፣ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቭል ማህበራት፣ እንዲሁም ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ መወያየት አለበት። 

አፓርታይድ: ክፍል-7፡- ፖለቲካ ሲያረጅ አመፅ ይወልዳል!

አንድ መንግስታዊ ስርዓት አራት የለውጥ ደረጃዎች አሉት። እነሱም፡- ህልውና (Survival)፣ እድገት (Growth)፣ ልማት (development) እና ብልፅግና (Evolution) ናቸው። የትኛውም መንግስት ቢሆን ለውጥና መሻሻል ከማምጣት በፊት በቅድሚያ የስርዓቱን ሕልውና ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህ መንግስታዊ ስርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ አስር አመታት ውስጥ የሚከናወን ይሆናል። በኢትዮጲያ ከደርግ ውድቀት በኋላ እ.አ.አ. ከ1991 – 2001 (1983 – 1993 ዓ.ም) ባሉት አስር አመታት የተከናወነ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ ደግሞ የእንግሊዝ ቅኝ-አገዛዝ ስርዓት ካበቃበት እ.አ.አ. ከ1948 – 1959 ዓ.ም ድረስ ባሉት አስር አመታት ተከናውኗል።

የደርግ ሥርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግስት የመጀመሪያዎቹን አስር አመታት የብሔር-አፓርታይድ ስርዓትን በመዘርጋትና የሥርዓቱን ህልውና በማረጋገጥ ላይ ተወጥሮ የነበረበት ውቅት ነው። በተመሳሳይ፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የዘር-አፓርታይድ የነጮችን የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚረጋግጡ ሕጎችን በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ላይ ተወጥሮ ነበር። ለምሳሌ፣በዘር ላይ የተመሰረተ የሕዝብ አሰፋፈር የሚደነግገውን “The Group Areas Act” (1950)፣ በዘር ላይ የተመሰረተ የሕዝብ ምዝገባ አዋጅ “The Population Registration Act” (1950)፣ በመጨረሻም ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን በጎሳ የሚከፋፍለውን “The Promotion of Bantu Self-Government Act of 1959” የተባለውን አዋጅ አውጥቶ ተግባራዊ ያደረገበት ወቅት ነው።

በመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት የመንግስታዊ ስርዓቱን ህልውና ለማረጋገጥ (Survival) የሚደረገው ጥረት በመጨረሻ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንዲያስመዘግቡ ያስችላቸዋል። ይህ ወቅት በኢትዮጲያ እ.አ.አ. ከ2003 – 2013 (1994 – 2004) ዓ.ም፣ በደቡብ አፍሪካ ደግሞ እ.አ.አ. ከ1960 – 1970 ዓ.ም ያሉት አስር አመታት ናቸው። በመሰረቱ የኢኮኖሚ እድገት በዋናነት የጎንዮሽ መስፋፋት (Horizontal expansion) ነው። ይህ ወቅት በኢትዮጲያ ለዘመናት በከተማው ማህብረሰብ ዘንድ ብቻ ተወስነው የነበሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ የመሰረተ-ልማቶች አውታሮች እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ወደ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል፣ ወደ ገጠር የሚስፋፋበት ወቅት ነው። የሀገሪቱ የገጠር የመንገድ፣ ትምህርትና የጤና ሽፋን በከፍተኛ ፍጥነት ያደገበት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት አውታሮች ግንባታ እና አገልግሎት ለገጠሩ ማህብረሰብ ተደራሽ የሚሆንበት ነው።

እ.አ.አ. በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ከጃፓን ቀጥሎ በአለም ፈጣን የተባለውን የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቧል። በተመሣሣይ፣ የኢህአዴግ መንግስት እ.አ.አ. ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአለም ፈጣን የተባለው የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቧል። ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው፣ በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት ከ1991 – 2001 (1983 – 1993 ዓ.ም) የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት በከፍተኛ ሁኔታ ይዋዥቅ ነበር። በሁለተኛ አስር አመታት ግን እ.አ.አ ከ2002 – 2012 (1994 – 2004) ዓ.ም ጀምሮ ግን የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት ፈጣንና ብዙ መዋዠቅ አይታይበትም።

ምስል 1፡ የኢትዮጲያ አመታዊ የምርት መጠን እድገት፣ ከ1991 – 2014 (1983 – 2007) ዓ.ም

መንግስታዊ ስርዓቱ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የሚያደርገው ጥረት ስርዓቱን ወደ ሦስተኛው የለውጥ ደረጃ፥ ልማት (development) ያሸጋግረዋል። በኢኮኖሚ እድገት (Growth) ደረጃ ላይ የሚመዘገበው ለውጥና መሻሻል በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ያለውን የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም ያሻሽለዋል፣ ማህበራዊ ግንኙነቱን ከቀድሞ በተሻለ ፈጣንና ቀልጣፋ ያደርገዋል። በዚህም የሕዝቡ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናን ይጎለበታል፣ መብትና ግዴታቸውን ማወቅና መጠየቅ ይጀምራሉ።

በዚህ መሰረት፣ በሦስተኛው አስር አመታት ላይ መንግስታዊ ስርዓቱ ስር-ነቀል የሆነ ለውጥና መሻሻል ማምጣት ይኖርበታል። ምክነያቱም፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ከሚስተዋለው ለውጥና መሻሻል ጋር አብሮ መለወጥና መሻሻል አለበት። ፖለቲካዊ ስርዓቱ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ከሚታየው የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ የማይለወጥ፥ የማይሻሻል ከሆነ ግን የለውጥ አብዮት (Revolution) ይቀሰቀሳል። በዚህ ረገድ “Huntington” የተባለው ፀኃፊ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…It is most likely to occur in societies which have experienced some social and economic development and where the processes of political modernization and political development have lagged behind the processes of social and economic change.” Political Order in Changing Societies, New Haven – London: Yale University Press, 1968.

ከላይ እንደተገለፀው፣ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እየተመዘገበ ካለው ለውጥና መሻሻል ጋር አብሮ መሄድ አለበት። በሦስተኛው አስር አመት ላይ የሚነሳውን የለውጥ ወጀብ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ እድገትን እንደ አማራጭ መጠቀም አይቻልም። ምክንያቱም፣ በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ስር-ነቀል ለውጥ ማምጣት እስካልተቻለ ድረስ በሁለተኛው አስር አመታት የነበረውን የኢኮኖሚ እድገት ማስቀጠል አይቻልም። ለምሳሌ፣ “Thomas W. Hazlett” የተባለው ምሁር በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በሦስተኛው አስር አመት የኢኮኖሚ እድገቱን ማስቀጠል በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተውን የፖለቲካ ስርዓት ማስወገድ የግድ እንደነበር ይገልፃል፡-

“Beginning about 1970, the internal contradictions of apartheid finally caused its slow demise. After the massive legal discrimination of the early apartheid years, black income, relative to white, fell dramatically, and the advance of white workers was won. But much like the boom periods of the two world wars, the robust economic growth of the 1960s rendered apartheid’s protection increasingly obsolete and exceedingly expensive. Necessity became the mother of reform.” The Concise Encyclopedia of Economics: Apartheid

በመሰረቱ፣ ከሦስተኛው አስር አመት በኋላ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት በዋናነት በአዳዲስ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የተሻሻሉ የአሰራር ዘዴዎች እና አደረጃጀቶች ላይ የተመሰረተ ነው። ጨቋኝ ወይም አምባገነን መንግስት ምንም ያህል የበጀትና ድጋፍ ቢያደርግ ዜጎች አዳዲስ ፈጠራዎች፣ ቴክኖሎጂዎች እና አሰራሮችን እንዲፈጥሩ ሊያደርግ አይችልም። ነፃ የመረጃ ፍሰት በሌለበት፣ ሃሳብን በነፃ መግለፅ በማይቻልበት እና በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ ለአዳዲስ ፈጠራዎች ምቹ የሆነ አከባቢ መፍጠር አይቻልም። በመሆኑም፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደ አማራጭ የሚቀርብ ሳይሆን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገቱ የማስቀጠል ወይም ያለማስቀጠል ጉዳይ ነው። ከታች ባለው ምስል ላይ እንደሚታየው፣ ኢትዮጲያ ሦስተኛው አስር አመት ከተጀመረበት እ.አ.አ ከ2013 (2005) ዓ.ም ጀምሮ የኢኮኖሚ እድገት እያሽቆለቆለ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል።

ምስል 1፡ የኢትዮጲያ አመታዊ የምርት መጠን እድገት፣ ከ1991 – 2014 (1983 – 2007) ዓ.ም

ከላይ እንደተገለፀው፣ በአሁኗ ኢትዮጲያ እና በቀድሞ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች እየተመዘገበ ከነበረው ለውጥና መሻሻል ጋር ተያይዞ በፖለቲካዊ አስተዳደር ስርዓቱ ላይ ተመሳሳይ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ከአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ጥያቄ ተነስቷል። በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት በጎሳ በመከፋፈል በፖለቲካ ውስጥ የነበራቸውን አብላጫ ድምፅ አሳጥቷቸው የነበሩት ጥቁሮች በተቃውሞና አመፅ እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ሲመሩ ነበር። በተመሳሳይ፣ በብሔር ልዩነት ላይ የተመሰረተው የኢህአዴግ ፖለቲካ ቀድሞ የነበራቸውን አብላጫ ድምፅ የተቀሙት የአማራና ኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ባለፉት አመታት የታየውን የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ከፊት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ፣ በቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካና በአሁኗ ኢትዮጲያ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላነሳው ጥያቄ እየተሰጠ ያለው ምላሽ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። እሱም የሕዝቡን የለውጥ ጥያቄ በወታደራዊ ኃይል ለማፈን መሞከር ነው። በዚህ መሰረት፣ ልክ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ዘመን እንደተደረገው፣ ዛሬ በኢትዮጲያ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ንፁሃን ዜጎችን በጥይት በመግደል፣ የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎችን የረጅም አመት እስራት በመፍረድና በማሰር የሕዝቡን ጥያቄ በኃይል ለማኮላሸት ጥረት እየተደረገ ነው። በሦስተኛው አስር አመት ልክ የአፓርታይድ ስርዓት እንዳደረገው ሁሉ፣ በኢትዮጲያም የተነሳውን የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጇል። በዚህም፣ የሀገሪቱን መከላከያ ሰራዊት እንደ ፖሊስ በመጠቀም የሕዝቡን የፖለቲካ መብትና እንቅስቃሴ በወታደራዊ ኃይል ለማፈን እየተሞከረ ነው።

በአጠቃላይ፣ ከአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ከሚያነሳው የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ የተሳነው ፖለቲካዊ ስርዓት ይዝጋል። የዛገ፥ ያረጀ ፖለቲካ ደግሞ አመፅ ይወልዳል። ለምንና እንዴት የሚለውን በቀጣይ ክፍል እንመለስበታለን።   

የብሔር ፖለቲካ ጡዘት ከሰውነት እስከ አውሬነት ያደርሳል!

የሌላ ሀገር ዜጋን እየወደድን የሌላ ብሔር ተወላጅን እንጠላለን!

እስኪ አንድ ኢትዮጲያዊን ዝም ብላችሁ ታዘቡት። ወደ ቤተ-እምነት ሲሄድ “የሰው-ልጅ በአምላክ አምሳል የተፈጠረ ነው። ሰዎች እርስ-በእርስ ተዋደዱ፣ ጠላትህን እንደ ራስህ ውደድ፣…ወዘተ” የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮት “አሜን” ይቀበላል። ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ደግሞ ስለ ሰው ልጆች እኩልነት ይማራል። በሁሉም የትምህርት ደረጃ የታሪክና የሲቪክ መማሪያ መፅሃፍት ውስጥ በጥቁር-አሜሪካዊያን ላይ ስለደረሰው ባርነትና የጉልበት ብዝበዛ፣ በአፓርታይድ አገዛዝ ወቅት በጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ላይ ስለተፈፀመው የዘር መድሎና ጭቆና፣…ወዘተ በሰፊው ያስተምራሉ። የግል ሆነ የመንግስት ሚዲያ ተቋማት ዘወትር “ዘር-ቀለም ሳንለይል…” እያሉ ዘወትር ይዘምራሉ።

አብዛኛው ኢትዮጲያዊ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የቀድሞ ታሪክ ወይም ወቅታዊ ፖለቲካ በሰዎች ላይ ስለሚፈፀም የዘረኝነት መድልዎና መገለል፣ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና፣ ፖለቲካዊ እስራትና ግድያ፣…ወዘተ በየሚዲያው ይሰማል፣ በየትምህርት ቤቱ ይማራል፣ እርስ-በእርሱ ይወያያል፣ በጋራ ያወግዛል። በጦርነቶች ወይም በሽብር ጥቃቶች በሰዎች ላይ የሞትና አካል ጉዳቶች ሲደርሱ ሰብዓዊ ርህራሄ ይሰማዋል። ከማንም ቀድሞ ለተጎዱ ወገኖች የተሰማውን “ጥልቅ ሃዘን” በይፋ ይገልፃል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ በሀገሪቱ የቀድሞ ታሪክ ወይም በወቅታዊ ፖለቲካ አማካኝነት በዜጎች ላይ ስለተፈፀሙ በደሎች፣ ጭቆናዎች፣ አድልዎች፣ ግድያና እስራቶች ከቤተሰብ ወይም ከቅርብ ወዳጆቹ ጋር በግልፅ ይነጋገራል፥ ይወያያል፣ ይግባባል። በሌሎች ሰዎች ላይ የተፈፀሙ ታሪካዊና ፖለቲካዊ በደሎችና ጭቆናዎች በቤተሰቡ አባላት ወይም በወዳጆቹ ላይ እንዲፈፀም አይሻም።

እስካሁን ድረስ እንደተመለከትነው፣ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ለእሱ ቅርብ ከሆኑት የቤተሰብ አባላት ወይም ወዳጆች እና ሩቅ ካሉት የሌላ ሀገር ዜጎች ጋር ያለው ግንኙነትና አመለካከት በዋናነት በበጎ አመለካከትና በሰብዓዊነት የታነፀ ነው። ነገር ግን፣ ስለ ራሱ ሀገር የቀድሞ ታሪክና ወቅታዊ ፖለቲካ ውይይት ሲጀምር በአንድ ግዜ አቅሉን ይስታል። ስለኢትዮጲያ የቀድሞ ታሪክ ሆነ አሁን ስላለው ፖለቲካዊ ስርዓት የሚደረገው ውይይት ወዲያው “አማራ፣ ኦሮሞ፣ “ትግሬ”፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ሱማሌ፣….” እየተባባሉ መደናቆር ይጀመራል።

ታሪካዊ በደልና ጭቆና ወይም ፖለቲካዊ እስራትና ሞት በሌላ ሀገር ዜጋ ወይም በቤተሰባችን አባል ላይ ሲደርስ የነበረን ሰብዓዊነት እዚሁ ለሌላ ብሔር ተወላጅ የሀገራችን ዜጎች ሲሆን ከውስጣችን እንደ ጉም በኖ ይጠፋል። ለውጪ ሀገር ዜጋ የነበረን ሰብዓዊ አመለካከት ለሌላ ብሄር ተወላጅ ሲሆን ወደ ፖለቲካ ይቀየራል።

ለምሳሌ፣ ባለፈው አመት አንድ ወዳጄ “በጎንደር የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ከመኖሪያ ቄያቸው ተፈናቀሉ” በሚል አምርሮ ሲቃወም ነበር። በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት መሰረት በአማራ፣ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል ከአራት ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ 669 ሰዎች መገደላቸው ስነግረው “እነዚህ ፋብሪካ ለማቃጠል የወጡ ወንጀለኞች ናቸው” አለኝ። ይሄው ሰው ግን፣ ባለፈው በለንደን ከተማ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት አንዲት የፓርላማ አባል መገደሏን እንደሰማ ጥቃቱን በማውገዝ ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ሲገልፅ ማንም አልቀደመውም። ታዲያ ይህ ወዳጄ ለውጪ ሀገር ዜጋ የነበረውን ሰብዓዊ አመለካከት ለሌላ ብሔር ተወላጅ ሲሆን በአንዴ ወደ ፖለቲካ ለምን ቀየረ?

በተመሣሣይ ስለ ሀገራችን የቀድሞ ታሪክና ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ከውጪ ሀገር ዜጎች ጋር መወያያት እየቻልን የሌላ ብሔር ተወላጅ ከሆነ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ጋር ግን መግባባት ቀርቶ መደማመጥ አንኳን አይቻልም። ለምሳሌ፣ ባለፈው ሳምንት ከአንድ ኢጣሊያናዊትና ኤርትራዊት ጋር ለመወያያት እድሉ ገጥሞኝ ነበር። ከኢጣላናዊቷ ጋር ስለ አደዋ ጦርነትና አፄ ሚኒሊክ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ውይይት አድረገን። በተመሣሣይ፣ ከኤርትራዊቷ ጋር በኤርትራና በኢትዮጲያ ስላለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በግልፅ ተወያየን። ወደ ሀገሬ ስመጣ ግን ስለ ኢትዮጲያ የቀድሞ ታሪክ ሆነ ስለ ወቅታዊ ፖለቲካ በግልፅ መወያያት አይቻልም። ስለ አደዋና አፄ ሚኒሊክ ከኢጣሊያን ዜጋ ጋር መወያያት ከቻልኩ ከአንድ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ጋር መወያያትና መግባባት የሚሳነኝ ለምንድነው? ከኤርትራዊቷ ጋር ያደረኩትን ግልፅ ውይይት ከአንድ የትግራይ ተወላጅ ጋር ማድረግ የሚከብደኝ ለምንድነው? ከሌላ ሀገር ዜጋ የነበረን ግልፅ ውይይት ከሌላ ብሔር ተወላጅ ጋር ሲሆን በጭፍን ጥላቻ መደናቆር የሚሆነው ለምንድነው?

በአጠቃላይ፣ ከሌላ ሀገር ዜጋ ጋር በግልፅ እየተወያየን ከሌላ ብሔር ተወላጅ ጋር እንኮራረፋለን። ለሌላ ሀገር ዜጋ የነበረን ስብዓዊነት ለሌላ ብሔር ተወላጅ ሲሆን ፖለቲካ ይሆናል። የሌላ ሀገር ዜጋን እየወደድን የሌላ ብሔር ተወላጅን እንጠላለን። በቤተሰባችን አባላት ላይ ቀርቶ በሌላ ሀገር ዜጋ ላይ እንኳን እንዲደርስ የማንፈልገውን መጥፎ ነገር በሌላ ብሔር ተወላጅ ላይ ለማድረስ እንዝታለን። ለመሆኑ ለኢትዮጲያዊ ከሌላ ሀገር ዜጋ እና ከሀገሩ ልጅ ማን ይቀርበዋል?

የ“እኛ” እና “እነሱ” ፖለቲካ፡ ከሰብዓዊነት እስከ አውሬነት

የሰው-ልጅ እርስ-በእርሱ የሚያደርገው ማህበራዊ ግንኙነት እና አንቅስቃሴ በዋናነት “እኛ” እና “እነሱ” በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በቋንቋ አጠቃቀማችን እና ትምህርት አሰጣጣችን መሰረት እያንዳንዱ ሰው ራሱን “እኛ” በሚል የቡድን እሳቤ ውስጥ ነው የሚመለከተው። ሌሎችን ደግሞ “እነሱ” በሚል የተፃራሪ ቡድን አባል አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ አለ። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ እንደ ሁኔታ የሚለያይ ነው። ለምሳሌ፣ “እኛ” ኢትዮጲያዊያን ከሆንን “እነሱ” ኢጣሊያዊያን፣ እንግሊዛዊያን፣ ኤርትራዊያን፣…ወዘተ፤ “እኛ” ኦሮሞ ከሆንን “እነሱ” አማራ፣ “ትግሬ”፣ ጉራጌ፣…ወዘተ፤ “እኛ” የአበበ ቤተሰቦች ከሆንን “እነሱ” የጫላ ቤተሰቦች፣ የሃጎስ ቤተሰቦች፣…ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ። በአጠቃላይ፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለውን እሳቤ እንደ ሁኔታው በቤተሰብ፣ ብሔርና ሀገር ደረጃ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል።

በሦስቱም ደረጃ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው አመለካከት የሚወሰነው በመካከላችን ካለው ግንኙነት አንፃር ነው። በዚህ መሰረት፣ ለአንድ ኢትዮጲያዊ የኢጣሊያኖችን ሃሳብና እንቅስቃሴ ማወቅና መገመት ከባድ ነው። ነገር ግን፣ የሁለቱ ሀገር ዜጎች በኢትዮጲያዊው ማህበራዊ ሕይወትና የዕለት-ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ውስን ነው። የኦሮሞዎች ሕይወት ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሃሳብና እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ አብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ስለ አማራ፣ ትግራይ ወይም ጉራጌ ብሔር ተወላጆች ሃሳብና እንቅስቃሴ ማወቅና መገመት ይፈልጋል። ይሁን እንጂ፣ ሁሉም የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ከማንም በፊት የቤተሰቡንና የቅርብ ወዳጆቹን ሃሳብና እንቅስቃሴ በትክክል ማወቅና መገመት አለበት።

እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ በሕይወቱ ውስጥ ቀጥተኛ ግንኘነትና ተፅዕኖ ስላላቸው ቤተሰቦቹና የቅርብ ወዳጆቹ ሃሳብና እንቅስቃሴ በእርግጠኝነት ማወቅ ይችላል። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ የቤተሰቡ አባላት ወይም የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት “እነሱዎች” ጋር በቃላሉ መነጋገርና መግባባት ይችላል። ማህበራዊ ግንኙነቱም በውይይትና ሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ ይሆናል። ነገር ግን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ስለ ሌላ ሀገር ዜጎች ሃሳብና እንቅስቃሴ በእርግጠኝነት ማወቅ አይችልም። ይሁን እንጂ፣ የውጪ ሀገር ዜጎች ከእሱ ጋር ያላቸው ግንኙነትና በዕለት-ከእለት ሕይወቱ ውስጥ ያላቸው ተፅዕኖ ውስን ነው። ስለዚህ፣ ሩቅ ያሉ የሌላ ሀገር ዜጎች “እነሱዎች” ጥሩ ሥራና ምግባር እንዳላቸው ይገምታል።

“Edmund Leach” የተባለው ምሁር፣ ቅርብ ባሉት “እነሱዎች” እና ሩቅ ባሉት “እነሱዎች” መካከል ሌላ ሦስተኛ “እነሱዎች” እንዳሉ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ብዙውን ግዜ ሰዎች ስለ ከሦስተኛው “እነሱዎች” ጋር ያላቸው ግንኙነት በውይይት ላይ ያልተመሰረተና ለሌሎች ያላቸው አመለካከት ሰብዓዊነት የጎደለው ነው፡-

“But lying in between the remote Heavenly other and the close predictable other there is a third category which arouses quite a different kind of emotion. This is the other which is close at hand but unreliable. If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” REITH LECTURES 1967: A Runaway World, Lecture 3: Ourselves and Others: 26 November 1967 – Radio 4

ከውጪ ሀገር ዜጋ ጋር በግልፅ መወያየትና መግባባት እንችላለን። ከእነሱ ጋር መወያየትና መግባባት ባንችል እንኳን የእነሱ ሃሳብና እንቅስቃሴ በእኛ ሕይወት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ዝቅተኛ ስለሆነ ይህን ያህል አሳሳቢ አይደለም። ሆኖም ግን፣ በአንድ ሀገር ውስጥ አብረን እየኖርን እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ከተሳነን፤ የጠበቀ ማህበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እያለን አንዳችን የሌላችንን ሃሳብና እንቅስቃሴ ማወቅና መገመት ከተሳነን፣ እንደ ሰው ያለን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ አመለካከታችን ከውስጣችን ይጠፋል። ከቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን፣ ከጎጥ፣ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል ነዋሪዎች ጋራ የነበረን በውይይትና ምክንያታዊ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ አመለካከት፣ እንደ ሰው የነበረው ሰብዓዊነት ለሌላ ክልል ነዋሪዎች ወይም ብሔር ተወላጆች ሲሆን ከውስጣችን ተሟጥጦ ይጠፋል።

የሌላ ሀገር ዜጋን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያየ፣ የሌላ ብሔር ተወላጅን ግን እንደ ዱር አውሬ አድኖ መግደል ይሻል። በእርግጥ ለአንዳንዶቻችሁ አገላለፁ በጣም የተጋነነ ሊመስላችሁ ይችላል። ነገር ግን፣ የራሱን ዝርያ እንደ አውሬ ወይም ጠላት አድኖ የሚገድል ፍጡር ቢኖር የሰው ልጅ ብቻ ነው። በጣም ውስን በሆኑ አጋጣሚዎች ካልሆነ በስተቀር ሌሎች እንስሳት የሚያድኑትና የሚገድሉት ሌላ የእንስሳት ዝርያን ነው። እንደ “Edmund Leach” አገላለፅ፣ የራሱን ዝርያ እንደ አውሬ ማደንና መግደል የሚሻው የሰው-ልጅ ብቻ ሲሆን ይህም በዋናነት በቃላት ላይ የተመሰረተ የመግባቢያ ቋንቋ በምክንያትነት ይጠቀሳል፡-

“…our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. In the non-human world whole species function as a unity. Wolves do not kill each other because all wolves behave the same language. If one wolf attacks another wolf, the victim automatically responds with a gesture which compels the aggressor to stop. … The complication in our own case is that if a human victim is to be safe, the attacker and the attacked must not only behave the same language, they must speak the same language, and be familiar with the same code of cultural symbols. And even then each individual can make his own decision about what constitutes ‘the same language’.’’ REITH LECTURES 1967: A Runaway World, Lecture 3: Ourselves and Others: 26 November 1967 – Radio 4

ከላይ በጥቅሱ ውስጥ እንደተገፀው፣ የብሔር ፖለቲካ የአንዱን ወይም የሌላን ብሔር እኩልነት በማረጋገጥ ላይ ብቻ የሚቆም አይደለም። የሰው-ልጅን ምክንያታዊ አስተሳሰብና ሰብዓዊነት ከላዩ ላይ ገፍፎ የሚወስድ፣ የአንዱን ብሔር ሕልውና ለማረጋገጥ በሚል የሌላውን ብሔር ሕልውና እስከማሳጣት የሚደርስ ነው። አጉል ብሔርተኝነት የሰው ልጅን ባህሪ ከሰብዓዊነት ወደ ተራ እንስሳነት ይቀይረዋል። ከሁሉም እንስሳት በተለየ ሰዎችን እንደ የዱር አውሬ እያደነ የሚገድል ጨካኝ ፍጡር ያደርገዋል። በታዝማኒያዎች (Tasmanians) እና በአይሁዶች ላይ የፈፀመው የዘር-ማጥፋት፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የአፓርቲይድ አገዛዝ በጥቁሮች ላይ የተፈፀመው አድሎና በደል፣… ሁሉም የሌላ ብሔር ተወላጆችን እንደ ሌላ ዓይነት ፍጥረት አድርጎ በብዙሃን አዕምሮ ውስጥ በመሳልና፣ ለታሪካዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እነሱን ተጠያቂ በማድረግ የተፈፀሙ ናቸው።

በአንድ ሀገር ውስጥ አብረው እየኖሩ የማይነጋገሩ፣ ከወደፊት የተስፋ ይልቅ የታሪክ ጠባሳዎችን በመዘከር፣ በጋራ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸው ዙሪያ ከመወያየት ይልቅ በመፈራራት፣ በአጠቃላይ እርስ-በእርስ ተነጋግሮ ከመተማመን ይልቅ በጥርጣሬ አይን በመተያየት ላይ የተመሰረተው ብሔራዊ አንድነት መጨረሻው እንጥርጥሮስ ነው።