መሪ-አልባ ሕዝብ እርስ-በእርስ ይጋጫል!

የትኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪ ያስፈልገዋል። እንቅስቃሴው አብዮታዊ (revolutionary) ከሆነ የለውጥ መሪ ያስፈልገዋል። ፀረ-አብዮታዊ (reactionary) ከሆነ ደግሞ የስርዓት መሪ ያስፈልገዋል። ለስኬት ብቻ ሳይሆን ለውድቀትም መሪ ያስፈልጋል። ምክንያቱም፣ ከስኬታማ ለውጥ በስተጀርባ ውጤታማ አወዳደቅ አለ። በእርግጥ በውድቀት ውስጥ ሽንፈት ነው ያለው። ነገር ግን፣ ውድቀትን አውቆ ሽንፈትን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ አመራር ከሌለ ፖለቲካዊ ቀውስ ይከሰታል። የቀድሞ ስርዓት ወድቆ-አይወድቅም፣ አዲሱ ስርዓት አይመሰረትም። ይህን ተከትሎ የቀድሞ ስርዓት ሳይወድቅ በቁሙ ይፈራርሳል፣ ሕዝባዊ ንቅናቄው ግቡን ይስታል። ይህ ሲሆን የብዙሃንን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረ ንቅናቄ አቅጣጫውን ስቶ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ይወስዳል። ይህ በምናባዊ እሳቤ ላይ ሳይሆን በመሰረታዊ የኃይል ፅንስ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህንንም የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት አወዳደቅን እንደ ማሳያ በመውሰድ በዝርዝር እንመለከታለን።

በመሰረቱ፣ “ኃይል” (power) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ነው። የኃይል ፅንሰ-ሃሳብ ለሁለት ይከፈላል። የመጀመሪያው አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል ቀጥተኛ ኃይል (Active power) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተግባሩን ወይም ለውጡን ለመቀበል የሚያስችል ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል (Passive power) ነው። ይህን ጽንሰ-ሃሳብ ለማስረዳት እንግሊዛዊው ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ እሳት እና ወርቅን እንደ ማሳያ ይጠቅሳል። እሳት ወርቅን ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ለመቀየር የሚያስችል ኃይል አለው። በሌላ በኩል፣ ወርቅ በሙቀት አማካኝነት ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ለመቀየር የሚያስችል ኃይል አለው። እሳት ወርቅን የማቅለጥ ወይም ቀጥተኛ ኃይል ሲኖረው ወርቅ ደግሞ በእሳት የመቅለጥ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል አለው። ወርቅ እንደ አፈር እሳት ሲነካው የሚፈረካከስ ቢሆን ኖሮ የወርቁ ቅርፅ መለወጥ ወይም መቀየር አይቻልም ነበር። ስለዚህ፣ የወርቅ ጌጥ የሚሰራው የእሳት ሙቀት ከወርቅ የመቅለጥ ባህሪ ጋር በመጣመር ነው። ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው ቀጥተኛ ኃይል ለዉጥን መቀበል ከሚያስችለው ቀጥተኛ ያልሆኑ ኃይል ጋር ካልተጣመረ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ አይቻልም።

በተመሣሣይ፣ አንድን ፖለቲካዊ ስርዓት በተሳካ ሁኔታ መቀየር የሚቻለው በስርዓቱ በደጋፊና ተቃዋሚ ጎራ ያሉ የፖለቲካ መሪዎች የለውጡን አስፈላጊነት እና አይቀሬነት ተገንዝበው በጥምረት መንቀሳቀስ ሲችሉ ብቻ ነው። ይህን ማየት ከመጀመራችን በፊት ግን “ኃይል”ከፖለቲካ አንፃር ያለውን ትርጉምና ፋይዳ በግልፅ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ “ኃይል” (power) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ለመለወጥ የሚያስችል አቅም ነው። ከዚህ አንፃር፣ የፖለቲካ ኃይል (political power) ማለት ደግሞ የአንድን ሀገርና ሕዘብ ለማስተዳደር ወይም ፖለቲካዊ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል አቅም፥ ስልጣን ነው። ለፖለቲካዊ አስተዳደር ወይም ለለውጥ የሚያስችለው አቅም ምንጩ የብዙሃኑ አመለካከት (public opinion) ነው።

የአንድ ሕዝብ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ያለውን በጥቅሉ የመንግስት ደጋፊና ተቃዋሚ በማለት ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። “የመንግስት ደጋፊ” በሚለው ጎራ ያለውን ማህብረሰብ በቀጥታ የመንግስት ደጋፊዎች እና መንግስትን በይፋ ባይደግፉ-የማይቃወሙ ናቸው። በተመሳሳይ፣ “የመንግስት ተቃዋሚዎች” የሚባሉት ደግሞ በቀጥታ የመንግስት ተቃዋሚዎች እና መንገስትን በይፋ ባይቃወሙ-የማይደግፉ ናቸው። በዚህ መሰረት፣ በስልጣን ላይ ያለ መንግስት ሀገሪቷንና ሕዝቡን መምራት የሚችለው አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የመንግስት ደጋፊ ወይም መንግስትን በይፋ ባይደግፍ እንኳን የማይቃወም ከሆነ ነው። ነገር ግን፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መንግስትን የሚቃወም ወይም በይፋ ባይቃወም እንኳን የማይደግፍ ከሆነ ፖለቲካዊ ስርዓቱ መቀየር ወይም መሻሻል አለበት።

አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መንግስትን የሚቃወምበት፣ በይፋ ባይቃወም እንኳን የማይደግፈበት መሰረታዊ ምክንያት የእኩልነት ጥያቄ ነው። የሰው ልጅ ፖለቲካዊ አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚመራው በእኩልነት መርህ ነው። እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር በእኩል አይን መታየት ይሻል። በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ዜጋ ከሌሎች እኩል መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ሊኖረው ይገባል። “እኩልነት” (equality) የዴሞራሲያዊ ስርዓት መርህና መመሪያ የሆነበት ምክንያት ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። በመሆኑም፣ ዴሞክራሲ የብዙሃንን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። በተቃራኒው፣ ጨቋኝ ወይም አምባገነን የሆነ መንግስታዊ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ነው። እንዲህ ያለ መንግስታዊ ስርዓት ባለበት ሀገር ዜጎች ያለማቋጥ የእኩልነት ጥያቄ ያነሳሉ።

በእርግጥ ገና ከአመሰራረቱ ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት የለም። ይሁን እንጂ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በየግዜው ከሕዝብ ለሚነሳው የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፤ ሥራና አሰራሩን ያሻሽላል። ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ግን በተለያየ ግዜ ከዜጎች የሚነሳውን የእኩልነት ጥያቄ በኃይል ለማፈን ጥረት ያደርጋል። ሆኖም ግን፣ የእኩልነት ጥያቄ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንደመሆኑ በሰው-ሰራሽ ኃይልና ጉልበት ማስቆምና ማስቀረት አይቻልም። ስለዚህ. የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ለውጥና መሻሻል ከማምጣት ይልቅ የዜጎችን ተፈጥሯዊ ፍላጎት በኃይል ለማፈን የሚሞክር መንግስት በራሱ ላይ ውድቀት እየደገሰ ነው። በመጀመሪያ በአመፅና ተቃውሞ የተጀመረ እንቅስቃሴ ቀስ-በቀስ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ያመራል። ከዚያ ቀጥሎ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ይከተላል። በመጨረሻም፣ በጉልበት ላይ የተመሰረተ መንግስት በተመሳሳይ ኃይል ከስልጣን ይወገዳል። በዚህ መልኩ፣ የሕዝቡ ንቅናቄ ከተቃውሞ ወደ አመፅ፣ ከአመፅ ወደ ሁከትና ብጥብጥ ተሸጋግሮ በመጨረሻ ስርዓት-አልበኝነትና ጦርነት እንዳያስከትል የፖለቲካ መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ መወጣት አለባቸው።

በብዙሃኑ አመለካከት ላይ ካላቸው ተፅዕኖ ወይም ኃይል አንፃር የፖለቲካ መሪዎችን ሚና ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። ቀደም ሲል እንደተገለፀው፣ የፖለቲካ ኃይል (political power) ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ በሚል ለሁለት ይከፈላል። በዚህ መሰረት፣ የዜጎችን መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ መሪዎች መንግስታዊ ስርዓቱን ለመቀየርና መምራት የሚያስችል ቀጥተኛ ኃይል (Active power) ያላቸው ሲሆን የስርዓቱ መሪዎች ግን ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል (Passive power) አላቸው። ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይል መንግስታዊ ስርዓቱን በቀጣይነት ለመምራት ወይም ለመቀየር የሚያስችል አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የሚደረገውን እንቅስቃሴ መቀበል ወይም አለመቃወም (Passive) ነው። ስለዚህ፣ የተቃዋሚ መሪዎች ኃይል የፖለቲካ ስርዓቱን ለመቀየር የሚያስችል ሲሆን የጨቋኝ ስርዓት መሪዎች ኃይል ግን የለውጡን እንቅስቃሴ መደገፍ ነው። ይሁን እንጂ፣ የሚፈለገው ለውጥ ለማምጣት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ኃይሎች እኩል አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው።

በተለያየ ግዜና ቦታ ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሳሉ። በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን የመንግስት ድርሻ የሕዝብን ጥያቄ በተገቢ ሁኔታ ተቀብሎ ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግ ነው። የሕዝቡን የለውጥና መሻሻል ጥያቄ በተገቢ ሁኔታ ለመመለስ የተቃዋሚ መሪዎች ንቅናቄውን ከፊት ሆነው መምራት ያለባቸው ሲሆን የስርዓቱ መሪዎች ደግሞ የለውጡን አይቀሬነት አውቀውና ተቀብለው ከዚህ ተፃራሪ የሆኑ ተግባራትን ከመፈፀም መታቀብ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን፣ የተቃዋሚ መሪዎች ለሞት፥ እስራትና ስደት በማድረግ ሕዝባዊ ንቅናቄውን መሪ-አልባ ካደረጉት፣ እንዲሁም ለውጡን የማይቀበሉና ለእንቅስቃሴው እንቅፋት የሚሆኑ ከሆነ የሀገሪቱ ፖለቲካ ሚዛኑን ይስታል።

የዜጎችን ጥያቄ በጉልበት ለማፈን መሞከር ውድቀትን ከማፋጠን የዘለለ ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም፣ የእኩልነት ጥያቄ በየግዜው የሚለኮስ እሳት ነው። እሳቱ በተለኮሰ ቁጥር እንደ ወርቅ መቅለጥ የተሳነው መንግስት እንደ አፈር ተፈረካክሶ ይወድቃል። ይህ ሲሆን የብዙሃኑን መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚል የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄ አቅጣጫውን በመሳት ወደ ሁከት፥ ብጥብጥ፥ ግጭትና ጦርነት ያመራል። ይህ እንዳይሆን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆኑ ኃይሎች እኩል አስፈላጊና ጠቃሚ ናቸው። የለውጡ መሪዎች ሕዝባዊ ንቅናቄው አቅጣጫውን እንዳይስት፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከበዳይ-ተበዳይ ስሜት ይልቅ በእኩልነትና ነፃነት መርህ መመራት አለበት። በሌላ በኩል፣ የስርዓቱ መሪዎች የለውጡን አይቀሬነት፥ የስርዓቱን ውድቀት አምኖ መቀበል፣ እንዲሁም ከለውጡ መሪዎች ጋር ያለ ቅድመ-ሁኔታ ለመወያየት ፍቃደኛና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። በዚህ መልኩ፣ ጨቋኝ ስርዓትን በዘላቂነት ማስወገድና በእኩልነት መርህ የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ይቻላል።

ከዚህ አንፃር፣ በደቡብ አፍሪካ የነበረው አፓርታይድ ስርዓት የወደቀበትና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተዘረጋበትን አግባብ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ብዙውን ግዜ ስለ አፓርታይድ ሲነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው የቀድሞ ፕረዜዳንት ኔልሰን ማንዴላ እና የ”ANC” ፓርቲ ናቸው። ነገር ግን፣ በደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲዘረጋ በወቅቱ የአፓርታይድ መንግስት ፕረዜዳንት የነበሩት “ከዲ ክለርክ” (F. W. de Klerk) እና ፓርቲያቸው “National Party” ከኔልሰን ማንዴላ እና “ANC” ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። ምክንያቱም፣ ሁለቱም ወገኖች የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድ በጋራ ጥረት ባያደርጉ ኖሮ በደቡብ አፍሪካ የጥቁሮችን እኩልነትና ነፃነት ማረጋገጥ አይቻልም ነበር።

በኔልሰን ማንዴላ መሪነት ሲካሄድ የነበረው የለውጥ ትግል በዋናነት የአፓርታይድ ስርዓትን ለማስወገድና የጥቁሮችን መብትና ነፃነት ለማረጋገጥ ነው። የጥቁሮችን መብትና ነፃነት እስካልተረጋገጠ ድረስ አመፅና ተቃውሞ በሂደት ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ እርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ማምራቱ አይቀርም። በመሆኑም፣ በሀገሪቱ የተከሰተው ግጭትና አለመረጋጋት ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት የአፓርታይድ ስርዓትን ማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት  መዘርጋት የግድ ነበር። ፕ/ት ዲ ክለርክ ደግሞ ይህን እውነት አምኖ ተቀብሎ ኔልሰን ማንዴላና ሌሎች የፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪዎችን ከእስር በመፍታት በደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ስለሚዘረጋበት ሁኔታ መወያየት ነበር። ለዚህ ደግሞ ዲ ክለርክ የአፓርታይድ መንግስት ፕረዜዳንት ሆነው ከተመረጡ ከጥቂት ወራት በኋላ እ.አ.አ. በ1990 ዓ.ም (ለነጮች) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ባደረጉት ንግግር እንዲህ ብለው ነበር፡-

“…only a negotiated understanding among the representative leaders of the entire population is able to ensure lasting peace. The alternative is growing violence, tension and conflict. That is unacceptable and in nobody’s interest. The well-being of all in this country is linked inextricably to the ability of the leaders to come to terms with one another on a new dispensation. No-one can escape this simple truth.” Transition (1990 – 1994) – Documents and Reports – 1990

አሁን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዜጎች የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ  በማንሳት ላይ ይገኛሉ። የኢህአዴግ መንግስት የለውጡን አይቀሬነት አውቆና ተቀብሎ ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን ጥረት እያደረገ ነው። ይህ የኢህአዴግ መንግስት የለውጡን አይቀሬነት አውቆና ተቀብሎ አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል አመራር እንደሌለው በግልፅ ይጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የፖለቲካ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችንና የመብት ተሟጋቾችን በሽብርተኝነት ወንጀል እየከሰሰ በማሰር ሕዝቡን መሪ-አልባ እያደረገው ይገኛል።

የኢትዮጲያ ፖለቲካ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በተለያዩ አከባቢዎች የሚታየው ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ሁከትና ብጥብጥ፣ ብሎም ወደ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት የማምራት እድሉ ከፍተኛ ነው። በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲና “የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪዎቹን ይበላል” ነበር ያሉት፡፡ መሪ-አልባ ሕዝብ ግን እርስ-በእርስ ያባላል (ይጋጫል)! ስለዚህ፣ ሀገሪቷን ከእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነት ለመታደግ ሲባል  የኢህአዴግ መንግስት ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እና የፀረ-ሽብር ሕጉንና ሌሎች አፋኝ ሕጎችን ማስወገድ አለበት፡፡ በመቀጠል፣ በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶችን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቭል ማህበራት፣ እንዲሁም ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ መወያየት አለበት። 

Advertisements

የኢህአዴግ ዕድሜ ማስረዘሚያ እና ማሳጠሪያ!

“የኢህአዴግ መንግስት ጨካኝ ወይስ ጨቋኝ” በሚለው ፅሁፍ ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰድ በዜጎች ሕይወት፥ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ተመልክተናል። በዜጎች ላይ እንዲህ ያለ የጭካኔ እርምጃ የሚወስደው ደግሞ እንደ ጨቋኝ ስርዓት የእኩልነት ጥያቄን ተቀብሎ ማስተናገድ ስለማይችል እንደሆነ በዝርዝር ተገልጿል። ስለዚህ፣ አምባገነናዊ መንግስት ለአመፅና ተቃውሞ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ የሚወስደው የሕልውና ጉዳይ ስለሆነበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ “የእንካ ግን አትንካ ፖለቲካ” በሚለው ፅሁፍ እንደተገለፀው፣ ሁሉም አምባገነን መንግስታት በጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፣ የመብት ተሟጋቾችና ተቃዋሚዎች ላይ የሆነ ኢ-ፍትሃዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተመልክተናል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የእነዚህ አካላት እንቅስቃሴ ከዜጎች የፖለቲካ መብትና ጥያቄ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ስለሆነ ነው።

የጨቋኝ ስርዓት የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፈልን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የቆመ ነው። ስለዚህ፣ የጨቋኙ ስርዓት ሕልውና ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እንዳያነሱ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው። ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ የማያነሱት ስለራሳቸው ሆነ ስለሌሎች ሰዎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት መረጃና ግንዛቤ ከሌላቸው ብቻ ነው። የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ከእነሱ የበለጠ መብትና ነፃነት እንዳለውና የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆነ ካላወቁ በስተቀር የእኩልነት ጥያቄ አያነሱም። በዚህ መሰረት፣ የተወሰኑ ሰዎች፥ ቡድኖች ወይም ማህብረሰብ ከእነሱ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሆኑ ሲያውቁ፣ ወይም ደግሞ ማግኘት ከሚገባቸው በታች እያገኙ እንደሆነ ሲያውቁ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ ማንሳት ይጀምራሉ።

ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እንዲያነሱ በቅድሚያ ስለ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እና ስለ መንግስት ስራና አሰራር ማውቅ አለባቸው። በተለያዩ አከባቢዎች ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ከራሳችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዞ ማየትና መገንዘብ ያስፈልጋል።  ስለዚህ፣ ዜጎች ስለራሳቸው መብትና ነፃነት፣ ስለ መንግስት ስራና አሰራር፣ በሌሎች አከባቢዎች ስላለው ጥቅምና ተጠቃሚነት ማወቅ አለባቸው። ይህ እንዲሆን ደግሞ፤ በተለያዩ አከባቢዎች ስላለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ትክክለኛ ሃሳብና መረጃ የሚያቀርቡ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች፣ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትንታኔ የሚቀርቡ የፖለቲካ ልሂቃንና ጦማሪያን (ፀኃፊዎች)፣ ስለ ዜጎች መብትና ነፃነት መከበር የሚወተውቱ የፖለቲካ መሪዎችና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች መኖር አለባቸው። እነዚህ አካላት በንቃት በሚንቀሳቀሱበት ሀገር ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን ጠንቅቀው ያውቃሉ፥ ይጠይቃሉ።

የመንግስት መሰረታዊ ዓላማ የሁሉንም ዜጎች መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። የጨቋኝ መንግስት መሰረታዊ ዓላማ ደግሞ የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ፣ የጨቋኝ ስርዓት ዓላማና ተግባር ከመሰረታዊ የመንግስት ዓላማና ፋይዳ ያፈነገጠ ነው። በመሆኑም፣ የጨቋኞች ስራና አሰራር ቀጣይነት እንዲኖረው እነሱና እነሱ ብቻ ሀገሪቷ መምራት አለባቸው። በተመሳሳይ፣ የጨቋኞች ስራና ተግባር በጥቂቶች መብትና ጥቅም ላይ ማዕከል ያደረገ እንደመሆኑ የሚናገሩት ሆነ የሚፅፉት ነገር በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተዓማኒነት አይኖረውም። ስለዚህ፣ ሃሳብና አመለካከታቸው በብዙሃን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ እነሱና እነሱ ብቻ መናገር አለባቸው።

በአጠቃላይ፣ የጨቋኝ ስርዓት ሕልውና ዜጎች እውነታን እንዳያውቁና እንዳይጠይቁ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለዚህ፣ ዜጎች ትክክለኛ እውነታውን እንዳያውቁና እንዳይጠይቁ ለማድረግ ከመንግስት በስተቀር ሌሎች መናገርና መፃፍ የለባቸውም። ከመንግስት አፈ-ቀላጤዎችና ቃል-አቀባዮች ውጪ ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን ከማዳመጥ የዘለለ ሚና ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ለዚህ ደግሞ ስለ መብት፥ ነፃነትና ተጠቃሚነት የሚናገሩ፥ የሚከራከሩ፥ የሚያስተምሩ፥… ወዘተ፣ በአጠቃላይ ከስርዓቱ መሪዎች ፍላጎትና ምርጫ ውጪ የሆነ ማንኛውም ዓይነት ሃሳብና አስተያየት የሚሰጡ ግለሰቦች፥ ቡድኖችና ተቋማት መወገድ አለባቸው።

በዚህ መሰረት፤ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ መኖር የለበትም፣ በእውነታ ላይ የተመሰረተ መረጃና ትችት የሚቀርቡ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መኖር የለባቸውም፣ የዜጎች መብትና ነፃነት እንዲከበር የሚወተውቱ የፖለቲካ መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች መኖር የለባቸውም። በአጠቃላይ፣ በጨቋኝ ስርዓት ስር የሚኖሩ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄ እንዳይጠይቁ ለማድረግ በቅድሚያ እንዳያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ “Anti-Terrorism Law (2009)”፣ እንደ ስዋዚላንድ (Swaziland) በ¨Suppression of Terrorism Act (STA)”፣ እንደ አንጎላ (Angola) “በState Security Law”፣…ወዘተ በመሳሰሉ አፋኝ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች አማካኝነት የግል ሚዲያዎችን፣ ጋዜጠኞችን፥ ጦማሪያንን፣ የመብት ተሟጋቾችንና የፖለቲካ መሪዎችን እስራትና ስደት ደብዛቸውን ማጥፋት ያስፈልጋል።

ለምሳሌ፣ “CPJ” የተባለው የጋዜጠኞ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጲያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ በወጣ የመጀመሪያ አምስት አመታት ውስጥ ብቻ 57 ጋዜጠኞች ሀገሪቱን ለቅቀው ወጥተዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት ውስጥ ነፃና ገለልተኛ የሚባል ሚዲያ ከሞላ-ጎደል ጠፍቷል፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሲቭል ማህበራት “የሉም” በሚባሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፣ ከታዋቂ እስከ ጀማሪ ፖለቲከኛ በሽብር ወንጀል ተከሰው ታስረዋል፣ ከዚያ የተረፉት ሀገር ለቀቅው ተሰድደዋል።

ይህ ሁሉ ግፍና በደል የኢትዮጲያ ሕዝብ መብቱንና ነፃነቱን እንዳያውቅና እንዳይጠይቅ ለማድረግ ሲባል የተፈፀመ ነው። ምክንያቱም፣ የኢህአዴግ እድሜ ሕዝብ እንዳያውቅና እንዳይጠይቅ በማድረግ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። በዚህ መሰረት፣ የኢትዮጲያ ሕዝብ መብቱን ማውቅና መጠየቅ ሲያቆም የኢህአዴግ እድሜ ይረዝማል፣ ሕዝብ መብቱን ማውቅና መጠየቅ ሲጀምር የኢህአዴግ እድሜ ያጥራል። “ታዲያ ምን ይሻላል?” የሚለውን በሌላ ግዜ እንመለስበታለን።

አብረን እየኖር ተለያይተናል: ነፃነት ያስፈልገናል! (ክፍል-2)

እስኪ ልጠይቅህ ወዳጄ፣…”ኢትዮጲያዊ ነህ?” መልስህ “አዎ” ከሆነ አንዴ ቆየኝ፣ “አይደለም” ከሆነ ደግሜ ልጠይቅህ፣ “እሺ…ምንድን ነህ?” ከዜግነት ይልቅ ብሔር አስቀድመህ፤ “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ፥ አማራ ነኝ፥ ትግራዋይ ነኝ፥ … ቀጥሎ ደግሞ ‘ኢትዮጲያዊ ነኝ’” ከሚሉት ጎራ ነህ። አሁንም መልስህ “አዎ” ከሆነ መልካም፣ አይደለም ከሆነ ደግሞ “ታዲያ አንተ ማን ነህ?” ከደርግ ቀይ-ሽብር ወይም ከኢህአዴግ ፀረ-ሽብር በተዓምር ተርፈህ አሊያም በዲቪ-ሎቶሪ ወይም በስዳት ሀገር ጥለህ የወጣህ? ….ማንነትህን የገለፅከው በተወለድክበት/በኖርክበት ሀገር፥ ብሔር፥ ሰፈር፥… ለእኔ ልዩነት የለውም።

ከአንተ ጋር አንድ ዓይነት ዜግነትና ዘውግ፣ የፖለቲካ እምነትና አመለካከት ላይኖረን ይችላል። ነገር ግን፣ የጋራ የሆነ የቀድሞ ታሪክ እና የወደፊት መፃዒ እድል አለን። ወደድነውም-ጠላነውም፣ ተቃወምነው-ደገፍነው፣ ጥሩም ሆነ መጥፎ የጋራ ታሪክ አለን። ስኬት ሆነ ውድቀት መፃዒ እድላችን የጋራ ነው። ዛሬ ላይ ብዙ ብንሆንም በቀድሞ ታሪካችንና በወደፊት እድላችን ግን አንድ ነን። በቃ ይሄው ነው! – “አንድነት” ማለት የዛሬ ልዩነት ሳይሆን የጋራ የሆነ ታሪክና የወደፊት ተስፋ ነው።

የጋራ የሆነ ታሪክና የወደፊት እጣ-ፈንታ ይኑረን እንጂ ትላንት በሆነው፣ ዛሬ ላይ እየሆነ ባለው እና ነገ በሚሆነው ነገር ላይ ተወያይተን፥ ተግባብተን ሆነ ተስማምተን አናውቅም። በቀድሞ ታሪካችን፣ በዛሬ ሕይወታችን አና በወደፊት ተስፋችን ዙሪያ መግባባት ቀርቶ መደማመጥ ተስኖናል። በእርግጥ ሁላችንም ቤተሰብ ብንሆንም ቤተሰባችን ግን “ደስተኛ” አይደለም። የቀድሞ ታሪካችን እና የወደፊት ዕድላችን አንድ ላይ የተሳሰረ ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን ተለያይተናል።

አዎ…እኛ ኢትዮጲያኖች ልክ እንደ ሊዮ ቶልስቶይ (Leo Tolstoy) “Broken Family” ሆነናል – “All happy families are alike; each unhappy family is unhappy in its own way.” አዎ…አንድ ላይ እየኖርን ተለያይተናል። እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል ራሱን ተበዳይ፣ ሌላውን ደግሞ በዳይ አድርጓል። ሁሉም በራሱ መንገድ ደስተኛ አይደለም። ይሁን እንጂ፣ ሁላችንም የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋና ምኞት አለን። ሁሉም የሚፈልገው ልውጥና መሻሻል፣ ሰላምና ደህንነት፣ እድገትና ብልፅግና፣ እኩልነት፥ ነፃነት፥ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሰፈነበት ፖለቲካዊ ስርዓት ነው፣…በዚህም እንደ ሌሎች “ደስተኛ ቤተሰብ” (happy family) መሆን እንሻለን። 

በእርግጥ ሁሉም “ደስተኛ ቤተሰብ” ግን ተመሳሳይ (alike) ነው። በተመሳሳይ፣ ሀገራችን እንደ በለፀጉ ሀገራት የዳበረ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስርዓት ቢኖራት የእኛም ቤተሰብ ልክ እንደነሱ ደስተኛ በሆነ ነበር። ስለዚህ፣ የበለፀጉ ሀገራት አሁን ካሉበት የእድገትና ብልፅግና ደረጃ ላይ የደረሱበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? እኛስ እነሱ ከደረሱበት የብልፅግና ደረጃ ላይ መድረስ የምንችለው፣ በዚህም ደስተኛ የሆነ ቤተሰብ የሚኖረን መቼና እንዴት ነው? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የምዕራባዊያን እድገትና ስልጣኔ ቁልፉን ፈልገን ማግኘት አለብን።

የምዕራባዊያን ስልጣኔ በስነ-እንቅስቃሴ (mechanization) ላይ የተመሰረተ ነው። ዛሬ ላይ በስፋት የምንጠቀምባቸው ውስብስብ ማሽንኖች የሁለትና ከዚያ በላይ ቀላል ማሽኖች ስብጥር ናቸው (Complex machines are merely combination of two or more simple machines)። ከሁሉም ማሽኖች የመጀመሪያው ደግሞ የግሪካዊው የሂሣብ ሊቅ “Archimedes” የማሽን መርህ ¨Lever Machine” የሚባለው ነው። ይህ ቀላል ማሽን በስነ-እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች መነሻ ነው። ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው፣ “Archimedes” ይህን ቀላል የሥነ-እንቅስቃሴ መርህ ተጠቅሞ መሬትን ብቻውን ማንቀሳቀስ እንደሚችል እንዲህ ሲል ገልጿል፤ ¨Give me a place to stand on, and I will move the earth.”

እ.አ.አ. በ1550ዎቹ ላይ በግሪክና ላቲን ቋንቋ ተፅፈው የተገኙት የ“Archimedes” መፅሃፍት በ16ኛውና 17ኛው ክፍለ ዘመን በነበሩት የሂሳብና ፊዝክስ ልሂቃን ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረገዋል። የአውሮፓ ሥልጣኔ የተመሰረተው በሳይንሳዊ ዘዴ (Scientific Method) ላይ ሲሆን የሳይንሳዊ አብዮት (Scientific Revolution) ከጀመሩት ውስጥ ደግሞ Galileo Galilei (1564-1642)፣ Rene Descartes (1596 – 1650) እና Johannes Kepler (1571 – 1630) በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው።  ሲሆን ከላይ እንደተገለፀው ሁለቱም የ“Archimedes” ተፅዕኖ ያረፈባቸው ናቸው። በአጠቃላይ፣ የ“Archimedes” የሥነ-እንቅስቃሴ ንድፈ-ሃሳብ ባይገኝ ኖሮ በምዕራብ አውሮፓ ከ1550 –  1650 ዓ.ም (እ.አ.አ.) በሂሳብና ሳይንስ የታይው እድገት በፍፁም አይታሰብም ነበር። 

በሥነ-አንቅስቃሴ ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተው ሳይንሳዊ ዘዴ በምዕራብ አውሮፓ በ16ኛውና 17ኛው ክፍለ ዘመን ለታየው የሳይንስ አብዮት ዋና ምክንያት መሆኑን ተመልክተናል። በተመሣሣይ፣ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአሜሪካና በአውሮፓ የታየው የፖለቲካ አብዮት በ”Archimedes” የሥነ-እንቅስቃሴ ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። “Edmund Burke” እ.አ.አ. የተባለው ልሂቅ የፈረንሳይ አብዮት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት በፃፈው ፅሁፍ የሥነ-እንቅስቃሴ ፅንሰ-ሃሳብ እንዴት በፖለቲከኞች ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል እንደሚከተለው ይገልፀዋል፡-

“A politician, to do great things, looks for a power… and if he finds that power, in politics as in mechanics, he cannot be at a loss to apply it.” Reflections On the Revolution in France, Page 121

እንደ “Edmund Burke” አገላለፅ፣ ልክ እንደ ሳይንሱ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት በሥነ-እንቅስቃሴ (mechanics) ውስጥ የተገኘው ኃይል በፖለቲካ ውስጥም ሊኖር ይገባል። ግሪካዊው “Archimedes” በ“Lever” ወይም “Simple mechanics” የሥነ-አንቅስቃሴ ዘዴ መሬትን ማንቀሳቀስ ይቻላል እንዳለው ሁሉ በፖለቲካውም ዘረፍ ሁሉንም ነገር በአንዴ ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ዘዴ ያስፈልጋል። እንግሊዛዊ ፈላስፋ “Thomas Paine” የ“Archimedes” የሥነ-እንቅስቃሴ ፅንሰ-ሃሳብ ለሳይንሳዊ አብዮት ዋና ኃይል እንደሆነ ሁሉ፣ “ነፃነት” የፖለቲካዊ አብዮት መነሻ ኃይል እንደሆነ እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“What Archimedes said of the mechanical powers, may be applied to Reason and Liberty. The revolution of America presented in politics what was only theory in mechanics. So deeply rooted were all the governments of the old world, and so effectually had the tyranny and the antiquity of habit established itself over the mind, that no beginning could be made in Asia, Africa, or Europe, to reform the political condition of man. Freedom had been hunted round the globe; reason was considered as rebellion; and the slavery of fear had made men afraid to think. But such is the irresistible nature of truth, that all it asks,- and all it wants,- is the liberty of appearing….” The Rights of Man, LONDON, Feb. 9, 1792 Page 89 – 92

የአውሮፓ ሥልጣኔ ግንባር ቀደም ሚና ያላቸው የአውሮፓ ፈላስፎች እና የአብዮት መሪዎች ትግላቸውን በአሜሪካ ነው የጀመሩት። ለዚህ ዋናው ምክንያት አሜሪካን ለፖለቲካዊ አብዮት እንደ ሰርቶ ማሳያ ለመጠቀም ነበር። በአሜሪካ ከተደረገው የተሳካ ሙከራ በኋላ በአውሮፓም ተመሳሳይ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መገንባት ተችሏል። በዚህም በቤተሰባዊ እና ሃይማኖታዊ መሰረት ላይ የቆመውን የአውሮፓ ፊዉዳላዊ ሥርዓት በግለሰብ ነፃነት (liberty) ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርገዋል። እዚህ ጋር እ.አ.አ. በ1789 የተካሄደው የፈረንሳይ አብዮት መሪ “Marquis de la Fayette” ስለ ነፃነት ያለውን መጥቀስ ያስፈልጋል፡-

“Call to mind the sentiments which nature has engraved on the heart of every citizen, and which take a new force when they are solemnly recognised by all:- For a nation to love liberty, it is sufficient that she knows it; and to be free, it is sufficient that she wills it.” (The Rights of Man, Part.1, page 14).  

አንድ ሀገር እድገትና ብልፅግና እንድትቀዳጅ፣ በእኩልነትና ነፃነት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዲኖራት በቅድሚያ ነፃነት ሊኖራት ይገባል። በአጠቃላይ፣ የሰው፥ የሀገርና የመንግስት ዓላማና ግብ “ነፃነት” ነው። ለዚህ ደግሞ ዜጎች፣ ሀገርና መንግስት በቅድሚያ ነፃነትን ማወቅና መፍቀድ አለባቸው። እያንዳንዱ ሰው የሕይወትን ትርጉምና ፋይዳ በግልፅ እንዲረዳ፣ ለራሱ የሚሰጠው ግምት እንዲሻሻልና የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋው እንዲኖረው፣ በቅድሚያ ስለ ነፃነት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል።

እናማ ወዳጄ፤ ከሀገር ዜግነት ይልቅ የብሔር ማንነት ያስቀደምከው፣ በቀይ-ሽብር ዘመቻ ሆነ በፀረ-ሽብር ሕጉ የተገፈፍከው፣ ከተወለድክበት ሀገር ይልቅ ስደት የመረጥከው፣…በነፃነት እጦት ነው። የጋራ ታሪክ እና መፃዒ እድል ይዘን ስለ ትላንት፥ ዛሬ ሆነ ነገ መወያየትና መግባባት ተስኖን፣ አንድ ላይ እየኖርን የተለያየነው ነፃነታችንን ተገፍፈን ነው። ትላንት ያልነበረን፣ ዛሬም ያጣነው፣ ነገም የምንሻው ነፃነትና ነፃነት ብቻ ነው። የዕውቀት መጀመሪያ ነፃነትን ማወቅ ነው!  

ከጨቋኝ መንግስት በፊት ጭቆናን የተቀበለ ሕዝብ መቀየር አለበት (ክፍል-1)

በአራት ተከታታይ ፅሁፎች “ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ትግል ከየትና እንዴት መጀመር አለበት?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ተሞክሯል። ከወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካ አንፃር ሲታይ በአብዛኞቹ የፖለቲካ ልሂቃን ዘንድ ቅድሚያ የተሰጠው በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትግል ስልት ነው። ይሁን እንጂ፣ “ብሔርተኝነት” በሚል መሪ ቃል፤ በክፍል አንድ ህዝብን ወደ ጦርነትና ጨቋኝ ስርዓት እንደሚወስድ፣ በክፍል ሁለት የሰው ልጅን ወደ አውሬነት እንደሚቀይር፣ በክፍል ሶስት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እንደማይጠቅም፣ እንዲሁም በክፍል አራት በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት የተካነበት የትግል ስልት እንደሆነ ለማሳየት ተሞክሯል። ከዚህ በመቀጠል ደግሞ “ነፃነት” በሚል መሪ ቃል በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሁሉን-አቀፍ የሰላማዊ ትግል አማራጭን በተከታታይ ክፍሎች እንመለከታለን። 

እርግጥ በነፃነት መኖር የማይፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። ይሁን እንጂ፣ “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” እንዲሉ ነፃነት’ም ካላወቁት አይናፍቅም። ነፃነትን የማያውቅ ሰው የነፃነትን ትርጉምና ፋይዳ አይረዳም። የራሱን ነፃነት አያስከብርም፣ የሌሎችን ነፃነት አያከብርም።ስለ ነፃነት ሙሉዕ ግንዛቤ የሌለው ሰው የሕይወትን ትርጉምና ፋይዳ እንኳን መገንዘብ አይችልም።

በመሰረቱ ነፃነት የሕይወት ትርጉም እና ፋይዳ ነው። የሰው-ልጅ ለሕይወት ያለው ስሜት አንፃራዊ ነፃነቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የሚገለፀው ባለው አንፃራዊ ነፃነት ነው። ሀብት እና ድህነት፤ መፈለግ እና አለመፈለግ፤ ሃይል እና ተገዢነት፤ ጤና እና በሽታ፤ ባህል እና አላዋቂነት፤ ሥራ እና ምቾት፤ ጥጋብ እና ረሃብ፤ መልካም እና መጥፎ፣ ሁሉም አንፃራዊ የነፃነት ማነስ እና መብዛት ውጤቶች ናቸው።

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ነፃነት” የሚለውን ቃል፤ “1ኛ፡- ሌላውን ሳይነኩ የፈለጉትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ፣ … መብት። 2ኛ፡- በባዕድ መንግስት ወይም በሌላ ሰው ቁጥጥር ስር አለመሆን። 3ኛ፡- ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት” እንደሆነ ይጠቅሳል። ሰው (person) ማለት ደግሞ በሃሳብ ወይም በተግባር ራሱን ወይም የሌሎች ሃሳብና ተግባር ወክሎ የሚንቀሳቀስ ነው። በራስ ወይም በሌሎች ሰዎች ፍላጎት መሰረት እየሰሩ፥ እየተናገሩ፥ እየፃፉ፣… በራስ ወይም በሌሎች ፍቃድ እየተንቀሳቀሱ እና ራስን-በራስ እያስተዳደሩ ወይም በሌሎች እየተመሩ መኖር ደግሞ “ሕይወት” ይባላል።

በዚህ መሰረት፣ ሕይወት ማለት እንደ ራስ ፍላጎትና ፍቃድ ወይም በሌሎች ፍላጎትና ፍቃድ መሰረት የሚተውኑባት ቤተ-ተውኔት ወይም ቲያትር (theatre) ናት! በሕይወት ውስጥ እያንዳንዱ ግለሰብ ተዋናይ (Actor) ነው። በእንግሊዘኛ “person” የሚለው ቃል ሥርዖ ቃሉ “persona” የሚለው የላቲን ቃል ሲሆን በመድረክ ላይ ያለ ሰው ውጫዊ ገፅታ ወይም መልክ “outward appearance of a man, counterfeited on the stage” የሚል ፍቺ አለው። ስለዚህ፣ ሰው (person) በሕይወት ትያቲር ላይ የራሱን ወይም የሌላን ሰው ገፀ-ባህሪ በመወከል የሚተውን (personate) ነው።

ሰው የተፈጥሮ (Natural Person) እና ሰው-ሰራሽ (Artificial person) በሚል ለሁለት ይከፈላል። የተፈጥሮ ሰው በራሱ የተውኔቱ ደራሲ (author) እና ተዋናይ (actor) ሊሆን ይችላል። “ሰው-ሰራሽ” ሰው ግን የተፈጥሮ ሰዎች ገፀ-ባህሪን በመወከል የሚተውን ተዋናይ (actor) ነው። “Thomas Hobbes” የተፈጥሮ እና ሰው-ሰራሽ ሰዎች በሕይወት ቲያትር ውስጥ ያላቸውን ሚና እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡-

“Of persons artificial, some have their words and actions owned by those whom they represent. And then the person is the actor, and he that owneth his words and actions is the author, in which case the actor acteth by authority. So that by authority is always understood a right of doing any act; and done by authority, done by commission or license from him whose right it is.” Leviathan – Thomas Hobbes, Page 84

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ “authority” የሚለው ቃል ሥርዖ-ቃሉ “author” የሚለው ቃል ነው። ስለዚህ፣ በአማርኛ “ስልጣን” (authority) ማለት አንድን ነገር ለማድረግ፣ ለመስራት፣ ወይም ለማሰራት የሚያስችል መብት ነው። “ባለስልጣን” ማለት ደግሞ፤ “አንድን ነገር ለማድረግ፥ ለመስራት፥ ወይም ለማሰራት ኣመራርን ለመስጠት፥ ለመወሰን የሚያስችል መብት ያለው ግለሰብ ወይም ድርጅት” ማለት ነው። በአጠቃላይ፣ “ስልጣን” ማለት በተፈጥሮ ወይም በውክልና የተሰጠና አንድን ነገር ለማድረግ፣ ለመስራት፣ ወይም ለማሰራት የሚያስችል “መብት” (right) ነው።

የመንግስት ስልጣን ከእያንዳንዱና ከሁሉም ዜጎች በውክልና የተሰጠ ሀገሪቷንና ሕዝቡን ለመምራት የሚያስችል መብት (authority) ነው። እንደ “Thomas Hobbes” አገላለፅ፣ “መንግስት” ማለት እያንዳንዱ ዜጋ ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ጋር በመስማማት፤ “1ኛ፡- የሌላውን መብት ሳይነካ የፈለገውን ነገር እየሰራ፣ እየተናገረና እየፃፈ በሰላም በሀገሩ እንዲኖር፣ እና 2ኛ፡- በባዕድ ሀገር መንግስት ወይም በሌላ ሰው በኃይል ተገዢ እንዳይሆን ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግለት፣ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን “ራስን በራስ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን፥ መብት”ን በውክልና ለተወሰኑ ሰዎች በመስጠት የፈጠረው አካል ነው።

በመጨረሻም ወደ ፅኁፉ ዋና ነጥብ ስንመለስ፣ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት በተለይ ባለፉት አስር አመታት የባሰ ጨቋኝና አምባገነን እየሆነ መምጣቱ እርግጥ ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በኃይል ታፍኗል። በመሆኑም፣ ይህን ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ከስልጣን በማስወገድ የዜጎች ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት አለበት የሚል አመለካከት በሰፊው ይንፀባረቃል። ነገር ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት ሆነ ሌላ ማንኛውም መንግስት ከእያንዳንዱና ከሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ከተሰጠው ፍቃድና ውክልና ውጪ ምንም ነገር የማድረግ ስልጣን የለውም።

በመሰረቱ፣ የኢህአዴግ መንግስት በሕዝብ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የሆነ ተግባር መፈፀም አይችልም። ሕገ-መንግስት ደግሞ በሀገሪቱ ሕዝብና በመንግስት መካከል የተፈረመ የውል ሰነድ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ሰው (person) እንደመሆኑ መጠን በራሱ ፍላጎት መሰረት እየሰራ፥ እየተናገረና እየፃፈ እና በራሱ ፍቃድ እየተንቀሳቀሰ ለመኖር እንዲችል ራሱን በራሱ የማስተዳደር፥ የመምራት መብትና ስልጣኑን ለመንግስት አሳልፎ ሰጥቷል። የኢህአዴግ መንግስት እንዲያስከብር የተሰጠውን ስልጣን የዜጎችን በነፃነት የመስራት፣ የመናገር፣ የመፃፍና የመንቀሳቀስ መብት ለመገደብ አውሎታል። የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት አስር አመታት በሕገ-መንግስቱ መሰረት ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ ሲንቀሳቀስ ውክልና የሰጠው የኢትዮጲያ ሕዝብ ምን ዓይነት እርምጃ ወሰደ?

በእርግጥ የኢህአዴግ መንግስት እንደ መንግስት በእያንዳንዱና በሁሉም ዜጎች ተፅፎ የተሰጠውን ቲያትር ከመተወን ባለፈ አዲስ ተውኔት የመፃፍና የመተውን ስልጣን የለውም። ነገር ግን፣ ለምሳሌ፣ የፀረ-ሽብር ሕጉን ሲያፀድቅና በዚህም በሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለእስር፣ ለስቃይና ለስደት ሲዳርግ የኢትዮጲያ ህዝብ “በውል ከተሰጠህ ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ አዋጅና መመሪያ አውጥተሃል” በሚል ውክልናውን አነሳ? በውሉ መሰረት ለመንግስት የሚከፍለውን ግብር አቋረጠ? ጥቂቶች ሺህዎች ለሞት፥ እስርና ስደት ሲዳረጉ ብዙ ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጲያ ሕዝብ መብትና ነፃነቱን ለማስከበር ምን ያህል እርምጃ ተራመደ።

ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ነፃነቱን አውቆ በራሱና ለራሱ ማስከበር እስካልቻለ ድረስ የኢህአዴግ መንግስት ተቀየረ፥ አልተቀየረ ምን ፋይዳ አለው? የደርግ ሆነ የኢህአዴግ መንግስት መብትና ነፃነቱን ከማረጋገጥ ይልቅ በደልና ጭቆና ሲፈፅሙበት አሜን ብሎ የተቀበለ ማህብረሰብ ሌላ መንግስት ቢመጣ-ባይመጣ ምን ለውጥ አለው? ትላንትና ዛሬ መብትና ነፃነቱን መብትና ነፃነቱን በራሱ ማስከበር የተሳነው ማህብረሰብ የኢህአዴግ መንግስት ከስልጣን ቢወገድ-ባይወገድ ምን የተለየ ነገር ይኖራል። መብትና ነፃነቱን እንዲከበር ሆነ እንዳይከበር ያደረገው መንግስት ሳይሆን ዋናው የስልጣን ባለቤት “ሕዝብ” ነው። ጨቋኝ ስርዓት ባለበት ሀገር ጭቆናን አምኖ የተቀበለ ማህብረሰብ አለ። በእርግጥ “ጨቋኝ” መባል ያለበት ጭቆናን ፈቅዶ የተቀበለ ነው። ሰጪ በሌለበት ተቀባይ አይኖርም። ስለዚህ፣ ጨቋኝ ህዝብ እንጂ ጨቋኝ መንግስት ብሎ ነገር የለም።   

በአጠቃላይ፣ መንግስት ሕዝብ እንደፈቀደለት ነው የሚሆነው። ለመብቱና ነፃነቱ የሚከራከር ጠያቂ ማህብረሰብ ባለበት መንግስት ወዶ ሳይሆን በግዱ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል። አለበለዚያ ሕዝብ ውክልናውን ስለሚያነሳበት የስርዓቱ ሕልውና ያከትማል። ስለዚህ፣ ዋናው ነገር መንግስትን መቀየር ሳይሆን ሕዝብን መቀየር ነው። ቁም ነገሩ ያለው ሕዝብ መብትና ነፃነቱን አውቆ በራሱ እንዲያስከብር ማድረጉ ላይ ነው። ሕዝብ ስለ መብቱና ነፃነቱ ያለውን ግንዛቤ በመቀየርና ጠያቂ የሆነ ማህብረሰብ መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ መንግስት መቀያየሩ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” የሚሉት አይነት ነው።

የሰቆቃ ልጆች ክፍል-4፡ የመንግስት ደጋፊ ምሁራን “የጭቆና ፈረሶች” ናቸው! 

4.1 ምሁርና ብሔር

እንደ አይሁዶች ወይም የደቡብ አፍሪካ ነጮች የራሱን ሀገርና መንግስት ለመመስረት፣ እንደ አልጄሪያ ከቅኝ-አገዛዝ ነፃ ለመወጣት፣ ወይም ደግሞ እንደ ኢትዮጲያ ወታደራዊ መንግስትን ከስልጣን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ውስጥ የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት ምን መሆን አለበት? በእርግጥ የምሁራን ስራና ተግባር በብሔር፣ ዘር ወይም ሀገር ሊገደብ አይገባም። ነገር ግን፣ የመጡበት ማህብረሰብ በጨቋኝ ስርዓት ግፍና በደል ሲፈፀምበት ግን በዝምታ ማለፍ አይቻላቸውም።

እያንዳንዱ ምሁር ከተወለደበትና ካደገበት ማህብረሰብ ጋር ያለው ቁርኝት ከየትኛውም ሙያዊ ግዴታና ስነ-ምግባር የበለጠ ጠንካራ ነው። ስለዚህ፣ አንድ ምሁር በተወለደበት ማህብረሰብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን ወደ ጎን ትቶ ማለፍ አይቻልም። በአንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ምሁራን በሙያተኝነት (professionalism) ስም ገለልተኛ መሆንና በደልና ጭቆናን በዝምታ ማለፍ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። ከዚያ ይልቅ፣ ማህብረቡን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ባላቸው አቅምና ባገኙት አጋጣሚ አስተዋፅዖ ማበርከት አለባቸው።

ነገር ግን፣ ጨቋኙ ስርዓት ሲወገድና የሚደግፉት የፖለቲካ ቡድን ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት ፍፁም መቀየር አለበት። ጨቋኝ ስርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣ የፖለቲካ ኃይል ስለ ቀድሞ ታሪኩ፣ አሁን ላይ ስላለው ሥራና አሰራር፣ ወይም ስለ ወደፊት አቅጣጫና ዕቅዱ ለመግለፅ አስፈላጊ የሆነ መንግስታዊ መዋቅርና ተቋማት አሉት። ለዚህ ተግባር የተመደበ የሰው ኃይልና ካፒታል ይኖረዋል። ስለዚህ፣ ምሁራን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ሥራና ተግባር እያጎሉ መናገርና መመስከር የምሁራኑ ድርሻና ኃላፊነት አይደለም።

4.2 የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት

የምሁራን ድርሻና ኃላፊነት በማህብረሰቡ ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አጉልቶ በማውጣት የግንዛቤና አመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መስራት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ነቅሶ በማውጣት እንዲስተካከሉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች አንፃር ሲታይ ምሁራን በሙያቸው ችግሮችን ቀድሞ የመለየትና መፍትሄያቸውን የመረዳት ብቃት አላቸው። እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ሙያዊ ትንታኔ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ነው።

እንኳን በጦርነት በሕዝብ ምርጫ ራሱ ወደ ስልጣን የመጡ የመንግስት ኃላፊዎችና የሕዝብ ተወካዮች ለሥራው የሚያስፈልገው በቂ ዕውቀትና ክህሎት የላቸውም። አብዛኛውን ግዜ የፖለቲካ ስልጣን የሚጨብጡ ሰዎች ሕዝብን የማደራጀትና የመቀስቀስ አቅም እንጂ ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ስላላቸው አይደለም። “John Stuart Mill” ስለ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አመሰራረትና አሰራር በሚተነትነው መፅሃፉ “Of the Proper Functions of Representative Bodies” በሚለው ክፍል ፅንሰ-ሃሳቡን እንዲህ ገልፆታል፡-

“….the very fact which most unfits such bodies for a Council of Legislation qualifies them the more for their other office- namely, that they are not a selection of the greatest political minds in the country, from whose opinions little could with certainty be inferred concerning those of the nation, but are, when properly constituted, a fair sample of every grade of intellect among the people which is at all entitled to a voice in public affairs. Their part is to indicate wants, to be an organ for popular demands, and a place of adverse discussion for all opinions relating to public matters, both great and small; and, along with this, to check by criticism, and eventually by withdrawing their support, those high public officers who really conduct the public business.”  Representative Government, Ch.5: Page  59

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሊኖር የሚቻለው በፖለቲከኞች/የፖለቲካ ቡድኖች እና በምሁራን መካከል ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ መቀጠል ሲችል ነው። በመሰረቱ፣ የፖለቲከኞች መደበኛ ስራ ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር ነው። የምሁራን ድርሻ ደግሞ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የመንግስት ፖለቲካዊ አመራርና አስተዳደር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል ነው።

ከዚህ አንፃር፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚችሉት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሚያደርጓቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እና በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና የሚስተካከሉበትን አማራጭ የመፍትሄ ሃሳቦችን ማቅረብ ነው። የፖለቲካ ስልጣን ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ከምሁራን የተሰጣቸውን ሃሳብና አስተያየት ተቀብለው በሀገሪቱና በሕዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚስተዋሉ ከፍተቶችን ለማስወገድ የፖለቲካ አመራር መስጠትና አስተዳደራዊ ስርዓቱን ማሻሻል ነው።

በዚህ መሰረት፣ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ከተወጡ በመንግስት ሥራዎችና አስራሮች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ወዲያው ይስተካከላሉ። መንግስት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ይሰጣል። የመንግስት ስራና አሰራር ግልፅነት እና ተጠያቂነት ይኖረዋል። የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጡ የብዙሃኑን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ይሆናል። ስለዚህ፣ ምሁራን ድርሻና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሲወጡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ላይ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ይኖራል።

ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ለዘላቂ ልማት፣ ለአስተማማኝ ሰላም እና ለዳበረ ዴሞክራሲ መሰረት ይሆናል። ያለ ምሁራን ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ፣ እንደ “John Stuart Mill” አገላለፅ፣ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ምሁራን ሕግ አውጪዎች የሚያፀድቋቸውን አዋጆች፣ የሕግ አስባሪዎች አሰራርና የፍትህ ስርዓቱ ገለልተኝነትን፣ የሕግ አስፈፃሚዎች የሚያሳልፏቸውን የአፈፃፀም መመሪያዎችና ደንቦች፣ በአጠቃላይ የመንግስት አካላት ሥራና አሰራርን አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ከሙያው አንፃር መተንተን፣ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦችን እያነሱ መወያየትና በኃላፊዎችና በሕብረተሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መጠቆም አለባቸው።

4.3 “የጭቆና ፈረሶች”

በእርግጥ ምሁራን እንደ ማንኛውም ዜጋ የመንግስት ባለስልጣን ሆነው መስራት ይችላሉ። ይህ ሲሆን እንደ ማንኛውም ባለስልጣን የመንግስትን ሥራና ተግባር ደግፈው ሃሳብና አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። የመንግስት ተሿሚ ወይም ባለስልጣን ካልሆኑ ግን የሕዝብን ድምፅ ተቀብለው ማስተጋባት አለባቸው። በዚህ መሰረት፣ የመንግስት ሰራተኛ ሆነ የግል ድርጅት ተቀጣሪ፣ እያንዳንዱ ምሁር ያለውን ሙያዊ ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ በተለይ የመንግስትን ስራና አሰራር የመተቸት ማህበራዊ ግዴታ አለበት።

ከዚህ በተቃራኒ፣ መሰረታዊ ችግር ያለባቸው አዋጆች፥ እቅዶችና ውሳኔዎች በተለያዩ የመንግስት አካላት ተግባራዊ ሲደረጉ እያዩ በዝምታ የሚያልፉ ሰዎች እንደ ምሁር ያለባቸውን ማህበራዊ ግዴታ እየተወጡ አይደለም። በተለይ የሕዝብ ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን እያጣጣሉ፣ የመንግስትን ስራና ተግባር እያጋነኑ የሚያቀርቡ፣ ከመንግስት ኃላፊዎች በላይ የመንግስት ጠበቃና ደጋፊ ለመሆን የሚቃጣቸው ሰዎች “ምሁር” ለሚለው የክብር ስያሜ አይመጥኑም።  

ምሁራን በዜጎች ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለውጥ ማምጣት፣ እንዲሁም የመንግስት ስራና አሰራር ማሻሻል የሚችሉት፣ በአጠቃላይ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም እንዲረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት የሚችሉት ራሳቸውን ከመንግስት ሲነጥሉ ነው። ልክ እንደ የመንግስት ተሿሚ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ፣ ጥሩን እያጋነኑ፥ መጥፎውን እየሸፋፈኑ የሚያቀርቡ ከሆነ፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰትን በማጣጣል የመንግስትን ጥሩ ምግባር አጉልተው ለማውጣት የሚጥሩ ከሆነ፣ ከሕዝብ ይልቅ በመንግስት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ የከፋ ነው። ምሁራን በደጋፊነት ስም ራሳቸውን ከመንግስት ጋር ማጣበቃቸው በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት “John Stuart Mill” እንዲህ ገልፆታል፡-   

“Nothing but the restriction of the function of representative bodies within these rational limits will enable the benefits of popular control to be enjoyed in conjunction with the no less important requisites of skilled legislation and administration. There are no means of combining these benefits except by separating the functions which guarantee the one from those which essentially require the other; by disjoining the office of control and criticism from the actual conduct of affairs, and devolving the former on the representatives of the Many, while securing for the latter, under strict responsibility to the nation, the acquired knowledge and practised intelligence of a specially trained and experienced Few.” Representative Government, Ch.5: P.59

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ምሁራን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሚያሳልፋቸው የብዙሃኑን እኩልነትና ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ እቅዶችና ውሳኔዎች እንዳይሻሻሉ፣ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዳይደረግባቸው፣ የሕዝብ ጥየቄዎችና ቅሬታዎችን እንዳይሰማ፣ እንዲሁም የመንግስት ኃላፊዎች ያለባቸውን የግንዛቤ እና የብቃት ማነስ ችግር እንዳይቀርፉ እንቅፋት ናቸው።

ምሁራን የመንግስትን እርምጃዎችን በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ሙያተኝነት ስም ገለልተኛ መስለው ለማለፍ መሞከራቸው በራሱ በህዝብ ላይ የሚፈፀም በደልና ጭቆናን እንደመደገፍ ይቆጠራል። ስለዚህ፣ በገለልተኝነት (neutrality) ስም መንግስትን ከመተቸት የሚቆጠቡ ምሁራን “የመንግስት ደጋፊ ነን” ከሚሉት በምንም የተለዩ አይደሉም።

እንደ ምሁር ከማህብረሰቡ የተጣለባቸውን ግዴታና ኃላፊነት አልተወጡም። በማህበራዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማንሳት የግንዛቤና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚያስከትሉትን ጭቅጭቅና ውዝግብ በመፍራት ማህበራዊ ግዴታቸውን የማይወጡ፣ “ፖለቲካ እሳት ነው!” የሚለውን ያረጀ አባባል እየደጋገሙ ጥግጥጉን የሚሄዱ ሰዎች ትክክለኛ መጠሪያቸው “ምሁራን” ሳይሆን “ፈሪዎች” የሚለው ነው።

በአጠቃላይ፣ “ምሁር” ለመባል በቅድሚያ እንደ ምሁር የተጣለብንን ማህበራዊ ግዴታ መወጣት ያስፈልጋል። ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈራ ወይም መንግስትን ለማሞገስ የሚተጋ ሰው “ምሁር” ለሚለው የከብር መጠሪያ አይመጥንም። ከዚያ ይልቅ፣ የመንግስት ደጋፊዎች ሕሊናቸው በጥቅም ሱስ ተለጉሞ፣ እንዲሁም መንግስትን ለመተቸት የሚፈሩት ደግሞ አንደበታቸው በፍርሃት ቆፈን ተለጉሞ፣ ጭቋኝ ስርዓትን በጀርባቸው ተሸክመው የሚጋልቡ “ፈረሶች” ናቸው። ወታዳራዊ ፋሽስቶች፣ አምባገነኖች፣ የአፓርታይድ ስርዓት አራማጆች፣ …ወዘተ በሕዝብ ላይ አሰቃቂ በደልና ጭፍጨፋ የሚፈፅሙት እነዚህን “የጭቆና ፈረሶች” እያጋለቡ ነው።

ያልተዘጋ እሰር ቤት ውስጥ ነፃነት ያስፈራል!

ከእስር ቤት የወጣሁ ሰሞን ወደ አንድ ባለሱቅ ደበኛዬ ጋር ስሄድ “እንኳን ለቤትህ አበቃህ….” እያለ አገላብጦ ከሳመኝ በኋላ “እኛ እኮ ‘እንትን’ ትመስለን ነበር” አለኝ። “‘እንትን’ ማለት ምን?” አልኩት። ፈራ-ተባ እያለ “እኛ እኮ የመንግስት ጆሮ-ጠቢ፥ ሰላይ ትመስለን ነበር” ሲለኝ ክት ብዬ ሳቅኩ። እንዲህ ማሰቡ በራሱ በጣም ገረመኝና “ያምሃል እንዴ? እስኪ አሁን እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” አልኩትና መልሱን ሳልጠብቅ ሄድኩ።

ከሳምንት በኋላ ደግሞ ለሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ከእኔ ጋር የአብሮነት ቆይታ ካላቸው ጓደኞቼ ጋር እየተጨዋወትን ሳለ ከመሃላቸው አንዱ “አይ ስዬ…እኔ እኮ ከእነሱ ጋር ትመስለኝ ነበር?” አለኝ። የረጅም ግዜ ጓደኛህ እንዲህ በጥርጣሬ ዓይን እያየህ መቆየቱን ስታውቅ የሆነ በቃ ያበሳጫል። “እንዴ… አንተ እንዴት ነው እንዲህ የምታስበው?” አልኩትና ወደ ሌሎቹ ዞሬ “ቆይ አንዴ ሁላችሁም…” ስል የሁሉም ትኩረት እኔ ላይ ሆነ። ከዚያ “ቆይ ከእናንተ ውስጥ ‘ስዬ ሰላይ ነው’ ብሎ የሚያስብ ነበረ?” እላቸዋለሁ ሁሉም በአንድ ድምፅ “አዎ!” አሉኝ።

ምላሻቸው ከማስገረም አልፎ አስደነገጠኝ። በለሆሳስ “ቆይ እኔ ምኔ ነው ሰላይ የሚመስለው?” ብዬ በውስጤ ማሰላሰል ስጀምር ከጎኔ የነበረው ጓደኛዬ “ቆይ ስዬ…አንተ ራስህ፣ ይህን ያህል ዓመት በነፃነት የፈለከውን እየተናገርክና እየፃፍክ ስትኖር ‘አለመፍራትህ በራሱ ሌላን ሰው አያስፈራም?’ እንደዛ በነፃነት ስትናገርና ስትፅፍ ሁላችንም ‘በቃ… ከኋላው የሆነ ነገር ቢኖር ነው’ ብለን አሰብን። ይሄ’ኮ አንተ የተለየ ነገር ስላደረክ ወይም ከሌሎቻችን በተለየ አንተን አለማመን አይደለም። እንደዛ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ከሁላችንም በተለየ አንተ ብቻ “ነፃ” ስትሆን አያስጠረጥርም ልትለኝ ነው?”

ይህ ከሆነ አምስት ወራት አለፉ። ነገር ግን፣ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስለኝ ነበር” የምትለዋ ጥያቄ ቀጥላለች። ዛሬ ምሳ ሰዓት ላይ ወደ ቤት እየሄድኩ ሳለ አንድ መስፍን የሚባል ጓደኛዬ አገኘኝና “ስዬ…ድሮ እኮ እንፈራህ ነበር” አለኝ። “ለምን?” እለዋለሁ “ያኔ’ኮ ‘እንትን’ ትመስ…” አላስጨረስኩትም! ወደ ቤት እንደገባሁ ይህን ፅሁፍ መፃፍ ጀመርኩ።

በመጀመሪያ ደረጃ ያለኝ ፖለቲካ አቋምና አመለካከት ትክክለኝነቱ የሚረጋገጠው በየእለቱ በማንፀባርቀው ሃሳብና በምሰራው ሥራ ሳይሆን በመታሰሬ መሆኑ በራሱ ያበሳጫል። ነገር ግን፣ ለራሱ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ “ባልተዘጋ እስር ቤት” ውስጥ እየኖረ እንደ እኔ “ታስሮ ለተፈታ” ሰው ከንፈሩን ሲመጥ ማየት በጣም ይገርማል። ኧረ እንደውም ከማስገረም አልፎ አንዳንዴ እንደ እብድ ለብቻ ያስቃል።

“‘እንትን’ ትመስለን ነበር” ሲሉ “ሰላይ ወይም የመንግስት ጆሮ-ጠቢ” ለማለት እንደሆነ ግልፅ ነው። ጥያቄው በጓደኞቼ ውስጥ የነበረውን ስጋትና ፍርሃት ያስከተለው ጥርጣሬን ያሳያል። እኔን የጠረጠሩበት ምክንያት ከሌሎች በተለየ መልኩ ሃሳብና አመለካከቴን በነፃነት በመግለፄ ነው። በእርግጥ ሁላችንም የራሳችንን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ እንሻለን። እንዲህ ያለ ነፃነት ለእስርና እንግልት እንደሚዳርግ ደግሞ እናውቃለን። ስለዚህ፣ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት የሚገልጽ ሰው እንደሚታሰር ይጠብቃሉ። ካልታሰረ ደግሞ “‘እንትን’ ቢሆን ነው” ብለው ይጠረጥራሉ።

ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ለመግለፅ የሚፈሩት ሆነ የሌሎችን ነፃነት የሚጠራጠሩት መንግስትን ስለሚፈሩ ነው። ይሁን እንጂ፣ እንደ ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Montesquieu” አገላለፅ፣ መንግስት የተፈጠረበት መሰረታዊ ዓላማ ዜጎች እርስ-በእርስ አንዳይፈራሩ ነው፡-

“The political liberty of the subject is a tranquility of mind arising from the opinion each person has of his safety. In order to have this liberty, it is requisite the government be so constituted as one man need not be afraid of another.” Baron de Montesquieu, The Spirit of Laws, trans. Thomas Nugent, 2 vols. (New York: The Colonial Press, 1899), 1:151–162.

የመንግስት ሥራና ተግባር ዜጎች እርስ-በእርስ ሳይፈራሩ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት አንዲገልፁ ማስቻል ነው። ሆኖም ግን፣ በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ዜጎች የራሳቸውን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት መግለፅ ይቅርና የጥቂቶች ነፃነት ብዙሃኑን ለስጋትና ጥርጣሬ እየዳረገው ይገኛል። ይህ የሆነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የተፈጠረበትን መሰረታዊ ዓላማ ስለሳተ ነው። መንግስታዊ ሥርዓቱ የዜጎችን መብትና ነፃነት ከማስከበር ይልቅ መንግስትን ሕዝቡን የሚፈራና ሕዝቡም እርስ-በእርስ እንዲፈራራ የሚያደርግ ስለሆነ ነው። በመሰረቱ ፍርሃት ለፍፁም አምባገነናዊ መንግስት የተግባር መመሪያና መርህ ነው፡-

“In a tyranny, the moving and guiding principle of action is fear. Fear in a tyranny is not only the subjects’ fear of the tyrant, but the tyrant’s fear of his subjects as well. [It] is not merely a psychological motive, but the very criteria according to which all public life is led and judged.”  On the Nature of Totalitarianism: An Essay in Understanding

በዚህ መሰረት፣ መንግስትን በመፍራት ሆነ በመጠራጠር፣ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ከመግለፅ የሚቆጠቡ ሰዎች በሙሉ በፍርሃት መርህና መመሪያ መሰረት ለሚመራው ሥርዓት ተገዢዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ስርዓቱን በስልጣን ላይ ለማቆየት የመሚያስፈልገውን ፍርሃት እየለገሱ ስለሆነ እንደ ቀንደኛ ደጋፊ መታየት አለባቸው።

ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ሌሎች በተደጋጋሚ ለእስርና እንግልት የሚዳረጉት በራሳቸው ያጠፉት ጥፋት ወይም የፈፀሙት ወንጀል ስላለ አይደለም። የአምባገነናዊ መንግስት ዓላማም እነሱን በማሰቃየትና በማስፈራራት ወደፊት ለሥርዓቱ ተገዢ እንዲሆኑ ለማድረግ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደ እነሱ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ እንዳይሞክር ለማስፈራራት ነው።

ብዙ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን እስር ቤት ውስጥ የተዘጋባቸው ከእስር ቤት ሲወጡ ነፃነታቸውን ስለሚቀዳጁ ነው። በዚህም፣ ከእስር ቤት ውጪ ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ስለሚገልፁና ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ልክ እንደነሱ ነፃነቱን እንዲቀዳጁ ፈር-ስለሚቀዱ ለእስር ይዳረጋሉ። ምክንያቱም፣ እነዚህ ሰዎች ነፃነታቸውን የሚያጡት እስር ቤት ሲገቡ ብቻ ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ከእስር ቤት ውጪ ሀኖ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ያለን ሰው ማሰርና ማሰቃየት አስፈላጊ አይደለም። በመኖሪያ ቤቱ እና በስራ ቦታ ሃሳብና አመለካከቱን በነፃነት ለመግለጽ የሚፈራ ሰው ባልተዘጋ እስር ቤት ውስጥ ራሱን ያሰረ ስለሆነ ድጋሜ ማሰር አያስፈልግም። ከዚህ በተጨማሪ፣ ፍርሃትን ማስፈን ለሚሻ ስርዓት ፈሪዎች ወዳጆቹና ደጋፊዎቹ ናቸው። በአጠቃላይ፣ ፀኃፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በተደጋጋሚ የሚታሰሩት አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ሃሳብና አመለካከቱን ለመግለፅ፣ መብትና ነፃነቱን በይፋ ለመጠየቅ ስለሚፈራ ነው። ስለዚህ፣ እነሱ የሚታሰሩት ሌሎችን ካልተዘጋው እስር ቤት ነፃ ለማውጣት ሲሞክሩ ነው። 

አምባገነኖች የሚጠሉትና የሚፈሩት እውነትን ነው!

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኒጄር፥ ኒያሜ ከተማ በአፍርካ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የተለያዩ ሰብሰባዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት በተካሄደው ስብሰባ ከ28 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) ተሳታፊ ሆነዋል። እኔም በቦታው የተገኘሁት በአፍሪካ ስላለው የኢንተርኔት ነፃነት፡ “Internet Freedom in Africa” በሚል ርዕስ ያለኝን ልምድና ተሞክሮ እንዳካፍል ተጋብዤ ነበር። ዩጋንዳዊው “ፔፔ” እና ኬኒያዊቷ “ሳሎሜ” እንደ እኔ በፓናል ውይይቱ ላይ ልምድና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

በመጀመሪያ በሀገሩ ስላለው የኢንተርኔት አጠቃቀምና ነፃነት ሁኔታ እንዲናገር እንደል የተሰጠው “ፔፔ” ነበር። “ፔፔ” በቀላሉ ከሰው ጋር መግባባት የሚችልና ጨዋታ አዋቂ ነው። በሀገሩ ዩጋንዳ የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በዚህም የላቀ ዕውቅና የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክተውለታል። በውይይቱ ወቅት የኢንተርኔት ነፃነትን ከግል ሕይወቱ ጋር አቆራኝቶ ያቀረበበት ሁኔታ ደግሞ እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር። “እኔና ጓደኞቼ” ይላል ፔፔ፡- 

“ እኔና ጓደኞቼ ከካምፓስ ከተመረቅን በኋላ በአመት አንዴ የመገናኘት ልማድ አለን። ያው እኔ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ስለምሰራ መንግስት ከብዙ ሰዎች ጋር እንድገናኝ አይፈልግም። …አመፅና ሁከት የምቀሰቅስ ስለሚመስላቸው በተደጋጋሚ ያስሩኛል። እስካሁን ድረስ ከስድስት ግዜ በላይ አስረውኛል። አንድ ቀን ታዲያ ከካምፓስ ጓደኞቼ ጋር አንድ ላይ ተሰብስበን እየተወያየን ሳለ ፖሊሶች በሩን በኃይል በርግደው ገቡ። በዚህ ቅፅበት በቲዊተር (Twitter) ገፄ ላይ “Arrested” ብዬ ፃፍኩ። በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና ዲፐሎማቶች ይህን ፅሁፍ እንዳዩ እኔን ለማስፈታት በየፊናቸው መሯሯጥ ጀመሩ …

ከፖሊስ አዛዡ “በአስቸኳይ ይፈታ” የሚለውን መልዕክት ይዞ የመጣው ፖሊስ በሩን ሲያንኳኳ በታሰርኩበት ክፍል ውስጥ ሁለት ፖሊሶች እጅግ ፀያፍ ተግባር ሊፈፅሙብኝ እየተዘጋጁ ነበር። በግልፅ ልንገራችሁ፤ አንዱ ፖሊስ የውስጥ ሱሪዬን እያወለቀ ነበር፣ ሌላኛው ፖሊስ ደግሞ “he was erecting…” አዎ…በቲውተር ገፄ ላይ የፀፍኳት አንዲት ቃል በግብረ-ሰዶም ፖሊሶች ሊፈፀምብኝ ከነበረው የአስገድዶ መድፈር ታድጋኛለች። ጥቃቱ ተፈፅሞብኝ ቢሆን ኖሮ እንደዚህ ከፊታችሁ ቆሜ ለመናገር የሚያችል የራስ መተማመን አይኖረኝም። በእርግጠኝነት አሁን ያለኝን ስብዕናና የራስ መተማመን ያሳጣኝ ነበር…”

“ፔፔ” ላይ ከደረሰው በደልና ስቃይ አንፃር የእኔ በጣም ቀላል እንደሆነ ተሰማኝ። እኔን በጣም የገረመኝ፣ የትም ሀገር ቢሆን የአምባገነን መንግስታት ሥራና ተግባር አንድና ተመሣሣይ ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት የሚገልፁ ሰዎችን ያስራሉ፥ ይደበድባሉ፥ ያሰቃያሉ፥ ይገድላሉ፥…ወዘተ። እነዚህን አምባገነን መንግስታት ከፊል እና ፍፁም በማለት ለሁለት ክፍሎ ማየት ይቻላል።  

ከፊል አምባገነን የሆኑ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦትንና ተጠቃሚዎቹን መቆጣጠር የሚሹት ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚደብቁት ነገር ስላለ ነው። የተዝረከረከ የመንግስት የአሰራር ግድፈቶችን፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ማጭበርበሮችን፣ እንደ ሙስና ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮችን ወይም ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮችን ከማህብረሰቡ መደብቅ ይሻሉ። ስለዚህ፣ በኢንተርኔት አማካኝነት እነዚህን ችግሮች የሚያጋልጡ ሰዎችን ብዙ ግዜ ያስፈራራሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ ያስራሉ።

ከላይ በተተቀሰው የውይይት መድረክ ተሳታፊ የነበረችው ኬኒያዊቷ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ “ሳሎሜ” በኬኒያ ስላለው የኢንተርኔት ነፃነት የሰጠችው አስተያየት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። “ሳሎሜ” ቅድሚያ የሰጠችው በቀጣዩ አመት በኬኒያ ስለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ነበር። የኬኒያ መንግስት ጎረቤት ዩጋንዳን እንደ ምሳሌ በመውሰድ፣ በምርጫ ወቅት አመፅና ብጥብጥን ለመከላከል በሚል የኢነተርኔት አገልግሎትን ሊዘጋ እንደሚችል ስጋቷን ገልፃለች።

ፍፁም አምባገነን የሆኑ መንግስታት ግን የኢንተርኔት አገልግሎትን ከማቋረጥና መከታተል አልፎ-ተርፎ ተጠቃሚዎቹን ከማስፈራራት፥ ማሰርና መደብደብ እስከ መግደል ሊደርሱ ይችላሉ። የኢንተርኔት ግንኙነት መረቡን በከፊል ሳይሆን ሙሉ-ለሙሉ መቆጣጠር ይሻሉ። የተወሰኑ ሰዎችን ሳይሆን ሁሉም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ለመከታተል ይሞክራሉ። ምክንያቱም፣ ፍፁም አምባገነን የሆኑ መንግስታት እንዳይታወቅ የሚሹት የፈፀሙትን ስህተት ወይም ለሕዝብ የተናገሩትን ውሸት ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በእውን የሚያውቀውን እውነት ለመደበቅ ይጥራሉ።

ለምሳሌ፣ እኔ በማህበራዊ ድህረ-ገፆች ላይ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ወንጀል” ተከስሼ ለ82 ቀን ታስሬያለሁ። ሰብዓዊ ክብሬንና ስብዕናዬን በሚነካ መልኩ ተደብድቤያለሁ፥ ተሰድቤያለሁ። ነገር ግን፣ ስለተፈፀመብኝ በደልና ጭቆና እንኳን በነፃነት ለመናገርና ለመፃፍ እንኳን ያስፈራኛል። ምክንያቱም፣ በእኔ ላይ በእውን የፈፀሙብኝን ነገር ሌሎች በምናብ እንኳን እንዳያውቁት ይፈልጋሉ። አንተ በእውን ስለሆንከው ወይም በገሃደድ ስለምታውቀው ነገር በግልጽ መናገርና መፃፍ በራሱ “ሕዝብን ለአመፅ በማነሳሳት ወንጀል” በሚል ዳግም ሊያስከስስ ይችላል።

በአጠቃላይ፣ አምባገነኖች ከምንም በላይ የሚጠሉትና የሚፈሩት እውነትን ነው። በኢንተርኔት አማካኝነት የእነሱን ውሸት አጋለጥክ ወይም በእውን የምታውቀውን ፃፍክ፣ ዞሮ-ዞሮ ያው እነሱ የሚጠሉትን ተግባር ፈፅመሃልና በሄድክበት መውጫና መግቢያ ያሳጡሃል። ስለዚህ፣ ወይ እነሱን ፍርተህ ትኖራለህ፣ አሊያም ያመንክበትን አድርገህ የሚመጣውን ትቀበላለህ።