Tag Archives: Ethnicity

ብሔርተኝነት የሰው-ልጅን ወደ አውሬነት ይቀይራል (ክፍል-2)

ታላቁ ደራሲ ስብሃት ገ/እግዜያብሄር አሁን ርዕሱን በረሳሁት ድርሰት ውስጥ በውሻና ሰው መካከል የተደረገ ቃለ-ምልልስ አለ። ሰውዬው ከሚጠጣው አረቄ ትንሽ የቀመሰው ውሻ ሲሰክር በሰውኛ ዘይቤ መሳደብ ይጀምራል፤ “እኛ ውሾች እንደ ሰው “እኛ” እና “እናንተ” ብሎ አናውቅም” ይላል። ባለቤቱ “እንዴት ባክህ?” ሲለው “በቃ…ሁላችንም “እኛ” ነን” ይለዋል። ደራሲው ጋሽ ስብሃት በዚህ ቃለ-ምልልስ ያስተላለፈው መልዕክት በደንብ የገባኝ ከአራት አመታት በኋላ ነው፡፡

የጋሽ ስብሃት ሃሳብ የገባኝ “Edmond Leach” የተባለውን ምሁር ትንታኔ ካነበብኩ በኋላ ነው። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ከሰው ልጅ በስተቀር በሁሉም እንስሳት ዘንድ አንድ ዝርያ እስከሆኑ ድረስ ሁሉም “እኛ” ናቸው። ለምሳሌ፣ ውሻ ጥቁር ሆነ ነጭ፣ የፈረንጅ ሆነ የሀበሻ፣ የጀርመን ሆነ የአሜሪካ፣…ወዘዘተተ ሁሉም ደመ-ነፍሳዊ በሆነ የምልክት ቋንቋ ይግባባሉ። ስለዚህ፣ ውሾች ሲጣሉ ሆነ ሲፋቀሩ የሚግባቡበት፥ ስሜታቸውን የሚገልፁበት የጋራ መግባቢያ አላቸው።

የሰው ልጅን ጨምሮ ሁሉም እንስሳት አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ባህሪ አላቸው። እሱም “ፀብና ጥቃት” (aggression) ውጫዊ እና ውስጣዊ አይደለም። ማለትም፣ የውሻ ፀብና ጥቃት ለምሳሌ በጅብ፥ ቀበሮ፥…ላይ እንጂ የራሱ ዝርያ በሆነ ሌላ ውሻ ላይ ያነጣጠረ አይደለም። በእርግጥ በውሾች መካከል የእርስ-በእርስ ፀብና ጥቃት ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን፣ በጣም በተለየ አጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር አንድ ውሻ በሌላ ውሻ ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ጥቃት አይፈፅምም። ብዙ ግዜ ታዝባችሁ እንደሆነ፣ አንድ ጉልበተኛ ውሻ ለፀብ ወይም ለመናከስ እየሮጠ ሲሄድ ሌላኛው ውሻ ጭራውን እያወዛወዘ ከተለማመጠው ወይም መሬት ላይ ከተኛ አይነክሰውም። እዚህ ጋር ሊሰመርባቸው የሚገቡ ሁለት ነጥቦች አሉ። አንደኛ፡- ጉልበተኛው ውሻ የሚፈልገው የሌላውን ውሻ ተገዢነት ወይም ተሸናፊነት ነው፣ ሁለተኛ፡- ውሾች በፀብና ግጭት ውስጥ የሆነው እንኳን እርስ-በእርስ በምልክት ይነጋገራሉ፥ ይግባባሉ።   

ከሁሉም እንስሳቶች በተለየ የራሱን ዝርያ የሚገድል ፍጡር የሰው-ልጅ ብቻ ነው። “Edmond Leach” ይሄን ኢ-ተፈጥሯዊ የሆነ የሰው ልጅ ባህሪ በዋናነት ከሰው ልጅ የቋንቋ አጠቃቀምና አስተሳሰብ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይገልፃል። በእርግጥ የሰው ልጅ ሁሉም ነገር ከራሱ አንፃር የማየት ባህሪ አለው። ቋንቋችንም ከዚሁ አንፃር የተቃኘ ነው። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው ለራሱ ቅርብ የሆኑትን ሰዎች፤ እናት፥ አባት፥ ልጆች፥ እህት፥ ወንድም፥ ልጆች፥…ወዘተ ያሉትን “እኛ” ሲል ከዚህ ቀረቤታ ውጪ ያሉትን ደግሞ “እነሱ” ይላል።

“የእኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። “እኛ” የስዩም ቤተሰቦች ከሆንን የጋሽ ስብሃት ቤተሰቦች “እነሱ” ናቸው፣ “እኛ” አሰላዎች ከሆንን “እነሱ” አደዋዎች፥ አሳይታዎች፥…ናቸው። “እኛ” ኦሮሞች ከሆንን እነሱ አማራዎች፥ ትግሬዎች፥ ወላይታዎች፣ “እኛ” ኢትዮጲያዊያን ከሆንን “እነሱ” ግብፃዊያን፥ ኤርትራዊያን፥ ጀርመናዊያን፣ “እኛ” በምድር ላይ የምንኖር ሰዎች ከሆንን “እነሱ” በሌላኛው ዓለም የሚኖሩ “መናፍስት”…ወዘተ ናቸው።

በጣም ቅርብ የሆኑትን “እኛ” ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት ይቻላል። በጣም ሩቅ የሆኑትን “እነሱ” ደግሞ ባህሪና እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ማወቅ፥ መገመትና መግባባት አይቻልም። ለእኛ በጣም ቅርብ የሆኑትን ስራና ተግባር በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም በንግግር መግባባት ስለሚቻል የፍርሃትና ስጋት ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም። ለእኛ በጣም ሩቅ የሆኑት ደግሞ በእለት-ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ስለሌላቸው ምንም ስጋትና ፍርሃት ሊፈጥሩ አይችሉም።

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ “እኛ” እና “እነሱ” የሚለው እሳቤ አንፃራዊ ነው። በዚህ መሰረት፣ ሩቅ ባሉት “እነሱዎች” እና ቅርብ ባሉት “እኛዎች” መካከል ሌላ ሦስተኛ “እነሱዎች” አሉ። እነዚህ ሦስተኞቹ “እነሱዎች” ከቦታና ግዜ አንፃር ለእኛ ቅርብ ቢሆኑም ሥራና ተግባራቸውን ግን በቀላሉ ማወቅና መገመት፣ እንዲሁም ተነጋግሮ መግባባት አይቻልም። “በእኛዎች” እና በሦስተኛ “እነሱዎች” መካከል ላለው ልዩነት መነሻ ምክንያቱ ተነጋግሮ መግባባት አለመቻል ነው። “እኛ” እና “እነሱ” በሚለው እሳቤ መሰረት፣ ሰዎች የተለየ ቋንቋ ሲናገሩ፣ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ሲሳናቸው፣ በዚህም አንዱ የሌላውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅና መገመት ሲሳነው፣ “እኛ” ሰዎች፥ ሌሎቹን ደግሞ ከሌላ የእንስሳት ዝርያ የመጡ ለምሳሌ “ውሾች” አድርገው ይስላሉ።

የሰው ልጅ በቅርቡ ካለ ሰው ጋር መነጋገርና መግባባት ከተሳነው፣ በዚህም የሰውዬውን እንቅስቃሴና ባህሪ ማወቅ ሆነ መገመት ከተሳነው፣ አንዱ በሌላው ላይ ስጋትና ፍርሃት ይጭራል። በቅርብ የሚኖሩ ሰዎች የማይነጋገሩ፥ የማይግባቡ፥ የማይተዋወቁና የማይተማመኑ እርስ-በእርስ እንደ ሌላ ፍጡር መተያየት ይጀምራሉ። አንዱ ራሱን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያየ ሌላውን ግን እንደ አውሬ ማየት ይጀምራል። እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ይህን ግዜ የሰው ልጅ ከሰብዓዊነት ወደ አውሬነት ይቀየራል፡-

“…our propensity to murder is a back-handed consequence of our dependence on verbal communication: we use words in such a way that we come to think that men who behave in different ways are members of different species. In the non-human world whole species function as a unity. …If anything in my immediate vicinity is out of my control, that thing becomes a source of fear. This is true of persons as well as objects. If Mr X is someone with whom I cannot communicate, then he is out of my control, and I begin to treat him as a wild animal rather than a fellow human being. He becomes a brute. His presence then generates anxiety, but his Jack of humanity releases me from all moral restraint: the triggered responses which might deter me from violence against my own kind no longer apply.” A Runaway World: Lec. 3: Ourselves and Others, 1967   

ከሰው ልጅ በስተቀር ሌሎች እንስሳት ምንም ያህል ቢራራቁ ወይም ቢቀራረቡ፣ አንድ ዓይነት ዝርያ እስከሆኑ ድረስ በምልክት ቋንቋ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ስለዚህ፣ በመካከላቸው ምንም ያህል ልዩነት ቢፈጠር አንዱ ሌላውን እንደ ሌላ ዝርያ ፍጡር አይመለከተውም። እዚህ ጋር ጋሽ ስብሃት በሰውኛ ዘይቤ “በውሾች ዘንድ “እኛ” እና “እነሱ” የሚባል ነገር የለም” ያለው ማስታወስ ተገቢ ነው። በእርግጥ ውሾች አንድ ዓይነት መግባቢያ ቋንቋ አላቸው። ስለዚህ፣ ከጎንደር ሆነ አሳይታ፣ ከአክሱም ሆነ ወላይታ፣ …ከየትኛውም አከባቢ የመጡ ውሾች እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ይችላሉ። ነገር ግን፣ ከተጠቀሱት አከባቢዎች የመጡ ሰዎች በአንድ ቦታ ቢገናኙ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት አይችሉም።

እንደ “Edmond Leach” አገላለፅ፣ ሁለት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች በጋራ ጉዳይ ላይ እርስ-በእርስ መነጋገርና መግባባት ከተሳናቸው አንዱ ራሱን እንደ ሰው ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) ማየት ይጀምራል። ይሄ ነገር ግን በውሾች መካከል አይከሰትም። በመሆኑም፣ ሰዎች በብሔርና በዘር ቡድን መስርተው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እርስ-በእርስ ሲጨፋጨፉ ውሾች ግን ሁሉም “እኛ” ስለሆኑ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም። በአጠቃላይ፣ በ”እኛ” እና “እነሱ” እሳቤ ከሚመራው የሰው ልጅ በስተቀር የአንድ ዝርያ እንስሳት እንዲህ በጭካኔ እርስ-በእርስ አይገዳደሉም።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እርስ-በእርስ መገዳደል እንደ ማንኛውም እንስሳ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ አይደለም። የሰው ልጅ ግን በዘር/ብሔር/ሀገር ተቧድኖ እርስ-በእርስ ይገዳደላል። ለዚህ ዋናው ምክንያት አንዱ ወገን ራሱን እንደ ሰው፣ ሌላውን ደግሞ እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) መመልከቱ ነው። የሰው ልጅ ራሱን “እኛ” እና “እነሱ” ብሎ ለመመደብ የሚጠቀምበት ዋና መለያ መስፈርት “ቋንቋ” ነው። በተመሣሣይ፣ አንድን ብሔር ከሌላው ለመለየት አንዱና ዋንኛው መስፈርት ቋንቋ ነው። በሀገራችን በስፋት የሚስተዋለው የብሔርተኝነት ስሜት በዋናነት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ነው።

ስለዚህ፣ “ብሔርተኝነት” ሁለት ጎን-ለጎን የሚኖሩ የተለያየ ብሔር ተወላጆችን እንደ ሌላ ፍጡር (አውሬ) እንዲተያዩና እንዲጨካከኑ፣ በዚህም እርስ-በእርስ እንዲገዳደሉ በሚያደርግ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በዚህ መሰረት፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅን የአውሬነት ባህሪ እንዲላበስ በማድረግ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው። እንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቼም፥ የትም ቢሆን ሕዝብን ወደ ጦርነትና እልቂት የሚወስድ ነው።         

ከዚህ በተጨማሪ፣ ብሔርተኝነት በራሱ የጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት ውጤት ነው። በአማርኛ መዝገበ ቃላት “ጠባብ አስተሳሰብ/አመለካከት” የሚለውን፤ “ጥልቀት የሌለው፣ በስፋት የማይገነዘብ፥ አርቆ ማየት የጎደለው” የሚል ፍቺ አለው። በተመሳሳይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው ደግሞ “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። ስለዚህ፣ ከብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ከእኛ ያነሰ ክብርና ዋጋ መስጠት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ ብሔርተኝነት የአንድን ብሔር መብትና ነፃነት ከማረጋገጥ ባለፈ ራስን ከሌሎች የተሻለ አድርጎ በማሰብ ወይም ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ዝቅተኛ ግምትና ክብር በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ራሱ ጎሳ ብቻ የሚያስብና በሌላው ላይ ጥላቻ ያለው የፖለቲካ ቡድን ከራስ-ክብር (Self-respect) ይልቅ በራስ-ወዳድነት (Egoism) የሚመራ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ለራስ ክብር (Self-respect) የሚደረግ የነፃነትና እኩልነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም የሰብዓዊነት (humanity) እና የጋራ እሰቶችን (common values) በማስረፅ የሚካሄድ ነው።

በራስ-ወዳድነት (Egoism) የተመሰረተ የብሔርተኝነት ትግል የመጨረሻ ግቡ የሁሉም ዜጎች መብትና ነፃነት ሳይሆን የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ እንቅስቃሴም በዋናነት የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም ብሔር ተወላጆችን ልክ እንደ አውሬ በመመልከትና በኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ጭካኔ የተሞላ ነው። ታዋቂው ፈላስፋ “Jean Jacques Rousseau” እንዲህ ያሉ በበታችነትና በራስ-ወዳድነት ስሜት የናወዘ የፖለቲካ አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ያለ ምንም ምክንያት ወይም ጉዳት ወደ ፍፁም አውሬነት ሊቀየሩ እንደሚችሉ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…men who neither valued nor compared themselves could do one another much violence, when it suited them, without feeling any sense of injury. In a word, each man, regarding his fellows almost as he regarded animals of different species, might seize the prey of a weaker or yield up his own to a stronger, and yet consider these acts of violence as mere natural occurrences, without the slightest emotion of insolence or despite, or any other feeling than the joy or grief of success or failure.” WHAT IS THE ORIGIN OF INEQUALITY AMONG MEN, AND IS IT AUTHORISED BY NATURAL LAW?, 1754, Trans. by G. D. H. Cole.

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ፍፁም ስህተት ከመሆኑ በተጨማሪ የአውሬነት መገለጫ ነው። በማንኛውም ግዜ ቦታ ቢሆን በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሀገርን ወደ የእርስ-በእርስ ጦርነት የሚያስገባና ጨቋኝ ስርዓት በመዘርጋት የሚቋጭ የድኩማኖች መንገድ ነው። በአጠቃላይ፣ ብሔርተኝነት የሰው ልጅ አውሬነት መገለጫ ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት የሚደርግ ሕዝባዊ ንቅናቄና ትግል እንዴት መጀመርና ምን መሰረት ማድረግ እንዳለበት በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።

አፓርታይድ ክፍል-8፡ የእኩልነት እና የፍርሃት ትግል

በእርግጥ የአንድ ሀገር ሕዝብ በብዙ ነገር ይለያያል። ለምሳሌ፣ በዘር፥ በብሔር፥ በጎሣ፥ በቋንቋ፥ በሃይማኖት፥ ባህል፥ ልማድ፥…ወዘተ። ስለዚህ፣ በተለያዩ ማህብረሰቦች መካከል ልዩነት መኖሩ እርግጥ ነው። በአንድ በኩል “በአንድነት” ስም እነዚህን ልዩነቶች በመጨፍለቅ ለማስተዳደር መሞከር ጨቋኝነት ነው። በሌላ በኩል “በብዙሃንነት” ስም በልዩነት መከፋፈል ደግሞ ሌላ የጭቆና ዘዴ ነው። ስለዚህ፣ ለፖለቲካዊ አስተዳደር ያለው ብቸኛ አማራጭ በልዩነት ውስጥ አንድነትን መፍጠር መቻል ነው።

የደቡብ አፍሪካ ዜጎች በዘር፥ በቀለም፥ በቋንቋ፥…ወዘተ ይለያያሉ፣ እንዲሁም ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን ደግሞ በጎሣና ነገድ ይለያያሉ። በተመሣሣይ፣ የኢትዮጲያ ሕዝብ በብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ አሰፋፈር፥ …ወዘተ ይለያያል። እያንዳንዱ ማህብረሰብ ከሌሎች ጋር ያለውን ልዩነት እንዳለ ይዞ በአንድ ሀገር ውስጥ በጋራ አብሮ ለመኖር መስማማትና መግባባት መቻል አለበት። ስለዚህ፣ በእንዲህ ያለ ሀገር ውስጥ በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለመፍጠር መጣር አለበት። አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ ልዩነትን በማስፋት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ከሆነ የፖለቲካ ስልጣኑ በብዙሃን ዘንድ ቅቡልነት እንደሌለው ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በዋናነት ከአንድ ዘር/ብሔር የተወጣጣና የዚያን ማህብረሰብ የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ከሆነ በእርግጥ እሱ የአፓርታይድ ስርዓት ነው።   

ከዚህ አንፃር፣ የአፓርታይድ ስርዓት ሁለት መሰረታዊ ባህሪያት አሉት። የመጀመሪያው ባህሪ ብዙሃኑን የሕብረተሰብ “መከፋፈል” ነው። “አፓርታይድ” (Apartheid) የሚለው ቃል በራሱ በራሱ “መለየት” (Separatedness) ወይም “መለያየት” (the state of being apart) ነው። በዚህ መሰረት፣ የደቡብ አፍሪካው የዘር-አፓርታይድ ስርዓት ዜጎችን በመጀመሪያ በዘርና ቀለም ለአራት ከፈላቸው። በመቀጠል ደግሞ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን በጎሣና ነገድ ለአስር ከፋፈላቸው። በተመሣሣይ፣ በኢትዮጲያ ያለው የብሔር-አፓርታይድ የሀገሪቱን ዜጎች በብሔርና በክልል ከፋፈላቸው።

ሁለተኛው የአፓርታይድ ባህሪ ደግሞ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። የደቡብ አፍሪካ የዘር-አፓርታይድ ዓላማ የነጭ ሰፋሪዎችን በራስ-የመወሰን መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ እንዲሁም በእንግሊዞች የተፈፀመባቸው በደልና ጭፍጨፋ ዳግም እንዳይከሰት ማድረግ ነው። በተመሣሣይ፣ በኢትዮጲያ የብሔር-አፓርታይድ ዓላማ የትግራይ ሕዝብን በራስ-የመወሰን መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ እንዲሁም በደርግ ስርዓት የተፈፀመባቸው በደልና ጭፍጨፋ ዳግም እንዳይከሰት ማድረግ ነው።

በክፍል ስድስት በዝርዝር እንደተገለፀው፣ የአፓርታይድ ስርዓት ዓላማ የአንድን ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲሆን የአተገባበር ስልቱ ደግሞ አብላጫ ድምፅ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል መከፋፈል ነው። የመከፋፈል መሰረታዊ ዓላማ ደግሞ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወይም ቡድኖች መካከል የሚደረገውን ትግል ማሸነፍ ነው። የትግሉ ማህበራዊ ፋይዳ ደግሞ ስልጣን (power) ነው። “Bourdieu” (1984) የተባለው ፈረንሳዊ ምሁር የመከፋፈልን መርሆች (Principles of division) እና የመጨረሻ ዓላማ እንዲህ ገልፆታል፡-  

“Principles of division, inextricably logical and sociological, function within and for the purposes of the struggle between social groups; in producing concepts, they produce groups, the very groups which produce the principles and the groups against which they are produced. What is at stake in the struggles about the meaning of the social world is power over the classificatory schemes and systems which are the basis of the representations of the groups and therefore of their mobilization and demobilization: …which modifies the schemes of perception, shows something else, other properties, previously unnoticed or relegated to the background (such as common interests hitherto masked by ethnic or national differences); a separative power, a distinction, diacrisis, discretio, drawing discrete units out of indivisible continuity, difference out of the undifferentiated” Distinction. A social critique of the judgement of taste, Harvard University Press, Cambridge, Mass

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ ከዚህ ቀድም በማህብረሰቡ ዘንድ ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን “ልዩነቶች” አጉልቶ በማውጣት ሕዝብን የመከፋፈሉ ፋይዳ የፖለቲካ ስልጣንን መቆጣጠር ነው። በተለይ የዘር/ብሔር አፓርታይድ የፖለቲካ ስልጣንን የሚቆጣጠረው አብላጫ ድምፅ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል በመከፋፈል ሲሆን ዓላማውም የአንድን ዘር/ብሔር የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ይህ የአንድን ዘር/ብሔር የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጠጥ የተቋቋመ ፖለቲካዊ ስርዓት የብዙሃኑን እኩልነት የሚገድብ ስለሆነ ጨቋኝ ስርዓት መሆኑ እርግጥ ነው። እንዲህ ያለ ጨቋኝ ስርዓት ደግሞ እንቅስቃሴው ሁሉ በፍርሃት (fear) የሚመራ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ እኩልነት (equality) የእያንዳንዱ ሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው።

በከላይ እንደተገለፀው፣ “እኩልነት” የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ሲሆን “ፍርሃት” ደግሞ የጨቋኝ ስርዓት ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ለምሳሌ፣ ፈረንሳዊው ምሁር “Montesquieu” “እኩልነት” (equality) የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደሆነ እና ራስን ከሌሎች አብልጦ መውደድ ግን ጤናማ አለመሆኑን እንዲህ ሲል ይገልፃልገ፡- -“[The] natural love of equality includes love of others as well as love of self, and egoism, loving one’s self at the expense of others, is an unnatural and perverted condition.” ከዚህ በተጨማሪ፣ “Montesquieu” “ፍርሃት” (fear) የጨቋኞች የተግባር መርህና መመሪያ ነው ይለናል፡-

“These moving and guiding principles— equality and fear —are principles insofar as they rule both the actions of the government and the actions of the governed… Fear in a tyranny is not only the subjects’ fear of the tyrant, but the tyrant’s fear of his subjects as well.” An Essay(pdf) in Understanding the Nature of Totalitarianism

“Why Men Rebel” በተሰኘው መፅሀፉ የሚታወቀው “Ted Gurr” የአንድ ሀገር ዜጎች ወደ ፖለቲካዊ አመፅ፤ ሁከት፥ ብጥብጥና ነውጥ ውስጥ የሚገቡበትን ምክንያት “relative deprivation” በማለት ይገልፀዋል። እንደ እሱ አገላለፅ፡- “relative deprivation is the discrepancy between what people think they deserve, and what they actually think they can get.” በዚህ መሰረት፣ ዜጎች ማግኘት ይገባናል ብለው በሚያስቡት እና በተግባር እናገኛለን ብለው በሚያስቡት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ በሄደ ቁጥር አመፅና አለመረጋጋት የመከሰቱ እድል በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል።

ጨቋኝ ስርዓት ደግሞ አመፅና ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር በአመፁ መሪዎችና ደጋፊዎች ላይ የሚወስደው የኃይል እርምጃ ከከዚህ ቀደሙ የበለጠ ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት ጨቋኞች ከቀድሞ የበለጠ የኃይል እርምጃ በወሰዱ ቁጥር በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎቻቸው ላይ የላቀ ፍርሃትና ሽብር በመፍጠር የፖለቲካ እንቅስቃሴውን በኃይል መግታት ወይም መቀነስ ይቻላል በሚል መርህ ስለሚመሩ ነው። ነገር ግን፣ ከበፊቱ የበለጠ አስፈሪና አሸባሪ ተግባር በፈፀሙ ቁጥር የአመፅና ተቃውሞ እንቅስቃሴ ይበልጥ እየተጠናከረና እየተስፋፋ ይሄዳል። ማህብረሰቡም ጨቋኞችን እየተቃወመ፣ ስርዓቱ ተቀባይነት እያጣና አመፅና ተቃውሞው እየተጠናከረ ይሄዳል።
አንድ ማህብረሰብ በደልና ጭቆና እየበዛበት በሄደ ቁጥር እኩልነትና ነፃነቱን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ትግልና የሚከፍለው መስዕዋትነት እየጨመረ ይሄዳል። ጨቋኝ ስርዓት ደግሞ አዲስ አመፅና ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ከቀድሞ የበለጠ ኃይልና ጉልበት ተጠቅሞ የበለጠ ፍርሃትና ሽብር ለመፍጠር ጥረት ያደርጋል። የሕዝብ ንቅናቄ በኃይልና በጉልበት ለማጥፋት የሚጥረው ጨቋኝ ስርዓት በሂደት ራሱን የሚያጠፋ አዲስ ኃይል ይፈጥራል። “Ted Gurr” ይሄንን “….exclusive reliance on force eventually rises up the forces that destroy it” በማለት ይገልፀዋል።

በአጠቃላይ፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የነጮች አፓርታይድ የጠፋው በዚህ ኃይል አማካኝነት ነው። በተመሣሣይ፣ በእስራኤል “የአይሁዶች አፓርታይድ” በዓለም ላይ ሽብርተኝነትን እየፈለፈለ ያለው በዚህ ምክንያት ነው። በኢትዮጲያ ያለው የብሔር.አፓርታይድ ከዚህ አንፃር የት ደረጃ ላይ እንዳለ በሚቀጥለው ክፍል እንመለስበታለን።

ወደ ትግራይ ሰዎች…

‘በደሜ በላቤ ደማቅ ታሪክ ፀፍኩ’ ባዩ ህ.ወ.ሃ.ት ለመንገዴ መቅናት ምክንያቱ የትግራይ ህዝብ አጋርነት ነው ይላል፡፡ ይህ ግማሽ እውነት ነው፡፡በህወሃት ጥላስር ይታገሉ የነበሩት ትግሬዎች ብቻ አልነበሩም፡፡የቀድሞው የህወሃት ታጋይ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እንደሚናገሩት ስሙ አይነሳም እንጅ ከህወሃት መስራቾች አንዱ ጎንደሬ አማራ ነው፤ሰውየው በአሁኑ ወቅት በሽተኛ እና ችግረኛ ሆኖ አንዳንዴ ቤታቸው እየጠሩ እንደሚያስታምሙትና እንደሚያሳክሙት በአንድ ወቅት መስክረው ነበር፡፡በቅርቡ እንደሰማሁት ይህ ሰው በቂ ህክምና እንኳ ሳያገኝ ህይወቱ እንዳለፈ አንብቤያለሁ፡፡

ከደርግ ግፈኛነት የተነሳ  ህ.ወ.ሃ.ት የሚለውን ስም እንደከልካይ ሳይቆጥር ትግሬ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም የህወሃት አባል ሆኖ ደርግን ተፋልሞ ነበር፡፡ህ.ወ.ሃ.ቶች ግን ይህን ማንሳት አይፈልጉም፡፡ከዚህ ይልቅ መላው ኢትዮጵያዊ ከደርግ ተፋልሞ ነፃነቱን ላቀዳጀው የትግራይ ህዝብ ባለ እዳ እንደሆነ፣የትግራይን ህዝብ ቤዛነት እና ጀግንነት በአንደበታቸውም በድርጊታቸውምያስተጋባሉ፡፡ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት “ኢንዶውመንት” በሚል የዳቦስም ትግራይን የፋብሪካ መክተቻ ማድረጉን ተያያዙት፡፡ ‘ምነው ይህ በረከት ለሌላው የኢትዮጵያ ምድር ቢደርስ?’ የሚል ከተገኘ መልሱ ‘የትግራይ ህዝብ በጦርነት የተጎዳ ጀግና ህዝብ ስለሆነ ይህ አይበዛበትም፤ተራ ቅናታችሁን ትታችሁ የትግራይን ልማት ሬት ሬት እያላችሁም ትቀበሉታላችሁ’ የሚል ነበር፡፡ይህን የሚሉት ስለ “እውቀት ጢቅነታቸው” በጀሌ ካድሬዎቻቸው ማህሌት የሚቆምላቸው አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ ጉድ የተባለ “ጥልቅ እውቀት” ጀግንነት በዘር የሚተላለፍ ቡራኬ አድርጎ ለማቅረብ የማያፍር ነው፡፡ እርሳቸው የወጡበትን ዘውግ ልዩ የሆነ የጀግንነት ቅመም እንዳለው ከአንድም ሁለት ሶስቴ በአፋቸው የተናገሩት አቶ መለስ በተግባራቸው ያደረጉት በአፋቸው ካወሩት እጅግ ዘለግ ያለ ነው፡፡

የኢፈርት እና ደጀና “ኢንዶውመንቶች” ነገር..!

አቶ መለስ የሚመሩትን መንግስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የሲቪል ስልጣን ለወንዛቸው ልጆች ካደሉ በኋላ ለወጡበት ዘውግ ይገባል ያሉትን ሁሉ ከማድረግ እጃቸውን አልሰበሰቡም፡፡ኢፈርት የተባለውን አደናጋሪ እና ሚስጥራዊ የንግድ ኩባንያዎች ባህር አቋቁመው ሚስታቸውን (ያለ አቅሟም ቢሆን)ይህን የፋብሪካ ባህር እንድታስተዳድር ሰየሟት፡፡ወ/ሮ አዜብ ወደ ኢፈርት ቁንጮነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት አዛውንቱ ስብሃት ነጋና ሌሎች ትግራዊያን ኢፈርትን ዘውረዋል፡፡የኢፈርት ፋብሪካዎች ወደ ሰማኒያ የሚደርሱ ሲሆኑ አንዱም “በስህተት” እንኳን ከትግራይ ውጭ አልተገነባም፤ከትግራይ ባልሆነ ኢትዮጵያዊም ተዳድሮ አያውቅም፡፡በአንፃሩ ፋብሪካዎቹ የሚያመርቱት ሸቀጥ በመላ ሃገሪቱ ይራገፋል፣ወደባህር ማዶም ይሻገራል፡፡የፋብሪካዎቹ በአንድ ቦታ መከማቸት ከትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ፋብሪካዎቹ ‘በስኩየር ኪሎሜትር ስንት?’ ተብለው ሊቆጠሩ ምንም ያልቀራቸው ያስመስላል፡፡ የኢፈርት በትግራይ ብቻ መከተም፣በትግራዊ አስተዳዳሪዎች ብቻ መተዳደር ጉዳይ በጣም እያነጋገረ ባለበት ሁኔታ ደግሞ ሌላ ወንድም “ኢንዶውመንት” በእዛው ክልል በቅርቡ ተመስርቷል፡፡የዚህ ምክንያቱ የኢፈርት ኩባንያዎች መበራከት አለቅጥ ሰፍቶ  ለአስተዳደር  አመች ወደ አለመሆን ግዝፈት በመድረሱ ሌላ ኢንዶውመንት እንዳስፈለገ ወ/ሮአዜብ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡የኢፈርት ግዝፈት ሊያመጣ የሚችለውን አስተዳደራዊ ውስብስቦሽ ለመታደግ “ደጀና” የተባለ ትግራይ ከታሚ ኢንዶውመንት በዚህ ከሶስት አመት አካባቢ በፊት ተቋቁሞ እነ አበርገሌን አይነት ኩባንያዎች አቅፎ ልማቱን እያሳለጠ እንደሆነ ሰርክ ይወራል፡፡ አዲሱ ደጀና ኢንዶውመንት ከአስር በላይ ኩባንያዎች በስሩ አቅፎ ታላቁን ኢፈርትን ለመፎካከር ድክ ድክ እያለ ነው፡፡

እነዚህ ኢንዶውመንቶች ከትርጉማቸው ጀምሮ ባለቤትነታቸው፣ኦዲት ያለመደረጋቸው ጉዳይ፣ በአንድ ክልል(በትግራይ) ብቻ እንዲከትሙ ያደረጋቸው ምስጢር ወዘተ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የሚያስቆጣ ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል፡፡የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት እነዚህ ፋብሪካዎች ኦዲት የማይደረጉበት፣የኦዲት ሪፖርታቸውም የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ለሆነው ፓርላማ የማይቀርብበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ተገቢ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ለዚህ የአቶ መለስ መልስ ‘እነሱ እኮ ኢንዶውመንቶች ናቸው ግልፅ ሪፖርት ማቅረብም አይጠበቅብንም’ የሚል የተለመደ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡ አቶ ተመስንም የዋዛ አይደሉምና “ኢንዶውመንት” የሚለውን ቃል ትርጉም በአማርኛ ሆነ በኦሮምኛ በአፋርኛ ሆነ በትግርኛ በፈለጉት ቋንቋ ተርጉመው እንደዚህ አይነኬ የመሆኑን ሚስጥር  ያስረዱን” ሲሉ ቢወተውቱም አቶ መለስ በማስቀየስ እንጅ መልስ በመመለስ ስማይታሙ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡የሆነው ሆኖ “ኢንዶውመንት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአብዛኛው የኮርፖሬት ፈንዶችን ለመግለፅ የሚያገለግል ፅንሰሃሳብ ነው፡፡ከሌሎች የንግድ ማህበሮች በተለየ ከኢንዶውመንት ኮርፖሬት ፈንዶች የሚገኝ ትርፍ ተመልሶ ለልማት የሚዉል  እንጅ  ለባለቤቶች የሚከፋፈል አይደለም፡፡ የአቶ መለስ “ኢፈርት እኮ ኢንዶውመንት ነው” የሚለው መልስም ትርፉ መልሶ ለሌላ ልማት የሚውል ነው ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ በግልፅ ኦዲት ካለመደረግ ጋር የሚያገናኘው ነገር በበኩሌ አይገባኝም፡፡

የኢንዶውመንቶቹን ባለቤትነት በተመለከተ የኢፈርት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአንድ ወቅት  ‘ኢፈርት በተዘዋዋሪ የትግራይ ህዝብ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ:: ‘በቀጥታስ ባለቤቱ የማን ነው?’ የሚለው እስከዛሬ ሚስጥር እንደሆነ አለ፡፡ ለጊዜው በግልፅ ወደ ተነገረን ተዘዋዋሪው ባለቤት የትግራይ ህዝብ እና የኢፈርት መስተጋብር ስንሄድ ኢፈርትን የሚያክል የፋብሪካ ባህር በትግራይ ብቻ እንዲንጣለል ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ማለፍ አይቻልም፡፡ ህወሃት እንደሚለው ኢፈርት እና ደጀና በትግራይ የከተሙት  የትግራይ ህዝብ ወኪል የሆነው ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያፈራውን ገንዘብ ለቆመለት ህዝብ ልማት ማዋል ስላለበት ነው፡፡እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ አንደኛው ለህዝብ ነፃነት የታገለው ህወሃት ምን ሰርቶ ይህን ያህል ገንዘብ አፈሰ? ጠመንጃ ተሸክሞ መባተልን የሚፈልገው የትጥቅ ትግል ሲራራ ንግድ አይደለምና ጥሪት አስቋጥሮ የኩባንያ ባህር ማቋቋም ያስቻለውስ እንዴት ነው? ገንዘቡ በትጥቅ ትግል ወቅት የተገኘነው ከተባለስ የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው በትግራይ ብቻ አልነበረምና ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ኢፈርት ያሉ ባለግዙፍ ኢንዶውመንቶች ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

የትግሬነት እና ህወሃትነት ልዩነት ትርክት ሳንካዎች

በሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንደ የትግራይ ህዝብ እና የህወሃት መስተጋብር ያለ ግራ አጋቢ፣ ብዙ እንደማነጋገሩ ፈር የያዘ መልስ ያልተገኘለት፣ለትንታኔ አስቸጋሪ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ህወሃት የኢህአዴግ ልብ ሆኖ ሃገሪቱን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሲዘውር ከፊት የሚያሰልፋቸው ዋና ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች  ከትግራይ የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ነገር ህወሃት ለሁለት ጥቅም ያውለዋል፡፡ አንደኛው የወንዙን ልጆች በወሳኝ ቦታዎች ኮልኩሎ ከውልደቱ ጀምሮ የተጣባውን የዘረኝነት ዝንባሌ ያፀናበታል፡፡ በሁለተኛ እና በዋነኝነት የትግራይን ህዝብ ደጀን ለማድረግ ልቡን ማግኛ መንገድ አድርጎ ያየዋል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለተመለከተ ለህወሃት ሁለቱም የተሳኩለት ይመስላል፡፡ለዚህ ማሳያው የህወሃት የሃረግ መዘዛ ፖለቲካ ከእርሱ አልፎ በመላ ሃገሪቱ ማርበቡ ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ የመተባበርም ሆነ ያለመተባበር፣ የመተማመንም ሆነ የመጠራጠር ምንጩ ሃረግ መማዘዝ ሆኗል፡፡ይህ በአንድ እናት ሃገር ልጆች መሃከል ከፍተኛ ያለመተማመን አምጥቷል፡፡ ሌላው ህዝብ እርስ በርሱ በጎሪጥ የሚተያይ ተጠራጣሪ ሲሆን የትግራይን ህዝብ ደግሞ የአፋኙ የህወሃት ጠበቃ አድርጎ የመፍራት አዝማሚያ ይታያል፡፡ይሄኔ ከላይ የተጠቀሰው የህወሃት እራሱን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እና ያው አድሮጎ የማቅረቡ አላማ ይሰምራል፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ጋር አንድ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ምንጩ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡በላይኛው የውትድርና ማዕረግ  ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከትግራይ የወጡ ሰዎች መያዙ፤ በሲቪሉ ክንፍም ቢሆን ለረዥም ጊዜ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትነት፣የሃገር ደህንነት ኤጀንሲ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣በስመ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመካሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን ማሾሩ፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር ከዝቅተኛ  እስከ ከፍተኛ የሃፊነት ቦታ የትግራይ ተወላጆች መበራከት፣ይህ ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሲወገዝ አለመታየት ለተመልካች ትግሬን እና ህ.ወ.ሃ.ትን አንድና ያው አድርጎ ያይ ዘንድ ይገፋዋል፡፡አሁን ሃገራችን በምትመራበት የዘውግ ፌደራሊዝም ሁኔታ ህ.ወ.ሃ.ት ድርና ማግ ሆኖ መምራት የሚችለው  የትግራይ ክልልን ብቻ መሆን ሲገባው የህ.ወ.ሃ.ት ሃያል ህልውና በአዲስ አበባም መስተዳድር ቢሮዎችም ሆነ አዲስ አበባ በከተመው የፌደራል መንግስትም ሚታይ የመሆኑ አደገኛ አካሄድ ለህወሃት መራሹ ኢህዴግ የታየው አይመስልም፡፡ባለሃብትነቱም ቢሆን ለሁሉም ባይሆንም ለትግራዊያኑ ብዙ ጊዜ የማይወስድ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡

ከትግራይ የሆኑ ዜጎች በስልጣን እና በሃብት ማማ ላይ በርከት ብሎ መታየት በተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚታይበትን መንገድ በሰፊው ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡መጠኑ ቢለያይም ትግሬ ሁሉ ህወሃትን ይደግፋል፤ትግሬ ሆኖ ከልቡ የህወሃትን ሁለንተናዊ የበላይነት ማብቃት የሚፈልግ ማግኘት አይቻልም የሚለው ሙግት ነው፡፡በዚህኛው ወገን ያሉ አሳቢዎች ክርክራቸውን የሚያጠናክሩት እስከዛሬ በትግራይ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶ አለማወቁን ነው፡፡ ተከራካሪዎቹ በተጨማሪ የሚያነሱት ነጥብ ከትግራይ የሚነሱ የህወሃት ተቃዋሚዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች እንደ ኢፈርት እና የወልቃይት ጥያቄን የተመለከተ ከህወሃት የተለያ አቋም ለማንፀባረቅ ይቸገራሉ የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የቆሙ ተከራካሪዎች ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ ተለያይተው መታየት እንዳለባቸው አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡እነዚህኞቹ ለክርክራቸው ማጥበቂያ የሚያነሱት ሃሳብ የትግራይ ህዝብም የህወሃት ብልሹ አሰራር ሰለባ መሆን፣ሌላ አማራጭ ሃሳብ መነፈግ እና በአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ መጠለፍ፣የአብዛኛውን የትግራይ ህዝብ የድህነት ኑሮ ወዘተ ነው፡፡

የትግራይን ህዝብ እና የህወሃትን አንድነት ልዩነት በተመለከተ የሚነሱት እነዚህ ጎራዎች በየፊናቸው ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎችን አስከትለው ሲያሟግቱ የኖሩ ቢሆኑም ሁለተኛው ማለትም የትግራይን ህዝብ እና ህወሃትን ለይተን እንይ የሚለው ክርክር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡በበኩሌ የዚህ ክርክር ደጋፊዎች መመናመን አብሮነታችንን የሚፈትን፣ የትግራይን ህዝብ ስጋት ላይ የሚጥል አሳሳቢ ነገር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ጥፋት የትግራይ ህዝብም አድርጎ የማየቱ ነገር  በተቻለ ፍጥነት መቀየር ያለበት ነገር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛውን ድርሻ መውሰድ ያለበት ደግሞ ራሱ የትግራይ ህዝብ ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ ምን ይጠበቃል?

ህወሃት እርሱ በስልጣን ሰገነት ላይ ከታጣ ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ እሳት ሆኖ እንደሚበላው ያስፈራራል፡፡  ቀላል የማይባለው ትግራዊም ይህን ተቀብሎ የህወሃት ወንበር የተነቃነቀ በመሰለ ቁጥር ስጋት ይወርሰዋል፡፡ይህን የአብዛኛው ትግራዊ ስጋት የሚረዳው ሌላው የሃገራችን ህዝብ ትግራዊያንን የግፈኛው ህወሃት ወንበር ጠበቃ አድርጎ ያስብና የህወሃት የግፉ ማህበርተኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ይህ ህ.ወ.ሃ.ት ታጥቆ የሰራበት እና ስኬታማ የሆነ የሚመስልበት ፈለግ ነው፡፡ ይህ ነገር ግን መቆም አለበት፡፡ ነገሩን ለመቀየር ደግሞ የትግራይ ህዝብ ማሰብ ያለበት የዚህን ሁሉ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ መነሻው የህወሃት ‘ከሌለሁ የላችሁም’ ስብከት ነው፡፡ ይህንን መመርመሩም ደግ ነው፡፡ የምርምሩ መነሻ ‘ህወሃት ሳይኖር ትግሬ አልነበረም ወይ?’ ብሎ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ሲሆን መልሱ ትግሬ ከህወሃት በፊት ነበረ ነው፡፡ ትግሬ ከህወሃት በፊት ከነበረ ዛሬ እኔ ከሌለሁ የላችሁም የሚለው የህወሃት ዜማ እንዴት መጣ የሚለውን ማስከተልም ተገቢ ነው፡፡የዚህ ዜማ መነሻው ብልጣብልጡ ህወሃት በመላው የትግራይ ህዝብ ስም ግን ለጥቂት ትግሬዎች የሰራው/የሚሰራው አድሎ እና ዘረኝነት ነው፡፡እንደ አሸን ፈልተው ትግራይ የከተሙ የኢፈርት እና ደጀና ኢንዲውመንት ፋብሪካዎች፣በሁሉ ቦታ ብቅ የሚሉ የትግሬ ሹማምንት፣የትግሬ ብቻ የጦር ጀኔራሎች፣ቱጃር ለመሆን የሳምንት እድሜ የሚበዛባቸው ትግራዊ ባለሃብቶች መበራከት ወደ ትግራዊያን  ያጋደለው የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል ማሳያዎች ናቸው፡፡ባልበላው እዳ ላለመጠየቅ የሚወድ ትግሬ ሁሉ ይህን አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን ማውገዝም አለበት፡፡

ወደዚህ ልቦና ለመምጣት ሰፊው የትግራይ ህዝብ ራሱን በሌላው ኢትዮጵያዊ ጫማ ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ ‘እኔ ትግሬ ባልሆን ኖሮ ይህን ጉዳይ እንዴት አየው ነበር’ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር መለስ እና ደቀመዛሙርቶቻቸው ትግሬነታቸው ቀርቶ አፋር ቢሆኑና ኢፈርትን እና ደጀናን የመሰሉ የልማት ተቋማት አፋር  ብቻ እንዲከቱ አድርገው፤ በአፋር አለቆች እንዲዘወሩ ቢያደርጉ፤ ይህ ሳያንስ ደግሞ የአፋር ህዝብ ለእንዲህ ያለው አስተዳደር እድሜ ሲለምን ባየው የሚሰማኝ ምንድን ነው ማለት ያስፈልጋል፡፡ከስልጣን የማይወርዱ የአፋር የመንደር ልጆች የራሳቸው ስልጣን ላይ ሙጥኝ ማለት ሳያንስ የአፋር ባለሃብቶችን የመፍጠር ፕሮጀክት ቀርፀው ሌላውን ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ ባይትዋር ቢያደርጉ ምን ይሰማኝ ነበር? የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ተብለው በፌደራል ወንበር የተቀመጡት ሰውየ የትግራይን ክልል የኢንዱስትሪ ዞን ለማድረግ እቅድ አውጥተው ነበር ተብሎ ከገዛ ባለቤታቸው ሲነገር መስማት ትግራዊ ላልሆነው ሰፊ ህዝብ ደስ የሚያሰኝ ትርጉም አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ አሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ስሜት ለመረዳት ይበጃል፡፡

በግሌ ከትግራዊ ወዳጆቼ እና ጓደኞቼ ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ በአብዛኛው የሚገጥመኝ ክርክር ‘ኢፈርት ትግራይ መከተሙ ለሰፊው ህዝብ ምንም የፈጠረው ነገር የለም፡፡ የፋብሪካዎቹ ባለቤት የህወሃት ባለስልጣኖች እና ዘመድ አዝማዶች ናቸው’ የሚል ነው፡፡ ይህም ግማሽ እውነት ነው፡፡ የእነዚህ ኢንዶውመንቶች ተጠራርቶ ትግራይ ላይ መከተም ለአካባቢው ሰዎች ቢያንስ የስራ እድል መፍጠሩ በሰፊው ትግራዊ መካድ የለበትም፡፡በቀጥታ የስራዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ለከተሞች ማደግ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የፋብሪካዎቹ መኖር የመግዛት ሃይል ያለው ተከፋይ ሰራተኛ በከተሞቹ እንዲኖር በማድረግ በቀጥታ በፋብሪካዎቹ ለመቀጠር ላልቻለው ህዝብ የንግድ እድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ሁሉ እድል ፋብሪካ በገፍ ላልተተከለለት ሌላው ኢትዮጵያዊ ያልተገኘ ነውና የእድገት ሁኔታ መዛባት ማምጣቱ ሃቅ ነው፡፡ ይህን ክዶ መነሳት የመግባቢያን ሰዓት ከማራቅ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

ሌላው ከትግራይ ወገኖቻችን የሚገጥመኝ ክርክር ‘የህወሃት ብልሹ አሰራር የትግራይን ህዝብም መድረሻ ያሳጣ ነገር ነው’ የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡የትግራይ ለፍቶ አዳሪ ድሃ ህዝብ በመዋጮ ብዛት ፍዳውን እንደሚያይ ከቦታው ከመጡ ሁሉ የሚነገር ነው፡፡ የሙስናው ነገር፣ሌላ ድምፅ እንዳይሰማ የማድረጉ አፈና ሁሉ በትግራይም ያለ ነው፡፡ ግር የሚያሰኘው ነገር ግን  የትግራይ ህዝብ አለበት የሚባለውን ግፍ በግልፅ ሲቃወም አይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ለዚህ አፈናው አያሰናዝርም የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ በበኩሌ ይህ አያሳምነኝም:: ምክንያቱም ሌላው ኢትዮጵያዊም የደረሰበትን ብልሹ አሰራር የሚያወግዘው መንግስት ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረለት ሳይሆን የደረሰበት ግፍ ብዛት አፈናውን ችላ ብሎ ድምፁን እንዲያሰማ ስለገፋው ነው፡፡ ስለዚህ የተበደለ ሁሉ በዳዮች ቀንበራቸውን እንዲያለዝቡ መጠየቁ ተፈፅሯዊ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ድምፁን አጥፍቶ አስተዳደራዊ በደሉን እንዲጋት ያደረገው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን መረጃ ከውስጥ አወቆች ለመስማት ጉጉት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ከትግራይ የሆኑ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ በደንብ ቢያስረዱን የትግራይ ህዝብ ያለበትን ችግር ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡

እንደ ህወሃት አገላለፅ በትግራይ የከተሙት  ኢንዶውመንት ተብየዎቹ አላማ ባመጡት ትርፍ ሌላ የልማት ተቋም በትግራይ መመስረት ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ  ልማት ልማትን እየወለደ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ለዚህ ምስክሩ በትግራይ የሚዋለዱት የፋብሪካዎች ብዛት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እንኳን በ850 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የጠርሙስ እና የብርጭቆ ፋብሪካ በእዛው ትግራይ ሊከትም እንደሆነ ትግራዊያን መኳንንት በቴሌቭዥን መስኮት እያወሩ ነበር፡፡ ከሳምት በፊት ደግሞ የመስፍን ኢንጅነሪንግ አልበቃ ብሎ  የምስራቅ አፍሪካን ገበያ ታሳቢ ያደረገ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዛው በትግራይ ስራ ሊጀምር እንደሆን ሰማን፡፡ይህን እያየን “ላለው ይጨመርለታል” ብለን እንድናልፍ ከታሰበ የማይሆን ነው፡፡

በአንፃሩ በሌላው የሃገራችን ክልል  የከባድ ፋብሪካዎች ተከላ ወሬ እንደ ሃምሌ ፀሃይ ተናፍቆም አይገኝ፡፡ ይህን እኔ ትግራዊ ሳልሆን ብሰማው ኖሮ ስሜቴ ዛሬ ትግሬ ሆኘ እንደሚሰማኝ ይሆን ነበር ወይ? ይህን የሚሰራው ህወሃት እድሜ ማጠርስ ያሳስበኝ ነበር ወይ?ይህን ጉልህ የተዛባ አሰራር እያዩ ዝም ማለትስ ይቻላል ወይ? የአንድ ሃገር ሰዎች ሆነን ሳለ ይህ ሲሳይ እኛጋ ያልደረሰው ለምንድን ነው ብሎ መሞገት ወንድም የሆነውን የትግራይ ህዝብ መጥላት ነው ወይ?  ብሎ መጠየቅ ደግ ነው፡፡ ህወሃቶችስ ይህን የፋብሪካ መንደር በትግራይ ብቻ እንዲከትም ያደረጉት ሊጠቅሙን ነው ሊጠቀሙብን? በዚህ ሁኔታ የምናገኘው ጥቅም ምን ያህል ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል፤ ብሎ መመርመር ከሃዲነት ሳይሆን ብልህነት ነው፡፡

የህወሃት ወንበር ሲነቀነቅ የትግራይን ህዝብ የሚያሳስበውን ያህል የብ.አ.ዴ.ን ህልውና የአማራን ህዝብ፣የኦ.ህ.ዴ.ድ በስልጣን ላይ መሰንበት የኦሮሞን ህዝብ፣የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በስልጣን ላይ መታየት የደቡብ ህዝብን፣የሶ.ህ.ዴ.ፓ እድሜ የሶማሌን ህዝብ ወዘተ ያሳስባል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡መልሱ ተቃራኒ ነው፡፡አብዛኛውን ትግራዊ የህወሃት ህልውና ክፉኛ ሲያሳስበው ሌላው ኢትዮጵያዊ እነዚህን ቆምንልህ የሚሉትን የገዥው ፓርቲ  አባል/አጋር  ፓርቲዎች እንደ የባርነት ወኪል አድርጎ ያያል፡፡ የእድሜያቸው ማጠር ከሚያስከፋው የሚያስደስተው በብዙ እጥፍ ይበዛል፡፡ለዚህ ከሰሞኑ በሃገራች ከተሞች ወከለናችኋል የሚሉዋቸውን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባል ፓርቲዎች ለማውገዝ ጎዳና የወጣው ህዝብ ብዛት ማሳያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብም እንደሌሎች ወንድሞቹ ቆምኩልህ እያለ ሌት ተቀን የሚሰብክ የሚያስፈራራውን ህወሃት ህፀፆች ለማውገዝ ማመንታት የለበትም፡፡ ‘ከሌሉ የለሁም’ የሚለውን አጓጉል አስተሳሰብ ትቶ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኖ ህወሃትን ታገስ ተመለስ ፣ካልሆነ ለሚችል ልቀቅ መለት አለበት፡፡ ይህንንም በአደባባይ ማሳየት አለበት፡፡ በተጨባጭ የሚታየውግን ሌላ ነው፡፡

ከላይ በትቂቱ ለማሳየት የተሞከረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል አንስቶ በምክንያት የሚሞግት ሰው ከአብዛኛው ትግራዊያን ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ‘እንዲህ የሚያስበው ትግሬን ስሚጠላ ነው’ የሚል ሲሆን ያጋጥማል፡፡ ይሄ ደመነፍሳዊነቱ የበዛ፣ ለመሞገት የሚያስችል የእውነት ስንቅ የማጣት የሚያመጣው የሽሽት መልስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሬ ወገኖቹን ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ጀማሪ፣እጅግ ሰው አክባሪ፣እንግዳ ተቀባይ ነውና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ህዝብ የሚወድበት እንጅ ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምክንያት የለውም፡፡ልክ ያልመሰለውን ነገር ሲጠይቅ ደግሞ ‘ይህን ያልከው እኛ ትግሬ ስለሆን’ ነው ማለት የጥላቻን መንገድ መጥረግ እንጅ ሌላ ጥቅም የለውም፡፡አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርቡ ‘የምታዩትን አድሎ እንዳላያችሁ እለፉ፤ያኔ እንደምትወዱን እናውቃለን’ ማለት አብሮነትን የሚፈትን አስቸጋሪ አቋም ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ አንፃር ይህ ሁሉ ሲጠበቅ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለትግራዊ ወንድሞቹ የሚያቀርበውን ጥያቄ የሚሰነዝረው ረጋ ብሎ፣ ጥላቻን አርቆ መሆን አለበት፡፡እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት የሆነውን መዛባት ሁሉ ያመጣው ህወሃት ከትግራይ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ተመካክሮ አይደለም፡፡ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ወደትግራይ የሚተመው ፋብሪካ ሁሉ ሲተከል ሰፊው የትግራይ ህዝብም እንደ እኛው በቴሌቭዥን ይሰማል እንጅ የሚያውቀው የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ‘ሌላውን ረስታችሁ ለእኔ ይህን አድርጉልኝ’ ብሎ አዞ ያስደረገው ነገርም አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከትግራዊ ወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር ይህን ሁሉ አስበን መሆን አለበት፡፡ ‘ህወሃት የትግራይን ህዝብ አይወክልም’ ከሚለው ሾላ በድፍን የሆነ ዘይቤ ወጥተን ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ነባራዊ ሃቆች ላይ ተመስርተን አፍረጥርጠን መነጋገር ያለብን ቢሆንም ንግግራችን ‘እኛ እና እነሱ’ የሚል ግድግዳ የተገነባበት መሆን የለበትም፡፡ ከዛ ይልቅ የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን እያሰብን፤ እንደቤተሰብ ውይይት ፍቅር እና መተሳሰብ ባልተለየው መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሁን እያነጋገረን ያለው ጉዳይ ረዥም ዘመን ከተጋራነው ወንድማማችነት የሚገዝፍ አይደለም፡፡ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ከስሜታዊነት የራቀ መሆን አለበት፡፡ ከስሜታችን ምክንያታችን መብለጥ አለበት፡፡ ይህ ካሆነ ዛሬ እንደቀልድ ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር  ነገ የምንፀፀትመበትን ጥፋት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ስለዚህ ጉዟችን ሁሉ ማስተዋል የተሞላበት መሆን አለበት፡፡ በፍቅር ከመነጋገር  እንጅ ከጥላቻ እና ከመጠፋፋት ትርፍ ያገኘ ህዝብ የለምና ንግግራችን ሁሉ ፍቅርን፣እርጋታን እና ምክንያታዊነትን የተሞላ መሆን አለበት፡፡ይህ ካልሆነ ህወሃትን እያገዝነው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡


For your comments and suggestion you can reach her via (e-mail meskiduye99@gmail.com )

“የኔታ መስፍን ምን አጠፉ?” (በመስከረም አበራ)

ሃገራችን ኢትዮጵያ መማር ብቻውን “ንወር ክበር!” የሚያስብልባት ምድር ነች፡፡ ተምሮ ለወገኑ ምን ሰራ? ለሃገሩ ምን አበረከተ? የሚሉት ወሳኝ ነገሮች ከክብሩ በፊት ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ነገሮች አይደሉም፡፡ ብዙሃኑ ምሁራን በበኩላቸው ትምህርታቸው ደሃ አደግነታቸውን የሚበቀሉበት ብርቱ በትር፣ የቅንጦት ህይወት የይለፍ የሚወስዱበት ሰልፍ ብቻ ይመስላቸዋልና ዲግሪ በደራረቡ ቁጥር ከትናንት በተሻለ ራሳቸውን ለማገልገል፣ ከሰው በልጦ ለመታየት ይታጠቃሉ፡፡ ትምህርታቸው ያልሰራውን ቁስ ከየፈረንጁ ሃገር ይሰበስባሉ፡፡ ቁሱን ይበልጥ ለማጋበስ ከግፈኛ መንግስት ጋር ማህበር ይጠጣሉ፡፡ ከደም አፍሳሽ ጋር ግንባር ይገጥማሉ፤ ከእናት ሃገር ሆድ ወጥተው የሷኑ ደካማ ጎን ይመታሉ፡፡

ከትናንት በስቲያ እግረኛ ወታደር የነበረ ኩሽሹን በከረባት ቀይሮ ባላዋቂ እጁ ሲያቦካው የኖረው ፖለቲካ እንደ ቂጣ ምጣዱ ላይ እንክትክት ሲልበት ‘ኑና ስራየ ልክ እንደ ነበረ ዱክትርናችሁን እየጠቀሳችሁ ከሙያ አንፃር አስረዱ ሲላቸው’ ሊያስረዱ ይሽቀዳደማሉ፡፡ በኢቢሲ አንድ ሁለት ቀን ካናዘዛቸው በኋላ አያያዛቸውን አይቶ፣ ፍልስፍናቸው እንደ ቅማል “እራስ ደህና” ማለት እንደሆነ አጥንቶ ለሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ያጫቸዋል፡፡ “የዶክተሮች ካቢኔ አቋቋምኩ” ብሎ ከመጠላቱ በላይ እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ለነሱ ክብር መስሎ ይታያቸዋልና ሹመቱ ሃሴታቸው፣ የሹመቱ ቱርፋት እርካታቸው ይሆናል፡፡

የመማር ዋና አላማው በስብ መጥገብ ከሆነ ዳርቻው ይህ ቢሆን አይስገርምም፡፡ በስብ ለመጥገብ ግን መማር ግድ አልነበረም፡፡ እንደውም ለቁስ ሰቀቀን ፍቱን መድሃኒቱ፣ የቀጥታ መንገዱ ተደራራቢ ዲግሪ የግድ የማይለው የመነገድ ማትረፉ ጎዳና ነው፡፡ መማር ግን ቁስ ከማንጋጋት፣ ሆድ ከመቀብተት ያለፈ ተልዕኮ ያለው ነገር ነው፡፡ መማር መንጋው ያላየውን ቀድሞ አይቶ ማሳየትን፣ ባልደላው ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛ ድሎት እንደማይኖር የመገንዘብ ራስ ወዳድነትን የመሰናበት ልዕልና፤ ለእውነት እና ለሃቅ ብቻ የመወገን እና ይሄው የሚያመጣውን ቱርፋትም ሆነ ችግር የመቀበል ልቅና ነው፡፡ ይህ ልቅና በተለይ በድሃ ሃገር እንደልብ የሚገኝ አዘቦታዊ ገጠመኝ ሳይሆን እንደ ማዕድን በመከራ ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ነገር ነው፡፡

ፕ/ሮ መስፍን ወ/ልደማርያም በግብር መማራቸውን ከሚመስሉ፣ ሁሉን ከሚመረምሩ፣ ሳይደክሙ ከሚጠይቁ፤ የቁስ ምኞት የራስ ድሎት እምብዛም ከማያስጨንቃቸው ብርቆች ወገን ናቸው፡፡ ሰውየው ከጉብዝና እስከ ሽምግልናቸው ወራት ሲፅፉ ሲሞግቱ የኖሩ የሃገር አድባር ናቸው፡፡ እውቀት ልምዳቸውን በወረቀት አስፍረው፣ በቃል ተናግረው አይጠግቡም፡፡ የተናገሩ የፃፉት ለብዙ የፖለቲካችን ህማማት መልስ አለው፡፡ ሆኖም የሚታያቸውን ለማየት፣ የሚሰማቸውን ለመረዳት አቅሙም ልምዱም የሚያጥረን ሰዎች ልንወርፋቸው እንጣደፋለን፤ የምናስበውን እንዲናገሩልን እንሻለንና ብዙ ጊዜ ባልሆኑት እንከሳቸዋለን፡፡ በበኩሌ ሰው ፍፁም ነው ብየ አላምንም፤ ይህን መጠበቅም ደግ አይመስለኝም፡፡ ሰው ናቸውና ፕ/ሮ መስፍንም ሊስቱ፣ ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ ወይም በእኛ ግንዛቤ ያጠፉ ሊመስለን ይችላል- ሁላችንም የግንዛቤያችን ነፀብራቅ ነንና! ይሄ ጤናማ ነው፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን ጥፋትን እና ልማትን የመመዘን እርጋታ፣ ቅሬታችንን የምንገልፅበት ሁኔታ፣በተለይ የተቃውሟችን ሁለመና ሌት ተቀን ከምናወራለትን ኢትዮጵያዊ ማንነት አንዱ የሆነውን ታላቅን የማክበር ጨዋነት ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ያስባለኝ በተደጋጋሚ ከፕ/ሮ መስፍን ጋር በማይጥም ሁኔታ የሚሟገተው የርዕዮት ሚዲያ ባልደረባ አቶ ታምራት ነገራ ከሰሞኑ ፕ/ር መስፍን የተናገሩትን አንስቶ ከሰውየው ጋር ያለውን ልዩነት የገለፀበት ድንፋታ ነው፡፡ ራሴም በአንድ ወቅት ከፕ/ሮ መስፍን ሃሳብ ጋር ባለመስማማት ተሟግቼ ነበርና ታምራት ነገራ ለምን የፕ/ሮ መስፍንን ሃሳብ ሞገተ የሚል አቋም የለኝም፡፡ ጥያቄየ እሳቸውን ሲሞግት እንደዚህ ጣራ አድርሶ በሚያፈርጥ ንዴት የሚበግነው ለምንድን ነው የሚል ነው፡፡በእውነት እና በእውቀት፣በደንብ በገባው ነገር ላይ ለሚሞግት ሰው ጥርስ በሚያፋጭ ብግነት ውስጥ መሆን ምን ይረዳዋል? በንዴት ፈረስ ላይ ሆኖ አያት የሚሆንን ትልቅ ሰው መዘርጠጥስ አስተዳደግን ከማስገመት፤ የራስን ኪሎ ከማቅለል ያለፈ ምን ረብ አለው? ንዴት እውቀት፣ስድብ ሙግት ሆኖ አያውቅም! ማወቅ ያረጋጋል እንጅ አያንተገትግም፤ስድብ እና ዝርጠጣ ያዋቂነት ምልክት አይደለም፡፡ ስድብ የመከነ አእምሮ ውላጅ እንጅ እንደ ታምራት ነገራ ሃሳብ አለኝ ብሎ ሚዲያ ላይ ከተሰየመ ሰው የሚጠበቅ “አበጀህ” የሚያስብል ነገር አይደለም፡፡ በተለይ ፕ/ሮ መስፍንን ከመሰለ ባለ ከባድ ሚዛን ምሁር ጋር ሲሟገቱ ሰውየው የተናገሩትን በደንብ መረዳት፣መረጋጋት፣ የሚናገሩትን ማወቅ፣ራስን መግዛት ተሻይ ነው፡፡ ካልሆነ ንግግር የሚያስገምተው ራስን ነው! ስለተደጋጋመ ዝም ብየ ማለፍ ስለከበደኝ የታምራትን ጉዳይ አነሳሁ እንጅ የፅሁፌ አላማ ስላልሆነ በዚህ ትቼ ፕ/ሮ መስፍን ሰሞኑን በሲያትል ተገኝተው በተናገሩት ጠቃሚ ንግግር ዙሪያ ወዳለኝ ሃሳብ ልለፍ፡፡

ስለ ጎሳ አጥራችን ገበና፤ የልዩነት አንድነት እንዴትነት

ፕ/ሮ መስፍን ያደረጉት ንግግር የሚጀምረው በሃገራችን ወቅታዊ ፖለቲካ ዋነኛ መዘውር የሆነው አግላይ የጎሳ ፖለቲካ የሃገራችንን የማህበረ-ፖለቲካዊ ታሪክ የማይወክል ልብ ወለድ ነው በማለት ነው፡፡ይህው ስሁት እሳቤ ስህተቱን የሚያባብሰው በጎሳ መሃል አንድነት እንጅ ልዩነት የለም ብሎ ሲደመድም፤የዚህ ተቃራኒ የአንድነት አቀንቃኖች ደግሞ በሚዘምሩለት አንድነት ውስጥ ልዩነትነትን የሚያስተናግዱበት ቦታ የሌለ ወይ የጠበበ መሆኑ ነው በሚል ግራ ቀኙን የሚገስፅ እና ልብ ላለው በዚህ መሃል ያለውን አዋጭ መንገድ የሚያሳይ ነው -የፕ/ሮ መስፍን ተግሳፅ አዘል ንግግር፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ማቆሚያ የሌለው የሽንሸና እና የማነስ ጉዞ እንደሆነም ጠቆም አድርገዋል፡፡መስማት የምንችል ብልሆች ከሆንን ይህ የፕ/ሮ መስፍን ንግግር ለፖለቲካችን ፍቱን ፈውስ የሚሆን መድሃኒት ያለው ነገር ነው፡፡

ነገሩን ከነባራዊው የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ለማመሳከር ያህል ቆየት ካለው የኦሮሞ ጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እሳቤ አንፃር ብናየው ሰፊው የኦሮሚያ ክልል ያቀፋቸውን ኦሮምኛ ተናጋሪ ሰፊ ህዝቦችን እንደመንታ ልጆች ተመሳሳይ መልክ፣እሳቤ፣ፍላጎት ያቸው አድርጎ “ኦሮሙማ” የሚል የጅምላ ማንነት ሊያላብስ ይለፋል፤ከኦሮሞ በቀር ለኦሮሞ የሚያስብ እንደሌለ እርግጠኛ ሆኖ ‘ኦሮሞዎች ብቻ ተሰብሰቡና ምከሩ’ ሲል በር አዘግቶ ሲያስዶልት አይተናል፡፡ በዚህ እሳቤ መሰረት ኦሮሞዎች እንደነዶ ለብቻቸው ታስረው የተቀመጡ ህዝቦች ስለሆኑ እነሱ ለብቻቸው የሚወስኑት ውሳኔ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ ተፅዕኖ የለውም፤ወይም ሌላው ኢትዮጵያዊ የነሱን የብቻ ውሳኔ አሜን የማለት እዳ አለበት፡፡ኦሮሞ በተባለው ሰው ውስጥ በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት ካገኘው አንዱ ማንነቱ (ኦሮሞነት) በቀር ሌላ ማንነት ስለሌለው ፍላጎቶቹ፣ጥያቄዎቹ፣ምኞቶቹ ሁሉ የሚመነጩት ከሚናገረው ቋንቋ ብቻ ስለሆነ መነጋገር ያለበት ከቋንቋ መሰሎቹ ጋር ብቻ ነው-እንደ እሳቤው፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡

የሚናገሩት ቋንቋ (ጎሳቸው) በፍፁም የማይገናኝ ሁለት በገጠር የሚኖሩ አማራ እና ኦሮሞ አርሶ አደሮችን በአንድ በኩል ሁለት ከተሜ አማራ እና ኦሮሞዎችን በሌላ በኩል አስቀምጠን ምኞት ፍላጎታቸውን ችግር ጥያቄቸውን ብንጠይቅ ከሚናገሩት ቋንቋ ይልቅ በተሰማሩበት የኑሮ ፈርጅ የተነሳ ተመሳሳይ እምነት፣ ፍላጎት፣ ጥያቄ፣ ዝንባሌ እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም፡፡ ይሄን በጾታ፣ በእድሜ፣ በትምህርት ደረጃ ወዘተ እየተካን ብናሰላው ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም አካባቢ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ሰዎች ተመሳሳይ ቋንቋ እየተናገሩም ቢሆን እምነት፣ ዝንባሌ፣ ጥያቄ፣ ፍላጎታቸው በአጠቃላይ ባህላቸው ከመመሳሰል ይልቅ እየተለያየ መሄዱ ሳይንሳዊ ነው፡፡ ፕ/ሮ መስፍን ‘በጎሳ ውስጥ ልዩነት የሌለ አይምሰላችሁ’ የሚሉት እንዲህ ያለውን ጉራማይሌነት ነው፡፡ ሌላ ማሳያ ለማከል ያህል አንድ አይነት ቋንቋ መናገር አንድ ወጥ ማንነት የሚያመጣ ቢሆን ኖሮ ኦሮሞው አቶ አባዱላ የተሰለፉበት የፖለቲካ እምነት ኦሮሞውን አቶ በቀለ ገርባን እስርቤት የሚያመላልስ አይሆንም ነበር፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከምክንያታዊነት እና ነባራዊነት ጋር ጥብቅ ጠብ የተጣላው የጎሳ ፖለቲካችን ለምክንያት የዝሆን ጆሮ ሰጥቶ ይነጉዳል፡፡ በየጎሳ ፖለቲካ “ቄሰ-ገበዙ” አቶ ጃዋር መሃመድ በአንድ ወቅት አቶ አባዱላ ገመዳ ዛሬ ኦ.ኤም.ኤን ካባረረው ጋዜጠኛ አብዲ ፊጤ እና ሌሎች ጋር የነበራቸውን እራት ግብዣ አስመልክቶ ‘እንዴት የኦሮሞ ወጣቶችን ከሚያስረው ሰው ጋር ማዕድ ትቀርባላችሁ?’ በሚል ትችት ሲቀርብበት ‘ኦሮሞ ሁሉ ወገናችን ነው አበሾች በልዩነታችን ማትረፍ ስለምትወዱ እኛ ስንሰባሰብ አትወዱም’ ሲል መልስ በሰጠ አንድ አመት ሳይሞላው ነው ኦህዴድ በሚመራው የኦሮሚያ ክልል የዚያ ሁሉ የኦሮሞ ደም የፈሰሰው፡፡ ጃዋር ባለው መሰረት ኦሮሞ ሁሉ የኦሮሞ ወገን፤ ኦሮሞ ያልሆነ ሁሉ ለኦሮሞ የማይተኛ ከሆነ ለምን ኦህዴድ በሚመራው ክልል፤ወገኔ ብሎ እራት ያቋደሳቸው አቶ አባዱላ ዋና በሆኑበት ስርዓት ያሁሉ ኦሮሞ ሞተ፣ ጃዋርስ እንዴት የሞት ነጋሪት ጎሳሚ ተደርጎ በስሙ ፋይል ተከፈተ? ‘ይህን መዛባት አጢኑና ወደ መስመር ግቡ’ ነው የፕ/ሮ መስፍን ምክርና ተግሳፅ፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት ለማስፈን የሚለፉ የአማራ የጎሳ ፖለቲከኞች እንደ ኦሮሞ ጓዶቻቸው አንድ አማራዊ ማንነት አለን እንጅ ጎጃሜ፣ጎንደሬ፣ወሎየ፣መንዜ አትበሉ ይላሉ፡፡እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትጵያዊ ደግሞ ይበልጥ የሚያውቀው ጎጃሜ፣ጎንደሬ፣ተጉለቴ የሚለውን እንጅ አማራ የሚለውን ማንነት አይደለምና ይህም ትልቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኖ ያነታርካል፡፡እንዲህ ብሎ ለያይቶ መጥራት የአማራን ህዝብ ማንነት የማጥፋት ሂትለራዊ ተንኮል ተደርጎ ይወገዛል፡፡ የአማራ ህዝብ ራሱ ግን ይህ ውድቅ የሚያደርግ በልጅነቴ እየሰማሁት ያደግኩት አንድ አባባል አለው -“የጎንደሬን አማርኛ እንኳን መንዜ ጎጃሜም አይሰማው” ይላል፡፡አባባሉ የሚያስረዳው በአሁኑ የሃገራችን የጎሳ ፖለቲካ ፈሊጥ የፍፁም መመሳሰል ዳርቻ እየተደረገ ባለው በአንድ አይነት ቋንቋ በመግባባት ውስጥ እንኳን ልዩነት መኖሩን ነው፡፡ እንደሚባለው አማራነት፣ከአማራ ምድር መወለድ እንደ ፋብሪካ ምርት አንድ የሚያደርግ፣ ሁሉን ፍጡር አንድ አይነት ነገር የሚያሳስብ ከሆነ በትቂቱ ቤተ-አማራ ከሞረሽ ወገኔ ተለይቶ አናየውም ነበር፡፡ እውነታው እና የሚያስኬደው መንገድ ፕ/ሮ እንዳሉት ሰው ባለበት ሁሉ ልዩነትም አንድነትም መኖሩን ተቀብሎ የማያልቀውን የጎሳ አጥር እያጠበቡ ሲያጥሩ ከመኖር እልፍ ማለቱ ነው፡፡

የጎሳ ፖለቲካ አጥር ማለቂያ የለውም የሚለው አባባል አሁንም ሰከን ብሎ ለሰማ፣ሰምቶም ለመማር ለተዘጋጀ ጥሩ ጥቁምታ ነው፡፡ ይህን ነገር ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በአንድ ወቅት “በዘር ፖለቲካ ሄደህ ሄደህ የምትገባው ቤትህ ነው” ካለው ግሩም እይታ ጋር መሳ ነው፡፡ ነገሩን ወደ ነባራዊው የሃገራችን የጎሳ ፖለቲካ ሃቅ ስንመልሰው እኔ የምኖርበት የደቡብ ክልል በርካታ ብሄረሰቦችን ያቀፈ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ከክልሉ ብሄር የአንዱ ተወላጅ ከሆነ ሰው ጋር እሱ ተወልዶ ባደገበት የገጠር ቀበሌ የኔ መስሪያቤት የሚሰራው ስራ ኖሮ ከእኛ ጋር ይጓዝ ነበር፡፡እናም የሄድንበትን ስራ ጨርሰን የእርሱን የትውልድ መንደር ለቀን ግን በዛው ዞን ውስጥ ከትውልድ መንደሩ አንድ አስር ኪሎሜትር ርቀን እንደተጓዝን አንዲት ትንሽ ከተማ እንደደረስን ሰውየው “እኔኮ እዚች ከተማ ልጄን ማስቀጠር አልችልም” ብሎ ዝምታችንን የሚሰብር ንግግር አመጣ፡፡ “ለምን አንድ ዞን አይደል እንዴ?” አልኩኝ በጣም ስለገረመኝ ተሸቀዳድሜ፡፡ “አንድ ዞን ቢሆን፣ ቋንቋው አንድ ቢሆን ጎሳችን ግን የተለያየ ነው፤ እነሱ ጎሳቸው ያልሆነን ሰው አበጥረው ያውቃሉና የኔ ልጅ ይወዳደር ይሆናል እንጅ መቀጠር የማይታሰብ ነው” ሲል የደረስንበትን አዘቅት ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ፡፡ ቀጥየ ጥያቄ አላነሳሁም፤ዝም ዝም ሆነ! የሚያፅናናው ነገር ግን ፕ/ሮ እንዳሉት የጎሳ ፖለቲካ ቀሳውስት ለስልጣን እና ለጥቅም ዘር እያቋጠሩ ሃረግ ሊያማዝዙት ቢሞክሩም የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ግን እየተጋባ እየተዋለደ ኢትዮጵያዊነቱን በሰውነቱላይ፤ዜግነቱን በኢትዮጵያዊነቱ ላይ እያፀና “ሃዘንህ ሃዘኔ፤ደምህ ደሜ” እየተባባለ በሩቅ እየተነጋገረ ይኖራል፡፡ ይህ ሁሉ ዘመን አመጣሽ እትብት የመማዘዝ ፖለቲካ የመጣውም በትቂቶች ነውና ፅናት አይኖረውም፤እነዚህ ትቂቶች የመሰረቱት ክፉ አግላይ ስርዓት በስብሶ ሲወድቅ ሁሉም ይስተካከላል፡፡

ቂም፣ ልግም፣ የክፋት አዙሪት – ቆሞ መቅረት!

ፕ/ሮ መስፍን እንደህዝብ ያለብንን ችግር በደንብ ተረድተው፣ የተረዱትን እውነት በሚገባን፣ መሬት በወረደ ቋንቋ ተርጉመው ጉድፋችንን በማስረጃ አበልፅገው በማንክደው ሁኔታ በማሳየት ተወዳዳሪ የሌላቸው ምሁር ይመስሉኛል፡፡ “የኔታ” የሚለው የኢ-መደባዊ ማዕረጋቸው ትርጉምም ይሄው ይመስለኛል፡፡ የኔታ የሚለው ማዕረግ ፊደል ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የመገሰፅ የመኮርኮም ሞራላዊ ስልጣንንም ይይዛል፡፡ ፕ/ሮ መስፍን በማህበረ-ፖለቲካዊ ችግሮቻችን እና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ በአማርኛም በእንግሊዝኛም በደንብ ፅፈዋል፡፡ፅፌያለሁ ብለው መናገራቸውንም አይተውም፡፡ የፃፉ የተናገሩትን ወጣቱ ትውልድ እንዲያነብ፤በትኩረት እንዲያደምጥ ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኛው የዘመናችን ጋዜጠኛ፣ፖለቲከኛና ተንታኝ ደግሞ ማንበብ ላይ ወገቤን ባይ ስለሆነ የተናገሩ የፃፉት የሚመልሰውን ጥያቄ ይዞ ወደ እሳቸው ሲመጣ ይቆጣሉ፤ይገስፃሉ፡፡ “ቁጣው የፃፍኩትን ሁሉ አሜን ብላችኑ እመኑ” ከማለት አይመስለኝም፡፡ አንብቦ “እርስዎ በመፅሃፍዎ እንዲህ ብለዋል ግን እኔ እንዲህ ይመስለኛል” ለሚላቸው ቦታ የሌላቸው ሰው አይደሉም፡፡ ሳያነቡ፣በውል ሳያዳምጡ ከበሬ ፊት ሊበሉ ለሚመጡ ጥጆች ግን ትዕግስት የላቸውም፡፡ ቁጣቸው ይነዳል፡፡ በበኩሌ ቁጣው አያስቀይመኝም፤ይልቅስ ከመናገር ከመፃፋችሁ በፊት አንብቡ የማለት የታላቅ ምክር አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡

ፕ/ሮ ረዥም የህወት ልምዳቸው እና ምጡቅ ታዛቢነታቸው እንዳቀበላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ግፈኛን የሚያሸንፍባቸውን ዘዴዎች አሳይተውናል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ግፍ ሲበዛበት ያቄማል፣አቂሞ ይለግማል፣ ለግሞም አይቀርም ጊዜ ጠብቆ ቂሙን ክፉን በክፉ በመመለስ ተንፈስ ያደርጋል፡፡ ክፉን በክፉ ሲመልስ የሚጠላውን፣የተቃወመውን ክፋት ራሱ መልሶ ያደርገዋል፡፡ ይህ አካሄድ ውጊያው ከክፋተኛው ግለሰብ እንጅ ከክፉ አስተሳሰቡ ስላልሆነ ክፋተኛ ነቅሎ ሌላ ክፋተኛ ይነተክላል፡፡ ስለዚህ የሃገራችን ፖለቲካ ከክፋት አዙሪት ሊወጣ አልቻለም ይላሉ፡፡ መፍትሄውን ሲያስቀምጡ መዋጋት ያለብን ክፋትን ራሱን አስተሳሰቡን መሆን አለበት፡፡ ይህ መንገድ በደንብ ገብቶን ከጀመርነው ክፋትን ለማጥፋት ሌላ ክፋትን እንደመሳሪያ አድርገን መጠቀም እናቆማለን ይላሉ፡፡ ክፉ አስተሳሰብን ለመዋጋት ደግሞ ከራስ ጋር ብቻ የማውራት አድፋጭነትን አስወግደን መነጋገርና መግባባት መጀመር አለብን፡፡ እስከዛሬ ሳንነጋገር ስንግባባ የኖርነው ክፋትን በክፋት በመመለሱ ማድፈጥ ውስጥ ባለ ክፉ ቋንቋ ነው፡፡ አሁን ግን እርስበርስ ተነጋግረን ከሃሳባችን ፍጭት ክፉን በክፉ ከመቃወም የተለየ፣የተሻለ፣የዘመነ መንገድ ማውጣት አለብን ባይ ናቸው-የኔታ መስፍን!


ሌላ ሳንካ…..!

ጨቋኝ መንግስታትን ለመንቀል ስንታገል የግፍ አስተዳደርን እሳቤ፣ክፋትን ራሱን በፅንሰሃሳብ ደረጃ ተቃውመን፤ክፉን ካስወገድን በኋላ በጎ የመትከሉ ነገር ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን እስከ ዛሬ አልተቻለንም፡፡ ለምን ቢባል ክፉን ለመንቀል የሚያስችለን የቂም፣የልግመኝነት እና ክፉን በክፉ የመመለስ ሃይል በሙላት ስላለን ክፉን መንቀል ችለናል፡፡ እነዚህ ክፉን ለማስወገድ ሃይል የሆኑን ነገርግን ቂም፣ልግመኝነት፣ማድፈጥና፣ክፉን በክፉ መመለስ በጎ ስርዓትን ለመትከል የሚያስችል ልዕልና የሌላቸው፤ለዘመነ ፖለቲካ ስፍነት፣የተሻለ አኗኗር እውንነት የማይመጥኑ ኋላ ቀር እና ተራ ልምዶች ስለሆኑ ፖለቲካችንን ቆሞ-ቀር አድርገውታል፡፡ እስከዚህ ድረስ ከፕ/ሮ መስፍን ጋር እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን ለፖለቲካችን ቆሞ መቅረት ሃላፊነቱን መውሰድ ያለበት አካል በየፈርጁ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡

እንደሚታወቀው አብዛኞቹ በኢትዮጵያ የተካሄዱ ጨቋኝ አስተዳደርን የማስወገድ እንቅስቃሴዎች ወጣኔያቸውን እና ፍፃሜያቸውን የሚያገኙት ከፖለቲካ ልሂቃን ሆኖ ህዝቡ የሚፈለገው መሃል ላይ ለለውጡ ጉልበት ለመስጠት ሲባል ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን የመጣበትን ሁኔታ ብናይ ፕ/ሮ መስፍን እንዳሉት በማራቶን ሩጫ ሃገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፈት የህዝቡን እርዳታ ማግኘት ምትክ የሌለው ወሳኝ ጉዳይ ነበር፡፡ወደ አፈሙዝ ላንቃ የሚማገድ እግረኛ ወታደር ወልዶ መስጠቱ፣ ለወታደሩ እህል ውሃ ማቅረቡ፣ቁስለኛ ማስታመሙ፣ የጠላትን ሁኔታ ሰልሎ መረጃ ማቀበሉ፣ ጠላት ገፍቶ ሲመጣ መደበቅ መሸሸጉ ሁሉ ኢህአዴግ በመጨረሻዎቹ አመታት ወደ አዲስ አበባ ለመገስገስ ያስቻሉት ቀደም ብሎ ያገኛቸው የህዝብ ድጋፎች ነበሩ፡፡ ‘ህዝቡ ይህን ድጋፍ ለምን ሊያደርግ ቻለ?’ ለሚለው ጥያቄ አንዱ መልስ ፕሮፌሰር መስፍን ያነሱት በግፈኛ ላይ የማቄም፣የመለገም፣ክፉን የመበቀል ዝንሌ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ህዝቡ ይህን ሲያደርግ ‘በወታደር ጫማ እየረገተህ ያለውን ክፉ ጥለን ዲሞክራሲን እናመጣልሃለን’ ያሉትን ሸማቂዎች አምኖ የተሻለ ያደርጉልኛል ብሎ ተማምኖ ይመስለኛልና ክፉን ነቅሎ ደግ ባለመትከል እጅግም መወቀስ ያለበት አይመስለኝም፡፡ ክፉ ነቅሎ በጎ ባለመትከል መወቀስ ያለበት ዲሞክራሲ ላመጣልህ እታገልኩ ነው ብሎ የህዝብን አጥንት እየጋጠ፣በህዝብ ጫንቃ ላይ እየተረማመደ ለስልጣን የበቃው የትናንት ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ሸማቂ የዛሬ ተረኛ ግፈኛ አስተዳደር ይመስለኛል፡፡

ይህ አካል በቃል አባይነት፣በመሰሪነት እና በአታላይነት መወቀስ፤ለፖለቲካችን ቆሞመቅረት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለበት፡፡ህዝባችን በየዋህ ልቦናው አምኗቸው የመሶብ የቡኾእቃውን ገልብጦ እንዲያበላቸው፣ ልጆቹን ለሞት መርቆ እንዲሰጥ ያደረገው የሸማቂዎቹ አስመሳይነት ነበር፡፡ ሸማቂዎቹ የልባቸውን እሲኪያደርሱ፤እንጦጦ አፋፍ እስኪደርሱ ዲሞክራትነታቸውን ለየዋሁ ህዝብ የሚያስረዱት “ቅጫማም” እየተባሉ ሲሰደቡ ዝም በማለት፣ “የተሰማችሁን ተናገሩ መብታችሁ ነው” በሚል ሽንገላ፣ሌባ የተባለን ሁሉ ያለፍርድ በየመንገዱ በጥይት በመቁላት ወዘተ እንደ ነበር ያየ የሰማ የሚናገረው ነው፡፡ያለፍርድ ሌባ የተባለን ሁሉ አስፋልት ላይ ሲያጋድሙ የነበሩት የፍትህ አለቃ ነን ባዮች በወንበራቸው ሲደላደሉ መንግስታቸው የሌባ መርመስመሻ እንደሆነ ራሳቸው ‘የመንግስት ሌባ ከቦናል’ ሲሉ በፓርላማ መስክረዋል፡፡ተራ ስድብ ሲሰደቡ ዝም ሲሉ እንደ ባህታዊ ይቃጣቸው የነበሩ ሸማቂዎች ዛሬ ጋዜጠኞች ስራቸውን ስለሰሩ ብቻ የሚያስሩ ፈርኦኖች ወጥቷቸዋል፡፡ ‘ደርግ የሰማኒያ አመት ሽማግሌ አሰረ ብለን ደደቢት ነጎድን’ ያሉ የነፃነት ነብያት ነን ባዮች ዛሬ የሰማኒያ አመት ሽማግሌ አስረው ቦክስ የሚያቀምሱ “ጎበዞች” ፤እናትን በልጇ አስከሬን ላይ አስቀምጠው የሚደበድቡ ጉዶች ሆነዋል፡፡

ከላይ በተንደረደርንበት ነባራዊ ሃቅ ላይ ቆመን ለፖለቲካችን ቆሞ-መቅረት፣አልለቅ ላለን የክፉ አስተዳደር አዙሪት ስፋኔ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች የትናንቶቹ የነፃነት ታጋይ፣የእኩልነት አደላዳይ፣የዲሞክራሲ ነብይ ነን ባዮቹ ሃገራችን የፖለቲካ ልሂቃን መሆን አለባቸው ብየአስባለሁ፡፡ የእነዚህ አካላት አታላይነት፣አስመሳይነት፣ግብዝነት እና መሰሪነት ፕ/ሮ መስፍን ለፖለቲካችን ክፉ አዙሪት በምክንያትነት ካነሷቸው ቂመኝነት፣ልግም፣ማድፈጥ፣እና ክፋት እኩል ፖለቲካችንን የክፋት አዙሪት ውስጥ የከተቱ መሆናቸው ታውቆ ለፈውሳችን መላ መባል አለበት፡፡

ያልተስማማኝ….

ከላይ እንደተቀስኩት ፕ/ሮ መስፍን እግራቸው ስር ቁጭ ብለን የፃፉ የተናገሩትን ልናስተውል የሚገባን ድንቅ መካር ናቸው፡፡ ብዙ የሚያመርት ፈጣን ጭንቅላት ያላቸው፣ፍርሃት የማያውቃቸው፣ብዙ ምሁራንን የሚያንገላታው የቁስሰቀቀን ሲያልፍም የማይነካካቸው፣ ሃገር ወዳድ አድባር እንደሆኑ አያነጋግርም፡፡ሆኖም ከሃሳባቸው ጋር አለመስማማትም ሆነ በከፊል መስማማት ተፈጥሯዊም ጤናማም ነው፡፡ግን አለመስማማታችንን ስንገልፅ ሽምግልናቸውን ብቻ ሳይሆን አዋቂነታቸውን የሚመጥን ክብር ልንነፍጋቸው አይገባም፡፡ ለትልቅነታቸው ያለኝ ክብር እንዳለ ሆኖ፤በንግግራቸው ብዙ በመማሬ እያመሰገንኩ ከንግግራቸው ያልተስማሙንን አንድ ሁለት ነጥቦች ላንሳ፡፡ አንደኛው ከላይ የጠቀስኩት ህዝቡን እና አታላዩን ልሂቅ በአንድ ላይ አይተው ለፖለቲካችን ክፉ አዙሪት በእኩል ተጠያቂ ያደረጉበት መንገድ ቢነጣጠል እና ልሂቁ እንደጥፋቱ መጠን ትልቁን ሃላፊነት ቢወስድ የሚል ነገር አለኝ፡፡ ፕ/ሮ መስፍን የሚሉት በጎ ስርዓትን ለመትከል ሚገፋውን በጎ ሃይል ያጣው አስመሳይ መልቲነትን ተከናንቦ ስልጣን ላይ ቂጢጥ ያለው ልሂቅ ነው፡፡ ‘ህዝቡስ በዚህ አዙሪት ውስጥ ድርሻ የለውም ወይ?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም ህዝቡ ከተወቀሰ የሚወቀሰው በደርሶ አማኝነቱ ምክንያት ለልሂቁን ብልጣብልጥነት መረዳት ባለመቻሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የግንዛቤ ነገርም ስላለበት በብዛት ላልተማረው ህዝባችን ይቅርታ ለማድረግ በቂ ምክንያት ነው ብየ አስባለሁ፡፡ ህዝቡ ሸማቂዎች ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ቃልአባይነታቸውን ተረድቶ ለምን በጊዜ አይሸኛቸውም የሚል ሌላ ጥያቄ ከመጣ ህዝቡ ይህን የሚያደርግበት የህግ የበላይነት፣ለይስሙላ ህግ በወረቀት ከመቸከቸክ ባለፈ ህግን የሚያስፈፅም ተቋማዊነት እንዳይኖር የልሂቃኑ አታላይ የፖለቲካ ማንነት ስላልፈቀደ፤ህዝቡ ገፍቶ ሲመጣም ልሂቁ በጥይት ቋንቋ ስለሚያናግረው አሁንም ወደ ማድጥፈጡ ከመመለስ ያለፈ አማራጭ የለውም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ስራ የቀረው ስልጣን ላይ ካለው የፖለቲካ ልሂቅ ይመስለኛል፡፡

ሁለተኛው ጥቅሙን ያጣሁት የፕ/ሮ መስፍን ንግግር ስለ በላይ ዘለቀ እና አፄ ኃ/ስላሴ፤ ኦሮሞነት ስለ ኃ/ማርያም የወላይታ የመጀመሪያው ባለስልጣን ያለመሆን ጉዳይ ያነሱት ነገር ነው፡፡ ይሄ በተለይ እንደ እርሳቸው ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መብት ለሚሟገት፤ይህንንም በሃገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋም መስርቶ በማስኬድ ለሚወደስ የሰብዐዊነት ምልክት ሰው አይመጥንም፡፡ ለፖለቲካችን ፈውስም አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡


የምንጣፉ ውበት!!!!

ፕ/ሮ መስፍን በንግግራቸው መጨረሻ ላይ በሃገራችን የፖለቲካ ወለል ላይ መነጠፍ ስላለበት በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በህግ ስርዓት የተማገረ ውብ ምንጣፍ የተናገሩት ውብ ንግግር በጣም ድንቅ ነው፡ ፡ምንጣፉ ዜጋን ሁሉ በእኩልነት የሚያንከባልል መሆን እንዳለበት፤ ሆኖም የሚንከባለሉ ሰዎች ወደ ምንጣፉ ሲመጡ ምንጣፉን እንዳያቆሽሹና ወደ ተለመደው አዙሪታችን እንዳይጨምሩን አእምሯቸውን፣ ከቂም በቀል ማፅዳት፣ ከክፋት መፈወስ አለባቸው ይላሉ፡፡ ነገሩ ድንቅ ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን ከምኞት ባለፈ ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ የፖለቲካ ንቃትን በህዝቡ አእምሮ ውስጥ ማስረፅ አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ሊጤን ይገባል፡፡ አእምሮን የሚያቆሽሽ፣ ክፋት የሚሞላ፣ጨለምተኝነት፣ ጠጠራጣሪነት፣ ቂም በቀልን የሚያሸክም፣ በምኞት ፈረስ የሚያስጋልብ፣ በልቼ ልሙት የሚያስብል ራስ ወደድነት፣ የህግ ማህበረሰብ ያለመሆን፣አምባገነንን ለመሸከም የማጎንበስ አድርባይነት ሁሉ ምንጩ አለማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ በሃገራችን የሲቪክ ማህበራት እንደልብ ተንቀሳቅሰው ህዝቡን ስለመብቱ፣ ግዴታው፣ ከመንግስት ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ተገቢ ግንኙነት እንዲያስተምሩ መሆን አለበት፡፡ ይሄኔ የነቃው ህዝብ ዲሞክራሲ መብቱን ለማስከበር ተቋማትን ገንብቶ ለመብቱ ተቋማዊ ጠበቃ ያቆማልና አምባገነን እየተፈራረቀ ሊያስጨንቀው አይችልም፡፡

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 3፡- ብሔርተኝነት ሳይወጣ እኩልነት አይገባም!

የዘር/ብሔር አፓርታይድ ተከታታይ ፅሁፍ የመጀመሪያ ክፍል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የትጥቅ ትግል የሚጀመርበት መሰረታዊ ምክንያት ለማህብረሰቡ የመብትና ነፃነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ሳይሰጥ ሲቀር ነው። ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ የእኩልነት፥ ነፃነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በኃይል ለማዳፈን መሞከር፤ በመጀመሪያ ወደ አመፅና ኹከት፣ በመቀጠል ወደ ግጭትና የትጥቅ ትግል እንደሚያመራ ተመልክተናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ፖለቲካ ልሂቃን የማህብረሰቡን ብሶትና ተቃውሞ በብሔርተኝነት ስሜት በማቀጣጠልና በራስ-የመወሰን መብትን ተሰፋ በመስጠት አመፅና ተቃውሞን ወደ ትጥቅ ትግል ያሸጋግሩታል።

በዚህ መሰረት፣ የትጥቅ ትግል ለማስጀመር በማህብረሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የብሔርተኝነት ስሜት በትግል ወቅት ከሚፈጠረው የጠላትነት ስሜት በመጣመር አክራሪ የፖለቲካ አመለካከት ይፈጠራል። በእርግጥ ያለ ብሔርተኝነት ስሜት ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ማስረፅ አይቻልም። በተመሣሣይ፣ በጨቋኙ ስርዓት ላይ የጠላትነት ስሜት መፍጠር ካልተቻለ የትጥቅ ትግል ማካሄድ አይቻልም። ነገር ግን፣ ልክ የትጥቅ ትግሉ እንደተጠናቀቀ አዲስ የፖለቲካ ማህብረሰብን መፍጠር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሰረፀውን በብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜት ላይ የተመሰረተ አክራሪ የፖለቲካ አመለካከት በአዲስ መቀየር ያስፈልጋል።

አዲስ የፖለቲካ ማህብረሰብ ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እሴቶችን ለመለየትና ለማዳበር ለትጥቅ ትግሉ መነሻ የሆነውን ምክንያት ተመልሶ ማየት ያስፈልጋል። በእርግጥ የትግሉ ዓላማ የማህብረሰቡን በራስ-የመወሰን መብት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። በራስ-የመወሰን መብት ያስፈለገበት ምክንያት የማህብረሰቡን እኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማስከበር ነው። የአብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ነፃነት ማስከበር የሚቻለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ሲቻል ነው።

የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ደግሞ በእኩልነት፥ ነፃነት፥ የህግ የበላይነት፥ ግልፅነት፥ ተጠያቂነት፥ …ወዘተ በመሳሰሉ እሴቶች የታነፀ የፖለቲካ ማህብረሰብ ሊኖር ይገባል። ይህ ደግሞ በትጥቅ ትግሉ ወቅት በማህብረሰቡ ውስጥ የሰረፀው አክራሪ ብሔርተኝነትና የጠላትነት መንፈስ ሙሉ-ለሙሉ መወገድ አለበት። በዚህ መሰረት፣ በጦርነት ወቅት የተፈጠረውን አሮጌ ነፍስ በአዲስ ነፍስ መተካት ያስፈልጋል።

በክፍል-2 ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ “የትጥቅ ትግሉ የመጨረሻ ግብ ደግሞ አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር ነው” (the invention of new souls) የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ይህን ያመለክታል። የትግል መሪዎች/ልሂቃን አዲስ ነፍስ የሚፈጥሩት በትግል ወቅት የተፈጠረውን የብሔርተኝነትና ጠላትነት ስሜት ከትግል በኋላ በእኩልነትና ነፃነት በመተካት ነው። ነገር ግን፣ እንደ “Frantz Fanon” አገላለፅ፣ አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር የሚቻለው ከትግል በኋላ አይድለም። ከዚያ ይልቅ፣ ጦርነቱ በተፋፋመበትና የታጋዮች የብሔርተኝነት/ብሔራዊ ስሜት በተጋጋለበት ወቅት ራስንና ሌሎችን፤ “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ መጠየቅና መመለስ ሲቻል ነው።

የትግሉ መሪዎችና ልሂቃን “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ራሳቸውንና የትግል አጋሮቻቸውን ያለገደብ፥ በግልፅ የሚጠይቁና የሚወያዩ፣ በዚህም ጥያቄውን በነባራዊ እውነታ ላይ ተመስርተው ጥያቄውን የሚመልሱ ከሆነ የትግሉን የመጨረሻ ግብ ማሳካት ይቻላሉ። ስለዚህ፣ በትግል ወቅት ይህን ማድረግ የቻሉ መሪዎችና ልሂቃን፣ የጨቋኙ ስርዓት ከተወገደ በኋላ በትግል ወቅት የተፈጠረውን አክራሪ ብሔርተኝነትና የጠላትነት ስነ-ልቦናን በማስወገድ በምትኩ በዴሞክራሲያዊ እሴቶች የታነጸ የፖለቲካ ማህብረሰብ መፍጠር ይችላሉ። ነገር ግን፣ በቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት የተፈፀመውን በደልና ጭፍጨፋ እያሰቡ የጠላትነት ስሜትን ማስወገድ አይቻልም። በተመሣሣይ፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚንፀባረቀውን አክራሪነት ብሔርተኝነት ሳያስወግዱ የዴሞክራሲ እሴቶችን ማስረፅ አይቻልም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በትግል ወቅት መጠየቅ የነበረበት ጥያቄ ከትግል በኋላ መልስ አያገኝም። “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” ለሚለው ጥያቄ በነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ መልስ መስጠት የሚቻለው በጦርነት ወቅት የተጠየቀ እንደሆነ ብቻ ነው። ምክያቱም፡- አንደኛ፡- በትግል ወቅት የተፈጠረው የብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜት ከትግል በኋላ ወደ ተበዳይነትና ፍርሃት ስለሚቀየሩ፣ ሁለተኛ፡- የጥያቄውን አውድ በግልፅ መገንዘብና በእውነታ ላይ የተመሰረተ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ራሳችንን በድርጊት ፈፃሚዎቹ ቦታና ግዜ ላይ በማስቀመጥ፣ ተግባሩን የፈፀመበትን ትክክለኛ አውድና ምክንያት መረዳት ስንችል ነው። ከዚህ ቀጥሎ የመጀመሪያውን ምክንያት በአጭሩ የምንመለከት ሲሆን ሁለተኛውን ምክንያት ደግሞ በቀጣዩ ክፍል አራት በዝርዝር ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ በጦርነት ወቅት የሰረፀው የብሔርተኝነት ስሜት ከትግል በኋላ ወደ ጭፍን ወገንተኝነትና የተበዳይነት ስሜት ይቀየራል። በተመሣሣይ፣ በጦርነት ወቅት የተፈጠረው የጠላትነት ስሜት ከጦርነቱ በኋላ ወደ ፍርሃትና ጥርጣሬ ይቀየራል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ በትግል ወቅት ስለተፈፀመ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ከስሜታዊነት በፀዳ መልኩ መወያየትና መግባባት በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።

በቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት የእሱ ማህብረሰብ ብቻ ተለይቶ እንደተበደለ ከሚስብና “የቀድሞ ስርዓት ተመልሶ ሊመጣ ይችላል” በሚል ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ካለ ሰው ጋር በመተማመን ላይ የተመሰረተ ውይይት ማድረግ አይቻልም። “Edward Said” እንዲህ ያለውን ውጥረት ለማስወገድ የአልጄሪያዊው የነፃነት ታጋይና ልሂቅ “Frantz Fanon” እንደ ምሳሌ በመጥቀስ የትግል መሪዎችና ልሂቃን ድርሻና ኃላፊነትን እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“It is inadequate only to affirm that a people was dispossessed, was oppressed or slaughtered, was denied its rights and its political existence without at the same time doing what [Frantz] Fanon did during the Algerian war: affiliating those horrors with the similar afflictions of other people. This does not at all mean a loss in historical specificity, but rather it guards against the possibility that a lesson learned about oppression in one place will be forgotten or violated in another place or time. …For the intellectual, the task is explicitly to universalise the crisis, to give greater human scope to what a particular race or nation suffered, to associate that experience with the sufferings of others.” REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual, Lecture 2: Holding Nations and Traditions at Bay, 1993.

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ የትግል መሪዎችና ልሂቃን በእነሱ ብሔርና ዘር ላይ የተፈጸመን በደልና ጭቆና በማስፋትና በሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች ላይ ከተፈጸመው በደልና ጭቆና ጋር አያይዘው ማቅረብ አለባቸው። ናጄሪያዊው ሎሬት “Wole Soyinka” የቀድሞውን የደርግ ወታደራዊ መንግስት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከነበሩ አምባገነናዊ እና ጨቋኝ መንግስታት ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልፃል። ሌላው ቀርቶ የደርግ መንግስት የፈፀመው በደልና ጭቆና፣ የኢራን ኢስላማዊ መሪዎች፣ በአፍጋንስታኑ ታሊባኖች፣ እንዲሁም በሩሲያ የሶቬት ሕብረት አምባገነናዊ ስርዓት ከፈፀሙት በደልና ጭቆና ጋር ፍፁም ተመሳሳይ እንደሆነ ይገልፃል።

“The saturation of society by near-invisible secret agents, the cooption of friends and family members – as has been notoriously documented in Ethiopia of The Dergue, former East Germany, Idi Amin’s Uganda or Iran of the Shah Palahvi and the Ayatollahs prior to the Reformist movement – all compelled to report on the tiniest nuances of discontent with, or indifference towards the state – they all constitute part of the overt, mostly structured forces of subjugation. To fully apprehend the neutrality of the suzerainty of fear in recent times, indifferent to either religious or ideological base, one need only compare the testimonies of Ethiopian victims under the atheistic order of Mariam Mengistu, and the theocratic bastion of Iran under the purification orgy of her religious leaders, or indeed the Taliban of Afghanistan and the aetheistic order of a Stalinist Soviet Union.” REITH LECTURES 2004: Climate of Fear, Lecture 2: Power and Freedom, 2004.

በደርግ መንግስት የተፈፀመው በደልና ጭቆና በሌሎች ዓለም ሀገራት ከሚፈጸሙ በድልና ጭቆናዎች ጋር ፍፁም ተመሳሳይ እንደሆነ ከላይ በአጭሩ ተመልክተናል። እንዲሁም የደርግ መንግስት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ ሲፈፅም የነበረው በደልና ጭፍጨፋ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ፣ በቀይ-ሽብር ዘመቻ የደርግ መንግስት ከሦስት አመት ባነሰ ግዜ ውስጥ እስከ 500ሺህ የሚደርሱ የሀገሪቱን ዜጎች ገድሏል።

በክፍል-2 የቀድሞውን የሕወሓት መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄን ዋቢ በማድረግ እንደተጠቀሰው በሰኔ 1980 ዓ.ም በሃውዜን በተፈፀመው የአውሮፕላን ድብደባ በአንድ ቀን 1800 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውና ይህም የትጥቅ ትግሉ ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ ብዙ ሰዎች በአንድ ቀን የተገደለበት እንደሆነ ተጠቅሷል። ነገር ግን፣ በ1970 ዓ.ም የቀይ-ሽብር ዘመቻ በተጀመረ የመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ብቻ 5ሺህ ተማሪዎችን ገድሏል፣ 30ሺህ አስሯል። ታዲያ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ የፈፀመው በደልና ጭፍጨፋ በአጠቃላይ የኢትዮጲያ ሕዝብ ከፈጸመው በምን ይለያል?

በአጠቃላይ፣ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ወይም በሌላ ብሔር ላይ ብቻ በደልና ጭፍጨፋ እንዳደረገ ወይም ለአንደኛው ብሔር ይበልጥ “ጥሩ” ሌላው ደግሞ “መጥፎ” እንደነበረ አድርጎ መግለፅ፥ መዘርዘርና መዘከር በትግል ወቅት የሰረፀው የብሔርተኝነትና ተበዳይነት ስሜት፣ እንዲሁም በጦርነት ወቅት የተፈጠረው የጠላትነት ስሜትና እሱን ተከትሎ የተፈጠረው የፍርሃትና ጥርጣሬ ምልክት ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት የሕወሃት መሪዎችና ልሂቃን የብሔርተኝነትና የጠላትነት ስሜትን በማስወገድ የእኩልነትና ነፃነት መርህን ማስረፅ አለመቻላቸው ነው። ሁለተኛውና ዋናው ምክንያት የሕወሓት መሪዎችና ልሂቃን ከደርግ ጋር ጦርነት ውስጥ በነበሩበት ወቅት “በእኛ ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ጭፍጨፋ በሌሎች ላይ እያደረስን ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅና ተገቢ የሆነ መልስ አለመስጠታቸው ነው። ሁለተኛውን ምክንያት እና በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ በቀጣዩ ክፍል-4 በዝርዝር እንመለከታለን።  

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 2፡- በትግል ወቅት የተፈፀመው ጭፍጨፋና ያልተመለሰው ጥያቄ

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 1 ፅኁፍ በብሔርተኝነትና በራስ-የመወሰን መብትን መሰረት ያደረገ የትግል እንቅስቃሴ እንዴት እንደሚጀመር የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችንና የትግራይ አማፂያንን በማሳያነት በመጥቀስ ተመልክተናል። በዚህ ፅኁፍ ደግሞ የደርግና እንግሊዝ ጦር ሰራዊት ከአማፂያኑ የደረሰባቸውን ያልተጠበቀ ሽንፈትና ውርደት ተከትሎ በነፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙትን በደልና ጭቆና እንመለከታለን። ከዚያ በመቀጠል፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአማፂያኑ መሪዎች/ልሂቃን ከጦርነቱ ጎን-ለጎን ለራሳቸው ማንሳት የነበረባቸው “መሰረታዊ ጥያቄ” ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

በክፍል አንድ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የደቡብ አፍሪካ ነባር ነጭ ሰፋሪዎች እና የትግራይ ሕዝብ የትጥቅ ትግል የጀመሩት በራስ-የመወሰን መብታቸውን ለማረጋገጥ ነው። በዚህ መልኩ የተጀመረውን የትጥቅ ትግል ለማክሸፍ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእንግሊዝ እና የደርግ ወታደሮች ተሰማርተው ነበር። የሁለቱም ጦር ሰራዊት በአማፂያኑ ከተደቀነባቸው አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ራሳቸውን ለማዳን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። እስኪ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች የፈፀሙትን ጭፍጨፋ እና ደርግ በትግራይ፥ ሃውዜን ላይ የፈፀመውን ጭፍጨፋ የምክንያት-ውጤት ተያያዥነትና ተመሳሳይነት በአጭሩ እንመልከት። 

1. በትግል ወቅት የተፈፀመው ጭፍጨፋ

1.1 በደቡብ አፍሪካ፡ “መሬቱን በእሳት መለብለብ”
እ.አ.አ በ1899 ዓ.ም የእንግሊዝ ጦር አዛዦች በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች ግዛትን “Boers Republic” ለመቆጣጠር ሲዘምቱ ለሽምቅ ተዋጊዎቹ ዝቅተኛ ግምትና ከፍተኛ ንቀት ነበራቸው። ሽምቅ ተዋጊዎቹን “ኋላ-ቀር፣ ቀሽሞች እና የጫካ ሽፍቶች” በማለት ያጣጥሏቸው ነበር። በእርግጥ የነጭ ሰፋሪዎች ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ከ300 ሺህ አይበልጥም ነበር። ከዚህ ውስጥ ግን 27000 የሚሆኑ የሽምቅ ተዋጊዎች ነበሯቸው። በአንፃሩ በጦርነቱ የተሳተፈው የእንግሊዝ ጦር ሰራዊት ጠቅላላ ብዛት 500 ሺህ ይደርስ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ሽምቅ ተዋጊዎች ውጊያው በተጀመረ የመጀመሪያ ሁለት አመታት ውስጥ በእንግሊዝ ጦር ላይ ያልተጠበቀ ድል ተቀዳጁ። እንግሊዝ ከአሰማራቻቸው የወታደሮች አንፃር 5% የሚሆኑት የደቡብ አፍርካ ሽምቅ ተዋጊዎች 22000 የሚሆኑ የእንግሊዝ ወታደሮችን ገደሉ። በዚህም እንግሊዝ ከ1815 – 1915 ዓ.ም ባሉት መቶ አመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማታውቀው አሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ተከናነበች። 

አብዛኛው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች በሽምቅ ውጊያው ተሳታፊ ናቸው። ወደ ጦር ሜዳ ሳይሄዱ የቀሩት በአብዛኛው እናቶች፥ ሕፃናት ልጆችና አዛውንቶች ነበሩ። የእንግሊዝ ጦር በሽምቅ ተዋጊዎቹ የሚደርስበት ጥቃት ራሱን ለማዳን “ተዋጊዎቹን ለማጥፋት “መሬቱን በእሳት መለብለብ” (Scorched-earth) የተባለውን የውጊያ ስልት ተግባራዊ አደረገ። ተዋጊዎቹ በሚንቀሳቀሱበት አከባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች ሙሉ-ለሙሉ በእሳት ቃጠሎ እንዲወድሙ ተደረገ።

በዚህ ምክንያት፣ ከመቶ ሺህ በላይ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎችን በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ወደ ማጎሪያ ካምፕ ከገቡት ውስጥ 28000 የሚሆኑት በርሃብና በበሽታ ሲሞቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ 22000 (81%) የሚሆኑት ከ16 አመት በታች ሕፃናት ናቸው።  ለአንድ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪ ውርደት ማለት ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታጉረው በርሃብና በበሽታ ሲያልቁ እያዩ ምንም ማድረግ አለመቻል ነው። ከዚህ ሰቆቃ የተረፉት ነጭ ሰፋሪዎች እ.አ.አ በ1948 ዓ.ም እንግዝ ለቅቃ ስትወጣ “ከዳኒኤል ፍራንኮይስ ማለን” (Daniel Francois Malan) መሪነት የአፓርታይድ ስርዓትን መሰረቱ።

1.2 በኢትዮጲያ፡ “ባህሩን በቦምብ ማድረቅ” 

እ.አ.አ በ1979 ዓ.ም ወታደራዊ ደርግ መንግስት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የሚንቀሳቀሱትን አማፂያን በኃይል ለመደምሰስ ቆርጦ ተነሳ። ለዚህ ዓላማ ሁለተኛውን አብዮታዊ ጦር ከፍተኛ ትጥቅ ያለው ከ70ሺህ በላይ ወታደሮች አሰማራ። ከአንድ አመት በኋላ በመጋቢት ወር 1980 ዓ.ም ግን ከ15000 የማይበልጡ የሻዕቢያ ተዋጊዎች ወደ 10000 የደርግ ወታደሮችን በመግደል አሸነፉ። በቀጣዩ ሚያዚያ ወር 1980 ዓ.ም ደርግ ሦስተኛን አብዮታዊ ጦር በማደራጀት በትግራይ የሚንቀሳቀሱ አማፂያንን በኃይል ለመደምሰስ በለገሰ አስፋው መሪነት ተንቀሳቀሰ። 

ሦስተኛን አብዮታዊ ጦር በትግራይ በአማፂያኑ ቁጥጥር ስር የወደቁትን ቦታዎች ለማስለቀቅ እና የኤርትራ-ትግራይ መስመርን ለማስከፈት ያደረገው ጥረት በሕውሓት የውጊያ ስልት በተደጋጋሚ ከሸፈ። የደርግ ሰራዊት በኤርትራ ካጋጠመው አሳፋሪ ሽንፈት በኋላ ሻዕቢያን ለማሸነፍ በቅድሚያ ሕወሓትን መደምሰስ እንዳለበት ወስኖ ነበር የመጣው። ነገር ግን፣ የአማፂያኑን ይዞታ መልሶ ለማስለቀቅና የአዲስ አበባ – አስመራ መንገድን ለማስከፈት ባደረጋቸው ውጊያዎች ተደጋጋሚ ሽንፈት ገጠመው።

በመጨረሻም፣ በትግራይ አማፂያን እየደረሰበት ያለው ተደጋጋሚ ሽንፈት ከትግራይ በተጨማሪ ኤርትራንም እያሳጣው እንደሆነ ሲውቅ የወሰደው እርምጃ በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ እልቂት አሰከተለ። በደቡብ አፍሪካ የሸምቅ ተዋጊዎች የተደቀነባቸውን አሳፋሪ ሽነፈት ለማስቀረት ተግባራዊ እንደተደረገው የ¨Scorched-earth” ፖሊሲ፣ የደርግ ሰራዊት “ዓሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ” በሚል ሃውዜን ላይ የአየር ድብደባ ፈፀመ። የሕውሃት መስራችንና የቀድሞ አመራር የነበሩት አረጋዊ በርሄ የሃውዜን ጭፍጨፋንና በትግራይ ሕዝብ ስነ-ልቦና ላይ ያሰከተለውን ጉዳት እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

“…On on 22 June 1988, that Legesse ordered the aerial bombardment of Hawzien. This attack, conducted by helicopter gunships and MiGs, resulted in 1,800 civilian deaths, the worst single atrocity of the war since the start of the ELF insurrection in 1961…. Many elderly parents who had been reluctant to let their children join the Front were now not only encouraging them but also themselves requesting to be armed and join the militia forces. While the numbers of TPLF brigades grew to more than 20,000 fighters, the Dergue’s forces were dwindling.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Amsterdam 2008, Page 184 – 317.

ከላይ ከተገለፀው ክስተት በኋላ የደርግ ሰራዊት በሽንፈት ላይ ሽንፈት ማስተናገድ ቀጠለ። በየካቲት ወር 1981 ዓ.ም የሕወሃት ታጋዮች በእንዳ-ስላሴ የተደረገውን ውጊያ ካሸነፉ በኋላ በቀጣዩ አንድ ሳምንት ውስጥ 20000 የደርግ ሰራዊትና የመንግስት ሰራተኞች ትግራይን ለቀው ወጡ። ይህን ተከትሎ መላው ትግራይ በሕወሃት ቁጥጥር ስር ወደቀ። ግንቦት 20/1983 ዓ.ም የደርግ መንግስት ተገረሰሰ።

በአጠቃላይ፣ እንግሊዞች በደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የፈፀሙትን በደልና ጭፍጨፋ የደርግ መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ፈፅሞታል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሲካሄድ የነበረው ውጊያ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት የአማፂያኑ መሪዎች/ልሂቃን ከጦርነቱ ጎን-ለጎን ለራሳቸው ማንሳት የነበረባቸው “ጥያቄ” ምን እንደሆነ እንመለከታለን።

2. በትግል ወቅት ያልተመለሰው ጥያቄ

ለአንድ የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪ ወራሪውን የእንግሊዝ ጦር ለማስወጣት በሚደረገው የትጥቅ ትግል መሳተፍ ትክክለኛ ተግባር ነው። በተመሣሣይ፣ ለአንድ የትግራይ ተወላጅ አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ከስልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል መሳተፉ አኩሪ ተግባር ነው። በአጠቃላይ፣ ከኢምፔራሊዝም ወራሪ ሆነ ከአምባገነናዊ ስርዓት ነፃ ለመውጣት የሚደረገው የትጥቅ ትግል አግባብነቱ አጠራጣሪ አይደለም።

ነገር ግን፣ “Edward Said” የተባለው” ምሁር “Frantz Fanon” የተባለ የአልጄሪያ የነፃነት ታጋይን በመጥቀስ፣ የትግል መሪዎች/ልሂቃን የትጥቅ ትግሉን ከመምራት ባለፈ አንድን ጥያቄ መጠየቅና መመለስ እንዳለባቸው ይገልፃል፡-

“This is defensive nationalism of course, yet as Frantz Fanon analysed the situation during the height of the Algerian war of liberation against the French, going along with the approving chorus of Algerian nationalism as embodied in party and leadership is not enough. There is always the question of goal which, even in the thick of battle, entails the analysis of choices. Are we fighting just to rid ourselves of colonialism, a necessary goal, or are we thinking about what we will do when the last white policeman leaves? According to Fanon, the goal of the native intellectual cannot simply be to replace a white policeman with his native counterpart, but rather what he called the invention of new souls.”  REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual, Lec.2: Holding Nations and Traditions at Bay, 1993.

ከላይ እንደተገለፀው፣ ለነፃነት የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት፣ ጦርነቱ ተፋፍሞ የሰማዕታቱ ቁጥር እየጨመረ በሄደበት፤ እንደ ደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ወይም እንደ ትግራይ ሕዝብ በንፁሃን ላይ በደልና ጭፍጨፋ ሲፈፀም፣ በዚህም ምክንያት የታጋዮች ሕዝባዊ ወገንተኝነትና የጨቋኙ ስርዓት ጠላትነት በናረበት ወቅት፣…የትግሉ መሪዎችና ልሂቃን “የትግላችን የመጨረሻ ግብ ምንድነው?” ብለው መጠየቅና ለዚህም ተገቢ የሆነ ምላሽ መስጠት አለባቸው።

ይህን መሰረታዊ ጥያቄ ለራስ አለመጠየቅ ወይም በሌሎች ታጋዮች ዘንድ እንዲነሳ አለመፍቀድ እና በትግሉ የመጨረሻ ግብ ላይ ግልፅ የሆነ ግንዛቤና አቅጣጫ ማስቀመጥ አለመቻል በሚታገሉለት ሕዝብ እና በትግሉ ሰማዕታት ላይ ክህደት መፈፀም ነው። በትግል ወቅት ይህን ጥያቄ ራስንና ሌሎች ታጋዮችን በመጠየቅ፣ በጉዳዩ ዙሪያ የተለያየ ሃሳብና አስተያየት እንዲሰጥ በማድረግ፣ በውይይት የዳበረ ግንዛቤና የጋራ መግባባት ካልተፈጠረ በስተቀር የነፃነት ትግሉ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ ጨቋኙ ስርዓት በተወገደ ማግስት እንደ አልጄሪያ፥ ቦስኒያ፥ ደቡብ ሱዳን፥…ወዘተ የእርስ-በእርስ ጦርነት ይከተላል። ወይም ደግሞ እንደ ኤርትራ የሻዕቢያ መንግስት፥ እንደ ኢትዮጲያ የኢህአዴግ መንግስት፥ እንደ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት፥ …ወዘተ የትግሉ መጨረሻ የቀድሞው ስርዓት ጭቁኖችን አዲስ ጨቋኝ ስርዓት እንዲመሰርቱ ማስቻል ይሆናል።

እንደ አልጄሪያዊው የነፃነት ታጋይና ልሂቅ “Frantz Fanon” አገላለፅ፣ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ ግብ “አዳዲስ ነፍሶችን መፍጠር ነው” (the invention of new souls)። በመሰረቱ፣ የዘር/ብሔር አፓርታይድ የትጥቅ ትግል መሪዎችና ልሂቃን ለራሳቸው አሮጌ ነፍስ ይዘው አዲስ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመመስረት ሲያጣጥሩ የሚፈጥሩት ሌላ ጨቋኝ ስርዓት ነው። ነገር ግን፣ እነዚህን አዳዲስ ነፍሶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ መፍጠር ይቻላል? ከቀድሞ ጨቋኝ ስርዓት ጋር የትጥቅ ትግል ለመጀመር የተፈጠሩ አሮጌ ነፍሶች ምን ዓይነት ናቸው? በአሮጌ ነፍሶች ውስጥ ሆኖ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል? ለምንና እንዴት? እነዚህን እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በቀጣይ ክፍሎች በዝርዘር እንመለከታለን።    

የዘር/ብሔር አፓርታይድ – ክፍል 1፡- ከልዩነት ወደ ጦርነት

“የሰቆቃ ልጆች” በሚል ርዕስ ያቀረብናቸው አምስት ተከታታይ ፅሁፎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በጀርመንና ጃፓን ወታደራዊ ፋሽስት፣ እንዲሁም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ በእስራኤልና በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት የተመሰረቱበትን ሁኔታ በዝርዝር ለመዳሰስ ሞክረናል።  ከዚህ በመቀጠል “የዘር/ብሔር አፓርታይድ” በሚል ርዕስ በምናቀርባቸው ተከታታይ ፅሁፎች የኢትዮጲያና የደቡብ አፍሪካ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሁኔታን መሰረት በማድረግ የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረትን በዝርዝር ለመዳሰስ እንሞክራለን። በዚህ የመጀመሪያ ክፍል ለዜጎች የመብትና ነፃነት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ እንዴት ወደ ብሔርተኝነት እና ጦርነት እንደሚቀየር እንመለከታለን።

1. የዘር/ብሔር ልዩነት   

እ.አ.አ. በ1950 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት ያወጣው የሕዝብ ምዝገባ አዋጅ (Population Registration Act) የሀገሪቱን ዜጎች “ነጭ፥ ጥቁር፥ “ከለርድ” (colored) እና ህንዳዊያን” በማለት ለአራት ይከፍላቸዋል። በተመሣሣይ፣ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት በአንቀፅ 39(5) የሀገሪቱን ዜጎች በቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድና ስነ ልቦናን መሰረት በብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ይከፋፍላቸዋል።

በመሰረቱ “አፓርታይድ” (Apartheid) የሚለው ቃል “መለየት” (Separatedness) ወይም “መለያየት” (the state of being apart) ማለት ነው። ዜጎች የሚከፋፈሉት በዘር ሆነ በብሔር በመካከላቸው የሚኖረውን ልዩነት አይቀይረውም ወይም መለያየቱን አያስቀረውም። ስለዚህ፣ “አፓርታይድ” ማለት የአንድ ሀገር ዜጎችን በዘር/ብሔር በመለየትና በመለያየት የሚያስተዳድር ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። የአፓርታይድ ስርዓት አመሰራረትን ከማየታችን በፊት ግን የዘር/ብሔር ልዩነት እንዴት ለፖለቲካዊ አጀንዳ ማስፈፀሚያ እንደሚውል እንመልከት።

በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በዘር ሀረግ፥ በቆዳ ቀለም፣ በብሔር፥ በቋንቋ፥ በባህል፥ በልማድ፣ በሥነ-ልቦና፣ በሃማኖት፣…ወዘተ ይለያያሉ። ሰፋ ያለ የጋራ ጠባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልማዶች ያሉት፣ ሊግባባበት የሚችልበት የጋራ ቋንቋ ያለው፥ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና አለን ብሎ የሚያምን፥ የሥነ ልቦና አንድነት ያለውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖር ማኅበረሰብ እንደ ሁኔታው “ብሔር፥ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ” ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

ምንግዜም ቢሆን በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እና በሌላ መካከል ልዩነት ይኖራል። ከፖለቲካ አንፃር ሲታይ፣ ልዩነት የሰላም ወይም ጦርነት፣ የዴሞክራሲ ወይም ጭቆና መኖርና አለመኖር መለያ ነው። የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሃማኖት፥ ሕልውና (ማንነት)፣…ወዘተ “እኩል” በሚከበርበት፣ ሁሉም ዜጎች የራሳቸውን አመለካከት ያለማንም ጣልቃ-ገብነት የመያዝና ሃሳባቸውን “በነፃነት” መግለፅ በሚችሉበት፣ እንዲሁም ከሀገሪቱ ልማትና እድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚ ከሆኑ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ መኖሩን ያረጋግጣል።

በተቃራኒው፣ የብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ባልተረጋገጠበት ሀገር ጭቆና መኖሩና ጦርነት ማስከተሉ እርግጥ ነው። በአንድ አከባቢ የሚኖር ማኅብረሰብ ጭቆና ሲደርስበት በቅድሚያ መብቱና ነፃነቱ እንዲከበር በአመፅና ተቃውሞ ብሶትና አቤቱታውን በአደባባይ ይገልፃል። ሆኖም ግን፣ መንግስት የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት የሚያደርግ ከሆነ የሕዝቡ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ ግጭትና ጦርነት ይቀየራል።

በመሰረቱ በአንድ አከባቢ የሚኖር ማኅብረሰብ የራሱን መንግስት የሚመሰረተው ሕግና ስርዓት እንዲያስከብር፣ በዚሁም የሁሉንም መብትና ነፃነት እንዲያረጋግጥ ነው። የተወሰነ ሕብረተሰብ ክፍል የእኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ሲያነሳ መንግስት በምላሹ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ለእስራት፣ እንግልትና አካል ጉዳት የሚዳረግ ከሆነ እንደ መንግስት መሰረታዊ ዓላማውን ስቷል። መሰረታዊ ዓላማውን የሳተ ነገር ሁሉ ፋይዳ-ቢስ ነው። ስለዚህ፣ ከሕዝቡ የሚነሳን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚሞክር መንግስት ሕጋዊ መሰረት የለውም።

በዚህ ምክንያት በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ ውስጥ እንዲህ ያለ ቅሬታ ሲፈጠር የለውጥ አብዮት ማስነሳት ለሚሹ ልሂቃን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ልሂቃን በማህብረሰቡ ውስጥ የለውጥ አብዮት ለመቀስቀስ ከሚጠቀሟቸው ስልቶች ውስጥ ዋናዋናዎቹ የብሔርተኝነት ስሜት እና በራስ-የመወሰን መብት ናቸው። በዚህ መልኩ በአንድ ብሔር፥ ብሔረሰብ፥ ሕዝብ እና በሌላ መካከል ያለ ልዩነት በሂደት ወደ ግጭትና ጦርነት ያድጋል። የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት – TPLF) መስራችና የቀድሞ አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ድርጅቱ የትግል አጀማመር በሰጠው ትንታኔ እንዲህ ይላል፡-   

“Discontent can be caused by a variety of intervening factors but often is articulated in relation to the state that claims to possess the moral and legal authority to manage the affairs of the populace. Once discontent has been created, it can be easily politicized by the elite who seek change and civil disorder may follow. In this circumstance ‘loss of government legitimacy is an important if not critical factor in explaining civil strife events.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Ch.2, Page 24.

2. ብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት

ፖለቲካዊ ስርዓቱ የአንድን ማህብረሰብ እኩልነት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማያረጋገጥ ከሆነ የማህብረሰቡ ልሂቃን የተለያየ ዓይነት የለውጥ እርምጃ እንዲወሰድ ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ። በተለይ መንግስታዊ ስርዓቱ የዜጎቹን መብትና ነፃነት ማረጋገጥ ሲሳነው በቅድሚያ አስፈላጊ የሚሏቸውን የሕግና ፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ ይጎተጉታሉ። የሀገሪቱ መንግስት ስራና አሰራሩን በመቀየር ከሕዝቡ የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ ከተሳነው አመፅና ተቃውሞ ይቀሰቀሳል። መንግስት ለሕዝቡ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ብሶትና አብቱታውን በአደባባይ እንዳይገልፅ የሚያፍነው ከሆነ የለውጥ ንቅናቄው ወደ ትጥቅ ትግልና ጦርነት ያመራል።

በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የለውጥ ፍላጎት ወደ “አብዮት” (revolution) ለመቀየር እና የትግል ስልቱን ከአደባባይ አመፅና ተቃውሞ ወደ ውጊያና ጦርነት ለማሸጋገር የፖለቲካ ልሂቃኑ ሁለት ነገር መፍጠር አለባቸው። እነሱም፣ አንደኛ፡- በብሔሩ፥ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ የወገንተኝነትና የአንድነት ስሜት ለመፍጠር ብሔርተኝነትን ማስረጽ፣ ሁለተኛ፡- የትግሉን ዓላማና ግብ ደግሞ የብሔሩን፥ ብሔረሰቡን ወይም ሕዝቡን በራስ-የመወሰን መብት ማረጋገጥ እንዲሆነ ማሳመን አለባቸው።

ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት በሚደረጉ የሕዝብ ንቅናቄዎች ውስጥ ያለው መሰረታዊ ጥያቄ በራስ የመወሰን መብትን (right of self-determination) ነው። በራስ የመወሰን መበት አንድ ብሔር ወይም ሕዝብ የወደፊት ዕድሉን በራሱ የመወሰን፣ በራሱ ሕግና ደንብ የመተዳደር እና ከእሱ ፍቃድና ምርጫ ውጪ በሆኑ መሪዎች አለመመራት ነው። በዚህ መሰረት፣ ማህብረሰቡ ልዩነቱን በራሱ ማስከበር ይችላል። ከዚህ በፊት ሲያነሳቸው የነበሩት የእኩልነት፥ የነፃነትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን በራሱ ለራሱ መመለስ ይችላል። ብሔርተኝነት ደግሞ የማህብረሰቡን አባላት በትግሉ ዓላማና ግብ ዙሪያ አንድነትና ቁርጠኝነት እንዲኖረው ያስችላል። በደቡብ አፍሪካ የነጭ ሰፋሪዎች እና በኢትዮጲያ ትግራይ የትጥቅ ትግል የተጀመረው በብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት ላይ ተመስርቶ ነው።

2.1 በደቡብ አፍርካ የነጭ ሰፋሪዎች (Boers) የትጥቅ ትግል

በደቡብ አፍሪካ ቀድመው የሰፈሩት ነጮች “Boers” የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ “Boers Republic” በሚል ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ ነፃ ግዛቶች ነበሩ። ነገር ግን፣ እ.አ.አ. በ1866 የአልማዝ፣ እንዲሁም በ1886 ደግሞ የወርቅ ማዕድን በአከባቢው መገኘቱን ተከትሎ ብዙ የእንግሊዝና የሌሎች ሀገራት ዜጎች (utilanders) ወደ አከባቢው በብዛት መጉረፍ ጀመሩ። የአዲስ ሰፋሪዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄዶ በ1890ዎቹ የመጀመሪያ ላይ ከነባር ነጮች ”Boers” ጠቅላላ ብዛት በሁለት እጥፍ በለጠ። ይህ በነባር የደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ ራስን-በራስ የማስተዳደር መብታቸውና ነፃነታቸው ላይ የሕልውና አደጋ ተጋረጠበት። 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በራስ-የመወሰን መብታቸው ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማስወገድ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ አዲስ ረቂቅ አዋጅ በማውጣት ተግባራዊ አደረጉ። ይህ አዋጅ የነባር ሰፋሪዎችን በራስ-የመወሰን መብት የሚያረጋግጥ ሲሆን የአዲስ ሰፋሪዎችን ፖለቲካዊ መብትና ነፃነት የሚገድብ ነበር። አብዛኞቹ አዲስ ሰፋሪዎች ከእንግሊዝ ወይም ከቅኝ-ግዛቶቿ የመጡ እንደመሆናቸው በእንግሊዞች እና በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች (Boers) መካከል አለመግባባት አለመግባባት ተፈጠረ። አለመግባባቱ ወደ ጦርነት ተሸጋገረና በሁለቱ መካከል “Second Boers War” የተባለው፣ በዓለም ታሪክ አሰቃቂ በደልና ጭቆና የተፈፀመበት ጦርነት ተካሄደ። ይህ አሰቃቂ በደልና ጭቆና ደግሞ እ.አ.አ. በ1948 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ለተመሰረተው አፓርታይድ ስርዓት ዋና ምክኒያት ነው።  

2.2 በትግራይ የሕወሃት የትጥቅ ትግል 
በእርግጥ የትግራይ ሕዝብ በራስ የመወሰን ጥያቄን ማንሳት የጀመረው በቀዳማይ ወያኔ አማካኝነት ነው። በቀዳማይ ወያኔ የተካሄደው የአርሶ-አደሮች አመፅ ከባሌና ጎጃም የአርሶ-አደሮች አመፅ ጋር ተመሳሳይ ነው። የአርሶ-አደሮቹ አመፅና ተቃውሞ በዋናነት በእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ማዕከል ያደረገ ነበር። ሆኖም ግን፣ በወቅቱ የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ የወሰደው እርምጃ የአመፅ እንቅስቃሴውን በጦር ኃይል ማዳፈን ነበር። በዚህ መልኩ በወቅቱ የነበረው መንግስት ለሕዝቡ የመብትና ነፃነት ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ቀጣዩን የትግል ስልት በብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል።

በዚህ መሰረት፣ ዳግማዊ ወያነ – ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ሕወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የማህብረሰቡን የብሔርተኝነት ስሜት በማቀጣጠል እና በራስ-የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የሕወሓት (TPLF) መስራችና የቀድሞ አመራር አረጋዊ በርሄ ስለ ድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመር፣ የንቅናቄ ስልትና ድርጅታዊ አሰራር በተመለከተ እንዲህ ይላል፡- 

“…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one hand and the enforcement of strict internal discipline of its rank and file that able to take on rival forces decisively.” A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia, Ch.5, Page 151 – 152.

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ሁለቱ ወገኖች፤ በእንግሊዞች እና በደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች እና በደርግ መንግስት እና በሕውሃት ታጋዮች መካከል ጦርነት ተካሂዷል። በጦርነቱ ወቅት የእንግሊዝና የደርግ መንግስት እያንዳንዳቸው 22000 ወታደሮች በሦስት አመት ውስጥ ተገድሎባቸዋል። ይህን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ ነጮችና በትግራይ ሕዝብ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ፈፅመዋል። በሁለቱ ሀገራት የተፈፀመው አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ ለዘር/ብሔር አፓርታይድ መመስረት ያለውን አስተዋፅዖ በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።