​የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል!

በሕገ መንግስታዊ የፌደራል ስርዓት በምትመራ ሀገር፣ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በአራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፤ ህወሓት፥ ብአዴን፥ ኦህዴድ እና ደኢህዴን ጥምረት የሚመራ ሆኖ ሳለ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ህወሓትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ አድሏዊነት ሊመስል ይችላል። ነገር ግን፣ ይሄ እውነታ እንጆ አድሏዊነት አይደለም። ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ የፌደራል ስርዓቱና ተቋማት፣ እንዲሁም የክልል መንግስታትና ተቋማት የሚተዳደሩበት ሕግ፥ ስርዓትና መዋቅር በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነው። 
የፖለቲካ ጨዋታውን ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይጫወታሉ። የጨዋታውን ሕግ በማፅደቁ ሂደት ሁሉም ተሳታፊዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ ሕጉ የተረቀቀበት ፅንሰ-ሃሳብ የህወሓት ነው። ይህ የጨዋታ ሕግ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት ሲሆን የሕገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ደግሞ በህወሓት የብሔር ፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በመሆኑም የፌደራሉ መንግስትና ተቋማት ይህን የፖለቲካ መርህና አመለካከት ተግባራዊ ለማድርግ የተቋቋሙ ናቸው። 

የሕጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ፣ በሁሉም ደረጃ የሚወጡ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች ለሕገ መንግስቱ ተገዢ መሆን አለባቸው። ነገር ግን፣ የሕገ መንግስቱ ትርጉምና ፋይዳ በህወሓት የፖለቲካ መርህና አመለካከት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ፣ ለሕገ መንግስቱና ለመንግስታዊ ስርዓቱ ተገዢ መሆን ለህወሓት ተገዢ ከመሆን ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው።

በአጠቃላይ፣ በሀገሪቱ ለሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮች ከተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ህወሓት ተጠያቂ የሚሆንባቸው ምክንያቶች፤ አንደኛ፡- መንግስታዊ ስርዓቱ በህወሓት የፖለቲካ መርህና መመሪያ የተመሰረተ ስለሆነ፣ ሁለተኛ፡- ይህ የፖለቲካ መርህና አመለካከት ፍፁም ስህተት ስለሆነ፣ ሦስተኛ፡- የሥልጣን የበላይነቱን ለማስቀጠል እጅግ አደገኛ የሆነ ሸርና አሻጥር እየፈፀመ ስለሆነ። እነዚህን ችግሮች አንድ ላይ አያይዤ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።  

የዳግማዊ ወያነ ወይም የሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረው የትግራይ ህዝብን የለውጥ ፍላጎት የብሔርተኝነት ስሜት በመቆስቆስ እና በራስ የመወሰን መብትን ዓላማ በማድረግ ነው። የቀድሞ የህወሓት (TPLF) መስራችና አመራር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የድርጅቱን የትጥቅ ትግል አጀማመርና የንቅናቄ ስልት “…the prevalence of the TPLF at this stage of the struggle was attained by its rigorous mobilization of the people based on the urge of ethno-nationalist self-determination on the one” በማለት ገልፀውታል። 

ነገር ግን፣ ከህወሃት ብሔርተኝነት በስተጀርባ ለራስ ብሔር ተወላጆች የተሻለ ክብርና ዋጋ መስጠት፣ ለሌሎች ብሔር ተወላጆች ደግሞ ያነሰ ክብርና ዋጋ በመስጠት ላይ የተመሰረተ ነው። የትጥቅ ትግሉን ለማስጀመር በትግራይ ህዝብና የፖለቲካ ልሂቃን ስነ-ልቦና ውስጥ እንዲሰርፅ የተደረገው የአክራሪ ብሔርተኝነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ የተበዳይነትና ወገንተኝነት ስሜት ፈጥሯል። ከደርግ ጋር በተካሄደው ጦርነት የተፈጠረው ጥላቻና የጠላትነት ስሜት ዛሬ ላይ ወደ ፍርሃትና ጥርጣሬ ተቀይሯል። 

የዘውግ ብሔርተኝነት እና በራስ የመወሰን መብት ሕዝባዊ ንቅናቄን ለመፍጠር (mobilization) ተጠቅሞ ወደ ስልጣን የፖለቲካ ቡድን የተበዳይነትና ጠላትነት አመለካከት ያለው፣ ማንኛውንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ስጋት የሚመለከት ይሆናል። በሕወሃት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ ተፅዕኖዎች ያረፉበት ነው። 

በመጀመሪያ ደረጃ ሕወሃት ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክልና በጦርነት ወቅት በተፈጠረ ከፍተኛ የተበዳይነት፥ ጠላትነትና ፍርሃት አመለካከት የሚመራ ድርጅት እንደመሆኑ በድርጅቱ መሪነትና የፖለቲካ መርህ ላይ ተመስርቶ የተዘረጋው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት የሕወሃትን የስልጣን የበላይነት የማስቀጠል ዓላማ ያለው ነው። 

ሁለተኛ እንደ ሕወሃት ያለ የፖለቲካ ቡድን ሌሎች አብላጫ ድምፅ ያላቸው ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳይጀምሩ ማድረግ አለበት። ምክንያቱም አብላጫ ድምፅ ያላቸው ማህብረሰቦች ተመሳሳይ የፖለቲካ ንቅናቄ ማድረግ ከቻሉ የአነስተኛ ብሔር የስልጣን የበላይነትንና ተጠቃሚነትን በቀላሉ ያስወግዱታል። ስለዚህ አብላጭ ድምፅ ያላቸውን ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች በጎሳ፥ ብሔርና ቋንቋ በመከፋፈል የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ እና የተቀናጀ ንቅናቄ እንዳይኖራቸው ማድረግ አለበት።

እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን የቆመለትን የአንድ ወገን የስልጣን የበላይነትን ሊያሳጣው የሚችል ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ለውጥና መሻሻል፣ ሃሳብና አስተያየት ተቀብሎ ለማስተነገድ ዝግጁ አይደለም። በተለይ ደግሞ በመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሃሳብና ድርድር ለማድረግ ፍቃደኛ አይደለም። በዚህ ምክንያት፣ ላለፉት 25 ዓመታት ሕወሃት/ኢህአዴግ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሳውን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት ለማፈን ጥረት አድርጓል። 

በመሰረቱ ሕወሃት የስልጣን የበላይነቱ በሕገ መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ በዚያ ረገድ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል ለማድረግ ዝግጁ አይደለም። በመሆኑም እያንዳንዱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፍርሃትና ጥርጣሬ ይመለከታል። የሕዝቡን የመብትና ነፃነት ጥያቄ በኃይልና በጉልበት በማዳፈን ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እና የፖለቲካ ልሂቃን መንግስትን እንዲፈሩ፣ በዚህም የስርዓቱን ሕልውና ለማስቀጠል ጥረት ያደርጋል። 

በእርግጥ ፍርሃት (fear) የሕወሃት መርህና መመሪያ ነው። ሆኖም ግን፣ በየትኛውም ግዜ፥ ቦታና ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፖለቲካዊ ጥያቄ እኩልነት (equality) ነው። የሁሉም መብትና ነፃነት እስካልተከበረ ድርስ ዜጎች የእኩልነት ጥያቄን ከማንሳት ወደኋላ አይሉም። እንደ ሕወሃት ያሉ ጨቋኞችም የመብትና ነፃነት ጥየቄ ባነሳው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የኃይል እርምጃ በመውሰድ ጥያቄው ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ፣ ሕወሃት ከሚፈጥረው ሽብርና ፍርሃት ይልቅ እድሜ ልክ በተገዢነትና ጭቆና መኖር ይበልጥ ያስፈራል። 

ዛሬ የሕወሃትን የሰልጣን የበላይነት የሚቃወም፣ በጭቆና ተገዢነት መኖር የሚጠየፍ ትውልድ ተፈጥሯል። ስለዚህ፣ ወይ የሕወሃት የበላይነት በለውጥና ተሃድሶ ያበቃል፣ አሊያም ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ በሕዝባዊ አመፅና አምቢተኝነት ይፈርሳል። በመሆኑም የሕወሃት የበላይነት በውዴታ አሊያም በግዴታ ያበቃል። ሰሞኑን በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚታየውን ሕዝባዊ ንቅናቄ በሸርና አሻጥር ወደ ሁከትና ብጥብጥ በመውሰድ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማዳፈን የሚደረገው ጥረት ሁለተኛውን የለውጥ ጉዞ ከማፋጠን የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ የለውም። 

Advertisements

​ኦሮማይ-3፡ ያለ ለውጥ ብጥብጥ ውድቀትን ማረጋገጥ!

ከሕዝቡ ሲነሱ ለነበሩት የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ባለፉት ሁለት አመታት የኢህአዴግ መንግስት መውሰድ የነበረበት የለውጥ እርምጃዎች ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ ደረጃ ራሱ ኢህአዴግ መታደስ አለበት። በተለይ የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄን የሚያነሱ ግለሰቦችን በአሸባሪነት፣ እንዲሁም ተመሳሳይ አዝማሚያ ያላቸውን የራሱን አመራሮች በጠባብነትና ትምክህተኝነት መፈረጅ ማቆም አለበት። 

በመቀጠል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድ ስር ነቀል የለውጥ እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅበታል። በዚህ ረገድ ከኢህአዴግ የሚጠበቀው፤ አንደኛ፡- የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ማክበር ሁለተኛው ደግሞ የመልካም አስተዳደር እጦትን በዘላቂነት መቅረፍ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የኢህአዴግ መንግስት ከሕዝቡ እየተነሱ ያሉትን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ አስተዳደራዊ ተሃድሶ (Administrative reform) እና ፖለቲካዊ ተሃድሶ (Political reform) ማድረግ ይጠበቅበታል።

ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየተነሱ ያሉት የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ የአስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ጥራት ለማሻሻል በቅድሚያ ብቃት ያለው አመራር ሊኖር ይገባል፡፡ ከሙያዊ ብቃት ይልቅ በፖለቲካ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ አመራር ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበትና ጥራት ያለው አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ለመዘርጋት ዋና ማነቆ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሥር-ነቀል የሆነ ለውጥ ማድረግ ካልተቻለ ሕዝቡን ክፉኛ እያማረረ ያለውን የመልካም አስተዳደር እጦት ችግርን በዘላቂነት መቅረፍ አይቻልም፡፡
የፖለቲካ ተሃድሶ መሰረታዊ ዓላማው የብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ሥርዓት – ዴሞክራሲ – መገንባት ነው፡፡ ይህ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጣቸውን የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለ ምንም መሸራረፍ ማክበርና ማስከበር ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው በተለያየ ግዜ የወጡና የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድቡ ፖሊሲዎችን፣ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን፣ እንዲሁም ከሕገ-መንግስታዊ መርሆች ውጪ የሆኑ ሥራና አሰራሮችን ሙሉ ለሙሉ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ 

የኢህአዴግ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ

በዚህ መሰረት፣ የኢህአዴግ መንግስት ሊያከናውናቸው ከሚገቡ የለውጥ ተግባራት ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡- 

  • የታሰሩ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የመብት ተሟጋቾችን እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት፣
  • የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚገድበውን የፀረ-ሽብር አዋጁን መሻርና ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንደገና ማርቀቅ፣
  • የመንግስትና የግል ሚዲያ ተቋማትን ሥራና አሰራር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ማድረግ፣ ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆነውን የመረጃ ነፃነትና ሚዲያ አዋጅ ከሕገ-መንግስቱ ጋር በተጣጣመ እንደገና ማርቀቅ፣
  • የሙያና ሲቪል ማህበራት በሀገሪቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለተቋማቱ አንቅስቃሴ ማነቆ የሆነውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ እንደገና ማርቀቅ፣
  • የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን “ፀረ-ስላም…ፀረ-ሕዝብ…ፀረ-ልማት” ብሎ በመፈረጅ የጠላትነት መንፈስ እንዲያቆጠቁጥ ከማድረግ ይልቅ መልካም ግንኙነት ማዳበርና ለብሔራዊ መግባባት መስራት ይጠበቅበታል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የኢህአዴግ መንግስት ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ተግባራት አንዱን እንኳን ተግባራዊ አድርጓል? አላደረገም! ከዚያ ይልቅ፣ በሶማሌ ክልላዊ መስተዳደር አመራርና ልዩ ፖሊስ አማካኝነት ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ ጥያቄዎች ዳግም እንዳይነሱ ለማድረግ፣ በዚህም የለውጥና መሻሻል ንቅናቄውን በእጅ አዙር ለማዳፈን ጥረት እያደረገ ነው። 

በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭት በመፍጠር ወይም እንደ መንግስት የሚበቅበትን ድርሻና ኃላፊነት ከመወጣት ይልቅ ዳር-ቆሞ በመመልከት ላይ ይገኛል። በመሆኑም እንደ መንግስት ድርሻና ኃላፊነቱን በተግባር መወጣት ተስኖታል። ስለዚህ በግልፅ የፌደራሉ መንግስት መዋቅሩን ተከትሎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኖታል። በአጠቃላይ የፌደራሉ መንግስት በተግባር ወድቋል፥ አልቆለታል፥ አብቅቶለታል፥…. ኦሮማይ!!

​ኦሮማይ-2፡ ከለውጥ ማዕበል ወደ ብጥብጥ! 

በሕዝቡ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እስካልተሰጣቸው ድረስ ግጭትና አለመረጋጋቱ እየጨመረ ይሄዳል። ይህን የለውጥ ጥያቄ ለማስቆም መሞከር ከትውልድ ጋር ግጭት ውስጥ እንደ መግባት ነው። መንግስት ሕዝቡ እያነሳቸው ላሉት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በኃይል ለማፈን የሚደረገው ጥረት ሀገሪቱን ወደ ለየለት ግጭትና አለመረጋጋት ያስገባታል። 

የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሥራና አሰራራቸውን ከማሻሻል ይልቅ ፖሊሶች፣ ወታደሮችና የደህንነት ሰራተኞች በመላክ ሕዝቡን ለሞት፣ ጉዳትና ለእስራት የሚዳርጉት ከሆነ ባለስልጣናቱ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ቅቡልነት፣ እንደ መንግስትም ያላቸውን ተቀባይነት ከግዜ ወደ ግዜ እያጡ ይሄዳሉ። በዚህም አንደኛ፡- መንግስት በሕዝቡ ዘንድ ያለውን የማስተዳደር ስልጣን ይገፈፋል፤ ሁለተኛ፡- ሕዝቡ ራሱን-በራሱ ማስተዳደር መብቱን ተጠቅሞ የጋራ ሰላምና ደህንነቱን በራሱ ለማስከበር ጥረት ያደርጋል። ይህ ደግሞ ገና በ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በግልፅ ተጀምሯል። 

ነጭ ሽብር ተጀምሯል፣ ቀይ ሽብር ይከተላል” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርትን ዋቢ በማድረግ በ2008 ዓ.ም ብቻ በኦሮሚያ ክልል 173 ሰዎች ሲገደሉ ከእነዚህ ውስጥ 14 የፀጥታ ኃሎች ሲሆኑ ሌላ 14 ደግሞ የክልሉ መንግስት ኃላፊዎች ናቸው። በተመሳሳይ በዚያኑ አመት በጎንደር ከተማ በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱ ይታወሳል። እነዚህና ሌሎች ተያያዥ ክስተቶች በኦሮሚያና አማራ ክልላዊ መስተዳደሮች ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል። 

የአማራ ክልል መስተዳደርና የብአዴን አመራሮች ከሕዝቡ ለሚነሳው ጥያቄ የድጋፍ አዝማሚያ ማሳየታቸው ይታወሳል። በተቃራኒው የቀድሞ የኦህዴድ የበላይ አመራር በክልሉ ሲካሄድ የነበረውን የሕዝብ አመፅና ተቃውሞ በኃይል ለማዳፈን ያላሳለሰ ጥረት አድርጓል። ይህ ግን በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራውን አዲሱን የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን እንዲመጣ አድርጎታል። በሌላ አነጋገር፣ የአቶ ለማ መገርሳ አመራር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኦሮሞ ሕዝብ ጫና እና ግፊት ወደ ስልጣን እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሚመራው የአማራ ክልል መስተዳደር በስልጣን ላይ መቆየት የቻለው በወቅቱ የክልሉ ሕዝብ ላነሳቸው የነፃነት፥ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች የመደገፍ ዝንባሌ ስለነበረው ነው። 

ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ራሱን ለለውጥ ከማዘጋጀትና የተሃድሶ አቅጣጫ ከማስቀመጥ ይልቅ ለህዝቡ ጥያቄ የድጋፍ አዝማሚያ ያሳዩትን የብአዴን እና የኦህዴድ አመራሮችን ተጠያቂ ማድረግ መርጧል። በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባደረገው ስብሰባ ህዝቡን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ በመጥቀስ በቀጣይነት “ከራሱ ጀምሮ” የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦች እና የጥገኝነት ተግባራትን ለመታገል መወሰኑን ገልፆ ነበር።  በወቅቱ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡- 

“… ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት ይደነቃቀፋል፡፡ መልካም አስተዳደርም ይጠፋል። …በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትት እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችም አዘጋጅቷል፡፡”

በመግለጫ መሰረት የጥገኝነት አስተሳሰብ፣ በዋናነት ጠባብነትና ትምክህተኝነት ይታይባቸዋል የሚባሉ የኢህአዴግ አመራሮች ለሕዝብ ጥያቄና አቤቱታ አዎንታዊ ምላሽ ወይም ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ናቸው። ላለፉት አስር አመታት ኢህአዴግ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ለእስርና ለስደት በመዳረግ በሀገሪቱ አማራጭ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳይኖሩ አድርጓል። በተለይ በጀማሪና መካከለኛ ደረጃ ላይ ያሉት አመራሮች የኢህአዴግ መንግስት አፋኝና ጨቋኝ መሆኑን ተከትሎ አባል ፓርቲውን ከውስጥ ለመቀየር ጥረት ያደረጉ ሰዎች ናቸው። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች እየታየ ያለው ግጭትና አለመረጋጋት የሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ስላልተመለሰ እንጂ በተወሰኑ የኢህአዴግ አመራሮች የተፈጠረ ችግር አይደለም። 

በ2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አማካኝነት ሀገሪቷ ሙሉ በሙሉ በወታደራዊ ቁጥጥር ስር የቆየች ቢሆንም የሁለቱን ክልሎች አመራር እንደ ቀድሞ ለፌደራል መንግስቱ ተገዢ እንዲሆኑ ማድረግ አልተቻለም። ከዚያ ይልቅ፣ ብአዴን እና ኦህዴድ አመራሮች የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ማስተጋባት በጀመሩበት ወቅት ለሕገ-መንግስቱና ለፌደራሊዝም ስርዓቱ ጥብቅና የቆሙት በዋናነት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች እና የሶማሌ ክልል መስተዳደር ናቸው። 

ህወሓት/ኢህአዴግ በሀገሪቱ የፖለቲካ ላይ ያለውን የበላይነት ለማረጋገጥ ብቸኛ አማራጭ እንደመሆኑ ለሕገ መንግስቱና መንግስታዊ ስርዓቱ ጥብቅና ከመቆም ውጪ ሌላ ምርጫና አማራጭ የለውም። የሶማሌ ክልል መስተዳደር ግን ከተላላኪነት የዘለለ ሚና የለውም። በተለይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ አብዲ መሃመድ ኦማር (አብዲ ኢሌ) ገና ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሞና አማራ ሕዝብ የመብት ጥያቄን በማጣጣልና የመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ቀጥተኛ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎታቸውን በይፋ መግለፃቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ወቅት የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ አከባቢዎች ላይ ጥቃት መፈፀም ጀምሯል። 

የህወሓት/ኢህአዴግ አባላትና አመራሮች

የሶማሌ ልዩ ፖሊስ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በሚገኙ አከባቢዎች ላይ ተከታታይ ጥቃት በመፈፀም በመቶዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎችን ከሞት፣ ከ200ሺህ በላይ ደግሞ ማፈናቀሉ ይታወሳል። ይህ ሲሆን የፌደራሉ መንግስት፥ የሀገር መከላከያ፥ የደህንነትና ፖሊስ ኃይሎች በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ የሚፈፀመውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ለማስቆም በተጨባጭ ይሄ ነው የሚባል ጥረት አላደረግም። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂ የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይል መዋቅር በበላይነት የተቆጣጠረውና አዲሱን የኦህዴድ አመራር ለፌደራል መንግስቱ ተገዢ እንዲሆን ከፍተኝ ጥረት እያደረገ ያለው ህወሓት/ኢህአዴግ ነው። 

የብአዴን አመራር በራሱ ከፌደራሉ መንግስት ቁጥጥር ለመውጣት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ሲሆን የደኢህዴን አመራር ደግሞ በፌደራል መንግስቱ መዋቅርና እንቅስቃሴ ላይ ያለው የመወሰን አቅም እጅግ በጣም ውስን ነው። በዚህ መሰረት፣ የፌደራሉ መንግሰት ህወሓት ብቻውን የሚንከላወስበት ኦና ቤት ሆኗል። በአጠቃላይ የመከላከያና ደህንነት ኃይሉን በበላይነት የተቆጣጠረው የህወሓት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር ግራ ተጋብቶ ሀገሪቷን ወደ እርስ በእርስ ግጭትና እልቂት ውስጥ ሊያስገባት ከቋፍ ላይ ደርሷል።    

​ኦሮማይ-1፡ በይስሙላ ምርጫ ወደ ለውጥ ማዕበል!

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የተነሳ ሰሞን ባወጣሁት “ኢትዮጲያ የማን ናት”  የሚል ፅሁፍ፤ “የኢህአዴግ መንግስት በ2002ቱ ምርጫ 99.6%፣ በ2007ቱ ደግሞ 100% ‘አሸነፍኩ’ ብሎ ተሳልቋል። ይህ “የይስሙላ ምርጫ” ግን በዴሞክራሲ መቃብር ላይ የበቀለ አረም ነው” ብዬ ነበር። ይህ ዛሬ ላይ በድንገት የተገለጠልኝ እውነት አይደለም። ልክ የ2007ቱ ምርጫ ውጤት ይፋ እንደተደረገ “100% የምርጫ ቅሌት እንጂ ውጤት አይባልም” በማለት የሚከተለውን ፅፌ ነበር፡- 

“100% የሚባለውን አሰቃቂ ክስተት “የምርጫ ውጤት” በሚል ሰርግና ምላሽ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። በዞንና ወረዳ ደረጃ ያሉትስ አይፈረድባቸውም። በፌዴራልና ክልል ደረጃም ተመሳሳይ አቋም የሚያራምዱ ባለስልጣናት ካሉ ግን በጣም አስገራሚ ነው የሚሆነው ። ይሄ 100% ተብዬ ነገር’ኮ ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ሀገሪቱ በዲሞክራሲ ረገድ ያሳየችውን ለውጥና መሻሻል ወደ ኋላ የቀለበሰ፣ ህዝቡ ሰላማዊ ፖለቲካ፣ በሕግ የበላይነት እና በሌሎች ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ ያለውን እምነት ሽርሽሮ በመናድ ዴሞክራሲን በጭቅላቱ ዘቅዝቆ ያቆመ፣ ልክ እንደ ደርጉ ቀይ-ሽብር ህዝብን በፍርሃት ቆፈን የሚቀፈድድ እጅግ አስቀያሚ ድርጊት ነው።” 

በተለይ ባለፉት አስር አመታት የኢህአዴግ መንግስት፤ በፀረ-ሽብር ሕጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በሚዲያና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ የሲቪል ማህበራትን አጥፍቷቸዋል። የኢህአዴግ መንግስት እነዚህን የዴሞክራሲ ተቋማት ከማጥፋቱ በተጨማሪ፣ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸውን የራሱን አመራሮች “በሃይማኖት አክራሪነት፣ ብሔርተኝነት ወይም ትምክህተኝነት” እየፈረጀ የተወሰኑትን ለእስርና ስደት ሲዳርጋቸው፣ የተቀሩት ደግሞ ሃሳባቸውን ከመግለፅ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። 

በአጠቃላይ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያ እና የሲቭል ማህበራት ከሌሉ፣ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ የተለየ ሃሳብና አመለካከት የማስተናገድ ባህል ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ (Constitutional Democracy) አብቅቶለታል። በተቃራኒው፣ ከ2008 ዓ፣ም ጀምሮ ባለው ግዜ ውስጥ ብቻ በሕዝቡ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ የታየው ለውጥ የሩብ ምዕተ አመታት ያህል ሰፊ ነው። ሕዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና እያሳየ ያለው የለውጥ ፍላጎት ከእለት-ወደ-እለት እየተቀያየረና እየጨመረ መጥቷል። በዚህ ፈጣን የለውጥ ሂደት ውስጥ ባለበት የቆመው የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ነው። 

በ2008 ዓ.ም 3ኛው ማዕበል በሚለው ባወጣሁት ፅሁፍ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት በሀገሪቱ ውስጥ የታየው ለውጥ በሀገሪቱ ታላቅ የፖለቲካ ማዕበል እንደሚያስነሳ ገልጬያለሁ። ሆኖም ግን፣ የኢህአዴግ መንግስት አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት አንዲት እርምጃ መራመድ ተስኖታል። ለኢህአዴግ መንግስት ዛሬም፥ የዛሬ ሁለት አመት ሆነ የዛሬ አስር አመት “ፈተናዎቹ”፤ የመልካም አስተዳደር እና ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፡- ትምክህተኝነት፥ ጠባብ ብሔርተኝነት እና አክራሪነት” ናቸው።  

የህዝቡ ጥያቄና እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ የለውጥ ሂደትን ተከትሎ የመጣ እንደመሆኑ አይቀሬና አስገዳጅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የህዝቡ ኑሮና አኗኗር እየተለወጠ፣ በተለይ ደግሞ የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም እየተሻሻለ በሄደ ቁጥር፣ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል መብትና ግዴታውን ይበልጥ ያውቃል፥ ይጠይቃል። በልማትና ዴሞክራሲ ረገድ ህዝቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይበልጥ እየሰፉና እየተወሳሰቡ መሄዳቸው እርግጥ ነው። 

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እየታየ ያለው ተቃውሞ ህዝቡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መብቱን ለማስከበር የሚችልበት አማራጭ መንገድ በማጣቱና ብሶትና ምሬቱን የሚተነፍስበት ትንሽ ቀዳዳ ባለመኖሩ የተከሰተ ነው። በአንድ በኩል ህዝቡ በፍትህና የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት እየተሰቃየ ነው። በሌላ በኩል፣ ለአስር አመታት የተጠራቀመ ብሶቱንና ምሬቱን የሚያስተነፍስበት ቀዳዳ ሲያጣ፣ አመፅና ተቃውሞ ብቸኛ አማራጭ ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ፣ ቀልጣፋ አገልግሎትና ፍትህ ያልሰፈነበት ምክንያት ሌላ ሳይሆን መንግስት የአስተዳደርና ፍትህ ሥርዓቱን ማሻሻል ስለተሳነው እንደሆነ በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ሲኖረው ህዝብ ይቆጣል፣ ህዝባዊ አመፅ ይቀሰቀሳል።  

በጅምላ የታሰሩ ወጣቶች እርስ በእርሳቸው ፀጉራቸውን እንዲላጩ ይደረጋል!

ከዚያ በመቀጠል “ኢህአዴግ፡ ከለውጥና ሞት አንዱን ምረጥ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ፅሁፍ የኢህአዴግ መንግስት ሁለት አማራጮች እንዳሉት ገልጩ ነበር። የመጀመሪያ አማራጭ የሕዝቡን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት ጋር አብሮ በመጓዝ በሀገሪቱ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገር። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ እየተነሳ ያለውን ጥያቄና የለውጥ ፍላጎት በማፈን የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋውን ማጨለም ነው። በዚህ መንገድ የብዙ ንፁሃን ዜጎችን ሕይወት መስዕዋት የሚጠይቅ ይሁን እንጂ እንደ ማንኛውም አምባገነናዊ ሥርዓት መጨረሻው ውድቀት ይሆናል። 

ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ  የኢህአዴግ መንግስት አካሄድ የፈጠረብኝን ስጋት፤ “አሁን ላይ ይበልጥ እያሳሰበኝ ያለው ነገር፣ ኢህአዴግ ከሕዝቡ ጥያቄና ፍላጎት ጋር አብሮ መሄድ አለመቻሉ ሳይሆን በዚህ ምክንያት የሀገሪቱ ዜጎች ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ እየወደቀ መምጣቱ ነው!” በማለት ገልጩ ነበር። ከዚሁ ጋር አያይዤ፣ ከ2008 ዓ.ም ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ከለውጥ እና ሞት አንዱን እንደመምረጥ መሆኑን ጠቅሼ ነበር። ሆኖም ግን፣ በቀጣዩ የ2009 አመት የተካሄደውን “ጥልቅ ተሃድሶ” ከተመለከትኩ በኋላ “ኢህአዴግ እና ፀጉራም ውሻ አንድ ናቸው” የሚል ፅሁፍ አወጣሁ። ይህ የኢህአዴግ መንግስት ከለውጥ ይልቅ ሞትን እንደመረጠና እንደ ፀጉራም ውሻ ማንም ሳይውቅለት ውስጥ-ለውስጥ እየሞተ እንደሆነ ይጠቁማል። 

የጄነራል ፃድቃን መልሶ ልብ ማውለቅ….

ከዕለት ተዕለት ግላዊ የኑሮ ግብ ግብ አለፍ ብሎ ለህዝብ ነፃነት፣ የህይወት ለውጥ፣ መከራ ቅለት ሊታገሉ መነሳት ራመድ ያለ ማንነትን ይጠይቃል፡፡ ታግሎ ማሸነፍ ደግሞ የበለጠ ብርታት ይጠይቃል፡፡ ጀነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ የልጅነት ዘመናቸውን በጫካ የገፉ በመሆናቸው እንዲህ ካሉት ወገን ለመመደብ የሚችሉ ናቸው፡፡ ለህዝብ ነፃነት የልጅነት ጊዜን ሰውቶ በረሃ መገኘት ከበድ ያለ ስብዕና አካል ቢሆንም በረሃ መውረዱ፣ ጠመንጃ ዘቅዝቆ አቀበት ቁልቁለቱን መሮጡ በራሱ ውጤት ስላልሆነ በቂ ነገር አይደለምና ውጤቱ በምክንያት መመርመር አለበት፡፡

በረሃ የወረደ ሁሉ፤ ነፍጥ አንስቶ ባሩድ ያቦነነ ባጠቃላይ፤ “ታግየ ነፃ አወጣኋችሁ” ባይ ውለታ አስቆጣሪ በነሲብ፤ “ዘር አዝርቴ ሞቶ አቆማችሁ” ባይ ሃረግ መዛዥ በሞላ  “ከተዋጋ ዘንዳ እንደፈለገ ይሁን፣ ያሻውን ያጥፋ፤ ጥፋትም በጥፋት ላይ ይደራርብ” የሚባልበት ዘመን ከነበረም አልፏል፡፡ ያለንበት ጊዜ የምክንያታዊነት እንጂ የግዝት ዘመን አይደለም፡፡ ስለዚህ፣ ድርጊቱ ተመርምሮ መጠየቅ ያለበት ሁሉ በህግም፣ በህሊናም ይጠየቃል፡፡ በአንድ ወቅት ደደቢት በረሃ ወይ ደንቆሮ ዋሻ መገኘት የተጠያቂነት ድነሽነት (Immunity) አይደለምና ጀ/ል ፃድቃን እና ጓዶቻቸው ላጠፉትም ሆነ በጥፋታቸው ላይ እየደራረቡት ላለው ከቀደመው የባሰ ጥፋታቸው መጠየቅ አለባቸው፡፡

ደርግን መጣል የህግ ሁሉ ፍፃሜ፣ የትክክለኝነት ሁሉ ዳርቻ የሚመስላቸው ህወሃቶች በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያላቸው ግምት ራሳቸው ለራሳቸው ካላቸው ሚዛን ጋር በእጅጉ ይራራቃል፡፡ እነሱ ራሳቸውን የኢትዮጵያ መድህን፣ ምትክ አልቦ ክስተት፣ መታደስ እንጅ መቀየር የሌለባቸው ምጡቃን አድርገው ሲያስቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ለእነሱ ብቻ የሚታያቸውን ፍፅምናቸውን መሬት ላይ ፈልጎ ከማጣቱ የተነሳ ነገራቸው ሁሉ ታክቶታል፡፡ እነሱ የትም እንደ ማይሄዱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተናግረዋል፤ አለፍ ሲልም ጠመንጃቸው በትከሻቸው ነው፡፡ ህዝቡም መሄጃ ስለሌለው እንዳለ አለ፡፡ ህዝቡ በህወሃት/ኢህአዴግ ለሃገር የመቆም ልዕልና ላይ ተስፋ ከቆረጠባቸው ምክንያቶች አንዱ ትልቋን ሃገር ወደብ አልቦ ለማድረግ የሮጠበት የእብድ እሩጫ ነው፡፡ ወደብን ያክል ወሳኝ ነገር እንደ መርገም ‘ነገ ዛሬ ሳትሉ ከእጄ ላይ ውሰዱልኝ’ የሚል “አዋቂ” ከህወሃት ውጭ፣ ከአቶ መለስ ሌላ ከየት ምድር ተፈልጎ ይገኛል? ጄሌ ካድሬዎቹ ተናግረው የማይጠግቡለት የአቶ መለስ “እውቀት ጢቅነት” ኢትዮጵያን ለባህር እጅግ ቀርባ ወደብ አልቦ የሆነች የመጀመሪያዋ የጉድ ሃገር አድርጓታል፡፡

የዓለማችን ወደብ አልባ ሃገራት (ለምሳሌ ቻድ፣ ዩጋንዳ፣ ፓራጓይ፣ ሞንጎሊያ) ወደብ ወደማጣቱ ችግር የከተታቸው የሃገራቸው ጅኦ-ግራፊያዊ አቀማመጥ ከባህር እጅግ ርቀው ከመገኘታቸው የተነሳ ይህን እድል የሚነፍጋቸው በመሆኑ እንጅ “ነፃ አውጭዎቻቸው” ከወደዱት ጋር ፍቅር ለማፅናት በገፀ-በረከትነት ስላስረከቡባቸው አይደለም፡፡ እንደውም የእውነት የህዝብ መንግስት ያላቸው ሃገራት ድንበራቸው ለባህር ቅርብ ሳይሆን እንኳን እንደምንም ብለው ለባህር በር ባለቤትነት የሚያበቃ ኮሪደር ባለቤቶች ይሆናሉ (ለምሳሌ ኮንጎ)፡፡ የጉድ ሃገራችንን ብናይ ግን ለግመል ውሃ መጎንጫነት በታጨው አሰብ ወደብ በኩል ከባህር ያላት ርቀት አዲስ አበባ ከቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) የሚርቀውን ያህል ነው፡፡ ስለ ወደብ ጉዳይ ጮኽው የማይደክማቸው ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያም እንደውም ርቀቱን ‘የእግር መንገድ ያህል የቀረበ’  ይሉታል፡፡

የአሰብን ወደብ ለሃገራችን አስቀርቶም የጠናባቸውን የኤርትራ ፍቅርም አለማጣት ይቻል እንደነበር ለማሰብ ፅኑ ፍቅሩ የፈቀደላቸው ያልመሰለኝ አቶ መለስ እና ጓዶቻቸው ወደብ አስረክበው ያመጡብን ፈተና ከዚህ በመለስ የሚሉት እንዳልሆነ ከነባራዊው ህይወታችን በተጨማሪ የዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያምን “አሰብ የማናት?” የሚል መፅሃፍ ማንበብ ነው፡፡ የትልቁን ጉዳት ጥቂት ገፅታ ለማንሳት ያህል ወደብ የሌለው ሃገር ለዓለም አቀፉ ንግድ ያለው ቅርበት በሰው እጅ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ መርፌ ምላጭ ሳይቀር ከውጭ ለሚያስመጣ ድሃ ሃገር ሁለመናውን የሚያስገባው የሚያስወጣው በሰው ደጅ ነውና ጥብቅ ሚስጥራዊነት የሚሻው የፀጥታም እና የደህንነት ጉዳዮቹ ሁሉ አደባባይ የተሰጡ ናቸው፡፡ ልመና አኮፋዳ ይዘን፣ የሰው ደጅ ላይ ቆመን የምናገኘው የእርዳታ እህል ርሃብ ለሚቆላቸው ወገኖቻችን በጊዜ እንዲደርስ የራስ የሆነ ወደብ ይመረጣል፡፡ እንደ መድኃኒት ነፍስ አድን፣ እንደ ነዳጅ አጣዳፊ የሆኑ ፍጆታዎች እንደልብ ይመላለሱ ዘንድ ማን እንደራስ ወደብ! መንግስት ባለወደቡን ሃገር ካስቀየመ የአስመጭ ነጋዴዎች ንብረት ወደብ ላይ ቀልጦ ሊቀር የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የብዙ ነጋዴ ወገኖቻችን ንብረት ቀልጦ እንደቀረ ይነገራል)፡፡

ከሁሉ በላይ ለወደብ ኪራይ የሚወጣ ገንዘብ እኛን ጎስቋሎችን ቀርቶ የባለፀጋ ሃገሮችን ወገብም የሚቆርጥ ነው፡፡ አወቅኩ ባዮቹ መለስ ዜናዊ እና ጓደኞቹ እንደሚያስቡት ወደብ ገንዘብ ስላለ ብቻ እንደ በቆሎ እና ገብስ በደረሱበት የሚያፍሱት ወይ ደግሞ ከሆነ ዘመን በኋላ ትዝ ሲል ሄደው ‘አሁን የወደብ ባለቤት መሆን አለብኝ’ ብለው አፈፍ የሚያደርጉት ጥይት እንደመግዛት ያለ ርካሽ ነገር አይደለም፡፡ ረብጣ ገንዘብ ተከፍሎም እንኳን በዲፕሎማሲው መስክ ባለወደብ ሃገራትን ማባበልን፣ መለማመጥን ይጠይቃል፡፡ ያለአባት በሆነ ሁኔታ ደረጃችንን አውርዶ ጅቡቲን የሚያለማምጠን ይሄው ነው፡፡ ወደብ ማግኘት ቀላል እንደሆነ ሲናገር የነበረውን መለስ ዜናዊን ላሙ ኮሪደርን ለመገንባት ዙሪያ ጥምጥም ያባዝነው የነበረው ወደብ  እሱ ከጫካ እንደመጣ እንዳሰበው በዋዛ የሚገኝ ነገር ባለመሆኑ ነው፡፡ የሰራውን የሚያውቀው ህወሃት/ኢህአዴግ ለወደብ ኪራይ ስንት እንደሚከፍል በግልፅ ተናግሮ ባያውቅም አመታዊ ወጭው እጅን በአፍ የሚያስጭን እንደሆነ (ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል) ማንም አይጠፋውም፡፡ ይህን ለወደብ የምናወጣውን ወጭ በየትኛው የወጭ ንግድ ምርታችን በምናገኘው ዶላር እንደምናካክሰው   ወደባችንን መርቆ ያስረከበውን አካል የሚያስጨንቅም አይመስለኝ፡፡

ህወሃት ከጫካው ድል መልስ ኤርትራን ካላስገነጠለ እንቅልፍ በአይኑ እንደማይዞር ‘ኤርትራን እንደመንግስት እወቁልኝ’ ከሚለው ጭቅጨቃው የተረዱት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጂሚ ካርተርም ሆኑ  የአፍሪካ ጉዳይ አማካሪያቸው ኽርማን ኮህን ‘እባካችሁ ሃገሪቱን ወደብ አልባ የማድረጉን ነገር ደጋግማችሁ አስቡት’ ብለዋቸው እንደ ነበር ወቅቱን አስመልክቶ የተፃፉ መዛግብትም ያልሞቱት ኽርማን ኮህንም ምስክር ናቸው፡፡ የራሳቸው የኢኮኖሚክስ ህግ ያላቸው አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበራቸው መልስ ‘ወደብ ያለመኖር በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የለውም’ የሚል እብሪት አይኑን የጨፈነው ነበር፡፡ እሺ የኢኮኖሚው ይቅርና በሃገር ደህንነት ላይ ያለው ተፅዕኖስ ምንድን ነው ተብሎ ታስቦ ይሆን?

በወቅቱ ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ዛሬ መልሰው ልብ የሚያደርቅ ክርክር እያመጡ ካሉት ከጄነራል ፃድቃን እና ከሜ/ጄነራል አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ) የሚቀድም ሰው መኖር አልነበረበትም፡፡ እውነታው ግን እነዚህ ዛሬ ሆድ ሲያውቅ በሆነ ሁኔታ ደርሰው ለወደብ ደረት ደቂ የሆኑ ሰዎችም ከአቶ መለስ የተለየ ነገር እንደሌላቸው ነው፡፡ ነበረን ቢሉ እንኳን ዛሬ ላይ ይሄን ቢያወሩ ማሞ ቂሎን ካልሆነ ማንንም ሊያሳምኑ አይችሉም፡፡ አቶ መለስ በዚህም አያበቁም የአሰብን ጉዳይ የሚያነሳ ሰው ‘የሃገር ሉአላዊነት የማይገባው ተስፋፊ ነውና ብቻውን እንደሚያወራ ይቆጠራል’ ይሉ ነበር፡፡

እውነት ለመናገር አቶ መለስም ሆኑ ጓዶቻቸው ወደቡን መርቀው ያስረከቡት  ጆቤ በቅርቡ (ለእኔ ቀልድ በመሰለኝ ሁኔታ) እንዳሉት የወደብ ጥቅም እጅግም ስለማይገባቸው ሳይሆን እንዲገባቸው ስላልፈለጉ ነው፡፡ ከህዎሃቶች ብዙ አደናጋሪ ባህሪያት በጣም የሚገርመኝ መልሰው መላልሰው ራሳቸውን ብቻ ማዳመጥ የሚወዱበት ይሉኝታ የራቀው ልማድ ነው፡፡ እነሱ የፈለጉት፣ እንዲሆን የወደዱት ነገር ሁሉ ለሌላው ሰውም ትርጉም የሚሰጥ/መስጠት የሚገባው እውነት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ያሰቡትን አስተሳሰብ ስሁትት እየተነገራቸውም ጆሮው ላይ ሄድፎን ሰክቶ እንደሚዘል ዲጄ በዛው ሙዚቃ ይደንሳሉ እንጂ የሰውም ሃሳብ ለመስማት ጆሯቸውን ሳያዘነብሉ ጎልማሶቹ አረጁ፤ ያረጁት ባሰባቸው፡፡ ይሄ አንድም ለእውቀት ርቆ መቆም ሁለትም ሰው ንቀት ሶስትም “መተኮስ ደጉ” ያመጣው ማናለብኝነት ነው፡፡

ሰሞኑን ጄ/ፃድቃን ፍፁም ብርሃነ ከተባለ ጋዜጠኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃገራችን በቀይ ባህር አካባቢ የነበራትን ህልውና መልሳ ማምጣት አለባት ብለዋል፡፡ ቀጥተኛ፣ ቅን እና የሰውን ግንዛቤ ዝቅ ባላደረገ መንገድ መልስ እንደሚሰጡኝ ተስፋ በማድረግ በዚህ ንግግራቸው ዙሪያ  እና  አጋጣሚውን በመጠቀም ስለ በእርሳቸው እና የ1993 ስንጥቃት ጓዶቻቸው ዙሪያ ያሉኝን አንዳንድ ጥያቄዎች ላንሳ፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄየ እናት ድርጅትዎ ህወሃት ኤርትራን ነፃ ማውጣትን ከትግል ግቦቹ እንደ አንዱ አድርጎ አንግቦ አስራ ሰባት አመት ተዋግቶ፣ ኤርትራ ቀይ ባህርንም ጠቅልላ ነፃ ሃገር ከሆነች ሃያ ስድስት ክረምት እና በጋ ካለፈ በኋላ ዛሬ ብድግ አድርጎ በቀይ ባህር ላይ የኢትዮጵያን ጠንካራ ህልውና ያስመኘዎት ምን ጥብቅ ጉዳይ ቢገጥምዎ ነው?

ሁለተኛ ቀይ ባህር የሚገኘው ኤርትራን አልፎ እንደሆነ መቼም አያጡትም፡፡ እናት ፓርቲዎ ህወሃት የኤርትራን ሉዓላዊነት መንካት ቀድሞ የሚያጣላው ከእኔው ጋር ነው እያለ  ሲያስፈራራ እንደኖረም ለእርስዎ አይነገርም፡፡ ከሌላ ጥቃት የሚጠብቀውን የኤርትራን ሉአላዊነት ራሱ አይነካውምና ኤርትራን ሳይነኩ በቀይ ባህርን ዙሪያ የኢትዮያን ጠንካራ ህልውና መመስረቱ እንዴት ይሆናል ብለው አሰቡ?

ሶስተኛ የኤርትራ ግዛት እንዳልሆነ በደንብ የሚታወቀውን፣ በደርግ ዘመንም በኤርትራ ውስጥ ሳይሆን በራሱ ራስ ገዝ በሆነ አስተዳደር ሲተዳደር የነበረውን አሰብ ወደብ ያለበትን ክልል የኤርትራ ነው ብሎ የመስጠቱ፣ ቀይ ባህርም ሆነ ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት ሆነው አይውቁም የሚለው ህወሃት  አካል የነበሩ እንደመሆንዎ መጠን ዛሬ በጣም ከረፈደ በኋላ ቀይ ባህርን ለኢትዮጵያ ለመመኘት ሌላው ቢቀር ከሞራል አንፃር ተገቢው ሰው ነኝ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ንግግሬን ይቀበልና ያምነኛ ከዚህ ሃሳብ ጎን ቆሞም ለስምረቱ ይሰራል ብለው ያስባሉ?

አራተኛኤርትራ ከተገነጠለች ብዙ አመታትን ማስቆጠሯ ከፊትዎ የተሰዎረ ነገር አይደለም፡፡ ሃገሪቱ የምትገኝበት ጅኦፖለቲካዊ አቀማመጥ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የአረብ ሃገራትተን ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም በላይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ኢራን፣ ሳውዲ፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ እና ኳታር የበላይ ተቆጣጣሪነታቸውን ለማስረገጥ  የሚሻኮቱበት ቀጠና እንደሆነም አይጠፋዎትም፡፡ ኤርትራ ከአመት በፊት አሰብን ለተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ እና ለሳኡዲ በኪራይ እንደሰጠች ባለማወቅም አልጠረጥርዎትም፡፡ ከነዚህ ሃገራት አንፃራዊ ባለጠግነት፣ ሃያልነት እና የረዥም ዘመን ቀይ ባህርን ከኢትዮጵያ ነጥቆ የአረብ ሃይቅ የማድረግ ምኞት አኳያ እርስዎ የሚናገሩለት የኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ተመልሶ የመጠናከር ህልም እንዴት ስኬታማ ይሆናል ብለው ነው ይህን ሃሳብ ያመጡት?

አምስተኛ የሚያወሩለት የሃገራችን ተመልሶ በቀይባህር አካባቢ የመጠናከር ጉዳይ የሚከናወነው ለኤርትራ ጥብቅና በመቆም ይታወቅ በነበረው፣ ከሻዕብያ ጋር ለነፍስ እየተፈላለግኩ ነው እያለ ሳይቀር የኤርትራን የነፃነት ቀን ደግሶ በሚያከብረው፣ የወደብ አልቦነት ችግሩን ሁሉ በፈጠረው፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ዳርቻ እንድታፈገፍግና የአለም አቀፍ ፖለቲካዊ ተፈላጊነቷ እንዲሞት ያደረገው የእርስዎ ፓርቲ ህወሃት/ኢህአዴግ መሪነት ነው ወይስ በሌላ መንገድ? በህወሃት አጋፋሪነት ከሆነ የባድመውን መጨረሻ ያየው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ተመልሶ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ የሚማገድ ነው ብለው ያስባሉ?

በመጨረሻም ከላይ ካሉት ጥያቄዎቼ ለየት ያለ ነገር ላንሳ፡፡ እንደሚታወቀው ህወሃት/ ኢህአዴግ የምር የተጣላቸውን የቀድሞ ጓዶቹን ምን እንደሚያደርግ ከታምራት ላይኔ እስከ መላኩ ፋንታ፤ ከአቶ አንዳርጋቼው ፅጌ እስከ አቶ ኦኬሎ አኳይ ድረስ የደረሰባቸውን የምናውቀው ነው፡፡ እርስዎ እና የህወሃት ስንጥቃት ጓዶችዎ ግን ከህወሃት ጋር ከፉ የሚመስል ጠብ ተጣልታችሁም በሃገራችሁ እንደፈለጋችሁ እንድትወጡ እንድትገቡ እርስዎማ ጭራሽ ነግደው እንዲያተርፉ ሆነዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ለምን ይመስልዎታል? ለእርስዎ እና ለሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በተለይ የተደረገው የህወሃት ተፃራሪን የመታገስ ያልተለመደ ባህሪ ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ (ያለበት እንኳን በውል ለማይታወቀው) እና ሌሎች የኢህአዴግ የቀድሞ ጓዶች የአሁን ፀበኞች  ሲደገም ያልታየው እንዴት ነው? ይህን የምጠይቀው ለናንተ የዘነበው የህወሃት/ኢህአዴግ የምህረት ዝናብ ለሌሎች ወገኖችም እንዲያካፋ ከመመኘት በተነሳ ነው፡፡

በመጨረሻም በሰሞኑ ንግግርዎትን በተመለከተ በእርስዎ በኩል ያትን ነገሮች ጥያቄዎቼን ተንተርሰው ያስነብቡናል ብየ ተስፋ በማድረግ በራሴ በኩል የሚታዩኝን ነገሮች አንስቼ ላብቃ፡፡  እርስዎና ጓዶችዎ  ሌላውን ለጊዜው እንተወውና ቢያንስ ኢትዮጵያን በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ የባህር በር አልባ ሃገር በማድረጉ ጉልህ ስህተት የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ስራ መስራታችሁ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ ስህተት ማንም ይሳሳታል፡፡ እንዲህ እንደ ነጭ ፈረስ የጎላ ስህተት ግን እንደ እናንተ ፓርቲ በብልህነቱ ብዛት ደርግን መጣሉን መሽቶ እስኪነጋ ከሚተርክ፣ሁሉን አወቅ ነኝ ከሚል አካል የሚጠበቅ አይደለምና ለይቅርታ ይቸግራል፡፡ ይቅርታ መጣም አልመጣ ስህተትን ማመንም አንድ ነገር ቢሆንም ስህተትን ለማመን እና ለማረም እሩብ ምዕተ አመት መጠበቅም እንዲሁ የቅንነት አይደለምና ተቀባይነቱ የማይታሰብ ነው፡፡ በተለይ አሁን በሚያነሱት ጉዳይና ባነሱበት የጊዜ ሁኔታ የሃሳቡን ቅንነት ለመቀበል ይቸግራል፡፡ ያጠፋሰው (ያውም እንዲህ ከይቅርታ በላይ የሆነ ጥፋት) ያጠፋው ጥፋት ከይቅርታም፣ ከእርምትም ድንበር አልፎ እንደማይሆን ከሆነ በኋላ እንዲህ እንደ እርስዎ ተዝናንቶ መናገር ሰው ንቀት ይመስላል፤ ለሽንገላ እና ለበጣም ይቀርባል እንጅ ምንም ትርፍ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የወደቡ ነገር ከሆዱ ያልወጣ፣ መቼም ቀብሮት የማይገባው ጉዳይ ቢሆንም በእርስዎ እና በጓዶችዎ አንደበት እና አሳሳቢነት ያውም ከዚህ ረዥም ዘመን በኋላ ስለወደብ መስማት ግን ጅል ተደርጎ እንደተቆጠረ ከማሰብ የዘለለ ስሜት አይሰጠውም፡፡ ለእርምትም ፣ለይቅርታም፣ለመደመጥም ፣ ለመታመንም እንደ እርስዎ ፓርቲና ጓዶች ረዥም ዘመን እና ሰፊ እድል የተሰጠው የለም፡፡ ግን ያንን አልተጠቀማችሁበትም፡፡ አሁን በተለይ ይሄን ጉዳይ በተመለከተ የሚያምርባችሁ ዝምታ ነው!

 

 

ብሔርተኝነት ጨቋኝ ሰርዓትን ለማስወገድ እንጂ ዴሞክራሲን ለመገንባት አይጠቅምም! (ክፍል-3)

ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት የሚደረገው ትግል ከየትና እንዴት መጀመር አለበት? ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እንዲቻል የትግሉን መነሻ እና መድረሻ በግልፅ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል መነሻ ምክንያቱ የዜጎች ነፃነትና እኩልነት አለመከበሩ ነው። ስለዚህ፣ የትግሉ ዓላማ ከሕዝቡ ለሚነሳው የነፃነትና እኩልነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነው። በመሆኑም፣ የትግሉ የመጨረሻ ውጤት የዜጎች ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ፖለቲካዊ ስርዓት መዘርጋት ነው። በአጠቃላይ፣ ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል መነሻና መድረሻ የሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ናቸው።

በየትኛውም ግዜና ቦታ ቢሆን ጨቋኝ ስርዓት እስካለ ድረስ ዜጎች ብሶትና ቅሬታ ይኖራቸዋል። ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን ብሶትና ቅሬታ የሚገልፁበት ምርጫና አማራጭ ሲያጡ ለአመፅና ተቃውሞ ወደ አደባባይ ይወጣሉ። ነገር ግን፣ ጨቋኝ ስርዓት አመፅና ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር ከቀድሞ የበለጠ አስፈሪ የሆነ የኃይል እርምጃ በተቃዋሚዎች ላይ ይወስዳሉ። በእንዱህ ያለ ሁኔታ ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃን ሕዝባዊ ንቅናቄውን በትጥቅ ትግል ወይም በሰላማዊ ትግል ለመምራት ምቹ ዕድል ይፈጠርላቸዋል። በዚህ መሰረት፣ ምንም እንኳን አንድ ዓይነት መነሻና መድረሻ ቢኖረውም ጨቋኝ ስርዓትን ለማስወገድ የሚደረገው ትግል ሁለት አማራጭ መንገዶች እንዳሉት መገንዘብ ይቻላል፤ አንደኛ፡- በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል፣ ሁለተኛ፡- በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሁሉን-አቀፍ ሰላማዊ ትግል ናቸው። ከዚህ በመቀጠል የመጀመሪያውን የትግል ስልት መሰረታዊ ባህሪና ውጤታማነት እንመለከታለን።

የሕዝቡን አመፅና ተቃውሞ በትጥቅ ትግል የማስቀጠል ዝንባሌ ያላቸው የፖለቲካ ልሂቃን በዋናነት ብሔርተኝነት እና በራስ-የመወሰን መብትን ማቀንቀን ይጀምራለ። ብሔርተኘነት የሕዝቡን ንቅናቄ ለማቀጣጠል የሚያገለግል ሲሆን በራስ-የመወሰን መብት ደግሞ የትግሉ ግብ (ተስፋ) ሆኖ ያገለግላል። በአብዛኞቹ የዓለም ሀገራት የሚካሄዱ የትጥቅ ትግሎች በእነዚህ ሁለት እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ነገር ግን፣ በዚህ መልኩ የሚካሄድ የትጥቅ ትግል ከትግሉ መነሻ ምክንያትና የመጨረሻ ውጤት አንፃረ የተዛነፈ ነው።

በመጀምሪያ ደረጃ የትግሉ መነሻና መድረሻ የሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ነው። ነገር ግን፣ የትጥቅ ትግሉን ለማቀጣጠል ሲባል በማህብረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅ የተደረገው የብሔርተኝነት ስሜት ከነፃነትና እኩልነት ይልቅ በራስ-ወዳድነት (egoisim) እና ወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። ስለ ብሔርተኝነት ፅንሰ-ሃሳብና በሰው ልጅ ላይ ስለሚያስከትለው የሞራል ኪሳራ በክፍል ሁለት በዝርዝር ለመግለፅ ተሞክሯል። ስለዚህ፣ በዚህ ክፍል ዋና ትኩረታችን የትጥቅ ትግል በማህበራዊ ስነ-ልቦና ላይ በሚያስከትለው ተፅዕኖ ላይ ይሆናል። 

Skocpol (1994) and Goodwin (1994) የተባሉ የዘርፉ ምሁራን፣ የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ አማፂያን ስኬትና ውድቀታቸው የሚወሰነው በሕዝባዊ አመፅ፥ በብሔርተኝነት፥ በውጪ ኃይሎች ድጋፍ፥ የሽምቅ ውጊያ ስልት፥ ወይም ሌላ ሳይሆን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት ባህሪ እንደሆነ ይገልፃሉ። ጨቋኝ ስርዓት ለማስወገድ የሚደረግ የትጥቅ ትግል በአብዛኛው የሚጀምረው በሽምቅ ውጊያ ስልት ነው። ይህ ደግሞ አማፂያኑ ራሳቸውን በማህብረሰቡ ውስጥ በመደበቅ በመንግስት ላይ ጥቃት የሚፈፅሙበት ስልት ነው።

ከዚህ በተቃራኒ፣ ጨቋኝና አምባገነን መንግስታት ደግሞ ከአማፂያኑ ጥቃት በተፈፀመባቸው ቁጥር ከከዚህ በፊቱ የበለጠ የኃይል እርምጃ መውሰድ የተዋጊዎቹን ጥቃትና ድጋፍ ይቀንሳል የሚል እሳቤ አላቸው። ሽምቅ ተዋጊዎቹ በማህብረሰቡ ውስጥ ተደብቀው የሚንቀሳቀሱ እንደመሆኑ መጠን ጨቋ መንግስት በሚወስደው የአፀፋ እርምጃ በማህብረሰቡ አባላት በደልና ጭፍጨፋ ይደርሳል።በማህብረሰቡ ላይ በደልና ጭቆና በተፈፀመ ቁጥር ደግሞ የአማፂያኑ ድጋፍ ይጨምራል፣ የመንግስት ተቀባይነት ይቀንሳል። በዚህ መሰረት፣ የአማፂያኑን ጥቃትና ድጋፍ ለመቀነስ በሚል የሚወሰድ የአጸፋ እርምጃ የሽምቅ ተዋጊዎቹን አቅምና ድጋፍ እየጨመረ፣ የጨቋኙን ስርዓት አቅምና ተቀባይነት እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርገዋል።

በአጠቃላይ፣ በትጥቅ ትግል የአማፂያኑ ስኬትና የጨቋኝ ስርዓት ውድቀት የሚወሰነው በዚህ ስሌት መሰረት ነው። በመሆኑም፣ በትጥቅ ትግል ጨቋኝ ስርዓት የሚወድቀው ንፁሃንን በመጨፍጨፉ ምክንያት ሲሆን፣ አማፂያኑ ደግሞ የሚያሸንፉት ንፁሃንን ዜችን በማስጨፍጨፋቸው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ከዚህ አንፃር፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል በንፁሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ በደልና ጭፍጨፋ እንዲፈፀም ምክንያት በመሆኑ ተመራጭ አይደልም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የትጥቅ ትግል የመጨረሻ ውጤት በመግቢያው ላይ ከተጠቀሰው የትግሉ መነሻና መድረሻ ጋር ፍፁም ተቃራኒ ነው። የትግሉ መነሻ የሕዝብ ነፃነት እና እኩልነት ቢሆኑም በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሰረፀው በራስ-ወዳድነት ላይ የተመሰረተው የብሔርተኝነት ስሜት በሂደት ወደ ወገንተኝነት እና የተበዳይነት ስሜት ይቀየራል። ከላይ በጦርነት ወቅት አማፂያኑ በሚንቀሳቀሱበት ማህብረሰብ ላይ የሚደርሰው በደልና ጭፍጨፋ በሕብረተሰቡ ዘንድ የጠላትነትና ፍርሃት ስሜት እንዲሰርፅ ያደርገዋል። ስለዚህ፣ የትግሉ መነሻ ምክንያት ነፃነትና እኩልነት ናቸው። የትግሉ የመጨረሻ ውጤት ግን የወገንተኝነት/ተበዳይነት እና የጠላትነት/ፍርሃት ናቸው።

ከትጥቅ ትግል በኋላ የሚመሰረተው ፖለቲካዊ ስርዓትም በእነዚህ ስሜቶች ተፅዕኖ ስር ይወድቃል። የወገንተኝነት/ተበዳይነት እና የጠላትነት/ፍርሃት ስሜት በስፋት በሚንፀባረቅበት ማህብረሰብ ዘንድ እንደ አዲስ የሚዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ይሆናል። በእንዲህ ያለ የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ የብዙሃኑን ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ የሚያስችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጠበቅ የዋህነት ነው። ከዚያ ይልቅ፣ ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎ የሚነሱ የመብትና ነፃነት ጥያቄዎችን በፍርሃትና ጥርጣሬ የሚመለከት ይሆናል። እንደ ቀድሞ ስርዓት የዜጎችን ጥያቄ በኃይል ለማፈን የሚታትር ሌላ ጨቋኝ ስርዓት ይፈጠራል።             

በአጠቃላይ፣ በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የትጥቅ ትግል በማድረግ የብዙሃን ነፃነትና እኩልነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በፍፁም መገንባት አይቻልም። በብሔርተኝነት ላይ በተመሰረተ የትጥቅ ትግል ከስልጣን ያስወገዱት ጨቋኝ ስርዓት “አልሸሹም ዞር አሉ” የሚሉት ዓይነት ነው። ምክንያቱም፣ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ-አውጪ ሳይውል-ሳያድር ጨቋኝነቱ ፍትው ብሎ ይታያል። ለዚህ ደግሞ ጨቋኙን የደርግ ስርዓት በመገርሰስ ወደ ስልጣን ከመጡት የኢህአዴግና የሻዕቢያ መንግስት የበለጠ ጥሩ ማሳያ ያለ አይመስለኝም። (በቀጣዩ ክፍል ደግሞ በነፃነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ትግል እንዴት ማካሄድ እንደሚቻል በዝርዝር እንመለከታለን።)          

ስለ ትላንትና ዛሬ መነጋገር ከተሳነን ለነገ ቂም-በቀል አሳደርን፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በጀርመንና ኦስትሪያ የቀኝ-አክራሪ ብሔርተኞች ከእነሱ በስተቀር ሌላ ማንም ትክክል ሊሆን አይችልም በሚል ፅንፍ ረገጡ። ራሳቸውን ከሰው ዘር ሁሉ “ምርጥ” መሆናቸውን ለራሳቸው መሰከሩ። በመጀመሪያ ከሁሉም የተሻሉ ምርጦች መሆናቸውን ደጋግመው ለፈፉ። ቀጠሉና እነሱ ከሌሎች ሁሉ የተሻሉ ምርጦች ስለሆኑ ሌሎች ደግሞ ከእነሱ እኩል ምርጦች ሊሆኑ እንደማይችሉ ማሰብ ጀመሩ። እንዲህ እያለ ሄዶ በመጨረሻ ከምርጦች መሃል ተመራጮችን ለይተው አወጡ። በመጨረሻ ሰብዓዊ ክብራቸውን ከፍፈው በዓለም ታሪክ አሰቃቂ የሆነውን የዘር-ማጥፋት ፈፀሙ።

አክራሪ ብሔርተኞች ከመጨረሻው የሞራል ዝቅጠት ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያደረጉት ነገር ቢኖር ከእነሱ እስተሳሰብ ጋር አብሮ የማይሄድ፣ ፅንፍ አክራሪነትን የሚቃወም ፅንሰ-ሃሳብ ያላቸው መጽሃፍትን ሰብስቦ ማቃጠል ነው። በወቅቱ ሁኔታውን የታዘበው የስነ-ልቦና ልሂቁ ሲግመንድ ፍሮይድ፤ “በጣም ተሻሽለናል…ኧረ በጣም ተሻሽለናል! ድሮ ድሮ ፀኃፊዎችን ነበር የምናቃጥለው! ዛሬ ግን መፅሃፍቶቻቸውን እያቃጠልን ነው” ብሎ ነበር። በእርግጥ ይሄ መሻሻል ከሆነ እኛም በጣም ተሻሽለናል። ደርግ ፊደል የቆጠረን ሁሉ መንገድ ላይ በጥይት ዘርሮ ይፎክር ነበር። ኢህአዴግ ደግሞ ፊደል የፃፈን እስር ቤት አስገብቶ ሰብዓዊ ክብሩን ይገፈዋል። ከዚህ አንፃር በጣም ተሻሽለናል!

ሲግመንድ ፍሮይድ የስነ-ልብና ተመራማሪ (psychoanalyst) ነበር። ከዚህ ጋር የተያያዘ ደግሞ የታሪክ ስነ-ልቦና “Psychohistory” የሚባል የጥናት ዘርፍ አለ። የዚህ ዘርፍ ግንባር ቀደም ተመራማሪ የሆኑት እንደ “Hans Meyerhoff” and “H. Stuart Hughes” ያሉ ምሁራን እንደሚሉት ታሪክ (history) እና የስነ-ልቦና ምርምር (psychoanalysis) በአስገራሚ ሁኔታ ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ ግብ ነው ያላቸው። ለምሳሌ፣ David E. Stannard” የተባለው ፀኃፊ “Shrinking History” በተሰኘ መፅሃፉ ገፅ 45 ላይ የታሪክና የስነ-ልቦና ምርምር ግብን “to liberate man from the burden of the past by helping him to understand that past” በማለት ይገልፀዋል።

ከላይ እንደተጠቀሰው የታሪክ እና የስነ-ልቦና ምርምር ግብ መሆን ያለበት ሰውን ስላለፈው ግዜ እንዲያውቅ በማድረግ በአመለካከቱ ውስጥ የተቀረፀውን ጠባሳ ማስወገድ ነው። በቀድሞ ታሪክ በተፈፀመ በደልና ጭቆና በግልና በማህበራዊ ስነ-ልቦናችን ላይ ያሳረፈውን ጠባሳ መፋቅና ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ከተሳነን ጤናማ የሆነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም። የታሪክ ጠባሳን ዘወትር እያወሳን፤ መጥፎ-መጥፎውን በሌሎች ላይ እየለጠፍን፥ ስለራሳችን በጎ-በጎውን እያሰብን፣ የሌሎችን ጥፋት እየዘከርን የራሳችንን ጥፋት ከዘነጋን፣ ሌሎችን ለሁሉም ነገር ተጠያቂ፥ እኛ ደግሞ በሁሉም ነገር ተጠቂ አድርገን የምናስብ ከሆነ፣ እውነታን ማየት፥ ማስተዋል ይሳነናል፣ የሌሎችን መከራና ስቃይ መገንዘብ ይከብደናል። በቀድሞ ታሪክ በእኛ ላይ የተፈጸመውን በደልና ጭቆና ዳግም በሌሎች ላይ እየፈፀምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ ቀርቶ በትንሹ እንኳን መገመት ይሳነናል።

ያለፈ ታሪክ የወደፊት ተስፋችንን ማጨለም የለበትም። የታሪክ ጠባሳን እያሰብን ዛሬ ሌሎችን ማቁሰል የለብንም። የዛሬ ቁስል ነገ ላይ ሌላ ጠባሳ ይፈጥራል። የትላንት ቁስል እያከክን ዛሬ ላይ ያቆሰልነው ሰው ነገ በተራው ቁስሉን እያከከ ሊያቆሰለን ይመጣል። ያኔ ዛሬ ላይ እኛ ያላደረግነውን ነገ ላይ ሌሎች እንዲያረጉት መጠበቅ የዋህነት ነው። ዛሬ ላይ በጥፋቱ ሳይሆን ያለፈ ታሪክ እየቆጠርክ የዘራህው ቂም ነገ ላይ በቀል ሆኖ ይጠብቅሃል። የትላንቱን ቂም ይዘህ ዛሬ ላይ ስትበቀለው እሱም ነገ እንዲበቀልህ ቂም እየጠነሰስክ ነው።

ይሁን እንጂ፣ አሁን በኢትዮጲያ ያለው ሁኔታ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ ነው። በጥላቻ ክፉኛ የታመመው ማህበራዊ ስነ-ልቦናችን የታሪክ ጠባሳችንን ከማከም ይልቅ ቂም-በቀል እየደገሰልን ይገኛል። የጥላቻ ፖለቲካን ለማስወገድ በቅድሚያ ስለ ቀድሞ ታሪካችን፣ ስለ ወቅታዊ ፖለቲካችን፣ ስለ የወደፊት ተስፋችን በግልፅ መነጋገር አለብን። በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ተደብቆ ያለውን ቂምና ጥላቻ ፍቆ ለማስወገድ ሁላችንም ሃሳብና ስሜታችንን ያለገደብ መግለጽ መቻል አለብን።

እንደኛው ወገን ለብቻው የታሪክ ጠባሳን እያከከ የተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ግን እንኳን ስላለፈው ታሪክ፣ ዛሬ በእውን ያየውን፣ ስለ ወደፊቱ ያሰበውን እንዳይናገር የሚታፈን ከሆነ ነገ ላይ ሌላ ትልቅ ጠባሳ ይኖረናል። እንደ ሀገርና ሕዝብ፣ የቀድሞ ታሪካችን የነገ ተስፋችንን እያጨለመ ነው። ስለ ቀድሞ ታሪክ መፃፍና መናገር ዘረኝነትና ጥላቻ ከሆነ፣ ስለ ዛሬው ፖለቲካ መፃፍና መናገር ወንጀል ከሆነ፣ ነገ ላይ ምን አለን? ስለ ትላንትና ዛሬ መነጋገር ከተሳነን ለነገ ቂም-በቀል አሳደርን፡፡